በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምትችለው እንዴት ነው?

ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምትችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 16

ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምትችለው እንዴት ነው?

1. በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ ምን ዓይነት መመሳሰል ይታያል?

አንድን የሩቅ ምሥራቅ አገር በመጎብኘት ላይ የምትገኝ ቱሪስት በአንድ የቡድሂስቶች ቤተ መቅደስ በተመለከተችው የአምልኮ ሥርዓት በጣም ተደንቃለች። በዚያ የተመለከተቻቸው ምስሎች የማርያም ወይም የክርስቶስ ባይሆኑም የአምልኮ ሥርዓቶቹ ግን በአገሯ በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ከሚደረጉት ሥርዓቶች ጋር እንደሚመሳሰሉ ተመለከተች። ለምሳሌ ያህል አምላኪዎቹ በመቁጠሪያ ሲደግሙና በዜማ ሲጸልዩ አስተውላለች። ይህን ተመሳሳይነት ያስተዋሉ ሌሎች ሰዎችም አሉ። በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ ሰዎች ከአምላክ ወይም ከሚያመልኳቸው ነገሮች ጋር ለመቀራረብ የሚሞክሩባቸው መንገዶች የሚያስደንቅ ተመሳሳይነት አላቸው።

2. ለጸሎት ምን ፍቺ ተሰጥቷል? ብዙ ሰዎችስ የሚጸልዩት ለምንድን ነው?

2 ብዙዎች ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚሞክሩት በተለይ በጸሎት አማካኝነት ነው። ጸሎት “ሰው ቅዱስ አድርጎ ከሚመለከተው አምላክ፣ አማልክት፣ ከገሐዱ ዓለም ውጭ ካላው ዓለም ወይም ከተፈጥሮ በላይ ከሆኑ ኃይላት ጋር የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርግበት መንገድ” እንደሆነ ተገልጿል። (ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ሐሳባቸውን በጸሎት ለአምላክ ለመግለጽ በሚቀርቡበት ጊዜ የሚያስቡት ከጸሎቱ ስለሚያገኙት ነገር ወይም ጥቅም ብቻ ነው። ለምሳሌ በአንድ ወቅት አንድ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱን “ብትጸልይልኝ በቤተሰቤ፣ በሥራ ቦታና በጤንነቴ ረገድ የሚያጋጥመኝ ችግር ይወገዳልን?” ሲል ጠይቋል። ይህ ሰው ነገሩ እንደዚያ ሳይመስለው አልቀረም፤ ሆኖም ብዙ ሰዎች ቢጸልዩም ከችግራቸው አልተላቀቁም። ይህም በመሆኑ ‘ታዲያ ወደ አምላክ መቅረብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

ወደ አምላክ መቅረብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

3. ጸሎታችን መቅረብ የሚኖርበት ለማን ነው? ለምንስ?

3 ጸሎት ትርጉም አልባ የሆነ የአምልኮ ሥርዓት ወይም አንድ ነገር ለማግኘት ሲባል ብቻ የሚደረግ ነገር አይደለም። ወደ አምላክ የምንቀርብበት አንዱ ትልቅ ምክንያት ከእርሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ነው። ስለዚህም ጸሎታችን መቅረብ የሚኖርበት ወደ ይሖዋ አምላክ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው” ብሏል። (መዝሙር 145:​18) ይሖዋ ከእርሱ ጋር ሰላማዊ ዝምድና እንድንመሠርት ይጋብዘናል። (ኢሳይያስ 1:​18) ይህን ግብዣ የሚቀበሉ ሁሉ “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” በሚለው የመዝሙራዊው አባባል ይስማማሉ። ለምን? ምክንያቱም ወደ ይሖዋ አምላክ የሚቀርቡ ሁሉ እውነተኛ ደስታና የአእምሮ ሰላም ያገኛሉ።​— መዝሙር 73:​28

4, 5. (ሀ) ወደ አምላክ መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና ልንመሠርት እንችላለን?

