በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 4

የሞቱ አያት፣ ቅድመ አያቶቻችን ያሉት የት ነው?

የሞቱ አያት፣ ቅድመ አያቶቻችን ያሉት የት ነው?

1, 2. ብዙ ሰዎች ሙታንን በተመለከተ ምን ብለው ያምናሉ?

በአፍሪካ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት የሕይወት ፍጻሜ ሳይሆን በሌላ ዓለም ወዳለ ሕይወት የሚያሸጋግር ድልድይ እንደሆነ ያምናሉ። ብዙዎች በሞት ያንቀላፉ አያት፣ ቅድመ አያቶቻቸው ከሚታየው ዓለም ወደማይታየው ዓለም እንዲሁም ከሰዎች ዓለም ወደ መናፍስት ዓለም እንደተዛወሩ አድርገው ያስባሉ።

2 እነዚህ ቅድመ አያቶች ወይም የእነሱ መንፈስ ምድር ላይ የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚጠብቁና እንደሚያበለጽጓቸው ይታመናል። በዚህ አመለካከት መሠረት የአያት፣ ቅድመ አያቶች መንፈስ ጥሩ ምርት፣ ጤናና ደኅንነት ሊያስገኝ እንዲሁም ከክፉ ነገር ሊጠብቅ የሚችል ከፍተኛ ኃይል ያለው ወዳጅ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። ይህ መንፈስ ከተቀየመ ወይም ችላ ከተባለ ደግሞ ከባድ ጉዳት ይኸውም በሽታ፣ ድህነትና ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ይታመናል።

3. አንዳንድ ሰዎች የሞቱ አያት፣ ቅድመ አያቶቻቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው?

3 በሕይወት ያሉ ሰዎች የሞቱ ቅድመ አያቶቻቸውን መንፈስ ለማስደሰትና ለመለማመን ሲሉ የተለያዩ ልማዶችንና የአምልኮ ሥርዓቶችን ይፈጽማሉ። በአንዳንድ ባሕሎች በተለይ ከቀብር ሥርዓት ጋር በተያያዘ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ይታያል። በሞት ያንቀላፉ አያት፣ ቅድመ አያቶችን የማምለክ ልማድ የሚታይባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች የአልኮል መጠጥ ከመጠጣታቸው በፊት ለሞቱ ቅድመ አያቶቻቸው ሲሉ መሬት ላይ ትንሽ ፈሰስ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ምግብ ካበሰሉ በኋላ በሞት ካንቀላፉት አያት፣ ቅድመ አያቶቻቸው አንዱ ቢመጣ የሚበላው እንዳያጣ በሚል በዕቃው ላይ የተወሰነ ምግብ ያስቀራሉ።

4. ብዙ ሰዎች ነፍስን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው?

4 ሌሎች ደግሞ በሕይወት ያለ ሰው በውስጡ የማትሞት ነፍስ እንዳለችና በሚሞትበት ጊዜ ከሥጋው ተለይታ እንደምትሄድ ያምናሉ። ግለሰቡ ጥሩ ሰው ከነበረ ነፍሱ ወደ ሰማይ ወይም ወደ ገነት እንደምትወሰድ፣ ክፉ ሰው ከነበረ ደግሞ ወደ ሲኦል እንደምትጣል አድርገው ያስባሉ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ይህን አስተሳሰብ ከባሕላዊ እምነቶች ጋር ለማዛመድ ይሞክራሉ። ለምሳሌ በጋዜጦች ላይ የሚወጡ የአንድን ሰው ዜና እረፍት የሚገልጹ ማስታወቂያዎች “እግዚአብሔር ነፍሱን በገነት ያኑራት” ወይም “ነፍሱን ይማር” እንደሚሉት ያሉ አባባሎችን ይጠቀማሉ። እነዚህ አባባሎች አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ወይም መንፈሱ ከሥጋው ተለይቶ በሕይወት መኖሩን ይቀጥላል በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ነፍስ እና መንፈስ

5, 6. በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ነፍስ ምንድን ነች?

