ምዕራፍ 17
‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
1, 2. ሰባተኛውን ቀን በተመለከተ የይሖዋ ዓላማ ምን ነበር? በዚህ ቀን መጀመሪያ ላይ የአምላክን ጥበብ የሚፈትን ምን ሁኔታ ተከሰተ?
በስድስተኛው የፍጥረት ቀን ከተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ የላቀውን ቦታ የያዘው የሰው ልጅ ታላቅ አዘቅት ውስጥ ወደቀ። ይሖዋ የሰውን ልጅ ጨምሮ “የሠራውን እያንዳንዱን ነገር” ከተመለከተ በኋላ “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) ይሁን እንጂ በሰባተኛው ቀን መጀመሪያ ላይ አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጋር በማበር በአምላክ ላይ ዓመፁ። በዚህም ሳቢያ ለኃጢአት፣ ለአለፍጽምና እና ለሞት ተዳረጉ።
2 ይሖዋ ሰባተኛውን ቀን በተመለከተ የነበረው ዓላማ ሁሉ የከሸፈ ይመስል ነበር። ይህ ቀን ቀደም ሲል እንደነበሩት ስድስት ቀናት ሁሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝማኔ አለው። ይሖዋ ይህን ቀን ቀድሶት የነበረ ሲሆን በዚህ ቀን ማብቂያ ላይ መላዋ ምድር ገነት እንድትሆንና ፍጹም በሆኑ የሰው ልጆች እንድትሞላ ዓላማ ነበረው። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:3) ሆኖም የሰው ልጅ በአምላክ ላይ ማመፁ ብዙ መዘዝ አስከትሏል። ታዲያ ይህ ዓላማ ዳር ሊደርስ የሚችለው እንዴት ነው? አምላክ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? ይህ ሁኔታ የይሖዋን ጥበብ በከፍተኛ ደረጃ የሚፈትን ነበር ማለት ይቻላል።
3, 4. (ሀ) ይሖዋ በኤደን የተፈጸመውን ዓመፅ በተመለከተ የወሰደው እርምጃ ድንቅ የሆነውን ጥበቡን የሚያሳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ጥበብ ስንመረምር የትኛውን ሐቅ በትሕትና አምነን ልንቀበል ይገባል?
3 ይሖዋ ወዲያው እርምጃ ወሰደ። በኤደን ባመፁት ላይ የፍርድ ብያኔ ያስተላለፈ ከመሆኑም በላይ በእነሱ ዓመፅ ሳቢያ የተፈጠሩትን ችግሮች ለማስወገድ ዓላማ እንዳለው የሚጠቁም ተስፋ ፈንጥቋል። (ዘፍጥረት 3:15) አርቆ ማስተዋል የተንጸባረቀበት ይህ የይሖዋ ዓላማ በኤደን ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለብዙ ሺህ ዓመታት የዘለቀና የወደፊቱንም ጊዜ የሚያካትት ነው። ይህ ዓላማ የተወሳሰበ ባይሆንም እንኳ ከፍተኛ ጥልቀትና ትርጉም ያለው በመሆኑ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ይህን ዓላማ በመመርመርና በማጥናት በእጅጉ ሊጠቀም ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ዓላማ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። ክፋት፣ ኃጢአትና ሞት ይወገዳሉ። ታማኝ የሰው ልጆች ፍጹም ይሆናሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ሰባተኛው ቀን ከማብቃቱ በፊት ነው። በመሆኑም ዓመፁ ያስከተለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ምድርንና የሰው ልጆችን በተመለከተ ያለው ዓላማ አስቀድሞ ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ፍጻሜውን ያገኛል!
4 ይህ ጥበብ ለአምላክ ጥልቅ አክብሮት እንዲያድርብን አያደርግም? ሐዋርያው ጳውሎስ በአድናቆት ስሜት ተገፋፍቶ ‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’ ሲል ጽፏል። (ሮም 11:33) የዚህን መለኮታዊ ባሕርይ የተለያዩ ገጽታዎች በምንመረምርበት ጊዜ፣ ማለቂያ ስለሌለው የይሖዋ ጥበብ ልናውቅ የምንችለው ጥቂቱን ብቻ እንደሆነ በትሕትና አምነን መቀበል አለብን። (ኢዮብ 26:14) በመጀመሪያ እስቲ የዚህን ድንቅ ባሕርይ ትርጉም እንመርምር።
መለኮታዊ ጥበብ ምንድን ነው?
5, 6. በእውቀትና በጥበብ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? የይሖዋ እውቀትስ ምን ያህል ሰፊ ነው?
