በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ የገለጸውን እውቀት የያዘ መጽሐፍ

አምላክ የገለጸውን እውቀት የያዘ መጽሐፍ

ምዕራፍ 2

አምላክ የገለጸውን እውቀት የያዘ መጽሐፍ

1, 2. ከፈጣሪያችን መመሪያ ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን ለመላው የሰው ልጅ ትምህርትና መመሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ ያዘጋጃል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። አንተስ የሰው ልጅ መመሪያ ማግኘት ያስፈልገዋል ቢባል በዚህ አትስማማም?

2 ከ2,500 ዓመታት በፊት አንድ ነቢይና ታሪክ ጸሐፊ “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ሲል ጽፏል። (ኤርምያስ 10:​23) የዚህ ቃል እውነተኝነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ግልጽ ሆኖ ሊታይ ችሏል። ስለሆነም የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ዊልያም ኤች መክኒል እንደሚከተለው ብለዋል:- “የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት እልባት ያልተገኘላቸው ውዝግቦች ሲፈራረቁና ጸንተው የኖሩ ማኅበራዊ ሥርዓቶች ያለማቋረጥ ሲፈራርሱ የታየበት ነው።”

3, 4. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን በምን ዓይነት መንፈስ ተነሳስተን ማጥናት ይገባናል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር የምንጀምረው እንዴት ነው?

3 የሚያስፈልገንን ጥበብ የተሞላበት መመሪያ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አገላብጠው በማየት ብቻ ፈርተው ይሸሹታል። ትልቅ መጽሐፍ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፉን አንዳንድ ክፍሎች መረዳት ይከብዳል። ይሁን እንጂ አንድ ትልቅ ውርስ ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚገባህ በዝርዝር የሚገልጽ የሕጋዊ ኑዛዜ ሰነድ ቢሰጥህ ሰነዱን ጊዜ ወስደህ በጥንቃቄ አታጠናውም? የሰነዱን አንዳንድ ክፍሎች መረዳት ቢያስቸግርህ ስለ ጉዳዩ በቂ ልምድ ያለው ሰው እንዲረዳህ መጠየቅህ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስንስ ለምን በዚህ ዓይነት መንፈስ ተነሳስተህ አትመረምረውም? (ሥራ 17:​11) መጽሐፍ ቅዱስን ባለመመርመርህ ምክንያት የሚያመልጥህ ነገር ከሀብት ውርስ የበለጠ ነገር ነው። ባለፈው ምዕራፍ እንደተማርነው አምላክን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ ይችላል።

4 እስቲ የአምላክን እውቀት የሚገልጠውን ይህን መጽሐፍ እንመርምር። በመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ይዘት እንመለከታለን። ከዚያም ስለ ጉዳዩ ብዙ እውቀት ያካበቱ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው ብለው ስለሚያምኑባቸው ምክንያቶች እንወያያለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት

5. (ሀ) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የትኞቹ መጻሕፍትና ዘገባዎች ተካትተው ይገኛሉ? (ለ) በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችስ ስጥ?

5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለምዶ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብለው በሚጠሩ ሁለት ክፍሎች ውስጥ የተካተቱ 66 መጻሕፍት ይገኛሉ። ሠላሳ ዘጠኙ መጻሕፍት የተጻፉበት ዋነኛ ቋንቋ ዕብራይስጥ ሲሆን 27ቱ የተጻፉት በግሪክኛ ነው። ከዘፍጥረት እስከ ሚልክያስ ያሉት መጻሕፍት የተካተቱባቸው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ፍጥረት ከማስረዳታቸውም በላይ የሰው ልጆችን የመጀመሪያ 3,500 ዓመት ታሪክ ይተርካሉ። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስንመረምር እስራኤላውያን በብሔርነት ከተደራጁበት ከ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እስከ 5ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ * አምላክ ከዚህ ሕዝብ ጋር ስለነበረው ግንኙነት እንመለከታለን። ከማቴዎስ እስከ ራእይ የሚገኙትን መጻሕፍት ያካተቱት የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በኢየሱስ ትምህርቶችና ተግባራት እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በፈጸሟቸው ነገሮች ላይ ያተኩራሉ።

6. ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

6 አንዳንዶች “ብሉይ ኪዳን” የሚያገለግለው ለአይሁዳውያን ሲሆን “አዲስ ኪዳን” የሚያገለግለው ለክርስቲያኖች ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16 (አዓት) እንደሚለው “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው።” ስለዚህ ትክክለኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መላውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠቃልል መሆን ይኖርበታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እርስ በርሳቸው ተደጋግፈው አንድ አጠቃላይ የሆነ መልእክት ወይም ጭብጥ የሚያስተላልፉ ናቸው።

7. የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ምንድን ነው?

