የአልኰል መጠጦችን መውሰድ ይገባሃልን?
ምዕራፍ 14
የአልኰል መጠጦችን መውሰድ ይገባሃልን?
1–4. (ሀ) አንተ ከምታውቃቸው ወጣቶች ውስጥ የአልኰል መጠጦችን የሚወስዱ አሉን? (ለ) በአካባቢያችን ያሉት ሰዎች የአልኰል መጠጦችን ስለመውሰድ ምን ይሰማቸዋል? እንደዚህ ላሉት መጠጦች ያለው አመለካከት በየትም ቦታ አንድ ዓይነት ነውን?
በዛሬው ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ወጣቶች ይህ ጥያቄ እየተደቀነባቸው ነው። ለምን? ምክንያቱም ብዙዎች በአደንዛዥ መድኃኒቶች ወይም ዕፆች ፋንታ ወደ አልኮል ዘወር እያሉ በመሆኑ በአልኮል መጠቀም በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች መካከል እየጨመረ በመምጣቱ ነው። ከዚህ አንፃር አንዳንድ ሐቆችን እንመርምርና ለዘለቄታ ጥቅማችን ጉዳዩን በአስተዋይነት እንድንመለከተው እነዚህ ሐቆች ይረዱን እንደሆነ እንይ።
2 የአልኰል መጠጦች ሲባል ብዙ ዓይነት መጠጦችን ያካትታል። እንደ ቢራ የመሳሰሉት አንዳንድ መጠጦች የአልኰል ይዞታቸው ዝቅተኛ ነው። በገበታ ላይ እንደሚቀርበው ወይን ጠጅ ያሉት ሌሎች ደግሞ ትንሽ ጠንከር ይላሉ። ከዚያም “ፍጹም አልኮል” ተብለው የሚጠሩት ከፍተኛ የአልኰል መጠን ያላቸውም አሉ። ብራንዲ፣ ዊስኪ፣ ጂን፣ ቮድካና ሌሎች ከእነዚህ አንዳንዶቹ ናቸው።
3 የየአካባቢው አስተያየቶችና ልማዶችም እንዲሁ በሰፊው ይለያያሉ። በአንዳንድ አገሮች ለምሳሌ በፈረንሳይ፣ በኢጣልያ፣ በስፔይን፣ በግሪክና በሌሎችም ወይን ጠጅ በቤተሰብ ገበታ ላይ የሚቀርብ የተለመደ መጠጥ ነው። ይህ ልማድ ሊያድግ የቻለው ጥሩ የውኃ አቅርቦት ለማግኘት ችግር በመኖሩ ወይም ባሕል ስለሆነ ብቻ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በእነዚህ አገሮችም
እንኳን ስለ አልኰል መጠጦች አጠቃቀም የሰዎች አስተያየት ይለያያል። ይህም ብቻ አይደለም፤ የአልኰል መጠጦችን መውሰድ የሚያስከትለው ውጤት ከአገር ወደ አገርና ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። እንደነዚህ ስላሉት መጠጦች አስተዋይነት ያለበት አመለካከት ለመያዝ ይህን ሁሉ ማስታወስ ያስፈልግሃል።4 ታዲያ ይህ ሁሉ ልዩነት ከመኖሩ አንጻር ሲታይ በዚህ ጉዳይ ላይ መመሪያ ሊሆንልህ የሚችል ቋሚ የሆነ ወይም የማይለዋወጥ የአቋም ደረጃ ይኖራልን? አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን የአቋም ደረጃ አውጥቷል። እርሱ የሚለውን ስትመረምር ጥበብ የተሞላበትና ሚዛናዊ ከሆነው ምክሩ ጋር አትስማማ እንደሆነ ተመልከት።
ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
5–7. (ሀ) ባለፉት ዘመናት በአምላክ ሕዝቦች መካከል በወይን ጠጅ ስለመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? (ለ) አንድ ጥሩ ነገር ያላግባብ ወይም ያለ ጊዜው ከተሠራበት ከባድ ችግሮች ሊያስከትል እንደሚችል የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ልትሰጥ ትችላለህን?
