በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለጥሩ ሕይወት ቁልፉ አደንዛዥ መድኃኒቶች ናቸውን?

ለጥሩ ሕይወት ቁልፉ አደንዛዥ መድኃኒቶች ናቸውን?

ምዕራፍ 15

ለጥሩ ሕይወት ቁልፉ አደንዛዥ መድኃኒቶች ናቸውን?

1, 2. (ሀ) አንተ በምታውቃቸው ልጆች ዘንድ አደንዛዥ መድኃኒቶችን መውሰድ ምን ያህል ተስፋፍቶ ይገኛል? (ለ) ወጣቶች አደንዛዥ መድኃኒቶችን የሚወስዱት ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ብዙዎቻችን የምንኖረው ከመድኃኒት ጋር በተቆራኘ ህብረተሰብ ውስጥ ስለሆነ በቤታችሁ እንደ ሥቃይ ማስታገሻ ያሉ መድኃኒቶች ይኖሩ ይሆናል። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የመድኃኒቶች ኢንዱስትሪ ሽያጭ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከሰላሳ እጥፍ በላይ አድጓል። ሐኪሞች በቅርብ ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “እያንዳንዱን ወንድ፣ ሴትና ሕፃን ለአንድ ወር ሙሉ ሊያነቁ ወይም ሊያፈዙ ወይም ‘ ችግሩን እንዲረሳ ሊያደርጉ’ የሚችሉ ስሜትን የሚለዋውጡ አደንዛዥ መድኃኒቶች ለሰዎች አዘዋል” በማለት ዶክተር ሚሼል ኤስ ሮዜንታል ተናግረዋል።

2 አብዛኞቹ መድኃኒቶች የሚታዘዙት ለአዋቂዎች ነው። ይሁን እንጂ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ወጣቶች ‘ለደስታ’ ብለው በዛ ያለ አደንዛዥ መድኃኒት ይወስዳሉ። ለሕክምና አገልግሎት ተብለው ያልተመረቱ እንደ ሔሮይን፣ ኤል ኤስ ዲና ማሪዋና በመሳሰሉት ሌሎች አደንዛዥ መድኃኒቶችም ይጠቀማሉ። አንዳንድ ወጣቶች “አዋቂዎች ኪኒን የሚወስዱ ከሆነ፣ ትምባሆ ካጨሱና ከሰከሩ እኔስ ለምን ማሪዋና በማጨስ ወይም አደንዛዥ መድኃኒቶች በመውሰድ ራሴን አላስደስትም?” ብለው ወደማሰብ ያዘነብላሉ። አንተስ ምን ይመስልሃል? ከሕይወትህ የተሟላ ደስታ ለማግኘት አደንዛዥ መድኃኒቶች አስፈላጊ እንደሆኑ ይሰማሃልን?

ብዙዎች የሚረባረቡባቸው መድኃኒቶች

3–9. (ሀ) “ለምርቃና” ወይም ለደስታ ተብለው የሚወሰዱት አደንዛዥ መድኃኒቶች ምንድን ናቸው? በሚጠቀሙባቸው ሰዎች ላይስ ምን ውጤት ያስከትላሉ? (ለ) እነዚህ ውጤቶች በትክክል የሚደርሱ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ በሰዎች ላይ የደረሱ ተሞክሮዎች ታውቃለህን?

3 ሰዎች “ለምርቃና” ወይም ለደስታ ብለው የሚጠቀሙባቸው ዓይነታቸው የበዛ አደንዛዥ መድኃኒቶች ወይም ዕጾች አሉ። ምናልባትም ቀደም ብለህ ስለ እነርሱ ብዙ ሰምተህ ይሆናል። ቢሆንም ጥቂት ጊዜ ወስደህ እነርሱ ምን እንደሆኑ መርምር።

4 አንዳንድ ጊዜ “አፍዛዥ” መድኃኒቶች እየተባሉ የሚጠሩት ባርቢቹሬትስ አሉ። እነዚህ ሐኪሞች እንቅልፍ ለማስወሰድ የሚያዟቸው መድኃኒቶች ናቸው። ዓይነታቸው ከሁለት ደርዘን በላይ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በያመቱ ከ476 ሜትሪክ ቶን በላይ ይመረታሉ። ከዚህ ምርት ውስጥ ከፍተኛው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲሰራጭ የሚደረግ ነው።

