ጤንነቴ ሊያሳስበኝ ይገባል?
ምዕራፍ 10
ጤንነቴ ሊያሳስበኝ ይገባል?
ከታች ከተዘረዘሩት መካከል ልትደርሺባቸው በምትፈልጊያቸው ግቦች ላይ ✔ አድርጊ።
□ ጭንቀትን መቀነስ
□ ቁጣን መቆጣጠር
□ ይበልጥ በራስ መተማመን
□ ይበልጥ ንቁ መሆን
□ ሰውነትን ማጠንከር
□ የቆዳን ጥራት ማሻሻል
□ ክብደት መቀነስ
በሕይወትሽ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነገሮች በአንቺ ምርጫ ላይ የተመኩ አይደሉም፤ * ለምሳሌ ወላጆችሽን፣ ወንድሞችሽንና እህቶችሽን እንዲሁም የምትኖሪበትን ቦታ መምረጥ አትችዪም። ጤንነትሽን በተመለከተ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ከወላጆቻችን የምንወርሳቸው ነገሮች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቢኖርም አካላዊ ጤንነታችን በአብዛኛው የተመካው ሕይወታችንን በምንመራበት መንገድ ላይ ነው። *
‘ገና በዚህ ዕድሜዬ ስለ ጤንነቴ ምን አስጨነቀኝ!’ ትዪ ይሆናል። ይሁንና በገጽ 71 ላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች እስቲ መለስ ብለሽ ተመልከቺ። በስንቶቹ ላይ ምልክት አድርገሽ ነበር? ወደድሽም ጠላሽ፣ እነዚህ ግቦች እንዲሳኩልሽ ከፈለግሽ ጥሩ ጤንነት እንዲኖርሽ ጥረት ማድረግ አለብሽ።
አምበር የተባለች የ17 ዓመት ወጣት፣ ለጤና ተስማሚ ናቸው የሚባሉ ምግቦችን ለምሳሌ ካልተፈተገ ስንዴ የሚዘጋጅ ዳቦ እንዲሁም ቅባት ያልበዛበትና ስኳር የሌለው ምግብ ብቻ እየበላች መኖር እንደማትፈልግ ገልጻለች፤ አንቺም እንደ እሷ ይሰማሽ ይሆናል። ከሆነ አታስቢ፤ ጥሩ ጤንነት እንዲኖርሽ ጣፋጭ ነገሮችን እርግፍ አድርገሽ መተው ወይም በየሳምንቱ ረጅም ርቀት መሮጥ አያስፈልግሽም። በእርግጥም የተሻለ ቁመና እንዲኖርሽ፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማሽና ቀልጣፋ እንድትሆኚ ከፈለግሽ ጥቂት ማስተካከያዎችን ማድረግ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ እኩዮችሽ በዚህ ረገድ ሊሳካላቸው የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ጥሩ የአመጋገብ ልማድ—የተሻለ ቁመና!
መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ነገር ልከኞች እንድንሆን ይመክራል። በምሳሌ 23:20 (የ1980 ትርጉም) ላይ ‘ብዙ ምግብ መብላት’ ተወግዟል። እርግጥ ነው፣ ይህን ምክር መከተል ሁልጊዜ ቀላል አይደለም።
“እንደ አብዛኞቹ ወጣቶች ሁሉ እኔም ቶሎ ቶሎ ይርበኛል። በዚህም የተነሳ ወላጆቼ ‘እምብርት የለውም’ ይሉኛል!”—አንድሩ፣ 15
“አንዳንድ ምግቦች የሚያስከትሉት ጉዳት ወዲያው ስለማይታየኝ ያን ያህል እንደማይጎዱኝ ይሰማኛል።”—ዳንዬል፣ 19
ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ ራስሽን መግዛት ያስፈልግሽ ይሆን? አንዳንድ
እኩዮችሽ በዚህ ረገድ ጠቃሚ ሆነው ያገኟቸው ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።ልክን ማወቅ፦ የ19 ዓመቷ ጁሊያ “የምበላው ምግብ ምን ያህል ካሎሪ እንዳለው አሰላ ነበር፤ አሁን ግን ሆዴ እንደሞላ ሲሰማኝ መብላት አቆማለሁ” ብላለች።
ለጤና የማይጠቅሙ ምግቦችን አለመመገብ፦ የ21 ዓመቱ ፒተር “ለስላሳ መጠጣት ሳቆም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ አምስት ኪሎ ቀነስኩ!” ብሏል።
የአመጋገብ ልማድን ማስተካከል፦ ኤሪን የተባለች የ19 ዓመት ወጣት “ደጋግሜ እየጨመርኩ ላለመብላት ጥረት አደርጋለሁ” በማለት ተናግራለች።
ቁልፉ፦ ቁርስም ሆነ ምሳ አሊያም ራት አትዝለዪ! እንዲህ ማድረግ በጣም ስለሚያስርብሽ ብዙ ልትበዪ ትችያለሽ።
ስፖርት ሥሪ—ጥሩ ስሜት ይኖርሻል!
መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) ብዙ ወጣቶች ግን ስፖርት ለመሥራት ያን ያህል ፍላጎት የላቸውም።
“በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ ምን ያህል ልጆች በስፖርት ትምህርት እንደወደቁ ብነግራችሁ ይገርማችኋል። ደግሞም እንደ ስፖርት ትምህርት ቀላል ነገር አልነበረም!”—ሪቻርድ፣ 21
“አንዳንዶች ‘የቪዲዮ ጨዋታ በመጫወት ስፖርት የሠራሁ ሆኖ እንዲሰማኝ ማድረግ እየቻልኩ ላብ በላብ እስክሆን ድረስ በፀሐይ ምን አሯሯጠኝ?’ ብለው ያስባሉ።”—ሩት፣ 22
“ስፖርት” የሚለውን ቃል ስትሰሚ ገና ድክም ይልሻል? ከሆነ ጥሩ የስፖርት ልማድ ማዳበር የሚያስገኛቸውን ሦስት ጥቅሞች ተመልከቺ።
አንደኛ፦ ስፖርት መሥራት በሽታ የመከላከል አቅምን ያጠናክራል። የ19 ዓመቷ ሬቸል እንደሚከተለው ስትል ተናግራለች፦ “አባቴ ‘ስፖርት ለመሥራት ጊዜ እንደሌለሽ የሚሰማሽ ከሆነ ታመሽ ብትተኚ የበለጠ ጊዜ እንደምታጠፊ አስታውሺ’ ይለኝ ነበር።”
ሁለተኛ፦ ስፖርት መሥራት አንጎላችን ጥሩ ስሜት የሚፈጥሩ ኬሚካሎችን እንዲያመነጭ ያደርጋል። የ16 ዓመቷ
ኤሚሊ “አእምሮዬ በሚወጣጠርበት ጊዜ ሩጫ ቀለል እንዲለኝ ይረዳኛል። ሰውነቴ የሚታደስ ከመሆኑም በላይ ስሜቴ ይረጋጋል” በማለት ተናግራለች።ሦስተኛ፦ ስፖርት መሥራት ጥሩ መዝናኛ ሊሆን ይችላል። “ከቤት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ያስደስቱኛል፤ በእግር መንሸራሸር፣ መዋኘት፣ ብስክሌት መንዳትና የመሳሰሉትን ስፖርቶች የምመርጠውም ለዚህ ነው” በማለት የ22 ዓመቷ ሩት ተናግራለች።
ቁልፉ፦ በሳምንት ሦስት ጊዜ ቢያንስ ለ20 ደቂቃ ያህል የምትወጂውን ስፖርት ሥሪ፤ የምትመርጪው የስፖርት ዓይነት በደንብ እንድትንቀሳቀሺ የሚያደርግ መሆን አለበት።
በደንብ ተኚ—ቀልጣፋ ትሆኛለሽ!
መጽሐፍ ቅዱስ “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ [“በዕረፍት፣” የ1954 ትርጉም] የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል” ይላል። (መክብብ 4:6) በቂ እንቅልፍ ካላገኘሽ ነገሮችን በቅልጥፍና ማከናወን አትችዪም።
“በቂ እንቅልፍ ካላገኘሁ ምንም ነገር በትክክል መሥራት አልችልም። ሐሳቤን ማሰባሰብ እቸገራለሁ!”—ሬቸል፣ 19
“ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ ሲሆን በጣም ስለሚደክመኝ ከሰዎች ጋር እያወራሁ እንኳ እንቅልፍ ሊወስደኝ ይችላል!”—ክሪስቲን፣ 19
በቂ እንቅልፍ እንደማታገኚ ይሰማሻል? አንዳንድ እኩዮችሽ ምን እንዳደረጉ እስቲ እንመልከት።
በጊዜ መተኛት፦ የ18 ዓመቷ ካትሪን “በጊዜ ለመተኛት ጥረት እያደረግሁ ነው” ብላለች።
በእንቅልፍ ሰዓት ወሬ ማቆም፦ የ21 ዓመቱ ሪቻርድ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቼ በጣም ከመሸ በኋላ ይደውሉልኛል ወይም በሞባይል መልእክት ይልኩልኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወሬ ትቼ በጊዜ መተኛት ጀምሬያለሁ።”
በተመሳሳይ ሰዓት መተኛት፦ የ20 ዓመቷ ጄኒፈር “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምተኛበት እና የምነሳበት ሰዓት ቋሚ እንዲሆን ለማድረግ እየጣርኩ ነው” ብላለች።
ቁልፉ፦ በየቀኑ ቢያንስ ስምንት ሰዓት ለመተኛት ጥረት አድርጊ።
ጤንነትሽን ለመጠበቅ ቀላል የሆኑ ጥቂት እርምጃዎችን ብቻ መውሰድ ብዙ ጥቅሞች ያስገኝልሻል። ጥሩ ጤንነት የተሻለ ቁመና እንዲኖርሽ፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማሽና ቀልጣፋ እንድትሆኚ እንደሚረዳሽ አትዘንጊ። በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙሽን አንዳንድ ነገሮች መለወጥ ባትችዪም ጥሩ ጤንነት እንዲኖርሽ ለማድረግ ግን የራስሽን ድርሻ መወጣት ትችያለሽ። የ19 ዓመቷ ኤሪን እንደተናገረችው “ጤናማ መሆንሽ ዞሮ ዞሮ የተመካው በአንቺ ላይ ነው።”
