በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 29

‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’

‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’

1-3. (ሀ) ኢየሱስ አባቱን እንዲኮርጅ ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ፍቅሩን ያንጸባረቀባቸውን የትኞቹን ሦስት መንገዶች እንመረምራለን?

 አንድ ትንሽ ልጅ አባቱን ለመምሰል ሲጥር አይተህ ታውቃለህ? የአባቱን አረማመድ፣ አነጋገር ወይም ድርጊት ይኮርጅ ይሆናል። እያደገ ሲሄድ ደግሞ አባቱ የሚመራባቸውን ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ እሴቶች መከተል ሊጀምር ይችላል። አዎን፣ አንድ ልጅ አፍቃሪ ለሆነው አባቱ ያለው አድናቆትና ፍቅር እሱን ለመምሰል እንዲጣጣር ይገፋፋዋል።

2 በኢየሱስና በአባቱ መካከል ስላለው ግንኙነትስ ምን ማለት ይቻላል? በአንድ ወቅት ኢየሱስ ‘አብን እወደዋለሁ’ ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:31) ከሌላ ከማንኛውም ፍጡር ይበልጥ ረጅም ዘመን ከይሖዋ ጋር የኖረው ልጁ ኢየሱስ ነው፤ በመሆኑም ከእሱ ይበልጥ ይሖዋን የሚወድ ሊኖር አይችልም። ይህ ልጅ አባቱን እንዲኮርጅ ያነሳሳው ይህ ጥልቅ ፍቅር ነው።—ዮሐንስ 14:9

3 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ ኢየሱስ የይሖዋን ኃይል፣ ፍትሕና ጥበብ ፍጹም በሆነ መልኩ እንደኮረጀ ተመልክተናል። ሆኖም የአባቱን ፍቅር ያንጸባረቀውስ እንዴት ነው? ኢየሱስ ፍቅሩን ያንጸባረቀባቸውን ሦስት መንገዶች እስቲ እንመልከት፤ እነሱም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ፣ ርኅራኄ ማሳየትና ይቅር ባይነት ናቸው።

ከዚህ “የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም”

4. ኢየሱስ ከማንኛውም ሰው በላቀ መንገድ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ፍቅር በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ሲባል ከራስ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎትና ጥቅም ማስቀደም ማለት ነው። ኢየሱስ ይህን ዓይነቱን ፍቅር ያንጸባረቀው እንዴት ነው? “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ሲል እሱ ራሱ ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:13) ኢየሱስ ለእኛ ሲል ፍጹም ሕይወቱን በፈቃደኝነት ሰጥቷል። አንድ ሰው ፍቅሩን ሊገልጽበት የሚችል ከዚህ የላቀ መንገድ ሊኖር አይችልም። ሆኖም ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅሩን ያሳየው በዚህ ብቻ አይደለም።

5. የአምላክ አንድያ ልጅ ከሰማይ ወደ ምድር መምጣቱ ትልቅ መሥዋዕትነት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

5 የአምላክ አንድያ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ የተከበረ ቦታና ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ከይሖዋም ሆነ እጅግ ብዙ ከሆኑት መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው። ይህ የተወደደ የአምላክ ልጅ በዚህ ሁኔታ በሰማይ ይኖር የነበረ ቢሆንም “ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ያዘ፤ ደግሞም ሰው ሆነ።” (ፊልጵስዩስ 2:7) “በክፉው ቁጥጥር ሥር” በሆነው ዓለም ውስጥ ከኃጢአተኛ ሰዎች ጋር ለመኖር በፈቃደኝነት ወደ ምድር መጣ። (1 ዮሐንስ 5:19) በእርግጥም የአምላክ ልጅ በፍቅር ተገፋፍቶ ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍሏል!

6, 7. (ሀ) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳየው በምን መንገዶች ነው? (ለ) በዮሐንስ 19:25-27 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅትም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ታላቅ ፍቅር እንዳለው በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። ኢየሱስ ራሱን አይቆጥብም ነበር። በአገልግሎቱ በጣም ከመጠመዱ የተነሳ የሰው ልጆች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች እንኳ ሳይቀር መሥዋዕት አድርጓል። “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 8:20) ጎበዝ አናጺ እንደመሆኑ መጠን ለራሱ ልዩ የሆነ ቤት መሥራት ወይም ውብ የሆኑ የቤት ዕቃዎችን እየሠራ በመሸጥ ገንዘብ ማጠራቀም ይችል ነበር። ሆኖም ችሎታውን ቁሳዊ ሀብት ለመሰብሰብ አልተጠቀመበትም።

