በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 18

‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ

‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ

1, 2. ይሖዋ የጻፈልን “ደብዳቤ” ምንድን ነው? ይህን ያደረገውስ ለምንድን ነው?

 ሩቅ ካለ አንድ ወዳጅህ ወይም ዘመድህ ደብዳቤ ደርሶህ ያውቃል? ከምንወደው ሰው የተላከ ደብዳቤ ማግኘት በሕይወታችን ውስጥ በጣም ከሚያስደስቱን ነገሮች አንዱ ነው። ስለ ጤንነቱ፣ ስላጋጠሙት ሁኔታዎችና ስላቀዳቸው ነገሮች ስንሰማ እንደሰታለን። የምንወደው ሰው ምንም እንኳ በአካል ከእኛ የራቀ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱ የደብዳቤ ልውውጥ እንደሚያቀራርበን የታወቀ ነው።

2 ታዲያ ከምንወደው አምላክ የተላከ መልእክት ከመቀበል ይበልጥ ሊያስደስተን የሚችል ነገር ይኖራል? ይሖዋ “ደብዳቤ” ጽፎልናል ማለት ይቻላል፤ ይህ ደብዳቤ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ስለ ማንነቱ፣ ስላከናወናቸው ነገሮች፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ሌሎች ነገሮችም ገልጾልናል። ይሖዋ ቃሉን የሰጠን ወደ እሱ እንድንቀርብ ስለሚፈልግ ነው። ፍጹም ጥበበኛ የሆነው አምላክ ከሁሉ የተሻለውን መንገድ በመጠቀም ሐሳቡን ገልጾልናል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት መንገድም ሆነ የያዘው መልእክት የአምላክን ወደር የለሽ ጥበብ የሚያሳይ ነው።

ቃሉን በጽሑፍ ማስፈር ለምን አስፈለገ?

3. ይሖዋ ሕጉን ለሙሴ ያስተላለፈው በምን መንገድ ነው?

3 አንዳንዶች ‘ይሖዋ ለሰዎች ሐሳቡን ለመግለጽ ከዚህ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ሌላ መንገድ መጠቀም፣ ለምሳሌ በቀጥታ ከሰማይ ሆኖ መናገር አይችልም ነበር?’ የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ በመላእክት አማካኝነት ከሰማይ ሆኖ የተናገረባቸው ጊዜያት አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ለእስራኤላውያን ሕጉን የሰጠው በዚህ መንገድ ነበር። (ገላትያ 3:19) ከሰማይ የተሰማው ድምፅ በጣም ያስፈራ ስለነበር እስራኤላውያን ይሖዋ በቀጥታ ከሚያነጋግራቸው ይልቅ በሙሴ አማካኝነት ቢያነጋግራቸው እንደሚመርጡ ገልጸዋል። (ዘፀአት 20:18-20) በመሆኑም ይሖዋ ከ600 በላይ ደንቦችን የያዘውን ሕግ ለሙሴ በቃል ነግሮታል።

4. የአምላክ ሕግ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ በቃል ቢተላለፍ ኖሮ ምን ችግር ሊፈጠር እንደሚችል አስረዳ።

4 ይሁንና ሕጉ በጽሑፍ ባይሰፍር ኖሮ ምን ሁኔታ ይፈጠር ነበር? ሙሴ እያንዳንዱን ዝርዝር ደንብ በማስታወስ ምንም ሳያጓድል ለሕዝቡ ማስተላለፍ ይችል ነበር? ሕዝቡስ ሙሴ የነገራቸውን እያንዳንዱን ነገር አስታውሰው ከእነሱ በኋላ ለሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ማስተላለፍ ይችሉ ነበር? ይህ የአምላክን ሕግ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል አስተማማኝ መንገድ አይደለም። በረድፍ የተቀመጡ በርካታ ሰዎች አንድን ታሪክ አንዳቸው ለሌላው እየተናገሩ ታሪኩን እንዲያስተላልፉ ብታደርግ በመጨረሻ ላይ ምን ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ገምት። በረድፉ መጨረሻ ላይ ያለው ሰው ምን እንደሰማ ብትጠይቀው የታሪኩ ይዘት በእጅጉ ተለውጦ ታገኘዋለህ። የአምላክ ሕግ ግን በዚህ መንገድ እንዲተላለፍ ስላልተደረገ እንዲህ ዓይነት ችግር አላጋጠመውም።

