በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ነው!

የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ነው!

ምዕራፍ 11

የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ነው!

1. ብዙ ሰዎች ስለ ዓለም ሁኔታ ሲያስቡ ግራ የሚጋቡት ለምንድን ነው? ስለ ዓለም ሁኔታዎች አስተማማኝ የሆነ ማብራሪያ ልናገኝ የምንችለው የት ነው?

ይህ ሰላም ያጣ ዓለም አሁን ወደሚገኝበት ደረጃ የደረሰው እንዴት ነው? የምናመራውስ ወዴት ነው? እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ጠይቀህ ታውቃለህ? ብዙ ሰዎች የዓለምን ሁኔታ ሲመለከቱ ግራ ይገባቸዋል። እንደ ጦርነት፣ በሽታና ወንጀል ያሉትን ሁኔታዎች ሲመለከቱ ወደፊትስ ምን ይመጣ ይሆን? ብለው ያስባሉ። የመንግሥታት መሪዎች ችግሮቹን ይፈታሉ የሚል ተስፋ የለም። ይሁን እንጂ አስጨናቂ ስለሆነው ስለዚህ ዘመን አስተማማኝ ማብራሪያ ከአምላክ ቃል እናገኛለን። መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛው ዘመን እንደምንኖር አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ እንድናስተውል ይረዳናል። በዚህ የነገሮች ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀን’ ውስጥ እንደምንኖር ይገልጽልናል።​— 2 ጢሞቴዎስ 3:⁠1

2. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ጥያቄ አቅርበውለት ነበር? ምንስ ብሎ መለሰላ⁠ቸው?

2 ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አንስተዋቸው ለነበሩት አንዳንድ ጥያቄዎች የሰጣቸውን መልሶች እንመልከት። ኢየሱስ ከመሞቱ ከሦስት ቀናት በፊት “የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን ይሆናል?” ብለው ጠየቁት። * (ማቴዎስ 24:​3 አዓት) ኢየሱስም ሲመልስላቸው ይህ ለአምላክ ደንታ የሌለው ዓለም ወደ መጨረሻው ቀን የገባ መሆኑን በግልጽ የሚያመለክቱ ሁኔታዎችንና ክንውኖችን ነገራቸው።

3. ኢየሱስ መግዛት ሲጀምር በምድር ላይ ያሉት ሁኔታዎች የተባባሱት ለምንድን ነው?

3 ከዚህ በፊት በነበረው ምዕራፍ እንደተብራራው የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት የአምላክ መንግሥት ቀደም ሲል መግዛት የጀመረ መሆኑን ያመለክታል። ይሁን እንጂ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ነገሮች እየተባባሱ ሄዱ እንጂ አልተሻሻሉም። እንዲያውም ይህ ራሱ የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። እንዴት? መዝሙር 110:​2 ኢየሱስ ለተወሰነ ጊዜ “በጠላቶቹ መካከል” እንደሚገዛ ይነግረናል። ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንደጀመረ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ምድር አካባቢ መጣል ነው። (ራእይ 12:​9) ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስከተለ? በራእይ 12:​12 ላይ አስቀድሞ እንደተገለጸው ሆኗል:- “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በዚህ “ጥቂት ዘመን” ውስጥ ነው።

4. አንዳንድ የመጨረሻው ቀን ገጽታዎች ምንድን ናቸው? እነዚህስ ምን ያመለክታሉ? (ሣጥኑን ተመልከት።)

4 ስለዚህ ኢየሱስ የመገኘቱና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምን እንደሚሆን በተጠየቀ ጊዜ የሰጠው ምላሽ አሳሳቢ መሆኑ አያስደንቅም። የምልክቱ የተለያዩ ክፍሎች በገጽ 102 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል። መመልከት እንደምትችለው ክርስቲያን ሐዋርያት የነበሩት ጳውሎስ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ ስለ መጨረሻው ቀን ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ሰጥተውናል። እርግጥ ነው፣ ብዙዎቹ የመጨረሻው ቀን ምልክት ክፍሎች የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች እንደሚመጡ የሚገልጹ ናቸው። ቢሆንም የእነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘት ይህ ክፉ ሥርዓት ወደ ጥፋቱ የቀረበ መሆኑን ሊያሳምነን ይገባል። አንዳንዶቹን የመጨረሻው ቀን ዋና ዋና ምልክቶች ቀረብ ብለን እንመርምር።

