በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ሙሉ ሰውነት ማደግ

ወደ ሙሉ ሰውነት ማደግ

ምዕራፍ 3

ወደ ሙሉ ሰውነት ማደግ

1–6. እስከምንወለድበት ጊዜ ድረስ ባለው እድገታችን ያሉት አንዳንድ አስደናቂ እውነቶች ምንድን ናቸው? ለዚህ ሁሉስ ምክንያት በመሆኑ ሊመሰገን የሚገባው አለን? (መዝሙር 139:​13–18)

በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዳችን እንዴት ወደ መኖር እንደመጣን ብንመረምር ልንጠቀም እንችላለን። እስቲ አስበው:- ከጥቂት ዓመታት በፊት በብዕር ከሚጻፍ ነጥብ የምታንስ የነጠላ ሴል ጽንስ ነበርክ። ከዚያ እጅግ አነስተኛ አጀማመር ተነስተህ በእናትህ ማሕፀን ውስጥ ማደግ ጀመርክ። ከጊዜ በኋላ ሰውነትህ በሚያስብ አእምሮ፣ በሚያዩ ዓይኖች፣ በሚሰሙ ጆሮዎችና በሌሎች አስደናቂ የአካል ክፍሎች የተሟላ ሆነ። ይህ አስገራሚ እድገት የተከናወነው እንዴት ነው?

2 ወላጆችህ ምን ዓይነት ሰው መሆን እንዳለብህ የሚወስን ንድፍ አውጥተው አልወለዱህም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሁሉ የተከናወነው የአባትህ ዘር በእናትህ ማሕፀን ውስጥ ካለው የእንቁላል ሴል ጋር ተዋሕዶ በተጸነሰው እንቁላል ውስጥ ነው። በዚያ ረቂቅ ሴል ውስጥ ፍጹም አዲስ ሰው የሆንከውን አንተን ያስገኘው ፕላን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተነደፈ።

3 አንተን ለመፍጠር የሚያስፈልገው ጠቅላላው መረጃ የዚያች ረቂቅ የሴል ጽንስ ክፍል በሆነው ዲ ኤን ኤ (DNA) * ውስጥ ይገኛል። ዲ ኤን ኤ በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጂን ተብለው የሚጠሩት የዘር አወራረድን የሚቆጣጠሩት ንጥረ ነገሮች ዋነኛው ክፍል ነው። እነዚህ ጂን የሚባሉ ነገሮች በሃያ ሦስት ጥንድ ክሮሞሶሞች ውስጥ ተያይዘዋል። በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ የታመቀው መረጃ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ በሰው ቋንቋ ቢፃፍ ኖሮ አንድ ክፍል የሚሞሉ መጻሕፍት ባስፈለጉ ነበር። ሆኖም ከዚህ ይበልጥ አስገራሚ የሚሆነው ይህ ሁሉ ዝርዝር መረጃ ለእያንዳንዱ አዲስ የሰውነት ሴል የሚተላለፍ መሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት እያንዳንዱ ሴል የመጀመሪያው ጽንስ እንቁላል የያዘውን ያንኑ መረጃ ይዟል!

4 ‘ታዲያ ዲ ኤን ኤ የሰውን የተለያዩ ብዙ የአካል ክፍሎች ሲገነባ የሚፈልገውን መረጃ ብቻ በሚፈልገው ጊዜ ላይ ሊጠቀምበት ነጥሎ መውሰድ የሚችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለምሳሌ ዓይንን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን መመሪያዎች ብቻ ነጥሎ ለመምረጥ እንዴት ይችላል? ዓይንን በሚገነባበት ጊዜ ጆሮዎችህን፣ ኩላሊቶችህን፣ ጉበትህንና ሌሎችን የአካል ክፍሎች ለመገንባት የሚያገለግሉትን ሌሎች መረጃዎች የሚያግዳቸው እንዴት ነው?

5 ነገሩ ምስጢር ነው። ሰዎች ተመራምረው ገና አልደረሱበትም። የአንድ ታላቅ ፈጣሪ ንድፍ ነው! ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ ስለ ሰው አካል ካወቀው ተነስቶ ለአምላክ እንዲህ በማለት ተናገረ:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመስግንሃለሁ፣ ሥራህ ድንቅ ነው። ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።” (መዝሙር 139:​14) አንተስ የሚሰማህ እንደዚህ ነውን?