7 ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ጥልቅ ፍቅር እንደነበረው የሚያሳይ ልብ የሚነካ ዘገባ በዮሐንስ 19:25-27 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ብዙ ሐሳብ በአእምሮው ይጉላላ እንደነበር መገመት አያዳግትም። በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እየተሠቃየ ሳለ ስለ ደቀ መዛሙርቱ፣ ስለ ስብከቱ ሥራ በተለይ ደግሞ የእሱ ታማኝ መሆን አለመሆን በአባቱ ስም ላይ ስለሚያስከትለው ነገር ያወጣ ያወርድ ነበር። የሰው ዘር የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ በእሱ ጫንቃ ላይ ወድቆ ነበር! ይህ ሁሉ ጭንቀት እያለበትም እንኳ ለእናቱ ለማርያም በጣም ያስብ እንደነበረ አሳይቷል፤ ማርያም በወቅቱ መበለት ሳትሆን አትቀርም። ኢየሱስ፣ እንደገዛ እናቱ አድርጎ እንዲደግፋትና እንዲንከባከባት ለሐዋርያው ዮሐንስ አደራ ሰጠው፤ ዮሐንስም አደራውን ተቀብሎ ወደ ቤቱ ይዟት ሄደ። ኢየሱስ በዚህ መንገድ እናቱ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ እንክብካቤ እንዲደረግላት ሁኔታዎችን አመቻቸ። በእርግጥም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ታላቅ ፍቅር አሳይቷል!

“በጣም አዘነላቸው”

8. መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ርኅራኄ ለመግለጽ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል ትርጉም ምንድን ነው?

8 እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ሩኅሩኅ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚገልጹት ኢየሱስ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች በጣም ስለሚያዝን እነሱን ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ርኅራኄ ለመግለጽ የተጠቀመበት ግሪክኛ ቃል “በጣም አዘነላቸው” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ቃል . . . አንድ ሰው አንጀቱ በሐዘን እንዲንሰፈሰፍ የሚያደርገውን ጥልቅ ስሜት ያመለክታል። የርኅራኄን ስሜት ለመግለጽ ከሚያገለግሉት የግሪክኛ ቃላት ሁሉ የበለጠ ኃይል አለው።” ኢየሱስ ከአንጀቱ ራርቶ እርምጃ የወሰደባቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች እስቲ ተመልከት።

9, 10. (ሀ) ኢየሱስና ሐዋርያቱ ገለል ወዳለ ስፍራ መሄድ የፈለጉት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ፣ ሕዝቡ በሄደበት ሁሉ ሲከተሉት ምን ተሰማው? ለምንስ?

9 ርኅራኄ የሰዎችን መንፈሳዊ ረሃብ እንዲያስታግሥ አነሳስቶታል። በማርቆስ 6:30-34 ላይ የሚገኘው ዘገባ ኢየሱስ ለሰዎች እንዲያዝንና እንዲረዳቸው ያደረገውን ዋነኛ ምክንያት ይገልጻል። እስቲ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። ሐዋርያቱ ያደረጉትን መጠነ ሰፊ የስብከት ዘመቻ መጨረሳቸው ስለነበር በጣም ተደስተዋል። ወደ ኢየሱስ ተመልሰው ያጋጠማቸውን ሁሉ ለኢየሱስ በስሜት እየነገሩት ነው። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ገና እህል እንኳ በአፋቸው ሳይዞር ብዙ ሕዝብ በአንዴ አጠገባቸው ስብስብ አለ። ኢየሱስ ሁሌም አስተዋይ ስለሆነ ሐዋርያቱ እንደደከማቸው ተገነዘበ። ስለዚህ “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” አላቸው። ከዚያም ጀልባ ተሳፍረው በገሊላ ባሕር ሰሜናዊ ጫፍ ወደሚገኝ ጸጥ ያለ ስፍራ ሄዱ። ሆኖም ሕዝቡ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ወዴት እንደሄዱ ስላወቁ ወዲያውኑ ወደ ሰሜናዊው የባሕር ዳርቻ ጫፍ በመገስገስ ከጀልባዋ ቀድመው ደረሱ!

