በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ትምህርት ቤት እየሄድህ መማር ያለብህ ለምንድን ነው?

ወደ ትምህርት ቤት እየሄድህ መማር ያለብህ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 11

ወደ ትምህርት ቤት እየሄድህ መማር ያለብህ ለምንድን ነው?

1–3. (ሀ) ስለ ትምህርት ቤት እንዴት ይሰማሃል? (ለ) በገላትያ 6:7 ላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ለትምህርት ቤት ሊሠራ የሚችለው እንዴት ነው?

ትምህርት ቤት መሄድ ያለብህ ለምንድን ነው? ምናልባት በምትኖርበት አገር እስከ ተወሰነ ዕድሜ ድረስ ትምህርት ቤት የመሄድ ግዴታ ይኖር ይሆናል። ምንም ምርጫ የለህም። ወይም ገና ትንሽ ስለሆንክ ወላጆችህ የሚያዙህን ማድረግ ስላለብህ ይሆናል።

2 ይሁን እንጂ ትምህርት ቤት የምትገባባቸው ሌሎች ምክንያቶች ለአንተ በግል ይታዩሃልን? ትምህርትህን ስትከታተል ወይም የቤት ሥራህን ስትሠራ በሙሉ ልብ ጥረት ከማድረግ የሚገኙ ጥቅሞች አሉን? ፈተና ለማለፍ ያህል ብቻ የሚያጠኑ ወጣቶችን ታውቅ ይሆናል፤ ያውም በጣም ሠሩ ከተባለ ነው። አይደለም እንዴ? ሆኖም ለመማር ባላቸው አጋጣሚ ባለመጠቀማቸው አብዛኛውን ጊዜ የተቀረውን የሕይወታቸውን ዘመን ስንኩል ያደርጉታል። ለምን?

3 ምክንያቱም አንድ ሰው በወጣትነቱ ጊዜ የሚሠራው ነገር ሙሉ ሰው በሆነ ጊዜ ሊሠራ ከሚችለው ነገር ጋር በጣም ቅርብ የሆነ ግንኙነት ስላለው ነው። “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ትምህርት ቤትን በሚመለከትም ሊሠራ ይችላል። (ገላትያ 6:7) ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ቤት ለሚሰጥ ትምህርት ጊዜንና ጥረትን ‘ከመዝራት’ የሚመጡ ጥቅሞች ምንድን ናቸው? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

ተግባራዊ ሥልጠና

4–6. (ሀ) አንድ ሰው በትምህርት ቤት ሳለ ለመማር ያለውን አጋጣሚ ደህና አድርጐ ቢጠቀምበት የሚሻለው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 21:5) (ለ) በሕይወትህ የኋላ ኋላ ይጠቅሙኛል ብለህ የምታስባቸው በትምህርት ቤት የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ምንድን ናቸው?

4 ብዙ ዓመታት ሳትቆይ ራስህን ችለህ መኖር የሚገባህ መሆኑን መገንዘብ አለብህ። የኋላ ኋላ የባልነትና የአባትነት ወይም የሚስትነትና የእናትነትን ግዴታዎች መሸከም ይኖርባችኋል። እነዚህን ኃላፊነቶች ቀላልና ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ትፈልጋላችሁን? ሙሉ ሰው በምትሆኑበት ጊዜ ሊጠቅሟችሁ የሚችሉትን ነገሮች በመማር በትምህርት ቤት የምታሳልፏቸውን ዓመታት ከተጠቀማችሁባቸው ይህንን ለማድረግ ትችላላችሁ።

5 በብዙ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ መሠረታዊ ሙያዎች ሥልጠና የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች አሉ። ለወጣት ወንዶች የአናጢነት፣ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎችን የመግጠም፣ የብየዳ፣ የሂሳብ አያያዝና ሌሎች ትምህርቶች ይሰጣሉ። ወጣት ሴቶችም የፀሐፊነት፣ የቤት ባልትና ማለትም ምግብ የማብሰል፣ ልብስ የመስፋትና ይህንን የመሳሰሉ ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶችን ሊቀስሙ ይችላሉ።