5, 6. ይሖዋ ሙሴን ምን እንዲያደርግ አዝዞታል? የይሖዋ ቃል በጽሑፍ በመስፈሩ በእጅጉ ተጠቅመናል የምንለው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ ቃሉ በጽሑፍ እንዲሰፍር ማድረጉ ጥበብ ነበር። ሙሴን “ከአንተም ሆነ ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የምገባው በእነዚህ ቃላት መሠረት ስለሆነ እነዚህን ቃላት ጻፍ” ሲል አዝዞታል። (ዘፀአት 34:27) በመሆኑም በ1513 ዓ.ዓ. የአምላክን ቃል በጽሑፍ ማስፈር ተጀመረ። በቀጣዮቹ 1,610 ዓመታት ይሖዋ ወደ 40 ለሚጠጉ ሰዎች “በተለያዩ ጊዜያትና በብዙ መንገዶች” ቃሉን በመናገር በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ አድርጓል። (ዕብራውያን 1:1) በእነዚህ ጊዜያት ታማኝና ትጉህ የሆኑ ገልባጮች ቅዱሳን መጻሕፍት እንዳሉ ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ በጥንቃቄ ይገለብጡ ነበር።—ዕዝራ 7:6፤ መዝሙር 45:1

6 ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት ሐሳቡን ለእኛ በመግለጡ በእጅጉ ተጠቅመናል። ከምትወደው ሰው በጣም የሚያጽናና ደብዳቤ ደርሶህ ያውቃል? ሌላ ጊዜም ደግመህ ደጋግመህ ልታነበው ስለምትፈልግ ደብዳቤውን ታስቀምጠዋለህ። የይሖዋ “ደብዳቤም” እንዲሁ ነው። ይሖዋ ቃሉን በጽሑፍ ስላሰፈረልን አዘውትረን ማንበብና በያዘው መልእክት ላይ ማሰላሰል እንችላለን። (መዝሙር 1:2) መጽናኛ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ “ከቅዱሳን መጻሕፍት . . . መጽናኛ” ልናገኝ እንችላለን።—ሮም 15:4

በሰዎች ማስጻፍ ለምን አስፈለገ?

7. ይሖዋ ቃሉን ለማስጻፍ ሰዎችን በመጠቀም ጥበቡን ያሳየው እንዴት ነው?

7 ይሖዋ ቃሉን ለማስጻፍ ሰዎችን በመጠቀም ጥበቡን አሳይቷል። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ መላእክትን ቢጠቀም ኖሮ አሁን ያለው ዓይነት ጣዕም ይኖረው ነበር? እርግጥ ነው፣ መላእክት ይሖዋን እነሱ ካላቸው የላቀ ግንዛቤ አንጻር ሊገልጹት፣ ለእሱ ያላቸውን ታማኝነትና ፍቅር በሚጽፉት መልእክት ሊያንጸባርቁ እንዲሁም ታማኝ ስለሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ጥሩ የሆነ ዘገባ ሊያቀርቡ ይችሉ ነበር። ሆኖም ከእኛ እጅግ የላቀ እውቀት፣ ተሞክሮና ኃይል ያላቸው ፍጹም መንፈሳዊ ፍጥረታት ያሰፈሩትን ሐሳብ መረዳት እንችል ነበር?—ዕብራውያን 2:6, 7

8. ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ እንዲጠቀሙ ነፃነት የሰጣቸው በምን መንገድ ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

8 ይሖዋ ሰዎችን በመጠቀም ቃሉን ለእኛ ተስማሚ በሆነ መንገድ አስጽፎልናል፤ ይህ ዘገባ “በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈ ቢሆንም ሰብዓዊ ስሜት የተንጸባረቀበት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የራሳቸውን የማመዛዘን ችሎታ በመጠቀም “ደስ የሚያሰኙ ቃላትን” መርጠው “የእውነትን ቃል በትክክል” እንዲጽፉ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። (መክብብ 12:10, 11) መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ የአጻጻፍ ስልት ሊኖረው የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፤ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጸሐፊውን አስተዳደግና ሙያ እንዲሁም ባሕርይ ያንጸባርቃል። a ሆኖም እነዚህ ሰዎች “ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው” ተናግረዋል። (2 ጴጥሮስ 1:21) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ “የአምላክ ቃል” ነው።—1 ተሰሎንቄ 2:13

“ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው”

9, 10. መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ልባችንን የሚነካና ስሜታችንን የሚማርክ እንዲሆን ያስቻለው ለምንድን ነው?