4 አምላክ ‘የሚያስፈልገንን ነገር ገና ሳንጠይቀው የሚያውቅ’ ከሆነ እንዲረዳን የምንጸልየው ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 6:​8፤ መዝሙር 139:​4) ጸሎት በአምላክ ላይ እምነት እንዳለንና ‘የመልካም ስጦታ ሁሉ ምንጭ እርሱ እንደሆነ’ እንደምናምን ያመለክታል። (ያዕቆብ 1:​17፤ ዕብራውያን 11:​6) ይሖዋ ጸሎታችንን በመስማት ይደሰታል። (ምሳሌ 15:​8) አንድ አባት ትንሽ ልጁ በሚናገረው ከልብ የመነጨ የምስጋና ቃል እንደሚደሰት ሁሉ ይሖዋም የምናሰማውን የአድናቆትና የውዳሴ ቃል ሲያዳምጥ ደስ ይለዋል። (መዝሙር 119:​108) ጥሩ የአባትና የልጅ ዝምድና ካለ በመካከላቸው ሞቅ ያለ የሐሳብ ግንኙነት ይኖራል። የሚወደድ ልጅ ከአባቱ ጋር ለመነጋገር ይፈልጋል። ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድናም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። ስለ ይሖዋ የምንማረውንና እርሱ ያሳየንን ፍቅር ከልብ የምናደንቅ ከሆነ ይህን አድናቆታችንን በጸሎት ለመግለጽ ጠንካራ ፍላጎት ይኖረናል።​— 1 ዮሐንስ 4:​16–18

5 ከሁሉ በላይ ወደሆነው አምላክ በምንቀርብበት ጊዜ ስለምንጠቀምባቸው ቃላት ከልክ በላይ መጨነቅ ባያስፈልገንም አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ መናገር ይኖርብናል። (ዕብራውያን 4:​16) ወደ ይሖዋ ለመቅረብ መንገዱ ምን ጊዜም ክፍት ነው። በልባችን ያለውን ሁሉ በጸሎት አማካኝነት ለአምላክ ማፍሰስ መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (መዝሙር 62:​8) ይሖዋን የምናደንቅ ከሆነ ከእርሱ ጋር ሞቅ ያለ ዝምድና ለመመሥረት እንገፋፋለን። ታማኙ አብርሃምም የአምላክ ወዳጅ በመሆን እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና መሥርቶ ነበር። (ያዕቆብ 2:​23) ይሁን እንጂ ለአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ በምንጸልይበት ጊዜ ወደ እርሱ ሊቀርቡ የሚፈልጉ ሁሉ እንዲያሟሉ የሚፈለግባቸውን ነገሮች ማሟላት ይኖርብናል።

ወደ አምላክ ለመቅረብ መሟላት የሚኖርባቸው ነገሮች

6, 7. አምላክ ጸሎታችን ተሰሚነት እንዲያገኝ ገንዘብ እንድንከፍል የማይፈልግብን ቢሆንም በምንጸልይበት ጊዜ ምን ነገር መሟላት ይኖርበታል?

6 ወደ አምላክ ለመቅረብ ገንዘብ ያስፈልጋል? ብዙ ሰዎች ቄሶች እንዲጸልዩላቸው ገንዘብ ይከፍሏቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች የጸሎታቸው ተሰሚነት በሚሰጡት የገንዘብ መጠን የሚወሰን ይመስላቸዋል። የአምላክ ቃል ግን ወደ ይሖዋ በጸሎት ለመቅረብ የገንዘብ ስጦታ ያስፈልጋል አይልም። የአምላክን መንፈሳዊ ስጦታዎችና በጸሎት አማካኝነት ከእርሱ ጋር የምንመሠርተው ዝምድና ውጤት የሆኑትን በረከቶች አለ ምንም ክፍያ በነፃ ለማግኘት እንችላለን።​— ኢሳይያስ 55:​1, 2

7 ታዲያ እንድናሟላ የሚፈለጉብን ነገሮች ምንድን ናቸው? አንደኛው አስፈላጊ ነገር ቀና የሆነ የልብ ዝንባሌ ነው። (2 ዜና መዋዕል 6:​29, 30፤ ምሳሌ 15:​11) ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” መሆኑንና ‘ለሚፈልጉትም ዋጋቸውን እንደሚሰጣቸው’ ከልባችን ማመን ይኖርብናል። (መዝሙር 65:​2፤ ዕብራውያን 11:​6) በተጨማሪም ትሑት ልብ ሊኖረን ይገባል። (2 ነገሥት 22:​19፤ መዝሙር 51:​17) ኢየሱስ ከምሳሌዎቹ በአንዱ ላይ ትሑት ልብ የነበረው ቀራጭ ወደ አምላክ በጸሎት በቀረበበት ጊዜ ትዕቢተኛ ከሆነው ፈሪሳዊ ይበልጥ ጻድቅ ሆኖ እንደተገኘ አመልክቷል። (ሉቃስ 18:​10–14) ወደ አምላክ በጸሎት በምንቀርብበት ጊዜ “በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ” እንደሆነ እናስታውስ።​— ምሳሌ 16:​5

8. አምላክ ለጸሎታችን መልስ እንዲሰጥ ከፈለግን ራሳችንን ከምን ነገር ማንጻት ይኖርብናል?

