በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል ሁለት

ጭንቀት—‘በየአቅጣጫው እንደቆሳለን’

ጭንቀት—‘በየአቅጣጫው እንደቆሳለን’

“እኔና ባሌ በትዳር ዓለም 25 ዓመታት ካሳለፍን በኋላ ጋብቻችን በፍቺ ፈረሰ። ልጆቼ እውነትን ተዉ። እኔም ከባድ የጤና ችግሮች አጋጠሙኝ። ከዚያም በመንፈስ ጭንቀት ተዋጥኩ። ሰማይ ምድሩ ተደፋብኝ፤ ምንም ነገር መቋቋም እንደማልችል ሆኖ ተሰማኝ። ወደ ስብሰባዎች መሄድ አቆምኩ፤ እንዲሁም ከጉባኤው ጋር ማገልገል ተውኩ።”—ጁን

የአምላክን ሕዝቦች ጨምሮ ማንኛውም ሰው ጭንቀት ሊያጋጥመው ይችላል። መዝሙራዊው ‘በጭንቀት እንደተዋጠ’ ገልጿል። (መዝሙር 94:19) ኢየሱስም በፍጻሜው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ‘በኑሮ ጭንቀት’ የተነሳ ይሖዋን ማገልገል ተፈታታኝ ሊሆንባቸው እንደሚችል ተናግሯል። (ሉቃስ 21:34) አንተስ ምን ይሰማሃል? ከኢኮኖሚ፣ ከቤተሰብ ወይም ከጤና ጋር የተያያዙ ችግሮች ከአቅምህ በላይ ሆነውብሃል? ታዲያ ይሖዋ እነዚህን ችግሮች እንድትቋቋም የሚረዳህ እንዴት ነው?

“ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል”

ጭንቀትን በራሳችን መቋቋም አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በየአቅጣጫው እንደቆሳለን፣’ ‘ግራ እንጋባለን’ እንዲሁም ‘በጭንቀት እንዋጣለን’ በማለት ጽፏል። ያም ቢሆን “መፈናፈኛ አናጣም፣” “መውጫ ቀዳዳ አናጣም” እንዲሁም “አንጠፋም” በማለት አክሎ ተናግሯል። ታዲያ ለመጽናት ምን ይረዳናል? የሚረዳን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላካችን ከይሖዋ የሚገኘው “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል” ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:7-9

ቀደም ባሉት ጊዜያት ይሖዋ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ” የሆነውን ኃይል የሰጠህ እንዴት እንደሆነ ትዝ ይልሃል? አንድ የሚያበረታታ ንግግር መስማትህ ለይሖዋ ታማኝ ፍቅር ያለህ አድናቆት እንዲጨምር እንዴት እንደረዳህ ታስታውሳለህ? ሌሎችን ስለ ገነት ተስፋ ስታስተምር በይሖዋ ተስፋዎች ላይ ያለህ እምነት እንደጎለበተ ትዝ ይልሃል? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝና እምነታችንን ለሌሎች ስናካፍል የኑሮን ጭንቀቶች ለመቋቋም የሚያስችለን ብርታት እንዲሁም ይሖዋን በደስታ ለማገልገል የሚረዳን የአእምሮ ሰላም እናገኛለን።

“ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”

በሁሉም አቅጣጫ ፋታ እንደሌለህ ቢሰማህ የሚያስገርም አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን እንድንፈልግና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የምናከናውንበት ቋሚ ፕሮግራም እንዲኖረን ይጠብቅብናል። (ማቴዎስ 6:33፤ ሉቃስ 13:24) ይሁንና የሚደርስብህ ተቃውሞ፣ ጤናህ መታወኩ ወይም የቤተሰብ ችግሮች ኃይልህን እንዳሟጠጡት የሚሰማህ ከሆነስ? አሊያም ደግሞ ሰብዓዊ ሥራህ ከጉባኤው ጋር ማሳለፍ የምትፈልገውን ጊዜ የሚሻማና የሚያዝልህ ቢሆንስ? የሚጠበቅብህ ነገር ብዙ፣ ያለህ ጊዜና ጉልበት ደግሞ በጣም ትንሽ በመሆኑ ነገሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑ ሊሰማህ ይችላል። እንዲያውም ይሖዋ ከአንተ ብዙ እንደሚጠብቅብህ ይሰማህ ይሆናል።

ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ ይረዳል። ፈጽሞ ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። ደግሞም ሰውነታችን በሚዝልበትና በውጥረት በምንዋጥበት ወቅት ይህን ሁኔታ ለማሸነፍ ጊዜ እንደሚያስፈልገን ያውቃል።—መዝሙር 103:13, 14

ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ኤልያስን ይሖዋ እንዴት እንደተንከባከበው እንመልከት። ኤልያስ ተስፋ ቆርጦና በፍርሃት ተውጦ ወደ ምድረ በዳ በሸሸበት ጊዜ ይሖዋ ተግሣጽ በመስጠት ወደ ሥራ ምድቡ እንዲመለስ አዘዘው? በፍጹም። ይሖዋ ሁለት ጊዜ መልአክ ላከለት፤ መልአኩም ኤልያስን በቀስታ ቀስቅሶ የሚበላው ምግብ ሰጠው። እንደዚያም ሆኖ ከ40 ቀናት በኋላ ኤልያስ እንደገና በጭንቀትና በፍርሃት ተዋጠ። ታዲያ ይሖዋ እሱን ለመርዳት ያደረገው ሌላ ነገር ይኖር ይሆን? በመጀመሪያ፣ ለእሱ ጥበቃ ማድረግ እንደሚችል አሳየው። ሁለተኛ፣ ‘ዝግ ባለና ለስለስ ባለ ድምፅ’ ኤልያስን አጽናናው። በመጨረሻም ይሖዋ፣ እሱን በታማኝነት የሚያመልኩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች አገልጋዮች እንዳሉት ለኤልያስ ገለጸለት። ብዙም ሳይቆይ ኤልያስ እንደቀድሞው ቀናተኛ ነቢይ ሆኖ ማገልገሉን ቀጠለ። (1 ነገሥት 19:1-19) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ኤልያስ በጭንቀት ተውጦ በነበረበት ወቅት ይሖዋ በትዕግሥትና በርኅራኄ አጽናንቶታል። ይሖዋ አሁንም አልተለወጠም። እኛንም ልክ እንደዚሁ ይንከባከበናል።

ለይሖዋ ልትሰጠው ስለምትችለው ነገር ስታስብ ምክንያታዊ ሁን። ዛሬ ማድረግ የምትችለውን ነገር ቀደም ሲል ታደርግ ከነበረው ጋር አታወዳድር። በምሳሌ ለማስረዳት፦ ለብዙ ወራት ወይም ዓመታት ልምምድ ማድረጉን ያቆመ አንድ ሯጭ፣ ድንገት ተነስቶ እንደቀድሞው መሮጥ እንደማይችል የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ጥንካሬውንና ብቃቱን ቀስ በቀስ ለማጎልበት የሚረዱት ትናንሽ ግቦችን በማውጣት መለማመድ ይጀምራል። ክርስቲያኖችም እንደ ሯጮች ናቸው። አእምሯቸው አንድ ግብ ላይ እንዲያተኩር አድርገው ራሳቸውን ያሠለጥናሉ። (1 ቆሮንቶስ 9:24-27) አንተስ አሁን ባለህበት ሁኔታ ልትደርስበት እንደምትችል የሚሰማህን አንድ መንፈሳዊ ግብ ለምን አታወጣም? ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ የመገኘት ግብ ልታወጣ ትችላለህ። ግብህ ላይ ለመድረስ እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። መንፈሳዊ ጥንካሬ እያገኘህ ስትሄድ ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰህ ታያለህ።’ (መዝሙር 34:8) ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ለማሳየት የምታደርገው ማንኛውም ነገር፣ የቱንም ያህል ትንሽ ቢመስልም በእሱ ፊት ትልቅ ቦታ እንዳለው አስታውስ።—ሉቃስ 21:1-4

ይሖዋ ፈጽሞ ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም

“የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል”

ይሖዋ፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጁን ወደ እሱ እንድትመለስ ኃይል የሰጣት እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እንዲረዳኝ አዘውትሬ እጸልይ ነበር። ከዚያም የልጄ ባለቤት፣ ባለሁበት ከተማ ስለሚካሄድ አንድ ትልቅ ስብሰባ ነገረችኝ። እኔም በስብሰባው ላይ አንዱን ቀን ለመገኘት ወሰንኩ። ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር እንደገና መገናኘት ምንኛ ያስደስታል! ይህ ስብሰባ የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል። አሁን እንደቀድሞው ይሖዋን በደስታ እያገለገልኩ ነው። ሕይወት ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኖልኛል። ራሴን ማግለል ወይም ብቻዬን መጓዝ እንደማልችል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን ገብቶኛል። ጊዜው ሳይረፍድ መመለስ በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”