በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምችለው እንዴት ነው?

ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 39

ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምችለው እንዴት ነው?

ከአምላክ ጋር መቀራረብ? ለብዙ ሰዎች አምላክ ማንም እንዲቀርበው የማይፈልግ ሩቅ የሆነና የራሱ የሆነ ምንም ዓይነት ባሕርይ የሌለው ‘ፈጣሪ’ ሆኖ ይታያቸዋል። በመሆኑም ወደ እርሱ የመቅረብ ሐሳብ ሲነሳባቸው ይሸበራሉ፣ እንዲያውም ይፈራሉ።

ከዚህም ሌላ የእናንተ ተሞክሮ ሊንዳ የምትባለው ወጣት ሴት ያጋጠማት ዓይነት ሊሆን ይችላል። ሊንዳ ክርስቲያን ወላጆች ያሳደጓት ወጣት ስትሆን “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ በነበርኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የቀረሁባቸው ጊዜያት ትዝ አይሉኝም። ሳልሰብክ ያሳለፍኩት ወርም አልነበረም። ሆኖም ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና በግል አልመሠረትኩም ነበር” ብላለች።

ይሁን እንጂ የወደፊቱ ሕይወታችሁ ወደ አምላክ በመቅረባችሁ ላይ የተመካ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጸልይ “የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተን . . . ማወቅ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:​31980 ትርጉም) ይህ “ማወቅ” ስለ አምላክ አንዳንድ ነገሮችን ለመማርና ለመድገም ከመቻል የበለጠ ነገርን ያካትታል። ምክንያቱም አምላክ የለም ብሎ የሚያምን ሰው እንኳን ይህን ማድረግ አያቅተውም። ይህ “ማወቅ” ከአምላክ ጋር መዛመድን፣ የአምላክ ወዳጅ መሆንን ይጨምራል። (ከያዕቆብ 2:​23 ጋር አወዳድሩ።) አምላክ ሊቀረብ የማይችል አይደለም። እንዲያውም “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” ‘ፈልገን እንድናገኘው’ ይጋብዘናል።​— ሥራ 17:​27

አምላክን ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

ከርቀት የሚታዩትን ከዋክብት ተመልክታችሁ፣ የሚተምመውን የባሕር ድምፅ በመገረም አድምጣችሁ፣ ውብ በሆነች ቢራቢሮ ተማርካችሁ፣ ወይም በአንዲት ትንሽ ቅጠል ልስላሴና ውበት ተደንቃችሁ ታውቃላችሁ? እነዚህ የአምላክ ሥራዎች በሙሉ በጣም ከፍተኛ ስለሆነው የአምላክ ኃይል፣ ጥበብና ፍቅር ፍንጭ ይሰጡአችኋል። የአምላክ “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ . . . ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል።”​— ሮሜ 1:​19, 20

ይሁን እንጂ ስለ አምላክ ያላችሁ እውቀት ፍጥረት በሚገልጥላችሁ ነገር ብቻ ተወስኖ መቅረት አይኖርበትም። በዚህም ምክንያት አምላክ ቃሉን አስጽፎ ሰጥቶናል። ይህ መጽሐፍ አምላክ ስምና የራሱ ባሕርይ የሌለው አንድ ዓይነት ኃይል ሳይሆን እውን የሆነ አካልና ስም ያለው እንደሆነ ይገልጻል። መዝሙራዊው “ይሖዋ አምላክ እንደሆነ እወቁ” በማለት አስታውቋል። (መዝሙር 100:​3 አዓት) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ስም ባለቤት የሆነው አካል “መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት” መሆኑን ይገልጻል። (ዘጸአት 34:​6) መጽሐፉ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በነበረው ግንኙነት ስላደረጋቸው ነገሮች የሚገልጸው ዝርዝር ታሪክ የአምላክን አሠራር ግልጽ አድርጎ ያሳየናል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ወደ አምላክ ለመቅረብ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ክፍል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች እንዲሆን ማድረግ

