በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ አስተሳሰቤንና ስሜቴን የማይረዱልኝ ለምንድን ነው?

ወላጆቼ አስተሳሰቤንና ስሜቴን የማይረዱልኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 2

ወላጆቼ አስተሳሰቤንና ስሜቴን የማይረዱልኝ ለምንድን ነው?

ማንም ሰው ሌሎች ስሜቱንና አስተሳሰቡን እንዲረዱለት ይፈልጋል። ወላጆቻችሁ እናንተ የምትወዱትን ነገር ወይም አስፈላጊ ነው ብላችሁ የምታስቡትን ነገር ሲያናንቁባችሁ በጣም ልትበሳጩ ትችላላችሁ።

የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የሆነው ሮበርት አባቱ የሙዚቃ ምርጫውን እንደማይረዳለት ይሰማዋል። “‘ዝጋው!’ ብሎ ይጮህብኛል” ይላል ሮበርት። “ስለዚህ ሙዚቃውንም እርሱንም እዘጋቸዋለሁ።” ብዙ ወጣቶችም ወላጆቻቸው ስሜታቸውን የማይረዱላቸው መስሎ በሚሰማቸው ጊዜ ራሳቸውን አግልለው ራሳቸው በፈጠሩት የግል ዓለም ውስጥ መኖር ይጀምራሉ። በወጣቶች ላይ በተደረገ አንድ ሰፊ ጥናት መሠረት ጥናት ከተደረገባቸው ወጣቶች ውስጥ 26 በመቶ የሚሆኑት “አብዛኛውን ጊዜ ከቤት ውጭ ለመሆን እጥራለሁ” ብለዋል።

በብዙ ቤቶች በወጣቶችና በወላጆቻቸው መካከል ትልቅ የአስተሳሰብ ልዩነት ወይም የግንኙነት መሻከር አለ። ምክንያቱ ምንድን ነው?

በ“ጉልበት” እና በ“ሽበት” መካከል ያለው ልዩነት

ምሳሌ 20:​29 “የጎበዛዝት [የቆነጃጅት] ክብር ጉልበታቸው ናት” ይላል። ይሁንና ይህ ‘ጉልበት’ ወይም ጥንካሬ በእናንተና በወላጆቻችሁ መካከል ለሚነሳው ግጭት ሁሉ መንስዔ ሊሆን ይችላል። ምሳሌው በመቀጠል “የሽማግሌዎችም ጌጥ [“ግርማ” አዓት] ሽበት ነው” ይላል። ወላጆቻችሁ ቃል በቃል ‘የሸበቱ’ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ በዕድሜ ስለሚበልጧችሁ ሕይወትን ከእናንተ በተለየ መንገድ ወደማየት ያዘነብላሉ። በሕይወት ውስጥ ማንኛውም ሁኔታ አስደሳች ፍጻሜ እንደማይኖረው ይገነዘባሉ። ምናልባት በግል ያሳለፉት መራራ ተሞክሮ ወጣቶች በነበሩበት ጊዜ ስለ ሕይወት በነበራቸው ሕልምና ጥሩ ምኞት ላይ ጠባሳ ጥሎ ይሆናል። ከተሞክሮ ወይም ‘ከሽበት’ ባገኙት በዚህ ጥበብ ምክንያት በአንዳንድ ነገሮች ላይ እናንተ የሚኖራችሁ ዓይነት ስሜት አይኖራቸው ይሆናል።

