በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማስተርቤሽንና ግብረ ሰዶም

ማስተርቤሽንና ግብረ ሰዶም

ምዕራፍ 5

ማስተርቤሽንና ግብረ ሰዶም

1–4. (ሀ) ማስተርቤሽን ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) አንድ ተግባር የተለመደ መሆኑ ድርጊቱን ትክክል የማያደርገው ለምንድን ነው? (ሐ) አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?

የወንዶች ልጆችና የልጃገረዶች አካላት በጉርምስና ወቅት አድገው ልጅ ለመውለድ ወደሚችሉበት ደረጃ መድረሳቸው የሚያስደንቅ አይደለምን? ከዚህ የአካል ለውጥ ጋር ስለ ተቃራኒ ፆታ ያላችሁ ዝንባሌም አብሮ ይለወጣል። መሳሳብ ይጨምራል። ብዙውን ጊዜም ወንዶች ለልጃገረዶች ልጃገረዶችም ለወንዶች ከፍተኛ ፍላጎት ያድርባቸዋል። ይሁን እንጂ በዚሁ ጊዜ በፍጥነት በመለወጥ ላይ ስላለው ሰውነታችሁ የመደነቅና ሁኔታውን የማወቅ ጉጉት ሊያድርባችሁ ይችላል። ይህንን የማወቅ ጉጉት እንዴት ልታረኩት ይገባችኋል? በፆታ ብልቶቻችሁ ሙከራ ማድረግ ይገባችኋልን? በስሜት እስክትረኩ ድረስ የፆታ ብልቶቻችሁን በአንድ ዓይነት መንገድ ማሻሻት ስህተት ይኖረዋልን?

2 ይህ አድራጎት በእንግሊዝኛ ማስተርቤሽን ተብሎ ይጠራል። ይህ አድራጎት በጣም የተለመደ ሆኖአል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አንድ ምንጭ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “በእጃችን የሚገኝ እያንዳንዱ የጥናት ዘገባ በአሥራ ሦስትና በሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ መካከል ከሚገኙት ወንዶች ልጆችና ወጣት ወንዶች መካከል ቢያንስ ቢያንስ ዘጠና አምስት በመቶው የተለያየ ርዝማኔ ላላቸው ጊዜያት በማስተርቤሽን ልማድ ውስጥ እንደሚያልፉ በግልጽ ያሳያል”። ስለ ልጃገረዶችም ይኸው ምንጭ “ከአርባ እስከ ሃምሳ በመቶዎቹ በማስተርቤሽን እርካታ እንደሚያገኙ ተደርሶበታል” ይላል። አንዳንድ ሰዎች እነዚህን አሐዞች ‘ጤናማነትን’ የሚያመለክቱ እንደሆኑና “በማስተርቤሽን ለመርካት አለመሞከር አሳሳቢ ነገር እንደሆነ” ይናገራሉ።

3 ታዲያ ምን ይመስላችኋል? በዛሬው ዓለም ውስጥ ማስተርቤሽን በጣም የተለመደ ነገር መሆኑ ድርጊቱን ተገቢና ጤናማ የሰውነት ተግባር ነው የሚለውን አስተሳሰብ ትስማሙበታላችሁን? በዛሬው ጊዜ መዋሸትና መስረቅም የተለመዱ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ የተለመዱ መሆናቸው ጤናማና ተገቢ ያደርጋቸዋል ትላላችሁን? “ጉንፋን” በየትም ያለ ነገር ነው። ይህ ማለት ግን እናንተም ትፈልጉታላችሁ ማለት አይደለም። ነው እንዴ? ማስተርቤሽን ጉዳት የለውም የሚለው አባባልስ እንዴት ነው?

