የጀመርከውን ትጨርሳለህን?
ምዕራፍ 12
የጀመርከውን ትጨርሳለህን?
1, 2. አንድን ነገር ከማከናወን የሚገኘውን እርካታ ለማግኘት ምን ይፈለግብሃል?
ሰው የሚያገኘው ብዙው ደስታ አንድን የተጀመረ ሥራ ከማከናወን የሚመጣ ነው። ለምሳሌ ጊታር መጫወት ለመማር ብትወስን ችሎታው እስኪኖርህ ድረስ ብትቀጥልበት ከእርሱ ደስታን ታገኛለህ። ነገር ግን ከጀመርክ በኋላ ወዲያውኑ ብትተወው ችሎታ ቢኖርህ ኖሮ ልታገኝ የምትችለውን ደስታና እርካታ በጭራሽ አታገኝም። የተወሰነ ጊዜን የሚፈጅ ልምምድንና ሥልጠናን የሚጠይቅ የማንኛውም ውጥን ሁኔታም ያው ነው።
2 ይሁን እንጂ አንድ የተጀመረ ሥራ እስኪያልቅ ድረስ መጽናትን በሚመለከት ሁላችንም በዕድሜ እየገፋን በሄድን ቁጥር ልንተዋቸው ወይም ልናሸንፋቸው የሚገቡ አንዳንድ ዝንባሌዎች አሉ።
የጀመሩትን የመጨረስ ችግሮች
3–8. (ሀ) አንድ ሰው ትዕግስት የለሽነትን እንዲያሸንፍ ምን ሊረዳው ይችላል? (ለ) አንድን ሥራ ከመጀመርህ በፊት ምን ማድረጉ ጥበብ ነው? ውሳኔ ለማድረግ የማን ምክር ሊጠቅምህ ይችላል? (ሐ) የጀመርከውን ነገር አለመጨረስ የተሻለ የሚሆነው በምን ጊዜ ነው?
3 እንደምታውቀው ትንንሽ ልጆች ሐሳባቸውን ሰብስበው በአንድ ነገር ላይ ማሳረፍ የሚችሉት በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ነው። ጨዋታም እንኳን ቢጀምሩ ብዙ ሳይቆዩ ሃሳባቸው ወደ ሌላ ይወሰዳል ወይም ይሰለቻቸዋል። ነገር ግን አንድ ሰው እያደገ ሲሄድ ሐሳቡን ሰብስቦ በአንድ ነገር ላይ የማሳረፍ ትዕግሥቱ እየዳበረ ይሄዳል። ይህን በራስህ ላይ ተመልክተኸው ይሆናል። ይህ ጠባይ በአብዛኛው ኰትኵተህ የምታፈራው ነው።
ሆኖም ይህን ጥረት ማድረግ አይቆጭም፤ ምክንያቱም ከሕይወት ብዙ ነገሮችን እንድታገኝ ይረዳሃል።4 ሐሳብን ሰብስቦ በአንድ ነገር ላይ ለማሳረፍ አንድን የተለመደ ሌላ ጠባይ ማሸነፍ ያስፈልጋል። እርሱም ትዕግስት ማጣት ነው። ትንሽ ልጅ የነበርክበትን ጊዜ መለስ ብለህ አስብ። እንደምታስታውሰው ትንንሽ ልጆች ሁልጊዜ ነገሮችን አሁንኑ ማግኘት ይፈልጋሉ። ብዙውን ጊዜ አንድን ነገር መሥራት ይጀምሩና ጥቂት ጊዜ ሞክረው ሲያቅታቸው ይተዉታል። ይህ ጠባይ ገና ያልለቀቃቸው በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ብዙ ወጣቶችን ታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ በሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው አንዳንድ ነገሮች ጊዜና ጥረትን የሚጠይቁ መሆናቸውን መገንዘቡ በቀላሉ ተስፋ እንዳትቆርጥ ይረዳሃል።
5 ትዕግስት የሌለው ሰው አብዛኛውን ጊዜ ነገሮችን በስሜት ተገፋፍቶ በችኮላ ይጀምራል። ጥበብ አዘል የሆነ አንድ ምሳሌ “የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል፣ ችኩል ሰው ግን ለመጉደል ይቸኩላል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) ስለዚህ አንድ ዕቅድ ከመጀመርህ በፊት ወይም አንድ የሥራ ምድብ ከመቀበልህ በፊት በእርግጥ ጊዜህን ልታጠፋለት የሚገባው መሆኑን አረጋግጥ።
6 የጀመርከውን አለመጨረስ አስተዋይነት የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዴት? ምክንያቱም ውጥንህ መጀመሪያውኑ መጥፎ የነበረ ሊሆን ይችላል። ግቡ የተሳሳተ ማለትም ከትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይስማማ ሊሆን ይችላል። ወይም ለአንተ የማይጠቅም ይሆናል። ታዲያ ይህንን ነገር ከዳር ለማድረስ ለእርሱ የሚውለው ጊዜና ጥረት የሚገባው ነውን? እርሱንስ ዳር ለማድረስ እንደምትችል ለማመን በቂ ምክንያት አለህን?
