እቤት መሆን ይሰለችሃልን?
ምዕራፍ 9
እቤት መሆን ይሰለችሃልን?
1–3. (ሀ) በዛሬው ጊዜ በብዙ ቤቶች ላለው የመሰልቸት ስሜት ምክንያት የሆነው ምን ይመስልሃል? (ለ) ከቤትህ ውጭ ባሉት ነገሮች ላይ ፍላጎት ማሳደሩ ብቻውን ስህተት ነውን?
ፍጹም ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት ቤቶች የሉም። የመሰልቸት ችግር ግን በአሁኑ ጊዜ በብዙ ወጣቶች ዘንድ የተለመደ ነገር ነው። ከዚህ በፊት ይህ ችግር እምብዛም የነበረ አይመስልም። ከአያሌ ዓመታት በፊት ቤተሰቦች ብዙ ነገሮችን አብረው ይሠሩ ስለነበር ይበልጥ የተቀራረቡ ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ላሉ ብዙ ወጣቶች ግን “ቤት” ማለት እንዲሁ መኖሪያ፣ ምግብ የሚበላበትና የሚተኛበት ቦታ ማለት ብቻ ነው።
2 መሰልቸት ለአንተም ችግር ሆኖብሃልን? ከሆነ ከቤትህ የምታገኘውን ደስታ በጣም ሊቀንስብህ ይችላል። ምናልባትም አንዳንድ ጊዜ ለብቻህ ጎጆ መውጣትና በራስህ መንገድ አስደሳች ሕይወት የመፈለግ ስሜት ይመጣብህ ይሆናል።
3 ይህ ባንድ በኩል በወጣትነት ጊዜ ያለ ተፈጥሮአዊ የዕድገት ክፍል ነው። እያደግህ ስትሄድ አመለካከትህም በተፈጥሮ እየሰፋ ይሄዳል። ነገሮችን የማወቅ ፍላጎትህ ያድጋል። አዳዲስ ነገሮችን መወጠንና መሞከር ደስ ይልሃል። ጥያቄው ይህን የሰፋ አመለካከት የምትገልጸው እንዴት ነው? የሚል ነው። ቤትህ ወይም የወላጆችህ መመሪያና ቁጥጥር ሊሰለችህ ይገባልን? የአብዛኛው የመሰልቸት ስሜት ትክክለኛ መንስኤ ምንድን ነው? መፍትሔውስ?
አመለካከትህ ልዩነት ሊያመጣ ይችላል
4–6. (ሀ) የአንድ ሰው የራሱ አመለካከት ለመሰልቸትም ሆነ ላለመሰልቸት ከፍተኛ ወሳኝነት ያለው እንዴት ነው? (ለ) የቤትህን መንፈስ ለማሻሻል አንተ በግልህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? (ፊልጵስዩስ 2:3, 4)
4 እውነት ነው፤ አንዳንድ ቤቶች ሰላምና እርካታ የማያስገኝ እውነተኛ ችግር አለባቸው። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የቤተሰብ ሕይወትህን አስደሳች ወይም አሰልቺ መሆኑን የሚወስነው
የራስህ አመለካከት ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በተመሳሳይ ሁኔታ እየኖሩ ደስታን ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ወጣቶች ሲኖሩ በዚያው ዓይነት ሁኔታ የሚገኙ ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ይሰለቻሉ። ልዩነቱ አንዳንዶቹ ወጣቶች ስለ ቤተሰብ ኑሯቸው የተሻለ አመለካከት ያላቸው መሆኑ ነው። ስለዚህ መሰልቸትንና ሌሎች ብዙ ችግሮችንም መቋቋም በአብዛኛው ስለ ችግሮቹ ያለህ የራስህ አመለካከት ጉዳይ ነው።5 ለምን ጉዳዩን እንደሚከተለው አድርገህ አትመለከተውም:- እያንዳንዱ ቤተሰብ የየራሱ ባሕርይ አለው። ይህ ባሕርይ በአንድ ሰው ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለአጠቃላዩ የቤተሰብ ባሕርይ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ነገር አለው። የአንተ ቤተሰብ ምን ይመስላል? ቤታችሁ ሞቅ ያለና አስደሳች ቦታ ነውን? አብራችሁ ስትሆኑ ትደሰታላችሁን? በምግብ ሰዓቶች አስደሳች ጭውውቶች ታደርጋላችሁን? ነገሮችን አብሮ በመሥራትና