7 ምናልባት ለበርካታ ዓመታት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነበብ ሰምተህ ይሆናል። አለበለዚያም አንተ ራስህ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አንብበህ ይሆናል። መላው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራእይ ድረስ አንድ ወጥ የሆነ ሐሳብ እንዳለው ታውቅ ነበርን? አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያብራራው ስለ አንድ ጭብጥ ነው። ይህ ጭብጥ ምንድን ነው? አምላክ የሰው ልጆችን ለመግዛት ያለው መብት መረጋገጡና የአምላክ ፍቅራዊ ዓላማ በመንግሥቱ አማካኝነት የሚፈጸም መሆኑ ነው። ቆየት ብለን አምላክ ይህን ዓላማውን እንዴት እንደሚፈጽም እንመለከታ⁠ለን።

8. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ባሕርይ ምን ይገልጻል?

8 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ዓላማ በዝርዝር ከማስታወቁም በተጨማሪ ባሕርያቱንም ይገልጽልናል። ለምሳሌ ያህል አምላክ ስሜት እንዳለውና እኛ የሰው ልጆች የምናደርጋቸው ምርጫዎች እንደሚያስደስቱት ወይም እንደሚያሳዝኑት ከመጽሐፍ ቅዱስ እንረዳለን። (መዝሙር 78:​40, 41፤ ምሳሌ 27:​11፤ ሕዝቅኤል 33:​11) መዝሙር 103:​8–14 አምላክ “መሐሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቁጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ” እንደሆነ ይናገራል። ‘ከአፈር እንደተፈጠርን’ እና በምንሞትበትም ጊዜ ወደ አፈር እንደምንመለስ በማሰብ ይራራልናል። (ዘፍጥረት 2:​7፤ 3:​19) ባሕርያቱ ምንኛ አስደናቂ ናቸው! አንተስ ለማምለክ የምትፈልገው እንዲህ ያለውን አምላክ አይደለምን?

9. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን የሥነ ምግባር መስፈርቶች በግልጽ ያስቀመጠልን እንዴት ነው? እንዲህ ካለውስ እውቀት እንዴት ልንጠቀም እንችላለን?

9 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን የሥነ ምግባር መስፈርቶች በግልጽ አስቀምጦልናል። ከእነዚህ መስፈርቶች አንዳንዶቹ ሕግ ሆነው የተጻፉ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ግን ለማስተማሪያነት በቀረቡ ተጨባጭ ምሳሌዎች ውስጥ በተካተቱ መሠረታዊ ሥርዓቶች መልክ ይንጸባረቃሉ። አምላክ ለእኛ ጥቅም በማሰብ በጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ አንዳንድ ሁኔታዎች ተጽፈው እንዲቆዩልን አድርጓል። እነዚህ ሐቀኛ የሆኑ የታሪክ ዘገባዎች ሰዎች ከአምላክ ዓላማ ጋር ተስማምተው ሲኖሩ ምን እንደሚያገኙ በራሳቸው መንገድ ሲሄዱ ግን ምን ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚደርስባቸው ያሳያሉ። (1 ነገሥት 5:​4፤ 11:​4–6፤ 2 ዜና መዋዕል 15:​8–15) እነዚህን በሰዎች ሕይወት ውስጥ ስለ ተፈጸሙ ነገሮች የሚገልጹ እውነተኛ ትረካዎች ማንበባችን ልባችንን እንደሚነካ ጥርጥር የለውም። የተመዘገቡትን ሁኔታዎችና ክንውኖች በዓይነ ሕሊናችን ለመመልከት ብንሞክር ራሳችንን በባለ ታሪኮቹ ቦታ አስቀምጠን ለማየት እንችላለን። በዚህ መንገድ ጥሩ ምሳሌነታቸው እንዲጠቅመን ለማድረግና ክፉ አድራጊዎቹ ከወደቁበት ወጥመድ ራሳችንን ለመጠበቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናነበው ሐሳብ ሁሉ ከአምላክ የመነጨ ስለመሆኑ እንዴት እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን? የሚለው ዐቢይ ጥያቄ መልስ ያስፈልገዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን ልትተማመንበት ትችላለህን?

