በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቁሳዊ ንብረቶችን የምትመለከተው እንዴት ነው?

ቁሳዊ ንብረቶችን የምትመለከተው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 21

ቁሳዊ ንብረቶችን የምትመለከተው እንዴት ነው?

1–4. (ሀ) ብዙ ወጣቶች እንዲኖሩአቸው የሚፈልጉአቸው አንዳንድ ቁሳዊ ንብረቶች ምንድን ናቸው? (ለ) በቁሳዊ ነገሮች ላይ ብዙ ትኩረት ማድረግ አንድ ሰው ስለ ሰዎች የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረው የሚያደርገው እንዴት ነው?

በሺህ የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ መልካም ስጦታዎችን የተሞላ ቤት በዓይነ ሕሊናህ ሊታይህ ይችላልን? እዚያ ቤት ውስጥ ብትኖርና አባትህም የቤቱ ባለቤት ሆኖ ከእነዚህ ስጦታዎች ብዙዎቹን ቢሰጥህ ትወድ ነበርን? በእውነቱ አሁንም እንዲህ ዓይነት ቤት በሆነችው በዚች ፕላኔት ምድር ውስጥ እየኖርክ ነው። እርሷንም ይሖዋ አምላክ የሚያስገርም ብዛትና ዓይነት ባላቸው ጥሩ ጥሩ ነገሮች ሞልቷታል።

2 ይሁን እንጂ የሚገርመው ነገር ከእነዚህ ቁሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ ደስታ ማግኘታችን፣ እንዲያውም ከሕይወት ከራሱ የተሟላ ደስታ ማግኘታችን በጣም የተመካው ለእነዚህ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ ባለመስጠታችን ላይ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምክንያቱም ከቁሳዊ ንብረቶች የበለጠ ዋጋ ያላቸው ሌሎች ነገሮች ስላሉ ነው።

3 ለቁሳዊ ንብረቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጡ አንዳንድ ወጣቶችን እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። አንዳንዶች ከሁሉ የበለጠ ግምት የሚሰጡት ልዩ ዓይነት ሬድዮ ወይም ቴፕሪኮርደር፣ የስቴርዮ ማጫወቻዎች፣ አንዳንድ ልዩ የሆኑ የልብስ ዓይነቶች፣ ካሜራ፣ ሞተር ቢስክሌት ወይም የራሳቸው መኪናም እንኳ ሳይቀር ባለቤት መሆንን ነው። ብዙ ሰዎች ለትምህርታቸው፣ ለቤተሰባቸው ወይም ለማንኛውም ሌላ ነገር ሊኖራቸው ከሚገባው የበለጠ ፍቅር የሚያሳድሩት ለእነዚህ ነገሮች ነው። በተጨማሪም አንተንና ሌሎች ሰዎችን የሚለኩት ከእነዚህ ቁሳዊ ንብረቶች አንፃር ነው። ይህስ ተገቢ ይመስልሃልን?

4 እስቲ ቆም በልና አስብበት። እንደዚህ ያሉት ቁሳዊ ንብረቶች ባለቤት መሆንህ ወይም አለመሆንህ በማንነትህ ላይ በእርግጥ ለውጥ ያመጣልን? እነዚህ ነገሮች ካሉህ የተሻልክ ሰው ከሌሉህ ደግሞ ምስኪን ነህ ማለት ነውን? እንደ እውነቱ ከሆነ ላንተ የሚሰጠውን ግምት በእርግጥ የሚወስነውና ከፍተኛ እርካታና ደስታ ሊያመጣልህ የሚችለው በጣም ውድ የሆነው ሀብት የተለየ ዓይነት ሀብት ነው። ከእነዚህ በጣም ዋጋማ ከሆኑት ሀብቶች ውስጥ አንዳንዶቹን ልትጠቅስ ትችላለህን?

የበለጠ ዋጋ ያላቸው ሃብቶች

5–7. (ሀ) ሁለተኛ ቋንቋ ማወቅ ወይም አንዳንድ ነገሮች መሥራትን መቻል ከቁሳዊ ንብረቶች የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? (መክብብ 7:12) (ለ) የአምላክ ቃል እውቀት ከዚህም የበለጠ ዋጋ ያለው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 15:2፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16)

5 እውቀት ከእነዚህ ሃብቶች አንዱ አይደለምን? ለምሳሌ ያህል የስቴሪዮ ማጫወቻ ወይም የትራንዚስተር ሬድዮ ባለቤት መሆንን ሌላ ቋንቋ ከማወቅ ጋር እስቲ አወዳድረው። እርግጥ የእነዚህ ነገሮች ባለቤት መሆን ምንም ስህተት የለበትም። ሌላ ቋንቋ ብታውቅ ግን ከመቶ ሚልዮን የሚበልጡ ሌሎች ሰዎች ሲናገሩና ሲዘምሩ በመስማት ልትደሰት ትችላለህ። ያን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች አንተ የምትኖርበትን አገር ሊጎበኙ ይመጡ ይሆናል። ወይም አንተ ሌሎች አገሮችን የመጎብኘት ዕድል ብታገኝ ሌላ ቋንቋ ማወቅህ ከጉብኝትህ የምታገኘውን ደስታ ከፍ ያደርገዋል።

