በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከወንድሜና ከእህቴ ጋር መስማማት የሚያስቸግረኝ ለምንድን ነው?

ከወንድሜና ከእህቴ ጋር መስማማት የሚያስቸግረኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 6

ከወንድሜና ከእህቴ ጋር መስማማት የሚያስቸግረኝ ለምንድን ነው?

የወንድማማቾችና የእህትማማቾች ግጭት ከጥንት ከቃየንና ከአቤል ጊዜ ጀምሮ የኖረ ነገር ነው። ይህ ማለት ግን ወንድማችሁን ወይም እህታችሁን ትጠላላችሁ ማለት አይደለም። አንድ ወጣት እንደሚከተለው በማለት አምኗል:- “አሁን አይሰማኝ እንጂ በልቤ ወንድሜን እንደምወደው እገምታለሁ። የምወደው ይመስለኛል።”

በወንድማማቾችና በእህትማማቾች ዝምድና ውስጥ ብዙውን ጊዜ ግልጽ ሆኖ የማይታይ የጠላትነት ስሜት የሚኖረው ለምንድን ነው? ሀሪየት ዌብስተር የተባሉ ጸሐፊ የቤተሰብ ኑሮ አማካሪ የሆኑት ክላውዲያ ሽቫይዘር እንደሚከተለው በማለት እንደተናገሩ ጠቅሰዋል:- “እያንዳንዱ ቤተሰብ ያለው ቁሳዊና ስሜታዊ ንብረት የተመጠነ ነው። ወንድማማቾችና እህትማማቾች የሚጣሉት አብዛኛውን ጊዜ ከወላጅ ፍቅር ጀምሮ ገንዘብንና ልብስን የሚጨምሩትን የቤተሰብ ንብረቶችና ሀብቶች ስለሚሻሙ ነው።” ለምሳሌ ያህል ካሚልና አምስት ወንድሞቿና እህቶቿ በሦስት የመኝታ ክፍሎች በጋራ ይጠቀማሉ። “አንዳንድ ጊዜ ብቻዬን መሆን ስለምፈልግ” ትላለች ካሚል “ሁሉንም ከክፍሌ አስወጥቼ ልዘጋባቸው እፈልጋለሁ፣ እነርሱ ግን ሁልጊዜ እዚያው ናቸው።”

አንዳንድ መብቶችንና የቤት ውስጥ ኃላፊነቶችን በመካፈል ረገድም ብጥብጥ ሊነሳ ይችላል። ትልልቆቹ ልጆች የሚበዛው የቤት ውስጥ ሥራ በእነርሱ ላይ የሚጫን በመሆኑ የተቃውሞ መንፈስ ሊያሳዩ ይችላሉ። ትናንሾቹ ልጆች ደግሞ ትልልቆቹ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ሲያዟቸው እምቢ ይሉ ወይም ደግሞ እነርሱ የሚመኟቸው መብቶች ለታላላቅ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ብቻ ሲሰጡ ይቀኑ ይሆናል። ‘እህቴ መኪና መንዳት እየተማረች ነው። እኔ ግን አልተፈቀደልኝም’ በማለት አንዲት በአፍላ ጉርምስና የዕድሜ ክልል የምትገኝ እንግሊዛዊት ልጃገረድ ስሞታ አሰምታለች። ‘እህቴን በጥላቻ አያታለሁ፣ በማንኛውም ነገር እንድትቸገር ለማድረግ እጥራለሁ’ ትላለች።

አንዳንድ ጊዜ የወንድማማቾችና የእህትማማቾች አለመስማማት በጠባይ አለመጣጣም ምክንያት ብቻ የሚመጣ ነገር ሊሆን ይችላል። የአሥራ ሰባት ዓመቷ ዳያን ስለ ወንድሞቿና እህቶቿ ስትናገር “በየቀኑ ከጧት እስከ ማታ የምትተያዩ ከሆነና . . . ያው ሰው ያንኑ የሚያናድዳችሁን ነገር በየቀኑ ሲያደርግ ብትመለከቱ በጣም ያበሳጫችኋል” ብላለች። ወጣቱ አንድሬ ደግሞ “እቤት በምትሆኑበት ጊዜ . . . እውነተኛ ጠባያችሁ አይሸሸግም” በማለት ጨምሯል። የሚያሳዝነው ግን ‘የራሳችሁን እውነተኛ ማንነት አለመሸሸግ’ ብዙውን ጊዜ ጨዋነትን፣ ደግነትንና ሰውን ላለማስቀየም የሚደረገውን ዘዴኛነት አሽቀንጥሮ መጣል ማለት መሆኑ ነው።

በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚነሳው ሌላው የተለመደ የግጭት መንስዔ ወላጅ አንዱን ልጅ ከሌላው አስበልጦ መውደዱ (‘እማማ እኮ አስበልጣ የምትወደው አንተን/አንቺን ነው!’ እንደሚባለው ዓይነት) ነው። የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ሊ ሳልክ “ልጆች የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ግለሰቦች ስለሆኑና እኛ [ወላጆች] የምናደርግላቸው አያያዝ መለያየቱ ስለማይቀር አንዲት ወላጅ ሁሉንም ልጆቿን በእኩል ደረጃ ልትወድ የምትችልበት መንገድ የለም” በማለት አምነዋል። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ይደርስ የነበረ ነገር ነው። ጥንታዊ አበው የነበረው ያዕቆብ (እሥራኤል) “ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር።” (ዘፍጥረት 37:​3) የዮሴፍ ወንድሞች በጣም ይቀኑበት ነበር።

እሳቱን ማጥፋት

“እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል።” ይህን የሚለው ምሳሌ 26:​20 ነው። ብዙውን ጊዜ በደን ውስጥ አለፍ አለፍ ብሎ ዛፎችን በመቁረጥ ባዶ ቦታ በመተው የሰደድ እሳት እንዳይዛመት መከላከል ይቻላል። ቃጠሎ ከተነሳ አብዛኛውን ጊዜ የሚሄደው እስከ ተመነጠረው ገላጣ ሥፍራ ድረስ ስለሆነ ይጠፋል። በተመሳሳይም ጭቅጭቆች እንዳይነሱ ለማድረግ ወይም ቢያንስ ቁጥራቸውን ለመቀነስ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ። አንዱ መንገድ ጭቅጭቅ ከመነሳቱ በፊት ሐሳብ ለሐሳብ ተለዋውጦ አንድ ዓይነት መግባባት ላይ መድረስ ነው።

ለምሳሌ ያህል ችግራችሁ ብቻችሁን የምትሆኑበት ጊዜ ማጣት ነውን? ችግሩ ይህ ከሆነ በጉዳዩ ላይ በምትጨቃጨቁበት ጊዜ ሳይሆን ሰላም በምትሆኑበት ሌላ ጊዜ አንድ ላይ ተቀምጣችሁ ፕሮግራም አውጡ። (‘በእነዚህ ቀኖች/ሰዓቶች በክፍሉ ለብቻዬ ልጠቀምበት። አንተ/⁠አንቺ ደግሞ በእነዚህ ቀኖች/ሰዓቶች ለብቻህ/ለብቻሽ ተጠቀምበት⁠/ተጠቀሚበት’) ተባባሉ። ከዚያ በኋላ ስምምነታችሁን በማክበር “ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን።” (ማቴዎስ 5:​37) የፕሮግራም ለውጥ የሚጠይቅ ነገር ከመጣ ለወንድማችሁ/ለእህታችሁ ሳታስታውቁ ለውጡን ከማድረግ ይልቅ አስቀድማችሁ ንገሩት/ንገሯት።

