በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 23

‘እሱ አስቀድሞ ወዶናል’

‘እሱ አስቀድሞ ወዶናል’

1-3. የኢየሱስን ሞት ከሌላው ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

 የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ አንድ ሰው ባልሠራው ጥፋት ተወንጅሎ ከተፈረደበት በኋላ ተሠቃይቶ እንዲሞት ተደረገ። በሰው ዘር ታሪክ እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊና ጭካኔ የተሞላበት ፍርድ ሲፈረድ ይህ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አይደለም። ሆኖም ይህን የሞት ቅጣት ከሌላው ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ።

2 ይህ ሰው በከፍተኛ ሥቃይ እያጣጣረ በነበረባቸው የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በሰማይ ላይ የታየው ክስተት ራሱ በወቅቱ የተፈጸመው ሁኔታ ልዩ ትርጉም እንዳለው የሚጠቁም ነበር። ገና እኩለ ቀን የነበረ ቢሆንም ምድሪቱ በድንገት በጨለማ ተዋጠች። አንድ ታሪክ ጸሐፊ ‘የፀሐይ ብርሃን እንደጠፋ’ ዘግቧል። (ሉቃስ 23:44, 45) ይህ ሰው እስትንፋሱ ሊያቆም ሲል “ተፈጸመ!” በማለት የማይረሳ ቃል ተናግሯል። በእርግጥም ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት አንድ አስደናቂ ነገር ፈጽሟል። ይህ ሰው ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ ያሳየው ፍቅር በታሪክ ዘመናት ሁሉ የትኛውም ሰው ካሳየው ፍቅር የላቀ ነው።—ዮሐንስ 15:13፤ 19:30

3 ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚያ የመከራ ቀን (ኒሳን 14, 33 ዓ.ም.) ብዙ ሥቃይ እንደደረሰበትና እንደሞተ የሚገልጸውን ታሪክ የማያውቅ የለም ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ብዙዎች ልብ የማይሉት አንድ ትልቅ እውነታ አለ። ኢየሱስ ብዙ ሥቃይ የደረሰበት ቢሆንም እንኳ ከእሱ ይበልጥ የተሠቃየ አንድ አካል አለ። እንዲያውም በዚያ ዕለት የበለጠ መሥዋዕት የከፈለውና አቻ የማይገኝለት ፍቅር ያሳየው እሱ ነው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ ፍቅር ያሳየ ማንም የለም። ይህን ፍቅሩን የገለጸው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ የምናገኘው መልስ ቀጥሎ ለምንመረምረው በጣም አስፈላጊ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ማለትም ለይሖዋ ፍቅር ተስማሚ መግቢያ ነው።

ከሁሉ የላቀው የፍቅር መግለጫ

4. አንድ ሮማዊ ወታደር ኢየሱስ ተራ ሰው አለመሆኑን እንዲገነዘብ ያደረገው ምንድን ነው? ምን ብሎስ ተናግሯል?

4 በኢየሱስ ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ ያስፈጸመው ሮማዊ መቶ አለቃ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ምድሪቱን በሸፈነው ጨለማም ሆነ ከሞተ በኋላ በተከሰተው ኃይለኛ የምድር ነውጥ በጣም ተደናግጦ ነበር። “ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 27:54) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ተራ ሰው አልነበረም። ይህ ወታደር የተሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ ያስገደለው የልዑሉን አምላክ አንድያ ልጅ ነው። አምላክ ልጁን ምን ያህል ይወደው ነበር?

5. ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከአባቱ ጋር የኖረበት ጊዜ ምን ያህል ረጅም እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

5 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “የፍጥረት ሁሉ በኩር” ሲል ይጠራዋል። (ቆላስይስ 1:15) የይሖዋ ልጅ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እንኳ ይኖር እንደነበረ ልብ በል። እንግዲያው ኢየሱስ ከአባቱ ጋር የኖረው ለምን ያህል ጊዜ ነው? አንዳንድ ሳይንቲስቶች ጽንፈ ዓለም የ13 ቢሊዮን ዓመታት ዕድሜ እንዳለው ይገምታሉ። ይህ ምን ያህል ረጅም ዘመን እንደሆነ መገመት ትችላለህ? አንድ የጠፈር አካላት ማዕከል፣ ሰዎች የዚህን ዘመን ርዝማኔ እንዲረዱ ለማገዝ 110 ሜትር ርዝመት ያለው የጊዜ ሰንጠረዥ አዘጋጅቶ ነበር። ጎብኚዎች ይህን የጊዜ ሰንጠረዥ ተከትለው ሲጓዙ እያንዳንዱ እርምጃቸው የሚወክለው ከጽንፈ ዓለም ዕድሜ 75 ሚሊዮን ዓመት የሚሆነውን ጊዜ ነው። የሰው ዘር ምድር ላይ የኖረበት አጠቃላይ ዘመን፣ በጊዜ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ ከአንዲት የፀጉር ቅንጣት በማትበልጥ መስመር ተወክሏል። እንግዲህ ይህን የሳይንቲስቶቹን ግምት ይዘን ብንነሳ እንኳ የይሖዋን ልጅ ዕድሜ ለማስቀመጥ ሙሉው የጊዜ ሰንጠረዥ አይበቃም! ኢየሱስ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ምን ሲያከናውን ነበር?

6. (ሀ) የይሖዋ ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ምን ሲያከናውን ነበር? (ለ) ይሖዋና ልጁ ምን ዓይነት ወዳጅነት አላቸው?

6 የአምላክ ልጅ “የተዋጣለት ሠራተኛ” በመሆን አባቱን በደስታ ሲያገለግል ነበር። (ምሳሌ 8:30) መጽሐፍ ቅዱስ “[ያለኢየሱስ] ወደ ሕልውና የመጣ አንድም ነገር የለም” ሲል ይገልጻል። (ዮሐንስ 1:3) በመሆኑም ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ወደ ሕልውና ያመጣው ከልጁ ጋር አብሮ በመሥራት ነው። እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ አሳልፈው ይሆን! በወላጅና በልጅ መካከል ያለው ፍቅር እጅግ ጠንካራ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ደግሞም “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።” (ቆላስይስ 3:14) ይሖዋና ኢየሱስ ይህን ያህል ረጅም ዘመን አብረው ሲያሳልፉ በመካከላቸው ያለው ትስስር ምን ያህል የጠበቀ እንደሚሆን መገመት የሚችል ይኖራል? በእርግጥም በይሖዋ አምላክና በልጁ መካከል ያለው የጠበቀ ወዳጅነትና ፍቅር አቻ የለውም።

7. ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ይሖዋ ስለ ልጁ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው?

7 ይሁንና ይሖዋ፣ ልጁን ሰው ሆኖ እንዲወለድ ወደ ምድር ላከው። ይህን ለማድረግ ሲል የሚወደውን ልጁን ለተወሰኑ አሥርተ ዓመታት ከአጠገቡ ማጣት ግድ ሆኖበታል። ከሰማይ ሆኖ የኢየሱስን አስተዳደግ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በትኩረት ይከታተል ነበር። ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሲሆነው ተጠመቀ። ይሖዋ ስለ ልጁ ምን ተሰምቶት ነበር? “በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ራሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:17) ኢየሱስ አስቀድሞ ስለ እሱ የተነገሩትን ትንቢቶች በሙሉ በታማኝነት በመፈጸም ከእሱ የሚጠበቀውን ሁሉ እንዳከናወነ ሲመለከት አባቱ እጅግ እንደተደሰተ ምንም ጥርጥር የለውም!—ዮሐንስ 5:36፤ 17:4

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ምን ደረሰበት? በሰማይ ያለው አባቱስ ይህን ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን? (ለ) ይሖዋ ልጁ ይህ ሁሉ ሥቃይ እንዲደርስበትና እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?

