በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 12

“አምላክ ፍትሕ ያዛባል?”

“አምላክ ፍትሕ ያዛባል?”

1. ግፍ ሲፈጸም ስናይ ምን ሊሰማን ይችላል?

 አንዲት አረጋዊት መበለት ያጠራቀሟትን ገንዘብ ሰው አጭበርብሮ ወሰደባቸው። አንድ አራስ ልጅ አውላላ ሜዳ ላይ ተጥሎ ተገኘ። አንድ ሰው ባልሠራው ወንጀል ተከሶ ለእስር ተዳረገ። እንዲህ ስለመሳሰሉት ድርጊቶች ስትሰማ ምን ይሰማሃል? እነዚህ ነገሮች አእምሮህን እንደሚረብሹት የታወቀ ነው፤ ደግሞም አያስገርምም። የሰው ልጅ በተፈጥሮው ትክክል ወይም ስህተት ብሎ ለሚያስበው ነገር ጠንከር ያለ ስሜት አለው። በመሆኑም ግፍ ሲፈጸም ስናይ ያናድደናል። ግፍ የተፈጸመበት ሰው እንዲካስና በዳዩ ትክክለኛውን ቅጣት እንዲያገኝ እንፈልጋለን። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን ‘ለመሆኑ አምላክ ይህን ግፍ ያያል? የሚያይ ከሆነስ ለምን እርምጃ አይወስድም?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

2. ዕንባቆም ሲፈጸም ስላየው ግፍ ምን ተሰምቶት ነበር? ይሖዋስ ያልገሠጸው ለምንድን ነው?

2 ከጥንት ጀምሮ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በተለያዩ ጊዜያት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አንስተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ዕንባቆም “ለምን በደል ሲፈጸም እንዳይ ታደርገኛለህ? ጭቆናንስ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ የሚፈጸመው ለምንድን ነው? ጠብና ግጭትስ ለምን በዛ?” ሲል ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዕንባቆም 1:3) ዕንባቆም በቅንነት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በማቅረቡ ይሖዋ አልገሠጸውም፤ ምክንያቱም ሰዎች የፍትሕ ባሕርይ እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸው እሱ ራሱ ነው። አዎን፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የእሱን ፍጹም ፍትሕ እንድናንጸባርቅ አድርጎ ፈጥሮናል።

ይሖዋ ግፍን ይጠላል

3. ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ያውቃል ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይመለከታል። መጽሐፍ ቅዱስ በኖኅ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛና የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ እንደሆነ ተመለከተ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:5) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ተመልከት። ብዙውን ጊዜ ስለ ፍትሕ መጓደል ያለን ግንዛቤ በሰማናቸው ወይም ባየናቸው አንዳንድ ክስተቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በጣም ውስን ነው። በአንጻሩ ግን ይሖዋ በመላው ምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ይመለከታል! ከዚህም በላይ የሰዎችን የልብ ዝንባሌ ማለትም ከሚፈጽሟቸው ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በስተ ጀርባ ያለውን መጥፎ አስተሳሰብ ሁሉ ያያል።—ኤርምያስ 17:10

4, 5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ግፍ ለሚፈጸምባቸው ሰዎች እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በራሱ በይሖዋ ላይስ በደል የተፈጸመው እንዴት ነው?

4 ይሁን እንጂ ይሖዋ በምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ከማየት ባሻገር በዚህ ሳቢያ ለሚሠቃዩት ሰዎች ያስባል። ሕዝቦቹ “በሚጨቁኗቸውና በሚያንገላቷቸው [ጠላት ብሔራት] የተነሳ ሲቃትቱ” ይሖዋ ያዝን ነበር። (መሳፍንት 2:18) አንዳንድ ሰዎች የፍትሕ መጓደል የዕለት ተዕለት ክስተት ሲሆንባቸው ሁኔታውን እየተላመዱት ስለሚሄዱ በደል እየተፈጸመባቸው ላሉ ሰዎች ያላቸው አዘኔታ እንደሚቀንስ አስተውለህ ይሆናል። ይሖዋ ግን እንዲህ አይደለም! በመላው ምድር ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ለ6,000 ዓመታት ሲመለከት የቆየ ቢሆንም እንዲህ ላለው ድርጊት ያለው ጥላቻ አልቀነሰም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “ውሸታም ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች” እና “ባወራ ቁጥር ውሸት የሚናገር ሐሰተኛ ምሥክር” በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ መሆናቸውን ይገልጽልናል።—ምሳሌ 6:16-19

