በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 3

በሰማያት የሚኖሩት እነማን ናቸው?

በሰማያት የሚኖሩት እነማን ናቸው?

1. የአፍሪካን ባሕላዊ እምነት ከተራራ ጋር በማነጻጸር መግለጽ የሚቻለው እንዴት ነው?

የአፍሪካን ባሕላዊ እምነቶች የሚከተሉ ሰዎች ያላቸውን አመለካከት ከተራራ ጋር በማነጻጸር መግለጽ ይቻላል። ተራራው አናት ላይ ከሁሉ የላቀ መንፈሳዊ ሥልጣን ያለው አምላክ ይገኛል። በተራራው ጎን ላይ፣ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑና ከእሱ ዝቅ ያለ ሥልጣን ያላቸው አማልክት ወይም መናፍስት አሉ። ከእነሱ ጋር ደግሞ ምድር ላይ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስታውሱና ስለ ደህንነታቸው የሚያስቡ የቀድሞ አባቶች መናፍስት ይገኛሉ። በተራራው ግርጌ፣ እንደ አስማትና ጥንቆላ ያሉ መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው መናፍስት አሉ።

2. በአፍሪካ የሚነገር አንድ አባባል የትኛውን እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል?

2 እነዚህ ባሕላዊ እምነቶች በአፍሪካ በሚገኙ ሌሎች ሃይማኖቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። በአፍሪካ የሚነገር አንድ አባባል ይህን እውነታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፤ ይህ አባባል “የትኛውንም እምነት (ክርስትናንም ሆነ እስልምናን) መከተላችን የአገራችንን አማልክት ከማምለክ አያግደንም” ይላል።

3. በመንፈሳዊው ዓለም ስለሚኖሩ አካላት እውነታውን ልናውቅ የምንችለው ከየት ነው?

3 ይሁንና ባሕላዊ እምነቶች ትክክል ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈሳዊው ዓለም የሚኖሩ አካላትን በተመለከተ እውነታው ምን እንደሆነ ይነግረናል።

እውነተኛው አምላክ ይሖዋ

4. በአፍሪካ የሚገኙ ዋና ዋና ሃይማኖቶች በምን ይስማማሉ?

4 በአፍሪካ ያሉት ሦስቱ ዋና ዋና ሃይማኖታዊ ቡድኖች አምላክ በእርግጥ እንዳለና ከሁሉ በላይ እንደሆነ ይስማማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እሱ “የአማልክት አምላክና የጌቶች ጌታ እንዲሁም ታላቅ፣ ኃያል፣ የሚያስፈራ” አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። (ዘዳግም 10:17) ሙስሊሞችም የሁሉ የበላይ የሆነ አንድ አምላክ እንዳለ ያምናሉ። ፕሮፌሰር ጄፍሪ ፓሪንደር በአፍሪካ ስለሚገኙ ባሕላዊ ሃይማኖቶች ሲናገሩ “አብዛኞቹ አፍሪካውያን የአማልክትና የሰዎች አባት፣ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪና የሁሉ የበላይ በሆነ አምላክ ያምናሉ” ብለዋል።

5. ሰዎች አምላክን ለመጥራት ከሚጠቀሙባቸው ስያሜዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

5 ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች በአምላክ ቢያምኑም ስለ ማንነቱ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የላቸውም። አንድን ሰው ለማወቅ በቅድሚያ ስሙን ማወቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ የአምላክንም ስም ማወቅ አስፈላጊ ነው። ይሁንና የአምላክን ስም በተመለከተ በሃይማኖቶች መካከል የተዘበራረቀ አመለካከት አለ። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች አምላክ ብለው የሚጠሩት ሲሆን ብዙውን ጊዜ ይህ የማዕረግ ስም “ኃያል” የሚል ትርጉም አለው። ሙስሊሞች አላህ ብለው ይጠሩታል። ባሕላዊ እምነቶችን የሚከተሉ ሰዎች ደግሞ ከሁሉ በላይ የሆነውን አካል ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ስያሜ እንደየቋንቋው ይለያያል። ጆን ኤስ ምቢቲ ኮንሴፕትስ ኦቭ ጎድ ኢን አፍሪካ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ከ500 የሚበልጡ ለአምላክ የተሰጡ መጠሪያዎችንና የማዕረግ ስሞችን ዘርዝረዋል። ለምሳሌ በዮሩባ ቋንቋ (ናይጄሪያ) ኦሎዱማሬ ተብሎ ይጠራል፤ ኪኩዩዎች (ኬንያ) ንጋይ ይሉታል፤ ዙሉዎች (ደቡብ አፍሪካ) ደግሞ ኡንኩሉንኩሉ ብለው የሚጠሩት ሲሆን በአማርኛ እግዚአብሔር የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

6, 7. የአምላክ ስም ማን ነው? እንዴትስ ማወቅ እንችላለን?