8 አምላክ ለጸሎታችን መልስ እንዲሰጠን የምንፈልግ ከሆነ ራሳችንን ከኃጢአት ድርጊቶች ማንጻት ይኖርብናል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ማበረታቻ ከሰጠ በኋላ አክሎ “እናንተ ኃጢአተኞች፣ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብ ያላችሁ እናንተ፣ ልባችሁን አጥሩ” ብሏል። (ያዕቆብ 4:​8) ሌላው ቀርቶ ክፉ አድራጊዎችም እንኳ ንስሐ ከገቡና የቀድሞ አኗኗራቸውን እርግፍ አድርገው ከተዉ ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ዝምድና ሊመሠርቱ ይችላሉ። (ምሳሌ 28:​13) ለይስሙላ ብቻ አካሄዳችንን ያነጻን መስለን ብንታይ በይሖዋ ዘንድ ተደማጭነት ለማግኘት አንችልም። “የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፣ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፣ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው” በማለት የአምላክ ቃል ይናገራል።​— 1 ጴጥሮስ 3:​12

9. ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚኖርብን በማን በኩል ነው? ለምንስ?

9 መጽሐፍ ቅዱስ “በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝም” ይላል። (መክብብ 7:​20) በዚህም ምክንያት ‘ታዲያ ወደ አምላክ እንዴት መቅረብ እንችላለን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 2:​1) ኃጢአተኞች ብንሆንም ቤዛ ሆኖ በሞተልን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ወደ አምላክ ሳንሸማቀቅ በድፍረት ለመቅረብ እንችላለን። (ማቴዎስ 20:​28) ወደ ይሖዋ አምላክ ለመቅረብ የምንችልበት የመገናኛ መስመር ኢየሱስ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 14:​6) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ባስገኘልን ዋጋ በመመካት ሆን ብለን ኃጢአት እየሠራን መኖር አይገባንም። (ዕብራውያን 10:​26) ይሁንና ከክፉ ነገሮች ለመራቅ የሚቻለንን ጥረት ሁሉ እያደረግን አንዳንድ ጊዜ ብንሳሳት ንስሐ ልንገባና አምላክ ይቅር እንዲለን ልንጠይቀው እንችላለን። ትሑት ልብ ይዘን ብንቀርበው ይሰማናል።​— ሉቃስ 11:​4

አምላክን ለማነጋገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎች

10. በጸሎት ረገድ ኢየሱስን ልንመስል የምንችለው እንዴት ነው? በየትኞቹ ጊዜያት የግል ጸሎት ለማቅረብ እንችላለን?

10 ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድና ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ነገር ይቆጥር ነበር። በዚህም ምክንያት ብቻውን ሆኖ አምላክን የሚያነጋግርበት ጊዜ ይመድብ ነበር። (ማርቆስ 1:​35፤ ሉቃስ 22:​40–46) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል አዘውትረን ወደ አምላክ ብንጸልይ ጥሩ ይሆናል። (ሮሜ 12:​12) ጠዋት ስንነሣ ዕለቱን በጸሎት ብንጀምርና ማታ ደግሞ ከመተኛታችን በፊት ይሖዋን በቀኑ ውስጥ ላከናወንናቸው ሥራዎች ብናመሰግነው ተገቢ ይሆናል። በተጨማሪም በቀኑ ውስጥ በየአጋጣሚው ለመጸለይ ትጋ። (ኤፌሶን 6:​18) እንዲያውም ይሖዋ እንደሚሰማን ስለምናውቅ ድምፃችንን ሳናሰማ በልባችን ለመጸለይ እንችላለን። ብቻችንን ሆነን ከአምላክ ጋር መነጋገራችን ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና በየቀኑ ያጠናክረዋል፤ ወደ ይሖዋ መጸለይ ደግሞ ወደ እርሱ ይበልጥ ቀረብ እንድንል ያደርገናል።

11. (ሀ) ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው መጸለይ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) በጸሎትህ መጨረሻ ላይ “አሜን” ስትል ምን ማለትህ ነው?