5 በተጨማሪም ይሖዋ የእስራኤልን ጨቋኝ ገዢዎች አጥብቆ እንዳወገዘ ልብ በል። “ትክክል የሆነውን ነገር [“ፍትሕን፣” አ.መ.ት] ማወቅ አይገባችሁም?” ሲል በነቢዩ አማካኝነት ጠይቋቸዋል። ሥልጣናቸውን ምን ያህል አላግባብ እየተጠቀሙበት እንዳሉ ኃይለኛ መልእክት ባላቸው ቃላት ከገለጸላቸው በኋላ እነዚህ ብልሹ መሪዎች ምን እንደሚጠብቃቸው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም። ክፉ ድርጊት በመፈጸማቸው፣ በዚያን ጊዜ ፊቱን ይሰውርባቸዋል።” (ሚክያስ 3:1-4) ይህ ሁኔታ ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን ምን ያህል እንደሚጠላ የሚያሳይ ነው! እንዲህ ያለው በደል በራሱም ላይ ደርሷል! ሰይጣን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይሖዋን ሲነቅፈው ኖሯል። (ምሳሌ 27:11) ከዚህም በተጨማሪ ‘ምንም ኃጢአት ያልሠራው’ ልጁ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ በተገደለበት ጊዜ የተፈጸመው ከሁሉ የከፋ ግፍ ይሖዋን በእጅጉ አሳዝኖታል። (1 ጴጥሮስ 2:22፤ ኢሳይያስ 53:9) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ግፍ በሚፈጸምባቸው ሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ይህ ሁኔታ በጣም ያሳስበዋል።

6. ግፍ ሲፈጸም ስናይ ምን ሊሰማን ይችላል? ለምንስ?

6 ይሁንና ግፍ ሲፈጸም ስናይ ወይም በራሳችን ላይ በደል ሲደርስብን መበሳጨታችን ወይም ማዘናችን ያለ ነገር ነው። የተፈጠርነው በአምላክ አምሳል ሲሆን ኢፍትሐዊ የሆነ ድርጊት ደግሞ ከይሖዋ ባሕርይ ጋር ጨርሶ አይሄድም። (ዘፍጥረት 1:27) ታዲያ ይሖዋ ፍትሕ ሲጓደል እያየ እርምጃ የማይወስደው ለምንድን ነው?

ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥያቄ

7. በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የተሰነዘረውና በአገዛዙ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ የተነሳው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

7 አምላክ የፍትሕ መጓደል እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት፣ ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው አንድ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ቀደም ሲል እንዳየነው ፈጣሪ ምድርንም ሆነ በእሷ ላይ የሚኖሩትን ሁሉ የመግዛት መብት አለው። (መዝሙር 24:1፤ ራእይ 4:11) ይሁን እንጂ በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ የተሰነዘረ ከመሆኑም ሌላ በአገዛዙ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው ሰው አዳም መኖሪያው በሆነችው ገነት ውስጥ ከነበረ አንድ ዛፍ እንዳይበላ አምላክ አዝዞት ነበር። ይህን ትእዛዝ ጥሶ ፍሬውን ቢበላስ? አምላክ “በእርግጥ ትሞታለህ” ሲል አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) አምላክ ለአዳምም ሆነ ለሚስቱ ለሔዋን የሰጠው ትእዛዝ ከባድ አልነበረም። ሆኖም ሰይጣን፣ አምላክ ፍሬውን እንዳይበሉ የከለከላቸው አላግባብ እንደሆነ ሔዋንን አሳመናት። ከፍሬው ብትበላስ? ሰይጣን እንዲህ በማለት ዓይን ያወጣ ውሸት ነገራት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።”—ዘፍጥረት 3:1-5

8. (ሀ) ሰይጣን ለሔዋን የነገራት ነገር ምን መልእክት ያዘለ ነው? (ለ) ሰይጣን ከአምላክ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያነሳው ምን ላይ ነው?

