በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መቅድም—ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች

መቅድም—ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች

መቅድም

ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች

‘ወላጆቼ ስሜቴን የማይረዱልኝ ለምንድን ነው?’ ‘አደንዛዥ ዕፆችንና የአልኮል መጠጦችን መውሰድ ልሞክር ይሆን?’ ‘ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ብፈጽምስ?’ ‘እውነተኛ ፍቅር ይዞኝ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት ላውቅ እችላለሁ?’ ‘ወደ ፊት ምን ይጠብቀኝ ይሆን?’

እንዲህ ዓይነቶቹን ጥያቄዎች መጠየቅ በእናንተ አልተጀመረም። ይሁን እንጂ ወጣቶች እንዲህ ዓይነቶቹን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሲያነሱ አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መልሶች ይጋረጡባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የአልኮል መጠጦችን ስለመጠጣት እናንሳ። ወላጆች ራሳቸው ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ እየጠጡ ልጆቻቸው እንዳይጠጡ ይከለክላሉ። መጽሔቶችና የቴሌቪዥን ፊልሞች ደግሞ አልኮል መጠጣትን ያወድሳሉ። እኩዮቻችሁ እንድትጠጡ ያደፋፍሯችኋል። በእውነቱ ብዙ ወጣቶች ማድረግ ስለሚኖርባቸው ጉዳዮች ግራ መጋባታቸው አያስደን⁠ቅም።

ንቁ! መጽሔት * በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ትክክለኛና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች ማስፈለጋቸውን በመገንዘብ ከጥር 1982 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) ጀምሮ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” የሚል ርዕስ ያለው አንድ አምድ ከፍቷል። በተከታታይ የወጡት ርዕሰ ትምህርቶች በአንባቢዎች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት አግኝተዋል። አንድ አንባቢ አድናቆቱን ሲገልጽ “እነዚህ በተከታታይ የሚወጡ ርዕሰ ትምህርቶች በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች በሚያጋጥሟቸው ችግሮች ለመርዳት የማያቋርጥ ፍላጎት ያላችሁ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው” በማለት ጽፏል። ሌላው አንባቢ ደግሞ “እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች እንደማያቋርጡ ተስፋ አደርጋለሁ፣ እንዳያቆሙም እጸልያለሁ” ሲል ጽፏል።

አንድ ሌላ ወጣት አንባቢ ደግሞ ‘ዕድሜዬ 14 ዓመት ነው። ማደግ ይህን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን አላወቅኩም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ብዙ ተጽእኖ አለባቸው። እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች በመውጣታቸው በጣም አመስጋኝ የሆንኩት ለዚህ ነው። አምላክ ርዕሰ ትምህርቶቹ ታትመው እንዲወጡ በማስቻሉ ሁልጊዜ ማታ ማታ አመሰግነዋለሁ’ በማለት ተናግሯል። ይሁን እንጂ ርዕሰ ትምህርቶቹ ለልጆች ወይም አነስተኛ የመረዳት ችሎታ ላላቸው ሰዎች ብቻ የተዘጋጁ አይደሉም። በመሆኑም “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” የአዋቂዎችንም አድናቆት አግኝቷል። አንድ ወላጅ “ዕድሜዬ 40 ዓመት ነው። እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች ለእኛ ለወላጆች በእርግጥ ከአምላክ የተላኩ ስጦታዎች ናቸው” ሲል ጽፏል። በተለይ ደግሞ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ርዕሰ ትምህርቶቹን በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ያሉትን ወጣቶች ስሜት ለመረዳትና እነርሱን በአግባቡ ለመያዝ ጠቃሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል።

“ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” ይህን የመሰለ ጥሩ ተቀባይነት ያገኘው ለምንድን ነው? የተሰጡት መልሶች በእርግጥ ተግባራዊ መሆን የሚችሉ በመሆናቸው ነው! እያንዳንዱ ርዕስ ሰፊ ጥናት ከተደረገበት በኋላ የተጻፈ ነው። ከዚህም በላይ የንቁ! መጽሔት ዘጋቢዎች የወጣቶችን አስተሳሰብና ስሜት ለማወቅ በዓለም ዙሪያ ካሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር ተነጋግረዋል! ወጣቶቹ በፍጹም ግልጽነት የሰጧቸው ሐሳቦች ርዕሰ ትምህርቶቹን ተጨባጭና ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ እርዳታ አበርክተዋል።

