በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወላጄን ሌላ የትዳር ጓደኛ ማግባት ልቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የወላጄን ሌላ የትዳር ጓደኛ ማግባት ልቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 5

የወላጄን ሌላ የትዳር ጓደኛ ማግባት ልቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“አባቴ ሪታን ያገባበት ዕለት በሕይወቴ ውስጥ ካሳለፍኳቸው መጥፎ ቀኖች ሁሉ የከፋ ነው” በማለት ሼን ታስታውሳለች። “ተናድጄ ነበር። አባቴ እናቴን በመክዳቱ በጣም ተናደድኩ። እናቴ የሕግ ትምህርት ለመማር ብላ ትታን በመሄዷ በእርሷም ተናደድኩ። በቤታችን ሊኖሩ በሚመጡት በሁለቱ የሪታ ቀበጥ ልጆችም ተናደድኩ። . . . ከሁሉ በላይ ግን የተናደድኩት በሪታ ነው። . . . ጠላኋት። መጥላት ትክክል አለመሆኑን ስለማምን በራሴም ተናደድኩ።”​— ስቴፕፋሚሊስ​—ኒው ፓተርንስ ኢን ሃርሞኒ የተሰኘው በሊንዳ ክሬቭን የተዘጋጀ መጽሐፍ

ከሁለቱ ወላጆቻችሁ አንደኛው ሌላ የትዳር ጓደኛ ማግባቱ ወይም ማግባቷ እንደገና ለማስታረቅ የነበራችሁን ተስፋ ያጨልመዋል። ፍርሃትና ስጋት፣ የመከዳትና የቅንዓት ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል።

ወላጃችሁ ሌላ ጋብቻ የፈጸመው ወይም የፈጸመችው የምትወዱት ወላጃችሁ ገና ከመሞቱ ወይም ከመሞቷ ብዙም ሳይቆይ ወዲያውኑ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ስሜታችሁ በጣም ሊጎዳ ይችላል። “የእናቴ ሞት በጣም አማሮኛል” ትላለች የ16 ዓመቷ ሚሲ። “የአባቴ እጮኛ በእናቴ እግር መተካቷን እያሰብኩ በጣም የሚያስቀይማትን ነገር ማድረግ ጀመርኩ።” ለሥጋ ወላጃችሁ ታማኝ ከመሆናችሁ የተነሳ ለእንጀራ እናታችሁ ወይም ለእንጀራ አባታችሁ የመውደድ ስሜት ከተሰማችሁ የሞተው ወላጃችሁን እንደከዳችሁ ሊሰማችሁ ይችላል።

እንግዲያውስ ብዙ ወጣቶች የቆሰለ ስሜታቸውን ጉዳት በሚያስከትል መንገድ መወጣታቸው አያስደንቅም። እንዲያውም አንዳንዶቹ የወላጃቸውን አዲስ ጋብቻ የሚያፈርሱበትን ዘዴ ይፈላልጋሉ። ይሁን እንጂ የሥጋ ወላጃችሁና የእንጀራ እናታችሁ ወይም የእንጀራ አባታችሁ በአምላክ ፊት ቃል ኪዳን መጋባታቸውን አስታውሱ። “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው [ልጅም ቢሆን] አይለየው።” (ማቴዎስ 19:​6) የወላጃችሁን አዲስ ጋብቻ ለማፍረስ ብትችሉም እንኳን ይህን ማድረጋችሁ የሥጋ ወላጆቻችሁን እንደገና እንዲጣመሩ አያደርጋቸውም።

ከእንጀራ እናት ወይም ከእንጀራ አባት ጋር ወደማያቋርጥ ግጭት ውስጥ መግባቱም ቢሆን የሚፈይደው ነገር የለም። ምሳሌ 11:​29 “ቤቱን [ቤተሰቡን] የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል” በማለት ያስጠነቅቃል። ይህም ማለት በቤተሰቡ ላይ ሁከት የሚያመጣ ሰው ምንም የሚያገኘው ጥቅም የለም ማለት ነው። የአሥራ አምስት ዓመቷ ጄሪ ለእንጀራ እናቷ ያላት ጥላቻ ከእርስዋ ጋር እስከ መደባደብ አደረሳት። ውጤቱስ? የእንጀራ እናቷ የጄሪን አባት ከእርሷ [ከሚስቱ] እና ከልጁ [ከጄሪ] አንዳቸውን እንዲመርጥ አስገደደችው። ጄሪም ሌላ ባል አግብታ ወደምትኖረው ወላጅ እናቷ ለመመለስ ተገደደች።

