በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ እንድዝናና የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?

ወላጆቼ እንድዝናና የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 37

ወላጆቼ እንድዝናና የማይፈቅዱልኝ ለምንድን ነው?

በአውስትራሊያ የምትኖር አሊሰን የተባለች ወጣት ሰኞ በመጣ ቁጥር ትምህርት ቤት ስትሄድ ጭንቅ ይላታል።

“ሁሉም የሚያወሩት ቅዳሜና እሁድን እንዴት እንዳሳለፉ ነው” በማለት ትናገራለች። “ከአነጋገራቸው አሪፍ ጊዜ ያሳለፉ ይመስላል፤ ለምሳሌ ምን ያህል ፓርቲዎች ላይ እንደተገኙ፣ ከስንት ወንዶች ጋር እንደተሳሳሙ፣ ሌላው ቀርቶ ፖሊሶችን እንዴት እንደሸወዱ ጭምር ያወራሉ . . . በጣም የሚያስፈራ ቢመስልም ደስ የሚል ነገር አለው! ቤታቸው የሚገቡት ሊነጋጋ ሲል 11 ሰዓት ላይ ቢሆንም ወላጆቻቸው ምንም አይሏቸውም። እኔ ወደ መኝታዬ በምሄድበት ሰዓት እነሱ ለመዝናናት ይወጣሉ!

“የክፍሌ ልጆች ቅዳሜና እሁድ ስላሳለፉት አስገራሚ ጊዜ ከነገሩኝ በኋላ እኔ ምን እንዳደረግሁ ይጠይቁኛል። . . . ያው እኔ ደግሞ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ሄጃለሁ፤ በአገልግሎት ተካፍያለሁ። ከእነሱ አንጻር ግን ብዙ ነገር እንዳመለጠኝ ይሰማኛል። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ስለ ቅዳሜና እሁድ ሲጠይቁኝ ምንም እንዳላደረግሁ እነግራቸዋለሁ። እነሱም ‘ታዲያ ለምን ከእኛ ጋር አልሄድሽም?’ ይሉኛል።

“እንደምንም ሰኞን ካለፍኩ ሁኔታው እንደሚቀልልኝ ታስቡ ይሆናል። ግን እንደምታስቡት አይደለም። ማክሰኞ ደግሞ ሁሉም ስለ መጪው ቅዳሜና እሁድ ማውራት ይጀምራል! በአብዛኛው እነሱ ሲያወሩ ቁጭ ብሎ ከመስማት ውጭ ምንም ማለት አልችልም። የቀረብኝ ነገር እንዳለ ስለሚሰማኝ ይከፋኛል!”

አንተም ሰኞ ሰኞ ትምህርት ቤት እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥምሃል? ሌሎቹ ልጆች ሁሉ እንደ ልባቸው ሲዝናኑ አንተ ግን እንዳትወጣ ወላጆችህ አንድ ክፍል ውስጥ እንደቆለፉብህ ሊሰማህ ይችላል፤ አሊያም ብዙ መጫወቻዎች ወዳሉበት የመዝናኛ ስፍራ ብትሄድም በአንዱም እንኳ እንዳትጫወት የተከለከልህ ያህል ይሰማህ ይሆናል። እርግጥ እኩዮችህ የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ ማድረግ ትፈልጋለህ ማለት አይደለም። ያም ቢሆን ግን አልፎ አልፎ መዝናናት ሊያምርህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ መጪውን ቅዳሜና እሁድ በምን መዝናናት ትፈልጋለህ?

□ ዳንስ

□ ፓርቲ

□ የሙዚቃ ትርዒት

□ ፊልም

□ ሌላ ․․․․․

መዝናናት እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው። ፈጣሪም ቢሆን የወጣትነት ጊዜህን አስደሳች በሆነ መንገድ እንድታሳልፍ ይፈልጋል። (መክብብ 3:1, 4) አንዳንድ ጊዜ ላይመስልህ ቢችልም እንኳ ወላጆችህም እንድትዝናና ይፈልጋሉ። ያም ሆኖ ወላጆችህ የሚያሳስቧቸው ሁለት ነገሮች አሉ፦ (1) የምትመርጠው መዝናኛ እና (2) አብረሃቸው የምትውላቸው ልጆች። ደግሞም እነዚህ ነገሮች ቢያሳስቧቸው የሚያስደንቅ አይደለም።

