በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡኝ ለማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ወላጆቼ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡኝ ለማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 3

ወላጆቼ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡኝ ለማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

እናንተ አሁን አድገናልና ቅዳሜና እሁድ እውጭ አምሽተን ለመምጣት እንችላለን ትላላችሁ። ወላጆቻችሁ ደግሞ በጊዜ እቤት መግባት አለባችሁ ይላሉ። እናንተ ሰው ሁሉ ሲያወራለት የሰማነውን ፊልም ለማየት እንፈልጋለን ስትሉ እነርሱ ደግሞ ማየት የለባችሁም ይላሉ። እናንተ ጥሩ ጓደኛ ስላገኘን አብረን ለመጫወት እንሂድ ስትሉ ወላጆቻችሁ ደግሞ በመጀመሪያ ጓደኛችሁን ለመተዋወቅ እንደሚፈልጉ ይነግሯችኋል።

ወደ ጉርምስና የዕድሜ ክልል በምትደርሱበት ጊዜ አንዳንድ ጊዜ ወላጆቻችሁ መፈናፈኛ ያሳጧችሁ ሊመስላችሁ ይችላል። “እፈልጋለሁ” የምትሉት ነገር ሁሉ “አይሆንም፣ አትችሉም” የሚል መልስ የሚያስከትል መስሎ ይታያችኋል። ማንኛውም የሕይወታችሁ ክፍል ወላጆቻችሁ ከሚያደርጉት “የዓይነ ቁራኛ” ክትትል ሊያመልጥ የማይችል ይሆንባችኋል። የ15 ዓመቷ ዴቢ “አባቴ ሁልጊዜ የት እንደምውልና እቤት በስንት ሰዓት እንደምመለስ ለማወቅ ይፈልጋል። ብዙ ወላጆች እንዲህ ያደርጋሉ። ግን ሁሉን ነገር ማወቅ ይኖርባቸዋል እንዴ? ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጡኝ ይገባቸዋል” ትላለች።

በተጨማሪም ወጣቶች ወላጆቻቸው እንደማያከብሯቸው ቅሬታ ሲያሰሙ ይታያሉ። አንድ ጥፋት ሲፈጸም ጥፋተኞች መሆናቸው ሳይረጋገጥ ወላጆቻቸው በጥፋተኝነት ይፈርዱባቸዋል እንጂ አያምኗቸውም። ወላጆች ልጆቻቸው የራሳቸውን ምርጫ እንዲያደርጉ በመፍቀድ ፈንታ አድርግ አታድርግ በሚሉ ሕጎች ይተበትቧቸዋል።

የአእምሮ ጭንቀት”

ወላጆቻችሁ አንዳንድ ጊዜ እንደ ሕፃናት ይመለከቷችኋልን? ይህን የመሰለ አመለካከት ካላቸው በእርግጥ ሕፃናት የነበራችሁበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ አስታውሱ። ራሳችሁን መርዳት የማትችሉ ሕፃናት የነበራችሁበት ጊዜ አሁንም ትዝ ስለሚላቸው ከወላጆቻችሁ አእምሮ በቀላሉ ሊፋቅ አይችልም። ስትፈጽሟቸው የነበሩትን የልጅነት ስህተቶች እስከ አሁን ድረስ ስለሚያስታውሱ እናንተ ፈለጋችሁም አልፈለጋችሁ፣ አሁንም ስህተት እንዳትሠሩ ሊጠብቋችሁ ይፈልጋሉ።

እናንተን ከክፉ ለመጠበቅ ያላቸው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው። አባባና እማማ ለእናንተ መጠለያ፣ ልብስና ምግብ ለማቅረብ ከሚሠሩት ሥራ ፋታ በሚያገኙበት ጊዜ ሁሉ እናንተን ለማስተማር፣ ለማሠልጠንና አዎን፣ እናንተን ከጉዳትና ከስህተት ለመጠበቅ ይጥራሉ። ለእናንተ የሚያሳዩትን አሳቢነት እንደ ቀላል ነገር አድርገው አይመለከቱም። እናንተን ስለሚያሳድጉበት ሁኔታ በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች ናቸው። (ኤፌሶን 6:​4) ደህንነታችሁ በአደጋ ላይ የወደቀ በሚመስላቸው ጊዜ ደግሞ ይጨነቃሉ።