ጂም የተባለ ወጣት “ወላጆቼ (ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት በነበረበት ዘመን የተወለዱ ስለሆኑ) ገንዘብ መቆጠብና አስፈላጊ ወይም በጣም ጠቃሚ ለሆኑ ነገሮች ብቻ ማውጣት እንደሚገባ ያምናሉ። እኔ ግን ለመኖር የምፈልገው ለመጪው ጊዜ ብቻ አይደለም። . . . ብዙ ቦታዎችን ለማየት እፈልጋለሁ” ይላል። አዎን፣ በአንድ ወጣት “ጉልበት” እና በወላጆቹ “ሽበት” መካከል ትልቅ ልዩነት ሊኖር ይችላል። በመሆኑም ብዙ ቤተሰቦች ስለ ልብስና ስለ ፀጉር አበጣጠር፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ሊኖር ስለሚገባው ቅርርቦሽ፣ በአደንዛዥ ዕፅና በአልኮል መጠጦች ስለ መጠቀም፣ በተወሰነ ሰዓት እቤት ስለ መግባት፣ ስለ ባልንጀሮችና ስለ ሥራ በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ በጣም የከረረ ልዩነት አላቸው። ይህ በዕድሜ ልዩነት ምክንያት የሚመጣው የሐሳብ ልዩነት ሊወገድ ይችላል። ነገር ግን ወላጆቻችሁ ስሜታችሁን እንዲረዱላችሁ ከመጠበቃችሁ በፊት እናንተ የእነርሱን ስሜትና አስተሳሰብ ለመረዳት መጣር ይኖርባችኋል።

ወላጆችም ሰዎች ናቸው

ጆን “ትንሽ ልጅ ሳለሁ እናቴ ‘ፍጹም’ እንደሆነችና እኔ ያለኝ ድክመትና ስሜት የሌላት መስሎ ይሰማኝ ነበር” ይላል። ከዚያ በኋላ ግን ወላጆቹ ተፋቱና እናቱ ብቻዋን ሰባት ልጆች ለማሳደግ ተገደደች። ኤፕሪል የምትባለው የጆን እህት ስትናገር “ሁሉን ነገር አስተካክላ ለማከናወን ስትጣጣር በሚገጥማት ብስጭት ምክንያት ስታለቅስ እንዳየኋት አስታውሳለሁ። የተሳሳተ አመለካከት እንደነበረን በዚህ ጊዜ ተገነዘብኩ። ማንኛውንም ነገር በተገቢው ጊዜና በተገቢው መንገድ ሁልጊዜ መሥራት አትችልም። እርስዋም ስሜት እንዳላትና እንደኛው ሰው መሆኗን አወቅን” ትላለች።

ወላጆቻችሁ የእናንተን የመሰሉ ስሜቶች ያሏቸው ሰዎች መሆናቸውን መገንዘባችሁ ስሜታቸውን እንድትረዱላቸው የሚያስችላችሁ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው። ለምሳሌ ያህል እናንተን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ ስላላቸው ችሎታ እርግጠኞች ላይሆኑ ይችላሉ። ወይም በሚያጋጥሟችሁ ብዙ ዓይነት የሥነ ምግባር አደጋዎችና ወደ መጥፎ የሚገፋፉ ሁኔታዎች ተጨንቀው አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን አምርረው ወደመቃወሙ ያዘነብሉ ይሆናል። በተጨማሪም የሚታገላቸው የአካል፣ የገንዘብ ወይም የስሜት ችግር ይኖርባቸው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንድ አባት ሥራውን ቢጠላውም ፈጽሞ አያጉረመርም ይሆናል። ስለዚህ ልጁ “ትምህርት ፈጽሞ ሰልችቶኛል” ቢለው ኃዘኔታ በተሞላበት መንገድ መልስ በመስጠት ፈንታ “ምን ሆነህ ነው የሚሰለችህ? እናንተ ልጆች እኮ ተሞላቃችኋል!” ብሎ በንዴት ቢመልስለት አያስደንቅም።