5 በተለምዶ “ፔፕ ፒልስ” ወይም “አነቃቂዎች” በመባል የሚታወቁ ብዙ መድኃኒቶችም አሉ። ከእነዚህ ዋነኞቹ አምፊታሚንስ የሚባሉት ናቸው። አንዳንድ ሐኪሞች የምግብን ፍላጐት ለማፈን፣ ድካምን ለመቀነስ ወይም የመንፈስን ጭንቀት ለማስታገስ ያዟቸዋል። ይሁን እንጂ በሕጋዊ መንገድ ከሚመረተው አነቃቂ መድኃኒት ግማሹ ሕጋዊ ወዳልሆነ አቅጣጫ እንደሚተላለፍ ተገምቷል።

6 በቅዠት ዓለም ውስጥ የሚገኝን ደስታ ከሚያመጡት ብዙ አደንዛዥ መድኃኒቶች ውስጥ በጣም ኃይለኛው ኤል ኤስ ዲ * ነው። በቅርብ ዓመታት “በድብቅ” የሚሠሩ ብዙ ላቦራቶሪዎች (ቤተ ሙከራዎች) ኤል ኤስ ዲን መሥራት ጀምረዋል። ኤል ኤስ ዲ በተጠቃሚዎቹ ላይ እንግዳ የሆኑ ስሜቶችን ያመጣል። በተለይ የማየት ችሎታን በጣም ይጐዳል። መድኃኒቱ ከተወሰደ ከወር በኋላም እንኳን ሳይቀር በእውኑ ዓለም የሌሉ ነገሮችን በሐሳብ የማየትና የመስማት ሁኔታና ከተሳሳተ እምነት የሚመጣ ፍርሃትን ሊያስከትል ይችላል። ሰውየው በምርቃና ላይ ሆኖ የሚያየው ቅዠት በጣም አስፈሪ ሊሆን ይችላል።

7 ካናቢስ ከተባለው ተክል የሚገኘው ማሪዋና በሰፊው ከሚሠራባቸው አደንዛዥ መድኃኒቶች አንዱ ነው። ይህን ያጨሰ ሰው አይተህ ታውቃለህን? እሱም እንደ ሌሎቹ አደንዛዥ መድኃኒቶች የስሜት መቃወስ የሚያስከትል ቢሆንም ኃይሉ ኤል ኤስ ዲ ከተባለው ትንሽ ቀለል ያለ ነው። አንድ ሰው ማሪዋናን ሲያጨስ አምስቱ ደቂቃ እንደ አንድ ሰዓት የረዘመ ሊሆንበት ይችላል። ድምፅና ቀለማት ከመጠን በላይ ጎልተውና ደምቀው ሊታዩ ይችላሉ።

8 ሔሮይን የሚቀመመው ኦፒየም ፖፒ ከተባለው ተክል ከሚገኘው ሞርፊን ከተባለው ቅመም ነው። ይህ አደንዛዥ መድኃኒት የባሰ አደገኛ ነው። ሰዎች ጥቂት ጊዜ ብቻ ደጋግመው በመርፌ ከተወጉት በኋላ ሱሰኞች ስለሚሆኑ እርሱን ካጡ ክፉኛ ይታመማሉ። ሰዎች የሔሮይን ሱሰኞች ሲሆኑ ለመማር ያላቸውን ፍላጎትና ችሎታ ሊያጠፋባቸው ይችላል። ቀስ እያለ ለሚያጠፋቸው ልማድ ባሪያ ይሆናሉ። አንድ የኒው ዮርክ ምክር ቤት አባል “ሔሮይን የትምህርት ቤቶቻችንን ያሠራር ሥርዓት አጥፍቶታል” በማለት ጽፈዋል።

9 ብዙ ሰዎች በሕይወት ውስጥ የበለጠ ደስታ ይሰጣሉ ብለው የሚያስቧቸው ሌሎች አደንዛዥ መድኃኒቶችም አሉ። ከእነዚህም አንዱ ኮኬይን ነው። በትምባሆ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን ደግሞ ሌላው ነው። በእነዚህ ነገሮች መጠቀም ይገባሃልን? ባለፈው ምዕራፍ ላይ እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱስ ሰውን ሊያዝናኑና ልብን ደስ ሊያሰኙ የሚችሉትን የአልኮል መጠጦች በልከኝነት መውሰድን አያወግዝም። ታዲያ ሕይወትን የበለጠ አርኪ ለማድረግ ሲባል በእነዚህ የተለያዩ አደንዛዥ መድኃኒቶች መጠቀም ተገቢ ወይም አስተዋይነት ነውን?