ይሁን እንጂ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” የተባለው መጽሐፍ የተሳካ ውጤት ያስገኘበት ዋነኛ ምክንያት የተሰጡት መልሶች በንድፈ ሐሳብ ወይም በግል አስተያየታችን ላይ ሳይሆን ዘላለማዊ እውነቶች በሚገኙበት በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው ነው። ‘መጽሐፍ ቅዱስ?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወጣቶች ብዙ የሚናገረው ነገር አለ። (ምሳሌ ምዕራፍ 1–7ን ተመልከቱ፤ ኤፌሶን 6:​1–3) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ‘የጎልማሳነትን ምኞት’ አሳምሮ በሚያውቀው በፈጣሪያችን መንፈስ አነሳሽነት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:​20–22፤ 3:​16) ሰብዓዊው ኅብረተሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈበት ዘመን ወዲህ ብዙ የተለዋወጠ ቢሆንም የጎልማሳነት ምኞቶች ግን እምብዛም አልተለወጡም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ለአሁኑም ሆነ ለጥንቱ ዘመን ይሠራል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለወጣቶቹ የቀረበው እየተሰበከላቸው እንዳለ ሆኖ እንዲሰማቸው በሚያደርግ መንገድ ሳይሆን ከእነርሱ ጋር በተደረገ ምክንያታዊ ውይይት መልክ ለማቅረብ ጥረት አድርገናል። መጽሐፉ የተጻፈው በመጀመሪያ ደረጃ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ለሚገኙ ወጣቶች ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ለያዘው ተግባራዊ ጥበብ አክብሮት ያለው ማንኛውም ሰው አንብቦ ሊደሰትበት ይች⁠ላል።

ብዙ አንባቢዎች ያቀረቡልንን ጥያቄ መሠረት በማድረግ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” ከሚለው ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ በርካታውን ክፍል በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅተናል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት 39 ምዕራፎች ከ1982 እስከ 1989 በታተሙት የንቁ! መጽሔቶች ላይ ከወጡት ወደ 200 የሚጠጉ ርዕሰ ትምህርቶች ከ100 በላይ ከሚሆኑት ውስጥ ተጨምቀው የወጡትን ሐሳቦች ይዘዋል። አንዳንድ አዳዲስ ሐሳቦችም ተጨምረዋል። በተጨማሪም በልዩ ልዩ አገሮች የሚኖሩ ልዩ ልዩ ዘርና ቀለም ያላቸው ወጣቶች ፎቶግራፎች የሚገኝበት በርካታ ሥዕላዊ መግለጫ አለው።

የመጽሐፉን ማውጫ በመቃኘት በቀጥታ ይበልጥ የሚያሳስባችሁን ጥያቄ ወደያዘው ምዕራፍ መሄድ ትችላላችሁ። ከዚያ በኋላ ግን ጥቅሶቹን ከራሳችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥታችሁ እያነበባችሁ መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር እንድታነቡት እንመክራችኋለን።

በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ በወላጆችና በልጆች መካከል የሐሳብ ግንኙነት የለም፣ ቢኖርም የሠመረ አይደለም። በመሆኑም በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የመወያያ ጥያቄዎች ብለን የሰየምነውን አምድ ጨምረናል። ጥያቄዎቹ ርዕሰ ትምህርቱን አንቀጽ በአንቀጽ ለመተንተን እንዲያገለግሉ ታስበው የተዘጋጁ አይደሉም። ወይም ደግሞ ወላጆች የልጆቻቸውን የመረዳት ችሎታ ለመፈተን የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች አይደሉም። በወጣቶችና በወላጆች መካከል ውይይት እንዲኖር ለማነቃቃት የተዘጋጁ ናቸው። ብዙዎቹ ጥያቄዎች የራሳችሁን አመለካከት ወይም ለውይይት የቀረበው ሐሳብ እንዴት እናንተን በግል እንደሚመለከት እንድትገልጹ ያስችሏችኋል።

ስለዚህ ብዙ ቤተሰቦች ይህን መጽሐፍ አንዳንዴ ለቤተሰብ ጥናታቸው ሊጠቀሙበት ይፈልጉ ይሆናል። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ የቤተሰቡ አባሎች በአንቀጾቹ ውስጥ የተመለከቱትን ጥቅሶች በማውጣት በየተራ ሊያነቡ ይችላሉ። የመወያያ ጥያቄዎቹ ከእያንዳንዱ ጥያቄ ጋር አግባብነት ያለው ንዑስ ርዕስ እንዳለቀ በየተራ ወይም መላው ምዕራፍ ካለቀ በኋላ በተከታታይ ሊጠየቁ ይችላሉ። የቤተሰቡ አባሎች በሙሉ ስሜታቸውን በግልጽና በሐቀኝነት እንዲገልጹ ሊበረታቱ ይችላሉ። ወጣቶችም እርስ በርሳቸው በመጽሐፉ ላይ ሊወያዩ ይችላሉ።

ያለንበት ጊዜ ለወጣቶችም እንኳን ሳይቀር “የሚያስጨንቅ ዘመን” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል በማወቅ በሕይወታችሁ ውስጥ አስቸጋሪ የሆነውን ይህን ጊዜ በተሳካ ሁኔታ ልታሳልፉት ትችላላችሁ። (መዝሙር 119:​9) ስለዚህ ግራ ለሚያጋቧችሁ ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የሚገኙበትን ይህን መጽሐፍ ስናቀርብላችሁ በጣም ደስ ይለናል።

አዘጋጆች

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በወር ሁለት ጊዜ የሚታተም።