5 ጥበብ ከእውቀት የተለየ ነው። ኮምፒውተሮች ብዙ እውቀትና መረጃ መያዝ ይችላሉ፤ ሆኖም እነዚህን መሣሪያዎች ጥበበኛ ብሎ መጥራት ይከብዳል። ይሁንና እውቀትና ጥበብ የተያያዙ ነገሮች ናቸው። (ምሳሌ 10:14) ለምሳሌ ያህል፣ አንድን በሽታ በተመለከተ ጥበብ ያለበት ምክር ማግኘት ብትፈልግ ስለ ሕክምና ምንም እውቀት የሌለውን ሰው ታማክራለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! ስለዚህ አንድ ሰው እውነተኛ ጥበብ ሊኖረው የሚችለው ትክክለኛ እውቀት ሲኖረው ነው።
6 ይሖዋ ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የማይችል እውቀት አለው። “የዘላለም ንጉሥ” እንደመሆኑ መጠን መጀመሪያ የሌለውና ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት የኖረው እሱ ብቻ ነው። (ራእይ 15:3) በመሆኑም ይሖዋ ሁሉን ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከአምላክ እይታ የተሰወረ አንድም ፍጥረት የለም፤ ይልቁንም ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው” በማለት ይገልጻል። (ዕብራውያን 4:13፤ ምሳሌ 15:3) ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የሠራቸውን ነገሮች ጠንቅቆ ያውቃል። የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ያደረጉትን ሁሉ ተመልክቷል። የሁሉንም ሰው ልብ የሚመረምር ሲሆን ከእሱ የተሰወረ ምንም ነገር የለም። (1 ዜና መዋዕል 28:9) የፈለግነውን የመምረጥ ነፃነት የሰጠን በመሆኑ ጥበብ ያለበት ምርጫ ስናደርግ ሲያይ ይደሰታል። “ጸሎት ሰሚ” አምላክ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ጊዜ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጸሎቶችን ማስተናገድ ይችላል! (መዝሙር 65:2) በተጨማሪም ይሖዋ ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ እንዳለው ግልጽ ነው።
7, 8. ይሖዋ ማስተዋል፣ ጥልቅ ግንዛቤና ጥበብ አለው የምንለው ለምንድን ነው?
7 ይሖዋ እውቀት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ እውነታዎች እርስ በርስ እንዴት እንደሚዛመዱና አንድ ላይ ሲቀናጁ ምን መልክ እንደሚኖራቸው የመረዳት ችሎታ አለው። ጥሩውንና መጥፎውን፣ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን የማመዛዘንና ለይቶ የማወቅ ችሎታ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ውጫዊ ገጽታን ከመመልከት አልፎ ልብን ይመረምራል። (1 ሳሙኤል 16:7) በመሆኑም ይሖዋ እውቀት ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ግንዛቤና የማስተዋል ችሎታ አለው። ይሁን እንጂ ጥበብ ከዚህ ሁሉ የላቀ ነው።
8 ጥበብ፣ እውቀትን፣ ግንዛቤንና ማስተዋልን በሥራ ላይ የማዋል ችሎታ ነው። እንዲያውም “ጥበብ” ተብለው የተተረጎሙት በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኙት አንዳንድ ቃላት በቀጥታ ሲተረጎሙ “የተፈለገውን ውጤት የሚያስገኝ ዘዴ” ወይም “ተግባራዊ ጥበብ” የሚል ፍቺ አላቸው። ስለዚህ የይሖዋ ጥበብ እንዲሁ ፅንሰ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊና የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ነው። ይሖዋ ጥልቅ የሆነውን እውቀቱንና ማስተዋሉን በመጠቀም ምንጊዜም ትክክለኛውን ውሳኔ የሚያደርግ ሲሆን ውሳኔውም ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንዲፈጸም ያደርጋል። እውነተኛ ጥበብ ማለት ይህ ነው! ይሖዋ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” የሚለው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ እውነተኛ መሆኑን የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። (ማቴዎስ 11:19) ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያከናወናቸው ሥራዎች ጥበቡን የሚያሳዩ ጥሩ ማስረጃዎች ናቸው።
የመለኮታዊ ጥበብ ማስረጃዎች
