በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል ሦስት

የስሜት መጎዳት—‘ቅር የተሰኘንበት ነገር’ ሲኖር

የስሜት መጎዳት—‘ቅር የተሰኘንበት ነገር’ ሲኖር

“በጉባኤያችን ያለች አንዲት እህት ገንዘብ እንደሰረቅኳት በመግለጽ ወነጀለችኝ፤ ይሁንና ይህ እውነት አልነበረም። ሌሎች የጉባኤው አባላትም ይህን ሲሰሙ ወገን መያዝ ጀመሩ። ውሎ አድሮ ይህች እህት ንጹሕ መሆኔን የሚያሳይ አዲስ መረጃ እንዳገኘች በመግለጽ ይቅርታ ጠየቀችኝ። ሆኖም ከደረሰብኝ ነገር አንጻር ፈጽሞ ይቅር ልላት እንደማልችል ተሰማኝ።”—ሊንዳ

አንተስ የእምነት አጋሯ ባደረገችው ነገር ስሜቷ በጥልቅ እንደተጎዳው እንደ ሊንዳ ተሰምቶህ ያውቃል? የሚያሳዝነው ነገር አንዳንዶች በሌሎች ድርጊት በጣም ከመረበሻቸው የተነሳ መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ተናግቷል። አንተስ ያጋጠመህ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ነው?

‘ከአምላክ ፍቅር ሊለየን የሚችል’ አለ?

ስሜታችንን የጎዳውን የእምነት አጋራችንን ይቅር ማለት ከባድ ሊሆንብን እንደሚችል አይካድም። ክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደድ አለባቸው። (ዮሐንስ 13:34, 35) አንድ የእምነት ባልንጀራችን ከበደለን ግን ይህ ከባድ ሐዘንና ሥቃይ ሊያስከትልብን ይችላል።—መዝሙር 55:12

እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች አንዳቸው ሌላውን ‘ቅር የሚያሰኙበት’ ጊዜ ሊኖር እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ቆላስይስ 3:13) ያም ሆኖ እንዲህ ያለ ሁኔታ በእኛ ላይ ሲደርስ ይህን መወጣት በጣም ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ ሊረዳን የሚችል ነገር ይኖር ይሆን? እስቲ ሦስት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመልከት፦

የሰማዩ አባታችን ሁሉንም ነገር ያውቃል። ይሖዋ የሚደርስብንን ማንኛውንም በደልና ይህ የሚያስከትልብንን ሥቃይ ጨምሮ ሁሉንም ነገር ይመለከታል። (ዕብራውያን 4:13) ከዚህም በላይ ይሖዋ ሥቃያችን ይሰማዋል። (ኢሳይያስ 63:9) “መከራ ወይም ጭንቀት” ወይም ማንኛውም ነገር ሌላው ቀርቶ የእሱ አገልጋይ የሆነ ሰው እንኳ ‘ከእሱ ፍቅር እንዲለየን’ ፈጽሞ አይፈቅድም። (ሮም 8:35, 38, 39) ታዲያ እኛስ ምንም ነገር ወይም ማንም ሰው በእኛና በይሖዋ መካከል እንዲገባ ባለመፍቀድ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ አይኖርብንም?

ይቅር ማለት ድርጊቱ ትክክል መሆኑን አያሳይም። የበደሉንን ይቅር በምንልበት ጊዜ ድርጊታቸውን አቅልለን መመልከታችን ወይም ችላ ብለን ማለፋችን አሊያም ደግሞ የሠሩት ነገር ትክክል እንደሆነ መግለጻችንና ለጥፋታቸው ምክንያት መፍጠራችን አይደለም። ይሖዋ ኃጢአትን ፈጽሞ ባይደግፍም እንኳ ይቅር ለማለት የሚያስችል ምክንያት ካለ ይቅር እንደሚል አስታውስ። (መዝሙር 103:12, 13፤ ዕንባቆም 1:13) ይሖዋ ሌሎችን ይቅር እንድንል ሲያበረታታን እሱን እንድንመስለው እየጠየቀን ነው። እሱ ‘ለዘላለም ቂም አይዝም።’—መዝሙር 103:9፤ ማቴዎስ 6:14

ቂም አለመያዝ የሚጠቅመው እኛኑ ነው። በምን መንገድ? ቀጥሎ የቀረበውን ሁኔታ ለማሰብ ሞክር። አንድ ኪሎ ገደማ የሚመዝን ድንጋይ ክንድህን ዘርግተህ ይዘሃል እንበል። ድንጋዩን ለጥቂት ጊዜ ይዘህ መቆየት አይከብድህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ረዘም ላለ ጊዜ ይህን ለማድረግ ብትሞክርስ? ምን ያህል ጊዜ ይዘኸው መቆየት ትችላለህ? ለጥቂት ደቂቃዎች? ለአንድ ሰዓት? ወይስ ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ? ሰዓቱ ሲረዝም ክንድህ በጣም እንደሚዝል ጥርጥር የለውም! እርግጥ ነው፣ የድንጋዩ ክብደት አልተለወጠም። ይሁን እንጂ ድንጋዩን ይዘኸው በቆየህ መጠን ይበልጥ እየከበደህ ይሄዳል። ቂም በመያዝ ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ቅያሜያችን ያን ያህል ከባድ ባይሆንም እንኳ ቂም ይዘን በቆየን መጠን ራሳችንን ይበልጥ እየጎዳን እንሄዳለን። እንግዲያው ይሖዋ ቂም እንዳንይዝ የሚያበረታታን መሆኑ አያስገርምም። በእርግጥም ቂም አለመያዝ የሚጠቅመው ራሳችንን ነው።—ምሳሌ 11:17

ቂም አለመያዝ የሚጠቅመው እኛኑ ነው

“ይሖዋ ራሱ ያነጋገረኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ”

ሊንዳ የእምነት ባልንጀራዋ ባደረገችው ነገር ቂም ይዛ እንዳትቀጥል የረዳት ምንድን ነው? ከረዷት ነገሮች አንዱ፣ ይቅር እንድንል ምክንያት በሚሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰሏ ነው። (መዝሙር 130:3, 4) ሊንዳ ይቅርታ ለማድረግ ይበልጥ ያነሳሳት፣ እኛ ሌሎችን ይቅር የምንል ከሆነ ይሖዋም በምላሹ ይቅር እንደሚለን ማወቋ ነው። (ኤፌሶን 4:32 እስከ 5:2) እነዚህ ጥቅሶች ምን ያህል እንደነኳት ስትገልጽ “ይሖዋ ራሱ ያነጋገረኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ” ብላለች።

ከጊዜ በኋላ ሊንዳ ቅሬታዋን ማንሳት ችላለች። ቅር ያሰኘቻትን እህት በነፃ ይቅር ያለቻት ሲሆን አሁን የቅርብ ጓደኛዋ ሆናለች። ሊንዳም ይሖዋን ማገልገሏን ቀጥላለች። አንተም እንዲሁ እንድታደርግ ይሖዋ ሊረዳህ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ሁን።