ስለ ወላጆቻችሁ ‘የግል ሁኔታ የምታስቡ’ መሆናችሁን አሳዩ

ታዲያ ወላጆቻችሁ ምን እንደሚሰማቸው እንዴት ለማወቅ ትችላላችሁ? ‘ስለ ራሳችሁ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ስለ ሌሎች የግል ጉዳይ ጭምር በማሰብ ነው።’ (ፊልጵስዩስ 2:​4) እናታችሁ ወጣት ሳለች ምን ዓይነት ጠባይ እንደነበራት ለመጠየቅ ሞክሩ። እንዴት ያለ ስሜትና የሕይወት ግብ ነበራት? ቲን የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “እናንተ ስለ እርሷ ለማወቅና ለስሜቶችዋ መንስዔ የሆኑትን ነገሮች ለመረዳት እንደምትፈልጉ ከተሰማት የእናንተንም ስሜት ከበፊቱ የበለጠ ለማወቅ ጥረት ታደርጋለች።” አባታችሁም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን አያጠራጥርም።

በወላጆቻችሁና በእናንተ መካከል ጥል ቢነሳ ወላጆቻችሁ የሰው ስሜት የማይገባቸው ናቸው ብላችሁ ለመወንጀል አትቸኩሉ። ራሳችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ጠይቁ:- ‘አባቴ ወይም እናቴ ምናልባት ጤንነቱ/ጤንነቷ ታውኮ ወይም የተጨነቀበት/የተጨነቀችበት ነገር ኖሮ ይሆን? ምናልባት እኔ ሳላስብ ባደረግሁት ነገር ወይም በተናገርኩት ቃል ተቀይሞ/ተቀይማ ይሆን? ወይም ሐሳቤ በትክክል ስላልገባቸው ይሆን?’ (ምሳሌ 12:​18) በዚህ ዓይነት የሌሎችን ችግር ለመረዳት መሞከር በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን የሐሳብ ልዩነት ለማጥበብ የሚያስችል ጥሩ ጅምር ነው። ከዚህ በኋላ ወላጆቻችሁ ስሜታችሁን እንዲረዱላችሁ ለማግባባት ትችላላችሁ! ይሁንና ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸው ስሜታቸውን ለመረዳት አዳጋች እንዲሆንባቸው የሚያደርግ ነገር ይፈጽማሉ። እንዴት?

ሁለት ዓይነት ሕይወት መኖር

ቪኪ የምትባል የአሥራ ሰባት ዓመት ወጣት የወላጆቿን ፈቃድ ጥሳ ከአንድ ወንድ ጋር ተደብቃ በመውጣት ሁለት ዓይነት ሕይወት ትኖር ነበር። ወላጆቿ ለወንድ ጓደኛዋ ያላትን ስሜት እንደማይረዱላት እርግጠኛ ነበረች። በዚህም ምክንያት በእርሷና በወላጆቿ መካከል ያለው የሐሳብ ልዩነት ሰፋ። “እኔ እነርሱን ሳበሳጭ እነርሱም እኔን ያበሳጩኝ ነበር” ትላለች ቪኪ። “እቤት መምጣት አስጠላኝ።” ከቤት ለመውጣት ስትል ብቻ ለማግባት ወሰነች!

በተመሳሳይም ብዙ ወጣቶች ሁለት ዓይነት ሕይወት እየኖሩ፣ ማለትም ወላጆቻቸው የሚከለክሉትን ነገር በስውር እያደረጉ ወላጆቻችን ‘ስሜታችንን አይረዱልንም!’ በማለት ያማርራሉ። ደግነቱ ቪኪ እንደሚከተለው በማለት ከነገረቻት በዕድሜ የምትበልጣት አንዲት ክርስቲያን ሴት እርዳታ አግኝታለች:- “ቪኪ፣ እስቲ ስለ ወላጆችሽ አስቢ፣ . . . እነርሱ እኮ አሳድገውሻል። ከወላጆችሽ ጋር ተስማምተሽ ለመኖር ካልቻልሽ ለ17 ዓመታት አብሮሽ ኖሮ እንደሚወድሽ ካላረጋገጠልሽ ከዚህ የዕድሜ እኩያሽ ጋር እንዴት ተስማምተሽ ትኖሪያለሽ?”

