መልክና ቁመናዬን ባልወደውስ?
ምዕራፍ 7
መልክና ቁመናዬን ባልወደውስ?
መልክና ቁመናሽ ብዙም አያስደስትሽም?
□ አዎ □ አይ
መልክሽን ወይም ቁመናሽን ለማስተካከል ስትይ የማሳመሪያ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ወይም ከልክ ያለፈ የአመጋገብ ሥርዓት ለመከተል አስበሽ ታውቂያለሽ?
□ አዎ □ አይ
ብትችዪ ኖሮ ከመልክሽ ወይም ከቁመናሽ ጋር በተያያዘ መለወጥ የምትፈልጊው የትኛውን ነው? (መልስሽን አክብቢ።)
ቁመት
የሰውነት ቅርጽ
የቆዳ ቀለም
ክብደት
ፀጉር
አፍንጫ
ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ጥያቄዎች የሰጠሽው መልስ ‘አዎ’ የሚል ከሆነና ለሦስተኛው ጥያቄ ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ ቢያንስ ሦስቱን መርጠሽ ከሆነ እስቲ ነገሩን ከሌላ አቅጣጫ ለመመልከት ሞክሪ፦ አንቺ የምታስቢውን ያህል ሌሎች ሰዎች መልክሽ ጉድለት ያለው ሆኖ አይታያቸው ይሆናል። ሳይታወቅሽ ስለ መልክሽ ከልክ በላይ የመጨነቅ አባዜ ሊጠናወትሽ ይችላል። እንዲያውም አንድ ጥናት እንደጠቆመው ብዙውን ጊዜ ወጣት ሴቶች ከኒዩክሌር ጦርነትና ከካንሰር ሌላው ቀርቶ ወላጆቻቸውን በሞት ከማጣትም እንኳ ይበልጥ የሚያስፈራቸው ውፍረት ነው!መልክሽና ቁመናሽ ለራስሽ ባለሽ አመለካከትም ሆነ ሌሎች አንቺን በሚይዙበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አይካድም። የ19 ዓመቷ ማሪትሳ እንዲህ ብላለች፦ “እያደግን ስንመጣ ሁለቱ ታላላቅ እህቶቼ በጣም ቆንጆ ሆኑ፤ እኔ ግን ድብልብል ያልኩ ነበርኩ። በትምህርት ቤት ልጆቹ በጣም ያሾፉብኝ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ አክስቴ ቸብስ [‘ዱብዬ’ እንደ ማለት ነው] ብላ ትጠራኝ ነበር፤ ወፍራም የሆነውን ድንክ ውሻዋን የምትጠራውም በዚህ ስም ነው!” የ16 ዓመት ወጣት የሆነችው ዩሊያም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሟታል፦ “አብራኝ የምትማር አንዲት ልጅ ጥርሴ ገጣጣ እንደሆነ በመናገር ትቀልድብኝ ነበር። ነገሩ ያን ያህል የሚካበድ ባይሆንም እንዲህ ማለቷ ስለ መልኬ ጥሩ ስሜት እንዳይኖረኝ አድርጎኛል፤ አሁንም ድረስ ጥርሴ ያሳፍረኛል!”
ያሳስብሻል ወይስ ከልክ በላይ ያስጨንቅሻል?
ስለ መልክሽ ማሰብሽ ምንም ስህተት የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ ሣራን፣ ራሄልን፣ ዮሴፍን፣ ዳዊትንና አቢግያን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሴቶችና ወንዶች ምን ያህል 1 ነገሥት 1:4
ቆንጆ እንደነበሩ ይናገራል። አቢሳ የተባለችው ወጣትም “እጅግ ቈንጆ” እንደነበረች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል።—ይሁንና በርካታ ወጣቶች ስለ መልካቸውና ስለ ቁመናቸው ከመጠን በላይ ይጨነቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወጣት ሴቶች ቁንጅና ሲባል ቅጥነት ይመስላቸዋል፤ የሰዎችን ትኩረት በሚስቡት መጽሔቶች ላይ የሚወጡት ሸንቃጣ የሆኑ ሞዴሎችን የሚያሳዩ ማስታወቂያዎችም እንዲህ ያለውን አመለካከት ያበረታታሉ። እነዚህ ወጣት ሴቶች የሚዘነጉት ነገር ግን ቀልብ የሚስቡት የሞዴሎቹ ፎቶዎች ምንም እንከን እንዳይኖርባቸው ልቅም ተደርገው በእጅ ሥራ የተሠሩ ወይም በኮምፒውተር አማካኝነት የተስተካከሉ መሆናቸውን ነው፤ ከዚህም በላይ እነዚህ ሸንቃጣና ውብ የሆኑ ሞዴሎች ቅርጻቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ምግብ የሚበሉት ላመል ያህል ብቻ ነው! ይህን እውነታ ብታውቂም እንኳ ራስሽን በመጽሔት ላይ ከምታያቸው ሞዴሎች ጋር ስታወዳድሪ የመልክሽ ነገር በጣም ያስጨንቅሽ ይሆናል። መልክና ቁመናሽን እንድትጠዪው የሚያደርግሽ በቂ ምክንያት እንዳለሽ ቢሰማሽስ? በመጀመሪያ ራስሽን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከት ይኖርብሻል።
የተዛባ አመለካከት አለሽ?
