በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አለባበሳችሁና የሰውነታችሁ አቋም ስለ እናንተ ይናገራል

አለባበሳችሁና የሰውነታችሁ አቋም ስለ እናንተ ይናገራል

ምዕራፍ 7

አለባበሳችሁና የሰውነታችሁ አቋም ስለ እናንተ ይናገራል

1–4. አለባበሳችን ከውስጥ ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችንን የሚናገረው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

በጸደይ ወራት መስክ ላይ የተለያዩ አስደሳች ሕብረ ቀለማት ያላቸውን አበቦች በማየት አድንቃችሁ ወይም በሞቃታማ አካባቢዎች የሚገኙ ዓሦች ባላቸው ውብ የቅርፊት መልክ ተገርማችሁ ታውቃላችሁን? እነዚህን ነገሮች ማየቱ ፈጣሪያችን የዓይነት መለያየትንና ውበትን የሚወድ መሆኑን ያስረዳናል። ሁሉም ነገር ደብዛዛ፣ ግራጫ ወይም አሰልቺ የሆነ አንድ ዓይነት መልክ እንዲኖረው አይፈልግም። በዓለም ዙሪያ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን የተለያየ ዓይነት አለባበስ ማየት እንዴት ያስደስታል! ይሁን እንጂ ውጭያዊ ቁመናችሁ ከውስጥ ምን ዓይነት ሰው እንደሆናችሁ ምን ያህል እንደሚናገር ቆም ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁን?

2 ሕፃን ሳላችሁ አለባበሳችሁ ምን ዓይነት ሰው እንደሆናችሁ ብዙም አይናገር ኖሮ ይሆናል። ልብሶቻችሁን የሚመርጡላችሁና ፀጉራችሁን የሚያበጥሩላችሁ ወላጆቻችሁ ነበሩ። እያደጋችሁ ስትሄዱ ግን ልብስ ስለ መምረጥ፣ ስለ ፀጉር አያያዝና ስለመሳሰሉት ነገሮች የበለጠ ምርጫ እንዲኖራችሁ ፈቅደውላችኋል። ከዚያ ወዲህ የራሳችሁ ምርጫ መታየት ጀምሮአል። ቁመናችሁና አለባበሳችሁ በውስጥ ምን ዓይነት ሰው እንደሆናችሁ ማንነታችሁን ማንፀባረቅ ጀምሮአል። ታዲያ የሰውነታችሁ አቋምና አለባበሳችሁ ስለ እናንተ የሚናገሩት ምንድን ነው?

ሚዛንን መጠበቅ

3 ስለ ራሳቸው በጣም የሚኮሩ ሰዎች ኩራታቸውን የሚያሳዩት ብዙውን ጊዜ ስለ አለባበስ ፋሽን ከመጠን በላይ በመጨነቅ ነው። በልብሳቸው ወይም በመልካቸው ሁልጊዜ “ሌሎችን አስንቀው” ለመታየት ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ስለ ልብስ ግድ የለሽ መሆንም ኩራት ወይም ራስ ወዳድነትን ሊገልጽ ይችላል። እንዴት? ዝርክርኩ ግለሰብ ስለ አለባበሱ ግድ የለሽ የሆነው በስንፍና ምክንያት ሊሆን ቢችልም አለባበሱና ቁመናው በሌሎች ላይ ስለሚኖረው ውጤት “ምን ቸገረኝ” የሚል የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ይኖረው ይሆናል። በእነዚህ በሁለቱ መሃል ስለራሱ እምብዛም የማይጨነቅና ስለ ሌሎች የሚጠነቀቅ ሰው አለ። ይህንንም የሚያሳየው የሰውነቱ አቋምና አለባበሱ ተገቢነትና ልከኛነትን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ ነው።

4 አንዳንድ ወጣቶች ኋላቀር መስለው እንዳይታዩ በጣም አዲስ ከሆነው ፋሽን ጋር መራመድ እንደሚገባቸው አድርገው ያስባሉ። ሆኖም “ከመጠን ያለፈ ወግ አጥባቂ” በመሆንና በጣም “ዘመናዊ” በመሆን መካከል አንድ አማካይ ቦታ አለ። ይህንን ልከኛነት ከያዝክ ሁልጊዜ ጥሩ አለባበስ ይኖርሃል። ሲባጎው በተሳበ ቁጥር ወዲያ ወዲህ እንደሚል አሻንጉሊት በየጊዜው ለሚመጣው የፋሽን ለውጥ ተገዥ አትሆንም።

5–7. (ሀ) አንድ ሰው አዲስ የወጡ የልብስ ፋሽኖች እንዳያልፉት የሚጥር ከሆነ በእርግጥ ተጠቃሚው ማን ነው? (ለ) አንድ ሰው ብዙ ገንዘብ ባይኖረውም አለባበሱ ራሱ ለራሱ አክብሮት ያለው መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ሐ) በፊልጵስዩስ 2:3, 4 እና በሮሜ 15:2 ላይ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለአለባበሳችንም ሊሠሩ የሚችሉት እንዴት ሊሆን ይችላል?