ቪኪ ራሷን በሐቀኝነት መረመረች። ወዲያውም ወላጆቿ ትክክል እንደሆኑና የራሷ ልብ ግን ስህተተኛ እንደሆነ ተገነዘበች። ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ያላትን ግንኙነት አቋረጠችና በወላጆቿና በእርሷ መካከል ያለውን የልዩነት ሸለቆ ማጥበብ ጀመረች። እናንተም እንደዚሁ ዋናውን የሕይወታችሁን ክፍል ከወላጆቻችሁ ደብቃችሁ ምሥጢር አድርጋችሁት ከሆነ ለወላጆቻችሁ ሐቀኛ መሆን የሚኖርባችሁ ጊዜው አሁን አይደለምን?—“ለወላጆቼ እንዴት ልነግራቸው እችላለሁ?” የሚለውን ክፍል ተመልከቱ።

ጊዜ ወስዳችሁ ተነጋገሩ

ጆን ከአባቱ ጋር ሆኖ ስላደረገው ጉዞ ሲናገር ‘ከአባቴ ጋር እንዲህ ያለ አስደሳች ጊዜ አሳልፌ አላውቅም!’ ብሏል። “በሕይወቴ ሙሉ እኔና እርሱ ብቻችንን ሆነን ስድስት ሰዓት ሙሉ የቆየንበት ጊዜ አልነበረም። ስንሄድ ስድስት ሰዓት ስንመለስ ስድስት ሰዓት አሳለፍን። የመኪና ሬዲዮ አልከፈትንም። ከልባችን ተነጋገርን። አዲስ እንደተዋወቅን ያህል ነበር። አባቴ ካሰብኩት በላይ ሆኖ አገኘሁት። ሽርሽሩ ጓደኛሞች እንድንሆን አስቻለን።” እናንተስ ከእናታችሁ ወይም ከአባታችሁ ጋር አዘውትራችሁ ጥሩ ጭውውት ለማድረግ ለምን አትሞክሩም?

ከሌሎች ትልልቅ ሰዎችም ጋር ጓደኝነት መመሥረቱ ጠቃሚ ነው። ቪኪ አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “ከትልልቆች ጋር ጭራሽ አልግባባም ነበር። ወላጆቼ ሌሎች ሰዎችን ሊጠይቁ በሚሄዱበት ጊዜ አብሬአቸው ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ከጊዜ በኋላ የወላጆቼ የዕድሜ እኩዮች ከሆኑት ሰዎች ጋር ወዳጅ ሆንኩ። ይህ ደግሞ ይበልጥ የተሟላ አመለካከት እንዳገኝ አስቻለኝ። ከወላጆቼ ጋር ለመጨዋወት ቀላል ሆነልኝ። በቤታችን ያለው ሁኔታ በሚያስደንቅ መንገድ ተሻሻለ።”

ካሳለፏቸው ዓመታት ጥበብ ካገኙ በዕድሜ ከሚበልጧችሁ ትልልቅ ሰዎች ጋር የወዳጅነት ጭውውት ማድረግ ወጣቶች ከሆኑ እኩዮቻችሁ ጋር ብቻ ብትወዳጁ ሊደርስባችሁ ከሚችለው የሕይወት አመለካከት ጠባብነትና አነስተኛነት ይጠብቃችኋል።​— ምሳሌ 13:​20

የሚሰማችሁን ነገር ተናገሩ

ወጣቱ ኤሊሁ “በልቤ ያለውን በቀጥታ እናገራለሁ፣ ከከንፈሮቼም የሚወጣውን እውቀት በቅንነት እናገራለሁ” ብሏል። (ኢዮብ 33:​3 በዊልያም ቤክ የተዘጋጀው ዘ ሆሊ ባይብል ኢን ዘ ላንጉዊጅ ኦቭ ቱደይ) እናንተስ አለባበስን፣ ሙዚቃንና በተወሰነ ሰዓት እቤት መግባትን በሚመለከቱ ጉዳዮች አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ከወላጆቻችሁ ጋር በልባችሁ ያለውን ገልጻችሁ በቅንነት ትነጋገራላችሁን?