9 መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መጻፉ ልባችንን የሚነካና ስሜታችንን የሚማርክ እንዲሆን አድርጎታል። ጸሐፊዎቹ የእኛው ዓይነት ስሜት ያላቸው ነበሩ። ፍጽምና የሌላቸው እንደመሆናቸው መጠን እንደ እኛው የተለያዩ ፈተናዎችንና ተጽዕኖዎችን መቋቋም አስፈልጓቸዋል። እንዲያውም የአምላክ መንፈስ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ስለ ራሳቸው ስሜትና ከገጠሟቸው ችግሮች ጋር ስላደረጉት ትግል እንዲጽፉ አነሳስቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) በመሆኑም መላእክት ቢሆኑ ኖሮ ሊገልጹት የማይችሉትን ሰብዓዊ ስሜት ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት ጽፈዋል።

10 የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዳዊት ከባድ ኃጢአቶችን ከፈጸመ በኋላ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን የሚገልጽ አንድ መዝሙር በማቀናበር አምላክ ይቅር እንዲለው ተማጽኗል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦- “[ከኃጢአቴ] አንጻኝ። መተላለፌን በሚገባ አውቃለሁና፤ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነው። እነሆ፣ በደለኛ ሆኜ ተወለድኩ፤ እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ። ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድ። አምላክን የሚያስደስተው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም።” (መዝሙር 51:2, 3, 5, 11, 17) ይህን ስታነብ ጸሐፊው ምን ያህል ልቡ በሐዘን እንደተደቆሰ አልተሰማህም? ፍጽምና ከጎደለው ሰው ሌላ እንዲህ ያለውን ጥልቅ ስሜት ማን ሊገልጸው ይችላል?

ስለ ሰዎች የሚናገረው ለምንድን ነው?

11. መጽሐፍ ቅዱስ “ለእኛ ትምህርት” የሚሆኑ ምን እውነተኛ የሕይወት ታሪኮችን ይዟል?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ማራኪ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረገ ሌላም ነገር አለ። በአብዛኛው የሚናገረው ስለ ሰዎች ይኸውም አምላክን ስላገለገሉ ወይም በእሱ ላይ ስላመፁ ሰዎች ነው። ስላጋጠሟቸው ነገሮች፣ ስለደረሱባቸው መከራዎችና ስላገኙት ደስታ የሚገልጹ ዘገባዎችን እናነባለን። በሕይወታቸው ውስጥ ያደረጉት ምርጫ ምን ውጤት እንዳስከተለባቸው የሚገልጹ ዘገባዎችንም እናገኛለን። እንዲህ ያሉት ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት “ለእኛ ትምህርት” እንዲሆኑ ነው። (ሮም 15:4) ይሖዋ እነዚህን እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች እንደ ምሳሌ በመጠቀም ልብ በሚነካ መንገድ ያስተምረናል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

12. ታማኝ ስላልሆኑ ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምን ጥቅም አላቸው?

12 መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ስላልሆኑ አልፎ ተርፎም ክፉ ስለሆኑ ሰዎችና ስለደረሰባቸው ነገር ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች ስለፈጸሟቸው ድርጊቶች የሚገልጹት ዘገባዎች ልንርቃቸው የሚገቡ መጥፎ ባሕርያትን በቀላሉ ለይተን እንድናውቅ ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከክህደት እንድንርቅ መመሪያ ሊሰፍርልን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ድርጊት ምን ያህል መጥፎ መሆኑን ለማስረዳት ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን እንደ ምሳሌ ከመጥቀስ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል? (ማቴዎስ 26:14-16, 46-50፤ 27:3-10) እንዲህ ያሉ ዘገባዎች መጥፎ ባሕርያትን ለይተን እንድናውቅና እንድንጠላ በማድረግ ረገድ ይበልጥ ኃይል አላቸው።

13. መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ባሕርያትን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