የምትጣሉት የንብረት ባለመብት በመሆን ጉዳይ ላይ ነውን? በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የምትገኝ አንዲት ልጅ እንደሚከተለው በማለት አማራለች:- “የእንጀራ እናቴ ልጅ ሁልጊዜ ሳትጠይቀኝ በንብረቶቼ ትጠቀማለች። የድፍረቷ ብዛት በሜክአፔም እንኳን ሳይቀር ተጠቅማ የገዛሁት ጥሩ ዓይነት እንዳልሆነ ትነግረኛለች!” ይህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ ልትስማሙ ካልቻላችሁ ወላጆቻችሁ እንዲሸመግሏችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። የሚሻለው ነገር ግን በተረጋጋችሁበት ጊዜ ከወንድማችሁ ወይም ከእህታችሁ ጋር ቁጭ ብላችሁ መወያየት ነው። “በባለ ንብረትነት” መብት ላይ ከመነታረክ ይልቅ ‘ለማካፈል የተዘጋጃችሁ’ ሁኑ። (1 ጢሞቴዎስ 6:​18) መዋዋስን በተመለከተ የሌላውን ንብረት ከመውሰድ በፊት ሁልጊዜ መጠየቅን በመሳሰሉት የመዋዋስ ደንቦች ላይ ለመስማማት ሞክሩ። አስፈላጊ ከሆነ የራሳችሁን ምቾት መሥዋዕት አድርጋችሁ የምትስማሙበትን ሁኔታ ፈልጉ። እንዲህ ስታደርጉ እሳቱ ከመቀጣጠሉ በፊት ‘ሲጠፋ’ ለማየት ትበቃላችሁ!

ነገር ግን የወንድማችሁ ወይም የእህታችሁ ጠባይ ፈጽሞ እሾህ ቢሆንባችሁስ? በእርግጥ ጠባዩን ለመለወጥ አትችሉም። ስለዚህ ‘እርስ በርሳችሁ በፍቅር ተቻችላችሁ መኖርን ተለማመዱ።’ (ኤፌሶን 4:​2) የወንድማችሁን ወይም የእህታችሁን ጥፋትና ጉድለት ከማጋነን ይልቅ “የኃጢአትን ብዛት የሚሸፍነውን” ክርስቲያናዊ ፍቅር ሥራ ላይ አውሉ። (1 ጴ⁠ጥሮስ 4:​8) ነጭናጫና ስልቹ ወይም ክፉ ከመሆን ይልቅ “ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፣ ከአፋችሁም ስድብን” አስወግዳችሁ “ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን።” — ቆላስይስ 3:​8፤ 4:​6

ትክክል አይደለም!’

“እህቴ የፈለገችውን ነገር ሁሉ ታገኛለች” በማለት አንዲት ወጣት ታማርራለች። “እኔ ግን ፈጽሞ ተረስቻለሁ።” እንዲህ ዓይነት ስሞታ አጋጥሟችሁ ያውቃልን? ነገር ግን “የፈለገችውን ነገር ሁሉ” እና “ፈጽሞ” የሚሉትን የተጋነኑ አነጋገሮች ልብ በሉ። ሁኔታው በእርግጥ ይህን ያህል አስከፊ ነውን? ይህ የማይመስል ነገር ነው። ቢሆንም እንኳን ለሁለት የተለያዩ ግለሰቦች እኩል አያያዝ እንዲደረግላቸው መጠበቅ ትክክል ነውን? በእርግጥ ትክክል አይደለም! ወላጆቻችሁ ማዳላታቸው ሳይሆን ሁላችሁንም እንደ ግል ፍላጎታችሁና ጠባያችሁ ሊይዟችሁ ብለው ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ ወላጆች አንዱን ልጅ ከሌሎቹ አብልጠው ቢወዱ ማዳላት አይሆንባቸውምን? ላይሆን ይችላል። ያዕቆብ ልጁን ዮሴፍን እንዴት ይወደው እንደነበረ አስታውሱ። ምክንያቱ ምን ነበር? ዮሴፍ የሟችቱ የያዕቆብ ተወዳጅ ሚስት የራሔል ልጅ ስለነበረ ነው። ያዕቆብ ዮሴፍን ከሌሎቹ ልጆቹ አብልጦ መውደዱ ምክንያታዊ አይደለምን? ይሁን እንጂ ያዕቆብ ለዮሴፍ ያለው ፍቅር ሌሎቹን ልጆቹን ፈጽሞ እንዲረሳ አላደረገውም። ምክንያቱም ስለ እነርሱም ደህንነት ከልብ ያስብ ነበር። (ዘፍጥረት 37:​13, 14) ስለዚህ በዮሴፍ ላይ የሚቀኑበት በቂ ምክንያት አልነበራቸውም!