6 ይሁንና አምላክ ራሱ ስለ ስሙ ምን ይላል? አምላክ፣ እስራኤላውያንን ከግብጽ መርቶ እንዲያወጣ ሙሴን ባዘዘው ጊዜ ሙሴ “ወደ እስራኤላውያን ሄጄ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው እነሱ ደግሞ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን ልበላቸው?” ሲል ጠይቆ ነበር።—ዘፀአት 3:13

7 አምላክ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ፣ . . . ይሖዋ ወደ እናንተ ልኮኛል።’ ይህ ለዘላለም ስሜ ነው፤ ከትውልድ እስከ ትውልድ የምታወሰውም በዚህ ነው።” (ዘፀአት 3:15) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህን መለኮታዊ ስም “አምላክ” ወይም “ጌታ” በሚሉት የማዕረግ ስሞች ቢተኩትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል።

8. ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው? የእሱን ሞገስ ማግኘት ከፈለግንስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

8 ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ ነው? ይሖዋ መንፈስ ነው፤ ሁሉን ቻይና ታላቅ ግርማ የተላበሰ እንዲሁም ተወዳዳሪና አቻ የሌለው ከሁሉ በላይ የሆነ አምላክ ነው። (ዘዳግም 6:4፤ ኢሳይያስ 44:6) ይሖዋ ሙሴን “እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ” ብሎታል። በሌላ አባባል የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን እሱን ብቻ ማምለክ ይኖርብናል። ከእሱ ሌላ ምንም ነገር ወይም ማንንም እንድናመልክ አይፈልግም።—ዘፀአት 20:3-5

የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ

9. ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር እኩል አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

9 በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የኢየሱስን ማንነት በተመለከተ የተለያየ አመለካከት አላቸው። ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ የሥላሴ አንድ አካል እንደሆነ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላክ አንድም ሦስትም እንደሆነ አያስተምርም። በተጨማሪም ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር እኩል እንደሆነ አይናገርም። ኢየሱስ ራሱ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ብሏል።—ዮሐንስ 14:28

10. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የት ነበር?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ምድር ላይ ከመኖሩ በፊት ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር እንደነበረ ያስተምራል። ይሖዋ በምድር ላይ አዳምንና ሔዋንን እንደፈጠረ ሁሉ በሰማይ ላይም መንፈሳዊ ፍጡራንን ፈጥሯል። ይሖዋ ከፈጠራቸው መንፈሳዊ ፍጡራን መካከል የመጀመሪያው ኢየሱስ ነው።—ዮሐንስ 17:5፤ ቆላስይስ 1:15

11. ኢየሱስ ሰው ሆኖ ሊወለድ የቻለው እንዴት ነው?

11 ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ይሖዋ የዚህን መንፈሳዊ ፍጡር ሕይወት ማርያም ወደምትባል ድንግል ማህፀን አዛወረ። መልአኩ ገብርኤል ማርያምን “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። . . . [እሱም] ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም” አላት።—ሉቃስ 1:31, 33 *

12. ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

12 በዚህ መንገድ ኢየሱስ ተወለደ፤ አድጎም ሙሉ ሰው ሆነ፤ ለሰዎችም የይሖዋን ፈቃድና ዓላማ አስተማረ። “እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመሥከር ነው” በማለት ለአንድ ሮማዊ ገዢ ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:37) ኢየሱስ ያስተማረውን ትምህርት በመመርመር ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ እውነቱን ማወቅ እንችላለን። በተጨማሪም የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።

13. ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ሁለተኛው ምክንያት ምንድን ነው?

13 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ሁለተኛ ምክንያት ሕይወቱን ለሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ነው። (ማቴዎስ 20:28) ይህን ያደረገው ከአባታችን ከአዳም ከወረስነው ኃጢአት ነፃ እንድንሆን ነው። ይህ ደግሞ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበት አጋጣሚ ይከፍትልናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” ሲል ጽፏል።—ዮሐንስ 3:16

14. (ሀ) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ምን ሆነ? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ በሰማይ ምን ሥልጣን ተሰጥቶታል?

14 ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ በመሄድ ዳግመኛ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ መኖሩን ቀጥሏል። (የሐዋርያት ሥራ 2:32, 33) በኋላም ይሖዋ “ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣ ክብርና መንግሥት” ሰጠው። (ዳንኤል 7:13, 14) ኢየሱስ ኃያል ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል፤ የይሖዋ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ነው። በቅርቡ ሥልጣኑን በመላው ምድር ላይ ያሳያል።

የአምላክ አገልጋዮች የሆኑት መላእክት

15. መላእክት የተፈጠሩት መቼና የት ነው?