የመጨረሻው ቀን ምልክቶች

5, 6. ስለ ጦርነትና ረሀብ የተነገሩት ትንቢቶች በመፈጸም ላይ የሚገኙት እንዴት ነው?

5 “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።” (ማቴዎስ 24:​7፤ ራእይ 6:​4) ኧርነስት ሄሚንግዌይ የተባሉት ደራሲ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት “በምድር ላይ ከተደረጉት ጦርነቶች በሙሉ እጅግ በጣም ትልቅና ለብዙ ሰዎች እልቂት ምክንያት የሆነ፣ ምንም ዓይነት ቁጥጥር ያልተደረገበት መተራረድ ነበር” ብለዋል። ዘ ወርልድ ኢን ዘ ክሩሲብል​—1914–1919 የተባለው መጽሐፍ “በሰው ልጅ ተሞክሮ ውስጥ በዓይነቱና በስፋቱ የመጀመሪያና አዲስ የሆነ ጦርነት ነበር። ጦርነቱ የቆየበት ዘመን፣ መጠኑና ስፋቱ ከዚያ በፊት ይታወቅ ወይም ይጠበቅ ከነበረው በጣም የላቀ ነበር” ብሏል። ከዚያም ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ይበልጥ አውዳሚ የነበረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጣ። የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሂዩ ቶማስ “ሃያኛው መቶ ዘመን ጠመንጃ፣ ታንክ፣ ቢ–52 የተባለው ቦምብ ጣይ አውሮፕላን፣ የኑክሌር ቦምብና በመጨረሻም ሚሳይል የሰለጠነበት ዘመን ሆኗል። በማንኛውም ሌላ ዘመን ከታዩት ጦርነቶች ይበልጥ አጥፊና ደም አፋሳሽ የሆኑ ጦርነቶች የታዩበት ዘመን ነው” ብለዋል። እርግጥ ነው፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ ወዲህ የጦር መሣሪያ ቅነሳ ስለማድረግ ብዙ ተብሏል። ይሁን እንጂ በአንድ ሪፖርት እንደተገመተው የተባለው ቅነሳ ከተደረገ በኋላ እንኳን ከ10,000 እስከ 20,000 የሚደርሱ የኑክሌር አረሮች ይቀራሉ። ይህ ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሥራ ላይ ከዋለው የጦር መሣሪያ ከ900 ጊዜ የሚበልጥ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል።

6 “ራብም . . . ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:​7፤ ራእይ 6:​5, 6, 8) ከ1914 ወዲህ ቢያንስ 20 ዋና ዋና የረሀብ ክስተቶች ታይተዋል። በረሀብ ከተመቱት አገሮች መካከል ባንግላዴሽ፣ ቡሩንዲ፣ ካምቦዲያ፣ ቻይና፣ ኢትዮጵያ፣ ግሪክ፣ ህንድ፣ ናይጄርያ፣ ሩሲያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያና ሱዳን ይገኛሉ። ነገር ግን ለረሀብ ምክንያት የሆነው የምግብ ዕጦት ብቻ አይደለም። አንድ የእርሻ ሳይንቲስቶችና ኢኮኖሚስቶች ቡድን “ባለፉት አሥርተ ዓመታት የዓለም የምግብ አቅርቦት ከሕዝብ ብዛት እድገት በበለጠ ፍጥነት አድጓል። ቢሆንም ከ800 ሚልዮን የማያንሱ ሰዎች በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ስለሆኑ . . . በብዛት ከሚመረተው እህል የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት በኩል ያለባቸውን ሥር የሰደደ ችግር ለመፍታት በሚያስችላቸው መጠን ለመግዛት አልቻሉም።” በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ ለረሀብ ምክንያት የሚሆነው የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነት ነው። የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር አብደልጋሊል ኤልሜኪ አገሮቻቸው በጣም ብዙ እህል ለሽያጭ ወደ ውጭ እየላኩ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው በረሀብ ያለቁባቸውን ሁለት አገሮች በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። እነዚህ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ከመመገብ ይበልጥ ይጨነቁ የነበረው ለጦርነቶቻቸው ማካሄጃ የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ነበር። ዶክተር ኤልሜኪ አብዛኛውን ጊዜ ረሀብ “በስርጭት ጉድለትና በመንግሥታት የተዛባ ፖሊሲ ምክንያት የሚመጣ ነው” ከሚል መደምደሚያ ደርሰዋል።