13 መጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ ስለሆኑ በርካታ የአምላክ አገልጋዮችም ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ለአምላክ ያደሩ እንደነበሩ የሚገልጹ ዘገባዎችን እናገኛለን። እኛም ወደ አምላክ ለመቅረብ ምን ዓይነት ባሕርያትን ማዳበር እንዳለብን ከእነዚህ ሰዎች ሕያው ምሳሌ ልንማር እንችላለን። እነዚህ ሰዎች የነበራቸውን እምነት እንደ ምሳሌ ልንወስድ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ምን ማለት እንደሆነና አምላክን ለማስደሰት ይህን ባሕርይ ማሳየታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጽልናል። (ዕብራውያን 11:1, 6) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እምነትን በተግባር ያሳዩ ሰዎችን ሕያው ምሳሌም ይዟል። አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ በነበረበት ወቅት ያሳየውን እምነት አስብ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 22፤ ዕብራውያን 11:17-19) እንዲህ ያሉት ዘገባዎች “እምነት” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ እንድንገነዘብ ያስችሉናል። ይሖዋ ጥሩ ባሕርያትን እንድናዳብር ከማሳሰብ በተጨማሪ እንዲህ ያሉ ሕያው ምሳሌዎችን በቃሉ ውስጥ ማካተቱ ምንኛ ጥበብ ነው!

14, 15. መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ስለመጣች አንዲት ሴት ምን ይገልጻል? ይህስ ታሪክ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

14 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች ይሖዋ ምን ዓይነት ባሕርያት ያሉት አምላክ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዱናል። ኢየሱስ በአንድ ወቅት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስላያት ሴት የሚገልጸውን ታሪክ ተመልከት። ኢየሱስ መዋጮ በሚደረግበት ሣጥን አቅራቢያ ተቀምጦ መዋጮ የሚያደርጉትን ሰዎች ይመለከት ነበር። ብዙ ባለጠጎች “ከትርፋቸው” መዋጮ ያደርጉ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ አንዲት ድሃ መበለት ያደረገችው መዋጮ ትኩረቱን ሳበው። ይህች ሴት “በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” መዋጮ አደረገች። b ያለቻት ገንዘብ ይህችው ነበረች። የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት የነበረው ኢየሱስ “በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች” ሲል ተናግሯል። ከኢየሱስ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው ሌሎች ሁሉ ያደረጉት መዋጮ አንድ ላይ ቢደመር እንኳ ይህች ሴት ካደረገችው መዋጮ ጋር አይተካከልም።—ማርቆስ 12:41-44፤ ሉቃስ 21:1-4፤ ዮሐንስ 8:28

15 በዚያን ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ከመጡት ሰዎች ሁሉ ይህች መበለት ተለይታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀሷ የሚያስገርም አይደለም? ይህ ምሳሌ ይሖዋ የምናደርገውን ነገር የሚያደንቅ አምላክ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። የምናቀርበው ስጦታ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ሊሆን ቢችልም እንኳ በሙሉ ነፍሳችን እስካደረግነው ድረስ ይሖዋ በደስታ ይቀበለዋል። ይሖዋ ይህን አስደሳች ሐቅ ለማስገንዘብ ሊጠቀምበት የሚችል ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም!

መጽሐፍ ቅዱስ የማይገልጻቸው ነገሮች

16, 17. ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን በቃሉ ውስጥ አለማካተቱም እንኳ ጥበቡን የሚያሳየው እንዴት ነው?

16 ለምትወደው ሰው ደብዳቤ በምትጽፍበት ጊዜ፣ ልትገልጽለት የምትችለው ብዙ ነገር ቢኖርም ሁሉንም በዝርዝር መጻፍ እንደማትችል የታወቀ ነው። ስለዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች መርጠህ መጻፍ ይኖርብሃል። በተመሳሳይም ይሖዋ በቃሉ ውስጥ የተወሰኑ ግለሰቦችንና ክንውኖችን ብቻ መርጦ አስፍሮልናል። ይሁንና እነዚህ ዘገባዎችም ቢሆኑ ሁልጊዜ እያንዳንዱን ዝርዝር ጉዳይ ይገልጻሉ ማለት አይደለም። (ዮሐንስ 21:25) ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ስለሚወስደው የፍርድ እርምጃ የሚሰጠው መግለጫ በአእምሯችን ውስጥ ለሚነሳው ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ አይሰጠን ይሆናል። ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን በቃሉ ውስጥ አለማካተቱ በራሱ ጥበቡን የሚያሳይ ነው። እንዴት?