10 ኢየሱስ ሕዝቡ መፈናፈኛ እንዳሳጣው ተሰምቶት ተበሳጨ? በፍጹም! ተሰብስቦ እየጠበቀው ያለውን በሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ሲመለከት ከልቡ አዘነ። ማርቆስ እንደሚከተለው ሲል ዘግቧል፦ “እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩም በጣም አዘነላቸው። ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።” ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ እጅግ ተርበው እንደነበር ተገንዝቧል። የሚመራቸው ወይም የሚጠብቃቸው እረኛ አጥተው እንደሚቅበዘበዙ በጎች ነበሩ። ኢየሱስ አፍቃሪ እረኞች መሆን ይጠበቅባቸው የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ለሕዝቡ ግድ እንደሌላቸውና ችላ ብለዋቸው እንደነበር አስተውሏል። (ዮሐንስ 7:47-49) የሕዝቡ ሁኔታ አንጀቱን ስለበላው “ስለ አምላክ መንግሥት” ያስተምራቸው ጀመር። (ሉቃስ 9:11) ኢየሱስ ለሕዝቡ ያዘነው ላስተማራቸው ነገር የሰጡትን ምላሽ ካየ በኋላ አለመሆኑን ልብ በል። በሌላ አነጋገር የኢየሱስ ርኅራኄ የሕዝቡን ምላሽ በማየት የመጣ ውጤት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ከመጀመሪያውም ሕዝቡን እንዲያስተምራቸው የገፋፋው ምክንያት ርኅራኄ ነው።

“እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው”

11, 12. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለሥጋ ደዌ በሽተኞች የነበረው አመለካከት ምን ይመስል ነበር? ሆኖም ኢየሱስ “የሥጋ ደዌ የወረሰው” አንድ ሰው ወደ እሱ ሲቀርብ ምን አደረገ? (ለ) ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽተኛውን መዳሰሱ በሰውየው ላይ ምን ስሜት አሳድሮ ሊሆን ይችላል? የአንድ ሐኪም ገጠመኝ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነውስ እንዴት ነው?

11 ርኅራኄ ሥቃያቸውን እንዲያስታግሥ አነሳስቶታል። የተለያየ ሕመም የነበራቸው ሰዎች ኢየሱስ ሩኅሩኅ እንደሆነ ስላወቁ ወደ እሱ ይቀርቡ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከብዙ ሕዝብ ጋር ሳለ የተፈጸመው ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው። “መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ የወረሰው ሰው” ወደ ኢየሱስ መጣ። (ሉቃስ 5:12) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሥጋ ደዌ በሽታ የያዛቸው ሰዎች በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳያዛምቱ ሲባል ተገልለው እንዲቆዩ ይደረግ ነበር። (ዘኁልቁ 5:1-4) ከጊዜ በኋላ ግን ረቢዎች የሥጋ ደዌ በሽታን በተመለከተ ርኅራኄ የጎደለው አመለካከት እንዲስፋፋ ያደረጉ ከመሆኑም በላይ የራሳቸውን ጨቋኝ የሆኑ ደንቦች አውጥተው ነበር። a ሆኖም ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽታ ያለበትን ይህን ሰው እንዴት እንደያዘው ልብ በል፤ ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰውም ወደ እሱ ቀርቦ ‘ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ’ በማለት ተንበርክኮ ተማጸነው። በዚህ ጊዜ በጣም አዘነለትና እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው፤ ከዚያም ‘እፈልጋለሁ! ንጻ’ አለው። ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው።” (ማርቆስ 1:40-42) ኢየሱስ ይህ ሰው ከሕዝቡ ጋር መቀላቀሉ ተገቢ እንዳልነበር ያውቃል። ሆኖም በጣም ስላሳዘነው ወደ እሱ እንዳይቀርብ ከመከልከል ይልቅ ጭራሽ የማይታሰብ ነገር አደረገ። ሰውየውን በእጁ ዳሰሰው!

12 የሥጋ ደዌ በሽተኛው ኢየሱስ ሲዳስሰው ምን እንደተሰማው ልትገምት ትችላለህ? ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ገጠመኝ ተመልከት። ዶክተር ፖል ብራንድ የተባሉ የሥጋ ደዌ ስፔሻሊስት በሕንድ አገር ስላከሙት አንድ የሥጋ ደዌ በሽተኛ የሚነግሩን ነገር አለ። ምርመራ እያደረጉለት ባሉበት ወቅት እጃቸውን ትከሻው ላይ ጣል አድርገው ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚደረግለት በአስተርጓሚ አማካኝነት ነገሩት። በሽተኛው ድንገት ማልቀስ ጀመረ። ዶክተሩ “የሚያስከፋ ነገር ተናገርኩ እንዴ?” ሲሉ ጠየቁ። አስተርጓሚዋ ታካሚውን ምን እንዳስለቀሰው በቋንቋው ከጠየቀችው በኋላ እንዲህ ስትል ለዶክተሩ መለሰችላቸው፦ “አይ አልተናገሩም። ‘ያለቀስኩት እጅዎን ትከሻዬ ላይ በማሳረፍዎ ነው’ እያለ ነው። እዚህ እስኪመጣ ድረስ ለብዙ ዓመታት ማንም በእጁ ነክቶት አያውቅም።” ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽተኛውን መዳሰሱ ከዚህም የላቀ ጥቅም ነበረው። ከሰዎች እንዲገለል አድርጎት የነበረው በሽታ በዚያው ቅጽበት ተወገደ!

