በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድንግልናዬን መጠበቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?

ድንግልናዬን መጠበቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 5

ድንግልናዬን መጠበቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?

“ከየአቅጣጫው የሚመጣው ተጽዕኖ ‘የፆታ ግንኙነት ምን እንደሚመስል ሞክሬ ባየው’ ብዬ እንዳስብ ያደርገኛል።”​—ኬሊ

“የፆታ ግንኙነት ሳልፈጽም እስካሁን መቆየቴ ያሳፍረኛል።”​—ጆርደን

“ዘንድሮም ድንግል ነሽ?” * እንዲህ ያለው ጥያቄ ሽምቅቅ እንድትዪ ያደርግሽ ይሆናል። በብዙ ቦታዎች አንዲት ወጣት ድንግል ከሆነች ችግር እንዳለባት ተደርጋ ትታያለች። ከዚህ አንጻር በርካታ ወጣቶች ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያሉ የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ መሆኑ ምንም አያስገርምም!

ፍላጎታችሁና እኩዮቻችሁ የሚያሳድሩባችሁ ተጽዕኖ

ክርስቲያን ከሆንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከዝሙት እንድትርቂ’ የሚሰጠውን ማሳሰቢያ ታውቂያለሽ። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ያም ሆኖ የፆታ ስሜትሽን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆንብሽ ይችላል። ፖል የተባለ ወጣት እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ሐሳቦች ያለ ምንም ምክንያት ወይም ሳልፈልግ ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ።” አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ስሜት በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው።

ይሁንና ድንግል በመሆንሽ ጓደኞችሽ ነጋ ጠባ የሚያሾፉብሽና የሚነዘንዙሽ ከሆነ ሁኔታው ከባድ ነው። ለምሳሌ፣ አንድን ወጣት እኩዮቹ ‘የፆታ ግንኙነት የማትፈጽም ከሆነማ ወንድ ነኝ አትበል’ የሚሉት ቢሆንስ? አሊያም ደግሞ አንዲትን ወጣት ጓደኞቿ ‘የፆታ ግንኙነት ካልፈጸምሽ ምኑን ሴት ሆንሽው’ ቢሏትስ? ሔለን እንዲህ ብላለች፦ “እኩዮቻችሁ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስደስትና ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነገር እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህም ከዚያም ጋር ካልተኛችሁ ከሰው የተለያችሁ እንደሆናችሁ አድርገው ይቆጥሯችኋል።”

ይሁንና ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ጋር በተያያዘ እኩዮችሽ የሚደብቁሽ ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የፆታ ግንኙነት የፈጸመች ማሪያ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ድርጊቱን ከፈጸምኩ በኋላ በኀፍረትና በጥፋተኝነት ስሜት ተዋጥኩ። ራሴን ጠላሁት፤ የወንድ ጓደኛዬንም ጨርሶ ላየው አልፈለግኩም።” አብዛኞቹ ወጣቶች ባያውቁትም እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ብዙውን ጊዜ የስሜት ሥቃይ የሚያስከትል ከመሆኑም ሌላ አስከፊ መዘዞች አሉት!

ያም ሆኖ ሻንዳ የተባለች ወጣት “አምላክ በጋብቻ ውስጥ ካልሆነ በቀር የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደሌለባቸው እያወቀ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንዲኖራቸው ለምን አደረገ?” የሚል ጥያቄ አንስታለች። ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፦

ከፆታ ፍላጎት ሌላ ኃይለኛ ስሜት አድሮብሽ አያውቅም? እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ አምላክ የፈጠረሽ የተለያየ ዓይነት ፍላጎትና ስሜት እንዲኖርሽ አድርጎ ነው።

እንዲህ ያሉ ስሜቶች በውስጥሽ በተቀሰቀሱ ቁጥር ልታስተናግጃቸው ይገባል ማለት ነው? በፍጹም። ምክንያቱም አምላክ ሲፈጥርሽ ስሜትሽን የመቆጣጠር ችሎታም ሰጥቶሻል።

ታዲያ ነጥቡ ምንድን ነው? አንዳንድ ስሜቶች በውስጥሽ እንዳይቀሰቀሱ ማድረግ አትችዪ ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህን ፍላጎቶችሽን ከመፈጸም ራስሽን መግታት ትችያለሽ። እውነቱን ለመናገር፣ የፆታ ስሜትሽ በተቀሰቀሰ ቁጥር ፍላጎትሽን ለማርካት መነሳት አንድ ሰው ባናደደሽ ቁጥር ከመማታት ባልተናነሰ ስህተትና ቂልነት ነው።

