በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ትልቅ ሴትነት መሸጋገር

ወደ ትልቅ ሴትነት መሸጋገር

ምዕራፍ 4

ወደ ትልቅ ሴትነት መሸጋገር

1–3. አንዲትን ልጃገረድ በኮረዳነትዋ ወቅት አካላዊ እድገቷን በሚመለከት የሚያሳስባት ምን ሊሆን ይችላል? ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ምን ይሆናል?

የፀደይ ወራት ያልፍና የበጋ ወራት ይገባል። ያበቡ ዛፎች ከጊዜ በኋላ ፍሬ የሚሰጡ ዛፎች ይሆናሉ። ወጣት ልጃገረዶችም ወጣት ሴቶች መሆናቸው ያለ ነገር ነው። እምቡጥ ፈክቶ አበባው ምን እንደሚመስል እንደሚያሳይ ሁሉ ይህ የኮረዳነት የመሸጋገሪያ ወቅትም ሲያልፍ ምን ዓይነት ሴት እንደሚወጣሽ በይበልጥ ግልጽ ሆኖ ይታያል። በዚህ እድገት ውስጥ አስደሳች የሆኑ ውጤቶች እንዲገኙ የምታበረክችው ብዙ ነገር አለ።

2 በኮረዳነትሽ ዓመታት በቁመትሽ ላይ ከ12 እስከ 15 ሳንቲ ሜትር በመጨመር በቁመት ታድጊያለሽ። ክብደትሽም ይጨምራል። እንደ ደንቡ ከሆነ “የዕድገት እመርታ” የሚታይባቸው ማለትም በቁመትና በክብደት የምታደርጊው የዕድገት መጠን ጉልህ በሆነ ሁኔታ የሚፋጠንባቸው አንድ ሁለት ዓመታት ይኖራሉ። በዕድሜ እኩዮችሽ የሆኑ ሌሎች ልጃገረዶች በድንገት በቁመት እየበለጡሽ ሲሄዱ ትመለከቺ ይሆናል። ወይም አንቺ ራስሽ በፍጥነት በቁመት እየበለጥሻቸው እንደሆነ ይታወቅሽ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በጉዳዩ ላይ መጨነቅ አያስፈልግም። የእያንዳንዱ ግለሰብ የፈጣን ዕድገት ወቅት የሚመጣበት የራሱ ጊዜ አለው። ባጠቃላይ ሲታይ ልጃገረዶች “የዕድገት እመርታቸውን” የሚጀምሩት በዕድሜ እኩዮቻቸው ከሆኑ ወንዶች በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ቀደም ብለው ነው። እንዲያውም ልጃገረዶች በተመሳሳይ ዕድሜ ከሚገኙ ወንዶች ልጆች ረዘም ብለው የሚታዩበት ወቅት አለ። ይሁን እንጂ ወንዶቹ ይደርሱባቸዋል። የወንድ ልጆች ዕድገት ከልጃገረዶች ዕድገት ይልቅ ረዘም ላለ ጊዜ ይቀጥላል። ይህም በመሆኑ ረዣዥሞችና አካለ ጠንካራ በመሆን ዕድገታቸውን ስለሚጨርሱ ልጃገረዶቹን ይበልጧቸዋል።

3 አንዳንድ ጊዜ ይህ የዕድገት እመርታ በመጀመሪያ ላይ ከሌላው የአካል ክፍል ይልቅ በአንዱ ክፍል ይበልጥ ፈጣን ነው። እግሮችሽ ወይም እጆችሽ ከሌሎቹ የአካል ክፍሎች ጋር ሲነፃጸሩ ይበልጥ የረዘሙ መስለው ይታዩ ይሆናል። ይህም ያስጨንቅሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ሌላውም የአካል ክፍል ወደ ዕድገት ሂደት ይገባና ሁሉም ነገር ይስተካከላል። አብዛኛውን ጊዜ የሽንጥሽ መርዘምና የደረት መጋጠሚያሽ መጎድጎድ በመጨረሻ ጊዜ የሚመጡ ነገሮች ናቸው። የፊትሽ ቅርጽም ይለወጣል። በዚሁ ጊዜ ሌሎች የአካል ክፍሎች ክብ የሴት ቅርጽ የሚሰጡትን የስብ ክምችቶች ማዘጋጀት ይጀምራሉ።