የኢየሱስ ክርስቶስን ወላጆች አስቡ። ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ሲመለሱ ሳያስቡት ኢየሱስን ትተው ጉዟቸውን ጀምረው ነበር። ከእነርሱ ጋር እንደሌለ በተረዱ ጊዜ አጥብቀው እንዲያውም ተጨንቀው ፈለጉት! በመጨረሻ “በቤተ መቅደስ ባገኙት” ጊዜ የኢየሱስ እናት “ልጄ ሆይ፣ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፣ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” አለችው። (ሉቃስ 2:​41–48፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) የኢየሱስ ወላጆች ፍጹም ለነበረው ልጃቸው ይህን ያህል ከተጨነቁ የእናንተ ወላጆች ምን ያህል ብዙ ሊያስጨንቁ የሚችሉ ምክንያቶች እንደሚኖሯቸው ገምቱ!

ለምሳሌ ያህል እቤት መግባት ስለሚኖርባችሁ ሰዓት ነጋ ጠባ የምትሰሙትን ውትወታ እንውሰድ። ወላጆቻችሁ ይህን ያህል ቁጥጥር የሚያደርጉበት ምክንያት ምናልባት አይገባችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ ነገሮችን በወላጆቻችሁ አመለካከት ተመልክታችሁ ታውቃላችሁን? በተማሪነት የዕድሜ ክልል የሚገኙት ዘ ኪድስ ቡክ አባውት ፔረንትስ የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲዎች ነገሮችን በወላጆቻቸው አመለካከት ለማየት ሞክረዋል። እነዚህ ደራሲዎች “ልጆች በተገቢው ሰዓት እቤት ካልገቡ ወላጆች ልጆቻቸው ያደርጋሉ ብለው የሚያስቧቸውን ነገሮች” ዘርዝረዋል። ‘አደንዛዥ ዕፆችን ሲወስዱ፣ የመኪና አደጋ ሲያጋጥማቸው፣ በመናፈሻዎች ውስጥ ተጎልተው አላፊ አግዳሚውን ሲለክፉ፣ ሲታሰሩ፣ የጾታ ብልግና ወደሚታይባቸው ፊልሞች ሲሄዱ፣ አደንዛዥ ዕፆችን ሲሸጡ፣ ተገደው ሲደፈሩ ወይም ታፍነው ሲወሰዱ፣ ወህኒ ቤት ሲገቡና በዚህም ምክንያት በቤተሰቡ ስም ላይ ስድብ ሲያመጡ’ እንደሚታያቸው ገልጸዋል።

ልጆቻቸው በሰዓቱ እቤት ባለመግባታቸው ምክንያት ወደዚህ ዓይነቱ የተጋነነ መስሎ የሚታይ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱት ሁሉም ወላጆች አይደሉም። ይሁን እንጂ ብዙ ወጣቶች እንደነዚህ ያሉትን ድርጊቶች መፈጸማቸው እውነት አይደለምን? ስለዚህ ከቤት ውጭ መቆየት መጥፎ ባልንጀርነት ሲታከልበት አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የሚቀርብላችሁን ምክር መቃወም ይኖርባችኋልን? የኢየሱስ ወላጆች እንኳን ልጃቸው የት እንዳለ ለማወቅ ፈልገዋል!

ወላጆች አላፈናፍን የሚሉበት ምክንያት

አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው ይህን ያህል በልጆቻቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚሰጉት ጤነኛ አእምሮ ባይኖራቸው ይሆናል ብለው ያስባሉ! ይሁን እንጂ እናንተን ለማሳደግ የደረሰባቸው የጊዜና የስሜት ወጪ በጣም ከፍተኛ መሆኑን አስታውሱ። ማደጋችሁንና ጥላችኋቸው የምትሄዱ መሆናችሁን ሲያስቡ ሊረበሹ ይችላሉ። አንዲት ወላጅ ስትጽፍ “ወንድ ልጄ፣ አንድያ ልጄ ነው፣ አሁን አሥራ ዘጠኝ ዓመቱ ነው። ከቤት ለቆ የሚሄድ መሆኑን ማሰቡ ራሱ ከአቅሜ በላይ ነው” ብላለች።

