በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 26

‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነ አምላክ

‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነ አምላክ

1-3. (ሀ) መዝሙራዊው ዳዊት ከባድ ሸክም ሆኖበት የነበረው ምንድን ነው? ማጽናኛ ያገኘውስ እንዴት ነው? (ለ) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ምን ነገር ሸክም ሊሆንብን ይችላል? ሆኖም ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?

 መዝሙራዊው ዳዊት “የፈጸምኳቸው ስህተቶች በራሴ ላይ ያንዣብባሉ፤ እንደ ከባድ ሸክም በጣም ከብደውኛል። ደነዘዝኩ፤ ፈጽሞም ደቀቅኩ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 38:4, 8) ዳዊት የሕሊና ወቀሳ ምን ያህል ከባድ ሸክም እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ የተረበሸውን ልቡን የሚያረጋጋ ማጽናኛ አግኝቷል። ይሖዋ ኃጢአትን የሚጠላ ቢሆንም እንኳ ንስሐ የገባንና መጥፎ ድርጊቱን እርግፍ አድርጎ የተወን ሰው እንደማይጠላ ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት፣ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ይቅር ማለት እንደሚፈልግ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ‘ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ’ ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 86:5

2 እኛም ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የሕሊና ወቀሳ እረፍት ሊነሳንና ከባድ ሸክም ሊሆንብን ይችላል። በሠራነው ድርጊት መጸጸታችን ተገቢ ነው። የሠራነውን ስህተት ለማረም አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይችላል። ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ በጥፋተኝነት ስሜት እንዳንዋጥ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ራሱን የመኮነን ዝንባሌ ያለው ልባችን፣ ምንም ያህል ንስሐ ብንገባ ይሖዋ ይቅር እንደማይለን ሆኖ እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። በመሆኑም “ከልክ በላይ በሐዘን [ልንዋጥ]” እንችላለን፤ ሰይጣን ደግሞ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በይሖዋ ፊት ዋጋ እንደሌለንና እሱን ለማገልገል ብቁ እንዳልሆንን ሆኖ እንዲሰማን በማድረግ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይሞክራል።—2 ቆሮንቶስ 2:5-11

3 ይሁንና ይሖዋ የሚመለከተን በዚህ መንገድ ነው? በፍጹም! ታላቅ የሆነው የይሖዋ ፍቅር አንዱ ገጽታ ይቅር ባይነት ነው። ከልብ የመነጨ እውነተኛ የንስሐ ፍሬ ካሳየን ይቅር እንደሚለን በቃሉ አማካኝነት ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 28:13) በይሖዋ ይቅር ባይነት ሙሉ በሙሉ መተማመን እንድንችል እስቲ በመጀመሪያ ይሖዋ ለምንና እንዴት ይቅር እንደሚል እንመርምር።

ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ የሆነው ለምንድን ነው?

4. ይሖዋ አፈጣጠራችንን በተመለከተ የማይዘነጋው ነገር ምንድን ነው? ይህስ እኛን በሚይዝበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

4 ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብ በሚገባ ያውቃል። መዝሙር 103:14 “እሱ እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስታውሳል” ይላል። ከአፈር እንደተሠራንና በአለፍጽምና ምክንያት ድክመት ወይም ጉድለት እንዳለብን ፈጽሞ አይዘነጋም። “እንዴት እንደተሠራን በሚገባ ያውቃል” የሚለው አገላለጽ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን ከሸክላ ሠሪ እኛን ደግሞ እሱ ከሚሠራቸው የሸክላ ዕቃዎች ጋር እንደሚያመሳስል እንድናስታውስ ያደርገናል። (ኤርምያስ 18:2-6) ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ በወረስነው ኃጢአት ምክንያት ያለብንን ድክመት ይረዳል፤ በመሆኑም ለእሱ አመራር የምንሰጠውን ምላሽ እያየ እኛን በሚይዝበት መንገድ ላይ በደግነት ማስተካከያ ያደርጋል።

