በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሰውነትህ ክብካቤ ማድረግ

ለሰውነትህ ክብካቤ ማድረግ

ምዕራፍ 6

ለሰውነትህ ክብካቤ ማድረግ

1, 2. የሰው አካል የላቀ የሥራ ውጤት የሆነው በምን መንገዶች ነው?

ጠቢቡ ሰሎሞን የሰውን አካል መስኮትና መዝጊያ ባለው ቤት መስሎታል። ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላም ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “መኖሪያችን” በማለት ጠርቶታል። (መክብብ 12:3–7፤ 2 ቆሮንቶስ 5:1, 2) ሰውነትህ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥህ ከተፈለገ ልክ እንደ ቤት ተገቢው ክብካቤ ያስፈልገዋል።

2 ሰውነትህን በመንከባከብ ረገድ ምን ዓይነት ባለቤት ነህ? የተሰጠህን ሰውነት ታደንቃለህን? የሰው አካል ከምድር ፍጥረቶች ሁሉ የላቀ የሥራ ውጤት ስለሆነ ማድነቅ ይገባሃል። ሰውነትህ ሰው ከፈለሰፈው ከማንኛውም ኮምፒተር ወይም መኪና ይልቅ እጅግ የተወሳሰበ ነው። ሆኖም በደንብ ተቀናጅቶ የሚሠራ፣ አስደናቂ ቅልጥፍና ያለውና ከፍተኛ የመተጣጠፍ ችሎታ ያለው ነው። አጥንቶች፣ ጡንቻዎች፣ የደም ሥሮች፣ የነርቭ አውታር ሥርዓቶችና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እንደ አንድ አካል በመሆን እንዴት ተባብረው እንደሚሠሩ ማሰብ ራሱ ያስጨንቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም ያው “አንድ አካል” ነው። ይህንን ብናስታውስና “አንድም ብልት ቢሰቃይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሰቃያሉ” የሚለውንም አባባል እውነተኝነት ብንገነዘብ መልካም ነው። አዎን፤ በብዙ ቢልዮን የሚቆጠሩ ሴሎች ቢኖሩትም አካል አንድ ነው። ከወጣትነትህና ከመላው ሕይወትህ ከሁሉ የላቀውን ጥቅም ለማግኘት ከፈለግህ ማንኛውንም የሰውነትህን ክፍል ችላ ለማለት አትችልም።—1 ቆሮንቶስ 12:12, 14–26

3–5. (ሀ) ለሰውነትህ በምታደርገው ክብካቤ የሚነካው ማን ነው? (ሮሜ 14:7, 8) (ለ) ለሰውነት ክብካቤ ማድረግን በተመለከተ ‘የዘራነውን የምናጭደው’ እንዴት ነው?

3 ሆኖም ለሰውነትህ የምትችለውን ክብካቤ ሁሉ ልታደርግ የምትፈልግበት የበለጠና ከፍ ያለ ምክንያት አለ። ይህም ለፈጣሪህና ለወላጆችህ ክብር ለማምጣትና ለጎረቤቶችህ መልካም ለማድረግ ልትጠቀምበት እንድትችል ነው። ጥሩ ክብካቤ የማይደረግለት ቤት ፕላን ነዳፊውን ወይም ሕንፃ ተቋራጩን አያስመሰግንም። የፈራረሰ፣ የቆሸሸ ወይም መጥፎ ጠረን ያለው ቤት አካባቢውን በሙሉ ያስጠላል። እኛም ለሰውነታችን ተገቢ ክብካቤ ሳናደርግ ከቀረን ሁኔታችን ያው ነው።

4 “ሰው የዘራውን ያጭዳል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ለሰውነትህ በምታደርገው ክብካቤ ላይም ይሠራል። (ገላትያ 6:7) ‘የሚታጨደው’ ፍሬ ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑ የተመካው በእኛው ላይ ነው። አንድ ሰው የዘራውን የሚያጭድበት ጊዜ እስኪያረጅ ድረስ ላይቆይ ይችላል። የዘራውን ማጨድ የሚጀምረው ከዚያ በጣም ቀደም ብሎ ነው፤ አንዳንድ ጊዜም ገና በወጣትነት ይጀምራል።

5 ለአካል ክብካቤ ማድረግ “መታመምን ለማስቀረት” ብቻ ታስቦ የሚደረግ ነገር አይደለም። ለደስታ፣ ለጥሩ ሥራ፣ አእምሮ አጥርቶ እንዲያስብና ሰዎች ሲቀርቡህ የማትቀፍ እንድትሆን አስተዋጽኦ የሚያደርገው የደህንነት ስሜት እንዲኖርህ መፈለግ ይኖርብሃል። ታዲያ ዘወትር ትኩረትን የሚጠይቁ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