አንዱ ለሌላው አንድ ነገር በማድረግ ደስታ ታገኛላችሁን? ወይስ እርስ በርስ እምብዛም ግድ ሳይኖራችሁ ወይም ምንም ደንታ ሳይኖራችሁ በየፊናችሁ የምትሄዱ ናችሁ? የትኛውን ትመርጣለህ?6 ነገሮች አንተ እንደምትፈልገው ሳይሆኑ ሲቀር ጥፋቱ የሌሎች ነው ብሎ ማሳበብ ቀላል ነው። ይሁንና ሌሎችን ከማማረርህ በፊት “እኔ ራሴ ለቤተሰቡ ባሕርይና መንፈስ ምን አስተዋጽኦ እያደረግሁ ነው? መሻሻልን ለማምጣት ምን ያህል እየጣርኩ ነው?” ብለህ ራስህን ጠይቅ። አንዲት መርከብ በባሕር ማዕበል እየተንገላታች ቢሆን አንዱ መርከበኛ ጥግ ይዞ ቢቀመጥና ቢያማርር ምንም ጥቅም የለውም። መርከቧ ወደተፈለገው ማረፊያ ቦታ ለመድረስ በሞገደኛው ባሕር ላይ መሄዷን እንድትቀጥል ለማድረግ እያንዳንዱ ሰው የእርዳታ እጁን በመሰንዘር መረባረብ ይኖርበታል።
7–9. በምንሠራው በማንኛውም ሥራ መሰልቸትን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
7 ብዙውን ጊዜ ወጣቶች እንዲሠሩት የተሰጣቸውን ሥራ የቱን ያህል ዋጋ እንዳለው ሳይገነዘቡ ይቀራሉ። በትምህርት ቤት ወይም በቤት ወይም በሥራ ቦታ የተሰጠህ ሥራ ምንም ይሁን ይህ ሥራ አሁንና ለወደፊቱም የአንተንና የሌሎችንም ሕይወት እንዴት እንደሚነካ ለመረዳት ሞክር። ይህን ማድረግ ከቻልክ የተሰጡህን ሥራዎች በዓላማ ለመሥራት ትችላለህ። ይህም በኑሮህ በመደሰትና በመሰልቸት መካከል ያለውን ልዩነት ሊያመጣ ይችላል።
8 እንዲያውም አሁን አሰልቺ ሆነው ያገኘሃቸው ሥራዎች ወደፊት በሕይወትህ ስኬታማ እንድትሆን ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ባሕርያትና ልማዶችን እንድትገነባ ሊያደርጉህ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ወጣት ከሆንክ የአይሮፕላን ሞዴል ሠርተህ ታውቃለህን? ከሆነ መጀመሪያ ፍሬም የሚሆኑትን ብዙ ቁርጥራጮች ማገጣጠምና ከዚያም ፍሬሙን መሸፈን አስፈልጎህ ነበር። ሞዴሉ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ፍሬሙ ላይታይ ይችላል። ይሁንና ለአይሮፕላኑ ጥንካሬና ቅርጽ የሰጠው ፍሬም ባይኖር ኖሮ ጥሩ ሞዴል ሊሆን አይችልም ነበር። ወይም ደግሞ ወጣት ሴት ከሆንሽ ቀሚስ ሰፍተሽ ታውቂያለሽን? ቀሚሱን ሰፍተሽ ከጨረሽ በኋላ ስፌቱ አይታይ
ይሆናል። ይሁንና እነዚያ ስውር ስፌቶች ባይኖሩ ኖሮ ቀሚስ አይኖርም ነበር።9 በትምህርት ቤት የምትማረው ብዙ ነገር ወይም እቤትህ ውስጥ የምትሠራው ነገርም እንደዚሁ ነው። ለወደፊቱ የውጤት መቃናትና የሥራ መሳካት የሚረዳህን መሠረት የሚጥሉት የጠቅላላ ነገሮች አንዱ ክፍል ይኸው ነው። ስሜት የማይቀሰቅሱና የማያስደስቱ ሥራዎችን ወይም አሰልቺ የሆኑ የዘወትር ሥራዎችን በተደጋጋሚም ቢሆን በመሥራት ጽናትንና ቁርጠኝነትን ልትማርና ውስጣዊ ጥንካሬን ልታገኝ ትችላለህ።
በራስ ተነሳስቶ መሥራትና እየሰፋ የሚሄድ ነገሮችን የማወቅ ፍላጎት
10–12. (ሀ) አንድ ሰው “የምሠራው አጣሁ” ሲል አብዛኛውን ጊዜ በግለሰቡ በኩል የጎደለው ምንድን ነው? (ለ) ለእንዲህ ዓይነቱ ጉድለት ምክንያት የሚሆነውስ ምን ዓይነት መዝናኛ ነው?