8 ሰይጣን እንዲህ ብሎ ሲናገር ይሖዋ ሔዋንን የደበቃት ትልቅ ቁም ነገር እንዳለ ብቻ ሳይሆን እንደዋሻትም መናገሩ ነበር። ይሖዋ በሚለው ስም የሚጠራውን አምላክ መልካምነት እንድትጠራጠር አደረጋት። ሰይጣን በዚህ መንገድ በአምላክ ስም ላይ ከባድ ነቀፋ ሰነዘረ። ከዚህም ሌላ በይሖዋ ሉዓላዊነት ማለትም በሚገዛበት መንገድ ላይ ጥያቄ አስነሳ። ሰይጣን ጥያቄ ያነሳው ‘አምላክ ሉዓላዊ ነው ወይስ አይደለም?’ በሚለው ሐቅ ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ያነሳው ጥያቄ ‘አምላክ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑ ተገቢ ነው? አገዛዙስ ትክክለኛ ነው?’ የሚል ነው። በሌላ አነጋገር ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢነቱን በአግባቡ ወይም ለተገዢዎቹ በሚበጅ መንገድ አልተጠቀመበትም ብሎ የተናገረ ያህል ነበር።

9. (ሀ) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ማመፃቸው ምን አስከተለባቸው? ሰይጣን የተናገረው ውሸት ምን ወሳኝ ጥያቄዎች አስነስቷል? (ለ) ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?

9 አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ በመብላት በአምላክ ላይ ዓመፁ። በዚህም ምክንያት አምላክ አስቀድሞ በደነገገው መሠረት ሞት ተበየነባቸው። ሰይጣን የተናገረው ውሸት መልስ የሚያሻቸው ወሳኝ ጥያቄዎችን አስነስቷል። ይሖዋ የሰውን ልጅ የመግዛት መብት አለው ወይስ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው? ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢነቱን የሚጠቀመው ለሌሎች በሚበጅ መንገድ ነው? ይሖዋ ሁሉን ማድረግ የሚያስችለውን ኃይሉን ተጠቅሞ እነዚህን ዓመፀኞች ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው ይችል ነበር። ሆኖም ጥያቄ የተነሳው በአምላክ ኃይል ላይ ሳይሆን በስሙ ማለትም በአገዛዙ ላይ ነው። ስለዚህ አዳምን፣ ሔዋንንና ሰይጣንን ወዲያውኑ ማጥፋት የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ አይሆንም። እንዲያውም እንዲህ ያለው እርምጃ የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት ይበልጥ አጠያያቂ ሊያደርግ ይችል ነበር። የሰው ልጆች ያለአምላክ እርዳታ በተሳካ ሁኔታ ራሳቸውን ማስተዳደር ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት የግድ ጊዜ መስጠት ያስፈልግ ነበር።

10. ታሪክ የሰውን ልጅ አገዛዝ በተመለከተ ምን ሐቅ አረጋግጧል?

10 ታዲያ ያለፈው የሰው ልጅ ታሪክ ምን ሐቅ አረጋግጧል? ባለፉት ሺህ ዓመታት ሰዎች አምባገነናዊም ሆኑ ዲሞክራሲያዊ አገዛዞችን እንዲሁም የሶሻሊዝምና የኮሚኒዝም ሥርዓትን ጨምሮ ብዙ ዓይነት መስተዳድሮችን ሞክረዋል። “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት የሰው ልጅ ራሱን በራሱ ለመግዛት ያደረገው ሙከራ ያስከተለውን ውጤት ጠቅለል አድርገው ይገልጻሉ። (መክብብ 8:9) ነቢዩ ኤርምያስ “ይሖዋ ሆይ፣ የሰው መንገድ በራሱ እጅ እንዳልሆነ በሚገባ አውቃለሁ። አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” ሲል መናገሩ ትክክል ነው።—ኤርምያስ 10:23

11. ይሖዋ የሰው ዘር መከራ እንዲደርስበት የፈቀደው ለምንድን ነው?