በዚህም ምክንያት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከመጠን በላይ በመጠበቅ አላፈናፍን ይሏቸዋል። የሆነ ሆኖ ወላጆቻችሁ እንዲህ በሚሆኑበት ጊዜ እናንተም በአጸፋው ይለይላቸው ብላችሁ ከቁጥጥር ውጭ ለመሆን ብትጥሩ በእርግጥ ስህተት መፈጸማችሁ ነው። አንዲት ወጣት ሴት ያለፈውን አስታውሳ ስትጽፍ እንደሚከተለው ብላለች:- “18 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ እኔና እናቴ በጣም እንቀራረብ ነበር። . . . እያደግሁ ስሄድ [ግን] ችግሮች ያጋጥሙን ጀመር። ከእናቴ ቁጥጥር ውጭ ለመሆን እጣጣር ጀመር፤ እርሷም ይህን ጥረቴን ዝምድናችንን እንደሚያበላሽ ነገር አድርጋ ሳትመለከተው አልቀረችም። በዚህ ምክንያት አጥብቃ ልትይዘኝ መጣር ስትጀምር እኔ ደግሞ በአጸፋው ይበልጥ እየራቅሁ ሄድሁ።”

መጠነኛ ነፃነት ማግኘት ጥሩ ቢሆንም ለዚህ ብላችሁ የቤተሰባችሁን ጥሩ ዝምድና አታበላሹ። ታዲያ ከወላጆቻችሁ ጋር ያላችሁን ዝምድና በጋራ በመግባባት፣ በመቻቻልና በአክብሮት ላይ በተመሠረተ ብስለት ልትይዙ የምትችሉት እንዴት ነው? ከሁሉ በፊት መገንዘብ ያለባችሁ ነገር አክብሮት አክብሮትን የሚወልድ መሆኑን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ ጊዜ እንደሚከተለው ሲል አሳስቦ ነበር:- “እኛ ሁላችን የሚቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር።” (ዕብራውያን 12:​91980 ትርጉም፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) የእነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች አባቶች የማይሳሳቱ ሰዎች አልነበሩም። ጳውሎስ ቀጥሎ (በቁጥር 10 ላይ) “እነርሱ [ሰብዓዊ አባቶቻችን] መልካም መስሎ እንደታያቸው ለጥቂት ጊዜ ቀጥተውናል” ብሏል።​— የ1980 ትርጉም

እነዚህ ወላጆች የሚሳሳቱባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ልጆቻቸው ሊያከብሯቸው ይገባቸው ነበር። የእናንተም ወላጆች መከበር ይገባቸዋል። አጥብቀው ስለሚቆጣጠሯችሁና ስለማያፈናፍኗችሁ ብቻ ልታምፁባቸው አትችሉም። ራሳችሁ ልታገኙ የምትፈልጉትን አክብሮት ለወላጆቻችሁም ስጡ።

አለመግባባቶች

ከቁጥጥራችሁ ውጭ በሆነ ምክንያት ከተለመደው ሰዓት አሳልፋችሁ ቤት የገባችሁበት ጊዜ አለ? ታዲያ ወላጆቻችሁ ተቆጥተው ነበርን? እንዲህ ዓይነቶቹ አጋጣሚዎች የወላጆቻችሁን አክብሮት ለማግኘት የሚያስችሏችሁ አጋጣሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ወጣቱ ኢየሱስ ተጨንቀው ይፈልጉት የነበሩት ወላጆቹ እስኪያገኙት ድረስ በቤተ መቅደስ ከአንዳንድ መምህራን ጋር የአምላክን ቃል በመነጋገር እንዴት ያለ ጨዋነት እንዳሳየ አስታውሱ። ኢየሱስ ወላጆቹ ውስጣዊ ፍላጎቱን መጠራጠራቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተሰምቶት በስሜት ግንፋሎት ለመናገር፣ ለማልቀስ ወይም ለመነጫነጭ ተገፋፍቶ ነበርን? በእርጋታ የሰጠውን መልስ አስተውሉ:- “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው። (ሉቃስ 2:​49) ኢየሱስ በዚህ አነጋገሩ ባሳየው ብስለት ወላጆቹ እንደተደነቁ አያጠራጥርም። ስለዚህ ‘የለዘበ መልስ’ መስጠታችሁ ‘ቁጣን ለማብረድ’ ብቻ ሳይሆን የወላጆቻችሁን አክብሮት ለማግኘት እንድትችሉም ይረዳችኋል።​— ምሳሌ 15:​1