ሌሎች አካላዊ ለውጦች

4–6. (ሀ) በኮረዳነት ወቅት የሚጀምረው “በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ” ምንድን ነው? በዚህ አካላዊ ሂደት የሚከናወነው ምን ዓላማ ነው? (ለ) በዚህ ጊዜ የሚደርሱ ሌሎች አካላዊ ለውጦችስ ምንድን ናቸው? ለምንስ?

4 ይሁን እንጂ በኮረዳነት ወቅት የሚከሰት ሌላ ዕድገትም አለ። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ወስጥ የተጠቀሰችው ራሔል “በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ” ብላ የጠራችው የወር አበባ መጀመር ነው። (ዘፍጥረት 31:34, 35) የወር አበባ መጀመር በአንድ በኩል አስደናቂ ወቅት ነው፤ ምክንያቱም ወደ ሙሉ ሴትነት መዳረሻ ጊዜ ላይ መግባትሽን የሚያሳይ ነው። በዚህ ወቅት በሰውነትሽ ውስጥ የሚመነጩ ሆርሞኖች (ንጥረ ቅመሞች) መሥራት ጀምረዋል። እነዚህ ንጥረ ቅመሞች እንቁላል የሚያዘጋጁትን የማህፀንሽን ክፍሎች የእንቁላል ሴሎችን መልቀቅ እንዲጀምሩ ይቀሰቅሷቸዋል። ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ቀኑን ጠብቆ ላይሆን ይችላል፤ በኋላ ግን እንቁላሉን በየአራቱ ሳምንት አካባቢ አንድ ጊዜ እያወጡ ይለቃሉ። የእንቁላሉ ሴል በተለቀቀ ጊዜ ወደ ማሕፀን ይወርዳል። ማሕፀንም ድንገት ዕንቁላሉ ከወንዱ ዘር ተገናኝቶ ጽንስ የተፈጠረ እንደሆነ ሲባል እርሱን የሚቀበልና ለጽንሱ በምግብነት የሚያገለግል አንድ ልዩ ገበር እንዲያዘጋጅ ይቀሰቀሳል። ጽንስ ሳይፈጠር ሲቀር ይህ ገበር ከጊዜ በኋላ ይረግፍና ይወገዳል። ወቅቱን እየጠበቀ የሚመጣው ደም፣ ፈሳሽና አንዳንድ የተቆራረጡ ሥጋዎች የሚወጡበትን የወር አበባ የሚያስከትለው ይህ በማሕፀን የውስጥ ግድግዳ ላይ የሚዘጋጀው ገበር መወገድ ነው። ከዚህ ጋር አብሮ ሕመምና መቅበጥበጥ ቢያጋጥምም የተለመደ ነገር ስለሆነ ከመጠን ያለፈ ጭንቀት ሊያስከትል አይገባውም።

5 እነዚህ ወርሐዊ ዑደቶች የሚጀምሩት መቼ ነው? የሚጀምሩበት ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። በብዙ አገሮች አማካዩ ዕድሜ አስራ ሦስት ዓመት አካባቢ ሲሆን አንዲት ልጃገረድ በአሥር ዓመቷ እንዲያውም ከዚያም ቀደም ብላ የወር አበባ ማየት ስትጀምር ሌላዋ ደግሞ እስከ አስራ ስድስት ዓመት ወይም ከዚያም በኋላ ላትጀምር ትችላለች። በተመሳሳይም የወር አበባው የሚወርድበት ጊዜ ከሦስት እስከ አምስት ቀኖች ርዝመት ሊኖረው ይችላል።

