አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች—ሕዝቅያስ
አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች—ሕዝቅያስ
ሕዝቅያስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ውሳኔ የሚያደርግበት ወቅት ላይ ደርሷል። ገና በ25 ዓመቱ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። ምን ዓይነት ንጉሥ ይወጣው ይሆን? አባቱ ንጉሥ አካዝ የተወውን መጥፎ ምሳሌ ይከተል ይሆን? አካዝ ከሃዲ የነበረ ሲሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ከክፉ ድርጊቱ አልተመለሰም። አካዝ ጣዖት አምልኮን በማስፋፋት ብቻ ሳይወሰን ከሕዝቅያስ ወንድሞች ቢያንስ አንዱን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 28:1-4) ሕዝቅያስ ግን የአባቱን የግብዝነት አካሄድ በማየት ከይሖዋ አምልኮ አልራቀም፤ ወይም ደግሞ የአባቱን የተሳሳተ አካሄድ ለመከተል አልተነሳሳም። ከዚህ በተቃራኒ ሕዝቅያስ ‘ከይሖዋ ጋር ተጣብቋል።’—2 ነገሥት 18:6
አባትህ ወይም እናትህ የይሖዋን አምልኮ ያጥላላሉ? አካላዊና ስሜታዊ ጥቃት ያደርሱብሃል? ወይም የሱስ ተገዢ ናቸው? ከሆነ አንተም የወላጅህን ስህተት መድገም የለብህም! ሕዝቅያስ መጥፎ የሆነ አባት ቢያሳድገውም ይህ ሕይወቱን እንዲያበላሸው አልፈቀደም። እንዲያውም በጣም ጥሩ ንጉሥ ከመሆኑ የተነሳ “ከእርሱ በኋላ ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ፣ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም” ተብሎለታል። (2 ነገሥት 18:5) አንተም የቤተሰብ ሕይወትህ አስቸጋሪ ቢሆንም እንደ ሕዝቅያስ የተሳካ ሕይወት መምራት ትችላለህ። እንዴት? ምንጊዜም ‘ከይሖዋ ጋር ተጣበቅ።’