አምላክ የመራቢያ አካላችንን የሰጠን አላግባብ እንድንጠቀምበት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ዕቃ እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት [ሊያውቅ ይገባል]” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 4:4) መጽሐፍ ቅዱስ “ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው” ይላል። በተመሳሳይም የፆታ ፍላጎትን ለማርካትም ሆነ ይህን ከማድረግ ለመቆጠብ ጊዜ አለው። (መክብብ 3:1-8) በዚያም ሆነ በዚህ ስሜትሽን መቆጣጠር የምትችይው አንቺ ነሽ!

ይሁን እንጂ አንዲት ወጣት በፌዝ መልክ “አሁንም ድንግል ነኝ እንዳትይኝ ብቻ” ብትልሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በዚህ ጊዜ መደናገጥ የለብሽም። ዓላማዋ በአንቺ ላይ ማሾፍ ከሆነ “አዎ፣ አሁንም ድንግል ነኝ። ደግሞም ድንግል በመሆኔ ቅንጣት ታክል አላፍርም!” ብለሽ ልትመልሺላት ትችያለሽ። አሊያም “ይህ የግል ጉዳዬ ስለሆነ አንቺን አይመለከትሽም” ማለት ትችያለሽ። * (ምሳሌ 26:4፤ ቆላስይስ 4:6) በሌላ በኩል ግን እንዲህ ላለችሽ ወጣት ስለ አቋምሽ የበለጠ ልታስረጃት እንደሚገባ ይሰማሽ ይሆናል። ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋምሽን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮች ልትነግሪያት ትችያለሽ።

አንዲት ወጣት በፌዝ መልክ “አሁንም ድንግል ነኝ እንዳትይኝ ብቻ” ብትልሽ ሌላስ ምን ልትያት ትችያለሽ? መልስሽን ከታች አስፍሪው።

․․․․․

ውድ ስጦታ

ሰዎች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ አምላክ ምን ይሰማዋል? ለአንድ ጓደኛሽ ስጦታ ገዝተሻል እንበል። ይሁንና ጓደኛሽ ስጦታውን ገና ሳትሰጫት ለማየት ጓጉታ ብትከፍተው ምን ይሰማሻል? በሁኔታው አትበሳጪም? አንቺም ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ብትፈጽሚ አምላክ ምን እንደሚሰማው ልትገምቺ ትችያለሽ። አምላክ ከሰጠሽ ስጦታ ማለትም ከፆታ ግንኙነት ደስታ ለማግኘት እስክታገቢ ድረስ እንድትቆዪ ይፈልጋል።​—ዘፍጥረት 1:28

‘ታዲያ የፆታ ስሜቴ እንዳያስቸግረኝ ምን ባደርግ ይሻለኛል?’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። በአጭር አነጋገር፣ ስሜትሽን መቆጣጠር መማር ይኖርብሻል። ደግሞም እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል ብቃት አለሽ! ይሖዋ እንዲረዳሽ ጸልዪ። የአምላክ መንፈስ ራስን የመግዛት ባሕርይ ይበልጥ እንድታዳብሪ ሊረዳሽ ይችላል። (ገላትያ 5:22, 23) ይሖዋ “በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም” የሚለውን ጥቅስ አስታውሺ። (መዝሙር 84:11) ጎርደን የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ማሰብ ከጀመርኩ እንዲህ ያለው ድርጊት በመንፈሳዊነቴ ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት አሰላስላለሁ፤ ይህም ኃጢአት በመፈጸም የማገኘው ደስታ የፈለገ ቢሆን ከይሖዋ ጋር ካለኝ ዝምድና ሊበልጥብኝ እንደማይችል እንድገነዘብ ያደርገኛል።”

ድንግል መሆንሽ ችግር እንዳለብሽ የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ክብርን ዝቅ የሚያደርገውና የሚያሳፍረው ብሎም ጎጂ የሚሆነው የፆታ ብልግና መፈጸም ነው። በመሆኑም ዓለም የሚያናፍሰው ፕሮፓጋንዳ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖርሽ ስህተት እንደሆነ እንዲሰማሽ አያድርግሽ። ድንግልናሽን ጠብቀሽ መቆየትሽ ስሜታዊ ጉዳት እንዳይደርስብሽ የሚረዳሽ ከመሆኑም ሌላ ጤንነትሽን ለመጠበቅ ያስችልሻል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለሽ ዝምድና እንዳይበላሽ ይረዳሻል።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 24 ተመልከት