6 ከልጅነት ወደ ሙሉ ሴትነት ከሚደረገው ከዚህ ለውጥ ጋር ዳሌዎችሽ ይሰፋሉ፣ ጡቶችሽም ማደግ ይጀምራሉ። አንዳንዶቹ የሚታዩና ሌሎቹ ደግሞ የማይታዩ እነዚህ ብዙ ዕድገቶች የሰው ፈጣሪ ለሴት ለመደበላት ዕጥፍ የሕይወት ሚና ማለትም ሚስትና እናት ለመሆን የሚያዘጋጅዋት ናቸው። ልጃገረዶች የሚኖራቸው ሰፋ ያለ ዳሌ ወሊድን ብቻ ሳይሆን ትንንሽ ልጆችንም ለማዘልና ለማቀፍ ቀላል ያደርግላቸዋል። በሴቷ ሰውነት ውስጥ የተጠራቀመው የስብ ክምችት የተረገዘውን ወይም አዲስ የተወለደውን ሕፃን ለመመገብ መጠባበቂያ የሚሆን ቀለብ ነው። ልጅ በሚወለድበት ጊዜም ጡቶች ወተት ማመንጨት ይጀምራሉ።

እየጨመረ የሚሄድ ወንዶችን የሚማርክ ውበት

7–10. (ሀ) የአንዲት ልጃገረድ የአካል እድገት አድራጎቷን በተመለከተ ተጨማሪ ኃላፊነት የሚያመጣባት እንዴት ነው? (ለ) ይህስ ኃላፊነት በመኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን መጽሐፍ ውስጥ አንዲትን ልጃገረድ ‘ከግንብ’ እና ‘ከበር’ ጋር በማመሳሰል የተገለጸው እንዴት ነው?

7 የሰው ዘር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ለሴቶች የሰጣቸው መብቶች የፈጣሪን ዓላማዎች ማክበርንና ከእነርሱም ጋር የሚስማማ ተግባር የመፈጸምን ኃላፊነት ይጨምራሉ። አምላክ በተቃራኒ ፆታዎች መካከል እንዲኖር ያደረገው መሳሳብ በአብዛኛው ከመዋለድ ጋር የተያያዘ ነው። አንዲት ልጃገረድ ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ በሰውነቷ ላይ የሚታየው ለውጥ ለአቅመ አዳም የደረሱ ወንዶችን በኃይል የሚማርክ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ማራኪነት አለቦታው ሊውል ወይም አለአግባብ ሊሠራበት ይችላል። ታዲያ ትክክለኛውን መንገድ እንድትይዥ የሚያስችልሽ ማለትም ለወደፊቱ ዘላቂ ደስታሽ ዋስትና የሚሰጥና የአምላክን በረከቶች የሚያስገኝልሽ ልብ ልትይው የሚያስፈልግ ምን ነገር አለ?

8 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው መጽሐፍ በመኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን ውስጥ የሱነማይቷ ድንግል ታላቅ ወንድሞች የገለጹት ትኩረታችንን የሚስብ አነጋገር እናገኛለን። በመጀመሪያ አንዱ:- “እኛ ጡት የሌላት ታናሽ እህት አለችን ስለ እርሷ በሚናገሩበት ቀን ለእህታችን ምን እናድርግላት?” ብሎ እንደተናገረ ተጠቅሷል። በሌላ አነጋገር ልሙጥ ደረት መሆንዋ ቀርቶ ጡት አጎጥጉጣና አድጋ አንድ ሰው ለጋብቻ በሚጠይቃት ጊዜ ለእህታቸው ምን ያደርጉላት ይሆን? ሌላው ወንድሟ “እርስዋ ቅጥር ብትሆን የብር ግንብ በላይዋ እንሠራለን፤ ደጅም (በር) ብትሆን በዝግባ ሳንቃ እንከባታለን” በማለት መልስ ሰጠ። (መኃልይ 8:8, 9) ይህ ምን ማለት ነው?