6 አንተ የተጀመርክበት ጽንስ የሆነው ነጠላ ሴል በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሴሎችን የያዘ አስገራሚና የተወሳሰበ አደረጃጀት ያለው ሙሉ በሙሉ የዳበረ ሕፃን ሆነ። ከዚህ ወዲያ ዕድገትህ እንደዚህ የተፋ⁠ጠነ አይሆንም! ሆኖም ከተወለድህ ከአሥራ ሦስት ወይም ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ሌላ የተፋጠነ የዕድገት እመርታ ትጀምራለህ። በዚህ ልዩ ጊዜ ላይ ከልጅነት ጐልማሳ ወንድ ወደመሆን መለወጥ ትጀምራለህ። * ጉርምስና በመባል የሚታወቀው ጠቅላላ የሽግግር ወቅት ለተወሰኑ ዓመታት ይቆያል። ይህ ወቅት የሚያበቃው ወደ አካላዊ ጉልምስና ስትደርስ ይኸውም በአብዛኛው በሃያና በሃያ ሦስት ዓመታት ዕድሜ መካከል ነው። ይህ ወቅት ከዕድሜህ ውስጥ ቀላሉ ጊዜ አይደለም፤ ሆኖም በጣም በጣም ወሳኝ የሆነ ወቅት ነው። ለወደፊቱ ዕድገትህ የመፈተኛ መድረክ ነው።

በአፍላ ጉርምስና ጊዜ የሚከሰቱ ለውጦች

7–12. (ሀ) በአፍላ የጉርምስና ጊዜ በወንድ ላይ ምን ለውጦች ይደርሳሉ? ስለነዚህ ለውጦች ለመጨነቅ አንዳች ምክንያት ይኖራልን? (ለ) አንድ ወጣት የፆታ ብልቱ ልጆችን ለመውለድ ወደሚያስችለው ደረጃ ማደጉን እንዴት ሊያውቅ ይችላል?

7 በእንግሊዝኛ ፑበርቲ የሚባለው የአፍላ ጉርምስና ወቅት የጉርምስናን የመጀመሪያ ወቅት ይሸፍናል። ባጭሩ ይህ ወቅት በፆታ የመብሰል ምልክቶች የሚታዩበት ዕድሜ ነው። ይህ ዕድሜ በአጠቃላይ ለወንዶች አሥራ አራት ዓመት ለሴቶች ደግሞ አሥራ ሁለት ዓመት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል፤ ሆኖም ከዚህ ከፍና ዝቅ ሊልም ይችላል። በአሥራ አንድ ወይም በአሥራ ሁለት ዓመትህ ወደ አፍላ የጉርምስና ጊዜህ ገብተህ ይሆናል፤ አለዚያም አሥራ አምስት ወይም አሥራ ስድስት ዓመት ሆኖህ ገና በፆታ መብሰል አልጀመርህ ይሆናል። ቀደም ብሎ ወይም ዘግይቶ መብሰል ያልተለመደ ነገር ስላልሆነ ምንም የሚያስጨንቅህ ምክንያት የለም። በአፍላ ጉርምስናህ ጊዜ ይመጣሉ ብለህ መጠበቅ የምትችላቸው አንዳንድ ችግሮች ምንድን ናቸው?

8 አንደኛ ነገር ፈዛዛነትና የቅንብር ጉድለት ይታይብህ ይሆናል። ይህም የሚሆነው አጥንቶችህ እየረዘሙ ስለሆነና ጡንቻዎችህም አብረዋቸው ስለሚለጠጡ ነው። በዚህ መስፋፋት ወቅት አንዳንዶቹ የአካል ክፍሎች በፍጥነት ሲያድጉ ሌሎቹ ደግሞ ወደኋላ የቀሩ ይመስላሉ። ቢሆንም በዚህ ምክንያት የሚደርሰው የመፍዘዝ ሁኔታ ያልፋል። በአንድ ዓይነት አደጋ የሚደርስን ጉዳት ለመከላከል ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ ጠቃሚ ቢሆንም በዚህ ምክንያት መጨነቅ አያስፈልግም።