አደንዛዥ መድኃኒቶች ጥቅም አላቸውን?

10–12. (ሀ) አንድ ሐኪም አንድን ግለሰብ ለመርዳት በመድኃኒቶች ሊጠቀም የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሁን እንጂ በመድኃኒቶች ያላግባብ መጠቀም በሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትሉት እንዴት ነው?

10 በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው መድኃኒቶች ጥቅም ስላላቸው አንድ ሐኪም አንዳንድ ጊዜ ጤንነትህ ሲታወክ አንዱን መድኃኒት ያዝልህ ይሆናል። በከፍተኛ ሕመም እየተሰቃየህ ከሆነ ሐኪሙ ፋታ እንድታገኝ ሲል ሞርፊን እንድትወጋ ያዝልህ ይሆናል። ባርቢቹሬትስ (የሚያፈዝዙ) እና አምፊታሚንስ (የሚያነቃቁ) መድኃኒቶች የጤና ችግር ያለባቸውን አንዳንድ ሕመምተኞች እንደረዱ ምንም አያጠራጥርም። ሔሮይን ደግሞ በአንዳንድ ቦታዎች የማይድን ካንሰር ያለባቸው ሕመምተኞች ከሥቃይ ፋታ ለመስጠት ይሠራበታል።

11 ይሁን እንጂ በሌላ በኩል አደንዛዥ መድኃኒቶች በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ አስከፊ ጉዳት እያደረሱ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ሥቃይ ለሚያስታግሱ መድኃኒቶች ሱሰኞች የሆኑት አንድ ሚልዮን የሚያህሉ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ይህንን መድኃኒት ከመጠን በላይ በመውሰዳቸው ምክንያት በያመቱ ከ3, 000 የሚበልጡት ይሞታሉ። የሔሮይን ሱሰኛ መሆን የሚያስከትለው መዘዝ ከመጠን በላይ ከመውሰዳቸው የተነሳ በየቀኑ ብዙዎች እንዲሞቱ ማድረጉ ብቻ አይደለም። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩትን ሱሰኞች አደገኛ ወንጀለኞች አድርጓቸዋል። ሱሰኞቹ ይህን ብዙ ወጪ የሚጠይቀውን ልማዳቸውን ለመቀጠል ሲሉ በኒው ዮርክ ከተማ በየቀኑ በአማካይ ከ3, 000, 000 ዶላር በላይ የሚያወጣ ንብረት ይሰርቃሉ!

12 ይህ ምን ማለት ነው? መድኃኒቶች ሁሉ መጥፋት ይኖርባቸዋል ማለት ነውን? ብዙ መድኃኒቶች ለጥሩ ዓላማ ሊያገለግሉ ስለሚችሉ መጥፋት ይኖርባቸዋል ማለት አይቻልም። ችግሩ ግን በእነርሱ ያላግባብ ወይም ከመጠን በላይ መጠቀም መዛመቱ ነው። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው ሕክምና የሚያስፈልገው ምንም ሕመም ሳይኖርባቸውና ለሕክምና ተብሎ ከሚሰጠው በላይ አብዝተው በመውሰድ ነው። ብዙውን ጊዜ ተጠቃሚው በሕልም ዓለም ውስጥ ገብቶ ለመዋዠቅ ወይም ወደ አንድ ዓይነት ተመስጦ ለመግባት ይፈልጋል። ታዲያ ለዚህ ሲባል አደንዛዥ መድኃኒቶችን መውሰድ ተገቢ ነውን?