7. በቸነፈር ረገድ አሌ ሊባሉ የማይቻሉት ሐቆች ምንድን ናቸው?

7 “ቸነፈር” (ሉቃስ 21:​11፤ ራእይ 6:​8) ከ1918–1919 የደረሰው ስፓኒሽ ፍሉ ወይም የኅዳር በሽታ ቢያንስ የ21 ሚልዮን ሰዎችን ሕይወት ቀጭቷል። ኤ ኤ ኸሊንግ ዘ ግሬት ኤፒደሚክ (ታላቁ ወረርሽኝ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደጻፉት “ዓለም ይህን የሚያክሉ ብዙ ሰዎችን ይህን በሚያክል ፍጥነት በገደለ ቀሳፊ በሽታ የተመታችበት ጊዜ የለም” ብለዋል። ዛሬም ቢሆን ቸነፈሮች አልተገቱም። በየዓመቱ ካንሰር አምስት ሚልዮን ሰዎችን፣ የተቅማጥ በሽታዎች ከሦስት ሚልዮን የሚበልጡ ሕፃናትን፣ ሳንባ ነቀርሳ ሦስት ሚልዮን ሰዎችን ይገድላሉ። የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች፣ በተለይ የሳንባ ምች (ኒሞንያ) 3.5 ሚልዮን የሚያክሉ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸውን ልጆች በየዓመቱ ይገድላሉ። በተጨማሪም 2.5 ቢልዮን የሚያክሉ ሰዎች (የዓለም ሕዝብ ግማሽ መሆኑ ነው) በቂ ባልሆነ ወይም በተበከለ ውኃ ምክንያት ወይም በንጽሕና ጉድለት ምክንያት በሚደርሱ በሽታዎች ይሠቃያሉ። ኤድስ ደግሞ የሰው ልጅ በሕክምና ረገድ በቀላሉ የማይገመት እድገት ቢያደርግም ቸነፈሮችን ማስወገድ የተሳነው መሆኑን የሚያስገነዝብ ሐቅ ሆኗል።

8. ሰዎች “ገንዘብ ወዳዶች” መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

8 “ሰዎች . . . ገንዘብን የሚወዱ . . . ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:​2) በመላው ምድር የሚኖሩ ሰዎች ሀብት የማይጠግቡ ሆነዋል። ብዙውን ጊዜ “የኑሮ መሳካት” የሚለካው በደመወዝ ወይም በንብረት መጠን ሆኗል። የአንድ ማስታወቂያ ድርጅት ምክትል ፕሬዚደንት “ፍቅረ ንዋይ በአሜሪካ አገር ሰዎችን ከሚያንቀሳቅሱት ዋነኛ ግፊቶች አንዱ እንደሆነ ይቀጥላል። . . . በሌሎች አገሮችም ቢሆን ይኸው ግፊት ዋነኛ ኃይል መሆኑ እየጨመረ ይሄዳል” ብለዋል። አንተ በምትኖርበት አገርስ ሁኔታው ይህን የመሰለ ነውን?

9. ልጆች ለወላጆች እንደማይታዘዙ ስለተነገረው ትንቢት ምን ለማለት ይቻላል?