4 አብዛኞቹ ሐኪሞች አልፎ አልፎ ማስተርቤሽን ከአካላዊ ጤንነት አንፃር ጉዳት የለውም ይላሉ። እንደ አብዛኞቹ የሥነ አእምሮ ጠበብቶች ሁሉ እነርሱም ጉዳት የሚመጣው ይህን ድርጊት የሚፈጽመው ሰው የአእምሮና የስሜት መረበሽን የሚያስከትል የበደለኝነት ስሜት ካለውና ይህም በምላሹ አካላዊ ቀውስን ካስከተለ ብቻ ነው በማለት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሐኪሞችና የሥነ አእምሮ ጠበብቶች ለስሕተት የተጋለጡ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ስለሆኑ አመለካከታቸውም በየጊዜው ይለዋወጣል። ሆኖም ወጣቶች ምክር ማግኘት የሚችሉበት የማይለዋወጥና ከስሕተት ወይም ትክክል ካልሆነ ግምት ነፃ የሆነ ምንጭ አለ። እሱም የአምላክ ቃል ነው። ረዥም ዕድሜ ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ሞገስ ጋር የዘላለም ሕይወትን የምንፈልግ ከሆነ የእርሱን ጥበብና ምክር ለማግኘት መጣር ይገባናል። እርሱ ሰዎች ፈጽሞ ሊያደርጉልን የማይችሉትን ለደስታችን የሚሆነውን ነገር ሊያደርግልን ይችላል።

ከፍተኛው የምክር ምንጭ ያለው አመለካከት

5, 6. (ሀ) በቆላስይስ 3:5 ላይ ያለው ምክር ከማስተርቤሽን ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ልማድ “ከመጎምጀት” እና “ከስግብግብነት” ጋር የሚያዛምደው ለምንድን ነው?

5 እንግዲያውስ ዋናው ጥያቄ ማስተርቤሽን ምን ያህል አካላዊ ጉዳት ያመጣል የሚለው ሳይሆን መንፈሳዊ ጉዳት ያስከትላል ወይስ አያስከትልም የሚለው ነው። እውነት ነው “ማስተርቤሽን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ይሁን እንጂ በቆላስይስ 3:5 ላይ ካለው በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ምን ትረዳላችሁ? የአምላክን ሞገስ ማጣት ለማይፈልጉ ሰዎች “እንግዲህ በምድር ያሉትን ብልቶቻችሁን ግደሉ (አትቀስቅሱ) እነዚህም ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም፣ ክፉ ምኞትም፣ ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው” በማለት ይናገራል። ማስተርቤሽን አንድ ሰው በገዛ እጁ ብቻ የሚያደርገው በመሆኑ ከዝሙት የተለየ ነው። ይሁንና እንዲህ መሆኑ ድርጊቱን ርኩስ ከመሆን ያድነዋል? ወይስ እሱም “በፍትወት” መሸነፍ ማለት ነው?

6 ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው:- “ደንዝዘውም በመመኘት [በስግብግብነት አዓት] ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ” ስለሚላቸው ሰዎች ጽፏል። (ኤፌሶን 4:19) ጳውሎስ ቀደም ባለው አንቀጽ ውስጥ በተጠቀሰው ወደ ቆላስይስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤው ላይ “መጎምጀት” ብሎ ጠቅሷል። በኤፌሶን 4:19 ላይ ደግሞ “መመኘት” ወይም “ስግብግብነት” በማለት ተናግሮአል። ማስተርቤሽን በእርግጥ የእነዚህ ሁለት የማይፈለጉ ጠባዮች መግለጫ ነው። እንዴት? ምክንያቱም ድርጊቱ የራስ መብት ያልሆነውን ነገር መመኘትን ስለሚያመለክት ነው። አምላክ ፍትወተ ሥጋን ለማርካት የጋብቻን ዝግጅት ሰጥቶአል። ነገር ግን የፆታ ስሜቱን ማስተርቤሽንን ልማዱ ያደረገ ሰው ያንን እርካታ ያለምንም ዋጋ ለማግኘት እንደሞከረ ያህል ነው። ሊከፈል የሚገባው ዋጋ ከጋብቻ ጋር አብረው የሚሄዱትን ሃላፊነቶች መቀበልና መሸከም ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሐዋርያው ‘በፍትወት ለተቃጠሉት’ ምክር በሰጠ ጊዜ አምላክ በሰጠው ጋብቻ አማካኝነት እንዲረኩ እንጂ በማስተርቤሽን እፎይታ እንዲያገኙ እንዳልነገራቸው ልብ በሉ።—1 ቆሮንቶስ 7:2, 9

7, 8. (ሀ) አንድ ሰው የማስተርቤሽን ልማድ ካለው ለወደፊቱ የጋብቻውን ደስታ የሚነካበት እንዴት ነው? (ለ) የማስተርቤሽን ልማድ ያምላክን ሕግ በከፋ ሁኔታ ላለማፍረስ የሚጠቅም ዘዴ አድርጎ መመልከት ስሕተት የሚሆነው ለምንድን ነው?