7 ኢየሱስ የጀመረውን ግንብ ለመጨረስ ይችል እንደሆነ ወጪውን ሳያሰላ ግንብ መሥራት ስለጀመረ ስለ አንድ ሰው ተናግሮአል። ኢየሱስ እንደተናገረው ሰውየው መሠረቱን ከጣለ በኋላ ሥራውን መቀጠል ካልቻለ ሰዎች “ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው” ብለው ሊስቁበት ይችላሉ። (ሉቃስ 14:28–30) ስለዚህ የጀመርከውን ለመጨረስ ከፈለግህ አስቀድመህ ወጪውን አስላ።
8 ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝን። የሌሎችን በተለይም የወላጆችህን አስተያየት ጠይቅ። ከተሞክሮአቸውም ተጠቀም። እነርሱ የተሳሳቱባቸው ነገሮች ነበር። ስለዚህ አንተን ከእነዚህ ስሕተቶች ሊመልሱህ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስም የጥበብና የተግባራዊ ምክር ከፍተኛ ምንጭ ነው። መጽሐፉ ከአምላክ የተገኘ ስለሆነም በብዙ ሺህ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሰዎች ያገኟቸውን ትምህርቶች ያቀርባል። ለምሳሌ ንጉሥ ሰሎሞን ደስታን በሰብዓዊ ነገሮች ብቻ ለማግኘት ሰው ሊያደርገው የሚችለውን ነገር ሁሉ አደረገ። ውጤቱም “ነፋስን እንደመከተል ነበር” በማለት ይነግረናል። ታዲያ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ፍሬ ቢስ መንገድ ለምን ትከተላለህ? —ጀምሮ የሚያቆም አትሁን
9–12. (ሀ) ግብህን ከመረጥህ በኋላ ከግብህ ለመድረስ እቅድ ማውጣት የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? (ለ) ችግሮች ሲያጋጥሙህ እንዴት መታየት ይገባቸዋል? (ሐ) ጀምሮ የማቋረጥን ልማድ ማስወገድ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ሉቃስ 9:62)
9 ግብህ ጊዜህን ልታጠፋለት የሚገባው መሆኑን አንዴ ከተማመንህ ወደ ግብህ እንዴት መድረስ እንደምትችል ዕቅድ ማውጣት በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ ወጣቶች የጀመሩትን ሳይጨርሱ የሚቀሩት ተስፋ ስለሚቆርጡ ነው። አንዳንድ ያልታሰቡ ችግሮች ወይም እንቅፋቶች ይነሡ ይሆናል። ወይም ሊሠሩ የወጠኑት ነገር እነርሱ ካሰቡት የበለጠ አስቸጋሪ ሆኖ ያገኙት ይሆናል። ታዲያ አሁን ምን መደረግ አለበት?