9 በግልጽ እንደሚታየው የምሳሌያዊው አነጋገራቸው ትርጉም እህታቸው እንደ “ግንብ” የጸናች መሆኗን ካስመሰከረች ተገቢውን ወሮታና ክብር ይሰጧታል ማለት ነው። እንደ ግንብ የጸናች መሆኗን እንዴት ማስመስከር ትችላለች? ንጽሕናዋን ጠብቃ ለመቆየት ጽኑ ቆራጥነት በማሳየትና በማንኛውም ዓይነት የብልግና ድርጊት እንድትጠላለፍ የሚቀርቡትን ፈተናዎች በመቃወም ጠንካራ መሆኗን በማሳየት ነው። ለጋብቻ በምትደርስበት ጊዜ ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመያዝ በኩል ጽኑና ጥብቅ መሆኗን ታሳያለች። በሌላ በኩል ግን በትንሹ ገፋ ለሚያደርግ ባለጌ ሰውም ጭምር እንደሚከፈት “በር” ከሆነች ወንድሞቿ በተቃራኒ ፆታ ረገድ እንደማትታመን በመቁጠር እርስዋን ለመቆጣጠር በመቀርቀሪያ ‘ለመዝጋት’ እርምጃ እንዲወስዱ ይገደዳሉ። እንዲሁም በመጀመሪያ ከአንድ ወንድ ጋር በመክነፍ በኋላም እርሱን ትታ ሌላውን በመያዝ በፍቅሯ ልክ እንደሚከፈትና እንደሚዘጋ በር ልትሆን ትችላለች።

10 ኋላ ጡት ያወጣችውና የበሰለች ሴት የሆነችው ሱነማዊት ድንግል ይህን ፈተና በተሳካ ሁኔታ አልፋ ለወንድሞቿ “እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው፤ በዚያን ጊዜ በፊቱ [ማለትም ወደፊት ባሏ በሚሆነው ሰው ፊት] ሰላምን እንደምታገኝ ሆንኩ” ለማለት ችላለች። — መኃልይ 8:10

11–14. (ሀ) አጭር ቀሚስ ወይም አጣብቂኝ የሆነ ሹራብ መልበስ አንዲትን ወጣት ሴት ወደማይፈለጉ ችግሮች ሊያደርሳት የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ወጣት ሴት እንደመሆንሽ መጠን ወጣት ወንዶችን ለመማረክ የምትፈልጊው በተለይ በምን መሠረት ነው?

11 አንቺም ወደ ትልቅ ሴትነት ስትቃረቢ ተመሳሳይ የሆነ ፈተና ያጋጥምሻል። እውነተኛ የአእምሮ፣ የልብና የኅሊና ሰላም ለማግኘትና ሰላምን የሚያደፈርሱ ችግሮች እንዳይደርሱብሽ የምትፈልጊ ከሆነ ራስሽን መቆጣጠርና ትክክል ለሆነው ነገር ጠንካራ አቋም ማሳየት ያስፈልግሻል። ከወሊድ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን የሰውነትሽን ክፍሎች ለማሳየት ቁምጣ፣ አጣብቂኝ የሆኑ ጉርድ ቀሚሶችን፣ አጭር ቀሚስና ጠባብ ሹራቦችን በመልበስ ሆን ብለሽ ትኩረት መሳብ ይገባሻልን? ይህ አድራጎት የተቃራኒ ፆታዎችን ፍትወተ ሥጋ የመቀስቀስ ውጤት ይኖረዋል። ከዚያስ በኋላ ምን ይከተላል?