9 “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” (2 ጢሞቴዎስ 3:​2) ብዙ ልጆች ሰው የማያከብሩና የማይታዘዙ ለመሆናቸው የዘመናችን ወላጆች፣ አስተማሪዎችና ሌሎች ሰዎች የዓይን ምሥክሮች ናቸው። ከእነዚህ ወጣቶች አንዳንዶቹ መጥፎ ጠባይ የሚያሳዩት ወላጆቻ⁠ቸው ­በሚያደርጉት ነገር መበሳጨታቸውን ለመግለጽ ወይም እነርሱን ለመምሰል ሲሉ ነው። በትምህርት ቤት፣ በሕግ፣ በሃይማኖትና በወላጆች ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጡና የሚያምፁ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩ ሰው “ልጆች ለምንም ነገር አክብሮት ያላቸው አይመስልም” ብለዋል። ይሁን እንጂ በጠባያቸው ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው በርካታ ልጆች መኖራቸው በጣም ያስደስታል።

10, 11. ሰዎች ጨካኞችና የተፈጥሮ ፍቅር የጎደላቸው መሆናቸውን የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ?

10 “ጨካኞች” (2 ጢሞቴዎስ 3:​3) “ጨካኝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ‘ያልተገራ፣ ሰብዓዊ ሐዘኔታና ስሜት የጎደለው’ የሚል ትርጉም አለው። የዘመናችንን የዓመፅ አራማጆች በሚገባ የሚገልጽ ቃል አይደለምን? የአንድ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ “ሕይወት በጣም በሚያሠቅቁ ድርጊቶችና በደም የተጨማለቀ በመሆኑ ዕለታዊ ጋዜጦችን ለማንበብ እንደ ብረት የደነደነ አንጀት አስፈልጓል” ብሏል። የመኖሪያ አካባቢዎችን የሚቆጣጠሩ አንድ የፖሊስ ሃምሳ አለቃ ብዙ ወጣቶች ድርጊቶቻቸው የሚያስከትሉትን መጥፎ ውጤቶች እንዳያዩ ዓይናቸውን የጨፈኑ ይመስላሉ ሲሉ ገልጸዋል። “‘ስለ ነገ የማውቀው ነገር የለም። የምፈልገውን ሁሉ ዛሬውኑ ማግኘት አለብኝ’ የሚል ስሜት ያላቸው ይመስላል” ብለዋል።

11 “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” (2 ጢሞቴዎስ 3:​3 አዓት) ይህ ሐረግ የተተረጎመው “ርኅራኄ የሌለው፣ ሰብዓዊ ስሜት የጎደለው፣ የተፈጥሮና የቤተሰብ ፍቅር የሌለው” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል ነው። (ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስተመንት ቲዎሎጂ) አዎን፣ ፍቅር ከማንኛውም ሥፍራ ይልቅ አብቦ መታየት ከሚገባበት ቦታ ማለትም ከቤት እየጠፋ ነው። በትዳር ጓደኞች፣ በልጆች፣ በሸመገሉ ወላጆች ላይ ሳይቀር ስድብና ጥቃት እንደሚፈጸም የሚገልጹ ዜናዎች እየተለመዱ ሄደዋል። አንድ የምርምር ቡድን “ሰው የሚወስደው የኃይል እርምጃ፣ በጥፊ መምታትም ይሁን መገፍተር፣ በጩቤ መውጋትም ይሁን ተኩሶ መግደል፣ ከማንኛውም የኅብረተሰብ ክልል ይበልጥ በቤተሰብ ክልል ውስጥ መዘውተር ጀምሯል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

12. ሰዎች የአምልኮ መልክ ብቻ ነው ያላቸው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