10 እንደዚህ ያለው ሁኔታ አንተ በእርግጥ ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ ያሳውቃል። ችግሮች በአፍራሽና አይሆንልኝም በሚሉ አስተሳሰቦች እንዲሞሉህ ከፈቀድህ በዕቅድህ ለመቀጠል ያለህን ኃይል ያዳክመዋል። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው” እንደሚለው ነው። (ምሳሌ 24:10) ስለዚህ በዚህ ፋንታ ሁኔታውን እንደ ፈተና ወይም ትግል አድርገህ ተመልከተው። ተጨማሪ ጥረት ማለትም ተጨማሪ ሃሳብ፣ ኃይልና ጊዜ በመጠቀም ለትግሉ ተነሳ። ፈተናዎች ወይም ትግሎች ካልሸሸሃቸው ሕይወትን አስደሳች ሊያ ደርጉት ይችላሉ። በአሸናፊነት ስትወጣ በራስ መተማመንንና ብልሃት የመፍጠር ችሎታህን ታሳድጋለህ። ከዚያ በኋላ ወደፊት የምትወጥናቸውን ሥራዎች በበለጠ እርግጠኝነትና ደስተኝነት ልትጀምራቸው ትችላለህ።
11 ስለዚህ አንድ ነገር አስቸጋሪ ሲሆን የማቋረጥን ልማድ አስወግድ። አለዚያ ግን በሚቀጥለው ጊዜ ነገሮች ጠንከር ሲሉ የሚቀናህ ያው የተለመደው ማለትም “እጅ መስጠትና” የጀመርከውን ማቋረጥ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ልማድ እንዲጀምር ባለመፍቀድ ሕይወትህን የከሸፉና ተጀምረው ያላለቁ ውጥኖች የሞሉበት ከመሆን ልታድነው ትችላለህ።
12 በቀላሉ ተስፋ የማትቆርጥ፣ የጀመርከውን የማታቆም ወይም ጥለህ የማትወጣ መሆንህን ካስመሰከርክ የሌሎችን አመኔታና አክብሮት ታተርፋለህ። የጥንቱ ክርስቲያን ጢሞቴዎስ ገና ወጣት ሳለ በሁለት የተለያዩ ከተሞች የነበሩ “ወንድሞች የመሰከሩለት” ሆኖ ነበር። (ሥራ 16:2) ሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን የመረጠው ለዚህ ነበር። ጢሞቴዎስ ከሐዋርያው ጋር በብዙ የሮም ግዛት ክፍሎች ለመዘዋወር ልዩ የሆኑ መብቶችን አገኘ። ከአሥር በላይ ለሚያህሉ ዓመታት በታማኝነት ካገለገለ በኋላ (አንዳንድ ጊዜ አደገኛ ሁኔታዎች ያጋጥሙት ነበር) ከባድ ኃላፊነት የሚጠይቅ አደራ ተቀብሎ ፈጽሞታል። ይህንም ሲያደርግ የተሟላ ጤንነት አልነበረውም። አዎ፤ ጢሞቴዎስ በሥራው ላይ ሊጸና እንደሚችልና የተጣራ ሥራ እንደሚሠራ እምነት ሊጣልበት በቅቶ ነበር። የሚታመን ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ይህንን አመኔታ ለማግኘት ጊዜና ያላሰለሰ ጥረት ጠይቆበታል።
በጽናት ለመቀጠል የሚረዳ መሠረት
13, 14. (ሀ) ኖህ መርከቡን ሲሠራ በመጽናቱ እኛ የተጠቀምነው እንዴት ነው? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ሳይሰለች ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ካሳየው ምሳሌነት ምን ልንማር እንችላለን? (2 ጢሞቴዎስ 4:16, 17)
13 አንድን ነገር ልትሠራው የምትፈልገው ትክክል ስለሆነ ወይም አምላክን ለማስደሰት ባለህ ፍላጎት ተገፋፍተህ ከሆነ ከፍጻሜው እንድታደርሰው አምላክ ይረዳሃል። ለምሳሌ ኖኅን
