አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች—ጢሞቴዎስ
አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች—ጢሞቴዎስ
ጢሞቴዎስ ከቤተሰቡ ተለይቶ ሊሄድ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ግን የሐዋርያው ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ ሆኖ በሚስዮናዊነት ለማገልገል እንጂ ከቤተሰቦቹ ጋር መኖር ስላልፈለገ አይደለም። በዚህ ወቅት ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም፤ ያም ቢሆን “በልስጥራና በኢቆንዮን ባሉ ወንድሞች ዘንድ በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት” ኃላፊነት የሚሰማው ወጣት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 16:2) ጢሞቴዎስ በአምላክ አገልግሎት ትልቅ ነገር ማከናወን እንደሚችል ጳውሎስ ተማምኖበታል። ጢሞቴዎስም አላሳፈረውም! በቀጣዮቹ ዓመታት ጢሞቴዎስ ወደ በርካታ ቦታዎች በመጓዝ ጉባኤዎችን አቋቁሟል እንዲሁም ወንድሞችን አበረታትቷል። ጢሞቴዎስ ግሩም ባሕርያት ስለነበሩት በጳውሎስ ዘንድ ተወዳጅነት አትርፏል፤ ጳውሎስ ከ11 ዓመታት በኋላ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ ጢሞቴዎስ ሲናገር “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም” ብሏል።—ፊልጵስዩስ 2:20
አንተስ በአምላክ አገልግሎት ለመካፈል ራስህን ታቀርባለህ? እንዲህ ማድረግህ ብዙ በረከት ያስገኝልሃል! ይሖዋ ‘በገዛ ፈቃዳቸው’ ራሳቸውን የሚያቀርቡ ወጣቶችን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (መዝሙር 110:3) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ አምላክ ‘የምታከናውነውን ሥራ ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ እንዳልሆነ’ ማረጋገጫ ተሰጥቶሃል።—ዕብራውያን 6:10