7 እንደ እውነቱ ከሆነ ማስተርቤሽን ወደፊት በጋብቻ ውስጥ የምታገኙትን ደስታ አደጋ ላይ ይጥልባችኋል። አንድ ሰው ማስተርቤሽንን ልማድ ካደረገ ይህ ስለ ራስ ደስታና እርካታ ብቻ የማሰብ ልማድን ያሳድግበታል። ሆኖም በጋብቻ ውስጥ በተለይ በወንዱ በኩል ለሌላው ወገን ደስታና እርካታ ጭምር ማሰብ አስፈላጊ ነው። አለዚያ የጋብቻ ግንኙነቶች ይበላሻሉ፤ በዚህም ምክንያት ጭንቀትና ቅሬታ ይኖራል። ይኸው ሁኔታ ማለትም ባሎች የሚስቶቻቸውን ፍላጎት ችላ በማለት ስለ ራሳቸው ደስታ ብቻ ማሰባቸው በጋብቻ ውስጥ ከዋነኞቹ ችግሮች አንዱ ነው። ይህ ሁኔታ በአብዛኛው የሚመነጨው ከጋብቻ በፊት ይዘወተር ከነበረ የማስተርቤሽን ልማድ ነው።

8 “ታዲያ” ይላሉ አንዳንድ ሰዎች “አንድ ሰው ጋብቻ ለመመሥረት ገና ዕድሜው ያልደረሰ ቢሆንስ? የጋብቻውን ጊዜ እየተጠባበቀ የራሱን ስሜት በራሱ ቢያረካ እንደ ዝሙትና ግብረ ሰዶም ከመሳሰሉት ከበድ ያሉ የአምላክን ሕግ የመተላለፍ ድርጊቶች አይጠብቀውምን?” እንደዚያ ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ ምክንያታዊ ነውን? አይደለም። ማስተርቤሽን ከዝሙትና ከግብረ ሰዶም ሊጠብቁን የሚችሉትን ነገሮች ማለትም ጤናማ ሕሊናንና ትክክል ለሆነው ነገር ያለንን ፍቅር ያዳክማል። እንደ ዕፅ ሱሰኝነት ሁሉ የፆታን ስሜት በማስተርቤሽን ማርካትም አንድ ሰው ማንኛውም ዓይነት ጭንቀት ሲያጋጥመው በጭንቀቱ ምክንያት የመጡትን ችግሮች ተቋቁሞ በማሸነፍ ፋንታ ሁልጊዜ ዘወር የሚልበት አማራጭ ሊያደርገው ይችላል። በዚህም ምክንያት የመጥፎ ልማዶችን ዑደት ሊያስከትልና በመጨረሻውም ሰውየውን ባሪያ ሊያደርገው ይችላል። አምላክ ግን ሰውነታችን እንዲቆጣጠረን በመፍቀድ ፋንታ እኛ ሰውነታችን እንድንቆጣጠር ነግሮናል።

ግብረ ሰዶማዊ ልማዶች

9–13. (ሀ) የማስተርቤሽን ልማድ አንድን ሰው አንዳንድ ጊዜ ለግብረ ሰዶም ድርጊቶች የሚያጋልጠው እንዴት ነው? ግብረ ሰዶም ፈጻሚ ሆኖ የሚወለድ ሰው አለን? (ለ) አምላክ እንደነዚህ ያሉትን ልማዶች እንዴት ይመለከታቸዋል? (ሐ) ከእነርሱስ መላቀቅ ይቻላልን? (ሮሜ 1:24–27፤ ዘሌዋውያን 18:22, 23፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9–11)

