የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ለማየት የምትችለው ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 2
የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ለማየት የምትችለው ለምንድን ነው?
1–4. የመተማመንና የመረጋጋት ስሜት አንድ ሰው ከጀመረው ነገር መሳካት ወይም አለመሳካት ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብዙ ሰዎች ስለወደፊቱ ጊዜ እምብዛም የማይተማመኑት ለምንድን ነው?
በመሰናክል የከፍታ ዝላይ ለመዝለል ወይም በአጥር ላይ ወይም በግንብ ላይ እንኳን ለመዝለል ሞክረህ ታውቃለህን? ከፍታው በጣም ረጅም ካልሆነና ልትዘለውም እንደምትችል በራስህ ከተማመንህ ምናልባት ዝላዩን በተሳካ ሁኔታ አከናውነኸው ይሆናል። እንደማይሆንልህ በማሰብ ፈርተህ ከነበረ ግን ዝላዩ ከሽፎ በአንተም ላይ መጥፎ ውጤት አስከትሎብህ ይሆናል።
2 በብዙ ነገሮች ረገድም ሁኔታው እንደዚሁ ነው። ለምሳሌ ውኃ ውስጥ ለመግባት የምትፈራ ከሆነ ዋና ለመማር በፍጹም አትችልም።
3 ከወጣትነትህ ከሁሉ የላቀውን ውጤት በማግኘት ረገድም እንደዚሁ ነው። የእርግጠኝነትና የመረጋጋት ስሜት እዚህ ላይ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ወደፊት ስለሚመጣው ነገር እርግጠኛ ሆነህ የመረጋጋት ስሜት ካላደረብህ በእርግጥ ደስተኛ ለመሆንና በሕይወት መንገድ ጥሩ መሻሻል ለማድረግ አትችልም። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ልንተማመንበት የሚበቃ እርግጠኛ የሆነ ምን ነገር አለ?
4 ልበ ሙሉ ላለመሆን ምክንያት ስለሚሆኑ ነገሮች ብዙ መናገር ይቻላል። ፕላኔቷ ምድራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይብስ እየተበከለች በመሄድ ላይ ነች። የዱር አራዊት ሀብቷም እየተደመሰሰ ነው። የምግብ እጥረትና ሌሎች አሳሳቢ ችግሮችም አሉ። እነዚህ ነገሮች ወደፊት ተስፋ ሊደረግበት የሚበቃ ነገር ስለመኖሩ እንድ
ትጠራጠር ያደርጉህ ይሆናል። በምድር ላይ ያሉት ነገሮች እንደዚህ እየተበላሹ በመሆናቸው አንዳንድ ወጣቶች ለእነርሱ እምብዛም የወደፊት ተስፋ እንደሌለ ይሰማቸዋል። በእርግጥም እንደዚህ መስሎ ሊታይ ይችላል። ሆኖም የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ለመጠባበቅ ምክንያት የሚሰጡ ሆነው ሳለ ሰዎች ብዙም የማያወሩላቸው ነገሮች አሉ። እስቲ ከእነዚህ ጥቂቶችን ተመልከት።ፕላኔቷ መኖሪያህ
5–8. በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ አንዳንድ ነገሮችን ጥቀስ። ይህ አስገራሚ የነገሮች ቅንብር እንዴት ተገኘ?