12 “የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” (2 ጢሞቴዎስ 3:​5) መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥና የማሻሻል ኃይል አለው። (ኤፌሶን 4:​22–24) በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንደ ከለላ አድርገው በመጠቀም አምላክን የሚያሳዝን መጥፎ ድርጊት በመፈጸም ላይ ናቸው። የሃይማኖት መሪዎች ውሸት፣ ስርቆትና ከአግባብ ውጭ የሆነ ወሲባዊ ድርጊት ሲፈጸም እየተመለከቱ ዝም ይላሉ። ብዙ ሃይማኖቶች ስለ ፍቅር እየሰበኩ ለጦርነት ድጋፋቸውን ይሰጣሉ። ኢንዲያ ቱዴይ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ “የሰው ልጆች በኃያሉ ፈጣሪ ስም መሰሎቻቸው በሆኑ ፍጡሮች ላይ በጣም አሠቃቂ የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል” ይላል። እንዲያውም በቅርቡ ከተደረጉት ጦርነቶች ሁሉ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ያስከተሉት አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የፈነዱት ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ ነው።

13. ምድር በመበላሸት ላይ መሆኗን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

13 ‘ምድርን የሚያበላሹ’ (ራእይ 11:​18) 104 የኖቤል ተሸላሚዎች የሚገኙበት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ከ1,600 የሚበልጡ የሳይንስ ሊቃውንት ሁኔታዎች ያሳሰቧቸው ሳይንቲስቶች ኅብረት (ዩ ሲ ኤስ) የሰጠውን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ አጽድቀዋል:- “የሰው ልጆችና የተፈጥሮ አካባቢያችን ግንባር ለግንባር በሚያጋጫቸው አካሄድ ላይ ይገኛሉ። . . . ይህን ስጋት ለማስቀረት ያለን ዕድል ሊያመልጠን የቀረን ጊዜ ከጥቂት አሥርተ ዓመታት አይበልጥም።” ይህ ሪፖርት እንደሚለው የሰው ልጅ የሚፈጽማቸው በሕይወት ላይ አደጋ የሚያመጡ ድርጊቶች “የዓለምን ሁኔታ ፈጽሞ ሊለውጡ ስለሚችሉ ሕይወትን አሁን በምናውቀው መንገድ ጠብቆ ማቆየት የማይቻል ይሆናል።” የኦዞን ሽፋን መሳሳት፣ የውኃ ብክለት፣ የደኖች መመናመን፣ የለም አፈር መቀነስ፣ የብዙ እንስሳትና ዕፀዋት ዝርያዎች መጥፋት አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈለግላቸው የሚገቡ ችግሮች እንደሆኑ ተጠቅሷል። ሁኔታዎች ያሳሰቧቸው ሳይንቲስቶች ኅብረት “እርስ በርሱ በተሳሰረው የሕይወት ድር ላይ የምናደርሰው ጉዳት መጠኑ ሰፊ የሆነ አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በባዮሎጂያዊ ሥርዓቶች ላይ አሠራሩን ገና ያልተረዳነው ጥፋት ሊያመጣ ይችላል” ብሏል።

14. ማቴዎስ 24:​14 በዘመናችን በመፈጸም ላይ መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ ትችላለህ?

14 ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።” (ማቴዎስ 24:​14) ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ላይ እንደሚሰበክ ተንብዮ ነበር። በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በመለኮታዊ እርዳታና በረከት በቢልዮን የሚቆጠር ሰዓት በዚህ የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ያሳልፋሉ። (ማቴዎስ 28:​19,20) አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን ባያውጁ በደም ዕዳ እንደሚጠየቁ ያውቃሉ። (ሕዝቅኤል 3:⁠18, 19) ይሁን እንጂ በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት በደስታ ተቀብለው እውነተኛ ክርስቲያኖች ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን አዲስ አቋም ሲወስዱ በማየት እየተደሰቱ ነው። ይሖዋን በማገልገል የአምላክን እውቀት ለማሰራጨት መቻል በዋጋ ሊተመን የማይችል ታላቅ መብት ነው። ይህ የመንግሥት ምሥራች በመላው ዓለም ከተሰበከ በኋላ የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ይመጣል።

ማስረጃውን በማየት እርምጃ ውሰድ

15. የአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት የሚጠፋው እንዴት ነው?

