በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትምህርት ቤት ራሴን ከጥቃት መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

በትምህርት ቤት ራሴን ከጥቃት መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 14

በትምህርት ቤት ራሴን ከጥቃት መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

የሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች እውነት ናቸው ወይስ ሐሰት?

1. ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት አካላዊ ጥቃት በመሰንዘር ብቻ ነው።

□ እውነት

□ ሐሰት

2. ፆታዊ ትንኮሳ ሲባል በቃላት መተናኮልን አይጨምርም።

□ እውነት

□ ሐሰት

3. ሴቶች ልጆችም ጉልበተኞች ሊሆኑ ወይም ፆታዊ ትንኮሳ ሊፈጽሙ ይችላሉ።

□ እውነት

□ ሐሰት

4. ጉልበተኞች ጥቃት የሚያደርሱባችሁ ወይም ፆታዊ ትንኮሳ የሚፈጸምባችሁ ከሆነ ምንም ማድረግ አትችሉም።

□ እውነት

□ ሐሰት

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በትምህርት ቤት ጉልበተኞች ጥቃት ስለሚያደርሱባቸው ፍርሃት የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ክፍል ሆኗል። ራያን የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በአውቶቡስ ውስጥ ጉልበተኛ የሆኑ ልጆች በቃላት ከመተንኮስ አልፈው እየጎነታተሉ ስለሚያሠቃዩኝ የ15 ደቂቃው መንገድ የሰዓታት ያህል ይረዝምብኛል።” ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ፆታዊ ትንኮሳ ያጋጥማቸዋል። “በብዙዎች ዘንድ በጣም የሚወደድ አንድ ልጅ ኮሪዶር ላይ ሲያገኘኝ አስቆመኝ፤ ከዚያም ይደባብሰኝ ጀመር” በማለት አኒታ የተባለች ወጣት ተናግራለች። አክላም “እጁን እንዲሰበስብ በትሕትና ብነግረውም ሊሰማኝ አልቻለም። እየተግደረደርኩ መስሎት ነበር” ብላለች።

አንዳንድ ወጣቶች ሌላው ቀርቶ በኢንተርኔት አማካኝነትም እንኳ አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆች መጥፎ መልእክቶችን በመላክ ያስቸግሯቸዋል። አንተስ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ያስቸግሩሃል? ከሆነ ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም ምን ማድረግ ትችላለህ? ልታደርጋቸው የምትችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ! እስቲ መጀመሪያ ግን በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የቀረቡትን ዓረፍተ ነገሮች በመመርመር እውነታውን ለማወቅ እንሞክር።

1. ሐሰት። ሌሎችን የሚያስቸግሩ አብዛኞቹ ወጣቶች ጉልበታቸው ያለው ከጡንቻቸው ይልቅ ምላሳቸው ላይ ነው። ሌሎችን ለማስፈራራት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል ዛቻ፣ ስድብ፣ አሽሙርና ፌዝ ይገኙበታል።

2. ሐሰት። የብልግና ቀልድ መናገር፣ አንድን ሰው በፍትወት ስሜት መመልከት ወይም የፆታ ምኞት በሚንጸባረቅበት የድምፅ ቃና “ማድነቅ” እንኳ ከፆታዊ ትንኮሳ ሊመደብ ይችላል።

3. እውነት። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ጉልበተኞች ሊሆኑ ወይም ፆታዊ ትንኮሳ ሊፈጽሙ ይችላሉ።

4. ሐሰት። ልጆቹ እንዳያስቸግሩህ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ቡጢ ሳትሰነዝር ጉልበተኞችን ማሸነፍ የምትችልበት መንገድ

አንዳንድ ወጣቶች ምን እንደምታደርግ ለማየት ሲሉ ሆን ብለው ነገር ይፈልጉህ ይሆናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል” በማለት ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል። (መክብብ 7:9) ‘በክፉ ፋንታ ክፉ መመለስ’ በእሳት ላይ ነዳጅ እንደ ማርከፍከፍ ነው፤ ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። (ሮም 12:17) ታዲያ አንድን ጉልበተኛ ቡጢ ሳትሰነዝር ማሸነፍ የምትችለው እንዴት ነው?