5 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ወይን ጠጅ ከጥንት ጀምሮ እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅና ሌሎችም ብዙ ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረ ከምግብ ጋር የሚቀርብ የተለመደ መጠጥ ነበር። ኢየሱስ በአንድ የሠርግ ግብዣ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጧል። ሐዋርያው ጳውሎስም ጢሞቴዎስን “ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ” በማለት መክሮታል። — 1 ጢሞቴዎስ 5:23
6 መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጆች ደስታ ከቀረቡት የአምላክ ስጦታና በረከት ከሆኑት ነገሮች መካከል ወይን ጠጅን መጥቀሱ ተገቢ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙር “እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም፣ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል። ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፣ ዘይትም ፊትን ያበራል፣ እህልም የሰውን ጉልበት ያጠነክራል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 104:14, 15) በተጨማሪም የአምላክ ሕዝቦች አንዳንድ ጊዜ ቢራና ሌሎች ኃይለኛ መጠጦችን እንደጠጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።
7 ታዲያ ይህ ሲባል የአልኰል መጠጦችን በመውሰድ ረገድ ምንም ጥንቃቄ ማድረግ አያስፈልግህም ማለት ነውን? በጭራሽ አይደለም። ምክንያቱም የአምላክ ቃል የነገሩን ሌላ ገጽታ ጨምሮ ስለሚያሳይ ነው። በሕይወት ውስጥ በራሳቸው ስሕተት ያልሆኑ ነገር ግን ያላግባብ ወይም ቶሎ ቶሎ ከተሠራባቸው መጥፎ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። አምላክ ለሰዎች አባለ ዘር ሰጥቷቸዋል፤ ይሁን እንጂ ይህ ስጦታ ሊሠራበት የሚገባው በተከበረ ጋብቻ ውስጥ ብቻ ነው። በአባለ ዘር መጠቀምም ልጅ ወልዶ የማሳደግን ከባድ ኃላፊነት ሊያስከትል ይችላል። እሳት፣ እንፋሎት፣ ኤሌክትሪክና ሌሎች የተለያዩ ነገሮች ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በሥራቸው ውስጥ በጣም ጠቃሚ ናቸው፤ ይሁን እንጂ በግድ የለሽነት ከተጠቀምንባቸው በጣም ጐጂ ሊሆኑ ይችላሉ። የአልኰል መጠጦችን መጠጣትም ቢሆን ጥንቃቄ ካልተደረገበት አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።
አልኰል የሚያስከትለው ውጤት
8–11. (ሀ) መጠኑ አነስ ያለ አልኰል ወደ ሰውነት ሲገባ ምን ውጤት አለው? መጠኑ ከፍ ሲልስ ምን ይደርሳል? (ለ) ምሳሌ 23:29–35 የስካርን ውጤት እንዴት ይገልጸዋል? የዚህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰበት ሰው አይተህ ታውቃለህን?
8 አልኮል በሰው አካል ላይ የሚያስከትላቸውን ውጤቶች እንመልከት። አልኰል እንደ ሌሎቹ ምግቦች ከሰውነት ጋር ለመዋሐድ መፈጨት አያስፈልገውም። ወደ ደም ሥር የሚገባው በአብዛኛው በትንሹ አንጀት ውስጥ ቢሆንም ወዲያው ወደ ሆድህ እንደገባ ከደምህ ጋር መቀላቀል ይጀምራል። በፍጥነትም ወደ አንጐልህ፣ ወደ ጉበትህና ወደ ሌሎቹ የሰውነትህ ክፍሎች ይሰራጫል። አልኰል ካሎሪ ስላለው ሰውነትህ እንደ ነዳጅ አድርጎ ሊያቃጥለው ወደሚችለው ወደ ኬሚካልነት ይለውጠዋል። የሚበዛውን ይህን ሥራ የሚሠራው ጉበት ነው። ሳምባህና ኩላሊቶችህ ከአልኰሉ ጥቂቱን በትንፋሽና በሽንት በማስወጣት የጉበትን የሥራ ጫና በመጠኑ ያቃልላሉ።