9, 10. (ሀ) ይሖዋ ምን ዓይነት ጥበብ አለው? ይህን ጥበቡን ያሳየውስ እንዴት ነው? (ለ) የሴል አሠራር የይሖዋን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 ውብ የሆኑ ቁሳቁሶችን የሚሠራ አንድ ባለሙያ ያለውን የፈጠራ ችሎታ አድንቀህ ታውቃለህ? ይህ አስደናቂ የሆነ ጥበብ ነው። (ዘፀአት 31:1-3) የዚህ ዓይነቱ አስደናቂ ጥበብ ምንጭና ባለቤት ይሖዋ ነው። ንጉሥ ዳዊት “በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ስለተፈጠርኩ አወድስሃለሁ። ሥራዎችህ አስደናቂ ናቸው፤ ይህን በሚገባ አውቃለሁ” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል። (መዝሙር 139:14) በእርግጥም ስለ ሰው አካል ይበልጥ ስናውቅ በይሖዋ ጥበብ እጅግ እንደመማለን።
10 ለምሳሌ ያህል፣ ሕይወትህ ሀ ብሎ የጀመረው የአባትህ የወንድ ዘር በእናትህ ማህፀን ውስጥ ከነበረ እንቁላል ጋር ተገናኝቶ አንድ ነጠላ ሴል በተፈጠረበት ቅጽበት ነው። ወዲያው ይህ ሴል መባዛት ይጀምራል። አንድ ሙሉ ሰው 100 ትሪሊዮን ገደማ ሴሎች አሉት። እነዚህ ሴሎች ረቂቅ ናቸው። አማካይ የሆነ መጠን ያላቸው 10,000 ሴሎች አንድ ላይ ቢሆኑ ከአንዲት ስፒል አናት አይበልጡም። ሆኖም እያንዳንዱ ሴል ከምንገምተው በላይ ውስብስብ ነው። ከማንኛውም ሰው ሠራሽ ማሽን ወይም ፋብሪካ ይበልጥ የረቀቀ ነው። ሳይንቲስቶች እንደሚሉት አንድ ሴል በግንብ ከታጠረ ከተማ ጋር ይመሳሰላል፤ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው በሮች፣ የመጓጓዣ አገልግሎት፣ የመገናኛ አውታሮች፣ የኃይል ማመንጫ ተቋማት፣ ፋብሪካዎች፣ የቆሻሻ ማስወገጃ ዘዴ፣ ተረፈ ምርትን ወደ ጠቃሚ ምርት የሚቀይሩ ተቋማት፣ የመከላከያ ኃይልና ማዕከላዊ መስተዳድር አሉት። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሴል በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከራሱ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ ሌላ ሴል ሊያስገኝ ይችላል።
11, 12. (ሀ) በፅንስ ውስጥ ያሉ ሴሎች የተለያየ የሥራ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያደርገው ምንድን ነው? ይህስ በመዝሙር 139:16 ላይ ከሚገኘው አባባል ጋር የሚስማማው እንዴት ነው? (ለ) የሰው አንጎል “ግሩምና ድንቅ” ሆነን እንደተፈጠርን የሚያሳየው እንዴት ነው?
11 እርግጥ ሁሉም ሴሎች አንድ ዓይነት ናቸው ማለት አይደለም። የአንድ ፅንስ ሴሎች እየተባዙ ሲሄዱ የተለያየ የሥራ ድርሻ ይኖራቸዋል። አንዳንዶቹ የነርቭ ሌሎቹ ደግሞ የአጥንት፣ የጡንቻ፣ የደም ወይም የዓይን ሴሎች ይሆናሉ። ይህን የሥራ ክፍፍል የሚያደርጉት ዲ ኤን ኤ በተባለው ጀነቲካዊ ንድፍ ውስጥ በተቀመጠላቸው ፕሮግራም በመመራት ነው። ዳዊት “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ” ሲል በመንፈስ ተነሳስቶ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው።—መዝሙር 139:16
12 አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች በጣም ውስብስብ ናቸው። አንጎልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንዳንድ ሳይንቲስቶች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እስካሁን በምርምር ከተደረሰባቸው ነገሮች ሁሉ የአንጎልን ያህል ውስብስብ የሆነ ነገር የለም ይላሉ። አንጎል 100 ቢሊዮን ገደማ የነርቭ ሴሎች አሉት፤ ይህም እኛ በምንገኝበት ጋላክሲ ውስጥ ከሚገኙት ከዋክብት ብዛት ጋር የሚመጣጠን ነው። እያንዳንዱ የነርቭ ሴል ከሌሎች ሴሎች ጋር የሚገናኝባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አውታሮች አሉ። ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የሰው አንጎል በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አብያተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን መረጃ በሙሉ ምናልባትም ከዚያ በጣም የበለጠ መረጃ መያዝ ይችላል። ሳይንቲስቶች ይህን “ድንቅ” የአካል ክፍል ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲያጠኑ የኖሩ ቢሆንም የአንጎልን አሠራር ሙሉ በሙሉ መረዳት አዳጋች እንደሚሆን ተናግረዋል።
13, 14. (ሀ) ጉንዳኖችና ሌሎች ፍጥረታት “በደመ ነፍስ ጥበበኞች” እንደሆኑ የሚያሳየው ምንድን ነው? ይህስ ስለ ፈጣሪያቸው ምን ያስተምረናል? (ለ) እንደ ሸረሪት ድር ያሉ ነገሮች “በጥበብ” ተሠርተዋል የምንለው ለምንድን ነው?