6 ትምህርት ከጨረስህ በኋላ ከእነዚህ ስልጠናዎች ብዙዎቹ በቀላሉ ላይገኙ ይችላሉ። ስልጠናውን በኋላ ብታገኛቸውም እንኳን ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ወይም አንተን ለማስተማር ደንታ ከሌላቸው ሰዎች ጋር በመሥራት ለመማር ትገደድ ይሆናል። ታዲያ ገና ተማሪ እያለህ ከእነዚህ ነገሮች አንዳንዶቹን ለመማር ያለህን አጋጣሚ ለምን አትጠቀምበትም? በትምህርት ቤት የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን የምትመርጥበት ጊዜ ሲመጣም ከወላጆችህ ጋር ስለ ጉዳዩ ተወያይበት። ይህን በማድረግም ከእነርሱ የሕይወት ተሞክሮ ልትጠቀም ትችላለህ።

በደንብ ማንበብን ተማር

7–11. (ሀ) ጥሩ የንባብ ችሎታ በተለይ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (1 ጢሞቴዎስ 4:13፤ ኢያሱ 1:8) (ለ) የንባብ ችሎታህን ለማሻሻል ምን ሊረዳህ ይችላል?

7 ከትምህርት ቤት ልትቀስማቸው የምትችል ተግባራዊ ጥቅም ያላቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ ደስታ ሊያመጣልህ የሚችል አንድ ነገር አለ። እሱም በቀረው የትምህርት ቤት ሕይወትህና በጠቅላላው የጎልማሳነት ሕይወትህ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ይኖረዋል። እርሱም የማንበብ ችሎታ ይኸውም በደንብ ማንበብን መቻል ነው። በደንብ ማንበብ መቻል የብዙ ዓይነት እውቀት፣ የሥራ ችሎታና የደስታ በር መክፈቻ ቁልፍ ነው።

8 በየቀኑ የምታነባቸው ነገሮች ያጋጥሙሃል፤ እነሱም:- ምልክቶች፣ ማስታወቂያዎች፣ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ ቅጾችና ደብዳቤዎች ናቸው። ደህና አድርገው ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ይህ ሁሉ ደስታ የማይሰጥ አሰልቺ ሥራ ሊሆንባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ በደንብ ማንበብን ከተማርክ ሕይወትህ አስደሳች በሆነ መንገድ በልጽጐ ታገኘዋለህ።

9 በተለይ ክርስቲያን ከሆንክ በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ለማወቅ እንድትችል በደንብ ማንበብን ለመማር ትፈልጋለህ። ለሌሎች ስለ አምላክ ዓላማዎች ስትናገርም ቢሆን በጥሩ ችሎታ የቀረበ ንባብ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ትገነዘባለህ። አዎን፤ ጥሩ ንባብና ጥሩ ንግግር በቅርብ የሚዛመዱ ነገሮች ናቸው።

10 እንደ ብዙዎቹ ሰዎች የማንበብ ችግር ካለብህ ተስፋ አትቁረጥ። ነገሩ የልምምድና ቃላቱ የተጻፉበትን ፊደላት ለማስተዋል ንቁ የመሆን ጉዳይ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጮክ ብለህ አንብብ። ይህም በምታነብበት ጊዜ ትክክለኛውን ትርጉም ለማግኘትና ትክክለኛውን ስሜት ለማስተላለፍ ይረዳሃል። ከተቻለም ጥሩ አድርጐ ማንበብ የሚችል ሰው ስታነብ እንዲከታተልህ ጠይቅ። ይህም ስሕተቶችህን ወይም እያዳበርካቸው ያሉ መጥፎ ልማዶችን እንድታርም ይረዳሃል።

