በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 7

እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉት እነማን ናቸው?

እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉት እነማን ናቸው?

1. አምላክን ለማስደሰት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲኖረን ከፈለግን ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ሊኖረን አይገባም። እውነተኛውን ሃይማኖት መከተል ይኖርብናል። በዛሬው ጊዜ በመላው ምድር የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን እያደረጉ ነው።

2. የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙት የት ነው? ምን ዓይነት ሥራስ ያከናውናሉ?

2 መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች” የተውጣጡት የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ሆነዋል። (ራእይ 7:9) በ239 አገሮች ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች ፍቅር ስለሚንጸባረቅባቸው የይሖዋ መመሪያዎችና መሥፈርቶች እንዲያውቁ በመርዳት ላይ ናቸው።

እውነተኛዎቹን የአምላክ አገልጋዮች ለይቶ ማወቅ

3. የይሖዋ ምሥክሮች የሚያመልኩት ማንን ብቻ ነው? ከየትኞቹ የአምልኮ ዓይነቶችስ ይርቃሉ?

3 የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሊመለክ የሚገባው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ለጣዖታት ወይም ለሃይማኖታዊ ምስሎች አይሰግዱም። (1 ዮሐንስ 5:21) ለሞቱ ሰዎች ክብር ሲባል በሚደረጉ እንደ ፍታት ባሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ አይካፈሉም፤ እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖት እምነቶችንና ‘የአጋንንትን ትምህርቶች’ በሚደግፉ ሌሎች ሥርዓቶች ላይ አይገኙም። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ይሁን እንጂ የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ እንደሚያገኙና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንደሚኖሩ አምላክ የሰጠውን ተስፋ በመናገር ዘመዶቻቸውን በሞት የተነጠቁ ሰዎችን ያጽናናሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

4. የአምላክ ሕዝቦች ከአስማታዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው?

4 የይሖዋ ምሥክሮች ከአስማት፣ ከመተትና ከጥንቆላ ይርቃሉ፤ ምክንያቱም የእነዚህ ነገሮች ምንጭ ዲያብሎስ እንደሆነ ያውቃሉ። አስማታዊ ድርጊቶች ጥበቃ እንደሚያስገኙላቸው አያምኑም፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ይታመናሉ።—ምሳሌ 18:10

5. የይሖዋ ምሥክሮች “የዓለም ክፍል አይደሉም” የምንለው ለምንድን ነው?

5 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:16) እሱ ራሱም ቢሆን በወቅቱ በነበሩት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልነበረም። (ዮሐንስ 6:15) በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮችና የመደብ ትግሎች ላይ አይካፈሉም፤ እንዲሁም ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው እንቅስቃሴዎች አይሳተፉም። ይሁን እንጂ ግብር ይከፍላሉ፤ የሚኖሩበትን አገር ሕግም ያከብራሉ።—ዮሐንስ 15:19፤ ሮም 13:1, 7

6. የአምላክ አገልጋዮች ጋብቻንና ፍቺን በተመለከተ የትኞቹን መመሪያዎች ይከተላሉ?

6 የይሖዋ ምሥክሮች መንግሥታት ለሚያወጡት ሕግ ስለሚታዘዙ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ያደርጋሉ። (ቲቶ 3:1) የአምላክን መመሪያ ስለሚያከብሩ ከአንድ በላይ አያገቡም። (1 ጢሞቴዎስ 3:2) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ አገልጋዮች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወታቸው ተግባራዊ ስለሚያደርጉ ጋብቻቸው በፍቺ የሚያበቃበት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ ነው።

7. የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርሳቸው እንደሚዋደዱ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

7 የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርሳቸው ይዋደዳሉ። ከተለያዩ ዘሮችና ብሔሮች የተውጣጡ ቢሆኑም አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር፣ ለአምላክ ካላቸው ፍቅር ጋር ተዳምሮ አንድነት ያለው እውነተኛ የወንድማማች ኅብረት ለመመሥረት አስችሏቸዋል። የተፈጥሮ አደጋ ወይም አንድ ዓይነት ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ አንዳቸው ሌላውን ለመርዳት ፈጣን እርምጃ ይወስዳሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ ፍቅርን ያሳያሉ።—ዮሐንስ 13:35

የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ኅብረት መመሥረት ችለዋል

8. የአምላክ ሕዝቦች ከየትኞቹ መጥፎ ድርጊቶች ይርቃሉ?

8 የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኞች ለመሆንና ጥሩ ሥነ ምግባር ይዘው ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። አይሰርቁም፤ አይዋሹም፤ የብልግና ድርጊቶችን አይፈጽሙም፤ አይሰክሩም፤ እንዲሁም በንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ አያጭበረብሩም። ባሎች ሚስቶቻቸውን አይደበድቡም። አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክር ከመሆናቸው በፊት እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር፤ አሁን ግን በይሖዋ እርዳታ እነዚህን ነገሮች ማድረጋቸውን አቁመዋል። በአምላክ ዓይን ሲታዩ ‘ታጥበው ነጽተዋል።’—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

የአምላክን ፈቃድ ያደርጋሉ

9. አንድ መጽሐፍ በአፍሪካ ስለሚገኙ አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ምን ብሏል?

