አባቴና እናቴ የተለያዩት ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 4
አባቴና እናቴ የተለያዩት ለምንድን ነው?
“አባቴ ጥሎን የሄደበት ቀን አይረሳኝም፤ ያን ዕለት ከእናቴ ጋር ቤት ነበርኩ። በወቅቱ ገና ስድስት ዓመቴ ስለነበር የተፈጠረው ነገር አልገባኝም። ወለሉ ላይ ቁጭ ብዬ ቴሌቪዥን እያየሁ ሳለ እናቴ እያለቀሰች ትቶን እንዳይሄድ አባቴን ስትለምነው ይሰማኝ ነበር። አባቴ ግን ሻንጣውን ይዞ እኔ ወዳለሁበት መጣ፤ ከዚያም በርከክ ብሎ ከሳመኝ በኋላ ‘ምንጊዜም እወድሻለሁ እሺ?’ ብሎኝ ከቤት ወጥቶ ሄደ። ከዚያ በኋላ አባቴን ለረጅም ጊዜ አላገኘሁትም። አባቴ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ ‘እናቴም ትታኝ ትሄድ ይሆን?’ ብዬ እፈራለሁ።”—ኢሌይን፣ 19
ወላጆችህ ሲፋቱ ሕይወትህ ምስቅልቅሉ እንደወጣና መቼም ቢሆን እንደማይሻሻል ይሰማህ ይሆናል። የወላጆች መለያየት ልጆች ብዙውን ጊዜ በኀፍረት እንዲዋጡ፣ እንዲናደዱ፣ ስጋትና የጥፋተኝነት ስሜት እንዲያድርባቸው፣ እንደተተዉ እንዲሰማቸው፣ በጭንቀትና በጥልቅ ሐዘን እንዲዋጡ አልፎ ተርፎም የመበቀል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል።
ወላጆችህ በቅርቡ ተለያይተው ከሆነ አንተም እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ይሆናል። ይህ ምንም አያስገርምም፤ ምክንያቱም ፈጣሪያችን ቤተሰብን ሲመሠርት ዓላማው አባትና እናት አንድ ላይ ሆነው ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ነው። (ኤፌሶን 6:1-3) አሁን ግን የምትወደውን አባትህን ወይም የምትወዳትን እናትህን እንደ ወትሮው በየቀኑ አታገኛቸውም። የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ የተለያዩት ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “አባቴን በጣም ከፍ አድርጌ ስለምመለከተው ከእሱ ጋር መሆን ፈልጌ ነበር። ይሁንና እኛን የማሳደግ መብት የተሰጣት እናታችን ናት።”
ወላጆች የሚለያዩበት ምክንያት
ወላጆች በመካከላቸው ችግር በሚኖርበት ጊዜ ነገሩን ከልጆቻቸው ስለሚደብቁት በአብዛኛው ልጆቹ የወላጆቻቸው መለያየት ያልጠበቁት ነገር ይሆንባቸዋል። የ15 ዓመት ልጅ እያለች ወላጆቿ የተፋቱት ሬቸል “ነገሩ ዱብ ዕዳ ነበር የሆነብኝ” ብላለች። አክላም “በጣም እንደሚዋደዱ አስብ ነበር” በማለት ተናግራለች። ልጆች ወላጆቻቸው ሲጨቃጨቁ ቢያዩም እንኳ ጨክነው ሲለያዩ ሊደነግጡ ይችላሉ!
ብዙውን ጊዜ ለመለያየት ምክንያት የሚሆነው አንደኛው ወላጅ የፆታ ብልግና መፈጸሙ ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ታማኝ የሆነው ወገን የትዳር ጓደኛውን የመፍታት እና ሌላ ሰው የማግባት መብት እንዳለው የአምላክ ቃል ይናገራል። (ማቴዎስ 19:9) በሌላ በኩል ደግሞ “ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ” እየተባባሰ ሄዶ አካላዊ ጥቃት ወደ መሰንዘር ካመራ አንደኛው ወላጅ ለራሱና ለልጆቹ ደኅንነት በመስጋት መለየትን ይመርጥ ይሆናል።—ኤፌሶን 4:31
በእርግጥ አንዳንድ ባለትዳሮች የሚለያዩት አጥጋቢ ምክንያት ሳይኖራቸው ነው። እነዚህ ባለትዳሮች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከመጣር ይልቅ ‘በትዳሬ ደስተኛ አይደለሁም’ ወይም ‘ፍቅራችን አልቋል’ በሚል ሰበብ ይፋታሉ። እንዲህ ያለው የራስ ወዳድነት አካሄድ “ፍችን እጠላለሁ” ያለውን አምላክ ያሳዝነዋል። (ሚልክያስ 2:16) በሌላ በኩል ደግሞ አንደኛው ወገን ክርስትናን ሲቀበል ሌላኛው የትዳር ጓደኛ ትዳሩን ለማፍረስ ሊወስን እንደሚችል ኢየሱስ ጠቁሟል።—ማቴዎስ 10:34-36
ምሳሌ 24:10) እንዲሁም ለትዳራቸው አለመሳካት ሁለቱም ተጠያቂ መሆናቸውን መናገሩ አሳፍሯቸው እና አሸማቅቋቸው ሊሆን ይችላል።
ወላጆችህ የተፋቱበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ይህን ለአንተ ለመናገር ያልፈለጉት ወይም ከዚህ ጋር በተያያዘ የምታቀርብላቸውን ጥያቄዎች አድበስብሰው ለማለፍ የመረጡት ስለማይወዱህ አይደለም። ወላጆችህ ሁኔታው ስሜታቸውን በጣም ስለጎዳው ስለ ፍቺው ማውራት ይከብዳቸው ይሆናል። (ምን ማድረግ ትችላለህ?