5 ስለ ፋሽን በጣም በመጨነቄ የምጠቅመው ማንን ነው? እያልክ እስቲ ራስህን ጠይቅ። የምትጠቅመው በመሠረቱ ፋሽኖችን የሚያቀርበውንና የሚያበረታታውን የንግዱን ዓለም ነው። እነርሱ አንድ ትልቅ ዓላማ አላቸው:- እርሱም ገንዘብ ማግኘት ነው። ሁልጊዜ በእጃቸው ውስጥ የምትገባላቸው ከሆነ እነርሱን ትጠቅማቸዋለህ እንጂ አንተ ራስህን የምትጠቅምበት ምንም መንገድ የለም።

6 ዝርክርክነት ብዙ ገንዘብ የማያስወጣህ ይመስል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በሌሎች መንገዶች ብዙ ነገር ሊያስቀርብህ ይችላል። ሥራ ወይም የሌሎችን አክብሮት ሊያሳጣህ ይችላል። የአንድ ሰው ልብሶች በውድ ዋጋ የተገዙ ባይሆኑም ንጹሕና በሥርዓት የተያዙ ከሆኑ ይህ ስለ ራሱ እንደሚጠነቀቅ ያሳያል። ሌሎች ሰዎችም ይበልጥ ያከብሩታል፤ በእርሱም ላይ የበለጠ እምነት ያሳድራሉ።

7 በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ ልንከተለው የሚገባን ጥሩ ደንብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሮሜ 15:2 ላይ ይገኛል። እርሱም “እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ” ይላል። እኛ ራሳችንን ከምንመለከተው በላይ ሌሎች ሰዎች ይመለከቱናል። ታዲያ ቢመለከቱት የሚያስደስት አንድ ጥሩ ነገር ልንሰጣቸው መጣር የለብንምን? ይህም ስለ ስሜታቸው እንደምንጠነቀቅላቸው የሚያሳይ እንጂ ስለ ራሳቸው መልክና አለባበስ እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ መሆን የለበትም።

ማንነትን በልብስ ማሳወቅ

8–11. (ሀ) የተለያዩ ቡድኖች ወይም የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ማንነታቸው በአለባበሳቸው ተለይቶ የሚታወቀው እንዴት ነው? (ለ) ስለዚህ ሰዎች ከአንድ ሰው አለባበስ በመነሣት ምን ድምዳሜ ሊሰጡ ይችላሉ? ይህስ ችግር ሊያስነሳ የሚችለው እንዴት ሊሆን ይችላል?

8 አለባበስህ በሌላ መንገድም ስለ አንተ ይናገራል። ከአ ንድ ዓይነት ቡድን ወይም ክፍል ጋር ያስመድብሃል። ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመንም እንኳን ሁኔታው ያው ነበር። ለምሳሌ በሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ውስጥ የንጉሥ አካዝያስ መልዕክተኞች አንድ ዓይነት መልዕክት ከሰጣቸው ከአንድ ሰው ጋር መገናኘታቸውን ተመልሰው እንደተናገሩ ተጽፎአል። ንጉሡም “የሰውየው መልክ ምን ይመስላል?” ብሎ ጠየቃቸው። አለባበሱን በገለጹለት ጊዜ ንጉሡ ወዲያውኑ “ኤልያስ ነው” አለ። እንዴት አወቀው? ምክንያቱም ኤልያስ ነቢያት የሚለብሱትን ዓይነት ልብስ ለብሶ ስለነበረ ነው።—2 ነገሥት 1:2,5–8