ወጣቱ ግሪጎሪ እናቱ ጨርሶ ምክንያተ ቢስ እንደሆነች ተሰምቶት ነበር። በተቻለው መጠን ከቤት ውጭ ለመቆየት በመሞከር በመካከላቸው የሚነሳውን ጥል ለማስወገድ ይሞክር ነበር። ከዚያ በኋላ ግን አንዳንድ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የነገሩትን ምክር ተግባራዊ አደረገ። “ምን እንደሚሰማኝ ለእናቴ መናገር ጀመርኩ። ነገሮችን ለማድረግ ለምን እንደምፈልግና እሷ ታውቃለች ብዬ እንዳልገመትኩ ነገርኳት። አዘውትሬም የልቤን ገልጬ አጫውታትና ምንም ዓይነት ጥፋት ለመሥራት መሞከሬ እንዳልሆነና እርሷ ግን እንደ ትንሽ ልጅ ስትቆጥረኝ እንዴት እንደሚያናድደኝ ነገርኳት። ከዚያ በኋላ እርሷም ስሜቴን መረዳት ስለ ጀመረች ቀስ በቀስ ነገሮች በጣም ተሻሻሉ።”

እናንተም እንደዚሁ ‘በልባችሁ ያለውን በቀጥታ’ መናገር ብዙ አለመግባባቶችን ለመፍታት እንደሚጠቅም ልትገነዘቡ ትችላላችሁ።

አለመግባባቶችን ማስወገድ

ይህ ማለት ግን ወላጆቻችሁ ወዲያውኑ እናንተ ነገሮችን በምትመለከቱበት መንገድ መመልከት ይጀምራሉ ማለት አይደለም። ስለዚህ ስሜታችሁን መቆጣጠር አለባችሁ። “ሰነፍ ሰው መንፈሱን [ስሜቱን] ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ የሆነ ግን እስከ መጨረሻ ስሜቱን ያረጋጋል።” (ምሳሌ 29:​11 አዓት) ረጋ ብላችሁ አስተያየታችሁ ትክክል የሆነበትን ምክንያት ግለጹ። በውይይታችሁ ላይ “እንዲህ የማደርገው እኔ ብቻ አይደለሁም!” በማለት ከመነታረክ ይልቅ ለመግለጽ በምትፈልጉት ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሩ።

አንዳንድ ጊዜ ወላጆች የጠየቃችሁትን ነገር እሺ አይሏችሁ ይሆናል። ይህ ማለት ግን ስሜታችሁን አይረዱላችሁም ማለት አይደለም። ይህን የሚያደርጉት ከችግር ሊጠብቋችሁ ስለሚፈልጉ ብቻ ሊሆን ይችላል። “እናቴ በእኔ ላይ በጣም ጥብቅ ናት” ትላለች አንዲት የ16 ዓመት ልጃገረድ። “‘እንዲህ አታድርጊ፣ በተወሰነ ሰዓት እቤት መግባት አለብሽ’ ስትለኝ ያናድደኛል። ጠለቅ ብዬ ስመለከተው ግን ከልብ ታስብልኛለች። . . . ስለ እኔ ትጠነቀቅልኛለች።”

የጋራ መግባባት ለቤተሰብ የሚያስገኘውን የመተማመን ስሜትና መዋደድ በቃላት መግለጽ አይቻልም። ቤቱ በጭንቀት ጊዜ መሸሸጊያ እንዲሆን ያደርገዋል። ይሁን እንጂ ይህን ውጤት ለማግኘት የመላው ቤተሰብ አባላት ልባዊ ጥረት አስፈላጊ ነው።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ወጣቶችና ወላጆቻቸው ብዙ ጊዜ የሚጋጩት ለምንድን ነው?

◻ የወላጆቻችሁን ስሜት ይበልጥ መረዳታችሁ ለእነርሱ ያላችሁን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?