ሕጎችና ደንቦች

ወላጆቻችሁ የሚያደርጉላችሁ አያያዝ በአብዛኛው ለሚሰጧችሁ ትእዛዝና ጥያቄ በምትሰጡት አቀባበል ይወሰናል። አንዳንድ ወጣቶች ያኮርፋሉ፣ ይዋሻሉ፣ ወይም ደግሞ በግልጽ እምቢተኞች ይሆናሉ። እናንተ ግን ከዚህ የተሻለ የአዋቂነት አቀራረብ እንዲኖራችሁ ጣሩ። እውጭ ዘግይታችሁ እንድትመጡ እንዲፈቅዱላችሁ ከፈለጋችሁ “ሁሉም ልጆች እውጭ ዘግይተው ሲመጡ ወላጆቻቸው አይቆጧቸውም” ብላችሁ የሕፃን ጥያቄ አታቅርቡ ወይም አትነጫነጩ። አንድሪያ ኤገን የተባሉ ጸሐፊ እንደሚከተለው በማለት ይመክራሉ:- “[ወላጆቻችሁ] ሁኔታውን እንዲረዱላችሁ ለማድረግ የምትፈልጉት ምን እንደሆነ በተቻላችሁ መጠን አብራርታችሁ [ንገሯቸው] . . . የትና ከማን ጋር እንደምትሄዱ፣ እንዲሁም ከቤት ውጭ ለመቆየት አስፈላጊ ሆኖ ያገኛችሁበትን ምክንያት ከነገራችኋቸው . . . እሺ ሊሏችሁ ይችላሉ።”

ወይም ደግሞ ወላጆቻችሁ ከጓደኞቻችሁ መካከል ይኼ ጥሩ ነው ያ ደግሞ መጥፎ ነው ብለው ለማማረጥ ቢፈልጉ ይህን ማድረጋቸው ተገቢ በመሆኑ እንደ ሕፃናት አትነጫነጩ። ሰቨንቲን የተሰኘ መጽሔት “ከማሞ ጋር ፊልም ለማየት እሄዳለሁ ስትል፣ አባትህ ክፍሉ ውስጥ ሆኖ ‘ማሞ? ማሞ ደግሞ ማን ነው?’ ብሎ እንዳይጮህብህ ጓደኞችህን በየጊዜው ወደ ቤት አምጣቸው” በማለት ሐሳብ ያቀርባል።

‘ላለው ይጨመርለታል’

ጂም ታናሽ ወንድሙ ስለሆነው ስለ ሮን ሲናገር ሳቁ ይመጣበታል። “በመካከላችን ያለው የዕድሜ ልዩነት 11 ወራት ብቻ ነው” ይላል። “ነገር ግን ወላጆቻችን የሚያደርጉልን አያያዝ በጣም ይለያያል። ለእኔ በጣም ብዙ ነፃነት ይሰጡኛል። የቤተሰቡን መኪና እንድነዳ ይፈቀድልኛል። እንዲያውም አንድ ጊዜ አንድ ትንሽ ወንድሜን ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ይዤ እንድሄድ ፈቅደውልኝ ነበር።

“ለሮን ግን ሁኔታው የተለየ ነው” ይላል ጂም በመቀጠል። “እንዲያውም ብዙ ነፃነት ተሰጥቶት አያውቅም። ዕድሜው ቢደርስም አባባ መኪና መንዳት ሊያስተምረው አልፈለገም። ከተቃራኒ ፆታ ጋር አብሮ ለመውጣት ዕድሜው እንደሚፈቅድ በተሰማው ጊዜም ወላጆቼ አልፈቀዱለትም።”