5. የሮም መጽሐፍ ኃጢአት ያለውን ኃይል የሚገልጸው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ኃጢአት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ያውቃል። ቃሉ እንደሚገልጸው ኃጢአት የሰውን ዘር አንቆ የያዘ ኃይል ነው። ኃጢአት ምን ያህል ኃይል አለው? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ ወታደሮች ለአዛዣቸው ሥልጣን እንደሚገዙ ሁሉ እኛም “የኃጢአት ተገዢዎች” ነን (ሮም 3:9)፤ ኃጢአት በሰው ልጆች ላይ ‘ነግሧል’ (ሮም 5:21)፤ በእኛ ውስጥ ‘ይኖራል’ (ሮም 7:17, 20)፤ የኃጢአት “ሕግ” ያለማቋረጥ በውስጣችን ይሠራል፤ በሌላ አነጋገር አኗኗራችንን ሊቆጣጠረው ይሞክራል። (ሮም 7:23, 25) በእርግጥም ኃጢአት ፍጽምና የጎደለውን ሥጋችንን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎታል!—ሮም 7:21, 24

6, 7. (ሀ) ይሖዋ ከልባቸው ንስሐ ገብተው የእሱን ምሕረት ለሚሹ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አለው? (ለ) የአምላክን ምሕረት አላግባብ ልንጠቀምበት የማይገባው ለምንድን ነው?

6 በመሆኑም ይሖዋ እሱን ለመታዘዝ የቱንም ያህል ልባዊ ፍላጎት ቢኖረን ፍጹም በሆነ ደረጃ ልንታዘዘው እንደማንችል ያውቃል። ከልብ ንስሐ ገብተን ይቅር እንዲለን ብንለምነው ምሕረት እንደሚያደርግልን ዋስትና ሰጥቶናል። መዝሙር 51:17 “አምላክን የሚያስደስተው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም” ይላል። ይሖዋ ልቡ በጥፋተኝነት ስሜት “የተሰበረንና የተደቆሰን” ሰው መቼም ቢሆን ፊት አይነሳውም።

7 ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል አለፍጽምናችንን ለኃጢአት ማሳበቢያ በማድረግ የአምላክን ምሕረት አላግባብ ልንጠቀምበት እንችላለን ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ እንዲሁ በስሜት የሚመራ አምላክ አይደለም። ምሕረቱ ገደብ አለው። ምንም ዓይነት የንስሐ መንፈስ የማያሳዩና ሆን ብለው በልበ ደንዳናነት ኃጢአት መሥራታቸውን የሚቀጥሉ ሰዎችን ይቅር አይልም። (ዕብራውያን 10:26) በሌላ በኩል ግን ከልቡ የተጸጸተን ሰው ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። አስደናቂ የሆነውን ይህን የይሖዋ ፍቅር ገጽታ ሕያው አድርገው የሚገልጹ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫዎችን እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላል ሲባል ምን ማለት ነው?

8. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ሲል ምን ያደረገልን ያህል ነው? ይህስ ምን እምነት ያሳድርብናል?

8 ዳዊት ንስሐ ከገባ በኋላ “በመጨረሻ ኃጢአቴን ለአንተ ተናዘዝኩ፤ ስህተቴን አልሸፋፈንኩም። . . . አንተም ስህተቴንና ኃጢአቴን ይቅር አልክ” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 32:5) እዚህ ላይ “ይቅር አልክ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ “ማንሳት” ወይም “መሸከም” የሚል ነው። ቃሉ እዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራበት “በደልን፣ ኃጢአትንና መተላለፍን” አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ ማራቅ የሚለውን ሐሳብ በሚያስተላልፍ መንገድ ነው። በመሆኑም ይሖዋ የዳዊትን ኃጢአት ከላዩ አንስቶ ያራቀለት ያህል ነበር። ይህም ዳዊት እንደ ሸክም ሆኖበት የነበረውን የጥፋተኝነት ስሜት እንዳቀለለለት ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 32:3) እኛም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ምሕረቱን ለማግኘት ከለመንን አምላክ ኃጢአታችንን ከላያችን አንስቶ እንደሚያርቅልን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—ማቴዎስ 20:28

9. ይሖዋ ኃጢአታችንን ከእኛ ምን ያህል ያርቀዋል?

9 ዳዊት የይሖዋን ይቅር ባይነት ለመግለጽ ሌላ ሕያው የሆነ መግለጫም ተጠቅሟል፦ “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ።” (መዝሙር 103:12) ምሥራቅ ከምዕራብ ምን ያህል ይርቃል? ምሥራቅና ምዕራብ በተለያየ ጽንፍ የሚገኙ አቅጣጫዎች እንደ መሆናቸው መጠን ፈጽሞ ሊገናኙ አይችሉም። አንድ ምሁር እንዳሉት ይህ አገላለጽ “በጣም ሩቅ፣ ከምንገምተው በላይ ሩቅ” የሆነን ቦታ ያመለክታል። ዳዊት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ ይቅር ሲለን ኃጢአታችንን ከምንገምተው በላይ ከእኛ እንደሚያርቀው ይጠቁማሉ።

“ኃጢአታችሁ . . . እንደ በረዶ ይነጣል”

10. ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ካለን በቀሪው የሕይወት ዘመናችን ኃጢአታችን ያስከተለብንን ኀፍረት ተሸክመን እንደምንኖር ሆኖ ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው?