በአካል ላይ የሚያመጣው ጉዳት

13–17. (ሀ) በአንድ የሕክምና ጽሑፍ ውስጥ እንደተገለጸው መድኃኒቶች ሁሉ ምንድን ናቸው? (ለ) ስለዚህ ለሕክምና ጉዳይ በሚውሉበትም ጊዜ ቢሆን አውቆ የሚገባበት አደጋ የሆኑት እንዴት ነው? (ሐ) ከዚህ በታች ያሉት ጥቅሶች ለደስታ ወይም “ለሞቅታ ስሜት” ተብሎ በመድኃኒቶች ስለመጠቀም የአምላክን አመለካከት እንዴት እንደሚያሳዩ አብራራ:- 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ ሮሜ 13:13፤ 12:1

13 ብዙ መድኃኒቶች በሐኪም ትእዛዝ ብቻ ሊገኙ እንደሚችሉና እንዲያውም አንዳንዶቹ በብዙ አገሮች ከነጭራሹ የተከለከሉ መሆናቸውን ምናልባት ሳታውቅ አትቀርም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ለሁላችንም ጥበቃ ሲባል ነው። አዎን፣ መድኃኒቶች አደገኞች ሊሆኑ፤ አልፎ ተርፎም ሞትን ሊያስከትሉ ይችላሉ። በአንድ በኩል ለመፈወስ በሌላ በኩል ደግሞ ለመጉዳት ብሎም ለመግደል የሚችሉ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍ ናቸው ሊባል ይቻላል። መድኃኒቶች የተሰኘ በአንድ የፋርማኰሎጂ ፕሮፌሰር ተባባሪነት የተዘጋጀ መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:-

14 “መድኃኒቶች ሁሉ መርዝ ናቸው፣ መርዞችም ሁሉ መድኃኒት ናቸው። ‘ፖይዝን’ (‘poison’) እና ‘ፖሺን’ (‘potion’) የሚሉት የእንግሊዝኛ ቃላት ከአንድ ሥረ መሠረት የመጡ መሆናቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ‘ፋርማሲ’ እና ‘ፋርማኰሎጂ’ ለሚሉት የእንግሊዝኛ ቃላት መሠረት የሆነው ፋርማኮን የሚለው የግሪክኛ ቃል የቀድሞ ትርጉሙ የሚፈውስም ሆነ የሚገድል መጠጥ ማለት ነው።”

15 በዚህ ምክንያት በምትታመምበት ጊዜም እንኳ ቢሆን መድኃኒት መውሰድ አውቀህ የምትገባበት አደጋ አለው። ነገር ግን ሕይወትህን ስለምትወድ የመጣው ይምጣ ብለህ ከሕመሙ ለመገላገል ወይም የተጐዳ ጤንነትህን ለማሻሻል መድኃኒቱን ትወስዳለህ። ይሁን እንጂ በምርቃና የእውኑን ዓለም ለመርሳትና በሕልም ዓለም ውስጥ ለመግባት ብለህ አደንዛዥ መድኃኒት መዋጥ፣ በመርፌ መወጋት፣ ማጨስ ወይም መማግ ትክክል ይሆናልን? ይህን ከአምላክ የተሰጠህን አስደናቂ ሰውነት በዚህ መንገድ ብትጠቀምበት አድራጎትህ ከፈጣሪያችን ዓላማ ጋር ይስማማልን?

16 እስቲ ስለዚህ ጉዳይ አስብ። ለአንድ ሰው በጣም ውድ የሆነ ስጦታ ለምሳሌም አዲስ መኪና ብትሰጠውና ሰውዬው ሆነ ብሎ አላግባብ ቢጠቀምበት እንዴት ይሰማሃል? ዘይት ሳይጨምርበት ወይም ሳይለውጥለት ሊያሽከረክረው ቢሞክር እንዲሁም አዛባ ለማጋዝ ቢጠቀምበትስ? ስጦታህን እንደዚህ ላለ የማይረባ ዓላማ በማዋሉ ምናልባት ትናደድ ወይም ከሰውየው ጋር ትቀያየም ይሆናል። አይደለም እንዴ? ታዲያ “ለምርቃና” ወይም “ለመደሰት” ብለን ግሩም የሆነውን ሰውነታችንን ሳያስፈልግ በመርዝ በመሙላት ያላግባብ ብንጠቀምበት ይሖዋ አምላክ እንዴት የሚሰማው ይመስልሃል? ቃሉ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ብሎ በማበረታታት አምላክ ምን እንደሚሰማው ያስገነዝበናል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ስለዚህ “ለምርቃና” ወይም “ለመደሰት” ብለን ሰውነታችንን የሚያረክሰውን አደንዛዥ መድኃኒት ወደ አካላችን የምናስገባ ከሆነ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተን እየኖርን ሊሆን አይችልም።

