በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 6

አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል?

አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል?

1. የአምላክ ቃል በሚናገረው መሠረት ሃይማኖቶች በሙሉ በየትኞቹ ሁለት ቡድኖች ይፈረጃሉ?

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) የአምላክ ቃል እንደሚናገረው ሃይማኖቶች በሙሉ በሁለት ይፈረጃሉ፤ እውነተኛው፣ ትክክለኛውና ወደ ሕይወት የሚመራው ሃይማኖት አንድ ብቻ ሲሆን የቀሩት ግን ሐሰተኞች፣ የተሳሳቱና ወደ ጥፋት የሚመሩ ናቸው።

2. መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን የሚያስደስቱት ሁሉም ሃይማኖቶች እንዳልሆኑ የሚያሳየው እንዴት ነው?

2 አንዳንድ ሰዎች ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን እንደሚያስደስቱ ይሰማቸዋል። የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ግን ይህ ትክክል አለመሆኑን ያሳያሉ፦

  • “እስራኤላውያንም በይሖዋ ፊት እንደገና መጥፎ ነገር አደረጉ፤ ባአልን፣ የአስታሮትን ምስሎች፣ የአራምን አማልክት፣ የሲዶናን አማልክት፣ የሞዓብን አማልክት፣ የአሞናውያንን አማልክትና የፍልስጤማውያንን አማልክት ማገልገል ጀመሩ። ይሖዋን ተዉት፤ እሱንም አላገለገሉም። የይሖዋም ቁጣ በእስራኤል ላይ ነደደ።” (መሳፍንት 10:6, 7) ጣዖታትን ወይም ከእውነተኛው አምላክ ሌላ የትኛውንም አምላክ ብናመልክ ይሖዋ አይደሰትም።

  • “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው። የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።” (ማርቆስ 7:6, 7) ሰዎች፣ አምላክን እናመልካለን እያሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ሳይሆን የራሳቸውን አስተሳሰብ የሚያስተምሩ ከሆነ የሚያቀርቡት አምልኮ ከንቱ ነው። በአምላክም ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም።

  • “አምላክ መንፈስ ነው፤ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።” (ዮሐንስ 4:24) የምናቀርበው አምልኮ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው እውነት ጋር የሚስማማ መሆን ይገባዋል።

የሐሰት ሃይማኖት ፍሬ

3. እውነተኛው ሃይማኖት ከሐሰተኛው የሚለይበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

3 አንድ ሃይማኖት አምላክን የሚያስደስት መሆን አለመሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? ኢየሱስ “ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። . . . በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል። በሌላ አባባል በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃይማኖት ጥሩ ፍሬ ያፈራል፤ በሰይጣን የሚመራ ሃይማኖት ከሆነ ግን መጥፎ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርም።—ማቴዎስ 7:15-20

4. የይሖዋ አምላኪዎች ምን ዓይነት ባሕርይ ያሳያሉ?

4 የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች፣ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱ ከመሆኑም ሌላ ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ያሳያሉ። ምክንያቱም ይሖዋ ራሱ አፍቃሪ አምላክ ነው። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሃይማኖቶች፣ እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ከሚያሳውቀው ከዚህ መሥፈርት አንጻር ሲታዩ ምን ይመስላሉ?—ዮሐንስ 13:35፤ ሉቃስ 10:27፤ 1 ዮሐንስ 4:8

5. አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ በአፍሪካ ይካሄድ የነበረውን የባሪያ ንግድ አስመልክቶ ምን ብሏል?

5 በአፍሪካ ይካሄድ የነበረውን የባሪያ ንግድ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደተናገረው ከ650 እስከ 1905 ባሉት ዓመታት ውስጥ በግምት 18,000,000 የሚያክሉ አፍሪካውያን በሰሃራና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ ባሉ አገራት ለባርነት ተሸጠዋል። ኢንሳይክሎፒዲያው አክሎ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በ15ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ላይ አውሮፓውያን በአፍሪካ ምዕራባዊ ዳርቻ የባሪያ ንግድ ማካሄድ የጀመሩ ሲሆን እስከ 1867 ድረስ ከ7,000,000 እስከ 10,000,000 የሚሆኑ አፍሪካውያንን ወደ አዲሱ ዓለም በባርነት አግዘዋል።”

6. ሃይማኖቶች ከባሪያ ንግድ ጋር በተያያዘ ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል?