11 ይሖዋ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ ብዙ ሥቃይና መከራ እንደሚያስከትል መጀመሪያውኑም ያውቅ ነበር። ታዲያ ይህ እንደሚሆን እያወቀ የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀዱ ኢፍትሐዊ አይሆንም? በፍጹም! ለምሳሌ ያህል፣ ልጅህ በጣም በመታመሙ ሕይወቱ እንዲተርፍ የግድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልገዋል እንበል። ቀዶ ሕክምናው ልጅህን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንደሚያሠቃየው ስለምታውቅ ሁኔታው በጣም እንደሚያስጨንቅህ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሕክምናው ልጅህን ከበሽታው እንደሚገላግለውና በቀሪው ሕይወቱ ጤናማ ሆኖ እንዲኖር እንደሚረዳውም ታውቃለህ። በተመሳሳይም አምላክ ሰብዓዊ አገዛዝ ሥቃይና መከራ እንደሚያስከትል ያውቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:16-19) ሆኖም ዘላቂና አስተማማኝ እፎይታ እንዲገኝ ከተፈለገ የሰው ልጆች በሙሉ ዓመፅ የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት እንዲመለከቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያውቅ ነበር። በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ ለዘለቄታው ወይም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ ሊያገኝ የሚችለው በዚህ መንገድ ነው።

የሰውን ልጅ ታማኝነት በተመለከተ የተነሳ ጥያቄ

12. በኢዮብ ሁኔታ እንደታየው ሰይጣን የሰው ልጆችን ምን ብሎ ከስሷል?

12 ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳ አንድ ሌላ ጥያቄም አለ። ሰይጣን የአምላክ አገዛዝ ትክክለኛና ጻድቅ ስለመሆኑ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት የይሖዋን ስም ከማጥፋቱም በተጨማሪ የአምላክ አገልጋዮች ለፈጣሪያቸው ያላቸው ታማኝነት አጠያያቂ እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ የእነሱንም ስም አጥፍቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰይጣን ጻድቁን ሰው ኢዮብን አስመልክቶ ለይሖዋ ምን ብሎ እንደተናገረ ልብ በል፦ “እሱን፣ ቤቱንና ያለውን ነገር ሁሉ በአጥር ከልለህ የለም? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፤ ከብቱም በምድሪቱ ላይ በዝቷል። ሆኖም እስቲ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”—ኢዮብ 1:10, 11

13. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያቀረበው ክስ ምን መልእክት ያዘለ ነው? ይህ ክስ ሁሉንም የሰው ዘር የሚመለከት ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

13 እንደ ሰይጣን አባባል ከሆነ ኢዮብ ለአምላክ ያደረ ሰው ሊሆን የቻለው ይሖዋ ጥበቃ ስላደረገለትና ስለተንከባከበው ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ የሆነው በፍቅር ተነሳስቶ ሳይሆን በጥቅም ተደልሎ ነው። በመሆኑም ሰይጣን፣ ‘አምላክ በረከቱን ቢነፍገው ኢዮብ ፈጣሪውን ይሰድባል’ ሲል ተከራክሯል። ሰይጣን፣ ኢዮብ “በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” እንደነበረና በዚህ ረገድ ጎልቶ የሚታይ ግሩም ምሳሌ እንደሆነ ያውቅ ነበር። a ስለሆነም ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ማድረግ ቻለ ማለት የተቀረውን የሰው ዘር በተመለከተም ምን ትርጉም ሊያስተላልፍ እንደሚችል አስብ። በመሆኑም ሰይጣን ያነሳው ጥያቄ የሁሉንም የአምላክ አገልጋዮች ታማኝነት የሚመለከት ነው። እንዲያውም “[ሰው] ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል” በማለት ጥያቄው ኢዮብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሰው ልጆችንም የሚመለከት እንደሆነ ጠቁሟል።—ኢዮብ 1:8፤ 2:4

14. ሰይጣን በሰዎች ላይ የሰነዘረውን ክስ በተመለከተ ታሪክ ምን ይመሠክራል?