9 በማስተርቤሽን ለፍትወተ ሥጋ መሸነፍ ዝሙት ወይም ግብረ ሰዶም ለመፈጸም የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሲደቀኑባችሁ ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ አይሰጣችሁም። በተቃራኒው ግን የተሳሳተ አስተሳሰብና ምኞት ይኮተኩትባችኋል። እንዲያውም ማስተርቤሽን ወደ ግብረ ሰዶም ሊመራ ይችላል። እንደዚህ ባሉት ጊዜያት ሰውየው ብቻውን በሚፈጽመው የፆታ ድርጊቱ ባለመርካት ለጋራ እርካታ ሌላ ጓደኛ ይፈልጋል።

10 ይህም እናንተ ከምትገምቱት በላይ በተደጋጋሚ ሊደርስ ይችላል። ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት ግብረ ሰዶም ፈፃሚዎች እንደዚያ ሆነው አልተወለዱም። ነገር ግን ልማዱ በኋላ የተማሩት ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ገና በለጋ ዕድሜው በሌላው የፆታ አካሎች መጫወት ይጀምርና ከዚያም በኋላ የግብረ ሰዶም ተግባሮች መፈጸም ይጀምራል። አንድ ወጣት እንዲህ በማለት ይተርካል:-

11 “ወጣት በነበርኩበት ጊዜ የወላጆች መመሪያ አላገኘሁም። እንደፈለግሁት እንድሆንና የፈለግሁትን እንድሠራ ተለቅቄ ነበር። ገና የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ በዕድሜ ከኔ ከፍ የሚሉት የአጎቴና የአክስቴ ልጆች ከግብረ ሰዶም ድርጊት ጋር አስተዋወቁኝ። ይህንንም ድርጊት ደስታ የሚሰጥ ሆኖ ስላገኘሁት ከእነርሱ ጋርና በኋላም ከሌሎች ጋር ይህንን ልማድ ቀጠልኩበት። ብዙም ሳይቆይ የየዕለቱ ተግባሬ ሆነ። በመጀመሪያ ምንም ስሕተት ነገር እየሠራሁ ያለሁ መስሎ አይታየኝም ነበር። ወላጆቼ ስለ ሥነ ምግባር ምንም መመሪያ አልሰጡኝም፤ እኔም እነርሱን አማክሬያቸው አላውቅም።

12 “በዚያ ጊዜ የምንኖረው በአንድ የማዕከላዊ አሜሪካ አገር ነበር። በኋላም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ወደጨረስኩበት ወደ ኒውዮርክ ከተማ ተዛወርን። የግብረ ሰዶም ተግባሮችንም ቀጠልኩ። ትምህርት ቤቶቹና ከተማው በግብረ ሰዶማውያን የተሞሉ ስለሆኑ ብዙ አጋጣሚዎች አገኘሁ። በዕድሜ እየበሰልኩ ስሄድ የማደርገው ነገር ከተፈጥሮ ውጭ እንደሆነና ልክ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ይሁን እንጂ ፍላጎቱ ስለነበረኝ ቀጠልኩበት። እነዚህ የፆታ ድርጊቶች በጣም የሚፈታተኑኝ ሆኑ።”

13 ይህ ወጣት በዚህ ተግባር “ተጠምዶ” ስለነበር ልማዶቹን ሊያሸንፋቸው የቻለው ከብርቱ ጥረት በኋላ ብቻ ነበር። ለውጥ እንዲያደርግ ያነሳሳው ነገር ምን ነበር? ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ያደረበት ፍላጎት ነው። አምላክ የግብረ ሰዶምን ድርጊት “ከተፈጥሮ ውጪ” የሆነ ነገር አድርጎ እንደሚመለከተውና ጨርሶ እንደማይቀበለው በተረዳ ጊዜ ወጣቱ ሰው ይህን ልማድ ድል እስኪያደርገው ድረስ ተዋጋው። የአምላክ ቃል በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ግልጽ ነው:- “አትሳቱ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ [ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች] . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ይላል።​—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

ራስን ተቆጣጥሮ ማሸነፍ

14–16. (ሀ) የፆታ ፍላጎቶችን ለመቆጣጠር ምን ማድረግ ይቻላል? (ፊልጵስዩስ 4:8፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3–5) (ለ) የፆታ ስሜት እያየለብህ መምጣቱ ከተሰማህ ከስቃዩ ለመገላገል ምን ማድረግ ትችላለህ? (መዝሙር 1:1, 2፤ 63:6, 7)