6 ወንዶች፣ ሴቶችና ሕጻናት ከቤታቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተነጥቀው በሰንሰለት እየታሰሩና በጋለ ብረት እየተተኮሱ እንደ ከብት ይሸጡ በነበረበት በዚህ የአፍሪካ የመከራ ዘመን ሃይማኖቶች ምን ዓይነት አቋም ይዘው ነበር? ቤትዌል ኦጎት የተባሉ ምሁር በናይሮቢ፣ ኬንያ በሚታተመው ዴይሊ ኔሽን የተባለ ጋዜጣ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የክርስትናም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶች የሰው ልጆች አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያስተምራሉ፤ ይሁን እንጂ ሁለቱም ሃይማኖቶች ለሌላው ዘር ጥላቻ ያለውና ባሪያ አሳዳሪ የሆነ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር አድርገዋል። . . . ለብዙ መቶ ዓመታት በአፍሪካውያን ላይ ለደረሰው ይህ ነው የማይባል ሥቃይና መከራ ሙስሊሞችም ሆኑ ክርስቲያኖች፣ የምዕራቡ ዓለምም ሆነ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እንዲሁም በጊዜው የነበረው የሥነ ምግባር ድንቁርና ተጠያቂዎች መሆናቸውን አምነን መቀበል አለብን።”

ሃይማኖት እና ጦርነት

7. የሃይማኖት መሪዎች ከጦርነት ጋር በተያያዘ ምን ሚና ተጫውተዋል?

7 የሐሰት ሃይማኖት በሌሎች መንገዶችም የበሰበሰ ፍሬ እንደሚያፈራ ታይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ባልንጀራህን . . . ውደድ” ይላል፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ግን ጦርነትን ሲደግፉና ሲያበረታቱ ቆይተዋል።—ማቴዎስ 22:39

የሐሰት ሃይማኖቶች በጦርነቶችና በባሪያ ንግድ ላይ ተሳትፈዋል

8. (ሀ) በአፍሪካ በተካሄዱ ግጭቶች ላይ የሃይማኖት መሪዎች ደም መፋሰስን ሲያበረታቱ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) በናይጄሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት አንድ ፓስተር የሃይማኖት መሪዎችን አስመልክቶ ምን ብሏል?

8 አንዳንድ መነኮሳትና ቀሳውስት በ1994 በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ላይ እንደተካፈሉ በሰፊው የሚታወቅ ነው። በሌሎች የአፍሪካ አገራት በተደረጉ ግጭቶች ላይም ቢሆን ሃይማኖቶች ትልቅ ሚና ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በናይጄሪያ በተካሄደው አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ በሁለቱም ጎራ የተሰለፉት ሃይማኖቶች አባሎቻቸው በጦርነት እንዲካፈሉ ያበረታቱ ነበር። በጦርነቱ ወቅት አንድ ፓስተር፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን አስመልክቶ “አምላክ የሰጣቸውን ሥራ ቸል ብለዋል” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ራሳችንን የአምላክ አገልጋይ አድርገን የምንቆጥር ቢሆንም የሰይጣን አገልጋዮች ሆነናል።”

9. መጽሐፍ ቅዱስ የሰይጣንን አገልጋዮች በተመለከተ ምን ይላል?

9 መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሐሳብም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም፤ እንዲህ ይላል፦ “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣልና። ስለዚህ አገልጋዮቹም የጽድቅ አገልጋዮች ለመምሰል ራሳቸውን ቢለዋውጡ ምንም አያስገርምም።” (2 ቆሮንቶስ 11:14, 15) ብዙ መጥፎ ሰዎች ጥሩ መስለው እንደሚታዩ ሁሉ የሰይጣን አገልጋዮችም ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙና የበሰበሰ ፍሬ የሚያፈሩ ቢሆኑም ጻድቅ መስለው ይታያሉ፤ ሰይጣን እነዚህን አገልጋዮቹን በመጠቀም ሰዎችን ያታልላል።

10. የሃይማኖት መሪዎች አምላክን የካዱት እንዴት ነው?