9 አልኰል አንድ ጊዜ ወደ ደም ሥር ከገባ በሰው ላይ ምን ውጤት ያስከትላል? የተጠጣው አልኮል መጠኑ ጥቂት ከሆነ መጠነኛ የስሜት መረጋጋትን፣ መዝናናትን፣ ወይም ውስጣዊ
ጸጥታን ሊያስከትል ይችላል። መጠኑ ብዙ ከሆነም የአንጐልን የመቆጣጠር ኃይል ይጫነዋል። በዚህ ምክንያት ቢያንስ ቢያንስ በአንዳንድ ሰዎች ላይ እንደሚታየው ሰውዬውን በጣም ለፍላፊ፣ ከመጠን ያለፈ ንቁና እንዲያውም ጠበኛ ያደርገዋል። ይህ በሰዎች ላይ ደርሶ አላየህምን?10 በሰውነት ውስጥ የአልኰሉ ክምችት እየጨመረ ሲሄድ አንጐል እንዳይሠራ ክፉኛ ይጫነዋል። ማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓትም ይነካል። ስለዚህ ግለሰቡ የሰውነቱን እንቅስቃሴ ማቀናጀት ይሳነዋል። መራመድ፣ አጥርቶ ማየትና መናገር የሚቸገረው በዚህ ምክንያት ነው። ሐሳቡም ይዘበራረቅበታል። አልኰል ለሰውየው የስሜት ሕዋሳቶቹ ከምን ጊዜውም ይልቅ በተሻለ መንገድ እየሠሩ እንዳሉ እንዲመስለው የሚያደርግ የተለየ ጠባይ ስላለው ችግሮቹ ይባባሳሉ። ስለዚህ ከመጠን በላይ እንደጠጣ እንኳን አይገነዘበውም። አንዴ ስካር ደረጃ ላይ ከደረሰ ከዚያ ለመላቀቅ ጊዜ ይወስድበታል።
11 የአልኰል መጠጦችን ከመጠን በላይ መውሰድ የሚያስከትለውን አደጋና የስሜት መረበሽ ጥሩ አድርጎ የሚያስቀምጠውን የሚከተለውን ሥዕላዊ መግለጫ እስቲ ተመልከተው። ይህም የሚገኘው በምሳሌ 23:29– 35 ላይ ነው:- “ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው? የዓይን ቅላት ለማን ነው? የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን? የተደባለቀ የወይንን ጠጅ ይፈትኑ ዘንድ ለሚከተሉ አይደለምን? . . . ዓይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፤ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል። በባሕር ውስጥ እንደ ተኛ ትሆናለህ [ልክ በመስጠም ላይ እንዳለ ሰው ግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ ያጋጥምሃል።] በደቀልም [መርከብ ወዲያና ወዲህ ሲናወጥ ይበልጡን በሚሰማበት የአውታሩ ጫፍ] ላይ እንደ ተኛ። መቱኝ ያውም አልተሰማኝም፤ ጐሰሙኝ፣ አላወቅሁምም። [ይኸውም የሰከረ ሰው ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማወቅ ስለማይችልና ስካሩ እስከሚበርድለት ድረስ ቍስሉ ስለማይሰማው።] መቼ እነሣለሁ? . . . ትላለህ።” ይህ ደስ የሚል ሁኔታ አይደለም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሲሰክር የሚደርሰው ነገር ይኸው ነው።
ችግሩ እያደገ ሄዷል
12–17. (ሀ) በወጣቶች መካከል አልኰልን ያላግባብ መጠቀም ምን ያህል ተስፋፍቶአል? ወጣቶቹ መጠጣት የሚጀምሩት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሰው እንድትጠጣ ሊገፋፋህ የሚጥር ከሆነ ምን የውስጥ ዓላማ ሊኖረው ይችላል? (ዕንባቆም 2:15)
12 ይሁን እንጂ ወጣቶች የመስከር ወይም የአልኰል ሱሰኛ የመሆን አደጋ አለባቸውን? አዎ አለባቸው። በዋሽንግተን ዲ ሲ በአልኰል ያላግባብ ስለመጠቀምና ስለ አልኰል ሱሰኝነት ጥናት በሚያደርገው የምርምር ተቋም ውስጥ ዲሬክተር የሆኑት ዶናልድ ጂ ፌልፕስ እንዲህ አሉ:-