8 ይሁን እንጂ ይሖዋ ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. የተፈጸመውን ሁኔታ ሲመለከት ምን ተሰምቶት ይሆን? በዚያ ሌሊት ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ሲሰጠውና ሰዎች መጥተው ሲይዙት፣ ወዳጆቹ ትተውት ሲሄዱና አላግባብ ለፍርድ ሲቀርብ ይሖዋ ምን ተሰምቶት ይሆን? ጠላቶቹ ሲያፌዙበት፣ ሲተፉበትና በቡጢ ሲመቱት፣ ጀርባው እስኪተለተል ሲገርፉት ብሎም እጅና እግሩ በእንጨት ላይ በሚስማር ሲቸነከርና ተሰቅሎ እያለ አላፊ አግዳሚው ሲሰድበው አባቱ ምን ተሰምቶት ይሆን? የሚወደው ልጁ በጭንቅ እያጣጣረ ወደ እሱ ሲጮኽ እንዲሁም የመጨረሻዋን እስትንፋስ ተንፍሶ የሞትን ጽዋ ሲጎነጭና ለመጀመሪያ ጊዜ ከሕልውና ውጪ ሲሆን ይሖዋ ምን ተሰምቶት ይሆን?—ማቴዎስ 26:14-16, 46, 47, 56, 59, 67፤ 27:38-44, 46፤ ዮሐንስ 19:1

9 ይህን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል። ይሖዋ ስሜት ያለው እንደመሆኑ መጠን ልጁ ሲሞት የተሰማው ሥቃይ በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ነው። በቃል ልንገልጸው የምንችለው ነገር ቢኖር፣ ይሖዋ ይህን ሁኔታ እንዲፈቅድ የገፋፋውን ነገር ነው። አብ እንዲህ ያለው ሥቃይ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋ በዮሐንስ 3:16 ላይ አንድ አስደናቂ ሐሳብ ገልጾልናል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትልቅ ትርጉም ያለው መልእክት ያዘለ በመሆኑ የወንጌል ፍሬ ሐሳብ ተብሎ ይጠራል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” ስለዚህ ይሖዋ ይህን እንዲፈቅድ ግድ ያለው ፍቅር ነው። ይሖዋ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ለእኛ ሲል እንዲሠቃይና እንዲሞት በማድረግ ያሳየን ፍቅር ከዚህ ቀደም ከታዩት የፍቅር መግለጫዎች ሁሉ የላቀ ነው።

“አምላክ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል”

የመለኮታዊ ፍቅር ትርጉም

10. ሰዎች ምን ማግኘት ይሻሉ? “ፍቅር” የሚለው ቃል ትርጉምስ ምን እየሆነ መጥቷል?

10 “ፍቅር” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? የሰው ልጆች ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ፍቅር ነው። ሰዎች ከልደት እስከ ሕልፈት ፍቅርን ይሻሉ፣ ፍቅርን ሲያገኙ ሕይወታቸው ያብባል፣ ፍቅርን ሲያጡ ደግሞ ይኮሰምናሉ አልፎ ተርፎም ይሞታሉ። ያም ሆኖ ፍቅርን እንዲህ ነው ብሎ መግለጽ በጣም ያስቸግራል። እርግጥ ነው፣ ስለ ፍቅር ብዙ ተብሏል። ስለ ፍቅር ብዙ ተጽፏል፣ ብዙ ተዘፍኗል እንዲሁም ብዙ ተገጥሟል። ይሁንና ሁሉም ማለት ይቻላል፣ ፍቅርን በትክክል የሚገልጹ ሆነው አልተገኙም። እንዲያውም ስለ ፍቅር ብዙ ከመባሉ የተነሳ ትክክለኛ ትርጉሙ ግራ እያጋባ መጥቷል።

11, 12. (ሀ) ስለ ፍቅር ብዙ ትምህርት መቅሰም የምንችለው ከየት ነው? ለምንስ? (ለ) በጥንቱ የግሪክ ቋንቋ የተጠቀሱት የፍቅር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው የትኛው የፍቅር ዓይነት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ሐ) አጋፔ የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የተሠራበት ምን ዓይነት ፍቅርን ለማመልከት ነው?