11 እውነት ነው፤ ያላንዳች ችግር በቅልጥፍና የማንበብ ችሎታ ከልብ ጥረት ሳይደረግ አይገኝም። ይሁን እንጂ አሁን ለምታደርገው ጥረት እጥፍ ድርብ ዋጋ ታገኝበታለህ። ሕይወትህን ከሁሉ ነገር የላቀ ጥቅም እንድታገኝበት ይረዳሃል።

ከመማር የሚገኙ ሌሎች ጥቅሞች

12–14. (ሀ) በትምህርት ቤት አሁን እየተማርካቸው ያሉት የትምህርት ዓይነቶች ምን ተግባራዊ ጠቀሜታ አላቸው? (ለ) በመማር ረገድ ራስህን ስነ ሥርዓት ማስያዝን ማስለመድህ ለወደፊቱ ሕይወትህ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው?

12 በትምህርት ቤት የሚሰጡ አንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች ብዙ ተግባራዊ ጥቅም ያላቸው አይመስሉ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አመለካከትህን ለማስፋትና በሌሎች መንገዶችም ሊጠቅሙህ ይችላሉ። ታሪክን፣ ጂኦግራፊንና ቋንቋን መማር ስለ ሌሎች ሰዎችና ቦታዎች እንድትማር ያስችልሃል። ብዙዎች ከባድ ነው ብለው የሚገምቱት የሂሳብ ትምህርት ለብዙ ሙያዎችና ሥራዎች በጣም ይጠቅማል። ለቤት ባልትና ሠራተኛም እንኳን የምግብ አሠራር መምሪያን ለማስላትና በጀትን ለመቆጣጠር ይጠቅማታል።

13 የማትወዳቸውን የትምህርት ዓይነቶችም እንኳን በትምህርት ቤት ውስጥ መማር ሌላም ጥቅም አለው። መማር አእምሮህን ስለሚያሠራው በአእምሮህ ለመጠቀም ያለህን ችሎታ ያሻሽለዋል። አእምሮ ልክ እንደ ሰውነትህ ጡንቻዎች ነው። የበለጠ ስታሠራበት በተሻለ ሁኔታ ያገለግልሃል። አእምሮ ማድረግ የሚኖርበት ጥረት ቀስ በቀስ እየቀለለና የበለጠ ውጤታማ እየሆነ እንደሚሄድ ትገነዘባለህ። ነገር ግን ጡንቻ ካልተሠራበት ልፍስፍስ እንደሚሆን ሁሉ አእምሮህንም ካላሠራኸው ውጤቱ ያው ነው። አእምሮው እንደዚህ እንዲሆንበት ማን ይፈልጋል?

14 ትምህርትህን በደንብ በመከታተልህ የሚገኝ ሌላ የተለየ ጥቅም አለን? አዎ፤ ራስህን ስነ ሥርዓት ማስያዝን ትማራለህ። ይህ አሁን አንተን ላይማርክህ ይችላል። ዳሩ ግን እንደምታውቀው በሕይወትህ ሁልጊዜ አንተ ለመሥራት የምትመርጠውን ነገር ብቻ መሥራት አትችልም። ይህ በይበልጥ እውነት የሚሆነው ለራስህ ሠርተህ ራስህን መቻል ወይም የራስህን ቤተሰብ የማስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊነቶችን የምትወስድበት ጊዜ ሲመጣ ነው። አሁንኑ ልክ እንደ አንድ የሰለጠነ ስፖርተኛ ዲሲፕሊን ከተማርህ ጎልማሳ ሰው በምትሆንበት ጊዜ ሃላፊነቶችን ለመሸከም የሚያስፈልገውን ስነ ሥርዓታማነት ለማዳበር ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም ሐሳብን ሰብስቦ የመከታተል ችሎታ እንድታዳብርም ይረዳሃል። ይህም ብዙ ሰዎች ልጅ በነበሩበት ጊዜ በተማርነው ኖሮ ብለው የሚመኙት ነገር ነው።