5 መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ፣ ሰውየው ራሱ እንጂ በሰውየው ውስጥ ያለች ነገር እንደሆነች አድርጎ አይናገርም። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ አዳምን በፈጠረ ጊዜ ‘ሰውየው ሕያው ነፍስ እንደሆነ’ ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:7 የግርጌ ማስታወሻ) አዳም ነፍስ አልተሰጠውም፤ ከዚህ ይልቅ እሱ ራሱ ነፍስ ማለትም ሰው ነበር።

6 ስለሆነም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ነፍስ እንደሚወለድ የሚገልጽ ዘገባ እናገኛለን። (ዘፍጥረት 46:18 የግርጌ ማስታወሻ) ነፍስ ልትበላ ወይም ልትጾም ትችላለች። (ዘሌዋውያን 7:20፤ መዝሙር 35:13 የግርጌ ማስታወሻ) ነፍስ ታለቅሳለች እንዲሁም ትደክማለች። (ኤርምያስ 13:17፤ ዮናስ 2:7 የግርጌ ማስታወሻ) በተጨማሪም ነፍስ መያዣ ሆና ልትወሰድ፣ ሰዎች ሊያሳድዷት እንዲሁም በእግር ብረት ልትታሰር ትችላለች። (ዘዳግም 24:6፤ መዝሙር 7:5፤ 105:18 የግርጌ ማስታወሻ) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኘውን ቃል “ነፍስ” ብለው ሲተረጉሙት ሌሎች ትርጉሞች ደግሞ “ሰው፣” “ፍጡር” ወይም “ሕይወት” በማለት ተርጉመውታል። ያም ሆኖ ሁሉም የሚያስተላልፉት ሐሳብ ተመሳሳይ ነው።

7. ነፍስ እንደምትሞት የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?

7 ሰው ራሱ ነፍስ ስለሆነ አንድ ሰው ሞተ ማለት ነፍሱ ሞተች ማለት ነው። ሕዝቅኤል 18:4 “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እሷ ትሞታለች” ይላል። በተጨማሪም የሐዋርያት ሥራ 3:23 (የግርጌ ማስታወሻ) “ያንን ነቢይ የማይሰማ ሰው [ወይም ነፍስ] ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል” ይላል። ስለዚህ ነፍስ፣ ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይታ በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ነገር አይደለችም።

8. በሰው ልጆች ውስጥ ያለው መንፈስ ምንድን ነው?

8 መንፈስ ከነፍስ ጋር አንድ አይደለም። በሰው ልጆች ውስጥ ያለው መንፈስ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው የሕይወት ኃይል ነው። መንፈስ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የኤሌክትሪክ ኃይል የአየር ማራገቢያ መሣሪያን ወይም ማቀዝቀዣን ሊያሠራ ይችላል፤ ይሁን እንጂ እሱ ራሱ አየር ሊያራግብ ወይም ምግብ ሊያቀዘቅዝ አይችልም። በተመሳሳይም በውስጣችን ያለው መንፈስ እንድናይ፣ እንድንሰማና እንድናስብ ያስችለናል። ይሁንና ዓይን፣ ጆሮ ወይም አንጎል ከሌለን መንፈስ በራሱ እነዚህን ነገሮች ማድረግ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች ሲናገር “መንፈሱ ትወጣለች፤ ወደ መሬት ይመለሳል፤ በዚያው ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል” የሚለው በዚህ የተነሳ ነው።—መዝሙር 146:4

9. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈስም ሆነ ስለ ነፍስ ምን ብሎ አያስተምርም?

9 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ነፍስም ሆነ መንፈስ ሰው ሲሞት ከሥጋው ተለይተው በመንፈሳዊው ዓለም መኖራቸውን የሚቀጥሉ ነገሮች እንደሆኑ አድርጎ አያስተምርም።

ሙታን የሚገኙበት ሁኔታ

10. መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ምን ይላል?

10 ታዲያ ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? የሰው ልጆችን የፈጠረው ይሖዋ ስለሆነ ስንሞት ምን እንደምንሆን የሚያውቀውም እሱ ነው። የአምላክ ቃል ሙታን መስማት፣ ማየት፣ መናገርም ሆነ ማሰብ የማይችሉ በድኖች እንደሆኑ ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦

  • “ሙታን . . . ምንም አያውቁም።”—መክብብ 9:5

  • “ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ጠፍቷል።”—መክብብ 9:6

  • “አንተ በምትሄድበት በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።”—መክብብ 9:10

11. አዳም ኃጢአት በሠራ ጊዜ ይሖዋ ምን አለው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጀመሪያው አባታችን ስለ አዳም ምን እንደሚል አስታውስ። ይሖዋ አዳምን ‘ከምድር አፈር እንደሠራው’ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:7) አዳም የይሖዋን ሕግ ቢጠብቅ ኖሮ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ሊኖር ይችል ነበር። ይሁን እንጂ አዳም የይሖዋን ሕግ ጣሰ። ቅጣቱ ደግሞ ሞት ነበር። አዳም ሲሞት ወዴት ሄደ? አምላክ አዳምን “ከመሬት ስለተገኘህ ወደ መሬት [ትመለሳለህ] . . . አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ” ብሎታል።—ዘፍጥረት 3:19

12. አዳም ሲሞት ምን ሆነ?