11 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን በተመለከተ ግልጽ ማብራሪያ ይሰጣል። በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ “ፍቅርን ማወቅ የሚቻለው በሚያከናውነው ተግባር ብቻ ነው” በማለት ይገልጻል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ይሖዋ ለፍጥረታቱ ስላለው የጠለቀ ፍቅር ብዙ ያስተምሩናል። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ፍቅሩን በተግባር ከገለጸበት የቤዛ ዝግጅት ይበልጥ ይህን ባሕርይ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምን ነገር ይኖራል? በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ ይሖዋ ፍቅሩን በተግባር የገለጸባቸውን ሌሎች በርካታ ምሳሌዎች እንመለከታለን። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ፍቅርን” ለማመልከት የገቡትን ቃላት በመመርመር ግንዛቤያችንን ማስፋት እንችላለን። በጥንቱ የግሪክ ቋንቋ “ፍቅርን” ለማመልከት የሚያገለግሉ አራት ቃላት ነበሩ። a ከእነዚህ መካከል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሰው አጋፔ የሚለው ቃል ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ፍቅርን ለመግለጽ የሚያስችል ከዚህ የተሻለ ቃል የለም” ሲል ዘግቧል። ለምን?

12 አጋፔ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የተሠራበት በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራ ፍቅርን ለማመልከት ነው። ስለዚህ ይህ ዓይነቱ ፍቅር ለአንድ ሰው ባለን ስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የሚወዱንን ከመውደድም ያለፈ ነው፤ አንድ ሰው አስቦበትና በዓላማ የሚያሳየው የፍቅር ዓይነት ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ክርስቲያናዊ ፍቅር ፈጽሞ ከራስ ወዳድነት መንፈስ ነፃ በሆነ መንገድ የሚገለጽ ፍቅር ነው። እስቲ ዮሐንስ 3:16⁠ን በድጋሚ ተመልከት። አምላክ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ የወደደው የትኛውን “ዓለም” ነው? ከኃጢአት ሊቤዥ የሚችለውን የሰው ዘር ዓለም ነው። ይህም በኃጢአት ጎዳና እየተመላለሱ ያሉ ብዙ ሰዎችን ይጨምራል። ይህ ሲባል ይሖዋ እነዚህን ሰዎች የሚወዳቸው የቅርብ ወዳጁ አድርጎ የሚቆጥረውን ታማኙን አብርሃምን ይወድበት በነበረው መንገድ ነው ማለት ነው? (ያዕቆብ 2:23) እንደዚያ ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ቢጠይቅበትም እንኳ በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም ሰው ደግነት ያሳያል። ሁሉም ንስሐ እንዲገቡና አኗኗራቸውን እንዲለውጡ ይፈልጋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ደግሞም ብዙዎች ይህን አድርገዋል። እነዚህን ሰዎች ወዳጆቹ አድርጎ ይቀበላቸዋል።

13, 14. ክርስቲያናዊ ፍቅር በአብዛኛው ጥልቅ የመውደድ ስሜትን እንደሚያካትት የሚያሳየው ምንድን ነው?

13 ይሁንና አንዳንዶች አጋፔ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበትን መንገድ በተመለከተ ያላቸው ግንዛቤ የተሳሳተ ነው። ምንም ዓይነት ስሜት የማይንጸባረቅበት፣ እንዲሁ በደንብና በሥርዓት ብቻ የሚመራ ፍቅር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ክርስቲያናዊ ፍቅር ብዙውን ጊዜ ጥልቅ የመውደድ ስሜትን የሚያካትት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሐንስ “አብ ወልድን ይወዳል” ሲል በጻፈ ጊዜ የተጠቀመው አጋፔ የተባለውን ቃል ነው። ታዲያ ይህ ፍቅር ጨርሶ ስሜት የማይንጸባረቅበት ነው? በፍጹም፤ ኢየሱስ በዮሐንስ 5:20 ላይ ይህንኑ ሐሳብ ለመግለጽ ፊሌኦ የተባለውን የግሪክኛ ቃል መጠቀሙ ይህ ፍቅር የጠበቀ የመውደድ ስሜት የሚንጸባረቅበት መሆኑን ያሳያል። (ዮሐንስ 3:35) የይሖዋ ፍቅር ብዙውን ጊዜ ጥልቅ ስሜትን ያካተተ ነው። እንዲህ ሲባል ግን እንዲሁ በስሜት ይመራል ማለት አይደለም። ምንጊዜም ፍቅሩን የሚገልጸው ጥበብና ፍትሕ በሚንጸባረቅባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶቹ በመመራት ነው።