5 ምድርን እንደ ተራ ነገር ቆጥረን ያለ ምንም አድናቆት መመልከቱ ቀላል ነው። ሆኖም ይህች እኛ የተወለድንባትና የምንኖርባት ፕላኔት በእርግጥ አስገራሚ የሥራ ውጤት ነች። ምድር እንደምትሽከረከር ኳስ ሆና 93 ሚልዮን ማይሎች (150,000,000 ኪሎ ሜትር ያህል) ርቃ የምትገኘውን ፀሐይን ስትዞር በኅዋው ውስጥ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ትጓዛለች። ምድር አሁን ካለችበት በተለየ ቦታ ላይ ብትገኝ ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ለምሳሌ ፕሉቶና ኔፕቱን የሚባሉትን ፕላኔቶች ያህል ከፀሐይ ርቃ ብትገኝ ኖሮ ምድር ሕይወት ሊኖርባት የማይችል እጅግ ቀዝቃዛ የበረዶ ቁልል ትሆን ነበር። ምድር ቬኑስ እንደምትባለው ፕላኔት አሁን ካላት ርቀት በአንድ ሦስተኛው ወደ ፀሐይ ብትቀርብ ኖሮ እንደ ምድጃ የጋለች ትሆንና ሙቀቷ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሐይቆቿና ወንዞቿ ሳይቀር ፈልተው ይፍለቀለቁ ነበር።
6 ወይም ደግሞ መሬት ከፀሐይ ያላት ርቀት ተስማሚ ሆኖ አሁን በየሃያ አራት ሰዓቱ እንደምታደርገው በራስዋ ዛቢያ ላይ ባትሽከረከር ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ለምሳሌ በራስዋ ዛቢያ ላይ ዓመት ሊሞላ ጥቂት በሚቀረው ጊዜ ውስጥ አንድ ጊዜ እንደምትዞረው ሜርኩሪ እንደምትባለዋ ፕላኔት ቢሆን ኖሮስ? የምድሪቱ ግማሽ ክፍል ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች ወርዶ በበረዶ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው ግማሽ ክፍል ደግሞ ሕይወት የማይኖርበት ምድጃ በሆነ ነበር።
7 ይህ ብቻ አይደለም። ቢያንስ በአብዛኛው የምድር ክፍል ላይ በሚታየው የጸደይ ልምላሜና አበቦች፣ በሞቃቱ በጋ ፀሐያማ
ቀኖች፣ በመጸው ቅዝቃዜና በቀለሞች ያሸበረቀ ሁኔታ፣ በክረምት በረዶ ውበት የምንደሰተው ለምንድን ነው? እነዚህ ወቅቶች የሚፈጠሩት ምድር በፀሐይ ዙሪያ ከምትጓዝበት ምኅዋር ጋር በሚዛመድ መንገድ ትንሽ ጋደል ስለምትል ነው። ወቅቶቹ አብዛኛውን የፕላኔቷን ገጽ አስደሳች የመኖሪያ ቦታ ለማድረግ ይረዳሉ። የምድሪቱ ትልቅ ክፍልም ለሰውና ለእንስሳት የሚሆን ምግብ እንዲያፈራ ያስችላሉ።8 በዚች ፕላኔት ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ በአንድ ላይ የሚሠሩ በመቶ የሚቆጠሩ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ምን ያስተምረናል? ‘ይህ ሁሉ የነገሮች ቅንብር እንዴት ሊገኝ ቻለ?’ ብለህ እስቲ ራስህን ጠይቅ። ፕላኔቷ ምድራችን በእርግጥ ንድፍ አውጪ እንዳላት መቀበል አለብን። አዎን፤ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉት ብዙዎቹ የአሠራር ሥርዓቶች ሰብዓዊ ሳይንቲስቶች ከነደፉትና ከሠሩት ከማንኛውም የጠፈር መንኮራኩር የበለጠ የተወሳሰቡ ናቸው። የብዙ ሐሳብና ሥራ ውጤት የሆኑት የምድር ውስብስብ የአሠራር ሥርዓቶች የሚያስተምሩን ሌላም ነገር አለ። የምድር ንድፍ አውጪ በዚህች ምድር ላይ ለሚኖሩት ሰዎች ሕይወትን ማራኪና አስደሳች ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ያስተምሩናል። ይህ አንተንም ይጨምራል።
9–12. ምድር ብዙ ጉዳት የደረሰባት ቢሆንም ከጉዳቱ ለማገገም ያላትን ችሎታ የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?
9 እውነት ነው፤ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ምድርን በመበከልና ያለ አግባብ በመጠቀም በጣም እያበላሿት ነው። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ሊለወጥ የሚችል ነው። ብልሽቱም ሊስተካከል ይችላል።
10 ለምሳሌ በፓስፊክ ውቅያኖስ በምትገኘው በክራካቶዋ ደሴት የደረሰውን እስቲ ተመልከት:- ይህች ደሴት በታላቅ እሳተ ጎሞራ ፍንዳታ ብትንትኗ ወጣ። ይህ ከደረሰ በኋላ ወዲያውኑ ያን ቦታ ብትጎበኘው ኖሮ መላዋ ደሴት አመድ ብቻ መሆኗን ትመለከት ነበር። በደሴቷ ላይ በሕይወት የተረፈ አንድም ነገር ማለትም አንድም ሰው፣ እንስሳ ወይም ዕፅዋት አልነበረም። ይሁን እንጂ በኋላ ምን ሆነ?