ፍቅር ሁኔታውን ለመቋቋም ይረዳችኋል

ወላጅ ሌላ የትዳር ጓደኛ በሚያገባበት ጊዜ የሚያጋጥማችሁን ብሶት በተሳካ ሁኔታ ችሎ ለማሳለፍ የሚረዳችሁ ነገር ምንድን ነው? በ1 ቆሮንቶስ 13:​4–8 ላይ የተገለጸውን ሥነ ሥርዓታዊ ፍቅር ማሳየት ነው:-

ፍቅር “የራሱን ጥቅም አይፈልግም።” ይህ ማለት ‘የባልንጀራን ጥቅም እንጂ የራስን ጥቅም አለመመልከት’ ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:​24) ወላጃችሁ እንደገና የትዳር ጓደኛ ማግኘት እንደሚያስፈልገው ከወሰነ ወይም እንደሚያስፈልጋት ከወሰነች ይህን ውሳኔ መቃወም ይገባችኋልን?

“ፍቅር አይቀናም።” ብዙውን ጊዜ ወጣቶች የሥጋ ወላጃቸውን ፍቅር ከሌላ ሰው ጋር መጋራት አይፈልጉም። ይሁን እንጂ ፍቅር ሊሰፋ ስለሚችል የወላጃችሁ ፍቅር ያልቅብኛል ብላችሁ መፍራት አያስፈልጋችሁም። (ከ2 ቆሮንቶስ 6:​11–13 ጋር አወዳድሩ።) የሥጋ ወላጃችሁ ለእናንተ ያለውን ወይም ያላትን ፍቅር ሳይቀንስ ወይም ሳትቀንስ ፍቅሩን ወይም ፍቅሯን በማስፋት አዲስ የትዳር ጓደኛንም ለመውደድ ይችላል ወይም ትችላለች! እናንተስ ፍቅራችሁን አስፍታችሁ የእንጀራ እናታችሁን ወይም የእንጀራ አባታችሁን ለመውደድ እንድትችሉ ልባችሁን ልትከፍቱ ትችላላችሁን? እንዲህ ብታደርጉ የሄደውን ወይም የሞተውን ወላጃችሁን እንደ መክዳት አይቆጠርባችሁም።

ፍቅር “የማይገባውን አያደርግም።” አዲስ ካገኛችኋቸው ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር መኖር መጀመራችሁ የጾታ ግፊት ያመጣባችሁ ይሆናል። የእንጀራ እናትና የእንጀራ አባት ልጆች አንድ ላይ በሚኖሩባቸው ቤተሰቦች ውስጥ 25 በመቶ በሚሆኑት መካከል ሕገ ወጥ የጾታ ግንኙነት እንደሚደረግ ተደርሶበታል።

እናቱ ሌላ ባል በማግባቷ ምክንያት የእንጀራ አባቱ ልጆች የሆኑ አራት ሴቶች ወደ ቤቱ የመጡበት ዴቪድ ሲናገር “የጾታ ስሜትን በሚመለከት አእምሮዬን መዝጋት አስፈልጎኝ ነበር” ይላል። እናንተም አለባበሳችሁም ሆነ ጠባያችሁ የጾታ ስሜትን የሚያነሳሳ እንዳይሆንና ተገቢ ያልሆነ መቀራረብን ለማስወገድ እንድትችሉ ጠንቃቆች መሆን ያስፈልጋችኋል።​— ቆላስይስ 3:​5

ፍቅር “ማንኛውም ነገር ቢያጋጥመው ይታገሣል። . . . ማንኛውንም ነገር እንድንታገሥ የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል።” (የቻርልስ ቢ ዊልያምስ ትርጉም) አንዳንድ ጊዜ ከስሜት ቁስላችሁ የሚያላቅቃችሁ ምንም ነገር የሌለ ሊመስላችሁ ይችላል! ማርላ “በቤት ውስጥ ምንም ቦታ የሌለኝ መስሎ ተሰማኝ። አልፎ ተርፎ ለእናቴ ባልወለድ ይሻለኝ ነበር ብዬ እነግራት ነበር” ብላለች። ማርላ በቤተሰቦችዋ ላይ ዓምፃ ከቤት እስከ መኮብለል ደረሰች! አሁን ግን “ከሁሉ የሚሻለው ነገር መታገሡ ነው” ትላለች። እናንተም ከታገሣችሁ መጀመሪያ ላይ የተሰማችሁ የምሬት፣ የግራ መጋባትና የሥቃይ ስሜት ከጊዜ በኋላ ይጠፋል።

‘ እውነተኛ እናቴ አይደለሽም!/እውነተኛ አባቴ አይደለህም!’