12 አዳም፣ ይሖዋ ከምድር አፈር ሳይፈጥረው በፊት የት ነበር? የትም አልነበረም። ከሕልውና ውጭ ነበር። ስለዚህ ይሖዋ፣ አዳም ‘ወደ አፈር እንደሚመለስ’ ሲናገር አዳም ዳግመኛ ልክ እንደ አፈር ሕይወት አልባ ይሆናል ማለቱ ነበር። አዳም በመንፈሳዊው ዓለም መኖር አልቀጠለም። የአያት፣ ቅድመ አያቶች መንፈስ ይኖርበታል ተብሎ ወደሚታሰበው ዓለም አልተሻገረም። ወደ ሰማይም ሆነ ወደ እሳታማ ሲኦል አልሄደም። ከዚህ ይልቅ ሕይወቱ አከተመ፤ ተመልሶ ከሕልውና ውጭ ሆነ።

13. ሰዎችም ሆኑ እንስሳት በሚሞቱበት ጊዜ ምን ይሆናሉ?

13 የሰው ሁሉ ዕጣ ፈንታ ተመሳሳይ ነው? አዎ፣ ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “[ሰዎችም ሆኑ እንስሳት] ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ። ሁሉም የተገኙት ከአፈር ነው፤ ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳሉ” ይላል።—መክብብ 3:19, 20

14. ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ሙታንን አስነስቶ ገነት በሆነች ምድር ላይ እንደሚያኖራቸው ይናገራል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) ይህ የሚሆንበት ጊዜ ግን ገና አልደረሰም። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በሞት አንቀላፍተው ይገኛሉ። (ዮሐንስ 11:11-14) በመሆኑም ሊረዱንም ሆነ ሊጎዱን ስለማይችሉ ልንፈራቸውም ሆነ ልናመልካቸው አይገባም።

15, 16. ሰይጣን፣ ‘ሰው ከሞተም በኋላ በሕይወት መኖሩን ይቀጥላል’ የሚለውን እምነት ለማስፋፋት የሚሞክረው እንዴት ነው?

15 ‘ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት መኖሩን ይቀጥላል’ የሚለው አስተሳሰብ ሰይጣን ዲያብሎስ የሚያስፋፋው ውሸት ነው። ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎች ይህን ውሸት አምነው እንዲቀበሉ ለማድረግ ሲሉ ‘በሰው ላይ በሽታና ሌሎች ችግሮች የሚደርሱት በሞቱ ሰዎች መንፈስ የተነሳ ነው’ የሚል አመለካከት እንዲያድርባቸው ያደርጋሉ። በሰዎች ላይ አንዳንድ ችግሮች የሚያደርሱት አጋንንት እንደሆኑ አይካድም። ሌሎች ችግሮች የሚደርሱት ደግሞ ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች ተጽዕኖ ሳይሆን በሌሎች ምክንያቶች ነው። ይሁን እንጂ ሙታን በእኛ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚለው ሐሳብ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው።

16 የሰው ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን የሚናገረው ነገር ስህተት እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ ለማድረግ አጋንንት የሚጠቀሙበት ሌላ ዘዴም አለ። ሰዎች ሙታንን እንዳዩ ወይም እንዳነጋገሩ ሆኖ እንዲሰማቸው በማድረግ ያታልሏቸዋል። አጋንንት ይህን የሚያደርጉት በሕልም፣ በራእይ፣ በመናፍስት ጠሪዎች ወይም በሌሎች መንገዶች ነው። ይሁን እንጂ ሰዎቹ የሚገናኙት ከሙታን ጋር ሳይሆን የሞቱትን ሰዎች መስለው ከሚቀርቡ አጋንንት ጋር ነው። ይሖዋ መናፍስት ጠሪዎችንና ሙታንን የሚያነጋግሩ ሰዎችን አጥብቆ የሚያወግዘው በዚህ ምክንያት ነው።—ዘዳግም 18:10-12፤ ዘካርያስ 10:2