ነገሩን ቀለል አድርገህ እየው። ልጆቹ የሚያሾፉብህ መሳቂያ ሊያደርጉህ አስበው ከሆነ በነገሩ ቅር ከመሰኘት ይልቅ ስቀህ ለማለፍ ሞክር። ኤርምያስ የተባለ ወጣት “ለማናደድ ተብለው የሚሰነዘሩ አስተያየቶችን ቀለል አድርጎ መመልከቱ የተሻለ የሚሆንበት ጊዜ አለ” ብሏል። የሚያሾፍብህ ሰው ንግግሩን ከቁም ነገር እንደማትቆጥረው ሲመለከት አንተን ማስቸገሩን ሊያቆም ይችላል።

በለዘበ መንገድ መልስ ስጥ። መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” ይላል። (ምሳሌ 15:1) ጉልበተኛ የሆኑ ልጆች ደግነት የተሞላበት ምላሽ ስለማይጠብቁ እንዲህ ማድረግህ ሁኔታው እንዳይጋጋል ሊያደርገው ይችላል። ሌሎች በሚያጠቁህ ጊዜ በእርጋታ ምላሽ ለመስጠት ራስህን መግዛት እንደሚያስፈልግህ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን እንዲህ ማድረጉ ምንጊዜም የተሻለ ነው። ምሳሌ 29:11 “ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል” ይላል። በለዘበ መንገድ መልስ መስጠት የጥንካሬ ምልክት ነው። እንዲህ ያለው ሰው በቀላሉ ሚዛኑን አይስትም፤ በሌላ በኩል ግን ጉልበተኛ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በራሳቸው ስለማይተማመኑ ያልተረጋጉና ብስጩዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ . . . ይበልጣል” ማለቱ የተገባ ነው።​—ምሳሌ 16:32

ጉዳት እንዳይደርስብህ ራስህን ጠብቅ። ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ የሚሆን ከመሰለህ ማምለጫ መንገድ መፈለግ ይኖርብህ ይሆናል። ምሳሌ 17:14 “ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” ይላል። ስለዚህ ጠብ መቀስቀሱ እንደማይቀር ከተሰማህ ተረጋግተህ በመራመድ አሊያም በመሮጥ ከአካባቢው ዘወር ማለት ይኖርብሃል። ማምለጥ የማትችል ከሆነ ግን የተሻለ ሆኖ ባገኘኸው መንገድ የሚሰነዘርብህን ጥቃት መመከት ያስፈልግህ ይሆናል።

ለሌሎች ተናገር። ወላጆችህ ስላጋጠመህ ነገር የማወቅ መብት አላቸው። ከዚህም በላይ ጠቃሚ ምክር ሊሰጡህ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ለአስተማሪዎችህ ወይም በትምህርት ቤት ለሚገኙት አማካሪዎች ስለ ሁኔታው እንድትናገር ሐሳብ ያቀርቡልህ ይሆናል። ወላጆችህና አስተማሪዎችህ ተጨማሪ ችግር ውስጥ እንድትገባ በማያደርግ መንገድ ሁኔታውን በዘዴ ሊፈቱት እንደሚችሉ እርግጠኛ ሁን።

ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ ምንድን ነው? ጉልበተኛ የሆነ ልጅ እሱ እንዳሰበው ካልሆንክለት ሊያሸንፍህ አይችልም። በመሆኑም እሱ በቁጣ ገንፍሎ ሲናገርህ አንተም ተመሳሳይ ምላሽ በመስጠት እሳቱን ይበልጥ እንዳታራግበው ተጠንቀቅ። ከዚህ ይልቅ ከላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን ለማርገብ ሞክር።

ፆታዊ ትንኮሳን መከላከል

ፆታዊ ትንኮሳ እያጋጠመሽ ከሆነ በነገሩ ብትበሳጪ ምንም አያስገርምም! እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ‘ችግሩን ለመከላከል ምን ማድረግ ትችያለሽ?’ የሚለው ነው። ልታደርጊያቸው የምትችያቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ከዚህ በታች አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል። *