“ከወጣቶች መካከል ስንቶቹ አልኰል ያላግባብ ይወስዳሉ ብለን በመጠየቅ የምናገኘው አኀዝ ከአዋቂዎቹ መካከል ስንቶቹ በአልኰል ያላግባብ ይጠቀማሉ ብለን በመጠየቅ ከምናገኘው አኀዝ እምብዛም አይለይም። በአገር ደረጃ በተደረገው የታዳጊ ወጣቶች ጥናት ላይ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው በ13 ዓመት ዕድሜ ላይ ከሚገኙት ልጆች አሥር በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ይሰክራሉ። ይህም በዓመት 52 ጊዜ ማለት ነው።”
13 ፈረንሳይ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በልጆች የአልኰል ሱሰኝነት ከባድ ችግር ሲያጋጥማት ቆይቷል። አንዳንድ ሰዎች ገና በለጋ ዕድሜአቸው የጉበት ማበጥ ምልክት ታይቶባቸዋል። የራስን ሕይወት ማጥፋት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚታይባቸው አገሮች አንዷ በሆነችው በሐንጋሪ የሕክምና ማዕከሎች በቅርብ ዓመታት በስካር ምክንያት የሚታመሙ በሺህ የሚቆጠሩ ልጆችን በየዓመቱ ያክማሉ።
14 ለጋ ወጣቶች ወደዚህ ሁኔታ የሚገቡት ለምንድን ነው? በብዙዎቹ ረገድ እንደታየው ከቤተሰባቸው ውስጥ አንድ ከባድ ጠጪ በመኖሩ ነው። የሌሎች ችግር መንስዔ ደግሞ መጠጣት እንዲጀምሩ የሚገፋፉአቸው ሌሎች ወጣቶች መኖራቸው ነው። አንዳንድ ጊዜ አንድ ወጣት በዕድሜ እኵዮቹ የሆኑት ብዙ የአልኰል መጠጥ በመጠጣት ‘ወንድነቱን እንዲያስመሰክር’ ግፊት ያሳድሩበታል። ወይም አንዲት ወጣት ልጃገረድ ካልጠጣች በኅብረተሰቡ ዘንድ ኋላቀር እንደሆነች እንዲሰማት ትደረጋለች።
15 ነገር ግን የአልኰል መጠጦችን መጠጣት በእርግጥ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንኩ ያረጋግጣልን? ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንደማያረጋግጥ የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም እንስሶችም እንኳን
ሳይቀር እንዲጠጡና እንዲሰክሩ ሊደረጉ ይችላሉ። እንድትጠጣ የሚገፋፉህ ሰዎች በእርግጥ የሚፈልጉት ምንድን ነው? ለአንተ ጥሩ ወይም ጠቃሚ ነገር ማሰባቸው ነውን? ወይስ አንተንም ከራሳቸው ምድብ ሊያስገቡህ እየጣሩ ነው? ሰውነትህን መቆጣጠር አቅቶህ እንደ ትልቅ ወንድ ወይም ሴት ሳይሆን መራመድ፣ አጥርቶ መናገር ወይም ማየት እንደማይችልና የሚያጃጅሉ ነገሮችን እንደሚያደርግና እንደሚናገር ሕፃን ልጅ ሆነህ እንዲያዩህና “ለመሳቅ” ፈልገው ይሆንን?16 በዚህ ጉዳይ ላይ ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ጀርጂዮ ሎሊ የተናገሩትን አስተውል:-
“የአልኰል ሱሰኛው በአካልም ሆነ በሥነ አእምሮ ከጎልማሳነት ወደ ሕፃንነት እየሸሸ ነው። የአእምሮ ማስተዋሉና የሰውነት ስሜቶቹ ይደነዝዛሉ። እንደ ሕፃን ራሱን ሊረዳ የማይችል ስለሚሆን ለሕፃን የሚደረግ እንክብካቤ ያስፈልገዋል።”
ከዚህም ሌላ የጾታ ብልግና ለመፈጸም የሚፈልጉ ሰዎች ጓደኞቻቸው ራሳቸውን መቆጣጠር እንዲያቅታቸው ለማድረግ እንዲጠጡ ያበረታቷቸዋል።
17 እንግዲያው በእነዚህ ተጽእኖዎች መሸነፍ የሚያመለክተው አንድ ሰው ጥንካሬ እንዳለው ወይም ማደጉን ሳይሆን ደካማና የሞራል ጥንካሬ የጐደለው መሆኑን ነው። ምሳሌ 20:1 የወይን ጠጅ “ፌዘኛ”፣ “ብርቱ መጠጥም ሁከተኛ” እንደሚያደርግ “በእርሱም የሳተ ጠቢብ እንዳልሆነ” ያስጠነቀቀው በጥሩ ምክንያት ነው። የእግር መሰበር እንዴት እንደሚያም ለማወቅ እግርህን መስበር እንደማያስፈልግህ ሁሉ ስካር ቀፋፊ ነገር መሆኑን ለማወቅ ሰክረህ መሞከር አያስፈልግህም።
18, 19. አንድ ሰው የአልኰል ሱሰኛ ባይሆንም ከአልኰል መጠጥ ጋር የተያያዘ አንድ አደጋ ብቻ ምን ሊያስከትልበት ይችላል?