13 ሆኖም የይሖዋ የፈጠራ ጥበብ የታየው በሰው ልጆች ላይ ብቻ አይደለም። መዝሙር 104:24 “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! ሁሉንም በጥበብ ሠራህ። ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች” ይላል። የይሖዋ ጥበብ በዙሪያችን ባሉ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል ጉንዳኖች “በደመ ነፍስ ጥበበኞች” ናቸው። (ምሳሌ 30:24) ጉንዳኖች በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ የተደራጁ ናቸው። በቡድን ተደራጅተው የሚኖሩ አንዳንድ የጉንዳን ዝርያዎች፣ መጠለያ ሠርተው ጥቃቅን ነፍሳትን በማርባት ከእነሱ የሚያገኙትን ንጥረ ነገር ይመገባሉ። ሌሎች ጉንዳኖች ደግሞ ፈንገስ በማልማት የግብርና ሥራ ያከናውናሉ። ሌሎች በርካታ ፍጥረታትም በደመ ነፍስ ባላቸው ጥበብ በመጠቀም አስደናቂ ነገሮችን ያከናውናሉ። አንዲት ዝንብ በአየር ላይ የምታሳየውን ትርዒት በጣም ዘመናዊ የሚባሉት አውሮፕላኖች እንኳ ሊያሳዩ አይችሉም። አንዳንድ ወፎች በከዋክብት፣ በምድር መግነጢሳዊ መስክ ወይም በውስጣቸው ባለ ተፈጥሯዊ ካርታ በመመራት ወቅቶችን ጠብቀው ከቦታ ወደ ቦታ ይፈልሳሉ። የሥነ ሕይወት ባለሙያዎች በእነዚህ ፍጥረታት ውስጥ የተነደፈውን የረቀቀ ፕሮግራም ለብዙ ዓመታት ሲያጠኑ ኖረዋል። በእርግጥም ይህን ፕሮግራም የነደፈው ፈጣሪ እጅግ ጥበበኛ ነው!
14 ሳይንቲስቶች ከይሖዋ የፈጠራ ጥበብ ብዙ ትምህርት ቀስመዋል። ሌላው ቀርቶ ባዮሚሜቲክስ የሚባል የምሕንድስና ዘርፍ ያለ ሲሆን በዚህ ሙያ የተሰማሩ ሰዎች የተፈጥሮ ንድፎችን አስመስለው ለመሥራት ይሞክራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሸረሪት ድር ስትመለከት ውበቱ ያስገርምህ ይሆናል። አንድን መሐንዲስ ግን ይበልጥ የሚያስገርመው በሸረሪት ድር ላይ የተንጸባረቀው ንድፍ ሊሆን ይችላል። በቀላሉ የሚበጠሱ የሚመስሉ አንዳንድ የሸረሪት ድሮች ተመጣጣኝ መጠን ካለው ሽቦ እንዲሁም ጥይት የማይበሳው ልብስ ለመሥራት ከሚያገለግል ክር የበለጠ ጥንካሬ አላቸው። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? የሸረሪት ድር ተገምዶ የዓሣ ማጥመጃ መረብ የሚያህል መጠን እንዲኖረው ቢደረግ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ እየበረረ ያለን የመጓጓዣ አውሮፕላን ሊያቆም ይችላል! በእርግጥም ይሖዋ ሁሉን “በጥበብ” ሠርቷል።
በሰማይ ባሉ ፍጥረታት ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ
15, 16. (ሀ) የሰማይ አካላት ስለ ይሖዋ ጥበብ ምን ያስገነዝቡናል? (ለ) ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መላእክት በበላይነት ማስተዳደር መቻሉ ስለ ጥበቡ ምን ይጠቁመናል?