17 በተጨማሪም ይህን ጉዳይ ደግሞ እስቲ አስብበት። ቀደም ብለን ፈጣሪ ስለ ስካር የሰጠውን ምክር ተወያይተንበታል። ብዙ በመጠጣቱ ምክንያት ራሱን መቆጣጠር ያቃተው ሰው ራሱን እንደሚያዋርድ፣ አብዛኛውን ጊዜም የረከሰና ቂላቂል በመሆን በዙሪያው ላሉት ሰዎች ማፈሪያ እንደሚሆን አምላክ በቃሉ ውስጥ በግልጽ አመልክቷል። ፈጣሪያችን ስካርን ማውገዙ ተገቢ ስለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ታዲያ አንድ ሰው በሔሮይን፣ በማሪዋና ወይም በሌሎች አደንዛዥ መድኃኒቶች ምክንያት ራሱን መቆጣጠር ቢሳነው የአምላክ አመለካከት የተለየ ይሆናልን? ምንም እንኳን አደንዛዥ መድኃኒት የሚያስከትለው ውጤት አልኰል ከሚያስከትለው ጋር አንድ ዓይነት ባይሆንም አንድ ሰው በአልኮል የሰከሩትን ሰዎች ያህል ወይም ከዚያ በላይ ራሱን መቆጣጠር ሊሳነው ይችላል። ስለዚህ በደስታ ለመፈንጠዝ ብለን ወደ አደንዛዥ መድኃኒቶች ዘወር ያለማለትን ጥቅም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ጥበብ ያለበትና ምክንያታዊ ምክር ልናይ እንችላለን።

ስለ ትምባሆስ ምን ሊባል ይቻላል?

18–21. (ሀ) ትምባሆ ማጨስ ለጤንነት አደገኛ መሆኑ በደንብ እየታወቀ ብዙ ሰዎች የሚያጨሱት ለምንድን ነው? (ለ) ማጨስ ለአንድ ክርስቲያን ተገቢ እንደማይሆን የሚያሳዩ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶችን ስጥ።

18 “ታዲያ ኒኮቲን የሚባለውን ጐጂ ቅመም የያዘው ትምባሆስ እንዴት ነው? በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ትልልቅ ሰዎች ለደስታ እያሉ ያጨሱታል። ይህስ ተገቢ ነውን?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚሸጡ የሲጋራ ፓኬቶች ላይ ማጨስ ለጤናህ አደገኛ ነው የሚለው ማስጠንቀቂያ እንደሚያስረዳው ማጨስ ተገቢ አይደለም። የምትኖረው በየትኛውም አገር ቢሆን ሐቁ ይኸው ነው። ታዲያ ይህን ያህል ብዛት ያላቸው ትልልቅ ሰዎች ይህን እያወቁ በማጨስ ለወጣቶች መጥፎ አርአያ የሚሆኑትና የራሳቸውንም ጤና የሚያበላሹት ለምንድን ነው? ዋናው ምክንያት ሱስ ስለያዛቸው ነው። የሳይንስ ዓለም በተሰኘው መጽሔት ላይ የቀረበ አንድ ዘገባ እንዲህ በማለት ያስረዳል:-

19 “ሱስ የሚያስይዘው . . . ቅመም ኒኮቲን ነው። ሰውነት ኒኮቲኑን ሲያጣ ‘ይራባል’ ወይም ኒኮቲኑ ይናፍቀዋል። ሰውነት በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ እስከ መታመም ይደርሳል። የሱስ ምልክቶች የሆኑት የሕመም ስሜቶች ይጀምራሉ። . . . ከእነዚህ ምልክቶች አንዳንዶቹ መፍዘዝ፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማላብና የተዛባ የልብ አመታት ናቸው።”