9 እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ እምነቶች እውነተኛው ሃይማኖት የእነሱ እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህ አባባላቸው ማስረጃ እንዲሆናቸውም የሚሠሯቸውን ድንቅ ነገሮች ሊጠቅሱ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ አንድ መጽሐፍ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖችን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “[አዲሶቹ የክርስቲያን ቡድኖች] አብዛኛውን የአስማተኞች ወይም የመድኃኒተኞች ሥራ ወስደውታል። . . . ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንደሚያውቁና ተአምራት እንደሚፈጽሙ ይናገራሉ። በመካከላቸው ያሉ ነቢያት ራእይ ያያሉ፤ እንዲሁም ሕልም ይተረጉማሉ። ሰዎችን ለመፈወስ ወይም ከበሽታ ለመጠበቅ በጸበል፣ በቅብዓ ቅዱስ፣ በአመድ፣ በሻማና በዕጣን ይጠቀማሉ።”

10, 11. አንድ ሃይማኖት ተአምራት ናቸው የሚባሉ ድርጊቶችን መፈጸም መቻሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

10 እነዚህ ሃይማኖቶች ተአምራት መፈጸም የቻሉት የአምላክ ድጋፍ ስላላቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሃይማኖት ተአምራት ናቸው የሚባሉ ድርጊቶችን መፈጸም መቻሉ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ አይደለም። ሰይጣን የሐሰት እምነትን ለሚከተሉ አንዳንድ ሰዎች “ተአምራት” የማድረግ ኃይል ሊሰጣቸው ይችላል። (2 ተሰሎንቄ 2:9) በተጨማሪም ትንቢት እንደ መተንበይ፣ በልሳን እንደ መናገር እና ለየት ያለ እውቀት እንደ ማግኘት ያሉ አምላክ የሚሰጣቸው ተአምራዊ ስጦታዎች ‘የሚቀሩበት’ ጊዜ እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 13:8

11 ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው። በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23

12. ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት እነማን ናቸው?

12 ታዲያ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት እነማን ናቸው? የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉ ናቸው።

የአምላክ መንግሥት ሰባኪዎች

13. አምላክ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹ የትኛውን ሥራ እንዲያከናውኑ አዟል? ይህን ሥራ እያከናወኑ ያሉትስ እነማን ናቸው?

13 አምላክ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹ ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል? ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሥራ በቅንዓት በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

14. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የዚህ መንግሥት ገዢዎችስ እነማን ናቸው?

14 የይሖዋ ምሥክሮች፣ የአምላክ መንግሥት ምድርን ሁሉ በጽድቅ የሚያስተዳድር ሰማያዊ መንግሥት እንደሆነ “በመላው ምድር” ይሰብካሉ። ይሖዋ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሰው ልጆች መካከል ከተመረጡ 144,000 ተባባሪ ገዢዎች ጋር የዚህ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ እንደሾመው ያስተምራሉ።—ዳንኤል 7:14, 18፤ ራእይ 14:1, 4

15. የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያስወግዳል?

15 የይሖዋ ምሥክሮች፣ የአምላክ መንግሥት መላውን የሰይጣን ሥርዓት እንደሚያጠፋ ለሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያስተምራሉ። የሐሰት ሃይማኖትም ሆነ አምላክን የሚያቃልሉትና ዲያብሎስን ከፍ ከፍ የሚያደርጉት ትምህርቶቹ ይወገዳሉ። (ራእይ 18:8) በተጨማሪም አምላክን የሚቃወሙ ሰብዓዊ መንግሥታት በሙሉ ይጠፋሉ።—ዳንኤል 2:44

16. የክርስቶስ ኢየሱስ ተገዢዎች የሚሆኑት እነማን ናቸው? የሚኖሩትስ የት ነው?

16 ከዚህም በላይ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክን ለሚታዘዙ ሁሉ አስደናቂ በረከቶችን እንደሚያመጣላቸው ለሰዎች ያሳውቃሉ። እነዚህ ሰዎች በምድር ላይ ተገዢዎቹ ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እርዳታ ለማግኘት የሚጮኸውን ድሃ፣ እንዲሁም ችግረኛውንና ረዳት የሌለውን ሁሉ ይታደጋልና። ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤ የድሆችንም ሕይወት ያድናል።”—መዝሙር 72:12, 13

17. የአምላክን መንግሥት እያወጁ ያሉት እነማን ብቻ ናቸው?

17 የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሌላ ሃይማኖታዊ ቡድን የለም። በመላው ምድር የአምላክን መንግሥት እያወጁ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።