6 የእጅ ሙያ እውቀት ማግኘትም በተመሳሳይ ከፍተኛ ዋጋ አለው። ጥሩ ወጥ ቤትነት፣ ጥሩ ልብስ ሰፊነት፣ ችሎታ ያለው አናጢነት፣ ወይም ጥሩ የሜካኒካል ዕቃዎች አዳሽነት ችሎታ ማዳበር ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው እስቲ አስበው። እነዚህ ችሎታዎች የአንዳንድ ቁሳዊ ንብረቶች ባለቤት ከመሆን ይልቅ ለወደፊቱ በሕይወትህ ፋይዳ ያለው ነገር ስትሠራ የበለጠ ጠቀሜታ ይሰጡሃል።

7 ከሁሉ የበለጠ ዋጋ ያለው እውቀት የአምላክ ቃል እውቀት ነው። ለምን እንዲህ እንላለን? ምክንያቱም ከስቴሪዮ ማጫወቻ ከሚወጣ ሙዚቃ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ልባቸው ለተሰበረና ተስፋ ለቆረጡ ሰዎች መጽናናት ልታመጣላቸው ስለምትችል ነው። እንዲያውም ስለ አምላክ እውነት ባገኘኸው እውቀት ሕይወት ለማዳንም እንኳ ትችላለህ። ይህን ሊያደርግ ይችላል ብለህ የምታስበው ምን ዓይነት ቁሳዊ ንብረት አለ? ጠቢቡ ሰው “እውነትን ግዛ አትሽጣትም፣ ጥበብን ተግሳጽን ማስተዋልንም። የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፣ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሴትን ያገኛል። አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፣ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት” ባለ ጊዜ ወጣቶች የትኞቹን ነገሮች ቢገዙ እንደሚሻላቸው ማሳሰቡ ምንም አያስደንቅም። — ምሳሌ 23:23–25

8–12. (ሀ) በቁሳዊ ንብረት ረገድ ካለህ ነገር ሁሉ አንተነትህ የበለጠ ዋጋ ያለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የሚያሳየውስ እንዴት ነው? (ለ) እንግዲያውስ ምን ጠባዮችን ለመኮትኮት መጣር ይኖርብናል? (ገላትያ 5:22, 23)

8 በተጨማሪም ጥሩ ስም ወይም ዝና ማትረፍ የቁሳዊ ንብረት ባለቤት ከመሆን የቱን ያህል ብልጫ እንዳለው አስብ። ራስ ወዳድ አይደለም፣ ሐቀኛ፣ ትጉህ፣ እምነት የሚጣልበና የተከበረ ሰው ነው የሚል ስም ቢኖርህ በሰዎች ዘንድ ከማንኛውም ዓይነት ልብስ የበለጠ ያስወድድሃል። እንዲህ ዓይነት ስም ለጥሩ ጓደኝነት፣ ወይም ለሥራ ባልደረባነት ወይም ለሥራ ተቀጣሪነት ተፈላጊ ሊያደርግህ ይችላል። ሰዎች ወደ ቤታቸው መጥተህ እንድትጠይቃቸው ወይም ከእነርሱ ጋር አንዳንድ ነገር እንድትሠራ፣ እነርሱ ያላቸውን ጥሩ ነገሮች አብረሃቸው እንድትካፈል እንዲጋብዙህ ሊያደርጋቸው ይችላል። ታዲያ ከቴሌቪዥን ይልቅ ይህ ማንኛውንም የብቸኝነት ችግር የሚፈታ አይደለምን?

9 በእውነቱ በሕይወታችን የምናገኘው ደስታ በአብዛኛው የተመካው ተደናቂ እንደሆንን፣ ለሌሎች እንደምናስፈልጋቸው፣ እኛ ባንኖር ኖሮ ሊቀርባቸው ይችል የነበረ በሕይወታቸው ውስጥ አንድ ዓይነት ነገር እንዳበረከትንላቸው ሲሰማን ነው። በቁሳዊ ንብረቶች ሀብታም ከመሆን ይልቅ በጥሩ ጠባዮች ባለጸጋ መሆን በጥሩ ሰዎች ዘንድ የበለጠ ተደናቂ ያደርግሃል። የጥበብ ንግግሮችን የያዘው መጽሐፍ እንዳስቀመጠው “የልብን ንጽሕና የሚወድና ሞገስ በከንፈሩ ያለች [ሰው] ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል።” — ምሳሌ 22:11

10 ወጣት የነበረው ጢሞቴዎስ ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞው ወደ ብዙ አስደሳች ቦታዎች ሲሄድ አብሮት እንዲሄድ የመመረጥ መብት አግኝቶ ነበር። ይህም የሆነው ጢሞቴዎስ ቁሳዊ ሃብት ስለነበረው ሳይሆን በትንሹ እስያ በሚገኙ ሁለት ከተሞች የነበሩት ክርስቲያኖች ስለ መልካም ጠባዮቹ ስለመሰከሩለት ነው። በዚህ የተነሳ ጢሞቴዎስ ያየውና ያጋጠመው ተሞክሮ በዋጋ የማይተመን ነው። ይህ ተሞክሮ በኋላ ልዩ ኃላፊነቶችን ለመቀበልና ሐዋርያውም ትልቅ አደራ ሊሰጠው የሚችል ዓይነት ሰው ለመሆን አብቅቶታል። ጢሞቴዎስ ቁሳዊ ሀብትን በሕይወቱ ውስጥ ትልቁ ነገር እንዳላደረገ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በመቄዶንያ ወደሚገኘው የፊልጵስዩስ ጉባኤ በላከው ጊዜ የተናገረው ቃል ያሳያል:- “ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደ እርሱ ያለ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ ማንም የለኝም። ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፣ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንዳገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ። እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ እርሱን [ጢሞቴዎስን] ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ።” — ፊልጵስዩስ 2:19–23

11 እውነተኛ ወዳጆች የሚያደንቁህ ማንነትህን እንጂ ያለህን ነገር አይተው አይደለም። “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፣ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል።” (ምሳሌ 17:17) ከዚህም በላይ በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን አገልግሎት ትልቁ ነገር ካደረግህ እርሱ ራሱ ወዳጅህ ይሆናል። “የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት ] ደስ ያሰኘው እንደሆነ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል።” — ምሳሌ 16:7

12 በተጨማሪም እውቀት፣ መልካም ባሕርይና እውነተኛ ወዳጆች የመሳሰሉት ነገሮች የሚሰረቁ ወይም ደግሞ በጊዜና በአገልግሎት ብዛት አልቀው ዋጋቸውን የሚያጡ ነገሮች እንዳልሆኑም አስታውስ። ቁሳዊ ንብረትህን ግን ሰዎች ሊሰርቁት ወይም ሊያበላሹት ይችላሉ። በዚህም ምክንያት የአምላክ ልጅ “ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሰርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፣ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” በማለት መክሮናል። (ማቴዎስ 6:20, 21) በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ካለህና ያንንም ጠብቀህ ከያዝከው የወደፊት ደስታህ አስተማማኝና እርግጠኛ ይሆናል። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ሥርዓቱ ውስጥ ይህች ምድር በምትሰጣቸው የጥሩ ነገሮች ሃብት ሙሉ በሙሉ ለመደሰት ትችላለህ።

ጥንካሬና ጥበብ እንዳለህ አሳይ

13–15. (ሀ) የቁሳዊ ንብረቶች ምኞት ሕይወትህን የሚቆጣጠረው ከሆነ የምታበለጽገው ማንን ነው? በሌላ በኩል የምትከስረው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 6:33) (ለ) ሚዛናዊው የሆነው የቁሳዊ ንብረቶች አመለካከት ምንድን ነው?ረየ

13 ታዲያ ያሁኑ የንግድ ሥርዓቶች ከፍተኛ ኃይል ባለው ማስታወቂያቸው አማካኝነት ሕይወትህን በቁሳዊ ሀብት ዙሪያ እንድትገነባ እንዲያስገድዱህ ለምን ትፈቅድላቸዋለህ? እነርሱን አበልጽገህ በመጨረሻው በሕይወት ውስጥ ፋይዳ ባላቸው ነገሮች ረገድ ራስህን ለምን ታደኸያለህ? የፍቅረ ንዋይን ግፊት ለመቋቋምና ከቁሳዊ ሀብት የበለጠ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች በመፈለግ ሕይወትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም በመቁረጥ እውነተኛ ጥንካሬ እንዳለህ ለምን አታሳይም?

14 በተለይ ባሁኑ ጊዜ እንዲህ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያሁኑ ሥርዓት ከነንግድ ሥርዓቱ ወደ ፍጻሜው እየቀረበ መሆኑን ያሳያሉ። ቁሳዊ ነገሮችን ከመጠን በላይ ማግበስበስ ትኩረታችንን ወደ ሌላ በማዞር ወጥመድ ይሆንብናል። ባሁኑ ሥርዓት ባሕር ውስጥ እንሰጥምና አምላክ አዲሱን ሥርዓት ሲያመጣና ያሁኑን ሥርዓት ጠራርጎ ሲያስወግደው እኛም ከሥርዓቱ ጋር ልንጠረግ እንችላለን። ኢየሱስ እንዳስጠነቀቀው “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ።።” — ሉቃስ 12:15

15 ምንም ንብረት አይኑረን ማለት አይደለም። ቢሆንም ሕይወታችንን ሃብት እንዲቆጣጠረው አንፈልግም። ደግሞም በእርግጥ ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ሃብቶች ወደ ግባችን እንዳንደርስ ከሚከለክሉን ሃብቶች መለየት ይገባናል። እንግዲያውስ ምንም ዓይነት ንብረቶች ቢኖሩህ እነርሱን ለሌሎች ጥቅምና በተለይም ፈጣሪህን ለማክበር እንድትጠቀምባቸው ዓላማህ ይሁን።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]