በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አለባበሴ ስለ እኔ እውነተኛ ማንነት ይናገራልን?

አለባበሴ ስለ እኔ እውነተኛ ማንነት ይናገራልን?

ምዕራፍ 11

አለባበሴ ስለ እኔ እውነተኛ ማንነት ይናገራልን?

“በጣም አጭር አይደለም” አለች ፔጊ ለወላጆቿ ስትናገር። “እናንተ ዘመኑ ያለፈበትን ፋሽን ስለምትከተሉ ብቻ ነው!” ካለች በኋላ ወደ ክፍሏ ሮጣ ሄደች። ልትለብስ በፈለገችው ቀሚስ ምክንያት የተፈጠረው ጥል በዚህ አበቃ። እናንተም ብትሆኑ ወላጃችሁ፣ አስተማሪያችሁ ወይም አሠሪያችሁ እናንተ የምትወዱትን ልብስ ሲያንቋሽሽባችሁ ይህን ወደ መሰለ ንትርክ ገብታችሁ ታውቁ ይሆናል። እናንተ ሰውነት የሚያዝናና አለባበስ ነው የምትሉትን እነርሱ የተዝረከረከ አለባበስ ነው ይሏችኋል። እናንተ የዘነጠ ልብስ ነው የምትሉትን እነርሱ ግን ቅጥ ያጣ ወይም የብልግና ሐሳብ የሚቀሰቅስ ነው ይሏችኋል።

በእርግጥ ምርጫዎች ይለያያሉ፣ እናንተም የራሳችሁ ምርጫ ሊኖራችሁ ይችላል። ይህ ማለት ግን ሁሉም ዓይነት አለባበስ ‘ያስኬዳል’ ማለት ነውን?

ትክክለኛውን መልእክት ያስተላልፋልን?

“የምትለብሱት ልብስ” ትላለች ፓም የተባለች ልጃገረድ “በእርግጥ ማንነታችሁንና ስለ ራሳችሁ ያላችሁን ስሜት ያሳያል” ብላለች። አዎን፣ አለባበስ ስለ እናንተ የሚያስተላልፈው መልእክት ወይም የሚለው ነገር አለው። አለባበስ ስለ ትጋት፣ ስለ አቋም ጽናት፣ ስለ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ ሊናገር ይችላል። አለበለዚያም ግለሰቡ ዓመፀኛና ያለመርካት ባሕርይ ያለበት መሆኑን ጮክ ብሎ ሊናገር ይችላል። እንደ መታወቂያም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። አንዳንድ ወጣቶች የተተለተለ ልብስ መልበስ፣ የፓንክ ፋሽን በመከተል ወይም ውድ የሆኑ የሞዴል ማሳያ ልብሶችን በመልበስ ልዩ ሆነው ለመታየት ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ ተቃራኒ ጾታን የሚስቡ ወይም ከዕድሜያቸው በላይ ትልልቆች መስለው እንዲታዩ የሚያደርጉ ልብሶችን ይለብሳሉ።

ስለዚህ አለባበስ ለብዙ ወጣቶች ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነገር የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም። ይሁን እንጂ ጆን ቲ ሞሎይ የሚባሉ ድሬስ ፎር ሰክሰስ የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ “አለባበሳችን በምናገኛቸው ሰዎች ስሜት ላይ ከፍተኛ ኃይል ስለሚኖረው የሚያደርጉልን አያያዝ በአለባበሳችን በእጅጉ ይነካል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

እንግዲያውስ ወላጆቻችሁ ስለ አለባበሳችሁ በጣም መጨነቃቸው አያስደንቅም! ለእነርሱ አለባበሳችሁ የምርጫ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ወላጆቻችሁ የሚፈልጉት በአለባበሳችሁ ሚዛናዊ የሆናችሁና ኃላፊነት የሚሰማችሁ ሰዎች እንደሆናችሁ የሚያሳይ ትክክለኛ መልእክት እንድታስተላልፉ ነው። ይሁን እንጂ አለባበሳችሁ ይህን ዓይነቱን መልእክት ያስተላልፋልን? የልብስ አመራረጣችሁ የሚመራው በምንድን ነው?