13, 14. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ናይን ከተማ አቅራቢያ ሲደርስ ምን አጋጠመው? ሁኔታውን ይበልጥ አሳዛኝ ያደረገውስ ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በርኅራኄ ተነሳስቶ በናይን ላገኛት መበለት ምን አደረገላት?

13 ርኅራኄ ከሐዘናቸው እንዲላቀቁ ለማድረግ አነሳስቶታል። ኢየሱስ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ሲመለከት አንጀቱ ይንሰፈሰፍ ነበር። ለምሳሌ በሉቃስ 7:11-15 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። ጊዜው በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት አጋማሽ አካባቢ ነው፤ ኢየሱስ ናይን ወደምትባለው የገሊላ ከተማ እየተጠጋ ነበር። ወደ ከተማዋ በር ሲቃረብ ወደ ቀብር የሚሄዱ ሰዎች ተመለከተ። ሁኔታው በጣም የሚያሳዝን ነበር። የሞተው ወጣት የአንዲት መበለት አንድያ ልጅ ነው። ይህች ሴት ከዚህ ቀደም ባሏን ቀብራለች። አሁን ደግሞ አንድ ልጇን አጣች፤ ምናልባትም የምትተዳደረው ይህ ልጅ በሚያደርግላት ድጋፍ ብቻ ሊሆን ይችላል። ለቀብር ይጓዙ ከነበሩት ሰዎች መካከል አልቃሾች፣ ሙሾ የሚያወርዱ ሰዎችና የሐዘን ዜማ የሚጫወቱ ዋሽንት ነፊዎችም ሳይኖሩ አይቀሩም። (ኤርምያስ 9:17, 18፤ ማቴዎስ 9:23) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ትኩረቱ ያረፈው በእናቲቱ ላይ ነው፤ ምናልባትም የልጇን አስከሬን በያዘው ቃሬዛ አጠገብ እየሄደች ምርር ብላ እያለቀሰች ይሆናል።

14 ኢየሱስ በሐዘን ለተደቆሰችው ለዚህች እናት “በጣም አዘነላት።” ከዚያም በሚያረጋጋ ድምፅ “በቃ፣ አታልቅሺ” አላት። ቀረብ ብሎም ቃሬዛውን ነካ። ቃሬዛውን የተሸከሙት ሰዎች ምናልባትም ለቀስተኞቹ በሙሉ ቆሙ። ኢየሱስ “አንተ ወጣት፣ ተነስ እልሃለሁ!” በማለት ለአስከሬኑ ተናገረ። ከዚያስ ምን ተከሰተ? “የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠና መናገር ጀመረ”፤ ጭልጥ ካለ እንቅልፍ እንደነቃ ሰው ማለት ነው! ቀጥሎ ኢየሱስ ልጁን “ለእናቱ ሰጣት” የሚል ልብ የሚነካ ዘገባ እናነባለን።

15. (ሀ) ኢየሱስ ለሰዎች እንዳዘነ የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በርኅራኄና በድርጊት መካከል ምን ዝምድና እንዳለ ያሳያሉ? (ለ) በዚህ ረገድ ኢየሱስን ልንኮርጅ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ከእነዚህ ዘገባዎች ምን እንማራለን? በእያንዳንዱ ታሪክ ላይ በርኅራኄና እርምጃ በመውሰድ መካከል ያለውን ዝምድና ልብ በል። ኢየሱስ የሌሎችን መከራና ሥቃይ ሲያይ ሁሌም ይራራል፤ ርኅራኄው ደግሞ እነሱን ለመርዳት እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ግዴታ አለብን። ይህን እንድናደርግ የሚገፋፋን ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። ሆኖም ይህ ሥራ የርኅራኄ መግለጫ መሆኑንም መዘንጋት የለብንም። እንደ ኢየሱስ ለሰዎች ከልብ የምናዝን ከሆነ ልባችን ምሥራቹን ለእነሱ ለመንገር የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ማቴዎስ 22:37-39) ችግር ላይ ለወደቁ ወይም ላዘኑ የእምነት አጋሮቻችን ርኅራኄ ስለ ማሳየትስ ምን ማለት ይቻላል? ሰዎችን በተአምር ከበሽታ መፈወስ ወይም ከሞት ማስነሳት እንደማንችል የታወቀ ነው። ሆኖም አሳቢነታችንን በመግለጽ ወይም አቅማችን በፈቀደ መጠን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን።—ኤፌሶን 4:32