10 የመነቸከ ነጭ ልብስ ለማስለቀቅ ሞክረህ ታውቃለህ? የቱንም ያህል ብትፈትገው ቆሻሻው አልለቅ ይል ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይቅር ባይነቱን እንዴት እንደገለጸው ልብ በል፦ “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደማቅ ቀይ ጨርቅ ቢቀላም እንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ይሆናል።” a (ኢሳይያስ 1:18) በራሳችን ጥረት ኃጢአታችንን ልናጠራ ወይም ልናስወግድ አንችልም። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደ ደም የቀላውን ወይም እንደ ደማቅ ቀይ የሆነውን ኃጢአታችንን እንደ በረዶ ወይም እንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ነጭ ሊያደርገው ይችላል። ስለሆነም ይሖዋ ኃጢአታችንን አንዴ ይቅር ካለን በቀሪው የሕይወት ዘመናችን ሁሉ ኃጢአታችን ያስከተለብንን ኀፍረት ተሸክመን እንደምንኖር ሆኖ ሊሰማን አይገባም።

11. ይሖዋ ኃጢአታችንን ወደ ኋላው ይጥላል ሲባል ምን ማለት ነው?

11 ሕዝቅያስ ታሞ ከሞት አፋፍ ከተረፈ በኋላ ባቀናበረው ስሜት የሚነካ የምስጋና መዝሙር ላይ ይሖዋን “ኃጢአቴን ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልክ” ብሎታል። (ኢሳይያስ 38:17) ይህ ጥቅስ ይሖዋ፣ ንስሐ የገባ አንድ ኃጢአተኛ የሠራውን ኃጢአት ወደ ኋላው በመጣል ዳግመኛ እንደማያየውና ትኩረት እንደማይሰጠው የሚጠቁም አገላለጽ ይዟል። አንድ ጽሑፍ እንደሚለው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ “[ኃጢአቴን] ያልነበረ ያህል አደረግኸው” እንደ ማለት ነው። ይህ የሚያጽናና አይደለም?

12. ነቢዩ ሚክያስ ይሖዋ ይቅር ሲል ኃጢአታችንን ለዘለቄታው እንደሚያስወግደው ያመለከተው እንዴት ነው?

12 ነቢዩ ሚክያስ፣ ተሃድሶን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ሕዝቦቹን ይቅር እንደሚል ያለውን ጠንካራ እምነት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የርስቱን ቀሪዎች [በደል] የሚያልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? . . . ኃጢአታቸውን ሁሉ ወደ ጥልቅ ባሕር ትጥላለህ።” (ሚክያስ 7:18, 19) እነዚህ ቃላት በጥንት ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው አስብ። በዚያ ዘመን “ወደ ጥልቅ ባሕር” የተጣለን ነገር መልሶ ማግኘት የሚቻልበት ምንም ዓይነት መንገድ አልነበረም። በመሆኑም የሚክያስ ቃላት ይሖዋ ይቅር ሲል ኃጢአታችንን ለዘለቄታው እንደሚያስወግድ የሚያመለክቱ ናቸው።

13. “ዕዳችንን ይቅር በለን” የሚለው የኢየሱስ አነጋገር ምን ትርጉም አለው?

13 ኢየሱስ የይሖዋን ይቅር ባይነት ለማስረዳት በአበዳሪና በተበዳሪ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። “በደላችንን [“ዕዳችንን፣” የግርጌ ማስታወሻ] ይቅር በለን” ብለን እንድንጸልይ መክሮናል። (ማቴዎስ 6:12) በመሆኑም ኢየሱስ ኃጢአትን ከዕዳ ጋር አመሳስሎ ገልጾታል። (ሉቃስ 11:4 የግርጌ ማስታወሻ) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የይሖዋ ‘ባለዕዳ’ እንሆናለን። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ “ይቅር በለን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ “ዕዳን መተው፣ መሰረዝ ወይም አለማስከፈል” የሚል ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል። በመሆኑም ይሖዋ ይቅር ሲለን በእሱ ላይ ያለብንን ዕዳ የሰረዘልን ያህል ነው። ይህም ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን የሚያጽናና ነው። ይሖዋ ዕዳን አንዴ ከሰረዘ መልሶ አይጠይቅም።—መዝሙር 32:1, 2

14. “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ” የሚለው ሐረግ የይሖዋን ምሕረት ግልጽ የሚያደርገው እንዴት ነው?