የእናንተ ወላጆችም በተመሳሳይ ከወንድማችሁ ወይም ከእህታችሁ ጋር በጋራ የሚደሰቱበት ነገር ስላለ፣ አንድ ዓይነት ጠባይ ስላላቸው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሣ ከእናንተ ይበልጥ ያቀርቧቸው ይሆናል። ይህ ማለት ግን እናንተን አይወዷችሁም ማለት አይደለም። ጥላቻ ወይም ቅናት ከተሰማችሁ ፍጹም ያልሆነው ልባችሁ እንዳሸነፋችሁ ተገንዘቡ። እንደነዚህ ዓይነቶቹን ስሜቶች ለማሸነፍ ጣሩ። የሚያስፈልጓችሁ ነገሮች እስከተሟሉላችሁ ድረስ ወንድማችሁ ወይም እህታችሁ ለየት ያለ ትኩረት ያገኘ/ያገኘች ቢመስላችሁ ለምን ትረበሻላችሁ?

ወንድሞችና እህቶች በረከቶች ናቸው

ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ በተለይ በሚያበሳጯችሁ ጊዜ በረከቶች መሆናቸውን ለማመን አዳጋች ሆኖ ሊታያችሁ ይችላል። ወጣቷ ዳያን ግን “ወንድሞችና እህቶች መኖራቸው ያስደስታል” በማለት ታሳስበናለች። ሰባት ወንድሞችና እህቶች አሏት። “የምታዋሩትና የሚያስደስታችሁን ነገር የምታካፍሉት ሰው አላችሁ ማለት ነው።”

አን ማሪ እና ወንድሟ አንድሬ እንደሚከተለው በማለት ይጨምራሉ:- “ከጓደኞቻችሁ ጋር ሆናችሁ ወደ አንዳንድ ቦታዎች ልትሄዱ ብትችሉም ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው። አንድ ጨዋታ ለመጫወት ወይም ስፖርት ለመሥራት ወይም ወደ መናፈሻ ለመሄድ ብትፈልጉ ሁልጊዜ ልታገኟቸው የምትችሉት እነርሱን ነው።” ዶና ደግሞ “የቤት ውስጥ ሥራችሁን የሚያግዛችሁ ሰው አለላችሁ ማለት ነው” በማለት ወንድምና እህት መኖራቸው የሚያስገኘውን ሌላ ተግባራዊ ጥቅም አመልክታለች። ሌሎች ደግሞ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን “ልዩ አማካሪና አድማጭ” እንዲሁም “ስሜቴን የሚረዳልኝ⁠/የምትረዳልኝ” በማለት ይገልጻሉ።

ወደፊት አሁን ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር ያጋጠሟችሁ ችግሮች ከሌሎች ሰዎችም ጋር ያጋጥሟችኋል። ቅናት፣ የንብረት ባለመብትነት፣ በእኩል ዓይን አለመታየት፣ ለብቻችሁ የምትሆኑበት ጊዜና ቦታ ማጣት፣ ራስ ወዳድነት፣ የባሕርይ ልዩነትና የመሳሰሉት ችግሮች ሁሉ የሕይወት ክፍሎች ናቸው። ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር ተስማምታችሁ መኖርን መልመዳችሁ ወደፊት ለሚያጋጥሟችሁ የሰብዓዊ ዝምድና መስኮች ጥሩ ሥልጠና ይሰጣችኋል።

የአሥራ ሰባት ዓመቱ አንድሬ “ከምታዩአቸው ሰዎች ጋር ልትስማሙ ካልቻላችሁ ከማታዩት ከይሖዋ ጋር እንዴት ልትስማሙ ትችላላችሁ?” በማለት በ1 ዮሐንስ 4:​20 ላይ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት አስተጋብቷል። ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር በየጊዜው አለመግባባት መፈጠሩ አይቀርም። ይሁን እንጂ አብሮ መካፈልን፣ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግንና ከእኔ ይቅር ማለትን ልትማሩ ትችላላችሁ። እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋችሁ ምን ጥቅም ያስገኝላችኋል? ወንድም ወይም እህት ያላችሁ መሆኑ መጥፎ ነገር አለመሆኑን ለመገንዘብ ትችላላችሁ።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ብዙ ጊዜ የሚጋጩት ለምን ድን ነው?