9 ከሚለጠጡት የአካል ክፍሎች መካከል የድምፅ ጅማቶች ይገኙበታል። ተጨማሪው ርዝመት ድምፁ እንዲጎረንን ያደርገዋል። ሆኖም በመለጠጡ ሂደት ወቅት እየተናገርህ እያለህ ሳታስበው “ቀጭን” ድምፅ ታወጣ ይሆናል። ይህም ራሱ በጉርምስና ጊዜ የሚያጋጥም “አንዱ የዕድገት ችግር” ነው። ስለዚህ ይህ በሚደርስበትና ሌሎችም በሚስቁበት ጊዜ አንተም ከእነርሱ ጋር አብረህ ሳቅ። እንዲህ ካደረግህ ሊከተል የሚችለው ማንኛውም ሐፍረት ቶሎ ያልፍልሃል።

10 ለእነዚህ አካላዊ ለውጦች ሁሉ ምክንያቶቹ እጢዎችህ ናቸው። እነዚህም ታይሮይድ፣ አድሬናልና ጎናድስ (የፆታ እጢዎች) የሚባሉትን ይጨምራሉ። እነዚህ እጢዎች ሌላም ለውጥ ይፈጥራሉ። ከእነዚህም አንዱ በአባለዘር ብልቶች አካባቢና በብብትና በደረት ላይ የጸጉር መብቀል ነው። የጸጉሩ ብዛት ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ስለዚህ የቱን ያህል “ወንድ” እንደሆንህ የሚያመለክት ነገር አይደለም። በፊትህም ላይ ጸጉር መታየት ይጀምራል። ምንም እንኳን በመጀመሪያ “ለስለስ ያለ ስስ ጸጉር” ቢሆንም ጺምን የመላጨቱ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ በፍጥነት እየተቃረበ ነው።

11 አብዛኛውን ጊዜ ወደ አካለ መጠን በማደግ ላይ ላሉ ወንድ ልጆች ምናልባት የሚረብሽ ምክንያት የሚሆንባቸው አባለ ዘራቸውን የሚመለከት ይሆናል። በአፍላ ጉርምስና ጊዜ እነዚህ ብልቶች ሙሉ እድገታቸው ላይ መድረስ ብቻ ሳይሆን መሥራትም ይጀምራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በዘሌዋውያን 15:​16, 17 ላይ ‘ስለ ዘር መውጣት’ ይጠቅሳል። ወላጆችህ ቀደም ብለው ስለ ጉዳዩ ሳያወያዩህ ቀርተው ከሆነ የመጀመሪያው የዘርህ መውጣት በጣም የሚረብሽ ተሞክሮ ሆኖብህ ይሆናል። የዚህ ዘር መውጣት ምክንያቱ ምንድን ነው?

12 ልጅ ለመውለድ ወደሚያስችልህ ዕድገት ስትደርስ የፆታ ብልትህ የወንዴ ዘር የሚባል ፈሳሽ ማውጣት ይጀምራል። እሱም ከውኃ ወፈር ያለ ፈሳሽ ሲሆን ይህን ያህል ብዛት ባይኖረውም በሚልዮን የሚቆጠሩ ጥቃቅን የስፐርም ሴሎችን የያዘ ነው። ከነዚህ ሴሎች አንዱ የሴትን የዕንቁላል ሴል ጽንስ እንዲሆንና እያደገ ሄዶ በመጨረሻው ሕፃን እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። ሰውነትህ ይብዛም ይነስ እንጂ በየወቅቱ ይህንን ዘር ያስወጣል። አብዛኛውን ጊዜ የዘሩ መፍሰስ የሚከናወነው በእንቅልፍ ላይ ሆነህ በምታልምበት ጊዜ ነው።

የፆታ ግንኙነት ዓላማ

13–15. (ሀ) አምላክ ፆታን የሰጠው ለምን ዓላማ ነው? እርሱን የሚቆጣጠሩ ሕጎችን የደነገገውስ ለምንድን ነው? (ዕብራውያን 13:​4) (ለ) ስለ ፆታ ግንኙነት አስተማማኝ መረጃ የሚገኝበት የተሻለ ቦታ የት ነው? (ምሳሌ 6:​20)

13 ፈጣሪያችን ፆታን የሰጠው አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የጠለቀ ፍቅሩን የሚገልጽበትና ልጆችን የሚወልድበት መንገድ እንዲሆን ነው። ይሁን እንጂ አምላክ የፆታ ግንኙነት በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ብቻ መፈፀም እንደሚገባው በመግለፅ ሕጎችን ደንግጎአል። ይህም የሆነበት ምክንያት ወደ ዓለም የሚመጣው ማንኛውም ሕፃን የማሳደጉን ሙሉ ኃላፊነት የሚወስዱ አባትና እናት እንዲኖሩት አምላክ ዓላማው ስለሆነ ነው። በዚህ ምክንያት ያልተጋቡ ሰዎች የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ በአምላክ ፊት ኃጢአት ነው።