10. (ሀ) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ዘመኑ ያለፈበት መጽሐፍ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? (ለ) 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይናገራል?

10 ምክር የሚሰጡ በርካታ መጻሕፍት በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ጊዜ ያለፈባቸው እንደሚሆኑ አስተውለህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስስ? በጣም የቆየ መጽሐፍ ከመሆኑም በላይ የመጨረሻዎቹ ቃላት ከተጻፉ 2,000 ዓመት ሊሞላቸው ተቃርቧል። ስለዚህም አንዳንድ ሰዎች ለዘመናችን ሊሠራ እንደማይችል ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ከሆነ ምንም ያህል ዕድሜ ቢኖረው የሚሰጣቸው ምክሮች ዘመን ያለፈባቸው መሆን የለባቸውም። ቅዱሳን ጽሑፎች “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የሚጠቅሙ መሆን ይኖርባቸዋል።​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

11–13. መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን የሚሠራ ምክር ይሰጣል ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

11 የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠለቅ ብለን ስንመረምር በተጻፉበት ዘመን የነበራቸውን ጠቀሜታ ዛሬም ይዘው እንደቆዩ እንመለከታለን። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች ባሕርይ የሚገልጸው ነገር በማንኛውም የሰው ልጆች ትውልድ ትክክለኛ ሆኖ ተገኝቷል። ይህንንም በማቴዎስ መጽሐፍ በምዕራፍ 5 እስከ 7 ከሚገኘው የኢየሱስ የተራራ ስብከት በቀላሉ መመልከት እንችላለን። የህንድ መሪ የነበሩት ሟቹ ሞሃንደስ ኬ ጋንዲ ልባቸው በዚህ የተራራ ስብከት በመነካቱ ለአንድ የብሪታንያ ባለ ሥልጣን “የእኔም ሆነ የእርስዎ አገር ክርስቶስ በዚህ በተራራ ስብከት በገለጸው ትምህርት ቢመሩ የሁለታችንን አገሮች ችግሮች ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለም ችግሮች ለመፍታት እንችላለን” ብለው እንደተናገሩ ተገልጿል።

12 የሰው ልጆች በኢየሱስ ትምህርቶች መነካታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘውን መንገድ አመልክቶናል። በመካከላችን የሚነሳውን አለመግባባት እንዴት ልናስወግድ እንደምንችል ገልጿል። እንዴት እንደምንጸልይም መመሪያ ሰጥቷል። ለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ከመግለጹም በላይ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ስለሚያስችለው ወርቃማ ሕግ ተናግሯል። በዚህ ስብከት ውስጥ ከተካተቱት ቁምነገሮች መካከል ሃይማኖታዊ ማታለያዎችን እንዴት ለይተን እንደምናውቅና ወደፊት ዋስትና ያለው ሕይወት እንዴት እንደምናገኝ የተናገራቸው ቃላት ይገኙበታል።

13 መጽሐፍ ቅዱስ በተራራው ስብከት ላይም ሆነ በቀሩት ገጾቹ ላይ ኑሯችንን ለማሻሻል ምን ማድረግ እንደሚገባንና ምን ነገሮችን ማስወገድ እንደሚኖርብን ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸው ምክሮች በጣም ተግባራዊ ከመሆናቸው የተነሳ አንድ የሥርዓተ ትምህርት ባለሙያ እንደሚከተለው ለማለት ተገደዋል:- “የባችለርና የማስተርስ ዲግሪ ያለኝ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማካሪ ከመሆኔም በላይ ስለ አእምሮ ጤንነትና ስለ ሥነ ልቦና በርካታ መጻሕፍት ያነበብኩ ብሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የተሳካ ትዳር ስለ መመሥረት፣ ልጆች ዓመፀኞች እንዳይሆኑ ስለ መከላከል፣ ጥሩ ወዳጆችን አፍርቶ ወዳጅነቱ እንደጠበቀ እንዲኖር ስለማድረግና ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች የሚሰጠው ምክር በኮሌጅ ካጠናሁት ወይም ካነበብኩት ከማንኛውም ጽሑፍ በጣም እንደሚልቅ ለመረዳት ችዬአለሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ ለጊዜአችን የሚሠራ ምክር ያዘለ ከመሆኑም በተጨማሪ አስተማማኝ መጽሐፍ ነው።