◻ የወላጆቻችሁን ስሜት ይበልጥ ልትረዱላቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

◻ ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት በእናንተና በወላጆቻችሁ መካከል ያለውን የሐሳብ ልዩነት የሚያሰፋው ለምንድን ነው?

◻ አሳሳቢ ችግር ሲያጋጥማችሁ ችግሩን ለወላጆቻችሁ ማሳወቅ የተሻለ የሚሆነው ለምንድን ነው? የምትነግሯቸውስ እንዴት አድርጋችሁ ነው?

◻ ወላጆቻችሁ ስሜታችሁን በበለጠ እንዲረዱላችሁ ልታደርጉ የምትችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እናንተ ስለ እርሷ [እናታችሁ] ለማወቅና ለስሜቶችዋ መንስዔ የሆኑትን ነገሮች ለመረዳት እንደምትፈልጉ ከተሰማት የእናንተንም ስሜት ከበፊቱ የበለጠ ለማወቅ ጥረት ታደርጋለች።” ​— ቲን መጽሔት

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለወላጆቼ እንዴት ልነግራቸው እችላለሁ?

ጥፋታችሁን ለወላጆቻችሁ መናገር አያስደስትም። ቫንስ የሚባል ወጣት እንዲህ ይላል:- “ወላጆቼ በእኔ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው ሁልጊዜ ይሰማኝ ስለነበረና ላስቀይማቸው ስለማልፈልግ ጥፋት ስሠራ ለእነርሱ መናገር ይከብደኝ ነበር።”

ጥፋታቸውን የሚደብቁ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የሕሊና ቁስል በሚያስከትለው ሥቃይ ይጨነቃሉ። (ሮሜ 2:​15) ጥፋታቸው ሊሸከሙ የማይችሉት “ከባድ ሸክም” ሊሆንባቸው ይችላል። (መዝሙር 38:​4) ውሸት ለመናገር ስለሚገደዱ ወላጆቻቸውን በማታለል ተጨማሪ ጥፋት ይፈጽማሉ። በዚህም ምክንያት ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና ይበላሽባቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።” (ምሳሌ 28:​13) የ19 ዓመቷ ቤቲ እንደተናገረችው “ያም ሆነ ይህ ይሖዋ ማየቱ አይቀርም።”

ከባድ ጥፋት የተፈጸመበት ጉዳይ ከሆነ ጥፋታችሁን በጸሎት ለይሖዋ በመናዘዝ የይሖዋን ይቅርታ ለምኑ። (መዝሙር 62:​8) ከዚያም ለወላጆቻችሁ ንገሩ። (ምሳሌ 23:​26) ወላጆቻችሁ የሕይወት ተሞክሮ ስላላቸው ከጥፋታችሁ እንድትወጡና ጥፋቱን ከመድገም እንድትቆጠቡ ሊረዷችሁ ይችላሉ። የ18 ዓመቱ ክሪስ “ስለ ጥፋታችሁ መናገር በእርግጥ ይረዳችኋል” በማለት ይናገራል። “ጥፋታችሁን ከአእምሯችሁ ማውጣት ግልግል ነው።” ችግሩ ጥፋታችሁን ለወላጆቻችሁ የምትነግሯቸው እንዴት ነው? የሚለው ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ‘በተገቢው ጊዜ ስለሚነገር ቃል’ ይናገራል። (ምሳሌ 25:​11 አዓት፤ ከመክብብ 3:​1, 7 ጋር አወዳድሩ።) ተገቢው ጊዜ መቼ ሊሆን ይችላል? ክሪስ በመቀጠል “እስከ ራት ሰዓት እጠብቅና አባባን ላነጋግረው እንደምፈልግ እነግረዋለሁ” ይላል። የአንዲት ነጠላ ወላጅ ልጅ ደግሞ ከክሪስ በተለየ ጊዜ ላይ ሊያነጋግራት እንደሚሞክር ይናገራል:- “አብዛኛውን ጊዜ እማማን ወደ መኝታ ቤቷ ልትሄድ ስትል አነጋግራታለሁ፤ በዚህ ጊዜ እረፍት አግኝታ ዘና ትላለች። ከሥራ ወደ ቤት በምትመጣበት ጊዜ ውጥረት ይኖራታል።”