14 በሌላ በኩል ግን ለተጋቡ ሰዎች የፆታ ግንኙነት አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን የሚገልጹበት ግሩም የሆነ መንገድ ነው። ባልየው የወንዴ ብልቱ ወደ ሚስቱ ማሕፀን እንደሚገባ ሆኖ ወደ ሚስቱ ተጠግቶ ይተኛል። ይህ ለሁለቱም ከፍ ያለ ደስታ ሊሰጣቸው ይችላል። በዚህም ሂደት ወቅት የባልየው የስፐርም ሴሎች በወንድ ብልቱ በኩል ከሰውነቱ በመውጣት በቀጥታ ወደ ሚስቱ ማሕፀን ይተላለፋሉ። እነዚህ የስፐርም ሴሎች በማሕፀን ካናል ያልፉና በሚስቲቱ ውስጥ የበሰለ የእንቁላል ሴል ካለ ከባልየው የስፐርም ሴሎች አንዱ ከእንቁላሉ ጋር ይገናኛል። በባልየውና በሚስቲቱ የዘር ሴሎች ግንኙነት ምክንያት ጽንስ የያዘው ሴል እያደገ ይሄድና ሕፃን ይሆናል። ስለዚህ አምላክ የፆታ ብልቶችን ለተቀደሰ ዓላማ ይኸውም ሕይወትን ለማስተላለፍ እንደሠራቸው ለማየት ትችላለህ። በአምላክ ሕግ መሠረት ሊሠራባቸው የሚገባውም ለዚህ ነው።

15 የፆታን ዕድገት በሚመለከት ላሉህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ወላጆችህን በተለይ አባትህን መጠየቅ ነው። አባትህ አንተ ያለፍክበትን ማንኛውንም ነገርና ከዚያም ሌላ ብዙ ተሞክሮ አሳልፎአል። ሌሎች ወጣቶች ጥቂት እውነትና ብዙ የፈጠራ ወሬ ያለበት ከፊል እውነት ብቻ የያዘ መረጃ ሊሰጡህ ይችሉ ይሆናል፤ አባትህ ግን ሊረዳህና ደስታ ሊያመጡልህ የሚችሉ ጥሩ መረጃዎችን ሊሰጥህ ይችላል። አባትህ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ዕውቀት ወይም ምክር ሊሰጥህ የማይችል ከሆነ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል ማወቅ ይጠቅምሃል። በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች አንተን ለመርዳት ደስተኞች ሆነው ታገኛቸዋለህ።

ለኃላፊነት ብቁ መሆንህን ማሳየት

16–18. (ሀ)ወላጆች የተወሰነ ነፃነት እንድትይዝ የሚያበረታቱህ በምን መንገዶች ነው? በነዚህ መብቶች የምትሠራው ነገር ወደፊት መብት የማግኘት አጋጣሚህን እንዴት ሊነካብህ ይችላል? (ለ) ብዙ ወጣቶች “በዱርዬዎች ቡድን” ውስጥ የሚገቡት ለምንድን ነው? ይህስ ወደምን ሊመራቸው ይችላል? (1 ቆሮንቶስ 15:​33)

16 ጐልማሳ ወንድ ስትሆን ራስህን የማሳወቅ ይኸውም በግለሰብ ደረጃ ተለይተህ የምትታወቅ ሰው መሆንህን የማሳወቅ ምኞት ቢያድርብህ ይህ በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው። መጠነኛ ነፃነት የማግኘት ምኞት ቢኖርህም እርሱም ባሕሪያዊ ነገር ነው። ወላጆችህም ራስህን ችለህ መኖር ለምትችልበት ጊዜ ሊያዘጋጁህ ይችላሉ። እንዴት?