ይሁንና ጓደኞችህ አብረሃቸው ወጣ ብለህ እንድትዝናና ቢጋብዙህና ወላጆችህ የሚፈቅዱልህ ባይመስልህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሦስት አማራጮች አሉህ፤ እስቲ እነዚህን አማራጮች እና የሚያስከትሉትን ውጤት አንድ በአንድ እንመልከት።

አማራጭ ሀ ሳታስፈቅድ መሄድ

ይህን ማድረግ የምትፈልግበት ምክንያት፦ የወላጆችህን ፈቃድ ሳትጠይቅ የፈለግኸውን ማድረግ እንደምትችል ለእኩዮችህ ለማሳየት ብለህ ይሆናል። ወይም ከወላጆችህ የበለጠ እንደምታውቅ ስለሚሰማህ አሊያም የእነሱ አመለካከት ትክክል እንዳልሆነ ስለምታስብ ይሆናል።—ምሳሌ 14:18

ውጤቱ፦ እንዲህ በማድረግህ ጓደኞችህ ሊያደንቁህ ቢችሉም አታላይ እንደሆንህ ማሰባቸው አይቀርም። ዛሬ ወላጆችህን ካታለልህ ነገ ጓደኞችህንም ልታታልል ትችላለህ። ወላጆችህ ስለ ጉዳዩ ካወቁ ደግሞ በጣም ሊያዝኑብህ አልፎ ተርፎም በአንተ ላይ ያላቸውን እምነት ሊያጡና ተጨማሪ ገደብ ሊጥሉብህ ይችላሉ! በእርግጥም የወላጆችህን ትእዛዝ ጥሰህ ለመዝናናት መሄድህ ሞኝነት ነው።—ምሳሌ 12:15

አማራጭ ለ ማስፈቀዱንም መሄዱንም መተው

ይህን ማድረግ የምትፈልግበት ምክንያት፦ መዝናኛው አንተ ከምትከተላቸው መመሪያዎች ጋር እንደማይሄድ ወይም በቦታው ከሚገኙት መካከል አንዳንዶቹ ጥሩ ምግባር የሌላቸው እንደሆኑ ስለተገነዘብህ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ፊልጵስዩስ 4:8) በሌላ በኩል ደግሞ ለመሄድ ብትፈልግም ወላጆችህን ማስፈቀድ ትፈራ ይሆናል።

ውጤቱ፦ የጓደኞችህን ግብዣ ያልተቀበልከው መዝናኛው ጥሩ እንዳልሆነ ስለተሰማህ ከሆነ ጓደኞችህ ለምን እንደቀረህ ሲጠይቁህ በልበ ሙሉነት መልስ መስጠት ትችላለህ። ላለመሄድ የወሰንከው ወላጆችህን መጠየቁ ስላስፈራህ ብቻ ከሆነ ግን ጓደኞችህ ሲዝናኑ አንተ ብቻ እንደቀረህ በማሰብ ቤትህ ቁጭ ብለህ ስትብሰለሰል ልትውል ነው።

አማራጭ ሐ መጠየቅና የሚሉትን መስማት

ይህን ማድረግ የምትፈልግበት ምክንያት፦ ወላጆችህ በአንተ ላይ ሥልጣን እንዳላቸውና ከአንተ የተሻለ እንደሚያውቁ ስለተገነዘብህ ሊሆን ይችላል። (ቆላስይስ 3:20) አሊያም ወላጆችህን ስለምትወዳቸውና ከእነሱ ተደብቀህ በመሄድ ልታሳዝናቸው ስለማትፈልግ ይሆናል። (ምሳሌ 10:1) ይህን አማራጭ የምትፈልግበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ምን እንደምትፈልግ ለወላጆችህ ለመግለጽ አጋጣሚ ስለሚፈጥርልህ ሊሆን ይችላል።

ውጤቱ፦ ወላጆችህ እንደምትወዳቸውና እንደምታከብራቸው ይሰማቸዋል። በዚያ ላይ ደግሞ ጥያቄህን ምክንያታዊ ሆኖ ካገኙት ሊፈቅዱልህ ይችላሉ።