መጽሐፍ ቅዱስ በአጭር ጊዜ ተነብቦ የማያልቅ መጽሐፍ መሆኑ አይካድም። ብዙውን ጊዜ ወጣቶች የመጽሐፉን ግዙፍነት በመመልከት ብቻ ለማንበብ ይፈሩታል። አንዳንዶች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስልቺ ነው ብለው ያማርራሉ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሐሳቡን ለሰው ልጆች የገለጠበት መጽሐፍ ነው። እዚህ ምድር ላይ እንዴት እንደተገኘንና ወደፊትም ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚጠብቀን ይነግረናል። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም ለመኖር እንድንችል ምን ማድረግ እንደሚገባን በዝርዝር ይነግረናል። ታዲያ እንዲህ ያለው መጽሐፍ እንዴት አሰልቺ ሊሆን ይችላል? እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ለመዝናናት ተብሎ የሚነበብ መጽሐፍ አይደለም። በውስጡም “ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር” አለው። (2 ጴጥሮስ 3:​16) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አሰልቺና የማያስደስት ሥራ መሆን የለበትም።

ወጣቱ ማርቪን “ታሪኩ የተጻፈበትን ጊዜና ቦታ በሐሳቤ ለመሳል እሞክርና ራሴን በዚያ ጊዜና ቦታ ላይ አስቀምጣለሁ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን የሚረዳ አንድ ተግባራዊ ዘዴ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል በዳንኤል ምዕራፍ 6 ላይ ያለውን ታሪክ ውሰዱ። ይህን ታሪክ የድርጊቱ ተመልካች ብቻ ሆናችሁ ከምታነቡ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ዳንኤልን እንደሆናችሁ አድርጋችሁ አስቡ። ወደ አምላካችሁ በመጸለያችሁ ምክንያት በጭካኔ ክስ ቀርቦባችሁ ተያዛችሁ። ቅጣቱስ? ሞት! የፋርስ ወታደሮች እያዳፉ ወደ መቃብራችሁ ይወስዱአችኋል። የተራቡ አንበሶች በሞሉበት ጉድጓድ ውስጥ ልትጣሉ ነው።

ጉድጓዱ የተከደነበት ትልቅ ድንጋይ በቀስታ ተከፈተ። ከታች ያሉት አንበሶች ከግር እስከ ራስ የሚወርር ግሣት ያሰማሉ። በድንጋጤ ወደኋላ ስታፈገፍጉ በንጉሡ ወታደሮች ተገፍትራችሁ ወደሞት ጉድጓድ ተጣላችሁና ድንጋዩ ተገጠመባችሁ። በጨለማ እንደተከበባችሁ ወዲያው ጠጉራም ፍጡር መጥቶ ይታከካችኋል . . .

ታዲያ ይህ አሰልቺ ነውን? በጭራሽ አይደለም! ይሁን እንጂ የምታነቡት ለመዝናናት ብላችሁ እንዳልሆነ አስታውሱ። ታሪኩ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምራችሁ ለማስተዋል ጣሩ። ለምሳሌ ያህል የዳንኤል ተሞክሮ ይሖዋ አገልጋዮቹ አስቸጋሪ ፈተናዎች እንዲያጋጥማቸው እንደሚፈቅድ ያሳይ የለምን?