9 በነቢይነት መታወቅ ክብር ያለው ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ የአንድ ሰው ልብስ ወራዳ ከሆነ ነገር ጋር ሊያያይዘው እንደሚችልም ያሳያል። የይሁዳ ምራት ትዕማር የፈለገችውን አንድ ዓላማ ለማግኘት የመበለት ልብሷን አውልቃ መጎናጸፊያና መሸፈኛ ለብሳ ከመንገድ ዳር ተቀመጠች። ይሁዳ በዚያ በኩል ሲያልፍ “ጋለሞታ መሰለችው፣ [በመጎናጸፊያ] ፊትዋን ሸፍና ነበርና” በማለት የታሪክ መዝገቡ ይናገራል። አለባበሷ በጊዜው የነበሩትን ጋለሞታዎች አስመስሏት ነበር።—ዘፍጥረት 38:13–15

10 ልክ እንደ ቀድሞው ጊዜ ሁሉ ዛሬም ምንም እንኳን ሰዎቹ የሚያደርጉትን ባናደርግና እነርሱ የሚያምኑትን ባናምንም አለባበሳችን ከአንድ ዓይነት የሰዎች ቡድን ጋር ሊያስመድበን ይችላል። ሰዎች ሌላው ቢቀር የዚያ ዓይነት አለባበስ ያላቸውን የሰዎች ቡድን እንደምንደግፍ አድርገው ይገምቱናል። ታዲያ ልንፈርድባቸው እንችላለንን?

11 ልብስ የፖሊሶች፣ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ወይም የነርሶች ብቻ መለያ አይደለም። በወራዳ ተግባር የተሠማሩ ሰዎችንም ቢሆን ለይቶ ያሳውቃል። በዛሬው ጊዜ ሴትኛ አዳሪዎች ከሦስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በከነዓን እንደነበሩት ጋለሞታዎች መጐናጸፊያና የፊት መሸፈኛ እምብዛም አይለብሱም። ይሁን እንጂ አካልን የሚያጋልጠውና ምንዝርን የሚያሳስበው አለባበሳቸው ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ የተሰማሩበትን ተግባር ያመለክታል። ከወንዶችም መካከል ዓመፅን ወይም ሥር ነቀል የፖለቲካ እርምጃን የሚደግፉ ሰዎች ለይቶ የሚያሳውቃቸውን ፋሽን ለብሰዋል። አንዳንድ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎችም እንዲሁ አድርገዋል። ከእነዚህ እንደ አንዱ ሆነን ለመታየት እንፈልጋለንን? የእነርሱን አለባበስ ብንከተልና ሥራ ለመቀጠር ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት መብት ለማግኘት በምንሞክርበት ጊዜ ችግር ቢያጋጥመን ሊያስደንቀን ይገባልን?

የፀጉርን አያያዝ የሚወስነው ምን መሆን አለበት?

12–15. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ትኩረትን የሚስቡት ምን ዓይነት የፀጉር አያያዞች ይመስሏችኋል? ብዙ ትኩረት የሚስቡትስ ለምንድን ነው? (ለ) በ1 ጴጥሮስ 3:3 ላይ የተሰጠው ምክር ፍሬ ነገር ምንድን ነው? (ሐ) 1 ቆሮንቶስ 11:14, 15 ምን ማለት ነው? እሱስ ለዘመናዊ ሁኔታዎች ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው? (መ) ወንዶች በፀጉር አያያዛቸው ሴቶችን ቢመስሉ ለሌሎች ምን ሊጠቁም ይችላል?

12 ፀጉራችሁን ማሳመር የሚያስችሉ ብዙ የፀጉር አያያዝ ዘዴዎች አሉ። ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ የፀጉር አያያዝ ዘዴዎች ከአገር ወደ አገርና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጡ መጥተዋል። ማንኛውንም ዓይነት የፀጉር አያያዝ ብትመርጡ ልዩነት ያመጣልን? አዎን ያመጣል። የሰው ኩራት አንዳንድ ጊዜ ከልክ ያለፈ የፀጉር አያያዝን አስከትሏል። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ሴቶች ከመጠን እንዳያልፉ ወይም ለፀጉር አያያዝ ከመጠን ያለፈ ትኩረት እንዳይሰጡ መምከር አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። ጴጥሮስ “ለእናንተ ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናፀፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ” በማለት ጽፎአል።—1 ጴጥሮስ 3:3

13 ይሁን እንጂ በቅርብ ዓመታት ወጣት ወንዶች በፀጉር አያያዛቸው በተለይም ፀጉራቸውንና በጆሮ ግንድ አጠገብ የሚወርደውን ጢም በጣም በማስረዘም ልዩ ትኩረትን ስበዋል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ወንዶች ፀጉራቸውን በዛሬው ጊዜ በአብዛኞቹ አገሮች ከተለመደው በላይ ያስረዝሙ አልነበረምን? ያስረዝሙ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የዚያኑ ያህል እርግጠኛ የሆነ ሌላ ነገርም አለ። ምን? የወንዶች ፀጉር ከሴቶቹ ፀጉር ምን ጊዜም ያጠረ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በግሪክ አገር በቆሮንቶስ ከተማ ለነበረው ጉባኤ:- “ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት፣ ሴት ግን ጠጉሯን ብታስረዝም ክብር እንዲሆንላት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን?” በማለት ለመጻፍ የቻለው በዚህ ምክንያት ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:14,15) “ተፈጥሮ” ይህንን የሚያስተምረን እንዴት ነው?