14 እንደ ኢዮብ ያሉ ብዙ ሰዎች መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንደተገኙ ታሪክ ይመሠክራል። ይህ ደግሞ የሰይጣንን አባባል ውድቅ ያደርገዋል። እነዚህ ታማኝ አገልጋዮች የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኙ ሲሆን ይህ አቋማቸው ሰይጣን ‘የሰው ልጆች መከራ ከደረሰባቸው አምላክን ከማገልገል ወደኋላ ይላሉ’ ሲል ላነሳው ክርክር አጥጋቢ መልስ አስገኝቷል። (ዕብራውያን 11:4-38) አዎን፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክን ለመተው ፈቃደኞች አልሆኑም። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው እንኳ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጣቸው በመተማመን ይበልጥ ወደ እሱ ተጠግተዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:7-10

15. አምላክ ቀደም ሲል የወሰዳቸውንና ወደፊት የሚወስዳቸውን የፍርድ እርምጃዎች አስመልክቶ ምን ጥያቄ ሊነሳ ይችላል?

15 ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍትሕ የተገለጠው ሉዓላዊነቱንና ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸውን በተመለከተ ከተነሱት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም። ይሖዋ በግለሰቦችም ሆነ በብሔራት ላይ የበየነውን ፍርድ የሚገልጹ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን። በተጨማሪም ወደፊት የሚወስዳቸውን የፍርድ እርምጃዎች የሚገልጹ ትንቢቶች አሉ። ይሖዋ ቀደም ሲል የወሰዳቸውም ሆኑ ወደፊት የሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ትክክለኛ ናቸው ብለን ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

የአምላክ ፍትሕ የላቀ የሆነው ለምንድን ነው?

ይሖዋ በምንም ዓይነት ‘ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አያጠፋም’

16, 17. ሰዎች ከእውነተኛ ፍትሕ ጋር በተያያዘ ያላቸው ግንዛቤ ውስን መሆኑን የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

16 ይሖዋ “መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸው” መባሉ የተገባ ነው። (ዘዳግም 32:4) ማንኛችንም ብንሆን ስለ ራሳችን እንዲህ ብለን መናገር አንችልም። ምክንያቱም ስለ ማንኛውም ነገር ያለን ግንዛቤ ውስን በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር መለየት ሊሳነን ይችላል። አብርሃምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሰዶም በክፋት ድርጊቶች ተሞልታ የነበረ ቢሆንም እንኳ አብርሃም፣ ከተማዋን እንዳያጠፋት ይሖዋን ተማጽኖት ነበር። “በእርግጥ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህ?” ሲል ይሖዋን ጠይቋል። (ዘፍጥረት 18:23-33) ይሖዋ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር አያጠፋም። በሰዶም ላይ ‘እሳትና ድኝ ያዘነበው’ ጻድቁ ሎጥና ልጆቹ ሸሽተው ወደ ዞአር ከተማ ከገቡ በኋላ ነበር። (ዘፍጥረት 19:22-24) በአንጻሩ ደግሞ ዮናስ አምላክ ለነነዌ ሰዎች ምሕረት በማድረጉ ‘እጅግ ተቆጥቶ’ ነበር። ዮናስ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚጠፉ ተናግሮ ስለነበር ከልብ ንስሐ ቢገቡም እንኳ መጥፋት አለባቸው የሚል አቋም ይዞ ነበር።—ዮናስ 3:10 እስከ 4:1

17 ይሖዋ፣ ፍትሑ ክፉዎችን ለማጥፋት ብቻ ሳይሆን ጻድቃንንም ለማዳን የቆመ እንደሆነ ለአብርሃም አረጋግጦለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ዮናስ፣ ይሖዋ መሐሪ አምላክ መሆኑን መገንዘብ አስፈልጎት ነበር። ክፉ ሰዎች አካሄዳቸውን ካስተካከሉ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ ነው። (መዝሙር 86:5) ይሖዋ ለሥልጣናቸው እንደሚሰጉ ሰብዓዊ ገዢዎች፣ ኃይሉን በማሳየት ሌሎችን ለማስፈራራት ሲል ብቻ የቅጣት እርምጃ አይወስድም፤ ወይም እንደ ደካማ ሊያስቆጥረኝ ይችላል በሚል ስሜት ርኅራኄ ከማሳየት ወደኋላ አይልም። ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል በቂ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው።—ኢሳይያስ 55:7፤ ሕዝቅኤል 18:23

18. ይሖዋ በስሜት ብቻ ተገፋፍቶ እንደማይፈርድ የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥቀስ።