11 በተጨማሪም ይሖዋ አንድ ላይ የተሰበሰቡ ሰዎችን በመወከል የሚቀርቡትን ጸሎቶች ያዳምጣል። (1 ነገሥት 8:​22–53) በቤተሰብ መልክ በቤተሰቡ ራስ አማካኝነት ወደ አምላክ መቅረብ ይቻላል። ይህም ቤተሰቡን የሚያስተሳስረውን ሰንሰለት ያጠነክራል። በተጨማሪም ልጆች ወላጆቻቸው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ አምላክ ሲጸልዩ ሲመለከቱ ይሖዋ እውን ሆኖ ይታያቸዋል። አንድ ሰው የተሰበሰቡ ሰዎችን፣ ምናልባትም በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ የተገኙ ሰዎችን ወክሎ በሚጸልይበት ጊዜስ ምን መደረግ አለበት? በእነዚህ ሰዎች መሐል ከሆንን በጸሎቱ መጨረሻ ላይ ከሙሉ ልባችን “አሜን” ለማለት እንድንችል በጥሞና እናዳምጥ። “አሜን” ማለት “ይሁን፣ ተስማምቻለሁ” ማለት ነው።​— 1 ቆሮንቶስ 14:​16

ይሖዋ የሚሰማቸው ጸሎቶች

12. (ሀ) አምላክ ለአንዳንድ ጸሎቶች ምላሽ የማይሰጠው ለምንድን ነው? (ለ) በምንጸልይበት ጊዜ በግል ችግራችን ላይ ብቻ ማተኮር የማይኖርብን ለምንድን ነው?

12 አንዳንዶች በክርስቶስ በኩል ወደ አምላክ ቢጸልዩም ጸሎቶቻቸው መልስ እንደማያገኙ ሊሰማቸው ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስ ግን “እንደ ፈቃዱ [እንደ አምላክ ፈቃድ] አንዳች ብንለምን ይሰማናል” ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:​14) ስለዚህ ጥያቄያችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን ስለሚያስብ መንፈሳዊነታችንን የሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ሊጸለይለት የሚገባ ትክክለኛ አርዕስት ነው። በሚያስፈልጉን ሥጋዊ ነገሮች ላይ ብቻ የማተኮርን አዝማሚያ መከላከል ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል በሽታችንን ለመቋቋም የሚያስችለንን ማስተዋልና ኃይል እንዲሰጠን መጸለይ ተገቢ ቢሆንም መንፈሳዊ ጥቅሞቻችንን እስክንዘነጋ ድረስ ስለ ጤንነታችን መጨነቅ አይገባንም። (መዝሙር 41:​1–3) አንዲት ክርስቲያን ሴት ስለ ጤንነትዋ ከሚገባ በላይ እንደምትጨነቅ ከተገነዘበች በኋላ ስለ በሽታዋ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራት ወደ ይሖዋ ጸለየች። በዚህ ምክንያት የጤንነት ችግርዋ በጣም የማያሳስብ ሆኖ እንደታያትና በሽታዋን የምትቋቋምበት “ከወትሮው ላቅ ያለ ኃይል” እንደተሰጣት ተሰማት። (2 ቆሮንቶስ 4:​7 አዓት) ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ያላት ፍላጎት በጣም እየጋለ ስለሄደ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪ ሆነች።

13. በማቴዎስ 6:​9–13 ላይ እንደተመለከተው በጸሎታችን ውስጥ ልናካትታቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

13 ይሖዋ ጸሎታችንን በመስማት እንዲደሰት በጸሎቶቻችን ውስጥ ምን ዓይነት ጉዳዮችን ልናካትት እንችላለን? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። በማቴዎስ 6:​9–13 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው የናሙና ጸሎት ብንጸልይባቸው ተገቢ የሚሆኑትን ጉዳዮች ዘርዝሯል። በጸሎታችን ውስጥ ትልቁ ጉዳይ ምን መሆን አለበት? በጸሎታችን ውስጥ በቅድሚያ መጥቀስ የሚገባን ስለ ይሖዋ አምላክ ስምና መንግሥት ነው። ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮች መጸለይ ይቻላል። በተጨማሪም ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልንና ከፈተናና ከክፉው ከዲያብሎስ እንዲያወጣን መጸለይ አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ይህን ጸሎት በዝማሬ መልክ እንድናቀርበው ወይም ስለ ትርጉሙ ምንም ሳናስብ እንድናነበንበው አይፈልግም። (ማቴዎስ 6:​7) አንድ ልጅ አባቱን በሚያነጋግርበት ጊዜ ሁሉ አንድ ዓይነት ቃላት ብቻ ቢደጋግም በመካከላቸው ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖር ይችላል?