20 በግልጽ እንደሚታየው ማጨስ በሰውነት ያላግባብ መጠቀም ነው። ፈጣሪያችን ክርስቲያኖች ራሳቸውን እንዲያነጹ በጥብቅ ከሚያሳስባቸው ‘ሥጋን ከሚያረክሱ’ ነገሮች አንዱ ነው። ስለዚህ የሚያጨሱ ትልልቅ ሰዎች ራሳቸውን በአደንዛዥ መድኃኒቶች የሚበክሉትን ወጣቶች ለመንቀፍ በሚያስችል አቋም ላይ እንዳልሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ትክክል ነህ። ወላጆች ኒኮቲንን ወደ ውስጥ በመሳብ ራሳቸውን በመበከል የሚቀጥሉ ከሆነ ከአደንዛዥ መድኃኒቶች ስለመራቅ አስፈላጊነት የሚናገሩትን ልጆቻቸው በቁም ነገር እንዲቀበሉት እንዴት ሊጠብቁ ይችላሉ? የሆነው ሆኖ ሌሎች ምንም ያድርጉ ወይም ምንም ይበሉ እያንዳንዳችን በግል ለአድራጐታችን በአምላክ ተጠያቂዎች ነን። ማጨስ ለአንድ ክርስቲያን ተገቢ አለመሆኑን የሚያሳይ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሌላም ነገር አለ።

21 መጽሐፍ ቅዱስ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” በማለት ያዛል። (ማቴዎስ 22:39) ነገር ግን ሌሎች ባሉበት እያጨስክ ባልንጀራህን እንዴት ልትወድ ትችላለህ? ይህን ጥያቄ የምንጠይቀው ሜዲካል ትሪቢዩን የተሰኘው መጽሔት የሚያስረዳውን መሠረት በማድረግ ነው። እንዲህ ይላል:- “ሲጋራ ማጨስ የሚጎዳው ያጫሹን ጤንነት ብቻ ሳይሆን በአጫሹ አጠገብ ያሉትን የማያጨሱ ሰዎችንም ጤንነት ጭምር ሊሆን ይችላል።” አንድ ታዋቂ የሕክምና መጽሔትም “በተለይ ቦታው በቂ አየር የማይገባበት ከሆነ የማያጨሰው ሰው ከአጫሹ በሚወጣው ጪስ በጤንነቱ ላይ ጉልህ ጥቃት ሊደርስበት ይችላል” በማለት አመልክቷል። ማጨስ በአጫሹ ዙሪያ ያሉትንም የሚጎዳ ከሆነ እያጨስክ ባልንጀራህን መውደድ እንደማትችል ግልጽ አይደለምን?

ማሪዋና የተለየ ነውን?

22–25. (ሀ) ማሪዋናን በትንሹም ቢሆን መውሰድ ውጤቱ አልኰል ከሚያመጣው ውጤት የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ስለ ጎጂ ልማዶች ማስጠንቀቂያ ሲሰጠን ሕይወታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት በእርግጥ እየረዳን ያለው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 48:17፤ መዝሙር 16:11፤ ምሳሌ 3:1–7)

22 አንዳንድ ወጣቶች ማሪዋና ማጨስን የአልኰል መጠጥ ከመውሰድ ጋር ለማመሳሰል ይሞክራሉ። ወላጆቻቸው ወይም ሌሎች ትልልቅ ሰዎች አልኰል ወስደው “ሞቅ ሲላቸው” ያዩና ተመሳሳይ ውጤት ለማግኘት ማሪዋና ማጨስም ከዚህ የተለየ አይደለም ወደሚል መደምደሚያ ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ ነገሩ እንደዚህ ነውን?