ትክክለኛና ትምክህት የሚጣልበት

14. መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንሳዊ ጉዳዮች አንፃር ትክክለኛ መሆኑን የሚያሳየን ምንድን ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ሳይንስ ነክ ስለሆኑ ነገሮች የሚናገራቸው ሁሉ ትክክል ናቸው። ለምሳሌ ያህል አብዛኞቹ ሰዎች ምድር ጠፍጣፋ ነች ብለው ያምኑ በነበረበት ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ምድር ‘ክብ’ እንደሆነች ጽፏል። (እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቹግ የተባለ የዕብራይስጥ ቃል “ድቡልቡል” የሆነን ነገር ያመለክታል።) (ኢሳይያስ 40:​22) ምድር ድቡልቡል ናት የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት ያገኘው ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ቆይቶ ነው። በተጨማሪም ከ3,000 ዓመታት በፊት የተጻፈው ኢዮብ 26:​7 አምላክ ‘ምድር በባዶ ቦታ እንድትንጠለጠል’ እንዳደረገ ይናገራል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር “ኢዮብ በዘመናዊ የሥነ ፈለክ ጥናት የተደረሰበትን ምድር አለምንም ድጋፍ በራስዋ የተንጠለጠለች መሆንዋን የሚገልጸውን እውነት እንዴት ሊያውቅ ቻለ የሚለው ጥያቄ ቅዱስ ጽሑፉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የማይቀበሉ ሰዎች መልስ የማያገኙለት ጥያቄ ነው” ብለ⁠ዋል።

15. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለን ትምክህት በመጽሐፉ የታሪኮች አመዘጋገብ የሚጠናከረው እንዴት ነው?

15 በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የታሪክ አመዘጋገብ በዚህ ባለ ረዥም ዕድሜ መጽሐፍ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት ክንውኖች በውል ከተጠቀሱ ሰዎችና ዘመናት ጋር የተዛመዱ ስለሆኑ ከአፈ ታሪክ የተለዩ ናቸው። (1 ነገሥት 14:​25፤ ኢሳይያስ 36:​1፤ ሉቃስ 3:​1, 2) የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች የገዥዎቻቸውን ድሎች ከመጠን በላይ አጋንነው ሲጽፉ ሽንፈቶቻቸውንና ስህተቶቻቸውን ግን ይደብቁ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን ግልጽና ሐቀኞች ነበሩ። የራሳቸውን ከባድ ኃጢአት እንኳን አልሸሸጉም።​— ዘኁልቁ 20:​7–13፤ 2 ሳሙኤል 12:​7–14፤ 24:​10

የትንቢት መጽሐፍ

16. መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ስለመሆኑ ከሁሉ የሚበልጠው ማስረጃ ምንድን ነው?

16 ፍጻሜ ያገኙት ትንቢቶች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን በአስተማማኝ ሁኔታ ያረጋግጣሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር የተፈጸሙ በርካታ ትንቢቶች አሉ። ተራ ሰብዓዊ ፍጡሮች እነዚህን ትንቢቶች ከራሳቸው አመንጭተው ሊጽፉ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ታዲያ ከእነዚህ ትንቢቶች በስተጀርባ ያለው ኃይል ምንድን ነው? ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2 ጴጥሮስ 1:​21) ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

17. የባቢሎን ውድቀት በቅድሚያ የተነገረው በየትኞቹ ትንቢቶች ላይ ነው? እነዚህስ ትንቢቶች የተፈጸሙት እንዴት ነው?