“ጓደኞቼ ማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ አደርጋለሁ”

አለባበስ ለብዙ ወጣቶች ራሳቸውን የቻሉና የራሳቸው ማንነት ያላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን የሚያሳዩበት መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን ባሕሪያችሁ ገና አልሰከነም፤ ማለትም ገና በማደግና በመለዋወጥ ላይ ናችሁ። ስለዚህ የራሳችሁ ማንነት እንዲታወቅላችሁ የምትፈልጉ ብትሆኑም ይህ ማንነታችሁ ምን መሆን እንዳለበትና እንዴት መታወቅ እንደሚኖርበት ገና ላታውቁ ትችላላችሁ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ወጣቶች ቅጥ በሌለው ጋጠ ወጥ አለባበስ ያጌጣሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ በማድረጋቸው ‘ማንነታቸውን’ ከማሳወቅ ይልቅ ያልበሰሉ መሆናቸውን ያሳያሉ። ከዚያም አልፈው ወላጆቻቸውን ያሳፍራሉ።

ሌሎች ወጣቶች ደግሞ እኩዮቻቸው የሚለብሱትን ለመልበስ ይፈልጋሉ። ይህን ማድረጋቸው በራሳቸው እንዲተማመኑና ከእኩዮቻቸው ጋር እንዲመሳሰሉ የሚያደርጋቸው ይመስላቸዋል። በእርግጥ ከሌሎች ጋር ለመመሳሰል መፈለግ በራሱ ስህተት ላይሆን ይችላል። (ከ1 ቆሮንቶስ 9:​22 ጋር አወዳድሩ።) ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ከማያምኑ ወጣቶች ጋር አንድ ተደርጎ እንዲቆጠር ይፈልጋልን? በተጨማሪም የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ በእኩዮች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ጥበብ ነውን? አንዲት ልጃገረድ “ጓደኞቼ እንዳይተቹኝ ስል እነርሱ የሚፈልጉትን ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት ገልጻለች። ታዲያ ለሌላ ሰው የሚያጎበድድና ያ ሰው እንደሚፈልገውና እንደሚወደው የሚጠመዘዝን ሰው ምን ትሉታላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ “ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፣ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?” በማለት መልሱን ይሰጣችኋል።​— ሮሜ 6:​16

በወጣቶች ዘንድ “ከእኩዮቻቸው ጋር ተመሳስሎ የመታየት ፍላጎታቸው በጣም ጠንካራ ስለሚሆን የአንድ ቡድን አባሎች እንዴት መልበስ፣ እንዴት መናገር፣ ምን መሥራት እንዲሁም ምን ማሰብና ማመን እንዳለባቸው ሳይቀር ምክር ለማግኘት [በእኩዮቻቸው] ላይ በመመካት የቡድኑ ልማድ እስረኞች እስከመሆን ይደርሳሉ።”​— አዶለሰንስትራንዚሽን ፍሮም ቻይልድሁድ ቱ ማቹሪቲ (ጉርምስና፦ ከልጅነት ወደ ብስለት መሸጋገሪያ)

ነገር ግን ጓደኞቻችሁ እንዲህ ያለውን ምክር ለመስጠት ምን ያህል ብቃት አላቸው? (ከማቴዎስ 15:​14 ጋር አወዳድሩ።) በእናንተ ላይ እንደሚደርሱት ባሉ በዕድገት ምክንያት የሚመጡ የስሜት ቁስሎች የሚጠቁ አይደሉምን? ታዲያ የሚያወጡላችሁ የአቋም ደረጃዎች ምክንያታዊ እንደሆነ ከምታስቡት ወይም ወላጆቻችሁ ከፍ ያለ ግምት ከሚሰጡት ነገርና ከፍላጎታቸው ጋር የሚጋጩ መሆናቸውን እያወቃችሁ የምትመሩበትን የአቋም መመዘኛ እንዲያወጡላችሁ በየዋህነት መፍቀድ ጥበብ ነውን?

ዛሬ “ይመጣል”​—⁠ነገ “ይሄዳል”

ሌሎች ወጣቶች ደግሞ የሚመሩት በፋሽን ነፋስ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ የፋሽን ነፋሶች ምንኛ ተለዋዋጭ ናቸው! ይህም “የዚች ዓለም መልክ አላፊ [“ተለዋዋጭ” አዓት] ነው” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ያሳስበናል። (1 ቆሮንቶስ 7:​31) ዛሬ “ፋሽን” የሆነው ነገር ነገ በድንገት ከፍተኛ ኪሣራ አስከትሎ ጊዜ ያለፈበት ይሆናል። የልብስ ጠርዝ እጥፋቶች ከፍና ዝቅ ይላሉ፣ የሱሪ እግሮች ይሰፋሉ ይጠባሉ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት እንደፈለጉት በቀላሉ ሊጠመዘዙ ከሚችሉት ሰዎች ከፍተኛ ትርፍ የሚያገኙት የልብስ ሞዴል አውጪዎችና አምራቾች ናቸው።