12 ታዲያ እነዚህ የሰውነት ክፍሎች ጎላ ብለው እንዲታዩ በማድረግሽ የተሳቡ ወንዶች የሚያቀርቡልሽን ፈተና ሁሉ ለመቋቋም ጥብቅ አቋምና ኃይል ይኖርሻልን? አካላዊ ዕድገት ብታሳዪም ለጋብቻና እናት ለመሆን የሚያስፈልገው የአእምሮና የስሜት እድገት አለሽን? ድመት በ12 ወር ዕድሜዋ ግልገሎችን ልትወልድ ዝግጁ ትሆናለች። በተፈጥሮም ለልጆቿ ጥሩ ክብካቤ ለማድረግ ትችላለች። ይሁን እንጂ ሰዎች እንደ እንስሶች በተቀረፀላቸው የተፈጥሮ ችሎታ የሚመሩ ፍጡሮች አይደሉም። ሰዎች የሚበዛውን ዕውቀት የሚያገኙት ከውርስ ይልቅ በትምህርት ነው። መማር ደግሞ ጊዜ ይወስዳል። ሂደቱን ለማፋጠን መሞከር ጊዜው ሳይደርስ የጽጌረዳን እንቡጥ ለመክፈት እንደመሞከር ይሆናል። ይህም አበባውን ማበላሸትና ወደፊት ሊገኝ የሚችለውን ውበት መጉዳት ብቻ ይሆናል። ጋብቻ ማለት ሙሽራ መሆን ብቻ እንዳልሆነም አስታውሽ። የቤት አደራጅ፣ ምግብ አዘጋጅና ልብስ አጣቢ መሆን ማለት ነው። እናት መሆንም ልጆችን በመያዝ ረገድ ከፍተኛ ትዕግስትና ጽናት የሚጠይቅ ነው። ይህ ሁሉ ነገር በጥሩ ጊዜና በክፉ ጊዜ፣ በሕመምና በጤንነት ጊዜ ሁሉ ጭምር መደረግ የሚያስፈልገው ነው።

13 ከዚህም ሌላ አንዲት ሴት ለጋብቻ ዝግጁ እንደሆነች ቢሰማት ልትማርከው የምትፈልገው ምን ዓይነት ባልን ነው? አንድ ወጣት ወንድ የተማረከው አንዲት ልጃገረድ በፆታ ግንኙነት በኩል ልትሰጠው በምትችለው እርካታ ብቻ ከሆነ ጥሩ ባል የሚሆን ይመስልሻልን? ሰውን በዚህ ሁኔታ ለመማረክ ከመሞከር ይልቅ ማንነትሽን ተመልክቶ ማለትም በአእምሮሽና በልብሽ ውስጥ ያለውን አይቶ ዘላቂ ወዳጅነት እንዲመሠረት መፈለጉ በጣም የተሻለ አይሆንምን? ይህንንም ለማድረግ የምትችይው ሌሎችን የሚስቡ ጠባዮች በማፍራት ነው። በተጨማሪም ከሰው ጋር በምታደርጊው ንግግር፣ ስለ ሕይወት ባለሽ ጤናማና ደስተኛ አመለካከት፣ እንደዚሁም እንደ ታማኝነት፣ ልከኝነት፣ ጨዋነት፣ ደግነትና ራስ ወዳድ አለመሆን የመሳሰሉትን ጠባዮች እንደምታደንቂ በማሳየት ነው።

14 አንቺ በራስሽ ግምትና በምታከብሪያቸው፣ በምታደንቂያቸውና ከፍ አድርገሽ በምትመለከቻቸው ሰዎች ፊት ዝቅ ለሚያደርግሽ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ለሚቆይ ደስታ ብለሽ እነዚህን መልካም ባሕርያት ላለመጣል እምቢ በማለት በዚህ በኩል እውነተኛ ማንነትሽን ልታስመሰክሪ ትችያለሽ። በተለይም በሕይወት ውስጥ በእርግጥ ጠቃሚ የሆኑ ግቦች እንዳሉሽ፣ ‘በወጣትነትሽ ዘመን ፈጣሪሽን ለማሰብ እንደምትፈልጊ’ በማሳየት ምን ጊዜም እንደ ውድ ሃብት አድርገሽ የምትመለከቺውና እውነተኛ ደስታ ሊያመጣልሽ የሚችል ወዳጅነት በመመሥረት ጥሩ ወዳጆችን ለማትረፍ ትችያለሽ። — መክብብ 12:1

ስለ መልክ ሊኖርሽ የሚገባው ተገቢ አመለካከት

15, 16. (ሀ) ስለ ውጪያዊ መልክሽ ማሰብሽ ተፈጥሮአዊ ነገር ቢሆንም ወደፊት ለምታገኚው ደስታ የበለጠ ውጤት የሚኖረው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ምሳሌ 11:22 እንዲሁም ምሳሌ 31:30 ከዕለታዊ ሕይወት አንፃር እንዴት እንደሚሠሩ ግለጪ።