◻ ብቻችሁን ለመሆን በመፈለግና በንብረት ባለመብትነት ጉዳይ ላይ የሚነሳውን ጥል ልታስወግዱ የምትችሉት እንዴት ነው?

◻ ወላጆች አንዳንድ ጊዜ አንዱን ልጅ አብልጠው የሚወዱት ለምንድን ነው? ይህን ማድረጋቸው ከአግባብ ውጭ ይመስላችኋልን?

◻ ወንድምና እህት የሌለው ልጅ የሚያጣው ጥቅም አለን?

◻ ወንድሞችና እህቶች መኖራቸው ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

[በገጽ 52 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ልጆች የተለያዩ ግለሰቦች በመሆናቸው አንድ ወላጅ ሁሉንም በእኩል ደረጃ ሊወድ የሚችልበት መንገድ የለም።”​—⁠የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር ሊ ሳልክ

[በገጽ 54 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ወንድምም እህትም የለኝም’

ያላችሁበት ሁኔታ ይህ ከሆነ የቀረባችሁ ነገር ላይኖር ይችላል። አንደኛ ነገር ብዙ ወጣቶች ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር ለመስማማት ችግር ሲገጥማቸው እናንተ ግን (በወላጆቻችሁ ፈቃድ) የሚስማሟችሁን የቅርብ ጓደኞች ለመምረጥ ትችላላችሁ። እንዲያውም ለጥናት፣ ለማሰላሰል ወይም አንዳንድ የእጅ ሞያዎችን ወይም ችሎታዎችን ለማዳበር የበለጠ ጊዜ ልታገኙ ትችላላችሁ።—ስለ ብቸኝነት የሚናገረውን ምዕራፍ 14ን ተመልከቱ።

ወጣቱ ቶማስ “ወንድም ወይም እህት የሌለኝ በመሆኔ የወላጆቼን ሙሉ ትኩረት አገኛለሁ” በማለት አንድ ልጅ መሆን ያለውን ሌላ ጥቅም ያመለክታል። እውነት ነው፣ ከልክ ያለፈ የወላጅ ትኩረት ማግኘት አንድን ወጣት ራስ ወዳድ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። ወላጆች በትኩረት አሰጣጣቸው ሚዛናዊ ከሆኑ ግን የወላጆቻችሁን ትኩረት ማግኘታችሁ ወንድሞችና እህቶች ካላቸው ልጆች ይልቅ በቶሎ ብስለት እንድታገኙና ከትላልቅ ሰዎች ጋር በምትሆኑበት ጊዜ የተዝናና መንፈስ እንዲኖራችሁ ይረዳችኋል።

ይሁን እንጂ ነገሮችን የምታጋሯቸው ወንድሞች ወይም እህቶች የሌላችሁ መሆኑ ራስ ወዳዶች እንድትሆኑ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ኢየሱስ “መስጠትን ልማድ አድርጉ” በማለት መክሯል። (ሉቃስ 6:​38 አዓት ) ያሏችሁን ነገሮች ከጓደኞችና ከዘመዶች ጋር ለመካፈል ሞክሩ። ሌሎች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች እያሰባችሁ በምትችሉት ሁሉ እርዷቸው። ሰዎች እንዲህ ላለው ልግስና የአመስጋኝነት ምላሽ ይሰጣሉ። እንዲህ በማድረግም ወንድም ወይም እህት የሌላችሁ ብትሆኑም እንኳ ብቸኛ እንዳልሆናችሁ ትገነዘባላችሁ።

[በገጽ 53 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እህት የሌለኝ መሆኔ ብዙ ጊዜ ያሳዝነኛል፤ ሆኖም እህት የሌለኝ በመሆኔ ያገኘኋቸው ጥቅሞች አሉ