17 ይህን የሚያደርጉት ቀስ በቀስ ተጨማሪ ኃላፊነት በመስጠትና ስለምትሠራቸው ነገሮች አንዳንድ ውሳኔዎች በማድረግ ተካፋይ እንድትሆን መብት በመስጠት እንደሆነ አያጠራጥርም። በትምህርት ቤት ስለምትወስዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ያለህን ምርጫ እንድትገልጽ ይጠይቁህ ይሆናል፤ ወይም የትርፍ ሰዓት ሥራ እንድትይዝ ይፈቅዱልህ ይሆናል። በግልህ የምትጠቀምባቸውን አንዳንድ ዕቃዎች ራስህ እንድትገዛ ይፈቅዱልህ ይሆናል። ወላጆችህ በዚህ ረገድ የሚያደርጉት ምንም ይሁን ምን ለኃላፊነት ብቁ መሆንህን ማሳየቱ የአንተ ፋንታ ነው። የሕፃንነት ጠባይ የምታሳይ ከሆነ ወይም “ትዕቢት” ከተሰማህ ጐልማሳ ወንድ መሆንህን እስክታሳይ ድረስ መብቶችህን መቀነስ ይኖርባቸው ይሆናል።

18 ይህ ራስን የማሳወቅና መጠነኛ ነፃነት የመፈለግ ምኞት ሌሎች ተፈጥሮአዊ ምኞቶችን አስከትሎ ይመጣል። በግለሰብ ደረጃ ማንነትህንና ችሎታዎችህን ሌሎች ሊያደንቁልህ እንደሚያስፈልግ ይሰማሃል። አንዳንድ ወጣቶች ራስን የማሳወቅና የአንድ ወገን አባል የመሆን ስሜታቸውን የሚያረኩት “የዱርዬዎች” ቡድን አባል በመሆን ወይም ቡድኑን በማቋቋም ነው። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉት ቡድኖች ባጠቃላይ የየራሳቸውን የጠባይና የድርጊት መመሪያ ያወጣሉ። ይህም አብዛኛውን ጊዜ ወደ መጥፎ ተግባር፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ወደ ከባድ ወንጀል እንደሚመራ መረጃዎቹ ያሳያሉ። ወጣቶች ወደ ችግር ገብተው የሚገኙት ከማንኛውም ሌላ ምክንያት ይልቅ ምናልባት በመጥፎ ባልንጀርነት ሳይሆን አይቀርም።

19, 20. ከወላጆችህ ጋር ጥሩ ግንኙነት መያዝህ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ምንስ ሊያበላሸው ይችላል? (ምሳሌ 23:​24, 25)

19 በዚህ ዕድሜ ላይ ትልቅ ሰው ስትሆን ምን ዓይነት የሰውነት አቋም እንደሚኖርህ አንዳንድ ግንዛቤዎችን ማግኘት ትጀምራለህ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የተሰወረ የልብ ሰው” እንደሚለው ወደፊት በውስጥህ ምን ዓይነት ሰው እንደምትሆን የበለጠ ማሰብ መጀመርም ይገባሃል። (1 ጴጥሮስ 3:​4) ተጨማሪ ነፃነት የማግኘት ፍላጎትህ በዚህ የዕድገትህ ደረጃ ላይ ከወላጆችህና ከቀረው ቤተሰብህ እንዲነጥልህ የምትፈቅድበት ጊዜ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ በአፍላ የጉርምስና ጊዜህ የሚያጋጥሙህ ለውጦች የሚሰሙህና ልትቆጣጠራቸው የሚያስፈልግህ አዳዲስ ውስጣዊ ግፊቶች የቤተሰብህን ፍቅርና የማያቋርጥ ቁጥጥር አስፈላጊነት ይበልጥ ከፍ ያደርጉታል።

20 ስለዚህ ከወላጆች ከመራቅና በመካከላችሁ ክፍተት እንዲኖር በመፍቀድ ፋንታ ወደ እነርሱ የበለጠ ተጠጋና ወደ ሙሉ ሰውነት እየተቃረብህ ስትሄድ ልትማር የምትችለውን ሁሉ ከነርሱ ተማር። ይህን በማድረግህ የኋላ ኋላ በጭራሽ አትጸጸትም። እነርሱም አንተን በመውለዳቸው ኩራት እንዲሰማቸው በማድረግ እውነተኛ ደስታ ልታመጣላቸው ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ዲ ኤን ኤ (DNA) ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ (deoxyribonucleic acid) ለሚባለው አጭር መጠሪያ ነው።

^ አን.6 የሚቀጥለው ምዕራፍ ከልጃገረድነት አዋቂ ሴት ወደመሆን ስለመለወጥ ይገልጻል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ነጠላ ሴል በዘጠኝ ወራት ብቻ አንድ ሕፃን ይሆናል