23 መጽሐፍ ቅዱስ አልኰልን በልከኝነት መውሰድን ሲፈቅድ ከልክ ማለፍን ግን “ሰካሮች . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ያወግዛል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ሆኖም ብዙ ወጣቶች ማሪዋናን በልከኝነት እንደሚጠቀሙና ከስካር ጋር የሚመሳሰል ውጤት እስኪያደርስ ድረስ እንደማይወስዱት ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ማሪዋና ከአልኰል የተለየ ነው። ሰውነትህ አልኰልን በሕዋሳትህ ውስጥ እንደ “ነዳጅ” በመጠቀም ሊያቃጥለው ይችላል። አልኮል ምግብ ነው። ነገር ግን ሰውነትህ ማሪዋናን ሊጠቀምበት አይችልም። በተጨማሪም አልኰል በሰውነትም ሆነ በአንጐል ሴሎች ውስጥ ለረጅም ጊዜ አይቆይም። በሰዓታት በሚቆጠር ጊዜ ውስጥ ከሰውነት ውስጥ ተበታትኖ ይጠፋል። የማሪዋና መርዛም ቅመም ግን በፍጥነት አይለቅም፤ በሰውነትም ላይ ጎጂ ውጤት ያስከትላል። በኰሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የሐኪሞችና የቀዶ ጠጋኞች ኰሌጅ ውስጥ የሚገኙ ስድስት ዶክተሮች ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አዘጋጅ በላኩት ደብዳቤ ላይ እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር:-

“ማሪዋና በቅባት ብቻ ሊሟሙ የሚችሉና በሰውነት ውስጥና በአንጐልም ጭምር ተከማችተው ልክ እንደ ዲዲቲ ለሳምንታትና ለወራት ሊቀመጡ የሚችሉ መርዛማ ቅመሞችን ይይዛል። ሰውነት እነዚህን ቅመሞች የማከማቸት ችሎታው ከፍተኛ ስለሆነ በልማደኛ አጫሾች ላይ ቀስ እያሉ ጉዳት የሚያመጡትም በዚህ ምክንያት ነው። በሳምንት ከአንድ ጊዜ በላይ በእነዚህ ቅመሞች የሚጠቀም ማንኛውም ሰው ከእነርሱ ነፃ ሊሆን አይችልም።”

24 በመሆኑም በቱሌን ዩኒቨርስቲ አስተማሪ የሆኑት ዶክተር ሮበርት ሂዝ አልኰልን ከማሪዋና ጋር ማመሳሰል እንደ “ቂልነት” ቆጥረውታል። አልኰል “ጊዜያዊ ውጤት አለው። ማሪዋና ግን ቀጣይ ውጤት ያለውና የተወሳሰበ ነው” በማለት ተናግረዋል። የዴትሮይ ፍሪ ፕሬስ ጋዜጣ እንደሚከተለው በማለት እንደገለጸው በልከኝነትም ቢሆን በማሪዋና አዘውትሮ መጠቀም መጥፎ ውጤት ሊኖረው ይችላል:- “የሕክምና ተመራማሪዎች ማሪዋናና ታላቅ ወንድሙ [ሐሺሽ] በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜም እንኳ ቢሆን ዘወትር ከተወሰዱ ለአካላዊና ለአእምሮአዊ ጤንነት በእርግጥ ጎጂ እንደሆኑ የሚጠቁሙ አዳዲስ ግኝቶች ላይ እንደደረሱ ዘግበዋል።”

25 በእውነቱ ፈጣሪያችን የምንመራባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለሰጠን አመስጋኝ ልንሆን እንችላለን። እርሱ ይወደናል። በዚህም ምክንያት ለዘላቂ ደስታችንና ደኅንነታችን አስተዋጽኦ ከማድረግ ይልቅ ሰውነታችንን ከሚያረክሱና ከሚጎዱ ነገሮች እንድንርቅ አጥብቆ ያሳስበናል። አንዳንድ መድኃኒቶች የታመመን ሰው ሊጠቅሙ ይችሉ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ለደስታ ሲሉ ወደ እነርሱ ዘወር የሚሉትን ይጎዱአቸዋል እንጂ ምንም አይጠቅሟቸውም። ለጥሩ ሕይወት ቁልፉ አደንዛዥ ማድኃኒቶች አይደሉም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ላይሰርጂክ አሲድ ዳይኢትልአማይድ

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 108 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 113 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚልዮን የሚቆጠሩ ትልልቅ ሰዎች የሚያጨሱ መሆናቸው አንተም እንድታጨስ ምክንያት ይሆንሃልን?