14 በሐዋርያት ሥራ 3:19 ላይ ደግሞ የይሖዋ ይቅር ባይነት በዚህ መልኩ ተገልጿል፦ “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱ።” “እንዲደመሰስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ “ሙልጭ አድርጎ መጥረግን፣ . . . መሰረዝን ወይም ማጥፋትን” ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት እዚህ ላይ ያለው አገላለጽ አንድን የእጅ ጽሑፍ ማጥፋትን የሚጠቁም ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በጥንት ዘመን ሰዎች ለመጻፍ ይጠቀሙበት የነበረው ቀለም ከካርቦን፣ ከሙጫና ከውኃ የተሠራ ነበር። አንድ ሰው በዚህ ቀለም ሲጽፍ ከቆየ በኋላ ጽሑፉን በእርጥብ ስፖንጅ ሙልጭ አድርጎ ሊያጠፋው ይችል ነበር። ይህ የይሖዋን ምሕረት የሚያሳይ ግሩም መግለጫ ነው። ኃጢአታችንን ይቅር በሚልበት ጊዜ በስፖንጅ ሙልጭ አድርጎ የማጥፋት ያህል ሙሉ በሙሉ ይደመስሰዋል።

15. ይሖዋ ምን እንድናውቅ ይፈልጋል?

15 እነዚህን የተለያዩ ዘይቤያዊ አገላለጾች ስንመረምር፣ ይሖዋ ከልባችን ንስሐ እስከገባን ድረስ እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን እንድናውቅ እንደሚፈልግ በግልጽ እንረዳለን። ኃጢአታችንን በሌላ ጊዜ እንደሚያነሳብን በማሰብ ስጋት ሊያድርብን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ታላቅ ምሕረት የሚነግረን ሌላው ነገር ይህን ያረጋግጥልናል፤ ይህም ይሖዋ ይቅር ሲል የሠራነውን ኃጢአት እንደሚረሳው የሚገልጸው ሐሳብ ነው።

ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ መሆኑን እንድናውቅ ይፈልጋል

“ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም”

16, 17. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ኃጢአታችንን እንደሚረሳው ሲናገር ምን ማለቱ ነው? አብራራ።

16 ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉትን ሰዎች በተመለከተ “በደላቸውን ይቅር እላለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም” ሲል ቃል ገብቷል። (ኤርምያስ 31:34) እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ ይቅር ሲል የሠራነውን ኃጢአት ማስታወስ ይሳነዋል ማለት ነው? በፍጹም፣ እንደዚያ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊትን ጨምሮ የይሖዋን ምሕረት ያገኙ በርካታ ሰዎች ስለሠሯቸው ኃጢአቶች ይናገራል። (2 ሳሙኤል 11:1-17፤ 12:13) ይሖዋ ኃጢአታቸውን ይቅር ካላቸው በኋላም የፈጸሙትን ድርጊት እንደሚያውቅ ግልጽ ነው። የሠሩትን ኃጢአትም ሆነ ያሳዩትን የንስሐ ፍሬ እንዲሁም ይሖዋ ያደረገላቸውን ምሕረት የሚገልጸው ዘገባ ለትምህርታችን ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ እንዲቆይ ተደርጓል። (ሮም 15:4) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ይቅር ያላቸው ሰዎች የሠሩትን ኃጢአት ‘አያስታውስም’ ሲል ምን ማለቱ ነው?

17 “ከእንግዲህ አላስታውስም” የሚለው ሐረግ ላይ ‘ማስታወስ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ የሚያመለክተው እንዲሁ ያለፈውን ነገር ወደ አእምሮ መልሶ ማምጣትን አይደለም። ቲኦሎጂካል ወርድቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ቃሉ “ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የሚል መልእክትም ያስተላልፋል።” ከዚህ አንጻር ሲታይ ኃጢአትን ‘ማሰብ’ ወይም ‘ማስታወስ’ የሚለው አነጋገር በኃጢአተኞች ላይ እርምጃ መውሰድንም ያመለክታል። (ሆሴዕ 9:9) ሆኖም አምላክ “ኃጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስታውስም” ብሎ ሲናገር ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን አንዴ ይቅር ካለ ወደፊት በዚያ ኃጢአት ምክንያት እንደማይቀጣቸው ማረጋገጫ መስጠቱ ነው። (ሕዝቅኤል 18:21, 22) በመሆኑም ይሖዋ ኃጢአታችንን ይረሳዋል ሲባል የፈጸምነውን ድርጊት በየጊዜው እያነሳ በተደጋጋሚ አይቀጣንም ማለት ነው። ይሖዋ ይቅር የሚልና ኃጢአታችንን የሚረሳ መሆኑ የሚያጽናና አይደለም?