ታዲያ እነዚህ ወላጆች ማዳላታቸው ነበርን? አይደለም። ጂም እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “ሮን ኃላፊነት አይሰማውም ነበር። አስቦ የመሥራት ችሎታ ይጎድለዋል። ብዙ ጊዜ እንዲሠራ የታዘዘውን ሥራ ሳይጨርስ ይቀራል። እኔ ወላጆቼ ሲቆጡኝ ፈጽሞ መልስ ሰጥቼ አላውቅም፣ እርሱ ግን በሐሳባቸው እንደማይስማማ ሳይገልጽላቸው አያልፍም። በአጸፌታው ደግሞ እነርሱ የእርሱን ጥያቄ ስለማይቀበሉ ነገሩ መልሶ በራሱ ላይ ይጠመጠምበታል።” ኢየሱስ በማቴዎስ 25:​29 ላይ “ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” ብሏል።

ታዲያ ተጨማሪ ነፃነትና ኃላፊነት እንዲሰጣችሁ ትፈልጋላችሁን? እንግዲያውስ ኃላፊነት የሚሰማችሁ መሆናችሁን በተግባር አሳዩ። ወላጆቻችሁ እንድትሠሩ የሚሰጧችሁን ሥራ ሁሉ ችላ አትበሉ። ከኢየሱስ ምሳሌዎች ውስጥ በአንዱ እንደተጠቀሰው ወጣት አትሁኑ። ይህ ወጣት አባቱ “ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ” ሲለው “እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም።” (ማቴዎስ 21:​28–30) ወላጆቻችሁ አንድ ነገር እንድትሠሩ ሲያዟችሁ ሥራው ትንሽም ሆነ ትልቅ ተጠናቅቆ እንደሚጠብቃቸው እንዲተማመኑባችሁ አድርጉ።

“ኃላፊነት መሸከም የምችል መሆኔን ለወላጆቼ አሳይቻለሁ” በማለት ጂም ይናገራል። “ወደ ባንክ ቤትም ሆነ የመብራትና የውኃ ሂሣብ እንድከፍል ይልኩኛል። ወደ ገበያ ሄጄ ሸቀጦችን እሸምታለሁ። እናቴ ከቤት ውጭ ወጥታ ሥራ መሥራት ባስፈለጋት ጊዜ የቤተሰቡን ምግብ ሳይቀር አበስል ነበር።”

አስቦ መሥራት

ወላጆቻችሁ እንዲህ ዓይነቶቹን ሥራዎች እንድትሠሩ አዘዋችሁ የማያውቁ ከሆነስ? የተለያዩ ነገሮችን በራሳችሁ ተነሳስታችሁ ለመሥራት ሞክሩ። ሰቨንቲን የተባለው መጽሔት “ለቤተሰቦቻችሁ ምግብ መሥራት እንደምትፈልጉ ሐሳብ አቅርቡ። ሁሉንም ነገር፣ ለምሳሌ ለቤተሰቡ የሚዘጋጀውን የምግብ ዓይነት መምረጥ፣ ከገበያ የሚገዙትን የምግብ ሸቀጦች ዝርዝር ማውጣት፣ የገንዘብ ወጪውን መመደብ፣ መገብየት፣ ማብሰልና የምግብ ዕቃዎቹን ማጣጠብ የመሳሰሉትን ሁሉ ራሳችሁ ለመሥራት እንደምትፈልጉ ለወላጆቻችሁ ንገሯቸው” በማለት ያሳስባል። ምግብ ለማብሰል ችሎታው ከሌላችሁ ሌላ የሚሠራ ነገር ፈልጉ። የሚታጠቡ ድስቶችና ሣህኖች፣ ያልተጠረጉ ወለሎች ወይም መስተካከል ያለባቸው ክፍሎች ካሉ ወላጆቻችሁ ትእዛዝ እስኪሰጧችሁ መጠበቅ የለባችሁም።

ብዙ ወጣቶች ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ጊዜ ወይም ቅዳሜና እሁድ የትርፍ ጊዜ ሥራ ይይዛሉ። እናንተም እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ገንዘባችሁን መቆጠብ እና በአግባቡ መያዝ እንደምትችሉ በተግባር አሳይታችኋልን? ለመኖሪያችሁና ለምግባችሁ ለሚያስፈልገው ወጪ በፈቃደኝነት የገንዘብ መዋጮ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናችሁን አስታውቃችኋልን? (በአካባቢያችሁ አንድ ክፍል ለመከራየት ምን ያህል እንደሚያስከፍል ብትጠይቁ ምን ያህል ማዋጣት እንደሚኖርባችሁ ሐሳብ ለማግኘት ትችላላችሁ።) እንዲህ ማድረጋችሁ የኪስ ገንዘባችሁን ሊቀንስባችሁ ይችላል፣ ይሁን እንጂ ወላጆቻችሁ በገንዘብ አያያዝ ረገድ የምታሳዩትን ብስለት ሲመለከቱ ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጧችሁ እንደሚፈልጉ ጥርጥር የለውም።