የተመጣጠነ ምግብ የሚሰጠው ጥቅም

6–8. (ሀ) ካርቦሃይድሬት ምግቦችን (ለ) ፕሮቲኖችን (ሐ) ማዕድኖችንና (መ) ቪታሚኖችን በተመለከተ የተመጣጠነ ምግብ ስለሚሰጠው ጥቅም አንዳንድ ማብራሪያዎችን ስጥ።

6 የምትበላው ምግብ ኃይል ከመስጠት የበለጠ ነገር ያደርጋል። ሰውነትህ ራሱን እንዲጠግን የሚያስፈልጉትን ነገሮች የሚያቀርብለት ይህ ምግብ ነው። በስኳር፣ በዳቦና በድንች ውስጥ እንደሚገኙት ያሉ ካርቦሃይድሬት ምግቦች ኃይል ይሰጡሃል። ይሁን እንጂ የምትበላው ምግብ በአብዛኛው ይህ ዓይነት ብቻ ቢሆንስ? በለስላሳ መጠጦችና በከረሜላ ለመዋል ብትሞክር ምን ይደርስብሃል? ሰውነትህ የየቀኑን ጥገና ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ስለሚያጣ መሰቃየት ይጀምራል።

7 ዘወትር ከወተት፣ ከአይብ፣ ከጥራጥሬ፣ ከሥጋ፣ ከዓሣና ከመሳሰሉት የሚገኘው ፕሮቲን ያስፈልግሃል። እነዚህን ምግቦች ካላገኘህ ጡንቻዎችህ ወዲያውኑ ልልና ልፍስፍስ መሆን ይጀምራሉ። ዕድገትህም ይጐተታል። ማዕድኖችም ያስፈልጉሃል፤ ምክንያቱም በምግብህ ውስጥ እነርሱ ከሌሉ ጥርሶችህ ይበሰብሳሉ፣ አጥንቶችህም ይዳከማሉ። የቅጠላ ቅጠል ምግቦች በማዕድን የበለጸጉ ናቸው። ቪታሚኖችም ያስፈልጉሃል ምክንያቱም እነዚህ ምግቦች በሰውነት ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን የሚቆጣጠሩ ኬሚካሎች ስለሆኑ ሰውነትን ከአንዳንድ በሽታዎች ይከላከሉለታል። የቪታሚኖች ዋና ምንጮች ፍራፍሬዎችና ስንዴን የመሳሰሉ እህሎች ናቸው። ለደምህና በሥጋህ ውስጥ ላለው ፈሳሽ በሙሉ መሠረቱ ውኃ ስለሆነ ብዙ ውኃም ያስፈልግሃል።

8 ስልሳ ወይም ሰባ ዓመት ዕድሜ ላይ ስትደርስ ብቻ ሳይሆን ገና በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜህ ላይ የጥሩ ወይም የመጥፎ ምግብ ውጤቶችን ልታጭድ ትችላለህ። ለተማሪዎች ሻል ያለ ምግብ ሲሰጣቸው የመማር ችሎታቸው እንደተሻሻለ የተደረገው ጥናት አሳይቷል። አሸር ባሸር መመገብ ባጠቃላይ የተጓደለ ሥራን የሚያስከትል ሲሆን ሰዎችንም በይበልጥ ለአደጋ የተጋለጡ ያደርጋቸዋል። የሰውነትን ጤናማ መልክና የተፈጥሮ ውበት በፍጥነት ያሳጣል።

ንጽሕና ለጤና አስተዋፅኦ ያደርጋል

9–14. (ሀ) አዘውትሮ ገላን መታጠብ ጤናህን የሚጠብቀው እንዴት ነው? (ለ) በግል ንጽሕናህ በኩል ያለህ ልማድ ሌሎች ለአንተ ያላቸውን አመላከከት የሚነካው እንዴት ነው? ለምንስ? (ሐ) ጥርስን አዘውትሮና በጥንቃቄ ማጽዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (መ) መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ስለ ንጽሕና ምን ይናገራል? (ዘጸአት 30:17–21፤ ማቴዎስ 6:17, 18)