10 በዓለም ዙሪያ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም እና ስለ ጥሩነት ሲሰብኩ ይሰማሉ፤ ሆኖም ተግባራቸው ጥላቻን፣ ጦርነትንና ክፋትን የሚያበረታታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉትን የሃይማኖት መሪዎች ጥሩ አድርጎ ይገልጻቸዋል። እንዲህ ይላል፦ “አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል።”—ቲቶ 1:16

‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ውጡ

11. መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ሃይማኖትን እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?

11 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የራእይ መጽሐፍን ስናነብብ ይሖዋ ስለ ሐሰት ሃይማኖት ምን እንደሚሰማው ማወቅ እንችላለን። በዚህ መጽሐፍ ላይ የሐሰት ሃይማኖት “ታላቂቱ ባቢሎን” በተባለች አንዲት ምሳሌያዊት ሴት ተወክሏል። (ራእይ 17:5) አምላክ ይህችን ሴት እንዴት አድርጎ እንደገለጻት ተመልከት፦

  • ‘የምድር ነገሥታት ከታላቂቱ አመንዝራ ጋር አመነዘሩ።’ (ራእይ 17:1, 2) የሐሰት ሃይማኖቶች ለአምላክ ታማኝ ከመሆን ይልቅ በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ይገባሉ፤ እንዲሁም መንግሥታት ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ ሐሳብ ይሰጣሉ።

  • “በእሷም ውስጥ የነቢያት፣ የቅዱሳንና በምድር ላይ የታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቷል።” (ራእይ 18:24) የሐሰት ሃይማኖቶች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችን ሲያሳድዱና ሲገድሉ ቆይተዋል፤ እንዲሁም በጦርነት ምክንያት ላለቁት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደም ተጠያቂዎች ናቸው።

  • ‘ለራሷ ክብር ሰጥታለች፤ እንዲሁም ያላንዳች ኀፍረት ውድ ነገሮች በማከማቸት ተቀማጥላለች።’ (ራእይ 18:7) የሐሰት ሃይማኖቶች ብዙ ሀብት ያካበቱ ሲሆን መሪዎቻቸው የቅንጦት ሕይወት ይመራሉ።

  • ‘በመናፍስታዊ ድርጊቶቿ ብሔራት ሁሉ ተሳስተዋል።’ (ራእይ 18:23) የሐሰት ሃይማኖቶች ‘ነፍስ አትሞትም’ የሚል የሐሰት ትምህርት ስለሚያስተምሩ ጥንቆላና መናፍስታዊ ድርጊቶች እንዲስፋፉ እንዲሁም ሰዎች ሙታንን እንዲፈሩና የሞቱ አያት፣ ቅድመ አያቶቻቸውን እንዲያመልኩ በር ከፍተዋል።

12. መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ሃይማኖትን አስመልክቶ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

12 መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት መውጣት እንዳለባቸው በጥብቅ ያስጠነቅቃል፤ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ ውጡ።”—ራእይ 18:4, 5

13. የሐሰት ሃይማኖቶችም ሆኑ ተከታዮቻቸው ምን ይደርስባቸዋል?

13 የዓለምን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ የምትወክለው ታላቂቱ ባቢሎን በቅርቡ ድምጥማጧ ይጠፋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መቅሰፍቶቿ ይኸውም ሞትና ሐዘን እንዲሁም ረሃብ በአንድ ቀን [ይመጡባታል]፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ትቃጠላለች፤ ምክንያቱም የፈረደባት ይሖዋ አምላክ ብርቱ ነው።” (ራእይ 18:8) በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ከሚመጣው መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማንፈልግ ከሆነ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያለንን ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርብናል፤ ይህም አምላክን ከማያስደስቱ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች፣ በዓላትና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ መራቅን ይጨምራል። ዛሬ ነገ ሳንል ይህን ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ሕይወታችን አደጋ ላይ ወድቋል!—2 ቆሮንቶስ 6:14-18