10 ብዙውን ጊዜ በዕረፍት ጊዜያት “የምሠራው አጣሁ” የሚል እሮሮ ይሰማል። አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራ አስደሳችና ጠቃሚ ነገር ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ችግሩ በራስ ተነሳስቶ የመሥራት፣ የፈጠራና የማሰብ ችሎታ ማነስ ነው። ወይም ደግሞ እሮሮው የፍላጎታችን መስክ በጣም ጠባብና አነስተኛ መሆኑን ሊያሳይ ይችላል።
11 የአሁኑ ሥርዓት በተለይ እቤት ውስጥ የሚሠሩ ነገሮችን በሚመለከት በራስ ተነሳስቶ መሥራትን የሚያበረታታ አይደለም። በዛሬው ጊዜ ወጣቶችም እንኳን ሳይቀር የለመዱት ንቁ ተሳታፊዎች መሆንን ሳይሆን ተመልካቾች መሆንን ነው። በቤትህ ስትሆን ጊዜህን የምታሳልፈው ተንቀሳቃሽ ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመመልከት፣ በቴፕ የተቀዱ ሙዚቃዎችን በማዳመጥ ወይም ሌሎች በአንዳንድ ስፖርታዊ ውድድሮች ሲጫወቱ በመመልከት ነውን?
12 እንደዚያ ማድረጉ ነገሮችን ራስህ ከመሥራት ወይም ነገሮች እንዴት እንደሚሠሩ ከመማር በጣም የቀለለ ነው። ነገር ግን የኋላ ኋላ መሰልቸትን ሊያስከትል ይችላል። ለመዝናናት በሌሎች ላይ በጣም እንድትደገፍ ያደርግሃል። ሕይወትን አስደሳች ለማድረግ
ነገሮችን ራስህ መሥራት የማትችል ሆነህ እንድትቀር ያደርግሃል። ይህ ለሕፃናት ምንም አይደለም። በመጎልመስ ላይ ላሉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ግን አይበጅም።13, 14. የሚያስደስቱህና በአንተ በኩል በራስ መነሳሳትን ወይም መሳተፍን የሚጠይቁ አንዳንድ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
13 ታዲያ የፍላጎትህ መስክ የቱን ያህል ሠፊ ነው? የሚጠኑና የሚሞከሩ ጠቃሚ እንቅስቃሴዎችና የዕውቀት መስኮች ወሰን የላቸውም። ማንበብ ቴሌቪዥን ከመመልከት የበለጠ ጥረት ይጠይቃል። የሚከፍለው ዋጋ ግን የበለጠ ነው። መጻሕፍት ያልዳሰሱት ምንም ዓይነት የሙያ መስክ፣ ችሎታ ወይም ንግድ፣ ሥፍራ ወይም ሕዝብ ወይም እንስሳ የለም። ይበልጥ እያነበብክ በሄድክ ቁጥር ከማንበብ የምታገኘው ደስታ እየጨመረ ከመሄዱም ሌላ እውቀትን ለመቅሰም ያለህ ችሎታም ከፍ እያለ ይሄዳል። ነገር ግን ‘ጊዜን ለማሳለፍ’ ያህል ብቻ ማንበቡ በቂ አይደለም። ምን ብታነብ እንደሚጠቅምህ መወሰን ያስፈልግሃል። እንዲህ ካደረግህ በሐሳብህ አንድ ግብ ይዘህ ለማንበብ ትችላለህ። ይህ ግብ ነገሮችን መሥራትን እንድትለምድ በማድረግ አሁንም ሆነ ወደፊት ሕይወትህን ያበለጽግልሃል።
14 እርግጥ ነው፣ ሌሎች የሚወዱትን ነገር መሥራት የሚያስደስታቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች በእንጨት ወይም በብረታ ብረት መሥራት ደስ ሲላቸው ሌሎች ደግሞ ፎቶግራፍ ማንሳት ወይም አትክልተኛነት ሊወዱ ይችላሉ። አንዳንድ ልጃገረዶች ወጥ መሥራትና እንጀራ መጋገር ደስ ሲላቸው ሌሎች ደግሞ ልብስ መስፋት ወይም ፀጉር ማሳመር ሊመርጡ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ በቤትም ሆነ በሌላ ቦታ አዳዲስ ነገሮች መሥራትን መማርና ጥራት ያለው ሥራ የመሥራት ችሎታን ማሳደግ እርካታን ያስገኛል፤ ሕይወትንም አስደሳች ያደርገዋል።