11 ያለ ማንም እርዳታ ደሴቷ ማንሰራራት ጀመረች። በሦስት
ዓመት ውስጥ ሃያ ስድስት የሚያህሉ የዕፅዋት ዓይነቶች እንደገና መለምለም ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ የኮኮናት ዛፎች፣ የጫካ ሸንኮራ አገዳና ልዩ ልዩ አበቦች ማደግ ጀመሩ። ፍንዳታው ከደረሰ ከሃያ አምስት ዓመት በኋላ በክራካቶዋ 263 ዓይነት የእንስሳት ዘሮች ተገኙ። እሳተ ጎሞራው ያደረሰው ጉዳት ተወገደ። ገነት መሰል የነበረው የደሴቲቷ ሁኔታ ተመለሰ።12 የክራካቶዋ ደሴት እንደገና ያንሰራራችበት አስደናቂ ሁኔታ በምድር ሁሉ ላይ እንደገና ሊደገም ይችላል። በኋላ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደምናየው ይህ እንደሚሆን ለማመን ጥሩ ምክንያት አለን።
አስገራሚ የምግብ ፋብሪካ
13–17. ምግብ ከምድር የሚገኘው እንዴት ነው? (መዝሙር 104:14) ምድር የምታስገኘው ዓይነቱ የበዛ ምግብ አንድ ሰው በሕይወት እንዲደሰት ምን አስተዋጽኦ አለው? እንግዲያው የእነዚህ ሁሉ ነገሮች ንድፍ አውጪ ለእኛ ምን ዓይነት ኑሮ አስቦልን ነበር? (ኢሳይያስ 25:6፤ መዝሙር 67:6)
13 በሚቀጥለው ጊዜ ለምግብ ስትቀርብ እስቲ ላንዳፍታ ስለሚከተለው ነገር አስብ:- የምትበላው ነጭ ሩዝ ወይም ነጭ ድንች፣ ጥቁር ስንዴ ወይም ጥቁር አደንጓሬ፣ ቢጫ በቆሎ ወይም ቢጫ ፍራፍሬ፣ ጥቁር ወይም ቀይ እንጆሪ ይሁን ሁሉም የተገኙት አረንጓዴ ቅጠል ካላቸው አትክልቶች ነው። ለምን? ፎቶሲንተሲስ ተብሎ በሚጠራው አስደናቂ ሂደት ምክንያት ነው። *
14 አረንጓዴ ተክሎች በቅጠላቸው ውስጥ ክሎሮፊል የሚባል አረንጓዴ ንጥረ ነገር አላቸው። የፀሐይ ብርሃን ቅጠሎቹን ሲመታ ክሎሮፊሉ ውስብስብ የሆነ የኬሚካል ለውጦችን የመፍጠር ሥራውን ይጀምራል። በአትክልቶቹ ሴሎች ውስጥ ውኃና ካርቦንዳይኦክሳይድ (ተክሉ ከአየር ያገኘዋል) ለምግቦች ሁሉ መሠረት የሆነውን ቀላል ስኳር ለማስገኘት ይዋሃዳሉ። አረንጓዴ ተክሎች በዚህ ስኳር በመጠቀም ይበልጥ የተወሳሰቡትን እንደ ካርቦሃይድሬት፣ ቅባት፣ ፕሮቲኖችና ቫይታሚኖች ያሉትን ነገሮች ይሠራሉ። የዕፅዋት ተመራማሪ የሆኑት ፍሪዝ ደብልዩ ዌንት ፎቶሲንተሲስ ስለሚያስገኘው አስገራሚ ምርት ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ:-