15 በአሥራዎቹ ዓመታት የሚገኙ ወጣት ልጃገረዶች ስለ መልካቸው መጨነቃቸው በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ጠቅላላው የወደፊቱ ዕድልሽ በመልክ ላይ የተመካ ይመስል ስለ ቁመናሽ ወይም ስለ ፊትሽ ከመጠን በላይ አትጨነቂ። በአካባቢሽ ያሉትን የምትወጃቸውንና የምታደንቂያቸውን አዋቂ ሰዎች እስቲ ተመልከቻቸው። ብዙዎቹ ምናልባትም የሚበልጡት ተራ መልክ ያላቸው አይደሉምን? ወደፊት ለምታገኚው ደስታ እውነተኛው ቁልፍ የቁመና ማራኪነት አይደለም።

16 አካላዊ ውበት ላላት ልጃገረድም ቢሆን ሁኔታው እንዲሁ ነው። ብዙ ቆንጆ ሴቶች በጣም ከንቱና አብዛኛውን ጊዜም የብልግና ኑሮ የሚኖሩ ሆነው እንደቀሩ መገንዘብ ይኖርባታል። “የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደሆነ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ምንኛ እውነት ነው! (ምሳሌ 11:22) አዎን፤ መጽሐፍ ቅዱስ ጨምሮ እንደሚናገረው:- “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት ] የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች።” — ምሳሌ 31:30

የስሜት ሚዛንን ለመጠበቅ መጣር

17–19. (ሀ) አንዲት ልጃገረድ በኮረዳነትዋ ወቅት ምን የስሜት ለውጦች ሊያጋጥሟት ይችላሉ? የስሜት ሚዛናዊነትን ለማግኘት ምን ሊረዳት ይችላል? (ገላትያ 5:22, 23) (ለ) አንድ ሰው ጥብቅና ጽኑ አቋም እንዲኖረው አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉት ምን የግል ልማዶች ናቸው?

17 በኮረዳነት ወቅት የሚከሰቱ አካላዊ ለውጦች የስሜት ለውጦችን ያመጡ ይሆናል። አንዲት ወጣት ልጃገረድ ለአንድ ደቂቃ በብርታት የተሞላች እንደሚመስላትና በሚቀጥለው ደቂቃ ደግሞ ድክምክም እንደሚላት ሁሉ ስሜቷም በጣም ተለዋዋጭ ወደመሆን ሊያዘነብል ይችላል። የብሩህነትና የደስታ ወቅቶች በትካዜና በተስፋ መቁረጥ ወቅቶች ይተኩ ይሆናል። በዚህ ምክንያት በእርግጥ ጤናማ መሆንዋን ወይም ምን ዓይነት ሰው እንደሚወጣት ያሳስባት ይሆናል። በተለይ ጥሩ ናቸው የሚባሉት ነገሮች በፍጥነት በሚለዋወጡበት በዘመናዊው የኢንዱስትሪ ሕብረተሰብ ውስጥ ወጣት ልጃገረዶች ለጭንቀትና ለግራ መጋባት ይዳረጋሉ።

18 በዚህ ያለመረጋጋት ሁኔታ በቀላሉ ለመሸነፍ፣ ብቸኛና ዝምተኛ ወይም በጣም በራስሽ የምትመኪና እኔ ያልኩት ይሁን ባይ ትሆኚ ይሆናል። አንዳንድ ልጃገረዶች አክብሮት ለጐደለው አነጋገር፣ ለግልፍተኝነት ወይም ለሻካራ ንግግር ይሸነፋሉ። ሌሎችም ያልሆኑትን እንደሆኑ በማስመሰል ውጪያዊ የሆነ የታይታ መልክ ማሳየት ይጀምራሉ። ሆኖም ይህ ነገሮችን የበለጠ ያባብሳቸዋል እንጂ ምንም አይጠቅምም። አሁን ከልጅነት እየወጣሽ ስለሆነ የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ማለትም ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግስትን፣ ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ እምነትን፣ የዋኅነትንና ራስን መግዛትን ለማፍራት ብርቱ የግል ጥረት የምታደርጊበት ጊዜ ነው።