በእንጀራ እናት ወይም በእንጀራ አባት እጅ መቀጣት ቀላል አይደለም፣ የእንጀራ እናት ወይም የእንጀራ አባት አንድ ነገር እንድታደርጉ ሲያዟችሁ ‘እውነተኛ እናቴ/አባቴ አይደለሽም/አይደለህም እኮ!’ ብላችሁ እቅጩን ለመናገር ትገፋፉ ይሆናል። ነገር ግን በ1 ቆሮንቶስ 14:​20 ላይ የተገለጸውን “በአእምሮ ያደጋችሁ ሁኑ” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስታውሱ።​— ዘ ሆሊ ባይብል ኢን ዘ ላንጉዊጅ ኦቭ ቱደይ በዊልያም ቤክ

የእንጀራ እናታችሁ ወይም የእንጀራ አባታችሁ እናንተን ለመቅጣት ሥልጣን ያላት/ያለው መሆኑን መቀበል ‘በአእምሮ ያደጋችሁ’ መሆናችሁን የምታሳዩበት አንዱ መንገድ ነው። የእንጀራ አባታችሁ ወይም የእንጀራ እናታችሁ የሥጋ ወላጃችሁን ሥራና ኃላፊነት ስለሚያከናውን ወይም ስለምታከናውን አክብሮት ይገባዋል/ይገባታል። (ምሳሌ 1:​8፤ ኤፌሶን 6:​1–4) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አስቴር አባቷ ሲሞት አሳዳጊ አባት ወይም “ሞግዚት” ሆኖ ያሳደጋት ዘመዷ ነበር። መርዶክዮስ የሥጋ ወላጅዋ ባይሆንም ካደገች በኋላም እንኳን ሳይቀር ‘ሲያዛት’ ትእዛዙን ትፈጽም ነበር! (አስቴር 2:​7, 15, 17, 20) በእርግጥም የእንጀራ እናት ወይም የእንጀራ አባት የምትሰጠው/የሚሰጠው ቅጣት ብዙውን ጊዜ ለእናንተ ያላት/ያለው ፍቅርና አሳቢነት መግለጫ ነው።​— ምሳሌ 13:​24

ያም ሆኖ ግን ትክክለኛ መሠረት ያላቸው ቅሬታዎች መነሳታቸው የማይቀር ነው። ይህ ከሆነ ቆላስይስ 3:​13 “ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ” በማለት እንደሚያሳስበው በማድረግ ‘በአእምሮ ያደጋችሁ’ መሆናችሁን አሳዩ።

ማካፈልን ተማሩ፣ ከእኔ ይቅር ማለትን ልመዱ

የ15 ዓመቷ ጃሚ ከእናቷ ጋር ብቻ ትኖር በነበረበት ጊዜ የራሷ ክፍል ነበራት፣ ዋጋቸው ውድ የሆኑ ልብሶችን ትለብስ ነበር። እናቷ ሌላ ባል ስታገባና ከራሷ ጋር አራት ልጆች ባሉት ቤተሰብ ውስጥ መኖር ስትጀምር ግን ነገሮች ተለወጡ። “አሁን የራሴ ክፍል እንኳን ሊኖረኝ አልቻለም” በማለት አማርራለች። “ሁሉን ነገር ማካፈል አለብኝ።”