17 የባቢሎን ውድቀት። ኢሳይያስና ኤርምያስ ባቢሎን በሜዶናውያንና ፋርሳውያን እጅ እንደምትወድቅ ተንብየው ነበር። ኢሳይያስ ስለዚህ ጉዳይ ትንቢት የጻፈው ባቢሎን ድል ተደርጋ ከመውደቋ ከ200 ዓመት በፊት ነበር! በአሁኑ ጊዜ የሚከተሉት የትንቢቱ ክፍሎች የታሪክ ሐቅ ሆነው አልፈዋል። የኤፍራጥስ ወንዝ አቅጣጫውን ቀይሮ ሰው ሠራሽ ወደሆነ ሐይቅ እንዲፈስ በመደረግ መድረቁ (ኢሳይያስ 44:​27፤ ኤርምያስ 50:​38)፤ የባቢሎን የወንዝ በሮች በጥንቃቄ ጉድለት በቂ ጥበቃ ሳይደረግላቸው መቅረቱ (ኢሳይያስ 45:​1)፤ ቂሮስ በተባለ ገዥ ድል መደረጓ።​— ኢሳይያስ 44:​28

18. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በ“ግሪክ ንጉሥ” አነሳስና አወዳደቅ ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?

18 “የግሪክ ንጉሥ” አነሳስና አወዳደቅ። ዳንኤል አንድ አውራ ፍየል አንድን አውራ በግ መትቶ ሁለት ቀንዶቹን ሲሰብርበት በራእይ ተመለከተ። ከዚያ በኋላ ደግሞ የፍየሉ ታላቅ ቀንድ ተሰብሮ በቦታው አራት ቀንዶች ወጡ። (ዳንኤል 8:​1–8) ለዳንኤል የሚከተለው መግለጫ ተሰጥቶት ነበር:- “ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው። እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሡ፣ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፣ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም።” (ዳንኤል 8:​20–22) ከሁለት መቶ ዘመናት በኋላ ልክ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው “የግሪክ ንጉሥ” ታላቁ እስክንድር ባለ ሁለት ቀንዱን የሜዶ ፋርስ ግዛት ገለበጠ። እስክንድር ራሱ በ323 ከዘአበ ሞቶ በአራት ጄኔራሎቹ ተተካ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ በኋላ ከተነሱት መንግሥታት መካከል አንዱም ቢሆን ከእስክንድር መንግሥት ጋር ሊተካከል አልቻለም።

19. በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸሙት ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው?

19 የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በኢየሱስ ልደት፣ አገልግሎት፣ ሞትና ትንሣኤ ላይ ፍጻሜ ያገኙ በርካታ ትንቢቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል መሲሕ ወይም ክርስቶስ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ ከ700 ዓመታት በፊት ሚክያስ ተንብዮ ነበር። (ሚክያስ 5:​2፤ ሉቃስ 2:​4–7) ከሚክያስ ጋር በአንድ ዘመን ይኖር የነበረው ኢሳይያስ መሲሑ እንደሚመታና እንደሚተፋበት ተንብዮአል። (ኢሳይያስ 50:​6፤ ማቴዎስ 26:​67) ዘካርያስ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት መሲሑ በ30 ብር እንደሚሸጥ ተንብዮ ነበር። (ዘካርያስ 11:​12፤ ማቴዎስ 26:​15) ዳዊት አንድ ሺህ ከሚያክል ዓመታት በፊት ከመሲሑ ከኢየሱስ አሟሟት ጋር ተዛምዶ ስላላቸው ሁኔታዎች ትንቢት ተናግሯል። (መዝሙር 22:​7, 8, 18፤ ማቴዎስ 27:​35, 39–43) የዳንኤል ትንቢትም ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት መሲሑ የሚገለጥበትን ጊዜ፣ የአገልግሎቱን ዘመን ርዝመትና የሚሞትበትን ጊዜ ገልጿል። (ዳንኤል 9:​24–27) እነዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከተፈጸሙት ትንቢቶች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ስለ ኢየሱስ ቆየት ብሎ የሚቀርበውን ማብራሪያ ብታነብ ብዙ ጥቅም ታገኝበታለህ።

20. ስለ ተፈጸሙት ትንቢቶች የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ምን ዓይነት ትምክህት ሊያሳድርብን ይገባል?