17 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት መንገድ በልባችን ውስጥ ያለውን ለመመርመር የሚያስችል ነው። ዕብራውያን 4:12 እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ቃል [ወይም መልእክት] ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን . . . እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ወደ ልባችን ዘልቆ በመግባት ትክክለኛው አስተሳሰባችንና ዝንባሌያችን ምን እንደሆነ እንዲታወቅ ያደርጋል። መተቸት የሚቀናው ልብ ይዘው ቃሉን የሚያነቡ ሰዎች ዝርዝር መረጃዎችን ያልያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ ቅር ያሰኟቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ይሖዋ አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ፍትሐዊ አምላክ ስለ መሆኑም እንኳ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ።

18, 19. (ሀ) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ወዲያው መልስ ልናገኝላቸው ያልቻልናቸው ጥያቄዎች በአእምሯችን ውስጥ እንዲፈጠሩ ቢያደርግ መረበሽ የማይኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክን ቃል ለመረዳት አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ይህስ የይሖዋን ታላቅ ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

18 በአንጻሩ ግን ቃሉን በቅን ልቦና ተነሳስተን የምናነብ ከሆነ ስለ ይሖዋ የሚኖረን ግንዛቤ በአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። በመሆኑም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ወዲያው መልስ ልናገኝላቸው ያልቻልናቸውን ጥያቄዎች ቢያስነሳብን አንረበሽም። ሁኔታውን ከአንድ ትልቅ ተገጣጣሚ ሥዕል ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱን ሥዕል ስንገጣጥም አንዳንዴ የምንፈልገውን ቁራጭ ላናገኝ እንችላለን፤ አንዳንዶቹ ቁርጥራጮች ደግሞ የቱ ጋ እንደሚገቡ ግራ ሊገባን ይችላል። ሆኖም የሥዕሉን የተወሰነ ክፍል ገጣጥመን ከጨረስን አጠቃላይ መልኩ ምን ሊመስል እንደሚችል እንረዳለን። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብን መጠን ስለ ይሖዋ ያለን እውቀት ደረጃ በደረጃ እያደገና እየሰፋ ይሄዳል፤ ስለ ማንነቱ አጠቃላይ ምስል ይኖረናል። እስካሁን ያጠናነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይሖዋ አፍቃሪና ፍትሐዊ አምላክ እንደሆነ በአጥጋቢ ሁኔታ እንድንገነዘብ ያደረገን በመሆኑ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መረዳት ቢያዳግተን ወይም ከአምላክ ባሕርይ ጋር እንዴት እንደሚጣጣም ባይገባን ብዙም አንጨነቅም።

19 እንግዲያው የአምላክን ቃል ለመረዳት አዎንታዊ አመለካከት ይዘን በቅን ልቦና ልናነበውና ልናጠናው ይገባል። ይህ የይሖዋን ታላቅ ጥበብ የሚያሳይ አይደለም? አንዳንድ ምሁራን የሚጽፏቸውን መጻሕፍት አንብበው የሚረዱት ‘ጥበበኞችና አዋቂዎች’ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ብቻ ሊረዱት የሚችሉትን መጽሐፍ መጻፍ የሚችለው ጥበበኛ የሆነው አምላክ ነው!—ማቴዎስ 11:25

“ጥበብ” የያዘ መጽሐፍ

20. የተሻለውን የሕይወት ጎዳና ሊነግረን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ሊረዳ የሚችል ምን ነገር ይዟል?

20 ይሖዋ የተሻለው የሕይወት ጎዳና የቱ እንደሆነ በቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል። ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ምን እንደሚያስፈልገን ከእኛ በላይ ያውቃል። የመወደድ፣ ደስታ የማግኘትና ዘላቂ ወዳጅነት የመመሥረት ፍላጎትን ጨምሮ የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች አሁንም አልተለወጡም። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችን ዓላማ ያለው እንዲሆን የሚረዳ “ጥበብ” የሞላበት መጽሐፍ ነው። (ምሳሌ 2:6) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት አራት ክፍሎች እያንዳንዳቸው ጥበብ ያዘለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንዴት ሥራ ላይ ልናውል እንደምንችል የሚገልጽ ምዕራፍ ይዘዋል፤ ለአብነት ያህል አንድ ምሳሌ እንመልከት።

21-23. ቁጣንና ቂምን በውስጣችን አምቀን እንዳንይዝ የሚረዳን የትኛው ጥበብ ያዘለ ምክር ነው?