14. ከልመና በተጨማሪ ምን ዓይነት ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል?

14 ከልመናዎችና ከልብ ከሚመነጩ ምልጃዎች በተጨማሪ የውዳሴና የምስጋና ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል። (መዝሙር 34:​1፤ 92:​1፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​18) በተጨማሪም ስለ ሌሎች ሰዎች መጸለይ እንችላለን። መከራ ወይም ስደት ስለደረሰባቸው መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጸለያችን ስለ ደኅንነታቸው የምናስብ መሆናችንን ያሳያል። ይሖዋም ይህን አሳቢነታችንን በቃላት ተገልጾ ሲሰማ ደስ ይለዋል። (ሉቃስ 22:​32፤ ዮሐንስ 17:​20፤ 1 ተሰሎንቄ 5:​25) እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”​— ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

በጸሎት ጽና

15. ጸሎታችን መልስ እንዳላገኘ ቢሰማን ምን ነገር ማስታወስ ይገባናል?

15 ስለ አምላክ ያለህ እውቀት እየጨመረ ቢሄድም ጸሎትህ መልስ የማያገኝበት ጊዜ እንዳለ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ የሆነው በጸሎት የጠየቅከው አንድ ነገር መልስ የሚያገኝበት የአምላክ ጊዜ ገና ስላልደረሰ ሊሆን ይችላል። (መክብብ 3:​1–9) ይሖዋ ሁኔታው ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል ሊፈቅድ ይችላል፤ ቢሆንም አምላክ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል፣ መልስ የሚሰጥበትንም ከሁሉ የተሻለ ጊዜ ያውቃል።​— 2 ቆሮንቶስ 12:​7–9

16. በጸሎት መጽናት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግስ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና እንዴት ይነካል?

16 በጸሎታችን መጽናታችን ለአምላክ ስለተናገርነው ጉዳይ ከልብ የምናስብ መሆናችንን ያሳያል። (ሉቃስ 18:​1–8) ለምሳሌ ያህል ይሖዋ አንድ ዓይነት ድክመት እንድናሸንፍ እንዲረዳን ጠይቀነው ይሆናል። በጸሎታችን በመጽናትና ከልመናችን ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ልመናችን ልባዊ መሆኑን እናሳያለን። የፈለግነውን ነገር ለይተን መጥቀስና በሐቀኝነት መለመን ይገባናል። በተለይ ሊጥለን የሚፈታተነን ሁኔታ ሲያጋጥመን አምላክን መማጸን አለብን። (ማቴዎስ 6:​13) ከውስጣችን የሚመነጨውን የኃጢአት ግፊት እየተዋጋን ስንጸልይ ይሖዋ እንዴት እንደረዳን እናስተውላለን። ይህም እምነታችንንና ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክርልናል።​— 1 ቆሮንቶስ 10:​13፤ ፊልጵስዩስ 4:​13

17. አምላክን በምናገለግልበት ጊዜ የጸሎተኝነት ዝንባሌ ቢኖረን እንዴት ልንጠቀም እንችላለን?

17 ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት በምናቀርብበት ጊዜ የጸሎተኝነት ዝንባሌ ኮትኩተን ብናሳድግ አምላክን በራሳችን ኃይል እንደማናገለግል ለመገንዘብ እንችላለን። ሥራውን የሚያሳካው ይሖዋ ነው። (1 ቆሮንቶስ 4:​7) ይህን መገንዘባችን ደግሞ ትሑቶች እንድንሆን ከማስቻሉ በተጨማሪ ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና ያዳብርልናል። (1 ጴጥሮስ 5:​5, 6) አዎን፣ በእርግጥም በጸሎት እንድንጸና የሚያደርጉን ጠንካራ ምክንያቶች አሉን። ከልብ የምናቀርበው ጸሎትና ወደ ሰማያዊ አባታችን እንዴት እንደምንቀርብ ያገኘነው ውድ እውቀት ሕይወታችን ደስታ የሞላበት እንዲሆን ያደርገዋል።

ከይሖዋ ጋር የሚደረግ የሐሳብ ግንኙነት አንደኛው ወገን ብቻ ሰሚ የሚሆንበት አይደለም

18. የአምላክን ቃል ልንሰማ የምንችለው እንዴት ነው?