ለምሳሌ ያህል ከጥቂት ዓመታት በፊት በጣም ተወዳጅ የነበሩትን የጂንስ ልብሶች እንውሰድ። አንድ ወቅት ላይ ጂንስ ልብሶች በጣም ተወዳጅ ፋሽን ሆኑ። ሰዎች ካልቪን ክላይንና ግሎሪያ ቫንደርቢልት የመሳሰሉት ስሞች የተጻፉባቸውን ልብሶች በመልበስ ተንቀሳቃሽ የንግድ ማስታወቂያዎች ለመሆን ሲሉ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል። “ሰርጊዮ ቫሌንቴ” የተባሉትን ጂንስ ልብሶች የሚያመርተው ኩባንያ ፕሬዘዳንት የሆኑት ኤሊ ካፕላን “ሰዎች ስም ይፈልጋሉ” ብለዋል። ይሁን እንጂ ስሙ በጂንስ ልብሶች ኪስ ላይ በጉልህ የተጠለፈው ሚስተር ቫሌንቴ ማን ነው? ኒውስዊክ “እንዲህ የሚባል ሰው የለም” ብሏል። ካፕላን ራሳቸው ሲያስረዱ “ኤሊ ካፕላን ጂንስ ብለን ብንሰይመው ኖሮ ማን ይገዛን ነበር?” በማለት ጠይቀዋል።

‘ታዲያ ፋሽን መከተል ስህተት ነውን?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ላይሆን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች በአካባቢያቸው ተወዳጅ የሆነውን አለባበስ ይከተሉ ነበር። ለምሳሌ ያህል ትዕማር ብዙ ኅብር ያለውን ልብስ ለብሳ ነበር፣ በዚያን ጊዜ “እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።​— 2 ሳሙኤል 13:​18

ይሁን እንጂ አንድ ሰው የፋሽን ተገዥ መሆን አለበት? አንዲት ወጣት ልጃገረድ “በአንድ ሱቅ ውስጥ ሁሉም ሰው የለበሰው የሚያምር ሱሪ አይና ‘እማማ፣ ይህን ሱሪ ግዢልኝ’ ስላት እርስዋ ደግሞ ‘እቤት እሰፋልሻለሁ’ ትለኛለች። እኔም ‘የምለው አልገባሽም። የምፈልገው ይህን ሱሪ ነው’ እላታለሁ” በማለት እሮሮ አሰምታለች። የሆነ ሆኖ የፋሽን ሞዴል አውጪዎች ተጎታች መሆን የራሳችሁን ማንነት ገፎ እውነተኛ ማንነታችሁ እንዲሰወር አያደርግምን? ለምን ቀስቃሽ የሆኑ የንግድ ማስታወቂያዎች፣ አርማዎችና የሞዴል ስሞች ይቆጣጠሯችኋል?

መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 12:​2 ላይ “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” በማለት ይነግረናል። የልብስ ምርጫችሁን በተመለከተ ‘እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው ፈቃዱ’ ምንድን ነው?

ልከኛና በሚገባ የተደራጀ ልብስ

በ1 ጢሞቴዎስ 2:​9 (አዓት) ላይ ክርስቲያኖች “በልከኝነትና በጭምት አእምሮ በሚገባ በተደራጀ አለባበስ ራሳቸውን እንዲሸልሙ” ያበረታታል። “በሚገባ የተደራጀ ልብስ” ደስ የሚልና ንጹሕ ነው። “ልከኝነት” ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባል። በጥሩ ሁኔታ የተሰፋ ሙሉ ልብስ በሥራ ቦታ ለመልበስ ተስማሚ ሊሆን ይችላል፤ በባሕር ዳር ለመዝናናት ግን አይሆንም! በተቃራኒ ደግሞ የዋና ልብስ ለብሶ ወደ ቢሮ መሄድ እንደ ማላገጥ ይቆጠራል።