ከእናት ጉያ መውጣት

ወላጆቻችን ምሥጢራችንን የምንነግራቸው ጓደኞቻችንና መካሪዎቻችን መሆን ይኖርባቸዋል። (ከኤርምያስ 3:​4 ጋር አወዳድሩ።) ይህ ሲባል ግን እያንዳንዷን ጥቃቅን ውሳኔ እነርሱ እንዲያደርጉላችሁ ማድረግ አለባችሁ ማለት አይደለም። ውሳኔ ለማድረግ ችሎታ እንዳላችሁ እምነት ሊጣልባችሁ የሚችለው ‘የማሰብ ችሎታችሁን’ ስትጠቀሙበት ብቻ ነው።​— ዕብራውያን 5:​14

ስለዚህ ጥቃቅን ችግሮች ባጋጠሟችሁ ቁጥር ወደ ወላጆቻችሁ ከመሮጥ ይልቅ በመጀመሪያ አእምሯችሁን አሠሩትና ችግሩን ለመፍታት ሞክሩ። ስለ ነገሮች በጣም “ችኩል” ወይም በስሜት የምትነዱ ከመሆን ይልቅ በመጀመሪያ ‘እውቀትን አስተውሉ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተሉ። (ኢሳይያስ 32:​4) በተለይ ጉዳዩ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት የሚመለከት ከሆነ አንዳንድ ምርምሮችን አድርጉ። ረጋ ብላችሁ ነገሮችን ካመዛዘናችሁ በኋላ ወደ ወላጆቻችሁ ቀርባችሁ ስለ ችግሩ አወያዩአቸው። ሁልጊዜ ‘አባባ፣ ምን ላድርግ?’ ወይም ‘እማማ፣ አንቺ ብትሆኚ ኖሮ ምን ታደርጊ ነበር?’ ብላችሁ ከመጠየቅ ይልቅ ሁኔታውን ለወላጆቻችሁ አስረዱ። ጉዳዩን አውጥታችሁ አውርዳችሁ የደረሳችሁበትን መደምደሚያ አሳውቋቸው። ከዚያ በኋላ የእነርሱን አስተያየት ጠይቁ።

በዚህ ጊዜ ወላጆቻችሁ እንደ ሕፃን ሳይሆን እንደ አዋቂ ሰው መናገር መጀመራችሁን ይመለከታሉ። መጠነኛ ነፃነት ሊሰጣችሁ የምትገቡ አዋቂዎች መሆን መጀመራችሁን ለማሳየት የሚያስችላችሁ አንድ ትልቅ እርምጃ ወሰዳችሁ ማለት ነው። ወላጆቻችሁም እንደ አዋቂ ሰው አድርገው ሊመለከቷችሁ ሊጀምሩ ይችላሉ።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅና የት እንዳሉ ለማወቅ አጥብቀው የሚፈልጉት ለምንድን ነው?

◻ ወላጆቻችሁን በአክብሮት መመልከታችሁ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ከወላጆቻችሁ ጋር የሚኖራችሁ አለመግባባት እንዴት መፈታት ይኖርበታል?

◻ ከወላጆቻችሁ ሕጎችና ደንቦች ሳትወጡ አንዳንድ ነፃነቶች ሊኖሯችሁ የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ ኃላፊነት የሚሰማችሁ መሆናችሁን ለወላጆቻችሁ ልታሳዩ የምትችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አባቴ ሁልጊዜ የት እንደምውልና እቤት በስንት ሰዓት እንደምመለስ ለማወቅ ይፈልጋል። . . . ግን ሁሉን ነገር ማወቅ ይኖርባቸዋል እንዴ?”

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቻችሁ ተብትበው የያዟችሁ መስሎ ይሰማችኋልን?

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አለመግባባት ሲነሳ የለዘበ መልስ መስጠት አክብሮት የሚገኝበት አንዱ መንገድ ነው።