14 አንደኛ ነገር ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፈላቸው እንደ ሴም ዘሮችና አውሮፓውያን ያሉት ዞማ ፀጉር የነበራቸው ሕዝቦች መካከል አብዛኛውን ጊዜ በተፈጥሮ የወንዶቹና የሴቶቹ ፀጉር የሚያድግበት ርዝመት መካከል ጉልህ ልዩነት አለ። በአብዛኛው የወንዶቹ የፀጉር ርዝመት በተፈጥሮው ከሴቶቹ ፀጉር አጠር ያለ ነው። በተጨማሪም ወንዶች ጠጉራቸውን ከሴቶች አጠር ማድረጋቸው ‘ተፈጥሮአዊ’ የሆነ፣ ተገቢና ትክክለኛ ነገር ነው በማለት ሰዎች ባጠቃላይ ተቀብለውታል። ወንድ ሴት እስኪመስል ድረስ ፀጉሩን ቢያስረዝም ተፈጥሮአዊ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ግብረሰዶም እየተስፋፋ ባለበት ዘመንና አገር መለያ ምልክት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ግብረ ሰዶም በአምላክ አስተያየት የማይገባና አስጸያፊ እንዲሁም “ከተፈጥሮ ውጭ” የሆነ ድርጊት መሆኑን ይገልጻል።—ሮሜ 1:26,27

15 ታዲያ ይህ ምርጫችንን በጣም ጠባብ ያደርግብናልን? አያደርግብንም፤ ምክንያቱም እንደ ልብስ ሁሉ በፀጉር አያያዝ ረገድም ከልከኛነት ሳያልፉ ወይም ከተፈጥሮ ውጭ ሳይሆኑ በሚያስደስትና በሚያምር መንገድ ፀጉርን መያዝ የሚቻልባቸው ብዙ ዓይነት መንገዶች አሉ። በአምላክ ዓይን ትክክል ከሆነው ገደብ ሳይታለፍ የሚያማምሩ ልዩ ልዩ ዓይነቶችን ማግኘት ይቻላል።

ስለ መጋጌጫ ቅባቶችስ ምን ሊባል ይቻላል?

16–19. (ሀ) በመጋጌጫ ቅባቶች ስለ መጠቀም ምን ይሰማችኋል? (ለ) አንዳንድ ጊዜ ምን መጥፎ ውጤት አላቸው? (ሐ) በዚህ ጉዳይ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምን ሚዛናዊ መመሪያ ይሰጣሉ?

16 ሰዎች ከጥንት ጀምሮ መኳኳያዎችንና ቅባቶችን ይጠቀሙ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰዎች ልብስ የሚለብሱት ሰውነታቸውን ለመሸፈን ብቻ ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ያማሩ ሆነው ለመታየትም እንደሆነ እናውቃለን። የጥንት ዕብራውያን ለሚጠጋቸው ሁሉ ደስ የሚሉ እንዲሆኑ አዘውትረው ሽቶ ይቀቡ ነበር። በተጨማሪም የቆዳ ድርቀትን ለማስወገድና ውበታቸውን ለማሻሻል በቅባት ይጠቀሙ እንደነበር ማስረጃ አለ።

17 ታዲያ በዛሬው ጊዜ የአምላክን ሞገስ የሚያመጣላቸውን ነገር ለማድረግ የሚፈልጉ ወጣት ሴቶች በምን ነገር መመራት ይኖርባቸዋል? ዋናውን ጌጣቸው “በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለው የልብ ሰው” እንዲሆንላቸው በማድረግ ማንኛውንም ነገር “በልከኝነትና በጥሩ [በጤነኛ አስተሳሰብ አዓት]” እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ጥሩ ምክር መከተል ያስፈልጋቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:9,10፤ 1 ጴጥሮስ 3:3,4