14 የምታስቡት ነገር በውስጣችሁ ከሚያድርባችሁ ስሜትና ከምታደርጓቸው ነገሮች ጋር ብዙ ግንኙነት አለው። ስለዚህ እናንተ በእርግጥ የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው? ማስተርቤሽንን ልማድ በማድረግና ምናልባትም ወደ ግብረ ሰዶም ተግባሮች ሸርተት በማለት የፆታ ምኞት ሁልጊዜ እንዲረብሻችሁ ትፈልጋላችሁን? አእምሮአችሁ በፆታ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ከፈቀዳችሁለት ይህ ሊደርስባችሁ ይችላል። ነገር ግን እንደዚህ ያለው የፆታ ግፊት የሕይወታችሁን ደስታና ጠቃሚ ነገሮችን ከማከናወን እንዳያሰናክላችሁ ለመከልከል የምትፈልጉ ከሆነ ራሳችሁን መቆጣጠር ተለማመዱ፤ ሐሳባችሁንም ወደ ሌሎች ጉዳዮች ዘወር አድርጉት።

15 የፆታን ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ሥዕሎች፣ ጽሑፎች፣ ወይም ሌሎች ነገሮች ሲያጋጥሟችሁ ለእነርሱ በቀላሉ አትበገሩ። ሐሳባችሁ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች ላይ እንዲያርፍ ከፈቀዳችሁ ወይም እነርሱን የሚመለከት ጭውውት ሲደረግ ተካፋይ ከሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ብስጭት በማስከተልና ግፊቱ በውስጣችሁ እንዲደረጅ በማድረግ መከራችሁን ታያላችሁ። ይህም የሚሆንበት ምክንያት እንደዚህ ያለውን ነገር ለረዥም ጊዜ በተመለከታችሁ ወይም ስለነዚህ ነገሮች በተነጋገራችሁ መጠን ልባችሁ በነዚህ ነገሮች ይበልጥ በጥልቅ ስለሚነካ ነው። እናንተን ወደ ተግባር የሚገፋፋ ዋናው አንቀሳቃሽ ነገር ደግሞ ልባችሁ ነው።

16 ይሁን እንጂ አንዳችም ነገር ሳይኖር በውስጣችሁ ፍትወት እየተቀሰቀሰ እንዳለ ቢሰማችሁስ? እፎይታ ለማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? ወደ ማስተርቤሽን በመመለስ ሳይሆን አእምሮአችሁን፣ ልባችሁንና ሰውነታችሁን ወደ ሌላ አቅጣጫ በማዞር ነው። አንድ ዓይነት ሥራ ልትሠሩ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ልታደርጉ፣ ኳስ ልትጫወቱ ወይም በእግር ልትንሸራሸሩ ትችላላችሁ። የምታከብሩትን ሰው ፈልጋችሁ ማወያየት ወይም ካስፈለገ እንዲህ ካለው ሰው ጋር በስልክ መነጋገርም ጥሩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩትን አጋዥ ጽሑፎች ጮክ ብሎ ማንበብ ጥሩ እርዳታ ከምታገኙባቸው ነገሮች አንዱ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግሩን ወደ ሰማያዊው አባታችሁ ወደ ይሖዋ በጸሎት አቅርቡት።

17–20. (ሀ) አንድ ሰው በመኝታው፣ በአመጋገቡና በንጽሕና አጠባበቅ ልማዶቹ ማስተካከያ ማድረጉ እንዴት ሊረዳው ይችላል? (ለ) አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ለማድረግ ከባድ ትግል እያደረገ ቢሆንም የእርሱ ሁኔታ ተስፋቢስ እንደሆነ እንዲሰማው የማያስፈልገው ለምንድን ነው? (መዝሙር 103:13, 14)