ወላጆች ላይፈቅዱ የሚችሉበት ምክንያት

ይሁንና ወላጆችህ የጠየቅኸውን ነገር ባይፈቅዱልህስ? ይህ ሊያበሳጭህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሁኔታውን በወላጆችህ ቦታ ሆነህ ለመመልከት መሞከርህ ውሳኔያቸውን ለመቀበል ሊረዳህ ይችላል። ወላጆችህ ጥያቄህን ያልተቀበሉት ቀጥሎ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል።

ከአንተ የበለጠ እውቀትና ተሞክሮ ያላቸው መሆኑ። ለመዋኘት አስበሃል እንበል፤ በምትዋኝበት ወቅት ከተቻለ ሕይወት አድን ሠራተኞች በአካባቢው እንዲኖሩ እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ውኃው ውስጥ ስትሆን መዝናናትህ እንጂ ሊመጣ የሚችለው አደጋ አይታይህም። ሕይወት አድን ሠራተኞቹ የተቀመጡት ግን አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ለማየት በሚያስችላቸው የተሻለ ቦታ ላይ ነው።

በተመሳሳይም ወላጆችህ ከአንተ የተሻለ እውቀትና ተሞክሮ ስላላቸው አንተ የማታያቸውን አደጋዎች ሊያስተውሉ ይችላሉ። እንደ ሕይወት አድን ሠራተኞቹ ሁሉ የወላጆችህም ዓላማ እንዳትዝናና ማድረግ ሳይሆን ደስታህን ሊያሳጡህ ከሚችሉ አደጋዎች አንተን መጠበቅ ነው።

ለአንተ ያላቸው ፍቅር። ወላጆችህ አንተን ከጉዳት ለመጠበቅ ይፈልጋሉ። አንተን ስለሚወዱህ፣ የጠየቅኸው ነገር ተገቢ ሲሆን ሊፈቅዱልህ የሚፈልጉ ቢሆንም አደጋ ሊያጋጥምህ እንደሚችል ከተሰማቸው ይከለክሉሃል። አንድ ነገር ጠይቀሃቸው ከመፍቀዳቸው በፊት ሁኔታው ጉዳት የማያስከትል መሆን አለመሆኑን በደንብ ያስቡበታል። የጠየቅኸውን ነገር የሚፈቅዱልህ ምንም ጉዳት እንደማይደርስብህ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት ካለ ብቻ ነው።

ፈቃድ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?

በዚህ ረገድ ሊረዱህ የሚችሉ አራት ነጥቦችን እንመልከት።

ሐቀኛ ሁን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ራስህን እንዲህ እያልክ በሐቀኝነት መጠየቅ ይኖርብሃል፦ ‘መሄድ የምፈልግበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው? መዝናኛውን ስለምወደው ነው ወይስ በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ስለፈለግኩ? ወይም ደግሞ ደስ የምትለኝ ልጅ እዚያ ስለምትመጣ ነው?’ ወላጆችህን በምታስፈቅድበት ጊዜም ሐቀኛ ሁን። እነሱም በአንድ ወቅት ወጣቶች እንደነበሩ አትዘንጋ፤ ደግሞም አንተን በደንብ ያውቁሃል። ስለዚህ ለመሄድ የፈለግህበትን ትክክለኛ ምክንያት ልትደብቃቸው ብትሞክርም እንኳ ማወቃቸው አይቀርም። እውነቱን ብትነግራቸው ግን ደስ ይላቸዋል፤ አንተም ብትሆን እነሱ ከሚሰጡህ ጥበብ ያዘለ ምክር ትጠቀማለህ። (ምሳሌ 7:1, 2) በሌላ በኩል ግን ሐቀኛ ካልሆንህ በእነሱ ዘንድ ያለህን አመኔታ የምታጣ ከመሆኑም በላይ ፈቃድ የማግኘት አጋጣሚህ የጠበበ ይሆናል።

ጊዜ ምረጥ። ወላጆችህ ሥራ ውለው ገና እግራቸው ቤት ከመርገጡ ወይም አእምሯቸው በሌሎች ጉዳዮች ተወጥሮ ባለበት ሰዓት ጥያቄ ማቅረብ ወይም ፈቃድ እንዲሰጡህ መጎትጎት ጥበብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘና በሚሉበት ጊዜ ጠይቃቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ቀኑ እስኪደርስ አትጠብቅ፤ ባለቀ ሰዓት መጠየቅና መልስ እንዲሰጡህ መጎትጎት አያዋጣም። ወላጆችህ የችኮላ ውሳኔ ማድረግ አይፈልጉም። ቀደም ብለህ ብትጠይቃቸው ግን በጉዳዩ ላይ ለማሰብ ጊዜ ስለሚያገኙ ደስ ይላቸዋል።

