በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጽሞ መሳሳት እንደሌለብኝ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?

ፈጽሞ መሳሳት እንደሌለብኝ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 27

ፈጽሞ መሳሳት እንደሌለብኝ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?

በትምህርት ቤት ፈተና ካልደፈንክ በጣም ትበሳጫለህ?

□ አዎ

□ አይ

ጉዳዩ ከባድም ይሁን ቀላል እርማት ስለተሰጠህ ብቻ ምንም ነገር በተሳካ ሁኔታ ማከናወን እንደማትችል ይሰማሃል?

□ አዎ

□ አይ

ማንም ሰው አንተ እንደምትፈልገው እንደማይሆንልህ ስለሚሰማህ ጓደኛ ማግኘት ይቸግርሃል?

□ አዎ

□ አይ

ከላይ ከቀረቡት ጥያቄዎች ቢያንስ ለአንዱ ‘አዎ’ የሚል መልስ ከሰጠህ ፍጽምናን የመጠበቅ ችግር ይኖርብህ ይሆናል። ‘ታዲያ ነገሮችን አለምንም እንከን ለማከናወን መጣር ምን ችግር አለው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለነገሩ ምንም ችግር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “በሙያው ሥልጡን” የሆነን ሰው በማድነቅ ይናገራል። (ምሳሌ 22:29) ፍጽምናን የሚጠብቅ ሰው ግን ወደ ሌላኛው ጽንፍ ይሄዳል።

የ19 ዓመቱን ያሶንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ እንዲህ ይላል፦ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ልጨርስ አካባቢ፣ ሁሉንም ፈተናዎች ካልደፈንኩ ጎበዝ ተማሪ አይደለሁም ማለት ነው ብዬ ደመደምኩ። ፒያኖም የምጫወት ሲሆን የኮንሰርት ፒያኖ ተጫዋች ዓይነት ችሎታ ሊኖረኝ እንደሚገባ ይሰማኝ ነበር።”

አንድ ወጣት ነገሮችን አለምንም እንከን ለማከናወን መፈለጉ መንፈሳዊ ሕይወቱንም ሊነካበት ይችላል። ሁልጊዜ ለሌሎች አርዓያ እንደሆነ ተደርጎ የሚጠቀስ ወጣት ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል እንመልከት። በተወጠረ ገመድ ላይ እንደሚራመድ ስፖርተኛ የሰው ሁሉ ዓይን እሱ ላይ እንዳረፈና እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን በትኩረት እንደሚከታተሉት ይሰማው ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ወጣት አረጋዊ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች በጉባኤ ውስጥ በመኖራቸው ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ አንድ ወጣት በሁሉም ነገር ፍጹም ለመሆን መጣሩ በአምላክ አገልግሎት የሚያገኘውን ደስታ ሊያሳጣው ይችላል። ወጣቱ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመው እርዳታ ያስፈልገዋል። ይሁንና እርዳታ ቢጠይቅ ለእሱ ጥሩ ግምት ያላቸው ሰዎች እንዳያፍሩበት ስለሚፈራ ይህን ከማድረግ ወደኋላ ሊል ይችላል። እንዲያውም ‘እንደሚጠበቅብኝ ሆኜ መገኘት የማልችል ከሆነ እስከነጭራሹ ቢቀርብኝስ?’ ብሎ በማሰብ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ለመተው ይፈተን ይሆናል።

ፍጽምና የመጠበቅን ዝንባሌ መዋጋት

ፍጽምናን የሚጠብቁ ሰዎች፣ ፈጽሞ ስህተት መሠራት እንደሌለበት የሚሰማቸው ሲሆን እንዲህ ያለው ከእውነታ የራቀ ግብ ላይ ለመድረስ መከራቸውን ያያሉ። ይሁንና እንዲህ ያለው አመለካከት ፈጽሞ የተሳሳተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ሮም 3:23) በመሆኑም ማንኛችንም ብንሆን ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ፍጹም በሆነ መንገድ ማከናወን አንችልም። እንዲያውም ነገሮችን ፍጹም በሆነ መንገድ ማከናወን እንደምትችል ማሰብ እንደ ወፍ ክንፍ አውጥተህ መብረር እንደምትችል የማሰብ ያህል ዘበት ነው። ምንም ያህል ከልብህ ብትመኝ መብረር እንደማትችል የታወቀ ነው!

ፍጽምናን የመጠበቅ ዝንባሌ ሕይወትህን እንዳይቆጣጠረው ምን ማድረግ ትችላለህ? እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር፦

“ስኬትን” የምትለካበትን ሚዛን አስተካክል። ከሁሉ ልቀህ ለመገኘት ስትፍጨረጨር ራስህን እየጎዳህ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው ጥረት ‘ነፋስን እንደ መከተል’ እንደሆነ ይናገራል። (መክብብ 4:4) እንደ እውነቱ ከሆነ “ከሁሉ ልቀው” መገኘት የሚችሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። አንድ ሰው ልቆ መገኘት ቢችልም እንኳ በአብዛኛው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ከእሱም የሚልቅ መምጣቱ አይቀርም። ስኬት ሲባል የአንተ አቅም የሚፈቅድልህን ያህል ማድረግ ማለት እንጂ ሌላውን ሰው በልጦ መገኘት ማለት አይደለም።​—ገላትያ 6:4