የፈጸምነው ኃጢአት የሚያስከትለው መዘዝስ?

18. ንስሐ የገባ አንድ ኃጢአተኛ የይሖዋን ምሕረት አገኘ ማለት የፈጸመው ድርጊት ከሚያስከትልበት መዘዝ ሁሉ ነፃ ይሆናል ማለት አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ ንስሐ የገባን አንድ ኃጢአተኛ ይቅር ሲለው ግለሰቡ ኃጢአቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናል ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ኃጢአት ከሠራን የፈጸምነው ድርጊት ከሚያስከትልብን መዘዝ ነፃ እንሆናለን ብለን ልንጠብቅ አንችልም። ጳውሎስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” ሲል ጽፏል። (ገላትያ 6:7) በፈጸምነው ድርጊት ሳቢያ አንዳንድ ችግሮች ሊደርሱብን ይችላሉ። ይህ ማለት ግን ይሖዋ ይቅር ካለን በኋላ መከራ እንዲደርስብን ያደርጋል ማለት አይደለም። አንድ ክርስቲያን ችግር ሲገጥመው ‘ይሖዋ ቀደም ሲል ለሠራሁት ኃጢአት እየቀጣኝ ይሆናል’ ብሎ ማሰብ የለበትም። (ያዕቆብ 1:13) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ፣ የፈጸምነው ድርጊት የሚያስከትልብንን መዘዝ እንዳንቀምስ አይከላከልልንም። ፍቺ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ በሰዎች ዘንድ የነበረንን አመኔታ ወይም ክብር ማጣት፤ እነዚህ ነገሮች በሠራነው ኃጢአት ምክንያት የሚመጡ ልናስወግዳቸው የማንችላቸው መዘዞች ናቸው። ይሖዋ ንጉሥ ዳዊትን ከቤርሳቤህና ከኦርዮ ጋር በተያያዘ ለፈጸመው ኃጢአት ይቅር ካለው በኋላም እንኳ ድርጊቱ ካስከተለበት ከባድ መዘዝ እንዳልታደገው አስታውስ።—2 ሳሙኤል 12:9-12

19-21. (ሀ) በዘሌዋውያን 6:1-7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሕግ ተበዳዩንም ሆነ በዳዩን ወገን የሚጠቅመው እንዴት ነው? (ለ) በሠራነው ኃጢአት ምክንያት ሌሎች ተጎድተው ከሆነ ይሖዋ ምን እርምጃ እንድንወስድ ይፈልጋል?

19 በፈጸምነው ድርጊት ሌሎች ሰዎችም ተጎድተው ከሆነ የሠራነው ኃጢአት ተጨማሪ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዘሌዋውያን ምዕራፍ 6 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት። በዚህ ምዕራፍ ላይ የሰፈረው የሙሴ ሕግ አንድ ሰው የሌላውን እስራኤላዊ ንብረት በመስረቅ፣ በመቀማት ወይም አጭበርብሮ በመውሰድ ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ ሊደረግ ስለሚገባው ነገር ይናገራል። ኃጢአተኛው ጥፋተኛ መሆኑን ሊክድ ብሎም በሐሰት እስከ መማል ሊደርስ ይችላል። በዚህ ጊዜ ድርጊቱ ሲፈጸም ያየ ምሥክር ላይኖር ይችላል። ይሁንና ከጊዜ በኋላ በደሉን የፈጸመው ሰው ሕሊናው ይወቅሰውና ኃጢአቱን ይናዘዛል። ይህ ሰው የአምላክን ምሕረት ማግኘት እንዲችል ኃጢአቱን ከመናዘዝ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ነገሮች ማድረግ ይጠበቅበታል፦ የወሰደውን መመለስ፣ የሰረቀውን ንብረት ዋጋ 20 በመቶ የሚሆን ካሳ መክፈልና የበደል መሥዋዕት እንዲሆን አውራ በግ ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር። ከዚያም ሕጉ እንደሚለው ካህኑ “በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል፤ እሱም [በደሉ] ይቅር ይባልለታል።”—ዘሌዋውያን 6:1-7