18 አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን እርሱ የሚናገረውን መስማት ይኖርብናል። (ዘካርያስ 7:​13) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ መልእክቱን የሚያደርስልን በመለኮታዊ ኃይል አነሳሽነት በሚናገሩ ነቢያት አማካኝነት አይደለም። በመናፍስት አገናኞችም እንደማይጠቀም የተረጋገጠ ነው። (ዘዳግም 18:​10–12) ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት አምላክ የሚናገረውን ለመስማት እንችላለን። (ሮሜ 15:​4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) ምላሳችን ለጤንነታችን ከሚጠቅመን ምግብ ጣዕም ጋር እንዲላመድና እንዲወደው ለማድረግ እንደምንጥር ሁሉ ‘ንጹሕ የሆነውን የቃሉን ወተት ለመውደድ ራሳችንን ማስለመድ’ ይኖርብናል። በየቀኑ የአምላክን ቃል በማንበብ ለመንፈሳዊ ምግብ ያለህ ጉጉት እንዲዳብር አድርግ።​— 1 ጴጥሮስ 2:​2, 3 አዓት፤ ሥራ 17:​11

19. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምታነባቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰልህ ምን ጥቅም አለው?

19 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያነበብከውን ነገር አሰላስልበት። (መዝሙር 1:​1–3፤ 77:​11, 12) ያነበብከውን ነገር መላልሰህ ማሰብ ይኖርብሃል ማለት ነው። ይህም ምግብ በሆድ ውስጥ እንዲደቅ ከሚደረገው ሂደት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የምታነበውን ቀደም ሲል ከምታውቃቸው ነገሮች ጋር በማዛመድ የምትመገበውን መንፈሳዊ ምግብ ከራስህ ጋር እንዲዋሃድ ለማድረግ ትችላለህ። የቀረበው ትምህርት ሕይወትህን እንዴት እንደሚነካ ወይም ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ይሖዋ ነገሮችን እንዴት እንደሚይዝ ተመራመር። እንግዲያው በግል ጥናት አማካኝነት ይሖዋ የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ ትችላለህ። ይህም ከአምላክ ጋር በይበልጥ እንድትቀራረብና በየዕለቱ የሚያጋጥሙህን ችግሮች እንድትቋቋም ይረዳሃል።

20. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከአምላክ ጋር እንድንቀራረብ የሚረዳን እንዴት ነው?

20 በተጨማሪም እስራኤላውያን አንድ ላይ ተሰብስበው የአምላክ ሕግ ሲነበብ በጥሞና ያዳምጡ እንደነበረ አንተም የአምላክ ቃል በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሲብራራ በማዳመጥ ከአምላክ ጋር ለመቀራረብ ትችላለህ። በእስራኤላውያን ዘመን የነበሩት አስተማሪዎች የሚነበበውን ሕግ ትርጉም በማስረዳት አድማጮቻቸው የሰሙትን ነገር እንዲያስተውሉና ሥራ ላይ እንዲያውሉ ይረዷቸው ነበር። ይህም ታላቅ ደስታ ያመጣላቸው ነበር። (ነህምያ 8:​8, 12) ስለዚህ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔህ ይሁን። (ዕብራውያን 10:​24, 25) ይህ ደግሞ የአምላክን እውቀት እንድታስተውልና በሕይወትህ ውስጥ ሥራ ላይ በማዋል ደስታ እንድታገኝ ያስችልሃል። ምድር አቀፍ የሆነው ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት አባል መሆንህ ከይሖዋ ጋር ተቀራርበህ እንድትኖር ይረዳሃል። ቀጥለን እንደምንመለከተውም በአምላክ ሕዝብ መካከል ያለምንም ስጋት ተማምነህ ልትኖር ትችላለህ።

እውቀትህን ፈትሽ

ከይሖዋ ጋር መቀራረብ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

ከአምላክ ጋር ለመቀራረብ መሟላት የሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

በጸሎትህ ውስጥ ምን ነገሮችን ልታካትት ትችላለህ?

በጸሎት መጽናት የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ቃል መስማት የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 157 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]