በተጨማሪም መደበኛ የሆነ የንባብ ፕሮግራም እንዲኖራችሁ ጣሩ። በየቀኑ 15 ደቂቃ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ብታነቡ እንኳን በአንድ ዓመት ውስጥ አንብባችሁ ልትጨርሱት ትችላላችሁ። ጊዜያችሁን ቴሌቪዥን እንደመመልከት ካሉት በጣም አስፈላጊ ያልሆኑ ሥራዎች ቀንሳችሁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ አውሉት። (ኤፌሶን 5:​16) መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ራሳችሁን ባተጋችሁ መጠን ከምንጊዜውም የበለጠ ወደ አምላክ እንደቀረባችሁ ይሰማችኋል።​— ምሳሌ 2:1, 5

ጸሎት ከአምላክ ጋር ያቀራርባችኋል

ላቨርን የተባለች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የምትገኝ ወጣት “ከማታነጋግሩት ሰው ጋር የተቀራረበ ዝምድና ይኖራችኋል ብሎ ማሰብ አይቻልም” በማለት ገልጻለች። ይሖዋ ‘ጸሎት ሰሚ’ በመሆኑ እንድናነጋግረው ይጋብዘናል። (መዝሙር 65:​2) በእምነት ወደ እርሱ ብንጸልይና “እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል።”​— 1 ዮሐንስ 5:14

ሊንዳ (ቀደም ብለን የጠቀስናት) ይህን ከግል ተሞክሮዋ ተምራለች። በአንድ ወቅት ላይ በሕይወትዋ ውስጥ ችግሮችና ውጥረቶች ባጋጠሟት ጊዜ ‘ለችግሮቿ መፍትሔ ለማግኘት ለቀናት ሳታቋርጥ እንደጸለየች’ ታስታውሳለች። ችግሮቿን ለመቋቋም የሚያስችላት ጥንካሬ ባገኘች ጊዜ ከዚያ በፊት ሩቅ ይመስላት የነበረው አምላክ ቅርብ መሆኑ ይሰማት ጀመር። ኬይ የተባለች ሌላ ወጣትም በተመሳሳይ የጸሎትን ጥቅም ተገንዝባለች:- “አንዳንድ ጊዜ የውስጥ ስሜቶቻችሁን ለሆነ ሰው ለመግለጽ የምትፈልጉበት ጊዜ ያጋጥማችኋል። በዚህ ጊዜ ከይሖዋ የተሻለ ስሜታችሁን ልትገልጹለት የሚገባ ሰው ልታገኙ አትችሉም። ምክንያቱም ይሖዋ ችግራችሁን ስለሚረዳላችሁና ከእርሱ ይበልጥ ሊረዳችሁ የሚችል ባለመኖሩ ነው።”

ይሁን እንጂ የጸሎት ጥቅም ስሜታዊ እፎይታ ማስገኘት ብቻ ነውን? አይደለም። ያዕቆብ 1:​2–5 ልዩ ልዩ ችግሮች ሲያጋጥሙን ማድረግ ያለብንን ሲገልጽ “ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል” በማለት ያረጋግጥልናል። አምላክ ከችግሩ የምናመልጥበትን መንገድ ላይሰጠን ይችላል። ቢሆንም ችግሩን እንድንቋቋም የሚያስችል ጥበብ እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል! ችግሩን የሚመለከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ትዝ እንዲሉአችሁ ሊያደርግ ይችላል። (ከዮሐንስ 14:​26 ጋር አወዳድሩ።) ወይም ደግሞ አንዳንድ ነገሮች በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ወይም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት ትኩረታችሁን እንዲያገኙ ያደርግ ይሆናል። በተጨማሪም ‘ከአቅማችሁ በላይ እንድትፈተኑ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ መሆኑንና ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ እንደሚያደርግላችሁ’ አትርሱ። አዎን፣ “በማጥ ውስጥ” ተጥላችሁ እንድትቀሩ አይተዋችሁም። (1 ቆሮንቶስ 10:​13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​9) አንድን ችግር እንድትቋቋሙ ያስቻላችሁን የአምላክ እርዳታ ከቀመሳችሁ በኋላ ከእርሱ ጋር ይበልጥ እንደተቀራረባችሁ አይሰማችሁምን?

ይሁን እንጂ መጸለይ የሚገባችሁ ስለ ግል ችግሮቻችሁ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ ቅድሚያ የሰጠው የይሖዋ ስም እንዲቀደስ፣ መንግሥቱ እንዲመጣና ፈቃዱ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ነው። (ማቴዎስ 6:​9–13) በተጨማሪም ‘ምልጃና ምስጋና’ በጸሎታችን ውስጥ መካተት የሚገባቸው አስፈላጊ የሆኑ የጸሎት ዓይነቶች ናቸው።​— ፊልጵስዩስ 4:​6

መጸለይ የሚያስቸግራችሁ ወይም የሚከብዳችሁ ሆኖ ብታገኙትስ? ስለዚህም ጉዳይ ቢሆን ጸልዩ! ልባችሁን ከፍታችሁ ሐሳባችሁን እንድትገልጹለት አምላክ እንዲረዳችሁ ለምኑት። “በጸሎት ጽኑ።” እንዲህ ካደረጋችሁ ከጊዜ በኋላ ከቅርብ ጓደኛችሁ ጋር ያለ ምንም ችግር መነጋገር እንደምትችሉ ሁሉ ከይሖዋ ጋርም መነጋገር እንደምትችሉ ትገነዘባላችሁ። (ሮሜ 12:​12) “ችግር በሚያጋጥመኝ በማንኛውም ጊዜ” ትላለች ወጣቷ ማርያ፣ “አመራር እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት እንደምችልና እርሱም እንደሚረዳኝ አውቃለሁ።”

አምላክን ለማነጋገር በጣም ውብ በሆኑ ወይም በይስሙላ ቃላት መጠቀም አስፈላጊ አይደለም። “ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ” ብሏል መዝሙራዊው። (መዝሙር 62:​8) ስሜታችሁንና የሚያሳስቧችሁን ነገሮች እንዲያውቅ አድርጉ። ድክመቶቻችሁን ለመቋቋም እንድትችሉ እንዲረዳችሁ ጠይቁት። ቤተሰቦቻችሁንና ሌሎች ክርስቲያኖችን እንዲባርክ ጸልዩ። በምትሳሳቱበት ጊዜ ምሕረት እንዲያደርግላችሁ ለምኑት። ለሰጣችሁ የሕይወት ስጦታ በየቀኑ አመስግኑት። ጸሎት የሕይወታችሁ መደበኛ ክፍል ሲሆን ከይሖዋ አምላክ ጋር የተቀራረበና አስደሳች የሆነ ዝምድና እንዲኖራችሁ ያስችላችኋል።

ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት በሕዝብ ፊት ማሳወቅ

ከአምላክ ጋር ባላችሁ ወዳጅነት መደሰት ከጀመራችሁ ሌሎችም ይህን ውድ ዝምድና እንዲያገኙ ለመርዳት መጓጓት አይኖርባችሁምን? በእርግጥ የአምላክ ወዳጆች ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች ማሟላት ከሚኖርባቸው ብቃቶች አንዱ “በአፍ መመስከር” ነው።​— ሮሜ 10:​10 አዓት

ብዙዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው፣ ለጎረቤቶቻቸውና ለዘመዶቻቸው በመናገር እምነታቸውን ለሌሎች ማካፈል ይጀምራሉ። በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች “ከቤት ወደ ቤት” በሚያደርጉት የስብከት ሥራ መካፈል ይጀምራሉ። (ሥራ 5:​42) ይሁን እንጂ ይህ ሕዝባዊ ሥራ ለአንዳንድ ወጣቶች የማይወጡት እንቅፋት ሆኖባቸዋል። “ብዙ ወጣቶች ከቤት ወደ ቤት መሄድ የሚያሳፍራቸው ይመስለኛል” በማለት አንድ ወጣት ክርስቲያን ተናግሯል። “ከቤት ወደ ቤት ስሄድ ጓደኞቼ ቢያዩ ምን ይሉኛል ብለው ይፈራሉ።”

ይሁን እንጂ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጡት በማን ዘንድ ተወዳጅ ስለመሆን ነው? በእኩዮቻችሁ ወይስ በሰማዩ ወዳጃችሁ ዘንድ? ፍርሃት ወይም ኀፍረት ሕይወት ከማግኘት እንዲያግዳችሁ ትፈቅዳላችሁን? ሐዋርያው ጳውሎስ “እንዳይነቃነቅ [“በሕዝብ ፊት የምናደርገውን” አዓት] የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ [“አጥብቀን እንያዝ” አዓት]” በማለት በጥብቅ ይመክራል። (ዕብራውያን 10:​23) በቂ ሥልጠናና ዝግጅት ካደረጋችሁ በስብከቱ ሥራ እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንደምትጀምሩ ትገነዘባላችሁ!​— 1 ጴጥሮስ 3:​15

ከጊዜ በኋላም ለሰማያዊ ወዳጃችሁ የሚኖራችሁ አድናቆት ራሳችሁን አላንዳች ገደብ ለአምላክ አሳልፋችሁ እንድትሰጡና ይህንንም ውሳኔያችሁን በውኃ ጥምቀት እንድታሳዩ ሊገፋፋችሁ ይገባል። (ሮሜ 12:​1፤ ማቴዎስ 28:​19, 20) የተጠመቃችሁ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችሁን በሕዝብ ፊት ማሳወቅ በቀላሉ መታየት ያለበት ነገር አይደለም። ‘ራሳችሁን መካድን’ ማለትም የግላችሁን ምኞቶች ክዳችሁ የይሖዋን መንግሥት ፍላጎቶች ማስቀደምን ይጠይቃል። (ማርቆስ 8:​34) በተጨማሪም ከይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር መተባበርን ይጨምራል።

ሮበርት የሚባል ወጣት “ብዙ ወጣቶች ለመጠመቅ ፈራ ተባ የሚሉ ይመስለኛል” ብሏል። “ወደ ኋላ ሊመለሱበት የማይችሉት የማያዳግም እርምጃ እንደሆነ በማሰብ ይፈሩታል።” እውነት ነው፣ አንድ ሰው ለአምላክ ራሱን ከወሰነ በኋላ ያደረገውን ውሳኔ ከመፈጸም ወደኋላ ሊል አይችልም። (ከመክብብ 5:​4 ጋር አወዳድሩ።) ይሁን እንጂ “በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።” በዚህ ረገድ መጠመቅና አለመጠመቅ የሚያመጣው ልዩነት አይኖርም። (ያዕቆብ 4:​17) ጥያቄው የአምላክን ወዳጅነት ታደንቃላችሁን? እርሱንስ ለዘላለም እንድታገለግሉት የሚገፋፋ ፍላጎት አላችሁን? የሚል ነው። እንግዲያስ ፍርሃት የአምላክ ወዳጅ መሆናችሁን ከማስታወቅ ወደኋላ እንድትሉ አያድርጋችሁ!

የአምላክ ወዳጆች የሚያገኟቸው ዘላለማዊ ጥቅሞች!

የአምላክን ወዳጅነት መምረጥ ከመላው ዓለም ጋር የማትጣጣሙ ሰዎች እንድትሆኑ ያደርጋችኋል። (ዮሐንስ 15:​19) መዘባበቻ ልትሆኑ ትችላላችሁ። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟችሁ፣ ችግሮችና ፈተናዎች ሊያዋክቧችሁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ማንም ወይም ምንም ነገር እንዲነጥቃችሁ አትፍቀዱ። አምላክ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” በማለት የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚሰጣችሁ ቃል ገብቶላችኋል።​— ዕብራውያን 13:​5

ይህ መጽሐፍ ይሖዋና ድርጅቱ ለዘላለማዊ ደህንነታችሁ እንደሚያስቡ ከሚያሳዩት ማስረጃዎች አንዱ ብቻ ነው። በዚህ መጽሐፍ ገጾች ላይ ሁሉንም ጥያቄዎቻችሁንና ችግሮቻችሁን ለመዳሰስ የማይቻል ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ማለቂያ የሌለው ጥበብ ምንጭ መሆኑን ከምንጊዜውም የበለጠ እንድታደንቁ እንዳስቻላችሁ ጥርጥር የለውም! (2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) ግራ የሚያጋቡ ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ይህን ቅዱስ መጽሐፍ መርምሩ። (ምሳሌ 2:​4, 5) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ካሏችሁ ልባችሁን ከፍታችሁ ችግራችሁን ከገለጻችሁላቸው መንፈሳዊ ጥበብና ድጋፍ የምታገኙባቸው ተጨማሪ ምንጭ ይሆኑላችኋል።

ከሁሉ በላይ ግን ይሖዋ ለሁሉም ጥያቄዎቻችሁ መልስ ያለው መሆኑን አስታውሱ። እርሱ “ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” ስለዚህም ማንኛውም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥማችሁ እጃችሁን ይዞ ከችግራችሁ ሊያወጣችሁ ይችላል። (መዝሙር 46:​1) እንግዲያው ‘በዚህ በወጣትነታችሁ ወራት ታላቁን ፈጣሪያችሁን አስታውሱ።’ (መክብብ 12:​1) ይህም የይሖዋን ልብ ደስ የሚያሰኝ አካሄድ ነው። (ምሳሌ 27:​11) ደግሞም አምላክ ወዳጆቹ ለሆኑ ሰዎች በማይጠፋ ገነት ውስጥ ያዘጋጀላቸውን ዘላለማዊ የሕይወት ሽልማት ልታገኙ የምትችሉበት ብቸኛ መንገድ ይህ ነው።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን ይገልጻል?

◻ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁን አስደሳችና ውጤታማ ልታደርጉ የምትችሉት እንዴት ነው?

◻ እምነታችሁን “በሕዝብ ፊት ማስታወቅ” ምንን ይጨምራል? እንዲህ ለማድረግ ተገፋፍታችኋልን? ለምን?

◻ ከአምላክ ጋር በመቀራረብ ረገድ ስብሰባዎች ምን ሚና ይጫወታሉ? ከስብሰባዎቹስ በሚገባ ልትጠቀሙ የምትችሉት እንዴት ነው?

◻ የአምላክ ወዳጅ መሆን ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

[በገጽ 311 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወደ አምላክ ለመቅረብ በእርግጥ እችላለሁን?

[በገጽ 311 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሐሳቡን ለሰው ልጆች የገለጠበት መጽሐፍ ነው። እዚህ ምድር ላይ እንዴት እንደተገኘንና የወደፊቱ ሕይወታችን ምን እንደሚመስል ይነግረናል

[በገጽ 316, 317 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]

ስብሰባዎች ከአምላክ ጋር ለመቀራረብ ይረዳሉ

“ይሖዋን ከሚያፈቅሩ ጋር የማደርጋቸው ስብሰባዎች ከይሖዋ ጋር ተቀራርቤ ለመኖር እንደሚረዳኝ ተገንዝቤያለሁ።” እንዲህ ያለው አንድ ናይጄሪያዊ ወጣት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች እንደነዚህ ያሉትን ስብሰባዎች በየአካባቢዎቻቸው ባሉት የመንግሥት አዳራሾች ያደርጋሉ። (ዕብራውያን 10:​23–25) የ16 ዓመቷ አኒታ “በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ እውነተኛ ጓደኞች አግኝቻለሁ” ብላለች።

ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ስብሰባዎች ተራ የሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች ብቻ አይደሉም። በመንግሥት አዳራሾች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የሚሰጡባቸው አምስት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። በስብሰባዎቹም ላይ ስፋት ያላቸው ብዙ ርዕሶች ይሸፈናሉ:- ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ብንጠቅስ የቤተሰብ ኑሮ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት፣ ጠባይ፣ መሠረተ ትምህርቶችና ክርስቲያናዊ አገልግሎት ይገኙበታል። እንዲህ ባሉት ስብሰባዎች ላይ ከፍተኛ የሆኑ የመድረክ ዝግጅቶች አይቅረቡ እንጂ ትምህርቶቹ የሚቀርቡት በሚጥምና አስደሳች በሆነ መንገድ ነው። ንግግሮችና የቡድን ውይይቶች ብዙውን ጊዜ ቀስቃሽ ከሆኑ ቃለ መጠይቆችና ሠርቶ ማሳያዎች ጋር ተሰባጥረው ይቀርባሉ። በተለይ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች ጥሩ የሕዝብ ተናጋሪዎች እንዲሆኑ ያሠለጠነ በመሆኑ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው።

ቀደም ብላችሁም ቢሆን በስብሰባዎች ላይ የምትገኙ ከሆነስ? ይበልጥ በስብሰባዎቹ ለመጠቀም ተጣጣሩ። (1) ተዘጋጁ:- “በስብሰባዎች ላይ የምንጠቀምባቸውን መጻሕፍት የማጠናባቸውን ጊዜያት ወስኜያለሁ” ትላለች አኒታ። እንዲህ ብታደርጉ በስብሰባዎች ላይ (2) ተሳታፊ ለመሆን ቀላል ይሆንላችኋል። ኢየሱስ ወጣት ሳለ በቤተ መቅደሱ ውስጥ መንፈሳዊ ውይይት ሲደረግ በንቃት ያዳምጥ፣ ጥያቄ ይጠይቅና መልስ ይሰጥ ነበር። (ሉቃስ 2:​46, 47) እናንተም ሐሳባችሁን ለመቆጣጠር እንዲያስችላችሁ ማስታወሻ በመያዝ “ለሰማችሁት ነገር ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠት” ትችላላችሁ። (ዕብራውያን 2:​1 አዓት) የአድማጮች ተሳትፎ በሚጠየቅባቸው ጊዜያት ሐሳብ በመስጠት ተካፈሉ።

ሌላው ጠቃሚ ሐሳብ (3) የተማራችሁትን ሥሩበት:- የተማራችኋቸውን ቁም ነገሮች ለሌሎች አካፍሉ። ከዚህም በላይ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ለውጦችን በማድረግ የተማራችሁትን ነገር በኑሮአችሁ ውስጥ በሥራ ላይ አውሉ። እውነት ‘በእናንተ . . . እንደሚሠራ’ አሳዩ።​— 1 ተሰሎንቄ 2:​13

ለስብሰባዎች ቅድሚያ ስጡ። ከሌላው ጊዜ ይበልጥ የቤት ሥራ ወይም ጥናት የሚበዛባችሁ ከሆነ ከስብሰባ በፊት ለመሥራት ሞክሩ። “ከስብሰባዎች በኋላ ከወንድሞች ጋር መጨዋወትና ሰው ሁሉ ወጥቶ እስኪያበቃ ድረስ መቆየት እወዳለሁ” ይላል ሲሞን የተባለ ወጣት። “የቤት ሥራ ሲኖረኝ ግን ስብሰባው እንዳበቃ ወዲያውኑ ወደ ቤት እሄዳለሁ።” አመቺ ሆኖ ባገኛችሁት ማንኛውም ዓይነት መንገድ ሁኔታዎቻችሁን ማስተካከል ትችላላችሁ። በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ግን የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ። ስብሰባዎች ለመንፈሳዊ እድገታችሁ በጣም አስፈላጊ ናቸው።

[በገጽ 315 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማሳደግ አስፈላጊ ነው

[በገጽ 318 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“ችግር በሚያጋጥመኝ በማንኛውም ጊዜ አመራር እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት እንደምችልና እርሱም እንደሚረዳኝ አውቃለሁ”