“አባት ሆይ፣ . . . ይቅር በላቸው”

16. ኢየሱስ ተሰቅሎ እያለም እንኳ ይቅር ባይ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ በመሆንም የአባቱን ፍቅር ፍጹም በሆነ ሁኔታ አንጸባርቋል። (መዝሙር 86:5) ተሰቅሎ እያለም እንኳ ይቅር ባይ መሆኑን አሳይቷል። እጆቹና እግሮቹ በሚስማር ተቸንክረው ክብርን በሚነካ ሁኔታ እንዲሞት በተደረገበት ወቅት የተናገረው ቃል ምን ነበር? ይሖዋ፣ የሰቀሉትን ሰዎች እንዲቀስፍለት ተማጽኗል? በፍጹም፤ እንዲያውም “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ሲል አባቱን ለምኗል።—ሉቃስ 23:34 b

17-19. ኢየሱስ ሦስት ጊዜ የካደውን ሐዋርያው ጴጥሮስን ይቅር እንዳለው ያሳየው በምን መንገዶች ነው?

17 ስለ ይቅር ባይነቱ ከዚህም በላይ ልብ የሚነካ ምሳሌ የምናገኘው ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ስላሳየው ምሕረት በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። ጴጥሮስ ኢየሱስን ከልብ ይወደው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ኒሳን 14 በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት የመጨረሻ ምሽት ላይ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ወደ ወህኒ ለመውረድም ሆነ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” ሲል ተናግሮ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጴጥሮስ ኢየሱስን ጨርሶ እንደማያውቀው በመናገር ሦስት ጊዜ ካደው! መጽሐፍ ቅዱስ ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስን በካደበት ወቅት የሆነውን ሁኔታ ሲገልጽ “ጌታ ዞር ብሎ ጴጥሮስን ትክ ብሎ አየው” ይላል። ጴጥሮስ በሠራው ከባድ ኃጢአት ቅስሙ በመሰበሩ “ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።” በዚያው ዕለት ኢየሱስ ሲሞት ሐዋርያው ‘ጌታዬ ይቅር ብሎኝ ይሆን?’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 22:33, 61, 62

18 ጴጥሮስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ረጅም ጊዜ መጠበቅ አላስፈለገውም። ኢየሱስ ኒሳን 16 ጠዋት ላይ ከሞት ተነሳ፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው በዚያኑ ዕለት ለጴጥሮስ በግል ተገለጠለት። (ሉቃስ 24:34፤ 1 ቆሮንቶስ 15:4-8) ኢየሱስ ሽምጥጥ አድርጎ ለካደው ሐዋርያ እንዲህ ለየት ያለ ትኩረት የሰጠው ለምንድን ነው? ንስሐ ለገባው ለጴጥሮስ ያለው ፍቅርና ከፍ ያለ ግምት እንዳልቀነሰ ሊያረጋግጥለት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ የእሱን ይቅርታ እንዳገኘ እርግጠኛ እንዲሆን ሲል ሌላም ያደረገው ነገር አለ።

19 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። በዚህ ወቅት ኢየሱስ፣ ሦስት ጊዜ የካደውን ጴጥሮስን ይወደው እንደሆነ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ጠየቀው። ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ሲጠየቅ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰ። እርግጥ ነው፣ ልብን ማንበብ የሚችለው ኢየሱስ ጴጥሮስ ምን ያህል እንደሚወደው አሳምሮ ያውቃል። ሆኖም ለእሱ ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት አጋጣሚ ለጴጥሮስ መስጠት ፈልጎ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የእሱን ‘ግልገሎች የመመገብ’ እና ‘የመጠበቅ’ ተልእኮ ሰጠው። (ዮሐንስ 21:15-17) ጴጥሮስ ቀደም ሲል የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር። (ሉቃስ 5:10) ሆኖም በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን እንዲጠብቅ በማሳሰብ በጴጥሮስ ላይ ምን ያህል እምነት እንዳለው የሚያሳይ ከባድ ኃላፊነት ሰጠው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በሚያከናውኑት ሥራ ረገድ የጎላ ሚና የመጫወት ኃላፊነት ለጴጥሮስ ሰጥቶታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-41) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ይቅር እንዳለውና በእሱ ላይ ያለው እምነት እንዳልቀነሰ ሲያውቅ እንዴት እፎይ ብሎ ይሆን!