14 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሁሉም የይሖዋ ባሕርያት ፍጹም፣ ምንም እንከን የማይወጣላቸውና ማራኪ ናቸው። ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ ማራኪ የሆነው ግን ፍቅር ነው። የፍቅርን ያህል ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚገፋፋን ነገር የለም። የሚያስደስተው ደግሞ ከይሖዋ ባሕርያት ሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ፍቅር ነው። ይህን ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው?

“አምላክ ፍቅር ነው”

15. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ በተመለከተ ምን ይላል? ይህን አገላለጽ ለየት የሚያደርገውስ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

15 መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎቹ የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት በተለየ መልኩ ስለ ፍቅር የሚናገረው አንድ ነገር አለ። ቅዱሳን መጻሕፍት ‘አምላክ ኃይል ነው’ ወይም ‘አምላክ ፍትሕ ነው’ ወይም ደግሞ ‘አምላክ ጥበብ ነው’ አይሉም። ይሖዋ እነዚህ ባሕርያት አሉት፤ የእነዚህ ባሕርያት ዋነኛ ምንጭ እሱ ከመሆኑም በላይ በጥበብ፣ በፍትሕም ሆነ በኃይል ረገድ አቻ የለውም። አራተኛውን ባሕርይ በተመለከተ ግን “አምላክ ፍቅር ነው” የሚል ጠለቅ ያለ ትርጉም ያለው አነጋገር ተጠቅሶ እናገኛለን። b (1 ዮሐንስ 4:8) ይህ ምን ማለት ነው?

16-18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” የሚለው ለምንድን ነው? (ለ) በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ የሰው ልጅ የይሖዋን የፍቅር ባሕርይ ለመግለጽ ተስማሚ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 “አምላክ ፍቅር ነው” ሲባል “አምላክ ማለት ፍቅር ማለት ነው፤ ፍቅር ማለት አምላክ ማለት ነው” እንደማለት ያህል እንደሆነ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ይሖዋን እንደ አንድ ረቂቅ የሆነ ባሕርይ አድርገን ልንወስደው አይገባም። ከፍቅር በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ስሜቶችና ባሕርያት ያሉት አምላክ ነው። ይሁንና ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህን ጥቅስ አስመልክቶ ሲናገር “አምላክ ሁለንተናው ፍቅር ነው፤ ፍቅር ማንነቱ ነው” ብሏል። ነጥቡን በዚህ መንገድ ጠቅለል አድርጎ መግለጽ ይቻላል፦ የይሖዋ ኃይል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ያስችለዋል። ፍትሑና ጥበቡ ደግሞ ድርጊቱን ይመሩለታል። ለድርጊት የሚያነሳሳው ግን ፍቅር ነው። በተጨማሪም ሌሎቹን ባሕርያቱን የሚጠቀምባቸው ፍቅሩን በሚያንጸባርቅ መንገድ ነው።

17 ብዙውን ጊዜ ይሖዋ የፍቅር ተምሳሌት እንደሆነ ተደርጎ ይነገራል። በመሆኑም በመሠረታዊ ሥርዓት ስለሚመራው የፍቅር ዓይነት ማወቅ ከፈለግን ስለ ይሖዋ መማር ያስፈልገናል። እርግጥ ነው፣ ሰዎችም ይህን ግሩም ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን እያከናወነ በነበረበት ወቅት ልጁን “ሰውን በመልካችን እንደ አምሳላችን እንሥራ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 1:26) በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የማፍቀር ችሎታ ያላቸውና በዚህ ረገድ አምላካቸውን መምሰል የሚችሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያቱን ለመግለጽ የተለያዩ ፍጥረታትን ምሳሌ አድርጎ እንደተጠቀመ አስታውስ። ይሁንና ጎላ ብሎ የሚታየውን ባሕርይውን ማለትም ፍቅሩን ለመግለጽ ምሳሌ አድርጎ የተጠቀመው በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን የሰውን ልጅ ነው።—ሕዝቅኤል 1:10

18 በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራና ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር የምናሳይ ከሆነ ከሁሉ የላቀውን የይሖዋ ባሕርይ እያንጸባረቅን ነው ማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:19) ይሁን እንጂ ይሖዋ አስቀድሞ የወደደን እንዴት ነው?