20 ከረዥም ዘመናት በፊት ተነግረው ፍጻሜያቸውን ያገኙ ሌሎች ብዙ ትንቢቶች አሉ። ‘ታዲያ ይህ ሁሉ ሕይወቴን የሚነካው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለበርካታ ዓመታት እውነት የሆነ ነገር ብቻ ሲነግርህ የቆየ ሰው አሁን አንድ አዲስ ነገር ቢነግርህ በድንገት መጠራጠር ትጀምራለህን? አትጀምርም! አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገራቸው ሁሉ እውነት ናቸው። ታዲያ ይህ ሁኔታ ስለ መጪው ምድራዊ ገነት የሚናገሩትን ትንቢቶች ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለህን ትምክህት ከፍ ሊያደርገው አይገባም? ከመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው ጳውሎስ ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም’ ሲል የጻፈው ዓይነት ትምክህት ሊኖረን ይችላል። (ቲቶ 1:​2) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን የአምላክ እውቀት የሚገልጥ መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን ቅዱሳን ጽሑፎችን ስናነብና ምክራቸውን በሥራ ላይ ስናውል የሰው ልጆች በራሳቸው ችሎታ ሊደርሱበት የማይችሉትን ጥበብ እናገኛለን።

አምላክ ለሚሰጠው እውቀት ‘ጥማት’ ይኑርህ

21. ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትማራቸውን አንዳንድ ነገሮች መፈጸም የማትችል መስሎ ቢሰማህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

21 መጽሐፍ ቅዱስን በምታጠናበት ጊዜ ከአሁን በፊት ከተማርሃቸው ነገሮች የሚቃረኑ ነገሮች ማግኘትህ አይቀርም። እንዲያውም በጣም ከምትወዳቸው ሃይማኖታዊ ልማዶችህ አንዳንዶቹ አምላክን የማያስደስቱ እንደሆኑ ልትገነዘብ ትችላለህ። አምላክ በዚህ ስድ በሆነው ዓለም ከተለመደው በጣም የሚልቅ የስህተትና የትክክለኛ ምግባር መስፈርቶች እንዳሉት ትገነዘባለህ። ይህም በመጀመሪያ ላይ ሊያስፈራህ ይችላል። ይሁን እንጂ ታገሥ! አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ መርምር። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በአስተሳሰብህና በምታደርጋቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ እንድታደርግ ሊጠይቅብህ ስለሚችል ብቻ አእምሮህን አትዝጋ።

22. መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠናው ለምንድን ነው? ሌሎችስ ይህን ዓላማህን እንዲገነዘቡ ልትረዳቸው የምትችለው እንዴት ነው?

22 ወዳጆችህና ዘመዶችህ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትህን ይቃወሙ ይሆናል። ይህንንም የሚያደርጉት ስለ አንተ በማሰብ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሏል:- “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።” (ማቴዎስ 10:​32, 33) አንዳንዶች የአንድ ግትር ሃይማኖታዊ ኑፋቄ አባል ትሆናለህ ወይም አክራሪ አቋም ትይዛለህ ብለው ይሰጉ ይሆናል። አንተ ግን የምትጥረው ስለ አምላክና ስለ አምላክ እውነት ትክክለኛውን እውቀት ለማግኘት ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:​3, 4) ሰዎቹ ይህን አቋምህን እንዲረዱልህ ስለምትማራቸው ነገሮች በምትናገርበት ጊዜ ምክንያታዊ እንጂ ተከራካሪ አትሁን። (ፊልጵስዩስ 4:​5) ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ ሲመለከቱ ‘አለ ቃል ሊመለሱ’ እንደሚችሉ አስታውስ።​— 1 ጴጥሮስ 3:​1, 2

23. ለአምላክ ቃል ‘ጥማት’ ሊያድርብህ የሚችለው እንዴት ነው?

23 መጽሐፍ ቅዱስ “አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ” ሲል አጥብቆ ይመክራል። (1 ጴጥሮስ 2:​2) አንድ ሕፃን ሕይወቱ የቆመው ከእናቱ በሚያገኘው ወተት ላይ ነው። እናቱም ይህን ፍላጎቱን ካላሟላችለት ዕረፍት አይሰጣትም። እኛም በተመሳሳይ ከአምላክ የሚገኘው እውቀት የሕይወታችን ምሰሶ ነው። ጥናትህን በመቀጠል ለቃሉ ያለህን ‘ጥማት’ አሳይ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ የማንበብ ግብ ይኑርህ። (መዝሙር 1:​1–3) ይህም በጣም ብዙ በረከት ያስገኝልሃል፤ ምክንያቱም መዝሙር 19:​11 የአምላክን ሕግጋት አስመልክቶ ሲናገር “በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል” ይላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ከዘአበ “ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት” ማለት ሲሆን “ዓመተ ዓለም” ከማለት የተሻለ የዘመናት ስያሜ ነው። እዘአ ደግሞ “እንደ ዘመናችን አቆጣጠር” ማለት ሲሆን በብዙዎች ዘንድ “ዓመተ ምህረት” በመባል ይታወቃል።