‘የክርስቶስን ፍቅር ታውቃለህ?’

20, 21. በተሟላ ሁኔታ ‘የክርስቶስን ፍቅር ማወቅ’ የምንችለው እንዴት ነው?

20 በእርግጥም፣ የይሖዋ ቃል የክርስቶስን ፍቅር ግሩም በሆነ መንገድ ይገልጸዋል። ሆኖም እኛ ለኢየሱስ ፍቅር ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ “ከእውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስ ፍቅር [ለማወቅ]” እንድንጥር አጥብቆ ይመክረናል። (ኤፌሶን 3:19) ከላይ እንደተመለከትነው ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች ስለ ክርስቶስ ፍቅር ብዙ የሚያስተምሩን ነገር አለ። ሆኖም በተሟላ ሁኔታ ‘የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ’ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ የሚናገረውን መማር ብቻውን በቂ አይደለም።

21 ‘ማወቅ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በተግባር፣ በተሞክሮ” ማወቅ የሚል ፍቺ አለው። የኢየሱስን ስሜት በትክክል መረዳት የምንችለው ፍቅር በማሳየት ረገድ ስንመስለው ነው፤ ራሳችንን ሳንቆጥብ ለሌሎች በመስጠት፣ በርኅራኄ ተነሳስተን ለችግራቸው በመድረስና ከልብ ይቅር በማለት ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። በዚህ መንገድ “ከእውቀት በላይ የሆነውን የክርስቶስ ፍቅር” እንዲሁ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ‘ማወቅ’ እንችላለን። ደግሞም ኢየሱስ የይሖዋ ፍጹም ነጸብራቅ በመሆኑ እሱን እየመሰልን በሄድን መጠን አፍቃሪ ወደሆነው አምላካችን ይበልጥ እየቀረብን እንደምንሄድ መዘንጋት የለብንም።

a የረቢዎች ሕግ ማንም ሰው የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ሁለት ሜትር ገደማ መራቅ እንዳለበት ያዝዛል። ነፋስ የሚነፍስ ከሆነ ደግሞ ሕመምተኛው ቢያንስ 45 ሜትር ገደማ መራቅ ነበረበት። ሚድራሽ ራባ የተባለው የአይሁዶች መጽሐፍ አንድ ረቢ ከሥጋ ደዌ በሽተኞች ይሸሸግ እንደነበረ፣ ሌላው ረቢ ደግሞ እንዳይጠጉት ሲል ድንጋይ ይወረውርባቸው እንደነበር ይገልጻል። የሥጋ ደዌ በሽተኞች ሕዝቡ በጣም ያገልላቸውና ይጸየፋቸው የነበረ በመሆኑ ስሜታቸው ይጎዳ ነበር።

b የሉቃስ 23:34 የመጀመሪያ ክፍል በአንዳንድ የጥንት ቅጂዎች ላይ አይገኝም። ሆኖም ተአማኒነት ባላቸው በሌሎች ብዙ ቅጂዎች ላይ ስለሚገኝ በአዲስ ዓለም ትርጉም እና በሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ተካትቷል። እዚህ ላይ ኢየሱስ ስለሰቀሉት የሮም ወታደሮች እየተናገረ ሳይሆን አይቀርም። ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ማንነት የሚያውቁት ነገር ስላልነበረ የሚያደርጉትን አያውቁም ሊባሉ ይችላሉ። በተጨማሪም እንዲገደል የጠየቁትን በኋላ ግን በእሱ ያመኑትን አይሁዳውያን አስቦም ሊሆን ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 2:36-38) እርግጥ ነው፣ ሞት እንዲፈረድበት ያደረጉት የሃይማኖት መሪዎች ይህን ተግባር የፈጸሙት የኢየሱስን ማንነት አውቀውና በክፋት ተነሳስተው በመሆኑ በምንም ዓይነት ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ አይችሉም። ከእነሱ መካከል አብዛኞቹ ይቅር ሊባሉ አይችሉም።—ዮሐንስ 11:45-53