15 በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ የፍጥረት ሥራዎች የይሖዋን ጥበብ ያንጸባርቃሉ። በምዕራፍ 5 ላይ በተወሰነ ደረጃ የተመለከትናቸው የሰማይ አካላት እንዲሁ በዘፈቀደ የተቀመጡ አይደሉም። ከዋክብት በጋላክሲዎች የተደራጁ ናቸው። እነዚህ ጋላክሲዎች በአንድነት በመከማቸት ክላስተር የተባሉ የከዋክብት ረጨቶች ስብስብ ፈጥረዋል። እነዚህ ክላስተሮች ደግሞ አንድ ላይ በመሆን ሱፐርክላስተር የሚባሉ ይበልጥ ግዙፍ የሆኑ የከዋክብት ክምችቶችን ፈጥረዋል። ይህም ይሖዋ ያወጣቸው ‘ሰማያት የሚመሩባቸው ሕጎች’ ከፍተኛ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው እንደሆኑ ያሳያሉ። (ኢዮብ 38:33) ይሖዋ የሰማይ አካላትን “ሠራዊት” ሲል መጥራቱ ምንም አያስደንቅም! (ኢሳይያስ 40:26) ይሁን እንጂ የይሖዋ ጥበብ በላቀ ደረጃ የተንጸባረቀበት ሌላም ሠራዊት አለ።
16 በምዕራፍ 4 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈ ትልቅ ሠራዊት ዋና አዛዥ ስለሆነ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚል የማዕረግ ስም አለው። ይህም ይሖዋ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የይሖዋ ጥበብ የታየው እንዴት ነው? ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ምንጊዜም ሥራ ላይ እንደሆኑ አስታውስ። (ዮሐንስ 5:17) የልዑሉ አምላክ አገልጋዮች የሆኑት መላእክትም ምንጊዜም በሥራ የተጠመዱ እንደሆኑ መገመት ይቻላል። በተጨማሪም እነዚህ መላእክት ከሰው ልጆች የላቀ የማሰብ ችሎታና ኃይል እንዳላቸው አስታውስ። (ዕብራውያን 1:7፤ 2:7) ሆኖም ይሖዋ እነዚህ ሁሉ መላእክት በደስታ ‘ቃሉን በመፈጸምና’ ‘ፈቃዱን በማድረግ’ በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት በሥራ ተጠምደው እንዲኖሩ አድርጓል። (መዝሙር 103:20, 21) አምላክ እነዚህን ሁሉ መላእክት ማስተዳደር መቻሉ ምን ያህል ታላቅ ጥበብ እንዳለው የሚያሳይ ነው!
ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” ነው
17, 18. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” ነው የሚለው ለምንድን ነው? ጥበቡ እንድንደመም ሊያደርገን የሚገባውስ ለምንድን ነው?
17 ከዚህ ሁሉ ማስረጃ አንጻር ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ጥበብ ከሁሉ የላቀ እንደሆነ መናገሩ ሊያስገርመን ይገባል? ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ “ብቻ ጥበበኛ” እንደሆነ ይገልጻል። (ሮም 16:27) ፍጹም የተሟላ ጥበብ ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። የእውነተኛ ጥበብ ሁሉ ምንጭ እሱ ነው። (ምሳሌ 2:6) ምንም እንኳ ኢየሱስ ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ጥበብ ያለው ቢሆንም በራሱ ጥበብ ከመመካት ይልቅ የአባቱን መመሪያ ለመከተል የመረጠው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 12:48-50
18 ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋ ጥበብ አቻ የማይገኝለት መሆኑን ሲገልጽ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!” (ሮም 11:33) ጳውሎስ “እንዴት” የሚለውን ቃል በመጠቀም ለይሖዋ ጥበብ ያለውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጿል። “ጥልቅ” የሚለውን ቃል መጠቀሙም በአእምሯችን የሚፈጥረው ምስል አለ። ስለ ይሖዋ ጥበብ ስናሰላስል መጨረሻው የማይታይን ገደል ቁልቁል የመመልከት ያህል ጥልቅና ሰፊ ሊሆንብን ይችላል። በዝርዝር ልንገልጸው ቀርቶ ልንገምተው እንኳ አንችልም። (መዝሙር 92:5) ይህ ራሳችንን በትሕትና ዝቅ እንድናደርግ አይገፋፋንም?