18 ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልገው ሰካራም ወይም የአልኰል ሱሰኛ የመሆን አደጋ ስላለ ብቻ አይደለም። በአልኰል ምክንያት የተፈጠረ አንድ አደጋ ብቻ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። የራስህን ወይም የሌላውን ንጹሕ ሰው ሕይወት ወይም አካል የሚያሳጣ ከባድ የመኪና አደጋ ሊያደርስ ይችላል። ወይም በመላው ሕይወትህ ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥልና አስቸጋሪ ውጥንቅጥ የሚያስገባ የጾታ ብልግና ወደመፈጸም ሊያደርስ ይችላል። ወይም ስትጸጸትበት የምትኖር አምባጓሮን ሊያስ
ከትል ይችላል። ታዲያ ዓይንህን ጨፍነህ አስፈላጊ ያልሆነ አደገኛ ነገር ለምን ትሠራለህ?19 በዩናይትድ ስቴትስ አውራ ጐዳናዎች ላይ በየዓመቱ ከሚሞቱት 50, 000 የሚያህሉ ሰዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከአልኰል ጋር በተያያዘ ምክንያት በሚመጡ አደጋዎች የሚሞቱ መሆናቸው እነዚህ አሳዛኝ ውጤቶች ሊደርሱ እንደሚችሉ በግልጽ ያሳያል። አንድ የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባም “ከ80 በመቶ የሚበልጠው የነፍስ ግድያና የድብደባ ወንጀል የተፈጸመው በሰከሩ ሰዎች ነው” ይላል።
ጉዳዩን በጥበብ ማመዛዘን
20, 21. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ማንኛውንም የአልኰል መጠጥ በጭራሽ ላለመውሰድ የሚመርጡት ለምንድን ነው? (ሆሴዕ 4:11) (ለ) ከችግሮች ለማምለጥ ሲባል በእነዚህ መጠጦች መጠቀም ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
20 ጉዳዩን በምታመዛዝንበት ጊዜ የአልኰል መጠጦች እንደ አየር፣ ምግብና ውኃ ለሕይወት የግድ የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዳልሆኑ አስታውስ። ያለ መጠጥ ለመኖር ትችላለህ። ብዙዎችም ይህንኑ መርጠዋል። በተጨማሪም ሕይወት ሰጪ የሆነውን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልግ ሰው እርሱን ‘በሙሉ ልቡ፣ ነፍሱ፣ ሐሳቡና ኃይሉ’ ማገልገል እንደሚገባው አስታውስ። (ሉቃስ 10:27) በአልኰል ያላግባብ መጠቀም የአእምሮን አጥርቶ የማሰብ ችሎታና ንቃት እንዲሁም የሰውነትን ጉልበት መቀነስ ብቻ ሳይሆን መጥፎ የውስጥ ዓላማዎች እንዲያድጉ በማድረግ ልብንም ይነካል።
21 እውነት ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ወይን ጠጅ ያሉትን መጠጦች በልክ ስለመውሰድ ይናገራል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንደነዚህ ያሉትን የአልኰል መጠጦች ከሕይወት እውነታዎች ወይም ከመሰልቸት ስሜት እንደ ማምለጫ አድርጐ ቢመለከታቸውስ? አለዚያም ‘ለድፍረት’ ሲባል ሰውን ማፈርን ወይም መፍራትን ለማሸነፍ የሚረዳ መድኃኒት አድርጎ ቢመለከተውስ? ብዙም ሳይቆይ ፈውስ ነው የተባለለቱ ነገር ከበሽታው ብሶ ሊያገኘው ይችላል። የሐሰት ገንዘብ ቢገኝ ምን ዋጋ አለው? የደስታና የድፍረት ስሜትም አርቲፊሻል ብቻ ከሆነ ምን ይጠቅማል?