ስጋትህ ምን እንደሆነ ለይተህ እወቅ። የወላጆችህ መፋታት ነገሮች ድብልቅልቅ እንዲሉብህ ሊያደርግ ስለሚችል ከዚያ በፊት ያን ያህል የማያሳስቡህ ነገሮች አሁን ያስጨንቁህ ይሆናል። ያም ቢሆን ስጋትህ ምን እንደሆነ ለይተህ ማወቅህ ፍርሃትህን ለመቆጣጠር ሊረዳህ ይችላል። ቀጥሎ ከተዘረዘሩት መካከል የበለጠ ስጋት የሚፈጥርብህ ነገር ላይ ✔ አድርግ፤ አሊያም ደግሞ “ሌላ” በሚለው ክፍት ቦታ ላይ ይበልጥ የምትሰጋበትን ነገር ጻፍ።
□ አብሮኝ ያለው ወላጄም ጥሎኝ ይሄዳል
□ ቤተሰባችን የገንዘብ ችግር ያጋጥመዋል
□ ወላጆቼ የተፋቱት በእኔ ምክንያት ነው
□ ወደፊት ትዳር ብመሠርት ተመሳሳይ ዕጣ ያጋጥመኛል
□ ሌላ ․․․․․
ስለሚያሳስብህ ጉዳይ ሌሎችን አማክር። ንጉሥ ሰለሞን “ለመናገርም ጊዜ አለው” ብሏል። (መክብብ 3:7) ስለዚህ ከላይ የጠቀስካቸውን የሚያሳስቡህን ነገሮች አመቺ ጊዜ መርጠህ ለወላጆችህ አንሳላቸው። በፍቺው ምክንያት ምን ያህል እንዳዘንክ ወይም ግራ እንደተጋባህ ንገራቸው። ምናልባት ስለተፈጠረው ነገር ሊያስረዱህ ይችሉ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ጭንቀትህ ቀለል እንዲልልህ ያደርጋል። ወላጆችህ አንተ በፈለግከው ጊዜ ሊረዱህ ካልቻሉ ወይም ፈቃደኛ ካልሆኑ ብስለት ላለው አንድ ጓደኛህ ስሜትህን አውጥተህ ልትነግረው ትችላለህ። እርግጥ እንዲህ ያለውን ሰው ቅድሚያውን ወስደህ ማናገር ይኖርብህ ይሆናል። ያም ቢሆን ስሜትህን ለሌላ ሰው ማካፈል መቻልህ በራሱ ጭንቀትህ ቀለል እንዲልልህ ሊያደርግ ይችላል።—ምሳሌ 17:17
መዝሙር 65:2) ‘እሱ ስለ አንተ ስለሚያስብ’ የልብህን አውጥተህ ንገረው።—1 ጴጥሮስ 5:7
ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው የሰማዩ አባትህ አንተን ለመስማት ምንጊዜም ፈቃደኛ ነው። (ማድረግ የሌለብህ ነገር
ቂም አትያዝ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ ራስ ወዳድ ናቸው። ስለ እኛ ስሜትም ሆነ ውሳኔያቸው ስለሚያስከትልብን ነገር ቆም ብለው አላሰቡም።” ዳንኤል እንዲህ የተሰማው መሆኑ ምንም አያስገርምም፤ ደግሞም የተናገረው ነገር ትክክል ሊሆን ይችላል። ይሁንና እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር። መልሶችህን በክፍት ቦታዎቹ ላይ ጻፍ።
ዳንኤል በንዴት መብከንከኑን ካልተወ ምን ሊያጋጥመው ይችላል? (ምሳሌ 29:22ን አንብብ።) ․․․․․
ዳንኤል ወላጆቹ ያደረሱበትን በደል ይቅር ማለት ሊከብደው ቢችልም እንኳ ይህን ማድረጉ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ኤፌሶን 4:31, 32ን አንብብ።)
በሮም 3:23 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ዳንኤል የወላጆቹን ጥፋት በጣም አጋንኖ እንዳይመለከት ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?