ምናልባት እንደሚከተለው ለማለት ትችሉ ይሆናል:- “እማማና አባባ፣ አንድ ያስጨነቀኝ ነገር አለ።” ወላጆቻችሁ የሚያስጨንቃችሁን ነገር ለመስማት ጊዜ ባይኖራቸውስ? እንዲህ ልትሉ ትችሉ ይሆናል:- “ጊዜ እንደሌላችሁ አውቃለሁ፣ ግን አንድ የተቸገርኩበት ነገር አለ። ልንነጋር እንችላለን?” ከዚያ በኋላ “ለመናገር የሚያሳፍራችሁን ነገር ሠርታችሁ ታውቃላችሁ?” ­በማለት ልትጠይቁ ትችላላችሁ።

አሁን ከሁሉም በሚከብደው ደረጃ ላይ ደርሳችኋል። እርሱም የሠራችሁትን ጥፋት ለወላጆቻችሁ መናገር ነው። የጥፋታችሁን ክብደት ለማሳነስ ሳትሞክሩ ወይም ለመናገር ደስ ከማይሉት ዝርዝሮች አንዳንዶቹን ለመደበቅ ሳትሞክሩ በትሕትና ‘እውነቱን ተናገሩ።’ (ኤፌሶን 4:​25፤ ከሉቃስ 15:​21 ጋር አወዳድሩ።) ለወላጆቻችሁ በምትናገሩበት ጊዜ ወጣቶች ብቻ በሚግባቡባቸው ልዩ ቃላት ሳይሆን ወላጆቻችሁ በሚገቧቸው ቃላት ተጠቀሙ።

ወላጆቻችሁ መጀመሪያ ላይ ሊከፋቸውና ሊያዝኑ ይችላሉ። ስለዚህ በስሜት ግንፋሎት የቃላት ውርጅብኝ ቢያወርዱባችሁ አትገረሙ! ቀደም ብለው የሰጧችሁን ማስጠንቀቂያዎች ብትሰሙ ኖሮ በዚህ ሁኔታ ላይ ላትወድቁ ትችሉ ነበር። ስለዚህ ወላጆቻችሁ ሲገስጿችሁ በጸጥታ ተቀበሉ። (ምሳሌ 17:​27) ወላጆቻችሁን አዳምጡ፣ ለሚያቀርቡላችሁ ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ ተገቢውን መልስ ስጡ።

ነገሮችን ለማስተካከል የምታሳዩት ቅንነት በወላጆቻችሁ ላይ ጥልቅ ስሜት እንደሚያሳድርባቸው ጥርጥር የለውም። (ከ2 ቆሮንቶስ 7:​11 ጋር አወዳድሩ።) ይሁን እንጂ አንዳንድ ተገቢ ቅጣቶችን ለመቀበል ተዘጋጁ። “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” (ዕብራውያን 12:​11) በተጨማሪም የወላጆቻችሁን እርዳታና ብስለት ያለው ምክር ለመፈለግ ይህ የመጨረሻ ጊዜያችሁ እንደማይሆን አስታውሱ። ትልልቅ ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ በሐሳባችሁ ውስጥ ያለውን አውጥታችሁ መናገር እንዳትፈሩ ትንንሽ ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ለወላጆቻችሁ መናገርን ልማድ አድርጉ።

[ሥዕል]

ችግሮቻችሁን ለወላጆቻችሁ ለመናገር ስትፈልጉ ወላጆቻችሁ በተረጋጋ መንፈስ ሊያዳምጧችሁ የሚችሉበትን ጊዜ ምረጡ