ምክንያታዊ ሁን። ከራስህ የምትጠብቀው ነገር ያሉህን ችሎታዎችም ሆነ የአቅም ገደቦች ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። ከራስህ የምትጠብቀው ነገር በጣም የተጋነነ ከሆነ ይህ ልክህን እንደማታውቅ ምናልባትም ለራስህ ከመጠን ያለፈ ግምት እንደምትሰጥ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት” በማለት ጥሩ ምክር ሰጥቷል። (ሮም 12:3) ስለዚህ ምክንያታዊ ሁን! ከራስህ በምትጠብቀው ነገር ላይ ማስተካከያ አድርግ። የአቅምህን ያህል ለመሥራት እንጂ ፍጹም ለመሆን አትሞክር።

ነገሮችን ቀለል አድርገህ ተመልከት! በደንብ የማትችለውን ነገር ለማከናወን ለምሳሌ የሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ሞክር። ይህን ስታደርግ ብዙ ስህተት መሥራትህ አይቀርም። ያም ቢሆን ሁኔታውን ከሌላ አቅጣጫ ለመመልከት ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ “ለመሣቅም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:4) ስለዚህ ነገሮችን ቀለል አድርገህ ለመመልከት ለምን አትሞክርም? እንዲህ ማድረግህ አንድ ነገር ስትማር መሳሳት ያለ ነገር መሆኑን እንድትገነዘብ ይረዳሃል። ልትሳሳት እንደምትችል እየተሰማህ አንድን ሥራ መጀመር ሊከብድህ እንደሚችል ግልጽ ነው። ሆኖም አሉታዊ የሆኑ ሐሳቦችን ከአእምሮህ ለማውጣት ብሎም እንከን የመፈላለግ አዝማሚያን ለማስወገድ ብርቱ ጥረት አድርግ።

ይሖዋ በታማኝነት እንድናገለግለው እንጂ ፍጽምናን እንደማይጠብቅብን ፈጽሞ አትዘንጋ። (1 ቆሮንቶስ 4:2) ታማኝ ለመሆን ጥረት የምታደርግ ከሆነ ፍጹም ባትሆንም እንኳ በማንነትህ ልትኮራ ትችላለህ።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

በዛሬው ጊዜ ግብረ ሰዶም ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ ነው። ከዚህ ድርጊት መራቅ የምትችለው እንዴት ነው? እንደ አንተ ዓይነት ፆታ ላላቸው ሰዎች የፍቅር ስሜት ቢኖርህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።”​—መክብብ 7:20

ጠቃሚ ምክር

እንከን በማይወጣለት መንገድ ልትሠራው እንደማትችል ስለተሰማህ ዛሬ ነገ እያልክ ያቆየኸው ሥራ አለ? ካለ ሥራውን የምታጠናቅቅበትን ቀን ወስን።

ይህን ታውቅ ነበር?

ይሖዋ ፍጹም አምላክ ነው፤ ሆኖም ፍጽምና ከጎደላቸው የሰው ልጆች ጋር ባለው ግንኙነት ፍጽምናን አይጠብቅም። ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊና ሚዛናዊ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

በራሴ ላይ ስህተት የመፈላለግ አዝማሚያ ካለኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

የሌሎችን ስህተት የመለቃቀም አዝማሚያ ካለኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከአቅምህ በላይ የሆኑ ግቦችን የማውጣት አዝማሚያ የሚታይብህ በየትኛው የሕይወትህ ዘርፍ ነው?

● ይሖዋ አምላክ ከአገልጋዮቹ ፍጽምናን እንደማይጠብቅ በግልጽ የሚያሳዩት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው?

● ፍጽምናን የምትጠብቅ ከሆነ ሰዎች ከአንተ የሚርቁት ለምን ይመስልሃል?

● ከአሁን በኋላ ስህተት በምትሠራበት ጊዜ ምን ለማድረግ አስበሃል?

[በገጽ 226 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግና ፍጽምናን መጠበቅ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ ልዩነታቸው ምክንያታዊ መሆንና አለመሆን ነው።”​—ሜገን

[በገጽ 228 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ፍጽምናን መጠበቅ እና ጓደኝነት

አንተ እንደምትፈልገው ስላልሆኑልህ ብቻ የራቅሃቸው ሰዎች አሉ? አሊያም ደግሞ ከሌሎች የምትጠብቀው ነገር የማይደረስበት በመሆኑ ከአንተ እንዲርቁ ያደረግሃቸው ጥሩ ሰዎች ይኖሩ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “እጅግ ጻድቅ፣ እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ ራስህን ለምን ታጠፋለህ?” የሚል ምክር ይሰጠናል። (መክብብ 7:16) ፍጽምናን የሚጠብቅ ሰው በራሱ ላይ ጥፋት ሊያመጣ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ ጓደኞቹ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ሰዎች ከእሱ እንዲርቁ ማድረጉ ነው። አምበር የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ማንም ሰው ቢሆን የዝቅተኝነት ስሜት እንዲያድርበት ከሚያደርገው ሰው ጋር መሆን አይፈልግም፤ ፍጽምናን የሚጠብቁ ሰዎች በማይረባ ምክንያት ጥሩ ጓደኞቻቸውን ሲያጡ ተመልክቻለሁ።”

[በገጽ 229 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍጹም ለመሆን መጣር ለመብረር የመሞከርን ያህል ዘበት ነው