በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 1

ሁሉም ሃይማኖቶች እውነትን ያስተምራሉ?

ሁሉም ሃይማኖቶች እውነትን ያስተምራሉ?

1. በአፍሪካ ስላሉት ሃይማኖቶች ምን ማለት ይቻላል?

አፍሪካውያን በሙሉ ማለት ይቻላል፣ አምላክን ማምለክ ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ‘መመለክ ያለበት እንዴት ነው?’ በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች አምልኳቸውን የሚያከናውኑት በመስጊድ ሲሆን ሌሎች ይህን የሚያደርጉት በባሕላዊ የአምልኮ ስፍራዎች ነው። አንዳንዶች ደግሞ አምልኳቸውን የሚያከናውኑት በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ነው። እንዲህ ሲባል ግን በአፍሪካ ያሉት ሃይማኖቶች ሦስት ብቻ ናቸው ማለት አይደለም። በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የተለያዩ ሕጎችና እምነቶች አሉ። ባሕላዊ ሃይማኖቶችም ከቦታ ቦታ ይለያያሉ። የክርስትና እምነት ተከታዮች ነን በሚሉት መካከል ደግሞ ከዚህ የከፋ ክፍፍል አለ። በመላው አፍሪካ ከዋነኞቹ አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ።

ሃይማኖታችን በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት

2. (ሀ) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አንድን ሃይማኖት እንዲከተሉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? (ለ) የአንድ ሃይማኖት ትክክለኝነት በምን ሊወሰን አይችልም?

2 ሰዎች አንድን ሃይማኖት እንዲከተሉ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? አብዛኞቹ ሰዎች የወላጆቻቸውን ሃይማኖት ይከተላሉ። በተጨማሪም በጥንት ዘመን የተፈጸሙ ክንውኖች ሰዎች በሚከተሏቸው ሃይማኖቶች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ዘ አፍሪካንስትሪፕል ሄሪቴጅ የተባለ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ከሰሃራ በስተ ሰሜን ባሉት አካባቢዎች የእስልምና ሃይማኖት የተስፋፋው በወረራ ነው፤ ክርስትናም ቢሆን ከሰሃራ በስተ ደቡብ ባሉት አካባቢዎች የተስፋፋው በዚሁ መንገድ ነው። እስልምና ከሰሃራ በስተ ሰሜን የተስፋፋው በሰይፍ ከሆነ ክርስትና ደግሞ ከሰሃራ በስተ ደቡብ የተስፋፋው በጠመንጃ ነው።” እንዲያም ሆኖ አብዛኞቻችን የምንከተለው ሃይማኖት አምላክን እንደሚያስደስተው ይሰማናል። ይሁን እንጂ አንድ ሃይማኖት የወላጆቻችን ሃይማኖት ስለሆነ ወይም በተወለድንበት አካባቢ በአንድ የውጭ ኃይል አስገዳጅነት ተቀባይነት ስላገኘ ብቻ ትክክል ነው ማለት አይደለም።

3-5. ሁሉም ሃይማኖቶች እውነትን ያስተምራሉ ማለት የማይቻልበትን ምክንያት ለመረዳት የሚያስችለን የትኛው ምሳሌ ነው?

3 ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክ ስለሚመለክበት መንገድ ትክክለኛ ትምህርት እንደሚያስተምሩ ቢናገሩም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው። ስለ አምላክ ማንነትና እሱ ከእኛ ስለሚፈልጋቸው ነገሮች የሚያስተምሩት ትምህርት ይለያያል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ ሥራ አገኘህ እንበል። ሥራ በምትጀምርበት ቀን አለቃህ እረፍት እንደወጣ ሰማህ። በመሆኑም ምን መሥራት እንዳለብህ ለማወቅ ሦስት የተለያዩ ሠራተኞችን ጠየቅክ። የመጀመሪያው ሠራተኛ አለቃህ ወለሉን እንድታጸዳ እንደሚፈልግ ነገረህ። ሁለተኛው ሠራተኛ ግድግዳውን ቀለም መቀባት እንደሚጠበቅብህ ነገረህ። ሦስተኛው ደግሞ ፖስታ እንድታድል ነገረህ።

4 ከዚያም ሠራተኞቹን ስለ አለቃህ ማንነት እንዲነግሩህ ጠየቅካቸው። የመጀመሪያው ሠራተኛ አለቃህ ረጅም፣ ወጣትና ኮስታራ እንደሆነ ነገረህ። ሁለተኛው ሠራተኛ፣ አለቃህ አጭር፣ በዕድሜ ጠና ያለና ደግ እንደሆነ ነገረህ። ሦስተኛው ሠራተኛ ደግሞ ጭራሹኑ “አለቃህ ወንድ አይደለም፣ ሴት ናት” ብሎህ እርፍ አለ። በዚህ ጊዜ ሦስቱም ሠራተኞች የነገሩህ ነገር እውነት መሆኑን መጠራጠርህ አይቀርም። አዲሱን ሥራህን ይዘህ መቀጠል ከፈለግክ ስለ አለቃህ ማንነትና ምን እንድትሠራ እንደሚፈልግ ለማጣራት ጥረት እንደምታደርግ የታወቀ ነው።

5 በሃይማኖት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የአምላክን ማንነትና እሱ ከእኛ የሚፈልገውን ነገር በተመለከተ ብዙ ዓይነት አመለካከት ስላለ አምላክን የምናመልክበት መንገድ ትክክለኛ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልገናል። ሆኖም ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?