9 በንጹሕ ቤት ውስጥ በመኖር የበለጠ ደስታ እንደምናገኝ ሁሉ ሰውነታችንን በንጽሕህና የምንጠብቅ ከሆነም ከሕይወት የበለጠ ደስታ እናገኛለን። አዘውትሮ ሰውነትን መታጠብ አእምሮን የሚያድስና ጤና የሚሰጥ ነው። ሰውነትህ አየር ውስጥ ካሉትና በምትይዛቸው ነገሮች ላይ ከሚገኙት ረቂቅ ተዋሕስያን ጋር ዘወትር ይገናኛል። ከነዚህም አንዳንዶቹ በሽታን ሊያመጡ ይችላሉ። ሳሙና እነዚህን ለመግደል የሚያገለግል ፀረ ጀርም ሲሆን ውኃ ደግሞ እነርሱን አጥቦ ለመውሰድ ይረዳል። በተለይ ለእጆችህ ቶሎ ቶሎ ትኩረት መስጠት ያስፈልገሃል፤ ምክንያቱም ምግብህን የምትይዘውና ሌሎችን ሰዎች ወይም እነርሱ የተጠቀሙባባቸውን ነገሮች የምትነካው በእጅህ ነው።

10 ራስህን በንጽሕና ስትይዝ ውጤቱ ለአንተ ጥሩ ስሜት ከማምጣቱም በተጨማሪ ለሚያዩህና ለሚቀርቡህ ሁሉ ሕይወትን የበለጠ አስደሳች ያደርግላቸዋል። የቆሸሸና የተዝረከረከ ቤት ብታይ በውስጡ ስለሚኖሩት ሰዎች ምን ዓይነት ግምት ያድርብሃል? ሰዎችም የሰውነትህን አያያዝ አይተው አንተን የመገመት ዝንባሌ አላቸው። በፊትህ፣ በጆሮህ፣ በአንገትህ፣ በጸጉርህ፣ በእጆችህ ላይ ወይም በጥፍሮችህ ውስጥ ቆሻሻ መታየቱ የሌሎችን ወዳጅነትና አክብሮት ሊያሳጣህ ይችላል። ራስህን በንጽሕና የምትይዝ ከሆነ ራስህ ለራስህ የበለጠ አክብሮት ይኖርሃል።

11 አንድ ሰው ብዙ የአካል እንቅስቃሴ ባያደርግም ወይም ብዙ ሥራ ባይሠራም ገላው ያልበዋል። ላብ ከተጠራቀመ ገላህ ደስ የማይል ጠረን ያመጣበታል። አዘውትረህ ሰውነትህን፣ ብብትህንና ተመሳሳይ ቦታዎችን በመታጠብህ ሰዎች ሲቀርቡህ ደስ ይላቸዋል። ንጽሕናና የተመጣጠነ ምግብ ለተሻለና ለጠራ ደምግባት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

12 ጥርሶች ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ልዩ የሰውነት ክፍሎች ናቸው። የምግብ ድቃቂዎች ሊሰገሰጉባቸው ወይም በላያቸው ሊላከኩ ይችላሉ። እነዚህ የምግብ ድቃቂዎች የሚያወጡት አሲድ ኢናሜል የተባለውን የጥርስህን የላይኛውን ሽፋን ያጠቁታል። ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከደረሱበት በኋላ፣ ምናልባት በጥቂት ወራት ውስጥ፣ ጠንካራው ኢናሜል ይቦረቦርና ጥርሱ መበስበስ ይጀምራል። ወይም የድድ መቁሰል ያስከትልና ጥርሶችህ እንዲነቃነቁ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንዶቹም ይወልቁብህ ይሆናል። የሻገተ ወይም የወለቀ ጥርስ ውበትህን ይቀንሰዋል።

13 ንጹሕ አፍ ከትንፋሽ መሽተትም ይጠብቃል። በቀን ውስጥ በርካታ ብርጭቆ ውኃ መጠጣት ለዚህ ይረዳል። አፍህ እንደ አንድ ቤት በር ወይም መግቢያ እንደሆነ አስታውስ። የቤቱ መልክና በበሩ በኩል የሚወጣው ሽታ ጥሩ ካልሆነ ሰዎች ወደ መሸሽ ያዘነብላሉ።

14 በንጽሕና ረገድ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያደርጉት ከመጠን ያለፈ አይሁን እንጂ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ንጽሕናን ያበረታታል፣ ያስተምራልም። ንጹሕ እጆችና የታጠቡ ገላዎች አንድ ሰው በመንፈሳዊ ንጹሕና የጠራ መሆኑን ለማመልከት አገልግለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስም “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” በማለት አጥብቆ መክሯል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ከውስጥ፣ በልባችንና በአእምሮአችን ንጹሆች ነንን? ታዲያ በውጪም ቢሆን ንጹሆች ለመሆን ጥረት ማድረግ አይገባንምን?