20 ይህ ሕግ የአምላክን ምሕረት የሚያንጸባርቅ ዝግጅት ነው። ተበዳዩን ወገን ይጠቅማል፤ ምክንያቱም የጠፋበትን ንብረት መልሶ ያገኛል፣ ጥፋተኛው ሰው የሠራውን ኃጢአት ያመነለት መሆኑም ደስ እንደሚያሰኘው የታወቀ ነው። በተጨማሪም ሕጉ፣ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ተገቢውን እርምጃ ለሚወስደው ግለሰብም ትልቅ ጥቅም አለው። ምክንያቱም ጥፋቱን አምኖ ለመስተካከል ፈቃደኛ ካልሆነ የአምላክን ምሕረት ማግኘት አይችልም።

21 ምንም እንኳ እኛ በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ይህ ሕግ ይሖዋ ስለ ይቅር ባይነት ያለውን አመለካከት ጨምሮ የእሱን አስተሳሰብ ይበልጥ እንድንረዳ ያግዘናል። (ቆላስይስ 2:13, 14) እኛ በሠራነው ኃጢአት ሌሎች ተጎድተው ከሆነ አምላክ የበደልናቸውን ሰዎች ለመካስ የምንችለውን ሁሉ ጥረት ስናደርግ ሲያይ በጣም ይደሰታል። (ማቴዎስ 5:23, 24) ይህም ጥፋታችንን አምነን መቀበልና የበደልነውን ሰው ይቅርታ መጠየቅን ሊጨምር ይችላል። ከዚያም በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋ ይቅር እንዲለን መለመን እንችላለን፤ ይህን ስናደርግ ይሖዋ ምሕረቱን እንዳገኘን እንድንተማመን ያደርገናል።—ዕብራውያን 10:21, 22

22. የይሖዋ ምሕረት ምን ነገርንም ሊያካትት ይችላል?

22 እንደ ማንኛውም አፍቃሪ ወላጅ ሁሉ ይሖዋም ምሕረት በሚያደርግበት ጊዜ ተግሣጽ ሊሰጥም ይችላል። (ምሳሌ 3:11, 12) ንስሐ የገባ አንድ ክርስቲያን የሽምግልና፣ የጉባኤ አገልጋይነት ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት መብቱን ሊያጣ ይችላል። ከፍ አድርጎ ይመለከታቸው የነበሩትን መብቶች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ማጣቱ ከባድ ሐዘን ሊያስከትልበት ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ተግሣጽ ስለተሰጠው ይሖዋ ምሕረት አላደረገለትም ማለት አይደለም። ይሖዋ የሚገሥጸን ስለሚወደን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ተግሣጹን መቀበላችንና ተግባራዊ ማድረጋችን የሚጠቅመው እኛኑ ነው።—ዕብራውያን 12:5-11

23. የይሖዋን ምሕረት ልናገኝ እንደማንችል ሆኖ ሊሰማን የማይገባው ለምንድን ነው? የእሱን የይቅር ባይነት ባሕርይ ለመኮረጅ ጥረት ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?

23 አምላካችን ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ መሆኑን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ምንም ያህል ከባድ ስህተት ብንሠራ የይሖዋን ምሕረት ልናገኝ እንደማንችል ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ከልብ ንስሐ ከገባን፣ የሠራነውን ስህተት ለማረም አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰድንና በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ምሕረት ለማግኘት አጥብቀን ከጸለይን ይሖዋ ይቅር እንደሚለን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን። (1 ዮሐንስ 1:9) እንግዲያው እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ረገድ የይሖዋን የይቅር ባይነት ባሕርይ ለመኮረጅ ጥረት እናድርግ። ኃጢአት የማይሠራው አምላካችን ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ይቅር የሚለን ከሆነ ኃጢአተኛ የሆንነው እኛ የሰው ልጆች እርስ በርስ ይቅር ለመባባል የተቻለንን ጥረት ማድረግ አይገባንም?

a አንድ ምሁር እንደገለጹት እዚህ ላይ “እንደ ደም” ተብሎ የተተረጎመው የቀለም ዓይነት “የማይለቅ ወይም የማይደበዝዝ ነው። እርጥበት፣ ዝናብ፣ እጥበት ወይም የረጅም ጊዜ አገልግሎት ሊያስለቅቀው አይችልም።”