15 በሰማያት የሚኖሩት ይሖዋና ኢየሱስ ብቻ አይደሉም። ይሖዋ ሌሎች መንፈሳዊ ፍጡራንን ማለትም መላእክትን ፈጥሯል። ማርያምን ያነጋገራት ገብርኤል ከእነዚህ መላእክት አንዱ ነው። መላእክት ቀደም ሲል፣ ሰዎች ሆነው በምድር ላይ ይኖሩ የነበሩ ፍጡራን አይደሉም። በምድር ላይ ሰዎች ከመፈጠራቸው ከብዙ ዘመናት በፊት በሰማይ ላይ የተፈጠሩ መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው። (ኢዮብ 38:4-7) በሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክት አሉ።—ዳንኤል 7:10

ታማኝ መላእክት መመለክ አይፈልጉም

16. ሰዎች መላእክትን ማምለክ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?

16 ታማኝ መላእክት እንድናመልካቸው አይፈልጉም። ሐዋርያው ዮሐንስ ከአንድም ሁለት ጊዜ ለመላእክት ለመስገድ ሞክሮ መላእክቱ “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው! . . . ለአምላክ ስገድ!” ሲሉ ገሥጸውታል።—ራእይ 19:10፤ 22:8, 9

17. መላእክት የአምላክን አገልጋዮች ሊጠብቁ እንደሚችሉ የሚያሳየው ምንድን ነው? ይህን ማወቃችንስ ሊያጽናናን የሚገባው ለምንድን ነው?

17 መላእክት የኢየሱስን ሐዋርያት ከእስር ባስፈቱበት ወቅት እንዳደረጉት ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ምድር ላይ ለሚኖሩ የሰው ልጆች አይገለጡም። (የሐዋርያት ሥራ 5:18, 19) ይሁን እንጂ ይሖዋን፣ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ካመለክን ኃያል የሆኑትና የማይታዩት የአምላክ መላእክት እንደሚጠብቁን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋ መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል” ይላል። (መዝሙር 34:7፤ 91:11) ይህን ማወቃችን ሊያጽናናን የሚገባው ለምንድን ነው? በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እኛን ለማጥፋት የሚፈልጉ አደገኛ ጠላቶች ስላሉ ነው።

የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን

18. (ሀ) አንድ መልአክ በአምላክ ላይ ያመፀው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ ዓመፀኛ መልአክ ምን ስሞች ተሰጥተውታል?

18 ለአምላክ ታማኝ ሆነው የጸኑት ሁሉም መላእክት አይደሉም። አንዳንዶቹ ዓምፀውበታል። አልፎ ተርፎም የአምላክና የሰው ልጆች ጠላት ሆነዋል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ የፈጠራቸው መላእክት በሙሉ ጻድቃንና ጥሩዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ፍጹማን መንፈሳዊ ልጆች መካከል አንዱ ሰዎች እንዲያመልኩት ፈለገ፤ ይህን ፍላጎቱን ለማሳካትም እርምጃ ወሰደ። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ሰይጣን ተብሎ የተጠራ ሲሆን ትርጉሙም “[የአምላክ] ተቃዋሚ” ማለት ነው። በተጨማሪም ስለ ይሖዋ ተንኮል ያዘለ ውሸት ስለሚናገር ዲያብሎስ የሚል ስም ተሰጥቶታል፤ ይህ ቃል “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው።

19. ሰይጣን ኢዮብን ያሠቃየው ለምንና እንዴት ነበር?

19 ሰይጣን የሰው ልጆች በአምላክ ላይ በማመፅ ከእሱ ጎን እንዲሰለፉ ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል። የአምላክ ታማኝ አገልጋይ በነበረው በኢዮብ ላይ ያደረገውን እንመልከት። ኢዮብ በጣም ሀብታም ሰው የነበረ ሲሆን 7,000 በጎች፣ 3,000 ግመሎች፣ 1,000 ላሞችና በሬዎች እንዲሁም 500 እንስት አህዮች ነበሩት። በተጨማሪም አሥር ልጆችና ብዙ አገልጋዮች ነበሩት። ሰይጣን በመጀመሪያ የኢዮብን ከብቶችና አገልጋዮች ገደለ። ቀጥሎም “ኃይለኛ ነፋስ” በማስነሳት የኢዮብ ልጆች የነበሩበት ቤት እንዲደረመስና ሁሉም እንዲያልቁ አደረገ። ከዚያም ሰይጣን “ኢዮብን ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መታው።”—ኢዮብ 1:3-19፤ 2:7

20. (ሀ) ኢዮብ ለታማኝነቱ ምን ወሮታ ተከፈለው? (ለ) ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ቢጸናም ሰይጣን ሌሎች ብዙ ሰዎችን ምን ማድረግ ችሏል?