19 በተጨማሪም ጥብቅና ጽኑ አቋም ለመያዝ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ልማዶችን በውስጥሽ አሳድጊ። ክፍልሽ እንደተዝረከረከ በመተውና በማቆሸሽ ፋንታ ሥርዓታማና ንጹሕ አድርገሽ ያዥው። በእንቅልፍና በአመጋገብ ልማዶችሽም ሰዓት አክባሪ ለመሆን ጥረት አድርጊ። በማደግ ላይ ያለው ሰውነትሽ ልታደርጊለት የምትችይው እርዳታ ሁሉ ያስፈልገዋል። በዚህ በኩል የበለጠ ጥረት ባደረግሽ ቁጥር የበለጠ የፀጥታና የመረጋጋት ስሜት ይሰማሻል። ይህም የሚያጋጥሙሽን የስሜት ጫናዎች ቀላል ለማድረግ ይረዳሻል።

20, 21. (ሀ) ስለ ሕይወት ጥያቄ ሲኖርሽ ከሌሎች ወጣቶች ይልቅ ከወላጆችሽ የምታገኚው ዕውቀት ይበልጥ አስተማማኝ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) እውነተኛ ማራኪ ሴት የሚያደርግሽ በተለይ ምንድን ነው?

20 ይህ የመሸጋገሪያ ወቅት በምንም መንገድ ከወላጆችሽ እንዲነጥልሽ አትፍቀጂለት። በዚህ የለውጥ ጊዜ ውስጥ ሚዛንሽን ለመጠበቅ እነርሱ ልትተማመኚበት የሚያስፈልግ ሙሉ እርዳታና አስተማማኝ ጥንካሬ ሊሰጡሽ ይችላሉ። ለ“እኩዮችሽ ተጽዕኖ” ማለትም በአንቺ ዕድሜ ያሉ እንደ እነርሱ እንድትሆኚ ለሚያመጡት ብዙ ተጽዕኖ የተጋለጥሽ ብትሆኚም እነርሱ ራሳቸው በመለወጥ ላይ መሆናቸውን አትርሺ። በዚህም ምክንያት ዛሬ ያስደሰታቸው ነገር ነገ በጭራሽ ላያስደስታቸው ይችላል። እነርሱ ስለ አንቺ ምን እንደሚያስቡ ከመጠን በላይ መጨነቅ ትርፉ ችግርሽን ማባባስ ብቻ ነው። የግልና ምስጢራዊ ጥያቄዎች ሲኖሩሽ ወላጆችሽ ከማንም የተሻሉ የዕውቀት ምንጭ የሚሆኑት በዚህ ምክንያት ነው። የትምህርት ቤት ጓደኞችሽ ሊሰጡሽ ከሚችሉት ይበልጥ የተሟላና ሚዛናዊ የሆነ መልስ ወላጆችሽ ሊሰጡሽ ይችላሉ።

21 የክረምት ዝናብ ውብ አበቦችን እንደሚያስገኝ ሁሉ ማዕበሉን ሁሉ ተቋቁመሽ ነገሮችን በቁጥጥርሽ ሥር ካደረግሽ ወደ መረጋጋትና በራስ ወደ መተማመን የሚያደርሰውን መንገድ ታገኚአለሽ። በጥሩ ምግብና ቋሚ በሆነ የንጽሕና አጠባበቅ የሰውነትሽን ጤንነትና ጥራት ስለመጠበቅ ማሰብ ቢኖርብሽም ልታተኩሪ የሚገባሽ በውጪያዊው መልክሽ ላይ ሳይሆን በውስጣዊው ማንነትሽ ላይ ነው። ይህ ‘በተሰወረ የልብ ሰው’ የሚፈጠረው “የዋህና ዝግተኛ መንፈስ” የሚያስገኘው ጌጥ በአምላክና በሰው ዓይን በእርግጥ ማራኪ ያደርግሻል። — 1 ጴጥሮስ 3:3, 4

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ በር ነሽ . . .

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

 . . . ወይስ እንደ ግንብ?

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለውጪያዊ መልክሽ የተጋነነ ትኩረት ትሰጫለሽን?