በዚህም ምክንያት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ወይም ለሌሎች ሊሰብኩ በሚሄዱበት ጊዜ አለባበሳቸው እንደነገሩ ሳይሆን ወጣት የአምላክ አገልጋዮች እንደሆኑ የሚያሳውቃቸውን ልብስ መልበሳቸው ያሳስባቸዋል። ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 6:​3, 4 ላይ “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን [“እንገልጣለን” አዓት]” በማለት የተናገራቸውን ቃላት አስታውሱ።

በተጨማሪም ልከኝነት የሌሎችን ስሜት ግምት ውስጥ ያስገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው የአንድ ክርስቲያን ተግባሮች የራሱን ሕሊና ብቻ ሳይሆን ‘የሌላውን ሰው ሕሊና’ ጭምር ከግምት ያስገባሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:​29 አዓት) በተለይ እናንተ ወጣቶች ስለ ወላጆቻችሁ ሕሊና ማሰብ አይገባችሁምን?

ተገቢ አለባበስ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

መጽሐፍ ቅዱስ ንግሥት አስቴር ንጉሥ ወደሆነው ባሏ ፊት መቅረብ ፈልጋ ስለነበረበት ጊዜ ይናገራል። ይሁን እንጂ የንጉሡን ፈቃድ ሳያገኙ በፊቱ መቅረብ በሞት የሚያስቀጣ በደል ነበር! አስቴር አምላክ እንዲረዳት ከልብ ጸልያ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ “ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ” በመቅረብ ስለ መልኳና ቁመናዋ ልዩ ትኩረት አድርጋለች። ለወቅቱ የሚስማማ ልብስ ለብሳ ቀረበች! “ንጉሡም ንግሥቲቱ አስቴር በወለሉ ላይ ቆማ ባየ ጊዜ በዓይኑ ሞገስ አገኘች።”​— አስቴር 5:​1, 2

እናንተም የሚያምርና ልከኛ ልብስ መልበሳችሁ ሥራ ለማግኘት ቃለ መጠይቅ በሚደረግላችሁ ጊዜ ጥሩ ግምት እንድታገኙ ሊረዳችሁ ይችላል። የሥራ ዕድገት ማዕከል ዲሬክተር የሆኑ ቪኪ ኤል ባውም የሚባሉ ሴት “አንዳንድ ሴቶች የቃል ፈተና ለመውሰድ ሲዘጋጁ ግራ ይገባቸዋል። ከወንድ ጋር ተቀጣጥረው እንደመውጣት ይመስላቸውና የጾታ ስሜት በሚያነሳሳ ሁኔታ ተቆነጃጅተው ይቀርባሉ” ብለዋል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? “የሥራ ሰዎች ስለ መሆናቸው የሚሰጣቸውን ግምት ይቀንስባቸዋል።” “ሰውነትን የሚያጋልጡ ጠባብ ወይም የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ልብሶችን” እንዳይለብሱ እኚሁ ሴት ምክር ይሰጣሉ።

ወጣት ወንዶችም ቢሆኑ ሥራ ፍለጋ በሚሄዱበት ጊዜ ተስማሚ ልብስ ለመልበስ መጣር አለባቸው። የቀጣሪዎች “ፀጉር በሚገባ የተበጠረና ጫማቸውም በደንብ የተወለወለ ስለሆነ ሌሎች ሰዎችም እንደነርሱ እንዲያደርጉ የሚጠብቁ መሆናቸውን” ጆን ቲ ሞሌይ ገልጸዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ልከኛ ያልሆነ አለባበስ ከሌሎች ጋር የሚኖራችሁን ዝምድና ሊያበላሽባችሁ ይችላል። ሳይኮሎጂ ቱዴይ የተባለ መጽሐፍ “አጭር ቀሚስ፣ ቁምጣ፣ ጠባብ ጂንስ ሱሪዎች ወይም ደረትና ጡትን የሚያጋልጡ ልብሶች” መልበስ ለሩካቤ ሥጋ የሚጋብዙ እንደሆኑ ተደርገው በወንዶች ሊተረጎሙ እንደሚችሉ የሚያሳይ በጎረምሶችና በኮረዶች ላይ የተደረገ ጥናት መኖሩን አመልክቷል። አንድ ወጣት ሲናገር “እኔ በበኩሌ የወጣት ሴቶችን አለባበስ በማይበት ጊዜ ስለ እነርሱ ንጹሕ የሆነ ነገር ብቻ ለማሰብ ይከብደኛል” ብሏል። ልከኛ አለባበስ ግን ሰዎች ውስጣዊ ባሕሪዎቻችሁን እንዲገነዘቡና እንዲያደንቁ ዕድል ይሰጣቸዋል። አንድ ዓይነት አለባበስ ልከኛ ይሁን አይሁን እርግጠኞች ካልሆናችሁ የወላጆቻችሁን ምክር ጠይቁ።