20 ኢዮብ ይህ ሁሉ ከባድ ፈተና ቢደርስበትም ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ጸንቷል። በመሆኑም ይሖዋ ከበሽታው የፈወሰው ከመሆኑም ሌላ “ቀድሞ የነበረውን እጥፍ አድርጎ ሰጠው።” (ኢዮብ 42:10) ሰይጣን የኢዮብን ንጹሕ አቋም ማጉደፍ አይቻል እንጂ ሌሎች ብዙ ሰዎችን ከአምላክ ማራቅ ችሏል። መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም ግን በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” ይላል።—1 ዮሐንስ 5:19

21. (ሀ) ሰይጣን የመመለክ ፍላጎት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ሰይጣንን ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆነው ለምንድን ነው?

21 ሰይጣን እሱን እንድናመልክ ይፈልጋል። ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ለኢየሱስ ያቀረበው ፈተና ይህን በግልጽ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዲያብሎስ [ኢየሱስን] በጣም ረጅም ወደሆነ ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው። ከዚያም ‘አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ’ አለው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ‘አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” ተብሎ ተጽፏልና’ አለው።” (ማቴዎስ 4:8-10) ኢየሱስ የይሖዋን ሕግ ጠንቅቆ ያውቃል፤ በመሆኑም ሰይጣንን ለማምለክ ፈቃደኛ አልሆነም።

ክፉ መናፍስት የሆኑት አጋንንት

22. አጋንንት በሰው ልጆች ላይ ምን አድርገዋል?

22 ሌሎች መላእክትም በአምላክ ላይ በማመፅ ከሰይጣን ጋር ተባብረዋል። እነዚህ አጋንንት የሆኑ መላእክት ምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ጠላቶች ናቸው። ጨካኞችና ክፉዎች ናቸው። በድሮ ዘመን አንዳንድ ሰዎችን ዱዳና ዓይነ ስውር አድርገው ነበር። (ማቴዎስ 9:32, 33፤ 12:22) ሌሎችን ደግሞ ለበሽታና ለአእምሮ ሕመም ዳርገዋል። (ማቴዎስ 17:15, 18፤ ማርቆስ 5:2-5) ሕፃናትን እንኳ ሳይቀር አሠቃይተዋል።—ሉቃስ 9:42

23. (ሀ) ክፉ መናፍስት ከሰዎች ምን ማግኘት ይፈልጋሉ? (ለ) ሰይጣንና አጋንንት ሰዎችን በማታለል ምን እንዲፈጽሙ ያደርጓቸዋል?

23 እንደ ሰይጣን ሁሉ እነዚህ ክፉ መናፍስትም መመለክ ይፈልጋሉ። መመለክ የሚገባው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ በመገንዘብ የሰው ልጆች የሚያቀርቡላቸውን አምልኮ አንቀበልም ከማለት ይልቅ ለመመለክ ይቋምጣሉ፤ አልፎ ተርፎም እንዲህ ያለውን አምልኮ ያስፋፋሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ በማታለል፣ በመዋሸትና በማስፈራራት ሰዎች እንዲያመልኳቸው ያደርጋሉ። እርግጥ፣ ብዙ ሰዎች ሰይጣንንና አጋንንቱን እንደሚያመልኩ አያውቁም። አብዛኞቹ ሰዎች ሃይማኖታቸው ለሰይጣን ክብር እንደሚሰጥ ቢያውቁ ይደነግጣሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “አሕዛብ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቧቸውን ነገሮች የሚሠዉት ለአምላክ ሳይሆን ለአጋንንት ነው” ሲል ያስጠነቅቃል።—1 ቆሮንቶስ 10:20

24. ሰይጣን ሰዎችን ከሚያሳስትባቸው የተንኮል ዘዴዎች አንዱ ምንድን ነው?

24 ሰይጣንና አጋንንት ሰዎችን አሳስተው እነሱን እንዲያመልኩ ከሚያደርጉባቸው መንገዶች አንዱ የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ማሰራጨት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምር እንመልከት።

^ አን.11 ቁርኣን በሱራህ 19 (መርየም) ላይ ኢየሱስ በተአምራዊ መንገድ ስለ መወለዱ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “መንፈሳችንንም (ጂብሪልን) ወደርሷ [ወደ መርየም] ላክን። ለእርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት። ‘እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ፤ ጌታህን ፈሪ እንደ ኾንክ (አትቅረበኝ)’ አለች። ‘እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ፣ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ’ አላት። ‘(በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ኾኜ፣ አመንዝራም ሳልኾን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል!’ አለች። አላት፦ ‘(ነገሩ) እንደዚህሽ ነው።’ ጌታሽ ‘እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው፤ ለሰዎችም ታምር፣ ከኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው’ አለ።”