ራስህን የሚጎዳ አካሄድ ከመከተል ተቆጠብ። ዴኒ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ወላጆቼ ከተፋቱ በኋላ ደስታ የራቀኝ ከመሆኑም ሌላ በጭንቀት ተውጬ ነበር። የትምህርት ቤት ውጤቴ ማሽቆልቆል የጀመረ ሲሆን አንድ
ዓመት ደገምኩ። ከዚያ በኋላ ደግሞ . . . ክፍል ውስጥ የወጣለት አልምጥ ሆንኩ፤ እንዲሁም ካገኘሁት ሰው ጋር እደባደብ ጀመር።”ዴኒ ክፍል ውስጥ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ማሳየት የጀመረው ለምን ይመስልሃል? ․․․․․
ተደባዳቢ እንዲሆን ያደረገውስ ምን ሊሆን ይችላል? ․․․․․
መጥፎ አካሄድ በመከተል ወላጆችህን የመበቀል ስሜት ቢያድርብህ በገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘው መመሪያ አመለካከትህን ለማስተካከል ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? ․․․․․
ሁኔታዎች እያደር ይለወጡ ይሆን?
በሰውነትህ ላይ ጉዳት ቢደርስብህ ለምሳሌ እጅህ ቢሰበር ሙሉ በሙሉ ለመዳን ሳምንታት አልፎ ተርፎም ወራት ሊወስድብህ ይችላል። በስሜት ላይ ከሚደርስ ጉዳት ለማገገምም ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። አንዳንድ ባለሙያዎች፣ ፍቺ የሚያስከትለው የስሜት ቀውስ የሚያይለው እስከ ሦስት ዓመት ድረስ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ረጅም ጊዜ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል፤ ይሁንና እንደገና የተረጋጋ ሕይወት መምራት እንድትጀምር ብዙ መስተካከል ያለበት ነገር እንዳለ አትርሳ።
የቤተሰባችሁ የዕለት ተዕለት ሕይወት በፍቺው ምክንያት ተዘበራርቆ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ መደረግ ያለበት አንዱ ነገር ፕሮግራማችሁን እንደገና ማስተካከል ነው። ከዚህም ሌላ ወላጆችህ ከደረሰባቸው የስሜት ጉዳት ለማገገም ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ለአንተ ትኩረት መስጠት የሚጀምሩት ከዚያ በኋላ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን እንደ ቀድሞው ነገሮችን በፕሮግራም ማከናወን ስትጀምር ስሜትህም እየተረጋጋ ይመጣል።
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 25 ተመልከት
አባትህ ወይም እናትህ እንደገና ማግባታቸው አስጨንቆሃል? ይህን ስሜት መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
ቁልፍ ጥቅስ
“ለመፈወስም ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1, 3 የ1954 ትርጉም
ጠቃሚ ምክር
ወላጆችህ ተፋትተው ከሆነ ጥፋቱ የአንደኛው ወገን ወይም የሁለቱም ሊሆን ይችላል። ወላጆችህ የሠሩትን ስህተት ለይተህ ማወቅህ አንተም ወደፊት ትዳር ከመሠረትህ ተመሳሳይ ስህተት ከመሥራት እንድትቆጠብ ይረዳሃል።—ምሳሌ 27:12
ይህን ታውቅ ነበር?
ወላጆችህ ጥሩ ትዳር ያልነበራቸው መሆኑ አንተ ደስተኛ ትዳር እንዳትመሠርት ሊያደርግህ አይችልም።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
ስጋቴን ልነግረው የምፈልገው ሰው (ልታናግረው ያሰብከውን ብስለት ያለው ሰው ስም ጻፍ) ․․․․․
መጥፎ አካሄድ በመከተል ወላጆቼን የመበቀል ስሜት ሲያድርብኝ ስሜቴን ለመቆጣጠር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● ወላጆችህ ስለ ፍቺው ከአንተ ጋር መወያየት የሚከብዳቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
● ወላጆችህ የተፋቱት እርስ በርስ ስላልተግባቡ እንጂ በአንተ ምክንያት እንዳልሆነ ማስታወስህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እናቴ ጥላን ከሄደች በኋላ በጭንቀት ተውጬ በየቀኑ አለቅስ ነበር። ሆኖም አዘውትሬ የምጸልይ ከመሆኑም ሌላ ጊዜዬን የማሳልፈው ሌሎችን በመርዳት ነው፤ እንዲሁም በሳል ከሆኑ ጓደኞቼ ጋር ይበልጥ ተቀራረብኩ። ይሖዋ አምላክ በእነዚህ መንገዶች አማካኝነት ሁኔታውን መቋቋም እንድችል እንደረዳኝ ይሰማኛል።”—ናታሊ
[በገጽ 33 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እጅህ ቢሰበር ሙሉ በሙሉ እስክትድን ድረስ ሥቃይ እንደሚኖርህ ሁሉ የወላጆችህ ፍቺ ያስከተለብህ የስሜት ጉዳትም ለተወሰነ ጊዜ ያሠቃይህ ይሆናል፤ ውሎ አድሮ ግን መዳንህ አይቀርም