አስብ። እርሱና ልጆቹ የሠሩት መርከብ ሦስት ፎቅ ያለው ርዝመቱ ከ122 ሜትር በላይ የሆነ ሳጥን መሰል ቅርጽ ያለው ነበር። “የቅዳሜና እሁድ ፕሮጀክት” አልነበረም። ሆኖም ኖኅና ቤተሰቡ ሥራውን እስከ መጨረሻው ተግተው ስለተከታተሉት ከጥፋት ውኃ ተረፉ፤ ዘሮቹ የሆንነው እኛም ዛሬ በሕይወት ልንገኝ ቻልን።14 እንደገናም ሐዋርያው ጳውሎስን አስብ። ነገሮች አስቸጋሪ በሚሆኑበት ጊዜ ተስፋ ባለመቁረጡ ጥሩ ምሳሌ ነበር። ልዩ የአገልግሎት ምድቡ ከፍጻሜው እንዲደርስ ማንኛውንም ዓይነት ችግር ተቋቁሞ እንዲያከናውነው የሚገባው ነበር። መደብደብን፣ በድንጋይ መወገርን፣ መታሰርን፣ ከባድ ሥራ መሥራትን፣ እንቅልፍ ማጣትን፣ መጠማትን፣ መራብን፣ ብርድንና መታረዝን፣ ከእውነት ጠላቶችና ከተራ ወንጀለኞች የሚመጣ አደጋንና በባሕርና በየብስ ሲጓዝ ከዱር አራዊትና ከተፈጥሮ ኃይሎች የሚመጡበትን አደጋዎችም ጭምር ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነ። ጀምሮ የሚያቆም ባለመሆኑ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፣ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ” በማለት በትክክል ለመናገር ችሏል። እዚህ ደረጃ ሊደርስ የበቃው በምን መሠረት ነበር? በራሱ በመተማመን ሳይሆን ጳውሎስ ራሱ “ኃይልን በሚሰጠኝ [በእርሱ] ሁሉን እችላለሁ” በማለት በተናገረው መሠረት ነው። በተጨማሪም “በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 4:6–8፤ ፊልጵስዩስ 4:13፤ ሮሜ 8:35–39) ጳውሎስ ምሳሌውን ሊከተሉት የሚገባ ሰው አይመስልህምን?
15. (ሀ) ሁላችንም ከሌሎች ሰዎች ጋር መግባባት መቻል የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) ሰዎች የጠበቅነውን ሳይፈጽሙ ሲቀሩ በእነርሱ ተስፋ ለመቁረጥ እንዳንቸኩል የሚረዳን ምንድን ነው?
15 በሕይወት ለመደሰት ከሌሎች ጋር መግባባት፣ ትብብራቸውን ማግኘትና በእነርሱ መከበር መቻልም ይኖርብሃል። በሰዎች ተስፋ ለመቁረጥ የምትቸኩልና ወዳጅነት ጀምረህ የመጀመሪያውን ያለመግባባት ምልክት ስታይ የምትሸሻቸው ከሆነ ይህን ማድረግ አትችልም። እስቲ ራስህን መርምር። አንዳንድ ጊዜ ከሌምሳሌ 14:29
ሎች ጋር ያለህን ግንኙነት በጥንቃቄ ባለመያዝ እንዲጐዱብህ ምክንያት ትሆናለህን? ታዲያ ይህ በራስህም ተስፋ እንድትቆርጥ ያደርግሃል እንዴ? ታዲያ እንዲህ ከሆነ ሌሎች አንዳንድ ጊዜ የማትጠብቀውን ስላደረጉ ለመከፋት ወይም እነርሱን ለመራቅ ለምን ትቸኩላለህ? የሚያስፈልገውን ጊዜ በመውሰድ ችግሮችን በትዕግስት ፍታ። “ለትዕግስተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል” የሚለውን የመጽሐፈ ምሳሌ ጥበብ ለማስተዋል የማይችል ማን አለ? —16. ሳይሰለቹ ጥረት የማድረግን ጠባይ ማዳበራችን የክርስቲያን ተስፋችንን ፍጻሜ ከማየት ጋር ግንኙነት ያለው እንዴት ነው?
16 ሳይሰለቹ የማያሰልስ ጥረት ማድረግ የሚያስገኛቸው ሽልማቶች ብዙና ጥረት ሊደረግላቸውም የሚገቡ ናቸው። ነገሮችን ዳር የምታደርስ ሰው መሆንህን በማረጋገጥ ብዙ መብቶችንና ጥቅሞችን ታገኛለህ። ኢየሱስ እርሱን ስለሚከተሉት ሰዎች “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:13) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሩጫ ውድድር ላይ ነን። ታላቁ ሽልማትም የዘላለም ሕይወት ነው። ያንን ሽልማት ልትቀዳጅ የምትችለው የፈለገው ችግር ወይም መከራ ቢመጣም ነገሮችን ከፍጻሜ የማድረስ ችሎታን በማዳበር ብቻ ነው።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]