እናንተም ታላቅ ልጅ ወይም አንድያ ልጅ ሳላችሁ ታገኙ የነበረውን መብት መልቀቅ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። ወንድ ልጅ ከሆንክ ለረዥም ጊዜ የቤቱ ወንድ በመሆን አገልግለህ ይሆናል፤ እናትህ ሌላ ባል ስታገባ ግን ይህ ቦታ በእንጀራ አባትህ ይያዛል። ሴት ልጅ ከሆንሽ ደግሞ አንቺና እናትሽ እንደ እህትማማቾች ትተያዩ እንዲያውም አንድ ክፍል ውስጥ አንድ ላይ ስትተኙ ኖራችሁ ይሆናል። አሁን ግን የእንጀራ አባትሽ በመምጣቱ ምክንያት ወደ ሌላ ክፍል ትዛወሪያለሽ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ” አዓት ] ለሰው ሁሉ ይታወቅ” በማለት ይመክራል። (ፊልጵስዩስ 4:​5) “ገርነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “እሺ ባይነትን” እና ሕጋዊ መብቶቼ በሙሉ ይጠበቁልኝ ብሎ ድርቅ ያለማለትን መንፈስ ያስተላልፍ ነበር። ስለዚህ መብታችሁ የነበረውን ነገር በእሺ ባይነት የምትለቁና ከእኔ ይቅር የምትሉ ለመሆን ጣሩ። ያለፈውን ሁኔታ ብቻ ከማሰብ ይልቅ በተቻላችሁ መጠን አሁን ባላችሁበት ሁኔታ ለመደሰት ሞክሩ። (መክብብ 7:​10) ያላችሁን ነገር ከእንጀራ እናታችሁ ወይም ከእንጀራ አባታችሁ ልጆች ጋር ለመካፈል ፈቃደኞች ሁኑ፣ እንደ ባእድ አትቁጠሯቸው። (1 ጢሞቴዎስ 6:​18) ቶሎ ብላችሁ እርስ በርሳችሁ እንደ እውነተኛ እህትማማቾችና ወንድማማቾች መተያየት ከጀመራችሁ በመካከላችሁ የሚኖረው ጥሩ ስሜት ያድጋል። የእንጀራ አባታችሁን በጥላቻ አትመልከቱ። የቤተሰብ ኃላፊነቶችን በመሸከም ለመርዳት በመምጣቱ ደስ ይበላችሁ።

የማዳላት ሁኔታዎችን መቻል

አንዲት ወጣት ልጃገረድ የእንጀራ አባቷ ፍቅር እንደሚያሳይ ብታምንም “ግን ልዩነት አለ። እኩዮቻችን ከሆኑት የራሱ ልጆች ይልቅ . . . ከእኛ ብዙ ይጠብቃል፣ ብዙ ይቀጣናል፣ ስሜታችንንም መረዳት ያዳግተዋል። ይህ ብዙ ጊዜ እንደ ቁስል የሚያመን ደካማ ጎኑ ነበር” ብላለች።

የእንጀራ አባቶች ወይም እናቶች ብዙውን ጊዜ የእንጀራ ልጃቸውን ከሥጋ ልጃቸው ጋር እኩል አድርገው ሊመለከቱ እንደማይችሉ ተገንዘቡ። ይህም የሚሆነው ከሥጋ ልጃቸው ጋር ባላቸው የደም ትስስር ምክንያት ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር አብረው ያሳለፉ በመሆናቸው ምክንያት ነው። የሥጋ ወላጅም ቢሆን አንዱን ልጅ ከሌላው አስበልጦ ሊወድ ይችላል። (ዘፍጥረት 37:​3) ይሁን እንጂ እኩል በሆነ ፍቅርና ባልተዛባ ወይም አግባብነት ባለው ፍቅር መካከል ልዩነት አለ። ሰዎች የየግላቸው ባሕርይና የተለያየ ፍላጎት አላቸው። ስለዚህ ከሌሎች ጋር እኩል አያያዝ ካልተደረገልን ብላችሁ ከመጨነቅ ይልቅ የእንጀራ እናታችሁ ወይም የእንጀራ አባታችሁ ፍላጎታችሁን ሊያሟላላችሁ ወይም ልታሟላላችሁ ይጥር ወይም ትጥር እንደሆነና እንዳልሆነ ለመመልከት ሞክሩ። የሚያስፈልጓችሁ ነገሮች እንዳልተሟሉላችሁ ከተሰማችሁ በጉዳዩ ላይ ከእንጀራ እናታችሁ ወይም ከእንጀራ አባታችሁ ጋር ለመወያየት በቂ ምክንያት ይኖራችኋል።