22. በአንድ ዘገባ መሠረት በአልኰል መጠጦች መጠቀም ችግር ለማስከተል የሚኖረው አጋጣሚ አነስተኛ የሚሆነው እንዴት ያሉ ሁኔታዎች ካሉ ነው?
22 ብሔራዊ የአእምሮ ጤንነት ተቋም * ያቀረበው ዕውቀት የሚሰጥ አንድ ዘገባ በአልኰል ያላግባብ በመጠቀም የሚመጡ አደጋዎች ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ሁኔታዎች ከተገደቡ በጣም አነስተኛ እንደሚሆኑ ያሳያል:- (1) ግለሰቡ መጀመሪያ ከአልኰል ጋር የተዋወቀው በጠንካራ የቤተሰብ ወይም የሃይማኖት ቡድን ውስጥ እያለ ከሆነና የመጠጦቹም የአልኰል ይዞታ ዝቅተኛ ከሆነ (እንደ ገበታ ወይን ጠጅ ወይም ቢራ ያሉት) ከሆኑና በአብዛኛው ከምግብ ጋር ከተወሰዱ (2) በእነዚህ መጠጦች መጠቀም እንደ ጥሩ ነገር ወይም እንደ ኃጢአት የማይታይ ከሆነና መጠጣትም አንድ ሰው ለማደጉ ወይም ‘ለወንድነቱ’ መለኪያ ተደርጎ የማይታይ ከሆነ (3) ማንም እንዲጠጣ የማይገደድበትና አልጠጣም ማለት ቍራሽ ዳቦ አልበላም ከማለት ተለይቶ የማይታይ ከሆነ (4) ያለ ልክ መጠጣት በጥብቅ የሚነቀፍና “እንደ ቄንጠኛነት” ወይም እንደሚያስቅ ነገር ወይም ዝም ተብሎ እንደሚታለፍ ነገር ተደርጎ የማይታይ ከሆነና ምናልባት ከሁሉም በላይ ደግሞ (5) በእነዚህ መጠጦች መጠቀምን በሚመለከት ትክክልና ስሕተት በሆነው ነገር ላይ የተባበረና የማይለዋወጥ ስምምነት ከኖረና ወላጆችም ለልከኝነት በጥሩ ምሳሌነት የሚታዩ ከሆነ ነው።
23, 24. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኰል መጠጦች አጠቃቀም ምን መመሪያዎችን ይሰጣል? (ምሳሌ 23:20፤ 6:20፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) (ለ) በዚህ ጉዳይ ላይ የሮሜ 14:13–17, 21 ምክር ይሠራል የምትለው እንዴት ነው?
23 ከሁሉ በላይ ጥሩና ከአደጋ ነፃ የሆነው መመሪያ የአምላክ ቃል ነው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ በአልኰል መጠጦች በተገቢው መንገድ ስለመጠቀም የሚገልጹ ምሳሌዎችንና ያላግባብ ስለመጠቀም ደግሞ ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል። ወጣቶች የወላጆቻቸውን አስተሳሰብ ማክበር እንዳለባቸው ይመክራል። ስለዚህ ጠቢብ ሁን፤ የአልኰል መጠጦችን መጠጣት ይገባህ እንደሆነና እንዳልሆነ ወይም በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ልትጠጣ እንደምትችል የሚነግሩህን ስማቸው። በተጨማሪም በግብዣው ላይ የተገኙት ሁሉ ወጣቶች ከሆኑና ታዛቢና አራሚ የሚሆኑ ወላጆች ወይም ዘመዶች በቦታው በሌሉበት ከመጠጣት ብትቆጠብ አስተዋይነት ነው።
24 ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድትጠቀምበትና ዘላቂ ደስታ ለማግኘት የአምላክን ቃል እንደ መመሪያህ አድርገህ መመልከት ያስፈልግሃል። “እንግዲህ የምትበሉ፣ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ፣ ወይም ማናቸውንም ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።” — 1 ቆሮንቶስ 10:31
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.22 በዩ ኤስ የጤና፣ የትምህርትና የበጐ አድራጐት መምሪያ የታተመ
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]