በአለባበስ ረገድ ከወላጆችሽ ጋር መግባባት አቅቶሻል? ከሆነ ከእነሱ ጋር መስማማት የምትችዪው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.11 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።
^ አን.11 እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች የጤና ችግር ያጋጠማቸው ወይም የአካል ጉዳተኛ የሆኑት ለጤንነታቸው ስላልተጠነቀቁ አይደለም። ይህ ምዕራፍ እንዲህ ያሉ ሰዎች አቅማቸው በሚፈቅድላቸው መጠን ጤንነታቸውን ለማሻሻል ሊረዷቸው የሚችሉ ሐሳቦችን ይዟል።
ቁልፍ ጥቅስ
“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8
ጠቃሚ ምክር
ከሌሎች ጋር ስፖርት ለመሥራት ቀጠሮ ያዢ። እንዲህ ካደረግሽ የሌሎችን ፕሮግራም ላለማበላሸት ስትዪ በፕሮግራምሽ ትጸኛለሽ።
ይህን ታውቅ ነበር?
ስፖርት መሥራት ሰውነታችን ኢንዶርፊኖችን እንዲያመነጭ ያደርጋል፤ በአንጎላችን ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ኬሚካሎች የሕመም ስሜት እንዲቀንስ የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ስሜት ይፈጥራሉ።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
ከአመጋገቤ ጋር በተያያዘ ልደርስበት የምችለው ግብ ․․․․․
ከስፖርት ጋር በተያያዘ ልደርስበት የምችለው ግብ ․․․․․
በሚቀጥለው ወር በየቀኑ በአማካይ ․․․․․ ሰዓት ለመተኛት አስቤያለሁ።
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● ጤንነትን መጠበቅ በራስ የመተማመን ስሜትን የሚጨምረው እንዴት ነው?
● ከአካላዊ ጤንነት ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?—1 ጢሞቴዎስ 4:8
[በገጽ 74 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ስፖርት ስሠራ ጥሩ ስሜት ይኖረኛል። ከዚህም ሌላ ቁመናዬ እየተሻሻለ በመሆኑ በራስ የመተማመን ስሜቴ ጨምሯል!”—ኤሚሊ
[በገጽ 73 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ትልቅ ለውጥ አደረግሁ’
“በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለሁ ከመጠን በላይ ወፍራም ነበርኩ፤ እንደዚያ መሆን ደግሞ ፈጽሞ አልፈልግም ነበር። ቁመናዬ ስለሚያስጠላኝ ደስተኛ አልነበርኩም! ከዚህም ሌላ ጤንነት አይሰማኝም ነበር። ለየት ያለ የአመጋገብ ሥርዓት በመከተል ክብደት ለመቀነስ የሞከርኩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም መልሼ እወፍር ነበር። ስለዚህ 15 ዓመት ሲሆነኝ ትልቅ ለውጥ ለማድረግ ቆርጬ ተነሳሁ። ውፍረቴን መቀነስ ያለብኝ በትክክለኛው መንገድ ይኸውም ሁልጊዜ ልከተለው የምችል ልማድ በማዳበር እንደሆነ ወሰንኩ። ስለተመጣጠነ ምግብና ስለ ሰውነት እንቅስቃሴ የሚናገር መጽሐፍ ገዛሁና ያነበብኩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ። ፕሮግራሜን መከተል ቢያቅተኝ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ቢያጋጥመኝም እንኳ ጥረት ማድረጌን ከነጭራሹ ላለመተው ቆርጬ ነበር። ባይገርማችሁ ተሳካልኝ! በአንድ ዓመት ውስጥ ከ25 ኪሎ ግራም በላይ ቀነስኩ። ከዚያ በኋላ ለሁለት ዓመት ያህል ክብደት ሳልጨምር በዚያው መቀጠል ቻልኩ። ይህ ይሆናል ብዬ ፈጽሞ አላሰብኩም ነበር! ሊሳካልኝ የቻለው የአመጋገብ ልማዴን ስላስተካከልኩ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ስላደረግሁ እንደሆነ ይሰማኛል።”—ካትሪን፣ 18
[በገጽ 74 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጤንነት እንደ መኪና ነው፤ ተገቢው እንክብካቤ ካልተደረገለት ይጎዳል