“ፎቶሲንቴሲስ በብዛት በማምረት በኩል የሰውን ኢንዱስትሪዎች ከቁጥር የማይገቡ ያስመስላቸዋል። የዓለም የብረት ፋብሪካዎች በየዓመቱ 350 ሚልዮን ቶን ብረት ሲያመርቱ የዓለም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደግሞ 325 ሚልዮን ቶን ሲሚንቶ አምርተው ያወጣሉ። የዓለም አረንጓዴ ተክሎች ግን በየዓመቱ 150 ቢልዮን ቶን ስኳር ያመርታሉ።”
15 ሳይንቲስቶች በፎቶሲንቴሲስ ረገድ ምን እየተካሄደ እንዳለ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ፎቶሲንቴሲስ እንዴት እንደሚሠራ አሁንም አልገባቸውም። ተመራማሪዎች ሂደቱን “ጥቁሩ ሳጥን” ብለው እንደሚጠሩት አንድ የሳይንስ ጽሑፍ አዘጋጅ ተናግረዋል። ለምን? ምክንያቱም “ሳይንቲስቶቹ ወደ ውስጥ የሚገባውንና ወደ ውጭ የሚወጣውን ይወቁ እንጂ በውስጡ ስለሚካሄደው ነገር እርግጠኞች አይደሉም።” ሰዎች ባሏቸው የኬሚካል ላቦራቶሪዎች (ቤተ ሙከራዎች) በሙሉ ይህንን አስገራሚ ሂደት በፍጹም ደግመው ሊሠሩት አይችሉም።
16 የዚህኑ ያህል አስገራሚ የሆኑት ምድር የምታስገኛቸው ልዩ ልዩ የምግብ ዓይነቶች ናቸው። ምናልባት አንተ በተለይ አንዳንድ ዓይነት ምግቦችን ትወድ ይሆናል። ለምሳሌ እንጆሪ ትወዳለህ እንበል። ይሁን እንጂ የሁሉም ነገር ማለትም የድንች፣ የሩዝ፣ የዳቦ፣ የፖም፣ እንዲሁም የብርቱካን ጣዕም እንደ እንጆሪ ቢሆን ኖሮስ? ብዙም ሳይቆይ ጣዕሙ ይሰለችህ ነበር፤ አይደለም እንዴ? በዚህ ፋንታ የምድር የምግብ ፋብሪካ ከሚያመርታቸው ከተለያዩ ፍሬዎች፣ አትክልቶች፣ ለውዝና የእንጆሪ ዘሮች የመቅመሻ ሕዋሳቶችህን የሚያስደስቱ በሺህ የሚቆጠሩ የተለያዩ ጣዕሞችን ታገኛለህ።
17 አሁንም ይህ ሁሉ ምን የሚነግረን ነገር አለ? ይህንን አስገራሚ የምግብ ፋብሪካ ያስገኘው ፈጣሪ በምድር ላይ ኑሮ በጣም አስደሳች እንዲሆን እንደሚፈልግ በጣም ግልጽ ያደርግልናል። ወደፊት አስደሳች ኑሮ እንድናገኝ ያስባል። ፕላኔቷን ምድር ምቹ መኖሪያ አድርጎ የሠራት ይኸው ንድፍ አውጪ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩት ሁሉ ግሩም የሆነ ግብዣ በማዘጋጀት ይህችን መኖሪያ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ሁሉ እንድትሞላ አድርጓታል። በኋላ በምናየው በዚህ መጽሐፍ ክፍል ውስጥ ከዚህ ግብዣ ለመካፈል ለሚፈልጉት ሁሉ ይህ ግብዣ እንዲደርሳቸው አምላክ እንዴት እንዳሰበም እናያለን።
እስቲ ራስህን ተመልከት!
18–23. ከእንሰሶች እጅግ የላቅን እንድንሆን ታስበን እንደተሠራን የሚያሳይ በሰውነታችን ላይ የሚታይ ምን ነገር አለ?