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.15 ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሄሮድስ ጥያቄ ሲያቀርብለት ዝምታን እንደመረጠ መገለጹ ትኩረት የሚስብ ነው። (ሉቃስ 23:8, 9) ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ብዙውን ጊዜ የተሻለው ነገር መልስ አለመስጠት ነው።

ቁልፍ ጥቅስ

“[አንድ ሰው] ድንግልናውን ጠብቆ ለመኖር በልቡ ከወሰነ . . . መልካም ያደርጋል።”​—1 ቆሮንቶስ 7:37

ጠቃሚ ምክር

አንዳንድ ወጣቶች እንደ አንቺ ዓይነት እምነት እንዳላቸው ቢናገሩም እንኳ ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም ከሌላቸው ከእነሱ ጋር ጓደኝነት ላለመመሥረት ተጠንቀቂ።

ይህን ታውቅ ነበር?

ልቅ የሆነ የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ልማድ ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ካገቡም በኋላ ይህ አመላቸው አይለቃቸውም። በሌላ በኩል ደግሞ ከማግባታቸው በፊት ለአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ታማኝ የነበሩ ሰዎች ካገቡም በኋላ ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ የመሆናቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

እስከማገባ ድረስ ድንግልናዬን ጠብቄ ለመቆየት እንድችል እንዲህ ማድረግ ያስፈልገኛል፦ ․․․․․

ጓደኞቼ በአቋሜ እንዳልጸና የሚያስቸግሩኝ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

አንዳንዶች፣ ድንግል የሆኑ ወጣቶች ላይ የሚያሾፉባቸው ለምንድን ነው?

ድንግልናን ጠብቆ መቆየት አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

እስኪያገቡ ድረስ ድንግል ሆኖ መቆየት ምን ጥቅሞች አሉት?

ድንግልናን ጠብቆ መቆየት ያለውን ጥቅም ለታናናሾቻችሁ ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 51 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ሴሰኛ ወይም ርኩስ የሆነ ማንኛውም ሰው በአምላክ መንግሥት ምንም ውርሻ እንደሌለው’ ሁልጊዜ ማስታወሴ የፆታ ብልግና እንድፈጽም የሚያጋጥመኝን ፈተና ለመቋቋም አስችሎኛል።” (ኤፌሶን 5:5)​—ሊዲያ

[በገጽ 49 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመልመጃ ሣጥን

በእርግጥ ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል?

አብዛኛውን ጊዜ እኩዮችሽም ሆኑ በብዙኃኑ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ አድበስብሰው ያልፉታል። እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ሁኔታዎች እንመልከት። እነዚህ ወጣቶች በእርግጥ ምን ያጋጠማቸው ይመስልሻል?

● አብሮሽ የሚማር አንድ ወጣት ከበርካታ ሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት እንደፈጸመ በጉራ ይናገራል። ሁኔታው በጣም አስደሳች እንደሆነና ማናቸውም ምንም ችግር እንዳላጋጠማቸው ይገልጻል። ይሁንና እሱም ሆነ ሴቶቹ ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ ያጋጠማቸው ነገር በእርግጥ እንደጠበቁት የሚሆን ይመስልሻል? ․․․․․

● አንድ ፊልም እየተመለከትሽ ነው እንበል፤ ፊልሙ የሚደመደመው ሁለት የሚዋደዱ ወጣቶች ገና ሳይጋቡ የፆታ ግንኙነት ሲፈጽሙ በማሳየት ነው። በገሃዱ ዓለም ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ ምን የሚያጋጥማቸው ይመስልሻል? ․․․․․

● አንድ ቆንጆ ወጣት የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ጠየቀሽ። ድርጊቱን ብትፈጽሙ ማንም እንደማያውቅባችሁ ነግሮሻል። ከልጁ ጋር የፆታ ግንኙነት ብትፈጽሚና ሁኔታውን ለመደበቅ ብትሞክሪ ከዚያ በኋላ የሚያጋጥምሽ ነገር በእርግጥ እንደጠበቅሽው የሚሆን ይመስልሻል? ․․․․․

[በገጽ 54 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አንድ ስጦታ ሳይሰጥህ አስቀድመህ እንደመክፈት ነው