17 አንድ ሰው የፆታ ፍላጎት የሚፈጥርበትን ጭንቀት ለማስወገድ ወይም ለመቀነስ ሊረዱት የሚችሉ ቀላልና ምክንያታዊ የሆኑ ብዙ ተጨማሪ ነገሮች አሉ። ከሌሎች ጋር ማለትም ከጥሩ ሰዎች ጋር መሆን አንዱ መከላከያ ነው። በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻችሁ የምትተኙ ቢሆንና ሌሊት ወደዚህ አቅጣጫ የሚገፋፋ ልዩ ግፊት የሚሰማችሁ ከሆነ ከሌላው የቤተሰብ አባል ጋር ክፍሉን የምትዳበሉበትን ዝግጅት ለማድረግ ትችሉ ይሆናል። ደግሞም በጀርባችሁ ወይም በሆዳችሁ ከመተኛት ይልቅ በጎናችሁ መተኛት ጠቃሚ ሆኖ ታገኙት ይሆናል።

18 ሌላው ሊረዳችሁ የሚችል ጠቃሚ ነገር ደግሞ ልብሳችሁ ከፆታ ብልታችሁ ጋር የማያስፈልግ መፈጋፈግ እንዳይፈጥር መጠንቀቅ ነው። ከመተኛታችሁ በፊት የምታነቡት ወይም የምታወሩት ነገር መንፈስን የሚያረጋጋ እንጂ የዚህ ተቃራኒ ውጤት እንዳይኖረው ለማድረግ ሞክሩ። ልትተኙ ስትሉ በምትበሉት ነገር ላይም ጥንቃቄ አድርጉ። አንዳንዶች ከመተኛታቸው በፊት የሚበሉትንና የሚጠጡትን መጠን ሲቀንሱ ይበልጥ ጥሩ እንቅልፍ እንደሚያገኙና የፆታ ስሜት የመቀስቀስ ዝንባሌ እንደማይመጣባቸው ተገንዝበዋል። በተለይም ለወንዴ ወይም ለሴቴ ብልቶች ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። የንጽሕና ጉድለት የፆታ ብልቶች መቆጣትን ወይም ማሳከክን ሊያመጣ ስለሚችል ትኩረትን ወደዚያ አቅጣጫ ይስባል። በዚህ የግል ንጽሕና አጠባበቅ ጉዳይ ላይ ሃሳብ እንዲሰጧችሁ ወላጆቻችሁን ልትጠይቁ ትችላላችሁ።

19 ተገቢ የግል ንጽሕና አጠባበቅ የፆታ ብልቶችን መነካካትን ስለሚጠይቅ አንድ ሰው ይህን ማድረጉ በነዚህ ብልቶች ያለአግባብ ወደመጠቀም ይመራል ብሎ ያስብ ይሆናል። ነገር ግን ዓላማችሁ ትክክል በመሆኑ ማለትም የፆታ ፍላጎት መቀስቀስን ለማስወገድ ስለሆነ እንደዚህ ያለው አያያዝ ስለነዚህ ብልቶች ጤናማ የሆነ አመለካከት እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል። የፆታ ብልቶች የተሠሩት እናንተን “በቁጥጥራቸው ሥር እንዲያደርጓችሁና” መላውን ሕይወታችሁን እንዲገዙ ታስበው እንዳልሆነ ትገነዘባላችሁ።

20 አሁን የማስተርቤሽንን ልማድ እየተዋጋችሁ ከሆነ ይህ ችግር ያጋጠማችሁ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ወይም እናንተ ብቻ እንዳልሆናችሁ አስታውሱ። የማስተርቤሽንን ልማድ ለማሸነፍ ከባድ ትግል ቢኖርባችሁም ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን የተዉአችሁ መስሎ ከቶ አይሰማችሁ። ይህንን ልማድ ለማሸነፍ ልባዊ ጥረት ማድረጋችሁን ከቀጠላችሁበት ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት የምትወጡበትን አስፈላጊ ጥንካሬ እንድትገነቡ በደግነትና በትዕግሥት ይረዱአችኋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ገጽ 39 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ግብረሰዶማውያን ይህ ጠባይ አብሯቸው የተወለደ ነው ወይስ በኋላ የተማሩት ልማድ?

[በገጽ 41 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምታነበው ነገር ልዩነት ያመጣልን?