19, 20. (ሀ) ንስር ለመለኮታዊ ጥበብ ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን አሻግሮ የመመልከት ችሎታ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
19 በተጨማሪም ወደፊት የሚሆነውን ማወቅ የሚችለው ይሖዋ ብቻ በመሆኑ እሱ “ብቻ ጥበበኛ” መባሉ ተገቢ ነው። ይሖዋ መለኮታዊ ጥበብን ለማመልከት፣ ከርቀት የማየት ችሎታ ያለውን ንስርን እንደ ምሳሌ እንደተጠቀመበት አስታውስ። ጎልደን ኢግል የተባለው የንስር ዝርያ 5 ኪሎ ግራም ገደማ ብቻ የሚመዝን ቢሆንም ዓይኑ ከሰው ዓይን ይበልጣል። ንስር ከፍተኛ የማየት ችሎታ ያለው በመሆኑ ከብዙ መቶ ሜትሮች ምናልባትም ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ ሆኖ ትናንሽ እንስሳትን ማየት ይችላል! በአንድ ወቅት ይሖዋ ራሱ ስለ ንስር ሲናገር “ዓይኖቹም እጅግ ሩቅ ወደሆነ ቦታ ይመለከታሉ” ብሏል። (ኢዮብ 39:29) በተመሳሳይም ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ ‘ከሩቅ መመልከት’ ይችላል!
20 ይህ እውነት መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ይዟል፤ ይኸውም ያልተፈጸሙ የወደፊት ክስተቶችን እንደ ታሪክ አስቀድሞ አስቀምጧቸዋል። የተለያዩ ውጊያዎችን ማን ድል እንደሚያደርግ፣ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን አነሳስና አወዳደቅ አልፎ ተርፎም የአንዳንድ የጦር አዛዦችን የውጊያ ስልት ሳይቀር የሚገልጹ ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ የተነገሩት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድሞ ነው።—ኢሳይያስ 44:25 እስከ 45:4፤ ዳንኤል 8:2-8, 20-22
21, 22. (ሀ) ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ የምታደርጋቸውን ምርጫዎች ሁሉ አስቀድሞ ያውቃል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) የይሖዋ ጥበብ ፍቅር ወይም ርኅራኄ የጎደለው አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
21 እንዲህ ሲባል ግን አምላክ በሕይወትህ ውስጥ የምታደርጋቸውን ምርጫዎች አስቀድሞ ያውቃል ማለት ነው? የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች ለዚህ ጥያቄ ‘አዎን’ የሚል መልስ ይሰጣሉ። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ‘አምላክ የወደፊቱን የማወቅ ችሎታውን መቆጣጠር አይችልም’ የሚል አንድምታ ያለው በመሆኑ ሰዎች ለይሖዋ ጥበብ ዝቅ ያለ ግምት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ለመዝፈን የሚያስችል ጥሩ ድምፅ ቢኖርህ ይህ ችሎታህ ከቁጥጥርህ ውጭ ሆኖ ሁልጊዜ ትዘፍናለህ ማለት ነው? ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነው! በተመሳሳይም ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ የማወቅ ችሎታ ቢኖረውም ሁልጊዜ ይጠቀምበታል ማለት አይደለም። እንዲህ ቢያደርግ ራሱ የሰጠንን የመምረጥ ነፃነት መጋፋት ይሆንበታል፤ ይሖዋ ይህንን ውድ ስጦታ በፍጹም አይወስድብንም።—ዘዳግም 30:19, 20
22 ከሁሉ የከፋው ደግሞ የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው አስተሳሰብ፣ የይሖዋ ጥበብ ፍቅር፣ ርኅራኄ ወይም አዘኔታ የጎደለው ነው የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑ ነው። ይህ ግን ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ጥበበኛ ልብ አለው” ይላል። (ኢዮብ 9:4) ይህ ሲባል ግን ይሖዋ ቃል በቃል ልብ አለው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ይህን ቃል እንደ ፍቅር ያሉ ውስጣዊ ስሜቶችንና ዝንባሌዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። ስለዚህ የይሖዋ ጥበብ እንደ ሌሎቹ ባሕርያቱ ሁሉ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው።—1 ዮሐንስ 4:8
23. የይሖዋ ጥበብ እጅግ የላቀ መሆኑ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
23 የይሖዋ ጥበብ ሙሉ እምነት የሚጣልበት ነው። ከእኛ ጥበብ እጅግ የላቀ በመሆኑ የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ፍቅራዊ ምክር ይሰጠናል፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) ፍጹም ጥበብ ወዳለው አምላካችን ይበልጥ መቅረብ እንድንችል እስቲ የይሖዋን ጥበብ ጠለቅ ብለን እንመርምር።