18 እስቲ በመጨረሻው ትንሽ ስለ ራስህ አስብ። እርግጥ ነው፤ ለማሰብ በአንጎልህ መጠቀም አለብህ። ታዲያ ለምን ከአንጎል አትጀምርም? እንደሚታወቀው አንጎልህን ለማየት አትችልም። ቢሆንም ምን ይመስላል ብለህ ታስባለህ? የሰው አንጎል በተሟላ ዕድገት ላይ ሲደርስ ሐምራዊ ግራጫ ቀለም ያለው ትልቅ የለውዝ ፍሬ የሚመስል መልክ ያለው ሲሆን 1.3 ኪሎ ይመዝናል። ይሁን እንጂ በዚህ ትንሽ ቦታ ውስጥ እንዴት ያለ ከፍተኛ ችሎታ ታምቋል! በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ሳይንሳዊ ሪፖርት እንዲህ ይላል:-
“የአንጎል አሠራር . . . በጣም የተወሳሰበ ከመሆኑ የተነሳ ታላላቅ የኤሌክትሮኒክ ኮምፒተሮች ከእርሱ ጋር ሲነፃፀሩ እንደ ሕፃን መጫወቻ አሻንጉሊቶች ይቆጠራሉ።”
19 አዎን፤ አንተ ያለህና ልትጠቀምበት የምትችለው አንጎል “በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሚገኘው ቁስ አካል ሁሉ እጅግ በጣም የተወሳሰበ ነገር” ተብሎ ተገልጾአል። አንድ ሰው ጥሩ ሰዓት ወይም ዋጋው ውድ የሆነ ካሜራ ወይም ጠቃሚ የኤሌክትሮኒክ የስሌት መኪና ቢሰጥህ እንደምትጠነቀቅለትና በትክክል ልትጠቀምበት እንደምትሞክር አያጠራጥርም። አይደለም እንዴ? ለአንጎልህ ከዚህ በጣም የላቀ አድናቆት ሊሰማህ ይገባል።
20 ስለ ሰውነትህም ደግሞ እስቲ አስብ። እርግጥ ነው፤ አንበሳ ከአንተ የበለጠ ኃይል እንዳለው፣ ዝሆን ከአንተ የበለጠ ግዙፍ እንደሆነ፣ ዶልፊን የተባለ ዓሣም ከአንተ በበለጠ ፍጥነት መዋኘት እንደሚችል፣ ዝንጀሮ ከአንተ በተሻለ ሁኔታ ዛፍ ላይ እንደሚወጣ፣ ንስር በገዛ ክንፎቹ ወደ አየር እደሚመጥቅ አንተ ግን እንደዚያ ማድረግ እንደማትችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ፍጥረቶች መካከል ሰው ያለውን ችሎታ ሁሉ አጠቃልሎ የያዘ አንድም የለም። አንበሳና ዝሆን በሰማይ መብረር አይችሉም፤ ዓሦች ዛፍና ተራራ መውጣት አይችሉም፤ ንሥርም መዋኘት አይችልም። ሰዎች ግን በመሣሪያ ሳይታገዙም ሆነ ወይም በፈለሰፉአቸው መሣሪያዎች በመታገዝ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ይችላሉ። ከዚህም ሁሉ በላይ ሰዎች ማለቂያ የሌላቸውን የተለያዩ ነገሮች ለመሥራት ባላቸው ችሎታ ልዩ ፍጥረት ናቸው።
21
ለዚህም የሚያበቃ አንዱ ምክንያት እጅህ ነው። በእጆችህ መሥራት የምትችላቸውን ነገሮች ሁሉ ማለትም ከባድ ከሆነው የመካኒክነት ወይም የአናጢነት ሥራ ጀምሮ የሙዚቃ መሣሪያ እንደመጫወት፣ የሥዕል ሥራ ወይም የቤት ንድፍ እንደማውጣት የመሳሰሉ ጥንቃቄን የሚጠይቁ ሥራዎች ሊያከናውን የሚችል ሰው የፈለሰፈው አንድም መሣሪያ የለም።22 በእርግጥም ሰውነትህን በጣም አስደናቂ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል እጆችህ ይገኙበታል። ከቀዶ ጥገና ሐኪሞች ጋር የሚሠሩት መሐንዲሱ ዶክተር ደብልዩ ደብልዩ ኤከርስ ስለ ሰው አካል እንዲህ ብለው መናገራቸው አያስደንቅም:-
“በቴክኖሎጂ ፍጽምና ውስጥ የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ የሰው አካል ነው። ልታልሙት የምትችሉት ማንኛውም ማሽን ምንም ያህል የተራቀቀ ቢሆን የሰው አካል ይበልጠዋል።”
23 ታላቁ ንድፍ አውጪ ሰው ከእንሰሶች በጣም እንዲበልጥና ምድርን እስከሚቻለው ከፍተኛ ደረጃ ድረስ ሊደሰትባት እንዲችል እንደፈለገ ግልጽ ነው። ይህም የወደፊቱ ጊዜ የሥራችን ዋጋ የምናገኝበት አስደሳች ጊዜ እንዲሆንልን እንደሚያስብ ለመተማመን ምክንያት ይሰጠናል።
በልበ ሙሉነት ወደፊት መጓዝ ትችላለህ
24–28. ምድር ንድፍ አውጪና ሠሪ እንዳላት ማመኑ ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ሮሜ 1:20) እርሱስ ስለ ሕይወት ላሉን ጥያቄዎች መልስ የሰጠው የት ላይ ነው? (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ማድረግ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንመለከት ይረዳን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1–4)
