በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 1

“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው!”

“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው!”

1, 2. (ሀ) አምላክን መጠየቅ የምትፈልጋቸው ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ሙሴ ለአምላክ ምን ጥያቄ አቅርቧል?

 ከአምላክ ጋር ስለ መነጋገር አስበህ ታውቃለህ? ከጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ጋር ስለ መነጋገር ማሰቡ ብቻ እንኳ ፍርሃት ሊያሳድርብህ ይችላል! አምላክ ወደ አንተ ቀርቦ ቢያነጋግርህ መጀመሪያ ላይ ፈርተህ ዝም ትል ይሆናል፤ በኋላ ግን እንደምንም መልስ መስጠትህ አይቀርም። በዚህ ጊዜ በጥሞና ያዳምጥሃል፣ መልስ ይሰጥሃል አልፎ ተርፎም ዘና ብለህ የፈለግኸውን መጠየቅ እንደምትችል እንዲሰማህ ያደርጋል። እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ብታገኝ ምን ጥያቄ ታቀርብ ነበር?

2 ከብዙ ዘመናት በፊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠመው አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው ሙሴ ይባላል። ይሁንና ለአምላክ ያቀረበው ጥያቄ ሊያስገርምህ ይችላል። ሙሴ የጠየቀው ስለ ራሱ፣ ስለ ወደፊት ዕጣው ወይም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ስላለው መከራ ሳይሆን ስለ አምላክ ስም ነበር። የአምላክን የግል ስም ያውቅ ስለነበር ይህን ጥያቄ ማቅረቡ ግር ሊያሰኝህ ይችላል። እንግዲያው ሙሴ ያቀረበው ጥያቄ ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው መሆን አለበት። እንዲያውም ይህ ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ነው። የተሰጠው መልስ የሁላችንንም ሕይወት የሚነካ ነው። ወደ አምላክ ለመቅረብ የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ እንድትወስድ ሊረዳህ ይችላል። እንዴት? በአምላክና በሙሴ መካከል የተካሄደውን ይህን አስደናቂ ውይይት እስቲ ጠለቅ ብለን እንመርምር።

3, 4. አምላክ ሙሴን ከማነጋገሩ በፊት ምን ነገር ተከሰተ? አምላክ ከሙሴ ጋር ያደረገው ውይይት ምንድን ነው?

3 በወቅቱ ሙሴ የ80 ዓመት ሰው ነበር። በግብፅ በባርነት ከሚኖሩት እስራኤላውያን ወገኖቹ ተለይቶ በስደት መኖር ከጀመረ አርባ ዓመት ገደማ አልፏል። አንድ ቀን የአማቱን በጎች እየጠበቀ ሳለ አንድ ትንግርት ተመለከተ። በአካባቢው የነበረ አንድ ቁጥቋጦ በእሳት ተያያዘ። ይሁንና ቁጥቋጦው ከመንደድ ይልቅ እንደ ማሾ አካባቢውን ወገግ አደረገው። ሙሴ ሁኔታውን ቀረብ ብሎ ለመመልከት ወደ ቁጥቋጦው ተጠጋ። ከእሳቱ መካከል አንድ ድምፅ ሲያነጋግረው ምንኛ ደንግጦ ይሆን! አምላክ አንድን መልአክ ቃል አቀባይ አድርጎ በመጠቀም ከሙሴ ጋር ረዘም ያለ ውይይት አደረገ። ከዚያም ሙሴ መጀመሪያ ላይ ቢያቅማማም ሰላማዊውን ኑሮ ትቶ ወደ ግብፅ እንዲመለስና እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ እንዲያወጣ የተሰጠውን ተልእኮ ተቀበለ።—ዘፀአት 3:1-12

4 በዚህ ጊዜ ሙሴ ለአምላክ የፈለገውን ጥያቄ ማቅረብ ይችል የነበረ ቢሆንም ምን ጥያቄ ማቅረብ እንደመረጠ ተመልከት፦ “ወደ እስራኤላውያን ሄጄ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው እነሱ ደግሞ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን ልበላቸው?”—ዘፀአት 3:13

5, 6. (ሀ) ሙሴ ያቀረበው ጥያቄ ምን ሐቅ ያስገነዝበናል? (ለ) በአምላክ የግል ስም ላይ ምን አሳዛኝ ድርጊት ተፈጽሟል? (ሐ) አምላክ ስሙን ለሰው ልጆች መግለጡ ምን ያሳያል?

5 በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ጥያቄ አምላክ ራሱ ስም እንዳለው ያስገነዝበናል። ይህ ደግሞ ወሳኝ ነገር ነው። ብዙዎች ግን አቅልለው ይመለከቱታል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን የግል ስም በማውጣት “ጌታ” እና “አምላክ” እንደሚሉት ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል። ይህ በሃይማኖት ስም ከተፈጸሙት እጅግ አሳዛኝ ድርጊቶች አንዱ ነው። ከአንድ ሰው ጋር በምትተዋወቅበት ጊዜ መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው? ስሙን እንደምትጠይቅ የታወቀ ነው። ከአምላክ ጋር ለመተዋወቅም ልናደርግ የሚገባው ነገር ይኸው ነው። አምላክ፣ ልናውቀውና ልንቀርበው የማንችል ስም የለሽ አካል እንደሆነ አድርገን ልናስብ አይገባንም። የማይታይ ቢሆንም እንኳ በእውን ያለ አካል ነው። ደግሞም ስም አለው፤ ስሙም ይሖዋ ነው።

6 ከዚህም በተጨማሪ አምላክ የግል ስሙን መግለጡ እሱን በቅርብ እንድናውቀው ልዩና አስደሳች ግብዣ እያቀረበልን እንዳለ የሚያሳይ ነው። ወደ እሱ በመቅረብ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የተሻለውን የጥበብ እርምጃ እንድንወስድ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ስሙን ብቻ ሳይሆን ስለ ማንነቱም ነግሮናል።

የአምላክ ስም ትርጉም

7. (ሀ) ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት የአምላክ የግል ስም ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) ሙሴ የአምላክን ስም በጠየቀበት ጊዜ ማወቅ የፈለገው ነገር ምን ነበር?

7 ይሖዋ ለራሱ የመረጠው ስም ጥልቅ ትርጉም አለው። ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት “ይሖዋ” የሚለው ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በእሱ ነው። ከዚህም ሌላ ዓላማው በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደርጋል፤ አልፎ ተርፎም ፍጹማን ያልሆኑ አገልጋዮቹ እንኳ እሱ የሚፈልገውን ሁሉ እንዲሆኑ ማድረግ ይችላል። ይህ ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን ያደርጋል። ይሁን እንጂ የስሙ መሠረታዊ ትርጉም በዚህ ብቻ አይወሰንም። ሙሴ ከዚህ የበለጠ ሊያውቀው የፈለገው ነገር እንደነበረ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ይሖዋ፣ ፈጣሪ እንደሆነ እንዲሁም ስሙ ማን እንደሆነ ሙሴ ያውቅ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ መለኮታዊው ስም ለሰዎች አዲስ አልነበረም። ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ሙሴ የአምላክን ስም ሲጠይቅ ስሙ ስለሚወክለው አካል ማንነት መጠየቁ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። በሌላ አነጋገር ሙሴ ‘እስራኤላውያን ሕዝቦችህ በአንተ እንዲታመኑና ነፃ እንደምታወጣቸው እርግጠኛ እንዲሆኑ ስለ አንተ ምን ልነግራቸው እችላለሁ?’ ብሎ የጠየቀ ያህል ነበር።

8, 9. (ሀ) ይሖዋ ለሙሴ ምን መልስ ሰጠው? የሰጠው መልስ ብዙውን ጊዜ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጎመውስ እንዴት ነው? (ለ) “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” የሚለው አገላለጽ ምን ማለት ነው?

8 ይሖዋ፣ ስለ ማንነቱ አስገራሚ የሆነ ነገር በመግለጽ መልስ ሰጥቶታል፤ የተናገረው ነገር ከስሙ ትርጉም ጋር የተያያዘ ነው። ሙሴን “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” አለው። (ዘፀአት 3:14) የ1954ቱን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “‘ያለና የሚኖር’ እኔ ነኝ” ሲሉ ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ ትክክለኛው አተረጓጎም እንደሚያሳየው አምላክ ይህን ሲናገር ስለ ሕልውናው በአጽንኦት መግለጹ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ‘መሆን የሚፈልገውን’ ሁሉ እንደሚሆን ለሙሴ ብሎም ለሁላችንም መናገሩ ነበር። የጆሴፍ ብራያንት ሮዘርሃም ትርጉም “መሆን የምሻውን ሁሉ እሆናለሁ” በማለት ይህን ጥቅስ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁር የሆኑ አንድ ሰው የዚህን ሐረግ ትርጉም ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ሁኔታው ወይም የተፈለገው ነገር ምንም ይሁን ምን . . . አምላክ ለተፈለገው ነገር መፍትሔ ‘ሆኖ ይገኛል።’”

9 ይህ ለእስራኤላውያን ምን ዋስትና ይሰጣቸዋል? ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢያጋጥማቸው ወይም ደግሞ የሚገጥማቸው ሁኔታ ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን ይሖዋ እነሱን ከባርነት ነፃ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለማስገባት መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። በእርግጥም ስሙ በአምላክ እንዲታመኑ የሚያደርግ ነበር። ይህ ስም በዛሬው ጊዜም በአምላክ እንድንታመን ሊያደርገን ይችላል። (መዝሙር 9:10) እንዴት?

10, 11. የይሖዋ ስም፣ አምላክ ሁኔታው የሚጠይቅበትን ሁሉ መሆን የሚችል ከሁሉ የላቀ ጥሩ አባት እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው የሚገፋፋን እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

10 ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ልጆችን ማሳደግ ምን ያህል ሁለገብ መሆን እንደሚጠይቅ ያውቃሉ። አንድ ወላጅ በአንድ ቀን ውስጥ አስታማሚ፣ የወጥ ቤት ሠራተኛ፣ አስተማሪ፣ ሥርዓት አስከባሪ እንዲሁም ዳኛ ሆኖ መገኘትና ሌሎችንም ድርሻዎች መወጣት ሊያስፈልገው ይችላል። ብዙዎቹ ወላጆች፣ ሊወጧቸው የሚገቡት በርካታ የሥራ ድርሻዎች ከአቅማቸው በላይ ይሆኑባቸዋል። ሕፃናት በወላጆቻቸው በጣም ስለሚተማመኑ ቢያማቸው ሕመማቸውን የሚያስታግስ ነገር እንደሚያደርጉላቸው፣ ቢጣሉ እንደሚያስታርቋቸው፣ መጫወቻቸው ቢሰበር እንደሚጠግኑላቸውና ለሚያነሱት ማንኛውም ጥያቄ መልስ እንደሚሰጧቸው እርግጠኞች ናቸው። አንዳንድ ወላጆች እንዲህ ያለ እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ ዓይነት ሰዎች እንዳልሆኑ የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ ባለባቸው የአቅም ገደብ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ሲበሳጩ ይታያል። ከእነዚህ ኃላፊነቶች መካከል ብዙዎቹን መወጣት ባለመቻላቸው በጣም ያዝናሉ።

11 ይሖዋም አፍቃሪ የሆነ አባት ነው። ሆኖም ፍጹም የሆኑትን ደንቦቹን ሳይጥስ በምድር ያሉትን ልጆቹን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመንከባከብ ሁሉን መሆን ይችላል። ስለዚህ ይሖዋ የተባለው ስሙ ከሁሉ የላቀ ጥሩ አባት እንደሆነ አድርገን እንድንመለከተው ይገፋፋናል። (ያዕቆብ 1:17) ሙሴም ሆነ ታማኝ የሆኑት እስራኤላውያን በሙሉ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ልክ እንደ ስሙ መሆኑን በተግባር አይተዋል። ይሖዋ በማንም የማይበገር የጦር አበጋዝ፣ የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ አዛዥ፣ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሕግ ሰጪ፣ ፈራጅና ንድፍ አውጪ ሲሆን በመመልከታቸው ታላቅ አክብሮታዊ ፍርሃት አድሮባቸዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ምግብና ውኃ በማቅረብ እንዲሁም ልብሳቸውና ጫማቸው እንዳያልቅ በማድረግ ሌሎች ድርሻዎችንም ተወጥቷል።

12. ፈርዖን ለይሖዋ የነበረው አመለካከት ሙሴ ከነበረው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?

12 በዚህ መንገድ አምላክ የግል ስሙ እንዲታወቅ አድርጓል፣ ከስሙ በስተ ጀርባ ስላለው ማንነቱ አስገራሚ ነገሮችን ገልጿል፤ አልፎ ተርፎም ስለ ራሱ የሚናገረው ነገር እውነት መሆኑን በተግባር አሳይቷል። አምላክ እንድናውቀው እንደሚፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ እኛ ምን ምላሽ እንሰጣለን? ሙሴ አምላክን የማወቅ ፍላጎት ነበረው። ይህ ከፍተኛ ፍላጎት የሙሴን የሕይወት ጎዳና የለወጠው ከመሆኑም በተጨማሪ በሰማይ ካለው አባቱ ጋር በጣም እንዲቀራረብ አድርጎታል። (ዘኁልቁ 12:6-8፤ ዕብራውያን 11:27) የሚያሳዝነው ግን በሙሴ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ፍላጎት አልነበራቸውም። ሙሴ በፈርዖን ፊት የይሖዋን ስም በጠቀሰበት ጊዜ እብሪተኛው የግብፅ ንጉሥ “ይሖዋ ማነው?” ሲል ተናግሯል። (ዘፀአት 5:2) ፈርዖን እንዲህ ሲል የተናገረው ስለ ይሖዋ የማወቅ ፍላጎት ኖሮት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ‘ይሖዋ ደግሞ ማነው’ በማለት በንቀት መናገሩ ነበር። ይህ አመለካከት ዛሬም የተለመደ ሆኗል። ይህም ሰዎች፣ ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ እንደሆነ የሚገልጸውን በጣም አስፈላጊ እውነት እንዳያስተውሉ አድርጓቸዋል።

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ

13, 14. (ሀ) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ የማዕረግ ስሞች የተሰጡት ለምንድን ነው? ከእነዚህስ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ( ገጽ 14 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) “ሉዓላዊው ጌታ” ተብሎ ሊጠራ የሚገባው ይሖዋ ብቻ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ ሁኔታው የሚጠይቀውን ሁሉ መሆን የሚችል አምላክ ነው፤ ከዚህ አንጻር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተለያዩ የማዕረግ ስሞች መጠራቱ የተገባ ነው። ይሁንና እነዚህ የማዕረግ ስሞች የአምላክን የግል ስም ሊተኩ አይችሉም። ከዚህ ይልቅ ስሙ የሚወክለውን ነገር በተመለከተ ያለን ግንዛቤ እንዲሰፋ የሚያደርጉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ሳሙኤል 7:22) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ የሚገኘው ይህ ከፍ ያለ የማዕረግ ስም ይሖዋ ያለውን ቦታ በግልጽ የሚያሳይ ነው። መላውን ጽንፈ ዓለም የመግዛት መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። ይህ የሆነበትን ምክንያት ቀጥሎ ተመልከት።

14 ይሖዋ ብቸኛ ፈጣሪ ነው። ራእይ 4:11 እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ወደ ሕልውና የመጡትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።” ከይሖዋ በቀር እንዲህ ሊባልለት የሚችል ሌላ ማንም የለም። በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና ያመጣው እሱ ነው! ሁሉን የፈጠረ ሉዓላዊ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ክብር፣ ኃይልና ግርማ ሊቀበል እንደሚገባው ምንም አያጠያይቅም።

15. ይሖዋ “የዘላለም ንጉሥ” የተባለው ለምንድን ነው?

15 ሌላው ለይሖዋ ብቻ የተሰጠ የማዕረግ ስም “የዘላለም ንጉሥ” የሚለው ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ራእይ 15:3) ይህ ምን ማለት ነው? ሁኔታው ከእኛ የመረዳት አቅም በላይ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም። መዝሙር 90:2 “ከዘላለም እስከ ዘላለም አንተ አምላክ ነህ” ይላል። ከዚህ እንደምንረዳው ይሖዋ መጀመሪያ የለውም፤ እሱ ያልነበረበት ጊዜ የለም። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት የነበረ በመሆኑ “ከዘመናት በፊት የነበረው” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው! (ዳንኤል 7:9, 13, 22) ይሖዋ ሉዓላዊ ጌታ ሊሆን አይገባውም ብሎ ሊከራከር የሚችል ይኖራል?

16, 17. (ሀ) ይሖዋን ልናየው የማንችለው ለምንድን ነው? ይህስ ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ልናየው ወይም ልንዳስሰው ከምንችለው ከማንኛውም ነገር በላቀ ደረጃ እውን ነው ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?

16 ይሁንና አንዳንዶች እንደ ፈርዖን የይሖዋን ሉዓላዊነት መቀበል ያዳግታቸዋል። ምክንያቱም ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች በአብዛኛው አምነው የሚቀበሉት በዓይናቸው የሚያዩትን ነገር ነው። ሉዓላዊውን ጌታ ደግሞ ልናየው አንችልም። መንፈስ በመሆኑ በሰብዓዊ ዓይን አይታይም። (ዮሐንስ 4:24) ከዚህም በተጨማሪ ሰው ቃል በቃል በአምላክ ፊት ቢቆም በሕይወት ሊቀጥል አይችልም። ይሖዋ ራሱ ሙሴን “ማንም ሰው አይቶኝ በሕይወት መኖር ስለማይችል ፊቴን ማየት አትችልም” ብሎታል።—ዘፀአት 33:20፤ ዮሐንስ 1:18

17 ይህ ሊያስገርመን አይገባም። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሙሴ የአምላክ ወኪል በሆነ አንድ መልአክ አማካኝነት የይሖዋን ክብር በትንሹ ተመልክቷል። ውጤቱስ ምን ነበር? ይህ ከሆነ በኋላ እስራኤላውያን የሙሴን ፊት ማየት እስኪያስፈራቸው ድረስ ፊቱ ለተወሰነ ጊዜ ‘ያንጸባርቅ’ ነበር። (ዘፀአት 33:21-23፤ 34:5-7, 29, 30) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው የሉዓላዊውን ጌታ ክብር ሙሉ በሙሉ ሊያይ የሚችል ሰው የለም! እንዲህ ሲባል ታዲያ ይሖዋ በዓይናችን የምናየውን ወይም በእጃችን የምንዳስሰውን ነገር ያህል እውን ሊሆንልን አይችልም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ለምሳሌ እንደ ነፋስ፣ የሬዲዮ ሞገድና ሐሳብ ያሉ በርካታ ነገሮች ባናያቸውም እንዳሉ አምነን እንቀበላለን። ከዚህም በተጨማሪ በዓይን የሚታዩ ግዑዝ ነገሮች በጊዜ ሂደት ሊያረጁና ሊጠፉ ይችላሉ። (ማቴዎስ 6:19) ይሖዋ ግን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዓመታት ቢያልፉ እንኳ በጊዜ ሂደት የማይለወጥና ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር አምላክ ነው! ከዚህ አንጻር ሲታይ ይሖዋ ከምናየው ወይም ከምንዳስሰው ነገር በላቀ ደረጃ እውን ነው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ፣ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል ወይም የራሱ የሆነ ማንነት የሌለው አንድ ኃይል እንደሆነ አድርገን ልናስብ ይገባል? እስቲ ይህን ጉዳይ እንመርምር።

የራሱ ባሕርያት ያሉት አምላክ

18. ሕዝቅኤል ያየው ራእይ ምንድን ነው? በይሖዋ ዙሪያ የታዩት “ሕያዋን ፍጥረታት” አራት ፊቶችስ ምን ያመለክታሉ?

18 አምላክን ልናየው ባንችልም እንኳ በሰማይ ያለውን ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ የሚጠቁሙ አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አሉ። የሕዝቅኤል መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ለዚህ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። ሕዝቅኤል የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በራእይ ተመልክቷል፤ ያየው ነገር ግዙፍ ሠረገላ ይመስላል። ሕዝቅኤል በተለይ በይሖዋ ዙሪያ ስላሉት ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታት ያየው ነገር በጣም አስደናቂ ነው። (ሕዝቅኤል 1:4-10) እነዚህ “ሕያዋን ፍጥረታት” ከይሖዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን መልካቸው አምላክን በተመለከተ በጣም ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ይሰጠናል። እያንዳንዳቸው አራት ፊት ማለትም የበሬ፣ የአንበሳ፣ የንስርና የሰው ፊት አላቸው። እነዚህም አስደናቂ ለሆነው የይሖዋ ማንነት መሠረት የሆኑትን አራት የይሖዋ ባሕርያት የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው።—ራእይ 4:6-8, 10

19. (ሀ) በበሬ ፊት (ለ) በአንበሳ ፊት (ሐ) በንስር ፊት (መ) በሰው ፊት የተወከለው ባሕርይ ምንድን ነው?

19 በሬ ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው እንስሳ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአብዛኛው ኃይልን ለማመልከት እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል። አንበሳ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ፍትሕን ያመለክታል፤ እውነተኛ ፍትሕ ድፍረት የሚጠይቅ ሲሆን አንበሳም በዚህ ባሕርይው ይታወቃል። ንስር ከፍተኛ የሆነ የማየት ችሎታ ያለው በመሆኑ ከብዙ መቶ ሜትር ርቀት ላይ እንኳ ሆኖ ትናንሽ ነገሮችን ማየት ይችላል። ስለዚህ የንስሩ ፊት፣ የአምላክን አርቆ አስተዋይነት የተንጸባረቀበት ጥበብ በሚገባ ይወክላል። በራእዩ ላይ የታየው የሰው ፊትስ ምን ያመለክታል? ሰው በአምላክ መልክ የተፈጠረ ስለሆነ ከሁሉ የላቀውን የአምላክ ባሕርይ ማለትም ፍቅርን የማንጸባረቅ ችሎታ ተሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 1:26) እነዚህ የይሖዋ ባሕርያት ማለትም ኃይል፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጎላ ብለው የተገለጹ በመሆናቸው የአምላክ ዋነኛ ባሕርያት ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ።

20. የይሖዋ ባሕርይ ተለውጦ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ሊያድርብን ይገባል? እንደዚህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

20 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚሰጠው መግለጫ ከተጻፈ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ያለፉ በመሆኑ በእነዚህ ጊዜያት አምላክ ተለውጦ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ሊያድርብን ይገባል? በፍጹም፤ የአምላክ ማንነት አይለወጥም። “እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም” ብሏል። (ሚልክያስ 3:6) ይሖዋ እንዲሁ በስሜት ተገፋፍቶ ሐሳቡን አይለውጥም፤ ሁኔታዎችን እንደ አመጣጣቸው የማስተናገድ ችሎታው ግን ከሁሉ የላቀ አባት እንደሆነ ያረጋግጣል። ሁኔታው በሚጠይቀው መሠረት እንደ አስፈላጊነቱ የማንነቱን የተለያዩ ገጽታዎች ያሳየናል። ከባሕርያቱ ሁሉ መካከል ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ፍቅር ነው። አምላክ በሚያከናውነው በማንኛውም ነገር ላይ ፍቅሩ ይንጸባረቃል። ኃይሉን፣ ፍትሑንና ጥበቡን የሚያንጸባርቀው በፍቅር ላይ ተመርኩዞ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ይህን ባሕርይ ስለሚያንጸባርቅበት መንገድ አንድ አስደናቂ ነገር ይነግረናል። “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ ፍቅር አለው ወይም አምላክ አፍቃሪ ነው እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ አምላክ ፍቅር ነው ይላል። ፍቅር ማንነቱ ነው፤ በመሆኑም ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው።

“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው!”

21. ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ ምን ስሜት ያድርብናል?

21 አንድ ትንሽ ልጅ አባቱን ለጓደኞቹ እያሳየ ከልብ በመነጨ የደስታና የኩራት ስሜት “አባቴን አያችሁት?” ሲል ሰምተህ ታውቃለህ? የአምላክ አገልጋዮችም ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ እንዲሰማቸው የሚያደርግ በቂ ምክንያት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ የሆኑ ሰዎች “እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው!” ብለው በደስታ ስሜት የሚናገሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 25:8, 9) ስለ ይሖዋ ባሕርያት ይበልጥ ባወቅህ መጠን ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ጥሩ አባት እንደሆነ እየተሰማህ ይሄዳል።

22, 23. መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ስላለው አባታችን ምን መግለጫ ይሰጣል? ወደ እሱ እንድንቀርብ እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን?

22 እንዲህ ያለው አባት፣ ጥብቅ የሆኑ አንዳንድ ሃይማኖተኞችና ፈላስፎች እንደሚያስተምሩት ስሜት አልባ፣ ፍቅር የሌለው ወይም የማይቀረብ አይደለም። ፍቅር የሌለውን አምላክ መቅረብ እንደሚከብደን የታወቀ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን በሰማይ ስላለው አባታችን የሚሰጠው መግለጫ ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። እንዲያውም “ደስተኛው አምላክ” ሲል ይጠራዋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ይሖዋ ሊያዝንም ሊደሰትም የሚችል አምላክ ነው። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ ለእነሱ ደህንነት ሲል ያወጣቸውን ደንቦች በጣሱበት ወቅት ‘ልቡ እንዳዘነ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:6፤ መዝሙር 78:41) ይሁን እንጂ ጥበበኛ በመሆን ቃሉ የሚለውን ስናደርግ ‘ልቡን ደስ እናሰኘዋለን።’—ምሳሌ 27:11

23 አባታችን ወደ እሱ እንድንቀርብ ይፈልጋል። ቃሉ፣ አምላክን ‘አጥብቀን በመሻት እንድናገኘው’ የሚያበረታታን ከመሆኑም በላይ “ከእያንዳንዳችን የራቀ” አለመሆኑን ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) ይሁንና ተራ የሆኑ ሰዎች የጽንፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ እንዴት ሊቀርቡት ይችላሉ?