ቀድሞ የወደደን ይሖዋ ነው

19. በይሖዋ የፍጥረት ሥራ ውስጥ ፍቅር ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

19 ፍቅር ምንጊዜም የነበረ የይሖዋ ባሕርይ ነው። ለመሆኑ ይሖዋ ለመፍጠር እንዲነሳሳ የገፋፋው ምንድን ነው? ብቸኝነት ተሰምቶት ወይም አብሮት የሚሆን ፈልጎ አይደለም። ይሖዋ ምንም የሚጎድለው ነገር ስለሌለ ከሌላ የሚፈልገው አንዳች ነገር የለም። የሕይወትን ስጦታ የሚያደንቁ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታትን በመፍጠር የሕይወትን ጣዕም እንዲቀምሱ ያደረገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። “ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ የሆነው” አንድያ ልጁ ነው። (ራእይ 3:14) ከዚያም ይሖዋ አንድያ ልጁን ዋና ሠራተኛ አድርጎ በመጠቀም ከመላእክት አንስቶ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና አምጥቷል። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ቆላስይስ 1:16) መላእክት ነፃነት፣ የማሰብ ችሎታና ስሜት ያላቸው ኃያል መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው፤ በመሆኑም እርስ በርሳቸው በተለይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመመሥረት አጋጣሚ አግኝተዋል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ይሖዋ አስቀድሞ ስለወደዳቸው እነሱም ይወዱታል።

20, 21. አዳምና ሔዋን ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ፍቅር የሚያሳዩ ምን ነገሮችን ተመልክተዋል? ሆኖም ይሖዋ ላሳያቸው ፍቅር ምን ምላሽ ሰጡ?

20 የሰው ልጆችንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አዳምና ሔዋን ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ፍቅሩን በብዙ መንገዶች አሳይቷቸዋል። መኖሪያቸው በነበረችው ኤደን ገነት ውስጥ የሚያዩት ነገር ሁሉ ፈጣሪያቸው ለእነሱ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቅ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ አምላክ በስተ ምሥራቅ፣ በኤደን የአትክልት ስፍራ ተከለ፤ የሠራውንም ሰው በዚያ አስቀመጠው” ይላል። (ዘፍጥረት 2:8) ውብ የሆነ የአትክልት ስፍራ ወይም መናፈሻ አይተህ ታውቃለህ? በጣም የማረከህ ነገር ምንድን ነው? በዛፎች መካከል አልፎ የሚመጣው የፀሐይ ብርሃን? በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ የሚያማምሩ አበቦች? እየተንሿሿ የሚወርደው ጅረት? የአእዋፍ ዝማሬ ወይም የተለያዩ ነፍሳት የሚያሰሙት በጣም የሚመስጥ ድምፅ? ወይስ የዛፎቹ፣ የፍራፍሬዎቹና የአበቦቹ መዓዛ? በእርግጥም እንዲህ ያለ የአትክልት ስፍራ ያስደስታል፤ ያም ቢሆን በዛሬው ጊዜ፣ በኤደን የነበረውን የአትክልት ስፍራ የሚወዳደር መናፈሻ ሊኖር አይችልም። ለምን?