የተሟላ መረጃ ስጥ። ፈቃድ ስትጠይቅ ግልጽ ያልሆነ ነገር ከመናገር ይልቅ ማድረግ የፈለግኸውን ነገር በዝርዝር ንገራቸው። ወላጆችህ “እነማን ይገኛሉ?” “ኃላፊነት የሚሰማው ትልቅ ሰው በቦታው ይኖራል?” ወይም “ዝግጅቱ የሚያልቀው በስንት ሰዓት ነው?” ብለው ሲጠይቁህ “እኔ እንጃ” የሚል መልስ የምትሰጥ ከሆነ ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል።

ጥሩ አመለካከት ይኑርህ። ወላጆችህን እንደ ጠላት አትያቸው። ከዚህ ይልቅ ከአንተ ጎን እንደቆሙ አድርገህ ተመልከታቸው፤ ደግሞም ቆም ብለህ ካሰብህበት እውነታው ይህ ነው። ወላጆችህ ከጎንህ እንደሆኑ የምታስብ ከሆነ ስትናገር ቆጣ ቆጣ ከማለት ትቆጠባለህ፤ ይህ ደግሞ እንዲፈቅዱልህ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ለምሳሌ፣ “ለምን አታምኑኝም!” “ሌሎቹ ልጆች ሁሉ ይሄዳሉ፣” “የጓደኞቼ ወላጆች’ኮ ፈቅደውላቸዋል!” እንደሚሉት ያሉ አነጋገሮችን አትጠቀም። የወላጆችህን ውሳኔ በመቀበልና በመታዘዝ ብስለት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። እንዲህ ካደረግህ እነሱም ያከብሩሃል። ደግሞም በሌላ ጊዜ ፈቃድ ስትጠይቃቸው በተቻለ መጠን አንተን ለማስደሰት ጥረት ያደርጋሉ።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 32 ተመልከት

ቁልፍ ጥቅስ

“ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው።”—ምሳሌ 27:11

ጠቃሚ ምክር

ወደ አንድ ግብዣ ከመሄድህ በፊት፣ በግብዣው ላይ ነገሮች እንደጠበቅኸው ባይሆኑ ሕሊናህን የሚረብሽ ነገር ሳትፈጽም ለመውጣት ምን ልትል ወይም ልታደርግ እንደምትችል አስቀድመህ አስብ።

ይህን ታውቅ ነበር?

አፍቃሪ ወላጆች ‘ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ’ የሚለውን ብሂል መከተል ይመርጣሉ። ጥያቄህ ምን እንደሆነ ግልጽ ካላደረግህላቸው ወይም የተሟላ መረጃ እንዳልሰጠሃቸው ከተሰማቸው ላይፈቅዱልህ ይችላሉ።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ፊልም ቤት ወይም አንድ ግብዣ ላይ እያለሁ ሕሊናዬን የሚረብሽ ነገር ብመለከት ወይም ብሰማ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ወላጆችህ አንድ ነገር እንዲፈቅዱልህ ስትጠይቅ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳቸውን የተሟላ መረጃ ከመስጠት ወደኋላ የምትለው ለምን ሊሆን ይችላል?

● ለወላጆችህ በቂ መረጃ ሳትሰጥ እንዲፈቅዱልህ ማድረግ ብትችል እንኳ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

[በገጽ 268 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ልጅ እያለሁ በጣም ሞኝ ነበርኩ። አስደሳች ይመስሉኝ የነበሩ አንዳንድ ነገሮችን አሁን መለስ ብዬ ሳስባቸው ያን ያህል አስደሳች እንዳልሆኑ ይሰማኛል። የዘራነውን ማጨዳችን አይቀርም። ወላጆቼን አለመስማቴ አሁን ይቆጨኛል።”—ብራያን

[በገጽ 269 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ሕይወት አድን ሠራተኞች ሁሉ ወላጆችህም አደጋ የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ለማየት በሚያስችል የተሻለ ቦታ ላይ ናቸው