18 እርግጥ ወጣት ልጃገረዶች የመጋጌጫ ቅባቶች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ቢያውቁ ጥሩ ነው። ጥሩ ደም ግባትን ሊያበላሹ ወይም መልከ ጥፉነትን የባሰ መጥፎ ሊያደርጉት ይችላሉ። ከዚህም ሌላ መጋጌጫ ቅባቶች እነርሱን በመኳኳል ከሚፈጠረው ማራኪነት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ቁንጅና የሆነውን የወጣትነትን የፊት ጥራትና ወዝ ይደብቁታል።

19 ልጃገረዶች በመጋጌጫ ቅባቶች ያለልክ መጠቀማቸው አብዛኛውን ጊዜ ወደ ደካማ ጎናቸው ትኩረትን ከመሳብ በቀር የተለየ ጥቅም የለውም። ይባስ ብሎ ከጥሩ መልክ ይልቅ ማራኪና ዘላቂ የሆነው ማንኛውም የባሕርይ ውበት ጎልቶ እንዳይታይ ወይም እንዳይስተዋል ሊከለክል ይችላል። በመጋጌጫ ቅባቶች ያለልክ መጠቀም በሌሎች ዘንድ በመጥፎ ሊተረጎምባችሁና ከጊዜ በኋላ ባሕሪያችሁንም በውጪያዊ መልካችሁ ባሳያችሁት ወይም ባስተዋወቃችሁት ርካሽ አምሳል ወደ መቅረጹ ሊያዘነብል ይችላል።

ትክክለኛ መምሪያዎችን መከተል

20–22. (ሀ) በአለባበስና በፀጉር አያያዝ በኩል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሕጎች ፋንታ የምናገኘው ምንድን ነው? ስለዚህ እነዚህን መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል ከእኛ የሚፈለገው ምንድን ነው? (ምሳሌ 2:10, 11) (ለ) ወላጆች ለልጆቻቸው ተጨማሪ መምሪያዎችን የማውጣት መብት ያላቸው ለምንድን ነው?

20 እነዚህን ነገሮች በሚመለከት በአምላክ ቃል ውስጥ ተለይተው የተጠቀሱ ሕጎች ባይኖሩም ጥሩ መምሪያዎች ግን ተሰጥተዋል። ወጣቶች ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ መጣር ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስም በዚህ በኩል ይረዳቸዋል።

21 ወላጆቻችሁ ተጨማሪ መምሪያዎችን የማውጣት ተገቢ የወላጅነት መብት አላቸው። የምትኖሩበት ቤት እንዲያው እጅ እንዳመጣ ብዙ ዓይነት ቀለማት የተቀባ ቢሆን ተመልካቾችን የቤቱ ባለቤት ወይም ሚስቱ አእምሮአቸው ትክክል የሚያስብ ስለመሆኑ ጥያቄ ሊመጣባቸው ይችላል። ወይም ደግሞ ቤቱ ችላ በመባሉ ምክንያት ግድግዳው ፈራርሶና ቀለም ቅቡም ተላልጦ ቢታይ ሰዎች ለቤቱ ባለቤት እምብዛም አክብሮት አይኖራቸውም። አንድ ቤት ባለቤቶቹን ከሚወክለው ይበልጥ እናንተ ወጣቶች ወላጆቻችሁን ትወክላላችሁ። በወላጆቻችሁ ስም ትጠራላችሁ፤ የምታደርጉትና የምትናገሩት ነገር ወላጆቻችሁ የሰጧችሁን ሥልጠናና እነሱ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ እንደሚያንፀባርቅ ሁሉ ቁመናችሁም የሚያንፀባርቀው ይህንኑ ነው። ከሁሉ በላይ ግን የአምላክ አገልጋይ ነኝ የምትሉ ከሆነ እሱንም ትወክላላችሁ። ታዲያ የሰውነታችሁ አቋምና አለባበሳችሁ ከምትሉት ነገር ጋር ይስማማልን?

22 “ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] ናችሁ” ያለውን የኢየሱስን ቃል አስታውሱ። (ዮሐንስ 13:17) የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ትክክል እንደሆነ ይታያችኋልን? በሕይወታችሁ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ በማዋል እውነተኛ ማስተዋልና የባሕርይ ጥንካሬ እንዳላችሁ ልታሳዩ ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ በአምላክ፣ በልጁና አምላክን በሚወዱና በሚያገለግሉ ሰዎች ሁሉ ፊት አስደሳች መስላችሁ እንደምትታዩ በማወቅ ትደሰታላችሁ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 53 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ልብሶቻችሁ ስለ እናንተ ምን ይላሉ?