24 ይህች ፕላኔትና በውስጧ ያለው ማንኛውም ነገር በማንኛውም ቤት ወይም ሕንፃ ከሚታየው እጅግ በጣም የሚበልጥ የአእምሮ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ እንዳላት ማስረጃ እንደሚሰጥ አይተናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቷልና” ከሚለው ቀላል አገላለጽ ጋር ለመስማማት እንደምትችል አያጠራጥርም። (ዕብራውያን 3:4) ወደ አንድ ሰፊ ምድረ በዳ ሄደህ አንድ ቤት አገኘህ እንበል። በአካባቢው አንድም ሰው ባታይ ቤቱ ራሱ በራሱ ተሠራ ብለህ ታስብ ነበርን? ቤቱ ራሱን በራሱ ሠራ ብለህ አታስብም። እንደዚሁም እኛ ባናየውም ምድር ንድፍ አውጪና ሠሪ እንዳላት ግልጽ ነው። የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ማክስ ፕላንክ እንዲህ አሉ:-
“ከሁሉ በላይ የሆነ የመፍጠር ችሎታ ያለው አእምሮ እንዳለ ከመቀበል ውጭ አጽናፈ ዓለሙ እንዴት ተገኘ ለሚለው ጥያቄ ምንም መልስ አናገኝም።”
25 መጽሐፍ ቅዱስ መኖሪያችን የሆነችውን ምድርን የሠራት “ከሁሉ በላይ የሆነ የመፍጠር ችሎታ ያለው” ማን እንደሆነ ይነግረናል። እርሱም የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ይነግረናል።
26 ይህ ታላቅ ንድፍ አውጪ በጣም ኃያልና ጥበበኛ እንደሆነ ግልጽ ነው። አንተንም ጨምሮ ለሁላችንም ጥቅም ከልብ እንደሚያስብም ግልጽ ነው። ሌሎች ሰዎች የደረሱበትን ዕውቀት በትምህርት ለማወቅ ከቻልህ ከወጣትነትህ ከሁሉ የላቀውን ለማግኘትም ከእርሱ የበለጠ ነገር ለመማር ትችላለህ።
27 መጽሐፍ ቅዱስ የሚገባው እዚህ ላይ ነው። ፈጣሪ ለምድርና ለሁሉም የሰው ዘር ስላለው ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰዎች ላሏቸው ብዙ ጥያቄዎችም መልስ ይሰጣል። ችግሮቻቸው ከየት እንደመጡና እንዴት መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን በብዙ ችግርና አደጋ በሞሉት በአሁኖቹ ጎዶሎ ሥርዓቶች ላይ ተስፋህን እንድትጥል አይመራህም። እርሱ የሚያመለክተው ከዚህ በጣም የተሻለ ነገር ሊሰጡ ወደሚችሉ አዲስ ሥርዓቶች ነው።
28 መጽሐፍ ቅዱስን በመጠኑ አንብበኸው ቢሆንም ባይሆንም እርሱ የሚናገረው ነገር በእርግጥ ችግሮችህን ሊፈታና ጥያቄዎችህን ሊመልስ የሚችል ስለመሆኑ ጥያቄ አድሮብህ ይሆናል። ውስጡን በደንብ አድርገህ ካልፈተሽከው እርግጡን ልታውቅ አትችልም። አሁን በምታነበው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚልና ምን መልሶችና መመሪያዎችን እንደሚሰጥ እናያለን። መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ምክንያታዊ እንደሆነና ያለውን እውነታ እንደሚቀበል ራስህ ተመልከት። አዎ፤ የይሖዋ አምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በፊትህ ያሉትን ፈተናዎች ለመቋቋም እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል ተመልከት። ከዚያም አስደሳች ወደሆነና ልትጥርለት ወደሚገባህ የወደፊት ጊዜ ተረጋግተህ በመተማመን መንፈስ ተራመድ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 ፎቶ ማለት “ብርሃን” ማለት ሲሆን ሲንተሲስ ማለት ደግሞ “ነጠላ ንጥረ ነገሮችን በማቀላቀል ውሕደት መፍጠር” ማለት ነው።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ ምድር ፈጣሪ ማወቃችን የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት ለመመልከት መሠረት ይሆነናል