“ውስጣዊውን ሰው” መልበስ

ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን “በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ” በማለት መክሯል። አዎን፣ ይህ ዓይነቱ ጌጥ በሰዎችም ፊት ዋጋው ከፍተኛ የሆነ ጌጥ ሊሆን ይችላል! (1 ጴጥሮስ 3:​4) የጊዜውን ፋሽን የተከተለ ልብስ አንዳንድ እኩዮቻችሁን ያስደንቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልብስ የሰዎችን ልብ ሊማርክ ወይም እውነተኛ ወዳጅ ሊያፈራ አይችልም። የሰዎችን ልብ ለመማረክ ወይም ወዳጅ ለማፍራት የሚቻለው “ውስጣዊውን ሰው” በመልበስ፣ ውስጣዊ ሰውነታችሁን ለመለወጥ በመጣር ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:​16 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ውስጣዊ ውበት ያለው ሰው በቅርብ ጊዜ የመጣውን ፋሽን ወይም የንግድ ምልክቶች “የተለጣጠፉበት” ልብስ ባይለብስም በሌሎች ዘንድ ማራኪ ሆኖ ይታያል።

ቀጥሎ የሚመጣውና ወጣቶች ወደ ሱቆች እንዲጎርፉ የሚያደርጋቸው ፋሽን ምን እንደሚሆን ማን ያውቃል? እናንተ ግን ለራሳችሁ የሚስማማችሁን አስባችሁ ልትመርጡ ትችላላችሁ። ከፍተኛ የአቋም ደረጃን የሚያንፀባርቁ አለባበሶችን አጥብቃችሁ ያዙ። የጾታ ስሜቶችን ለመቀስቀስ ታስበው ከተዘጋጁ የፋሽን ልብሶች ራቁ። ፋሽን በማሳደዱ ግልቢያ ውስጥ የመጀመሪያውም፣ የግዴታ የመጨረሻውም ሳትሆኑ መካከለኛ ሁኑ። ልብስ ስትገዙ ቶሎ ፋሽናቸው የሚያልፍባቸውን ሳይሆን ለረዥም ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉ ጥራት ያላቸውን ልብሶች ምረጡ። ልብሶቻችሁ በመገናኛ ብዙኃን ወይም በእኩዮቻችሁ የተለፈፈውን አንድ ዓይነት መልክ ሳይሆን እውነተኛ ማንነታችሁን እና ትክክለኛውን መልእክት የሚያስተላልፉ ልብሶች መሆናቸውን አረጋግጡ!

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ አለባበስ አንድ ዓይነት መልእክት የሚያስተላልፈው እንዴት ነው?

◻ አንዳንድ ወጣቶች በልብስ አመራረጣቸው ቅጥ የለሽ ወደመሆን የሚያዘነብሉት ለምንድን ነው?

◻ የልብስ ምርጫን በተመለከተ እኩዮቻችሁ ምን ያህል ተጽእኖ ያሳድሩባችኋል?

◻ ሁልጊዜ ፋሽን ልብስ ለመልበስ መጣር የሚያመጣቸው አንዳንድ ጉዳቶች ምንድን ናቸው?

◻ አንድ ፋሽን ‘ልከኛና ተስማሚ’ መሆኑን የሚወስነው ምንድን ነው?

[በገጽ 94 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አለባበሳችሁ በእርግጥ ማንነታችሁን የሚያሳይና ስለ ራሳችሁ ያላችሁን ስሜት የሚያመለክት ነው”

[በገጽ 91 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች ልጆቻቸው በሚለብሱት ልብስ ላይ ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ አይስማሙም። ይህ የሚሆነው ወላጆች ጊዜው ያለፈበት ፋሽን ስለሚመርጡ ብቻ ነውን?

[በገጽ 92 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ወጣቶች ከሰው የተለየ አለባበስ በመልበስ የግል ማንነታቸውን ለማሳየት ይሞክራሉ

[በገጽ 93 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለሁኔታዎቹ እንደሚስማማ ልበሱ። አለባበሳችሁ ስለ እናንተ መልእክት ያስተላልፋል!