መልክን አዛብቶ በሚያሳይ መስተዋት ራስሽን ተመልክተሽ ታውቂያለሽ? ትክክለኛውን ቅርጽሽን አስተልቆ ወይም አሳንሶ ሊያሳይሽ ይችላል። በዚህም ሆነ በዚያ በመስተዋቱ ውስጥ የምታዪው ምስል የተሳሳተ ነው።
ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ በርካታ ወጣቶች ስለ መልካቸው ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው። እስቲ የሚከተሉትን አኃዛዊ መረጃዎች እንመልከት፦ በአንድ ጥናት
ላይ ከተካፈሉት ወጣት ሴቶች መካከል 58 በመቶ የሚሆኑት በጣም ወፍራም እንደሆኑ ቢሰማቸውም ከተገቢው ክብደት በላይ የሆኑት 17 በመቶዎቹ ብቻ ነበሩ። ሌላ ጥናት እንዳሳየው ደግሞ ከተገቢው በታች የሆነ የሰውነት ክብደት ካላቸው ሴቶች መካከል 45 በመቶ የሚሆኑት በጣም ወፍራም እንደሆኑ ይሰማቸዋል!አብዛኞቹ ወጣቶች ስለ ክብደታቸው የሚጨነቁት አለምክንያት መሆኑን አንዳንድ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ በእርግጥም ወፍራም ከሆንሽ ከላይ የቀረበው ሐሳብ ብዙም ላያጽናናሽ ይችላል። ታዲያ ሰውነትሽ እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው?
አንዱ ምክንያት የዘር ውርስ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች በተፈጥሯቸው ቀጠን ያለ ቁመና አላቸው። ይሁንና በተፈጥሮሽ ሞላ ያልሽ ከሆንሽና ሰውነትሽ ብዙ ስብ የሚያከማች ከሆነ አንቺነትሽን የሚወስነው ጂን ቀጭን እንድትሆኚ አይፈቅድልሽም ማለት ነው። ጤናማ የሚባል የክብደት መጠን ላይ ሆነሽም እንኳ ከምትፈልጊው በላይ እንደወፈርሽ ይሰማሽ ይሆናል። እንቅስቃሴ በማድረግና አመጋገብሽን በመቆጣጠር በተወሰነ መጠን ክብደትሽን መቀነስ ብትችዪም ብዙውን ጊዜ በዘር የወረስሽውን ቅርጽሽን መለወጥ አትችዪም።
ሌላው ምክንያት ደግሞ ከጉርምስና ዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ለውጥ ሊሆን ይችላል። በጉርምስና ወቅት ሴቶች ልጆች በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የስብ ክምችት ከ8 በመቶ ወደ 22 በመቶ ያድጋል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ለውጥ የሚመጣው ቀስ በቀስ ሲሆን ድምቡሽቡሽ ያለች የ11 ወይም የ12 ዓመት ልጅ የጉርምስና ዕድሜዋን ስታልፍ ቆንጆ ቅርጽ ያላት ኮረዳ ትሆናለች። በሌላ በኩል ግን ወፍራም የሆንሽው ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓት ስለማትከተዪ ወይም በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ስለማታደርጊ ቢሆንስ? ከጤንነትሽ አንጻር ክብደት መቀነስሽ የግድ ቢሆንስ?
ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
መጽሐፍ ቅዱስ ‘በልማዶቻችን ረገድ ልከኞች’ እንድንሆን አጥብቆ ያሳስበናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:11) ስለዚህ ቁርስ ወይም ምሳ አሊያም እራት በመተው ወይም ደግሞ ከልክ ያለፈ የአመጋገብ ሥርዓት በመከተል ክብደት ለመቀነስ መሞከር የለብሽም። ክብደት ለመቀነስ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ልማድ ማዳበርና መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሊሆን ይችላል።
ለመክሳት ይረዳሉ የሚባሉ ዘመን አመጣሽ ዘዴዎችን መከተል አያስፈልግሽም። ለምሳሌ፣ የምግብ ፍላጎትሽን የሚቀንሱ ኪኒኖች አሉ፤ ይሁንና ሰውነትሽ ብዙም ሳይቆይ እነዚህን መድኃኒቶች ስለሚለምዳቸው የምግብ ፍላጎትሽ ወደ ቀድሞው ይመለሳል። አሊያም ደግሞ እነዚህን መድኃኒቶች መውሰድሽ ሰውነትሽ ምግብ የሚያቃጥልበት ፍጥነት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ ዞሮ ዞሮ ክብደት መጨመርሽ አይቀርም፤ በዚያ ላይ ደግሞ እነዚህ መድኃኒቶች እንደ ማዞር፣ የደም ግፊት መጨመርና የመንፈስ ጭንቀት የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች ያስከትላሉ፤ አልፎ ተርፎም ለሱስ ሊዳርጉሽ ይችላሉ። በሰውነትሽ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ለመቀነስ ወይም ሰውነትሽ ምግብ የሚያቃጥልበትን ሂደት ለማፋጠን ተብለው የሚወሰዱ ኪኒኖችም ተመሳሳይ ጉዳት ያስከትላሉ።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ሚዛናዊ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓት መከተልና መጠነኛ ሆኖም ቋሚ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የተሻለ የሰውነት አቋም እንዲኖርሽና ስለ ራስሽ ጥሩ ስሜት እንዲሰማሽ ያደርጋል። በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራትሽ ለጤናሽ በጣም ጠቃሚ ነው። ቶሎ ቶሎ እንደ መራመድ አሊያም ደግሞ ደረጃ ወይም አቀበት እንደ መውጣት ያሉ እንቅስቃሴዎች በቂ ሊሆኑ ይችላሉ።
አኖሬክሲያ ወጥመድ እንዳይሆንብሽ ተጠንቀቂ!
አንዳንድ ወጣቶች ክብደታቸውን ለመቀነስ ካላቸው ጉጉት የተነሳ አኖሬክሲያ ወጥመድ ሆኖባቸዋል፤ ለሕይወት አስጊ የሆነው ይህ የአመጋገብ ችግር ያለባቸው ሰዎች ለመክሳት ሲሉ ራሳቸውን በረሃብ አለንጋ ይገርፋሉ። በአኖሬክሲያ ትሠቃይ የነበረች ማሳሚ የተባለች አንዲት ወጣት ከዚህ ችግር ለመላቀቅ እንድትችል ለአራት ወራት እርዳታ ከተደረገላት በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች ‘ተስማምቶሻል’ ሲሉኝ ‘እንዲህ የሚሉኝ ስለወፈርኩ መሆን አለበት’ ብዬ አስባለሁ። እንደዚህ
በሚሰማኝ ጊዜ ዘወር ብዬ አለቅሳለሁ፤ ‘ምናለ ከአራት ወር በፊት ወደነበረኝ ክብደት መመለስ በቻልኩ!’ የሚል ሐሳብ ይመጣብኛል።”አኖሬክሲያ እንዲሁ እንደ ዋዛ ሊጀምር ይችላል። አንዲት ወጣት ክብደቷን ትንሽ ለመቀነስ ብላ ምንም ጉዳት የሌለው የሚመስል የአመጋገብ ሥርዓት መከተል ትጀምር ይሆናል። ሆኖም ያሰበችው ግብ ላይ ስትደርስ በዚያ አትረካም። ራሷን በመስተዋት ስትመለከት በቁመናዋ ስለማትደሰት “አሁንም በጣም ወፍራም ነኝ!” ትላለች። በመሆኑም አሁንም ትንሽ ለመቀነስ ትወስናለች። ‘ትንሽ ትንሽ’ እያለች ሳይታወቃት ይህ ድርጊቷ ልማድ ይሆንባታል። በዚህ መንገድ በአኖሬክሲያ ወጥመድ ትያዛለች።
አኖሬክሲያ ወይም ሌላ የአመጋገብ ችግር እንዳለብሽ የሚጠቁም ነገር ካለ እርዳታ ማግኘት ያስፈልግሻል። ችግርሽን ለወላጆችሽ ወይም ለምትተማመኚበት ትልቅ ሰው በግልጽ ተናገሪ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል።—ምሳሌ 17:17
እውነተኛ ውበት ምንድን ነው?