እውቀትህን ፈትሽ

መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት የሚለየው በምን በምን መንገዶች ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ልትተማመንበት የምትችለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያረጋግጥልህ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጽሐፍ ቅዱስህን በደንብ ተጠቀምበት

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቅ አስቸጋሪ ሊሆንብህ አይገባም። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሚገኙበትን ቅደም ተከተልና ገጽ ለማወቅ በማውጫው ተጠቀም።

የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በምዕራፎችና በቁጥሮች የተከፋፈሉ ስለሆኑ አውጥቶ ለማየት አይከብድም። በምዕራፎች የተከፋፈሉት በ13ኛው መቶ ዘመን ሲሆን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን አሁን በምንጠቀምባቸው ቁጥሮች የከፋፈለው በ16ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ አንድ ፈረንሳዊ የማተሚያ ቤት ባለቤት እንደሆነ ሊታወቅ ተችሏል። በምዕራፎችና በቁጥሮች ተከፋፍሎ ለመታተም የመጀመሪያ የሆነው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ በ1553 የታተመው የፈረንሳይኛ እትም ነው።

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጥቅሶች በሚጠቀሱበት ጊዜ የመጀመሪያው ቁጥር ምዕራፉን የሚያመለክት ሲሆን የሚቀጥለው የሚያመለክተው ደግሞ የጥቅሱን ቁጥር ነው። ለምሳሌ ያህል “ምሳሌ 2:​5” ተብሎ ሲጻፍ መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 2 ቁጥር 5 ማለት ነው። ምዕራፋቸውና ቁጥራቸው ብቻ የተጻፉትን ጥቅሶች እያወጣህ ካነበብህ ብዙም ሳትቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቀላሉ ማውጣት ትለማመዳለህ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚገባ ለመተዋወቅ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብ ነው። በመጀመሪያ ላይ አዳጋች መስሎ ይታይህ ይሆናል። ይሁን እንጂ በየቀኑ እንደ ምዕራፎቹ ርዝመት ከሦስት እስከ አምስት ምዕራፎች ካነበብህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበህ ለመጨረስ ትችላለህ። ለምን ዛሬውኑ አትጀምርም?

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጽሐፍ ቅዱስ​—በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ መጽሐፍ

• መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት’ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16) ቃሎቹን የጻፏቸው ሰዎች ቢሆኑም ሐሳባቸውን ይመራ የነበረው አምላክ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ቃል” ነው።​— 1 ተሰሎንቄ 2:​13

• መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው 16 መቶ ዓመታት በሚያክል ዘመን፣ የተለያየ አስተዳደግና ማኅበረሰባዊ ደረጃ ባላቸው 40 በሚያክሉ ሰዎች ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ እርስበርሱ የሚስማማ ነው።

• መጽሐፍ ቅዱስ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ ብዙ ውዝግቦችን ተቋቁሞ አልፏል። በመካከለኛው ዘመን ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለያዙ ብቻ ግንድ ላይ ታስረው ተቃጥለዋል።

• በመላው ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዛት ታትሞ የተሸጠ መጽሐፍ የለም። በከፊልም ይሁን ሙሉ በሙሉ ከ2,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅጂዎች የታተሙ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ የማይገኝበት የዓለም ክፍል ማግኘት አይቻልም።

• ጥንታዊ የሚባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈው በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነው። ይህ የሆነው (በ1300 ከዘአበ ገደማ የተጠናቀቀው) የሂንዱዎች ሪግ ቬዳ ከመጻፉ ወይም የቡድሂስቶች “የሦስት ቅርጫቶች ጥንቅር” (አምስተኛው መቶ ዓመት ከዘአበ) ወይም የእስልምና ቁርዓን (ሰባተኛው መቶ ዓመት እዘአ) ወይም የሺንቶዎች ኒሆንጊ (720 እዘአ) ከመጻፉ ከብዙ ዘመናት በፊት ነው።

[በገጽ 85 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]