15 ይህ ሥርዓት የሚጠፋው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ዓለም የፖለቲካ ኃይሎች የሐሰት ሃይማኖት ዓለም አቀፍ ድርጅት በሆነችው በ“ታላቂቱ ባቢሎን” ላይ በሚወስዱት የጥቃት እርምጃ የሚጀምር “ታላቅ መከራ” እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​21፤ ራእይ 17:​5, 16) በዚህ ጊዜ ‘ፀሐይ እንደሚጨልም፣ ጨረቃ ብርሃንዋን እንደምትነሳና ከዋክብት ከሰማይ እንደሚወድቁ፣ የሰማይም ኃይላት እንደሚናወጡ’ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:​29) ይህ አባባል ቃል በቃል የሚፈጸሙ ሰማያዊ ክስተቶች እንደሚኖሩ ሊያመለክት ይችላል። ያም ሆነ ይህ የሃይማኖታዊው ዓለም ብርሃን ሰጪ መብራቶች ማንነታቸው መጋለጡና መደምሰሳቸው የማይቀር ነው። ከዚያ በኋላ “የማጎጉ ጎግ” ተብሎ የሚጠራው ሰይጣን ዲያብሎስ ምግባረ ብልሹ የሆኑ ሰዎችን በመጠቀም በይሖዋ ሕዝብ ላይ አጠቃላይ የጥቃት ዘመቻ ይጀምራል። ይሁን እንጂ አይሳካለትም፤ ምክንያቱም አምላክ ሕዝቦቹን ለማዳን ይነሳል። (ሕዝቅኤል 38:​1, 2, 14–23) “ታላቁ መከራ” አርማጌዶን በተባለው “ሁሉን የሚችል አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” ላይ የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃው ላይ ይደርሳል። በዚህ ጊዜ የሰይጣን ምድራዊ ድርጅት ቅሪት በሙሉ ተጠራርጎ ይጠፋል። ከዚያ በኋላ ከጦርነቱ ለሚተርፉት የሰው ልጆች ፍጻሜ የለሽ በረከት መፍሰስ ይጀምራል።​— ራእይ 7:​9, 14፤ 11:​15፤ 16:​14, 16፤ 21:​3, 4

16. ስለ መጨረሻው ቀን የተነገሩት ትንቢቶች በዚህ በእኛ ዘመን እንደተፈጸሙ እንዴት እናውቃለን?

16 ስለ መጨረሻው ቀን በተነገሩት ትንቢቶች ላይ የተዘረዘሩት አንዳንድ ሁኔታዎች በተናጠል ሲታዩ በሌሎች የታሪክ ወቅቶች የተፈጸሙ ሊመስሉ ይችላሉ። አንድ ላይ ሲዳመሩ ግን እነዚህ በትንቢት የተነገሩት ምልክቶች ለይተው የሚጠቁሙት የእኛን ዘመን ብቻ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በአንድ ሰው የጣት አሻራ ላይ የሚገኙት መስመሮች እርስ በርስ ተቀናጅተው ያ ግለሰብ ማንም ሌላ ሰው ሊኖረው የማይችል አሻራ እንዲኖረው ያስችሉታል። በተመሳሳይም የመጨረሻው ቀን የራሱ የሆነ መለያ ምልክቶች ወይም ክንውኖች አሉት። እነዚህ ምልክቶች አንድ ላይ ተዳምረው ይህ ዘመን ሌላ የታሪክ ዘመን ያልኖረው “አሻራ” እንዲኖረው አስችለዋል። እነዚህ ማስረጃዎች የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት በመግዛት ላይ መሆኑን ከሚያመለክቱት የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች ጋር ተገናዝበው ሲታዩ በእርግጥ የምንኖርበት ዘመን የመጨረሻው ቀን ነው ወደሚለው ድምዳሜ ያደርሱናል። ከዚህም በላይ የአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ የሚያረጋግጥ ግልጽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለ።