በጥቅሉ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ለውጫዊ መልክ ወይም ለሰውነት ቅርጽ ትልቅ ቦታ አይሰጥም። ከዚህ ይልቅ አንድን ሰው በአምላክ ዘንድ ውብ ሆኖ እንዲታይ ምሳሌ 11:20, 22
ወይም እንዳይታይ የሚያደርገው ውስጣዊ ማንነቱ እንደሆነ ይገልጻል።—የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነውን አቤሴሎምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አቤሴሎም ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “መቼም በመልኩ ማማር አቤሴሎምን የሚያህል አንድም ሰው በመላው እስራኤል አልነበረም፤ ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚወጣለት እንከን አልነበረም።” (2 ሳሙኤል 14:25) ሆኖም ይህ ወጣት አታላይ ነበር። ትዕቢትና የሥልጣን ጥማት በይሖዋ የተቀባውን ንጉሥ ለመገልበጥ እንዲያሴር አነሳሳው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አቤሴሎምን በጥሩ አያነሳውም፤ ከዚህ ይልቅ ዓይን ያወጣ ከሃዲና ከመግደል የማይመለስ ክፉ ሰው እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል።
ዋናው ቁም ነገር፣ ይሖዋ ‘የሚመዝነው ልብን’ ነው፤ በእሱ ፊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንዲት ሴት ሸንቃጣ መሆኗ ወይም አንድ ወንድ ጡንቻው የፈረጠመ መሆኑ አይደለም። (ምሳሌ 21:2) በመሆኑም አምሮ ለመታየት መፈለግ ስህተት ባይሆንም ከመልክና ቁመና ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለማንነት ነው። ውሎ አድሮ ወጣቶችን በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ የሚያደርጋቸው መንፈሳዊ ሰው መሆናቸው እንጂ ፈርጣማ ጡንቻ ወይም ሽንቅጥ ያለ ቁመና ያላቸው መሆናቸው አይደለም!
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 10 ተመልከት
ብዙ ወጣቶች ሥር በሰደደ ሕመም ይሠቃያሉ፤ አሊያም በበሽታ ምክንያት አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። አንተም ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ ከሆንክ ሁኔታህን ተቋቁመህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.14 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።
ቁልፍ ጥቅስ
“ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን ልብን ያያል።”—1 ሳሙኤል 16:7 NW
ጠቃሚ ምክር
ክብደት ለመቀነስ ስታስቢ . . .
● ቁርስሽን መተው የለብሽም። እንዲህ የምታደርጊ ከሆነ ሰውነትሽ በጣም ስለሚራብ እንዲያውም ከሌላ ጊዜው የበለጠ ትበያለሽ።
● ሁልጊዜ ምግብ ከመብላትሽ በፊት በትልቅ ብርጭቆ ውኃ ጠጪ። ውኃው ሆድሽን ስለሚይዘው ብዙ እንዳትበዪ ያደርግሻል።
ይህን ታውቅ ነበር?
አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚያስጠነቅቁት አንድ ሰው ክብደት ለመቀነስ በማሰብ ራሱን የሚያስርብ ከሆነ ሰውነቱ “አስጊ ሁኔታ” እንደተፈጠረ ስለሚሰማው ምግብ የሚያቃጥልበትን ፍጥነት ይቀንሳል፤ ይህም ግለሰቡ ወደ ቀድሞው ክብደቱ እንዲመለስ ያደርገዋል!
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
ጤንነቴን ይበልጥ ለመንከባከብ እንዲህ ማድረግ እችላለሁ፦ ․․․․․
ለእኔ ሚዛናዊ የሚሆነው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራም ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● ስለ መልክና ቁመናሽ ምን ይሰማሻል?
● የተሻለ አቋም እንዲኖርሽ ልትወስጃቸው የምትችያቸው ምክንያታዊ የሆኑ አንዳንድ እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?
● አንድ ጓደኛሽ የአመጋገብ ችግር ቢኖርባት ምን ትመክሪያታለሽ?
● ታናናሾችሽ ስለ መልካቸው ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው መርዳት የምትችዪው እንዴት ነው?
[በገጽ 69 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ዓይኔ ትልልቅ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ ሰዎች ያሾፉብኝ ነበር። እያደር ግን በራሴ ላይ ብቀልድ የተሻለ እንደሆነ እየተገነዘብኩ መጣሁ፤ እንዲሁም በማንነቴና ባሉኝ ጠንካራ ጎኖች ኩራት ይሰማኝ ጀመር። መልኬን በጸጋ ተቀብዬ መኖር እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ። ለራሴ አክብሮት ሊኖረኝ እንደሚገባም ተረድቻለሁ።”—አምበር
[በገጽ 68 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለራስሽ ያለሽ ግምት መልክን የሚያዛባ መስተዋት እንደሚያሳየው ምስል የተሳሳተ ሊሆን ይችላል