18 ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲሁ በስሜት የሚመራ አምላክ አይደለም። ሕዝቡ በጣዖት አምልኮ ተዘፍቀው በነበረበት ጊዜ ይሖዋ “እንደ መንገድሽም እፈርድብሻለሁ፤ ለፈጸምሻቸውም አስጸያፊ ድርጊቶች ሁሉ ተጠያቂ አደርግሻለሁ። ዓይኔ አያዝንልሽም፤ ደግሞም አልራራልሽም፤ የተከተልሽው መንገድ የሚያስከትለውን ውጤት አመጣብሻለሁ” ሲል ጥብቅ አቋሙን ገልጿል። (ሕዝቅኤል 7:3, 4) በመሆኑም ሰዎች ከመጥፎ ድርጊታቸው አልታረም ሲሉ ይሖዋ ተገቢውን ቅጣት ይሰጣቸዋል። ሆኖም ይሖዋ ፍርድ የሚሰጠው በቂ በሆነ ማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ነው። ለምሳሌ ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ ታላቅ ጩኸት በሰማ ጊዜ “ድርጊታቸው እኔ ዘንድ እንደደረሰው ጩኸት መሆን አለመሆኑን ለማየት ወደዚያ እወርዳለሁ” ሲል ተናግሯል። (ዘፍጥረት 18:20, 21) ይሖዋ ተጨባጭ ማስረጃ ሳያገኙ ለመፍረድ እንደሚቸኩሉ ሰዎች ባለመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! በእርግጥም ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ” ነው።—ዘዳግም 32:4

በይሖዋ ፍትሕ ላይ እምነት ይኑርህ

19. ይሖዋ የፍትሕ እርምጃ የሚወስድበትን መንገድ በተመለከተ አእምሯችን ውስጥ አንዳንድ ጥያቄዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን?

19 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ቀደም ባሉት ዘመናት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ለሚነሳው ለእያንዳንዱ ጥያቄ መልስ ይሰጣል ብለን ልንጠብቅ አንችልም። በተጨማሪም ይሖዋ ወደፊት በግለሰብም ይሁን በቡድን ደረጃ በሰዎች ላይ ስለሚወስደው የፍርድ እርምጃ ዝርዝር መረጃ አናገኝም። እንዲህ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወይም ትንቢቶች ግልጽ በማይሆኑልን ጊዜ “የሚያድነኝን አምላክ በትዕግሥት እጠብቃለሁ” ሲል እንደጻፈው እንደ ነቢዩ ሚክያስ ዓይነት ታማኝነት ልናሳይ እንችላለን።—ሚክያስ 7:7

20, 21. ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛ እርምጃ እንደሚወስድ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ትክክለኛውን እርምጃ እንደሚወስድ ልንተማመን እንችላለን። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚፈጸሙ አንዳንድ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ችላ የተባሉ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል። (ሮም 12:19) ይሖዋን በትዕግሥት የምንጠባበቅ ከሆነ “አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም!” ሲል እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ጠንካራ እምነት እንዳለን እናሳያለን።—ሮም 9:14

21 እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ብዙ ሰዎች በሚደርስባቸው “ግፍ” እና ጭቆና እየተሠቃዩ ነው። (መክብብ 4:1) ይሁን እንጂ ይሖዋ አልተለወጠም። አሁንም ቢሆን ግፍን የሚጠላ ሲሆን በዚህ ምክንያት እየተሠቃዩ ላሉ ሰዎች ከልብ ያዝናል። ይሖዋንና ሉዓላዊነቱን በታማኝነት ከደገፍን በመንግሥቱ አማካኝነት ግፍንና ጭቆናን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7

a ይሖዋ ኢዮብን አስመልክቶ ሲናገር “በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም” ብሏል። (ኢዮብ 1:8) ስለሆነም ኢዮብ የኖረው ዮሴፍ ከሞተ በኋላ ሆኖም ሙሴ የእስራኤል መሪ ሆኖ ከመሾሙ በፊት እንደሆነ መገመት ይቻላል። ስለዚህ በወቅቱ ንጹሕ አቋምን በመጠበቅ ረገድ እንደ ኢዮብ ያለ ሰው አልነበረም ሊባል ይችላል።