15–18. (ሀ) አንድ ሰው ለሌሎች አንድ ነገር መሥራትን ልማድ ሲያደርግ የራሱ ሕይወት የሚነካው እንዴት ነው? (ሥራ 20:35) (ለ) አንድ ክርስቲያን ወጣት ለሌሎች ሰዎች ሊያደርግላቸው የሚችለው ከሁሉ የበለጠ ነገር ምንድን ነው? (ማቴዎስ 24:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16) (ሐ) ጥረት ለሚደረግለት ለማንኛውም ጠቃሚ ነገር ጽናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ለራስህ ጥቅም ስትል አንድ ነገር ማድረግ የማያጓጓህ ከሆነ ከቤት ጀምረህ ለሌሎች ሰዎች የሚጠቅም ነገር ለምን አትሠ
ራም? ለራስህ ቢሆን ኖሮ ምንም ስሜት የማያሳድርብህ ሥራ ለሌላ፣ ለምሳሌም ለቤተሰብህ አባል፣ ለጓደኛ፣ በተለይም ለተቸገረ ሰው ስትሠራው እውነተኛ ፍላጎት ሊቀሰቀስብህ ይችላል። ይህም ጥልቅ እርካታ የሚሰጥ ሲሆን ለእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ማለቂያ የለውም። ሌሎች አንድ ነገር ሥራልኝ ብለው እስኪጠይቁህ አትጠብቅ። ለሌሎች የምትሠራላቸው ነገር በተለይ ሳይጠብቁት በሚደረግበት ጊዜ የሚያገኙት ያልታሰበ ደስታ ለአንተም ደስታ ይጨምርልሃል። ሞክረህ እየው።16 ለሌሎች አንዳንድ ነገሮችን በመሥራት ልትጠቀም የምትችልበት ሌላው መንገድ እነሆ። አምላክ አዲስ ሥርዓት ለማምጣት የሰጠው የተስፋ ቃል በእውነት የሚያስደስታቸው ወጣቶች ይህን የምሥራች ለሌሎች ማካፈሉ ለሕይወታቸው ተጨማሪ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ አግኝተውታል። እውነትን የተጠሙ ሰዎችን ማግኘትና እነሱን ለመርዳት መቻል መልሶ ራስን የሚክስ ሥራ ነው። እውነትን የተጠሙት ሰዎች እውነትን ከማይቀበሉት ጋር ሲነፃፀሩ በቁጥር በጣም አነስተኛ መሆናቸው የዚህን ሥራ አነቃቂነት አይቀንሰውም። በዚህ ፈንታ ይበልጡን ፍላጎት የሚቀሰቅስ ተፈታታኝ ሥራ ያደርገዋል። ጽናትንና እምነትን ይጠይቃል። ጽናትና እምነትም የመሰልቸትን ስሜት ለመዋጋት በጣም የሚያስፈልጉ ጠባዮች ናቸው።
17 ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ስለምናቀርበው አገልግሎትና አምላክን ለሚያገለግሉት ሰዎች “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” ብሎ ተናግሯል። (ገላትያ 6:9) በተመሳሳይም እውነተኛ ዓላማና ጥቅም ያላቸውን ችሎታዎች ለማዳበር በምትፈልግበት ጊዜ የድካምህን አንዳንድ ውጤቶች ማጨድ እስክትጀምር ድረስ መጽናት ያስፈልግሃል።
18 እንዲህ ስታደርግም ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር ልታዳብራቸው በሚገቡ ሌሎች ሙያዎች ላይ የምታደርገውን ጥናትና ሙከራ ልታሰፋና ከዚህ የተነሳ የተሻልክ፣ አስደሳችና ጠቃሚ ሰው ልትሆን ትችላለህ። ወላጆችህና ሌሎችም የቤትህ ሰዎች ከአንተ ጋር በመኖራቸው ደስ ይላቸዋል፤ አንተም በቤት ስትሆን ከመሰልቸት ትድናለህ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 68 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በባሕር ጉዞ ላይ ችግር ሲያጋጥም የሁሉንም ሙሉ ትብብር ይጠይቃል። በቤት ውስጥ ችግር ሲኖር ለሰላማዊ ሁኔታ መንገድ በመፈለግ እገዛ ታደርጋለህን?