17. የምንኖርበት ዘመን የመጨረሻው ቀን መሆኑን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

17 የምንኖረው በመጨረሻው ቀን መሆኑን የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች ስትመለከት ምን እርምጃ ትወስዳለህ? አንድ አስፈሪ የሆነ ዶፍ ሊጥል እንደተቃረበ ብናውቅ ሳንዘገይ ከአደጋው የምናመልጥበትን ዘዴ እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሥርዓት የሚተነብየው ነገርም እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይገባል። (ማቴዎስ 16:​1–3) በዚህ የዓለም ሥርዓት መጨረሻ ቀን እንደምንኖር በግልጽ ለማየት እንችላለን። ይህ ደግሞ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ስንል ማንኛውንም ለውጥ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል። (2 ጴጥሮስ 3:​3, 10–12) ኢየሱስ አዳኛችን መሆኑን በማመልከት የሚከተለውን አፋጣኝ ጥሪ ያቀርብልናል:- “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁልጊዜ ትጉ።”​— ሉቃስ 21:​34–36

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “የነገሮች ሥርዓት” ከማለት ይልቅ “ዓለም” ይላሉ። በደብልዩ ኢ ቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስተመንት ወርድስ የተባለ መዝገበ ቃላት “አይኦን” የሚለው የግሪክኛ ቃል ­“ከ⁠—እስከ ተብሎ ያልተወሰነ ዘመን ወይም በዘመኑ ውስጥ ከሚከናወኑት ነገሮች አንፃር የሚታይ ጊዜ ማለት ነው” ይላል። የፓርክረስት ግሪክ ኤንድ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ቱ ዘ ኒው ቴስተመንት (ገጽ 17) በዕብራውያን 1:​2 ላይ የተጠቀሰውን አይኦነስ (የብዙ ቁጥር) ሲያብራራ ከሰጣቸው ፍቺዎች አንዱ “ይህ የነገሮች ሥርዓት” የሚል ነው። ስለዚህ “የነገሮች ሥርዓት” የሚለው አተረጓጎም ከጥንቱ የግሪክኛ ጽሑፍ ጋር የሚስማማ ነው።

እውቀትህን ፈትሽ

መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ግዛት በሚጀምርበት ጊዜ ምን ዓይነት የዓለም ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ተንብዮአል?

የመጨረሻውን ቀን ልዩ የሚያደርጉት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

ይህ ዘመን የመጨረሻው ቀን መሆኑን የሚያሳምንህ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 102 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመጨረሻውን ቀን ልዩ የሚያደርጉት አንዳንድ ገጽታዎች

• ሆኖ የማያውቅ ጦርነት​— ማቴዎስ 24:​7፤ ራእይ 6:​4

• ረሀብ​— ማቴዎስ 24:​7፤ ራእይ 6:​5, 6, 8

• ቸነፈር​— ሉቃስ 21:​11፤ ራእይ 6:​81980 ትርጉም

• የዓመፅ መብዛት​— ማቴዎስ 24:​12

• የምድር መበላሸት​— ራእይ 11:​18

• የመሬት መንቀጥቀጥ​— ማቴዎስ 24:​7

• የሚያስጨንቅ ዘመን​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​1

• ከመጠን ያለፈ የገንዘብ ፍቅር​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​2

• ለወላጆች አለመታዘዝ​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​2

• የተፈጥሮ ፍቅር መጥፋት​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​3

• ከአምላክ ይልቅ ተድላ መውደድ​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​4

• ራስን አለመግዛት​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​3

• ጥሩ የሆነውን አለመውደድ​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​3

• ከላይ የሚያንዣብበውን አደጋ አለማስተዋል​— ማቴዎስ 24:​39

• ዘባቾች የመጨረሻውን ቀን ማስረጃዎች አለመቀበላቸው​— 2 ጴጥሮስ 3:​3, 4

• የአምላክ መንግሥት በመላው ምድር መሰበክ​— ማቴዎስ 24:​14

[በገጽ 101 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]