በትምህርትህ መትጋት ጥበቃ ነው

15–18. (ሀ) በትምህርትህ ትጉ መሆንህ ጥበቃ የሚሆንልህ በምን መንገድ ነው? (ምሳሌ 13:20) (ለ) በተለይ ክርስቲያን የሆነ ወጣት በትምህርት ቤት ጥሩ ምሳሌ ለመሆን መፈለግ የሚኖርበት ለምንድን ነው? (ቲቶ 2:6, 7, 10) (ሐ) ትምህርት ቤት ገብተህ እንድትማርና ተግባራዊ ሙያዎችን እንድትቀስም ጠንካራ ማነቃቂያ ሊሰጥህ የሚገባው ክርስቲያኖች ስለ ሕይወት ያላቸው ምን ተስፋ ነው? (1 ዮሐንስ 2:15–17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13)

15 ትምህርትህን በትጋት መከታተልህን በሚመለከት ሊጠቀስ የሚገባው ሌላ ጥቅምም አለ። በትምህርት መትጋትህ ጥበቃ ይሆንልሃል። በምን መንገድ?

16 በትምህርት ቤት ጓደኞችህ መካከል የሥነ ምግባር ችግሮች እንዳሉ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ሳትመለከት አትቀርም። አሳዛኝ ውጤቶች የሚያስከትሉ ብዙ የጾታ ብልግናና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት አለ። በተጨማሪም በብዙ ወጣቶች ዘንድ የዓመፀኝነት መንፈስ ተስፋፍቶ ይገኛል።

17 የአምላክ ቃል ለሚያስተምራቸው የመልካም ጠባይ ደረጃዎች አክብሮት ከሌላቸው ሰዎች ጋር መዋሉ ብዙ ያስጠላህ ይሆናል። እንደዚህ ካሉት ሰዎች ጋር መገናኘትን ማስቀረት ባትችልም ትምህርት ቤቱ ለሚሰጥህ ሥራ ከሚያስፈልገው በላይ ከነርሱ ጋር መገናኘቱን ለማስወገድ ትችላለህ። ለትምህርትህ ጥሩ ትኩረት ከሰጠህ ከትምህርት ሰዓት በኋላ ያለውን በዛ ያለ ጊዜ ይይዝልሃል። ይህም ሥነ ሥርዓት ከጎደላቸው ሰዎች ጋር የሚኖርህን ግንኙነት ውስን ያደርገዋል። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ፍላጎትህ ትምህርትህን መከታተል ብቻ መሆኑን ሲያዩ ከጊዜ በኋላ ሊተዉህ ይችላሉ። ይህም ለአንተ ጥበቃ ይሆንልሃል።

18 ከዚህም በተጨማሪ እንደ እውነተኛ ክርስቲያን ተደርገህ የምትታወቅ ከሆነ ትምህርትህን በትጋት በመከታተል ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ልትሆን ትችላለህ። ይህም ለአንተ፣ ለወላጆችህና ለምታመልከው አምላክ ምስጋናን የሚያመጣ ይሆናል። ወጣት ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን አሁን የምታዳብራቸው ብዙዎቹ ችሎታዎችና ሙያዎች ይህ የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት እስካለ ብቻ ሳይሆን ካለፈ በኋላም የሚጠቅሙ መሆናቸውን ማወቅህ ትልቅ ማበረታቻና ማነቃቂያ ይሰጥሃል። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ጠቅላላ ክፉ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየቀረበ መሆኑን ስለሚያረጋግጥ ነው። በቅርቡም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የዘላለም ሕይወት በሚያገኙበት የአምላክ ጻድቅ አዲስ ሥርዓት ይተካል። በዚያ አዲስ ሥርዓት ውስጥ “እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረዥም ዘመን ደስ ይላቸዋል” የሚለው ተስፋ እውን ይሆናል። (ኢሳይያስ 65:22) በዚህ ምክንያት አሁን በወጣትነትህ የምትማራቸው ጥሩ የጥናትና የሥራ ልማዶች ለዘላለም የእርካታና የደስታ ምንጭ ይሆኑልሃል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 81 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተግባራዊ ሥልጠና ለኋላ ሕይወትህ ያዘጋጅሃል