ተገቢ እረፍት አስፈላጊ ነው

15–18. (ሀ) ሰውነታችን እረፍትና እንቅልፍ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? (ለ) ብዙ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ኃይል እንዳለህ ቢሰማህም እንኳ በቂ እረፍት አለማግኘትህ እንዴት ይነካሃል? (ሐ) ለሰውነታችን ክብካቤ ማድረጋችን ለአምላክ አክብሮትን የሚያሳየው እንዴት ነው?

15 በየቀኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ የሰውነት ሴሎች ስለሚሞቱ መተካት ያስፈልጋቸዋል። ሰውነትህ በተለይ በሥራና በአካል እንቅስቃሴ ምክንያት በጡንቻዎች ውስጥ የሚጠራቀሙ ቆሻሻ ነገሮችን ያከማቻል። የድካም ስሜት እንዲሰማህ የሚያደርጉት እነዚህ ቆሻሻ ነገሮች ናቸው። ሰውነትህ የተጠራቀመውን ቆሻሻ ለማስወጣትና ሰውነትህ ጥሩ ቅርጽ እንዲኖረውና እንዲጠገን የሚያስፈልጉ አዳዲስ ሴሎችን ለመሥራት እንዲችል በቂ እረፍት ያስፈልገዋል። ማዕከላዊ የነርቭ አውታሮችህና አንጎልህም እረፍት ያስፈልጋቸዋል። እንቅልፍ ካልወሰደህ በስተቀር አንጎልህና የነርቭ አውታሮችህ ሊዝናኑ አይችሉም።

16 ወጣት ስለሆንህ ጥቂት እንቅልፍ ብቻ ካገኘሁ ይበቃኛል ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም የወጣትነት ብርታትና ጉልበት አታላይ ሊሆኑ ይችላሉ። በቂ እረፍት ባለማግኘትህ ምክንያት እየተፈጠሩ ያሉትን የብርቱ ጉዳት ምልክቶች ሊደብቁህ ይችላሉ። እንዲያውም የታዳጊ ወጣት ሰውነት የሚያስፈልገው እንቅልፍ ከአዋቂ ሰው ያነሰ ሳይሆን የበለጠ ነው። የእንቅልፍ እጦት የማሰብ ችሎታን ያዳክማል፤ መርሳትንም ያበዛል። የአንድን ሰው ንቃትና ሰውነት ለነገሮች የሚሰጠውን ፈጣን ምላሽ ዝቅ ያደርጋል። የምትጨነቅ፣ ቁንጥንጥ፣ ተነጫናጪና ከሰው ጋር መስማማት የማትችል ሰው ሊያደርግህ ይችላል። በተለይ ተጽዕኖና ውጥረት ሲደርስብህ እንዲህ እንደምትሆን የተረጋገጠ ነው።

17 ስለዚህ ሰውነትህ የሚያስፈልገውን ዕረፍት በመስጠት ተባበረው። ወላጆችህ በተወሰነ ሰዓት እንድትተኛ ሲነግሩህ የሰጡህ መመሪያ ተገቢ መሆኑን ተገንዘብ። በየምሽቱ በቂ እንቅልፍ ስታገኝ የሥራህ ፍጥነትና ጥራት ይሻሻላል። ሕይወት የበለጠ አስደሳች ይሆንልሃል፣ የጤና መታወክንም ይቀንስልሃል።

18 በአካላችን ላይ የሚታየውን የሕይወት ስጦታ የምናደንቅ ከሆነ ሰውነታችንን ለፈጣሪያችንና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል ሕይወቱን ለሰጠን ልጁ ክብር ልናውለው ይገባናል። በግዴለሽነት ወይም በሞኝነት ወይም በራስ ወዳድነት ምክንያት ሰውነታችንን አለአገባብ ልንጠቀምበት ወይም ክብካቤ ልንነፍገው አይገባንም። እንዲህ ማድረጉ ለሕይወት ሰጪአችን አክብሮት እንደጎደለን የሚያሳይ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንከተል:- “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።” ለፍቅራዊ ዝግጅቶቹ ስለምታሳዩት አድናቆት ዋጋችሁን በብዙ ይከፍላችኋል፣ ይባርካችኋልም።—1 ቆሮንቶስ 10:31

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 46 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ ለጥሩ ጤንነት አስፈላጊ ነው

[በገጽ 49 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰውነትህ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ በቂ እረፍት ያስፈልገዋል