ትንኮሳውን ጠንከር ባለ መንገድ ተቃወሚ። ፆታዊ ትንኮሳ የሚያደርገውን ሰው ቁርጥ ባለ መንገድ ከመቃወም ይልቅ የተለሳለሰ መልስ የምትሰጪው ከሆነ እየተግደረደርሽ እንደሆነ አሊያም ሐሳብሽን ልትቀይሪ እንደምትችዪ አድርጎ ሊያስብ ይችላል። ስለዚህ መልስሽ አይሆንም ከሆነ አይሆንም ይሁን። (ማቴዎስ 5:37) ሁኔታው አሳፍሮሽ ቢሆንም እንኳ የምትሽኮረመሚ ወይም የምትቅለሰለሺ ከሆነ ግለሰቡ በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳሽ ልታደርጊ ትችያለሽ። ግልጽና ቆራጥ ሁኚ። ከሁሉ የበለጠው መከላከያሽ ይህ ነው!

የሚያሳፍረውን ነገር አድርጊ። አኒታ የሚያስቸግራትን ልጅ ለማስቆም ያደረገችውን ስትገልጽ “ድምፄን ከፍ አድርጌ እጁን እንዲሰበስብ በመንገር በጓደኞቹ ፊት አሳፈርኩት!” ብላለች። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? “ጓደኞቹ በሙሉ ሳቁበት። ልጁ ለጊዜው ቅር ቢለውም ከጥቂት ቀናት በኋላ ላደረገው ነገር ይቅርታ ጠየቀኝ፤ እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ሌላ ልጅ ሲያስቸግረኝ ተከላክሎልኛል።”

የምትነግሪውን አልሰማ ካለ ትተሽው ሂጂ። አንዳንዴም መሮጥ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ማምለጥ የማትችዪ ከሆነ ግን ጥቃት እንዳይደርስብሽ የመከላከል መብት አለሽ። (ዘዳግም 22:25-27) አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ልጅ ሊይዘኝ ሲሞክር ባለ በሌለ ኃይሌ መታሁትና ሮጬ አመለጥኩ!”

ለአንድ ሰው ተናገሪ። የ16 ዓመቷ ኤደን “በመጨረሻ እንዲህ ማድረግ ግድ ሆነብኝ” ብላለች። “ጥሩ ልጅ እንደሆነ አስበው የነበረ አንድ ወጣት አላስቆም አላስቀምጥ ሲለኝ ስለ ጉዳዩ ወላጆቼን አማከርኳቸው። እንዲተወኝ አጥብቄ ብነግረውም ልጁ ጭራሽ እየባሰበት መጣ፤ ጨዋታ የያዝን ይመስል ይበልጥ ፉክክር ውስጥ ገባ።” የኤደን ወላጆች ችግሩን ለመወጣት የሚያስችል ጠቃሚ ምክር ሰጧት። የአንቺም ወላጆች ሊረዱሽ እንደሚችሉ እርግጠኛ ሁኚ።

ጉልበተኞች የሚያደርሱትን ችግር መቋቋም ወይም ፆታዊ ትንኮሳን መከላከል ቀላል ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ምንጊዜም ልታስታውሱት የሚገባ ነገር አለ፦ ክርስቲያን ወጣቶች ጉልበተኞች ሲያስቸግሯቸው ምንም ማድረግ አይችሉም ማለት አይደለም፤ ፆታዊ ትንኮሳ ሲያጋጥማቸውም ሁኔታውን ለማስቆም እርምጃ ሳይወስዱ ችለው መኖር ወይም እጅ መስጠት አይኖርባቸውም። ከላይ የቀረቡትን ነጥቦች ተግባራዊ በማድረግ እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች መቋቋም ትችላላችሁ።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 18 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ከፍተኛ ግፊት ከሚያሳድሩብህና ልትቋቋማቸው ከሚገቡህ ነገሮች አንዱ የእኩዮች ተጽዕኖ ነው። እንዲህ ያለውን ግፊት በልበ ሙሉነት መቋቋም የምትችለው እንዴት እንደሆነ መማር ያስፈልግሃል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.30 የቀረቡት ሐሳቦች ለወንዶችም ሊሠሩ ይችላሉ።

ቁልፍ ጥቅስ

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።”​—ሮም 12:18

ጠቃሚ ምክር

ጉልበተኞች ካስቸገሩህ ደፋር ሁን፤ ሆኖም በቁጣ እንዳትገነፍል ተጠንቀቅ። ጉልበተኛው እንዲተውህ ቁርጥ ባለ መንገድ ንገረው። በተረጋጋ ሁኔታ አካባቢውን ለቀህ ሂድ። ጉልበተኛው ማስቸገሩን ካላቆመ ጉዳዩን ለሌሎች ተናገር።

ይህን ታውቅ ነበር?