21 ያንን የአትክልት ስፍራ ያዘጋጀው ይሖዋ ራሱ ነው! በቃላት ልንገልጸው ከምንችለው በላይ እጅግ ውብ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ለዓይን የሚማርኩ ዛፎችና ግሩም ጣዕም ያላቸው ፍሬዎች የሞሉበት ነበር። ይህ ሰፊ የአትክልት ስፍራ በቂ ውኃ ያገኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ አስደናቂ የሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት እንስሳት ይርመሰመሱበት ነበር። አዳምና ሔዋን እርካታ የሚያስገኝ ሥራንና ፍጹም የሆነ ወዳጅነትን ጨምሮ በሕይወታቸው እንዲደሰቱ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ተሟልተውላቸው ነበር። ይሖዋ አስቀድሞ የወደዳቸው በመሆኑ እነሱም በአጸፋው ሊወድዱት ይገባ ነበር። ይሁንና ይህን ሳያደርጉ ቀሩ። የሰማይ አባታቸውን በፍቅር ተነሳስተው ሊታዘዙት ሲገባ ራስ ወዳድ በመሆን ዓመፁበት።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 2

22. ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን በኤደን ባመፁ ጊዜ የወሰደው እርምጃ ፍቅሩ ታማኝ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?

22 ይህ ይሖዋን እጅግ እንዳሳዘነው ምንም ጥርጥር የለውም! ይሁን እንጂ ይህ ዓመፅ ልቡ በሰው ልጆች ላይ እንዲጨክን አድርጎታል? በፍጹም! መጽሐፍ ቅዱስ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል። (መዝሙር 136:1) በመሆኑም የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውን የአዳምና የሔዋን ዘሮች ለመዋጀት የሚያስችል ፍቅራዊ ዝግጅት እንደሚያደርግ ወዲያውኑ አስታወቀ። ቀደም ሲል እንዳየነው ይህ ዝግጅት የሚወደውን ልጁን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ከፍተኛ መሥዋዕት መክፈል ጠይቆበታል።—1 ዮሐንስ 4:10

23. ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ምንድን ነው? የሚቀጥለው ምዕራፍ ለየትኛው ጥያቄ መልስ ይሰጣል?

23 አዎን፣ ይሖዋ ከመጀመሪያ አንስቶ ቀዳሚ በመሆን ለሰው ልጆች ፍቅሩን አሳይቷል። ይሖዋ ‘አስቀድሞ እንደወደደን’ የሚያሳዩ በርካታ ሁኔታዎች አሉ። ፍቅር ባለበት ሰላምና ደስታ ስለሚኖር ይሖዋ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ መገለጹ ምንም አያስደንቅም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ይሁን እንጂ እዚህ ላይ አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ይነሳል። በእርግጥ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ይወደናል? ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።

a “መውደድ (እንደ ቅርብ ወዳጅ ወይም ወንድም አድርጎ መመልከት)” የሚል ትርጉም ያለው ፊሌኦ የተባለው ግስ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተሠርቶበታል። ስቶርጊ የተባለው ቃል የጠበቀ ቤተሰባዊ ፍቅርን ያመለክታል፤ በ2 ጢሞቴዎስ 3:3 ላይ በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደሚጠፋ የተገለጸው የፍቅር ዓይነት ይህ ነው። ኤሮስ ወይም በተቃራኒ ፆታዎች መካከል በሚኖረው መሳሳብ የሚፈጠረው ፍቅር በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አልተጠቀሰም፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የሚናገርባቸው ቦታዎች አሉ።—ምሳሌ 5:15-20

b ከዚህ ጋር ተመሳሳይ አገላለጽ የሚጠቀሙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። ለምሳሌ ያህል “አምላክ ብርሃን ነው” እና “አምላካችን የሚባላ እሳት ነው” የሚሉ ጥቅሶች እናገኛለን። (1 ዮሐንስ 1:5፤ ዕብራውያን 12:29) ይሁን እንጂ እነዚህ አገላለጾች ይሖዋን የሚያነጻጽሩት ከቁሳዊ ነገሮች ጋር በመሆኑ ዘይቤያዊ አነጋገሮች መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። ይሖዋ ቅዱስና ጻድቅ ስለሆነ በብርሃን ሊመሰል ይችላል። “ጨለማ” ወይም ርኩሰት በእሱ ዘንድ የለም። ኃይሉን በመጠቀም ማጥፋት የሚችል በመሆኑም ከእሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል።