በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልክ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

መልክ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

ምዕራፍ 10

መልክ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

መልካችሁን እንደማትወዱት ትናገራላችሁን? በመልካችን ሙሉ በሙሉ የምንደሰት ሰዎች ካለን በጣም ጥቂት ነን። በኩሬ ውኃ ውስጥ ካየው የገዛ መልኩ ጋር ፍቅር ከያዘው ከናርሲሰስ በተቃራኒ አንዳንዶቻችን መልካችንን በመስተዋት ስንመለከት እንበሳጫለን።

የ16 ዓመቷ ማሪያ ‘ገላዬን በጣም እጠላዋለሁ’ ትላለች። ‘አስቀያሚ መልክ ያለኝ ይመስለኛል።’ የአሥራ ሦስት ዓመቱ ቦብም ተመሳሳይ ቅሬታ አለው:- ‘ፀጉሬን አልወደውም። እዚህ ከማጅራቴ ላይ ቀጥ ብሎ ሲቆም ያስጠላኛል’ ይላል። እንዲያውም በአፍላ ጉርምስና ላይ ያለ ወጣት መልኩ ቶሎ ቶሎ ስለሚለዋወጥ አንድ የሥነ ልቦና ተመራማሪ እንደተናገሩት ወጣቶች ብዙውን ጊዜ “ለራሳቸው ገላ እንግዶች እንደሆኑ ይሰማቸዋል።” በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ስለ ፊታቸው ገጽታ፣ ስለ ፀጉራቸው፣ ስለ ቅርጻቸውና ስለ ቁመናቸው ይጨነቃሉ።

እርግጥ ነው፣ አምላክ ራሱም ውበትን ያደንቃል። መክብብ 3:​11 “[አምላክ] ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” ይላል። በእርግጥ መልካችሁ ሌሎች ለእናንተ በሚኖራቸው አመለካከትና በሚያደርጉላችሁ አያያዝ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል። ዶክተር ጄምስ ፒ ካመር “ሰዎች ለውጪያዊው ሰውነት ያላቸው ግምት ለውስጣዊው ሰውነት በሚሰጡት ግምት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል። የአንድ ሰው መልክ በራሱ ላይ ያለውን እምነትና በሕይወቱ ውስጥ የሚያደርጋቸውንና የማያደርጋቸውን ነገሮች ሊነካበት ይችላል” በማለት ጨምረው ተናግረዋል። ይህም በመሆኑ ስለ መልካችሁ ጤናማ በሆነ መንገድ ማሰባችሁ አስተዋይነት ነው። ይሁን እንጂ ራሳችሁን ከሰዎች እስክታገልሉ ወይም ስለ ራሳችሁ መጥፎ ስሜት እስኪሰማችሁ ድረስ ስለ ራሳችሁ የምታፍሩ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት ጤናማ አይሆንም።

አታምሩም የሚላችሁ ማን ነው?

ይሁን እንጂ ብዙዎች ስለ መልካቸው የሚጨነቁት ሁልጊዜ አካላዊ ጉድለት ስለኖራቸው አይደለም። አንዲት ቀጭን ልጃገረድ በክፍል ውስጥ ተቀምጣ ምነው ወፍራም በሆንኩ ብላ ስትመኝ በማዶዋ የተቀመጠች ደልደል ያለ ውፍረት ያላት ልጃገረድ ደግሞ “ወፍራም” በመሆኗ ታማርር ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ በመልክ አለመደሰት የሚመጣው ከየት ነው? ጥሩ መልክ ያላቸው ወጣቶች አናምርም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር የሆኑት ሪቻርድ ኤም ሳርልስ እንዲህ ይላሉ:- “የጉርምስናና የኮረዳነት ጊዜ ሰውነት ታላላቅ የሆኑ የአካላዊ አደረጃጀት ሂደቶች የሚካሄዱበት የሽግግር ወቅት ነው። . . . አብዛኞቹ ወጣቶች አዲሱና ተለዋዋጩ ሰውነት የሚያስከትለውን እፍረት ለመቋቋምና መረጋጋት ለማግኘት የሚመኩት በእኩዮቻቸው ነው።” ይሁን እንጂ በእኩዮቻችሁ ዓይን ስትገመገሙ ምን ያህል ረዥም፣ አጭር፣ ወፍራም ወይም ቀጭን እንደሆናችሁ፣ ያውም የአፍንጫችሁን ወይም የጆሯችሁን ቅርጽ ሳናነሳ፣ የሚሰጧችሁ አስተያየት ከፍተኛ ጭንቀት ሊፈጥርባችሁ ይችላል። ሌሎች እናንተ ከምታገኙት የበለጠ ትኩረት ሲያገኙ ወይም ስለመልካችሁ ስትሰደቡ ስለ ራሳችሁ መጥፎ ስሜት ማሳደር ልትጀምሩ ትችላላችሁ።

ከዚህም ሌላ ከቴሌቪዥን፣ ከመጻሕፍትና ከፊልሞች የሚመጣ የትም ተስፋፍቶ የሚገኝ ተጽእኖ አለ። በቴሌቪዥን ፊልም ላይና በመጽሔት ገጾች ላይ የሚያማምሩ ወንዶችና ሴቶች ትኩር ብለው እየተመለከቱ ከሽቶና ከአንገት ሐብል ጀምሮ ማንኛውንም ነገር ለሽያጭ ሲያስተዋውቁ እንመለከታለን። በዚህ መንገድ መገናኛ ብዙኃን እንከን የማይወጣለት ለስላሳና ውብ የሆነ የፊት ቆዳ ከሌላችሁ ወይም ­ጡንቻችሁ የፈረጠመ “ጠብደል” ካልሆናችሁ ሰው ፊት ለመቅረብ እንደማትችሉ፣ አለዚያም ሰው የሚወዳችሁ ወይም ደስተኞች ለመሆን እንችላለን ብላችሁ እንዳታስቡ ሊያሳምኗችሁ ይጥራሉ።

‘በራሳቸው ቅርጽ እንዲሞርዷችሁ አትፍቀዱ!’

ይሁን እንጂ መልከ ጥፉ ነኝ የሚል ድምዳሜ ላይ ከመድረሳችሁ በፊት አካላዊ እንከኖቻችሁ ምን ያህል እውን ወይም ሐሳብ የወለዳቸው እንደሆኑ ራሳችሁን ጠይቁ። ያን ያህል የምትጠሉት (ወይም እንዲሳቅባችሁ ያደረገው) የፊታችሁ ቅርጽ በእርግጥ ይህን ያህል ያስቀይማልን? ወይስ አስቀያሚ እንደሆነ ያመናችሁት ሌሎች ግፊት አድርገውባችሁ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በአካባቢያችሁ ያለው ዓለም በራሱ ቅርጽ ሞርዶ እንዲያወጣችሁ አትፍቀዱ” በማለት ይመክራል።​— ሮሜ 12:​2 የፊሊፕስ ትርጉም

እስቲ አስቡት:- ተወዳጆች፣ የተሳካላችሁ ወይም ደስተኞች ለመሆን አንድ ዓይነት የተወሰነ መልክ ሊኖራችሁ ያስፈልጋል የሚለውን ሐሳብ የሚያስፋፉት እነማን ናቸው? ይህን የሚያደርጉት ፋሽን አመጣሽ አመጋገብን ወይም ውድ የሆኑ ውበት ጨማሪ መኳኳያዎችን በማሳደዳችሁ ትርፍ የሚያጋብሱ የሸቀጣ ሸቀጥ አምራቾችና የንግድ ማስታወቂያዎች አይደሉምን? ታዲያ እነዚህ ሰዎችና ድርጅቶች አስተሳሰባችሁን እንዲቀርጹት ለምን ትፈቅዱላቸዋላችሁ? እኩዮቻችሁ ስለ መልካችሁ የሚነቅፏችሁ ከሆነ ይህን የሚያደርጉት እናንተን ለመርዳት ፈልገው ነው ወይስ እናንተን ለማዋረድ? እናንተን ለማዋረድ ፈልገው የሚያደርጉት ከሆነ መጀመሪያውኑስ እንዲህ ዓይነቶቹ “ጓደኞች” ምን ያደርጉላችኋል?

መጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ “ልብህንም ወደ ማስተዋል አዘንብል” በማለት ይመክራል። (ምሳሌ 2:​2) አስተዋይ መሆን አካላዊ ቁመናችሁን በትክክለኛ ማመዛዘን እንድትመለከቱና የመገናኛ ብዙኃን ፕሮፓጋንዳዎች የሚሉትን ሁሉ እንዳታምኑ ይረዳችኋል። በመገናኛ ብዙኃን የምናያቸውን መልከኛ ሰዎች ሊመስሉ የሚችሉት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። ደግሞም “ውበት አረፋ ነው።” (ምሳሌ 31:​30 የባይንግተን ትርጉም) ለውበታቸው ብዙ ገንዘብ የሚከፈላቸው ሰዎች በዚያ ቁንጅናቸው የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። ሌላ ለጋ የሆነና አዲስ ፊት ሲመጣ እነርሱ እንደተጣሉ ያህል ይረሳሉ። በተጨማሪም ውበታቸው እንደዚያ ደምቆ የሚታየው በመጋጌጫዎች፣ በብርሃንና በፎቶግራፍ ጥበብ ብዙ ጥረት ተደርጎለት ነው። (አንዳንድ ሰዎች በመልካቸው ዝና ያተረፉትን ሰዎች የውበት ማሳመሪያቸውን በማይጠቀሙበት ጊዜ አይተዋቸው መልካቸው ምን ያህል ተራ እንደሆነ ሲመለከቱ በጣም ተገርመዋል!)

ስለዚህ በቴሌቪዥን ወይም በመጽሔት ላይ እንደወጣው ወይም እንደወጣችው የውበት ሞዴል ለምን አልመሰልንም ብላችሁ የምታዝኑበት ምንም ምክንያት የላችሁም። ወይም ደግሞ አምራችሁ እንድትታዩ ከተፈለገ ምን ያህል ረዥም፣ አጭር፣ ወይም ቀጭን መሆን እንዳለባችሁ የሚወስኑት የመጨረሻዎቹ ብይን ሰጪዎች እኩዮቻችሁ አይደሉም። መልካችሁ ለራሳችሁ ካላስጠላችሁ ለእኩዮቻችሁ ምንም ደንታ አይኑራችሁ። የሚገርማችሁ ነገር ቢኖር እናንተ ስለ ራሳችሁ መልክ የምትጠሉት ነገር ሌላው ሰው ምነው በኖረኝ ብሎ የሚቀናበት ሊሆን ይችላል።

የቻላችሁትን ያህል መልካችሁን አሳምሩ!

አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች ስለ መልካቸው እንዲጨነቁ የሚያደርጋቸው ተገቢ ምክንያት ማለትም የፊታቸውን ቆዳ የሚያበላሽ ነገር፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ ደፍጣጣ አፍንጫ፣ የተንቀረፈፈ ጆሮ፣ ከመጠን ያለፈ እጥረትና የመሳሰሉት ችግሮች ሊኖርባቸው ይችላል። በእርግጥ ታዳጊ ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን መልካችሁ ገና ይለዋወጣል። በአፍላ ጉርምስና ወቅት ብጉር፣ የክብደት መለዋወጥና በጣም ፈጣን (ወይም በጣም አዝጋሚ) የሆነ ዕድገት ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። እንዲህ ከመሳሰሉት ችግሮች ብዙዎቹ ጊዜ የሚፈታቸው ናቸው።

ሌሎቹን ችግሮች ደግሞ ጊዜም አይፈታቸውም። በዚህም ምክንያት ብዙ ወጣቶች መልካቸው የማያምር መሆኑን ተቀብለው ለመኖር ይገደዳሉ። ጆን ክሊንገር የሚባሉ ጸሐፊ “ለብዙ ሰዎች የደስ ደስ ያለው መልክ ማጣት በሕይወታቸው ውስጥ በጣም ከሚያሳዝኗቸው ነገሮች ውስጥ አንዱና ቀደም ብለው ቢያውቁትም በቀሪው ሕይወታቸው እምብዛም ሊያመልጡት የማይችሉት ነገር ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ መልካችሁ የደስ ደስ ያለው ባይሆንም ልታሻሽሉት ትችላላችሁ!

መልክ ለማስተካከል ቀዶ ሕክምና ማድረግ ብዙ ወጪ የሚያስወጣና ምናልባትም አደጋ ያለው ሊሆን ይችላል። * ይሁንና የሰውነትን ንጽሕና መጠበቅ ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ከመሆኑም በላይ ማራኪነታችሁን ለመጨመር ብዙ ሊረዳ ይችላል። ፀጉራችሁ የፊልም ተዋናይ የሆኑ ሰዎችን ዓይነት ዞማነት ባይኖረውም በንጽሕና ሊጠበቅ ይችላል፤ ፊታችሁ፣ እጆቻችሁና ጥፍሮቻችሁም ቢሆን እንደዚሁ ነው። ነጫጭ ጥርሶችና ንጹሕና ቀላ ያሉ ድዶች ማንኛውንም ፈገግታ ማራኪ ሊያደርጉት ይችላሉ። ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያስቸግራችኋልን? ክብደት የሚቀንስ አመጋገብ መከተልና የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ (ምናልባትም ሐኪምን በማማከር የሚደረግ ሊሆን ይችላል) ክብደታችሁን ለመቆጣጠር በጣም ሊረዳችሁ ይችላል።

እናንተም በወላጆቻችሁ ስምምነት የመልካችሁን ጠንካራ ጎኖች የሚያጎሉና ጉድለቶቻችሁን አጋንነው የማያሳዩ አለባበሶችና የፀጉር አበጣጠሮችን መሞከር ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል ጸሐፊ ሻሮን ፌተን እንዳሉት አንዲት ልጃገረድ “ፀጉሯን ወደፊት ደፋ እንዲል አድርጋ ብታበጥር ወይም ወደላይ ሰብስባ ብታስረው” ትልቅ አፍንጫዋ ጎልቶ እንዳይታይ ያደርግላታል። ቀጭንና ማዕዘናዊ ፊቶችን “ጠቅለል ባለ አበጣጠር” ማሻሻል ይቻላል። አንዲት ሴት በሜክአፕ አስተዋይነት በታከለበት ሁኔታ ብትጠቀም ያለባትን የፊት እንከን ሊቀንስላት ይችላል። ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች በልብስ አመራረጣችሁ ብዙ ልታደርጉ የምትችሉት ነገር አለ። የፊታችሁን ውበት የሚጨምሩና የሚያጎሉ አለባበሶችን ምረጡ። ልብስ ስትገዙ በልብሱ ላይ ያሉትን መስመሮች ልብ ብላችሁ አስተውሉ:- ከላይ ወደታች ቀጥ ያሉ መስመሮች ያሏቸው ልብሶች ቀጭን ሲያስመስሉ አግዳሚ መስመሮች ግን የዚህ ተቃራኒ ናቸው!

አዎን፣ በተፈጥሮ ያማረ መልክ ባይኖራችሁም እንኳን ጥረት በማድረግና የፈጠራ ችሎታችሁን በመጠቀም ልታሳምሩት ትችላላችሁ።

ሚዛናዊ የመሆን አስፈላጊነት

ስለ መልክ ማሰብ አስፈላጊ ቢሆንም መልካችሁና አለባበሳችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቁን ቦታ እንዲይዝ እንዳታደርጉት ተጠንቀቁ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰዎች መልክ ብዙ እንደማይናገር አስተውላችኋልን? አብርሃም፣ ማርያም፣ ወይም ኢየሱስም እንኳን ሳይቀር መልካቸው ምን ይመስል እንደነበረ ያልተነገረን ለምንድን ነው? አምላክ ከቁም ነገር ባይቆጥረው መሆኑ ግልጽ ነው።

በአንድ ወቅት ቁመናው በጣም ማራኪ የነበረውን ኤልያብ የሚባል ወጣት አምላክ ለንግሥና ሥልጣን ሳይቀበለው ቀርቷል! ይሖዋ አምላክ ሁኔታውን ለነቢዩ ሳሙኤል እንዲህ በማለት ገልጾለታል:- “ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” (1 ሳ⁠ሙኤል 16:​6, 7) ምን መስለን እንደምንታይ ልንጨነቅለት በሚገባን በአምላክ ዘንድ መልካችን ከቁም ነገር የሚገባ አለመሆኑን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነገር ነው! ‘እርሱ ልብን ያያል።’

ሌላው ልናስበው የሚገባ ነገር:- አብዛኞቹ ጓደኞቻችሁ በጣም ቆንጆ የማይባሉ አይደሉምን? አባታችሁ ወይም እናታችሁ በፋሽን መጽሔት ላይ ሞዴል ሆነው ሊወጡ የሚያስችል መልክ ያላቸው ናቸውን? ላይሆኑ ይችላሉ። በእርግጥ የወላጆቻችሁን መልካም ባሕርያት ስለምታውቁ የመልካቸው ነገር እምብዛም አይታያችሁም! እናንተም ያለባችሁን እውነተኛም ሆነ ልብ ወለድ የሆነ የመልክ ጉድለት የሚያስንቁ ጠንካራ ጎኖች አሏችሁ።

የሆነ ሆኖ መልክ በእኩዮቻችሁ ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነገር ስለሆነ የእነርሱን የአለባበስና የፀጉር አበጣጠር ሞድ እንድትከተሉ ግፊት ሊያሳድሩባችሁ ይችላሉ። ታዲያ ለዚህ ግፊት ምላሽ የምትሰጡት እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 ያገጠጠ ጥርስ የሚያስተካክል ብረት ማስገባትን የመሳሰሉ አንዳንድ የሕክምና አሠራሮች ለጤናና ለውበት የሚበጅ ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ወጣቶች ስለ መልካቸው በጣም የሚጨነቁት ለምንድን ነው? ­አንተ/አንቺ ስለ መልክህ/ስለ መልክሽ ምን ይሰማሃል/ይሰማሻል?

◻ መገናኛ ብዙኃንና እኩዮቻችሁ ስለ መልክ የሚያስፋፉት አመለካከት ምን ዓይነት ነው? እንዲህ ላለው ተጽእኖ ምላሽ መስጠት የሚኖርባችሁ እንዴት ነው?

◻ የብጉርን ችግር መቋቋም የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

◻ መልካችሁን ልታሳምሩት የምትችሉት እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

[በገጽ 82 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ገላዬን በጣም እጠላዋለሁ። . . . አስቀያሚ መልክ ያለኝ ይመስለኛል’

[በገጽ 88 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ማንኛውንም የመልክ ጉድለት የሚያስንቁ ጠንካራ ጎኖች አሏችሁ

[በገጽ 84, 85 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘ብጉሬን ማጥፋት አልችልምን?’

ብጉር ቆዳ እንዲዥጎረጎር የሚያደርግ ወይም በጥቁር ጠቃጠቆ፣ በቀይ እበጦችና እነዚህን በሚመስሉ የቆዳ ችግሮች መልክ የሚያጠፋ ሕመም ነው። ለብዙዎቹ ወጣቶች ለጥቂት ወራት ብቻ ቆይቶ የሚጠፋ ሳይሆን አሳሳቢ ችግር ነው። በሁሉም ዕድሜ ላይ ያሉ ሰዎች በብጉር ሊጠቁ ቢችሉም አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቁት ግን በአፍላ ጉርምስና ላይ ያሉ ወጣቶች ናቸው። አንዳንድ ጠበብቶች እንደሚሉት 80 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች መጠኑ የተለያየ ይሁን እንጂ ብጉር ይወጣባቸዋል።

እንግዲያውስ 2, 000 የሚሆኑ በአፍላ ጉርምስና ላይ የሚገኙ ወጣቶች በራሳቸው ላይ የሚጠሉት ነገር ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ የቆዳ ችግር ከማንኛውም ሌላ ቅሬታ በልጦ መገኘቱ አያስደንቅም። ገና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለች ብዙ ብጉር የወጣባት ሳንድራ የተባለች ወጣት ስትናገር “በጣም መጥፎ ብጉር ወጥቶብኝ ስለነበረ ሰዎች እንዳያዩኝ ፊቴን ሁልጊዜ እሸሽግ ነበር። በመልኬ አፍር ስለነበር ከሰው እሸሽ ነበር። . . . በጣም አስጠላ ነበር” ብላለች።​— ኮ-ኢድ መጽሔት

ይህ መቅሰፍት በጣም ማማር በምትፈልጉበት በአፍላ ጉርምስና ዕድሜያችሁ ላይ የሚመጣባችሁ ለምንድን ነው? ምክንያቱም በማደግ ላይ ስላላችሁ ነው። መጎርመስ ስትጀምሩ የቆዳችሁም ዕጢዎች ሥራቸውን ይጨምራሉ።

ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ሁኔታውን በቀላል አነጋገር ይገልጸዋል:- እያንዳንዱ ዕጢ የሚያመነጨውን ዘይት በቆዳችን ላይ ባለች በእያንዳንዷ ጠጉር ዙሪያ ባለው ቀዳዳ ላይ ይጨምራል። ብዙውን ጊዜ ዘይቱ በቆዳችን ላይ ባሉት ቀዳዳዎች አማካኝነት ወደውጭ የሚወጣ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ቆዳው ይደፈንና ዘይቱ በሚፈለገው ፍጥነት ወደ ውጭ መውጣት ያቅተዋል። ታፍኖ የቀረው ዘይት ከኦክስጅን ጋር ተዋህዶ ይደርቅና ስለሚጠቁር የተደፈነው ቀዳዳ ጥቁር ጠቃጠቆ ያበጃል። መግል ሲይዝ ደግሞ ትንሽ እብጠት ይፈጠራል። በታቆረው ዘይት ላይ ጀርሞች ከተራቡበት መጠኑ ከፍ ያለ ቀይ እብጠት ይፈጠራል። የማይጠፋ ጠባሳ ትቶ የሚያልፈው ቀዩ እብጠት ነው። ትንንሾቹ እብጠቶች በጀርም ካልተመረዙ በስተቀር ጠባሳ አይተውም። በጀርም ሊመረዙ የሚችሉት ደግሞ ራሳቸው እስኪረግፉ ድረስ በመተው ፈንታ ለማፍረጥ ወይም ለመላጥ ሲሞከር ነው። ስለዚህ አታፍርጧቸው ወይም አትላጧቸው!

ጭንቀትና የስሜት መረበሽ የቆዳ ዕጢዎችን ሊቀሰቅሳቸው ወይም ከወትሮው የበለጠ ሊያሠራቸው እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል። አንዳንዶች አንድ ትልቅ ነገር በሚጠባበቁበት ጊዜ ወይም ከፈተና በፊትና በፈተና ጊዜ ትልልቅ ብጉር በፊታቸው ላይ ይወጣል። በዚህ ምክንያት ኢየሱስ “ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል” በማለት የተናገራቸው ቃላት ተግባራዊ ጥቅም አላቸው።​— ማቴዎስ 6:​34

የሚያሳዝነው ነገር ፈጣን ፈውስ የሌለ መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ የቆዳ በሽታን ለመቆጣጠር የሚረዱ ያለ ሐኪም ትእዛዝ የትም ልታገኟቸው የምትችሉ ክሬሞች፣ ቅባቶች፣ መታጠቢያዎች፣ ሳሙናዎችና ቤንዞይል ፐርኦክሳይድ (ፀረ ባክቴሪያ ቅመም) ያለባቸው ቅባቶች አሉ። (ከዚህ ያለፈ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ ካስፈለገ ሐኪም ማማከር ይቻላል።) ብዙዎች ቆዳቸውን ቤንዞይል ፐርኦክሳይድ ባለበት ሣሙና ወይም መታጠቢያ ሙልጭ አድርጎ ማጠብ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ይሁን እንጂ ቅባትነት ባላቸው ወይም ከዘይት በተሠሩ መኳኳያዎች አትጠቀሙ።

አንዳንድ ወጣቶች ጠቅላላ ጤንነታቸውን በመንከባከብ፣ ማለትም የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በተቻለ መጠን ነፋሻ አየር በማግኘትና በቂ እንቅልፍ በመተኛት ብጉራቸው እንደቀነሳላቸው ተገንዝበዋል። ቅባት የሌለበት ምግብ መመገብ ጠቃሚ ስለ መሆኑ አንዳንዶች የሚከራከሩ ቢሆንም ጣፋጭ ነገር የበዛበት ምግብ ከመብላት መራቅና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ አስተዋይነት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ያም ሆነ ይህ ትዕግሥት የግድ አስፈላጊ ነው። አስታውሱ:- ረዥም ጊዜ የቆየ ችግር በአንድ ሌሊት አይለቅም። ቀደም ብለን የጠቀስናት ሳንድራ “ቆዳዬ ሙሉ በሙሉ ለመዳን ዓመት ያህል ጊዜ ሳይፈጅበት እንዳልቀረ እገምታለሁ፤ ይሁን እንጂ በስድስት ሳምንት ውስጥ በቆዳዬ ላይ ለውጥ ማየት ጀምሬ ነበር” ትላለች። ረዘም ላለ ጊዜ ሕክምናውን ሳታቋርጡ ብትከታተሉ መጠነኛ ፈውስ ማግኘታችሁ አይቀርም።

እስከዚያው ድረስ ግን በፊታችሁ ላይ የሚታዩ ጥቂት ነጠብጣቦች ለራሳችሁ ያላችሁን ግምት እንዲያጠፉት ወይም ከሌሎች ጋር እንደ ልብ ከመነጋገር እንዲከለክሏችሁ አትፍቀዱ። ስለ ቆዳችሁ በጣም ብታፍሩም ሌሎች የእናንተን ያህል አክብደው ላይመለከቱት ይችላሉ። ስለዚህ አዎንታዊና ደስተኛ መንፈስ ለመያዝ ሞክሩ። ብጉራችሁንም ለማጥፋት አሁኑኑ የተቻላችሁን አድርጉ!

[በገጽ 83 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እናንተ በራሳችሁ ላይ የምትጠሉት ነገር ሌሎች ምነው በኖረን ብለው የሚቀኑበት ሊሆን ይችላል

[በገጽ 86 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ፎቶግራፋቸው በመጽሔት ላይ የሚወጡ ሰዎች አንድ የውበት አሳማሪ ቡድን ተጨንቆ ተጠቦ ያሳመራቸው መሆኑን ብዙውን ጊዜ ወጣቶች አይገነዘቡም