አለባበስህ ለጥቃት ሊያጋልጥህ ይችላል። የወሮበሎች ቡድን አባል የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው የቡድናችን አባል ሳይሆን እንደ እኛ ከለበሰ ብዙውን ጊዜ ዓይን ውስጥ ይገባል። ወይ ከእኛ ጋር መቀላቀል አለበት አሊያም መደብደቡ አይቀርም።”

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አንድ ሰው ቢሰድበኝ ወይም ሊያበሳጨኝ ቢሞክር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ራሴን ችግር ውስጥ ላለመጨመር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በራስ የመተማመንና የመረጋጋት ስሜት ማዳበርህ ጉልበተኞች ሊያደርሱብህ የሚችሉትን ችግር ለመቀነስ የሚረዳህ እንዴት ነው?

● ፆታዊ ትንኮሳ ቢያጋጥምሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? (ሊያጋጥሙሽ የሚችሉ የተለመዱ ሁኔታዎችንና ልትሰጪ የምትችዪውን መልስ አስቢ።)

● ፆታዊ ትንኮሳን አቅልለሽ ልትመለከቺው የማይገባው ለምንድን ነው?

[በገጽ 123 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጠብ ሊጫር እንደሆነ ከተሰማህ በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት በመቆጠብ ወደ ቤትህ ሂድ። አንዳንዶች ወሬ ለማየት ብለው በአካባቢው ይቆያሉ፤ ይህም ችግር ውስጥ ያስገባቸዋል።”​—ሃይሮ

[በገጽ 125 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ፆታዊ ትንኮሳን መከላከል የሚቻልበት መንገድ

አትሽኮርመሚ። የምትሽኮረመሚ ከሆነ ለፆታዊ ትንኮሳ ራስሽን ታጋልጫለሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?” ይላል። (ምሳሌ 6:27) መሽኮርመም በእሳት የመጫወት ያህል አደገኛ ነው።

አብረሻቸው የምትሆኛቸውን ሰዎች ምረጪ። ‘ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ’ እንደሚባለው ሰዎች፣ አብረሻቸው የምትውያቸውን ወጣቶች በመመልከት በሥነ ምግባር ረገድ ያለሽ አቋም ከእነሱ የተለየ እንዳልሆነ ሊያስቡ ይችላሉ። ካርላ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች የሚሏቸውን በደስታ ከሚቀበሉ ወይም ትኩረት ማግኘት ከሚፈልጉ ልጆች ጋር አብራችሁ የምትሆኑ ከሆነ እናንተም የፆታዊ ትንኮሳ ዒላማ ትሆናላችሁ።”​—1 ቆሮንቶስ 15:33

ስለ አለባበስሽ በሚገባ አስቢ። አለባበስሽ ልከኛ ካልሆነ የተቃራኒ ፆታን ትኩረት ለመሳብ እንደምትፈልጊ በግልጽ ይጠቁማል፤ ደግሞም ትኩረት መሳብሽ የማይቀር ነው።​—ገላትያ 6:7

ክርስቲያን መሆንሽን አትደብቂ። ክርስቲያን መሆንሽን የምትደብቂ ከሆነ ሰዎች በክርስቲያናዊ መሥፈርቶች እንደምትመሪ አድርገው እንዲያዩሽ መጠበቅ የለብሽም።​—ማቴዎስ 5:15, 16

[በገጽ 124 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጉልበተኞች ሲያሾፉብህ በቁጣ መገንፈል በእሳት ላይ ነዳጅ እንደ መጨመር ነው

[በገጽ 127 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚያስቸግርሽ ልጅ ጫፍሽን እንዳይነካሽ ንገሪው!