21 ቂም የሚይዙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን እንደሚጎዱ አስተውለሃል? ቂም ከባድ ሸክም ነው። ቂም ከያዝን እሱን ብቻ የምናብሰለስል ከመሆኑም በላይ ሰላም ይነሳናል፤ እንዲሁም ደስታ ያሳጣናል። ቁጣን አምቆ መያዝ በልብ በሽታም ሆነ በሌሎች ከባድ በሽታዎች የመጠቃት አጋጣሚን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል አንዳንድ ሳይንሳዊ ጥናቶች ያመለክታሉ። እነዚህ ሳይንሳዊ ጥናቶች ከመካሄዳቸው ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው” የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል። (መዝሙር 37:8) ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

22 የአምላክ ቃል የሚከተለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል፦ “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል፤ በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል።” (ምሳሌ 19:11) ማስተዋል አንድን ነገር እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ሳይሆን ጠለቅ ብሎ የማየትና የመመርመር ችሎታ ነው። አንድ ሰው አንድን ነገር የተናገረበትን ወይም ያደረገበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል። ውስጣዊ ዝንባሌውን፣ ስሜቱንና ያለበትን ሁኔታ በትክክል ለመረዳት መጣራችን ስለ እሱ መጥፎ አመለካከት እንዳንይዝ ሊረዳን ይችላል።

23 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚል ምክር ይሰጣል። (ቆላስይስ 3:13) “እርስ በርስ መቻቻላችሁን . . . ቀጥሉ” የሚለው አባባል ሊያበሳጨን የሚችለውን ባሕርይ በመቻል ሌሎችን መታገሥ እንዳለብን የሚጠቁም ነው። እንዲህ ያለው ትዕግሥት በትንሽ በትልቁ ቅር እንዳንሰኝ ሊረዳን ይችላል። “ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለው አነጋገር ደግሞ ቅር የተሰኘንበትን ነገር እርግፍ አድርጎ መተውን ያመለክታል። ጥበበኛ የሆነው አምላካችን ይቅር ለማለት የሚያስችል ምክንያት እስካለ ድረስ ሌሎችን ይቅር ማለት እንደሚኖርብን ያውቃል። ይህን የምናደርገው ለእነሱ ጥቅም ብለን ብቻ ሳይሆን ለእኛም የአእምሮ ሰላም ስለሚሰጠን ነው። (ሉቃስ 17:3, 4) የአምላክ ቃል በእርግጥም ጥበብ ያዘለ ነው!

24. መለኮታዊውን ጥበብ የሕይወታችን መመሪያ የምናደርገው ከሆነ ምን ጥቅም እናገኛለን?

24 ይሖዋ ያለው ከፍተኛ ፍቅር ሐሳቡን ለሰው ልጆች እንዲገልጽ ገፋፍቶታል። ይህንንም ለማድረግ ከሁሉ የተሻለውን መንገድ ተጠቅሟል፤ ይኸውም ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ መልእክቱን እንዲጽፉ አድርጓል። በመሆኑም የይሖዋ ጥበብ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ ላይ ይገኛል። ይህ ጥበብ “እጅግ አስተማማኝ” ነው። (መዝሙር 93:5) ይህን ጥበብ የሕይወታችን መመሪያ አድርገን የምንጠቀምበትና ለሌሎች የምናስተምር ከሆነ ፍጹም ጥበበኛ ወደሆነው አምላካችን ይበልጥ እንቀርባለን። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በመተንበይና ዓላማውን በመፈጸም ረገድ ያለውን የላቀ ጥበብ እንመለከታለን።

a ለምሳሌ ያህል፣ እረኛ የነበረው ዳዊት በእረኝነት ባሳለፈው ሕይወት የተመለከታቸውን ነገሮች እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል። (መዝሙር 23) ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረው ማቴዎስ ገንዘብንና የተለያዩ አኃዞችን በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅሷል። (ማቴዎስ 17:27፤ 26:15፤ 27:3) ሐኪም የነበረው ሉቃስ ደግሞ የሕክምና እውቀት እንዳለው የሚያሳዩ አገላለጾችን ተጠቅሟል።—ሉቃስ 4:38፤ 14:2፤ 16:20

b መበለቷ የከተተችው ሁለት ሌፕተን ነበር፤ ሌፕተን በወቅቱ አይሁዳውያን ከሚጠቀሙባቸው ሳንቲሞች ሁሉ በጣም አነስተኛ ዋጋ ነበረው። ሁለት ሌፕተን የአንድ ሰው የቀን ደሞዝ 1/64 ነበሩ። እነዚህ ሁለት ሳንቲሞች በዘመኑ የነበሩት ድሆች ይመገቧት የነበረችውን በጣም ርካሽ የሆነች ወፍ ማለትም አንዲት ድንቢጥ እንኳ መግዛት አይችሉም ነበር።