በተጨማሪም የእንጀራ እናታችሁ ወይም የእንጀራ አባታችሁ ልጆች የጠብ መንስዔዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እነርሱም ቢሆኑ የእንጀራ እናት ወይም የእንጀራ አባት ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ለመኖር የተገደዱበትን ሁኔታ መለማመድ ሊቸግራቸው እንደሚችል አትርሱ። ምናልባትም በቤተሰባቸው ውስጥ ጥልቅ ብላችሁ እንደገባችሁባቸው በመቁጠር በጥላቻ ሊመለከቷችሁ ይችላሉ። ስለዚህ በተቻላችሁ መጠን ደግ ለመሆን ጣሩ። የንቀት ስሜት ቢያሳዩአችሁ ‘ክፉውን በመልካም ለማሸነፍ’ ሞክሩ። (ሮሜ 12:​21) ከዚህም ሌላ የሥጋ ወንድማማቾችና እህትማማቾችም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ስለሚጋጩ ከእንጀራ እናታችሁ ወይም ከእንጀራ አባታችሁ ልጆች ጋር ብትጋጩ ምንም አያስደንቅም።​— ምዕራፍ 6ን ተመልከቱ።

ትዕግሥት ጥሩ ውጤት ያስገኛል!

“የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፤ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል።” (መክብብ 7:​8) ብዙውን ጊዜ ከአንድ አባትና ከአንድ እናት የማይወለዱ ልጆች እርስ በርስ መተማመንና መዋደድ እስኪችሉ አያሌ ዓመታት ሊወስዱ ይችላሉ። የተለያዩ ልማዶቻቸውና አመለካከቶቻቸው ተዋሕደውና ተለማምደው የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለመምራት የሚችሉት ከዚያ በኋላ ብቻ ነው። ስለዚህ ትዕግሥተኞች ሁኑ! “ወዲያውኑ እንዋደዳለን” ወይም “ወዲያው አንድ ቤተሰብ” የመሆን መንፈስ ይፈጠራል ብላችሁ አትጠብቁ።

ቶማስ እናቱ ሌላ ባል ባገባች ጊዜ የጭንቀትና የስጋት ስሜት አድሮበት ነበር። እናቱ አራት ልጆች ሲኖሯት ሰውዬው ደግሞ ሦስት ልጆች ነበሩት። “እንጣላ፣ እንጨቃጨቅ፣ እንበጣበጥና ክፉኛ እስከ መቀያየም እንደርስ ነበር” ይላል ቶማስ ሲጽፍ። በመጨረሻ ስምምነት ያመጣላቸው ነገር ምን ነበር? “የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ በማዋል ነገሮች መፍትሔ ያገኙ ጀመር፤ አፋጣኝ እልባት የሚያገኙት ሁልጊዜ ባይሆንም በጊዜ ብዛትና የአምላክን መንፈስ ፍሬ በማፍራት ሁኔታዎች በመጨረሻው እየለዘቡ ሄዱ።”​— ገላትያ 5:​22, 23

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ማዋል በእንጀራ እናትና በእንጀራ አባት እንዲሁም በልጆቻቸው መካከል ስምምነትን ሊያመጣ እንደሚችል ቃለ ምልልስ ባደረግንላቸው በሚከተሉት ወጣቶች ተሞክሮ ታይቷል:-

የእንጀራ እናት ወይም የእንጀራ አባት ባሉባቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖሩ የተሳካላቸው ወጣቶች

ጠያቂየእንጀራ አባታችሁን ወይም እናታችሁን ቅጣት ከመቃወም የተቆጠባችሁት እንዴት ነበር?

ሊንችበቅጣት ረገድ እናቴና የእንጀራ አባቴ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት አቋም ይወስዱ ነበር። አንድ ነገር ሳጠፋ ቅጣቱን ለመፈጸም የሚወስኑት ሁለቱም ነበሩ። ስለዚህ በምገረፍበት ጊዜ ቅጣቱ የመጣው ከሁለቱም መሆኑን አውቅ ነበር።

ሊንዳመጀመሪያ ላይ የእንጀራ አባቴን ቅጣት መቀበል ይከብደኝ ስለነበር “ለእኔ እንዲህ ብለህ ለመናገር ምን መብት አለህ?” እለው ነበር። በኋላ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ እንደሚል አስታወስኩ። በሥጋ ባይወልደኝም በአምላክ ዓይን ግን አባቴ ነበር።

ሮቢንእናቴ የምትወደውን ሰው በጥላቻ ብመለከት በጣም እንደምታዝንብኝ አውቅ ነበር።

ጠያቂእርስ በርስ ተግባብታችሁ እንድትነጋገሩ የረዳችሁ ነገር ምን ነበር?

ሊንችየእንጀራ አባቴ በሚሠራው ነገር ላይ ፍላጎት ማሳደር ነበረብኝ። በዓለማዊ ሥራው እረዳው ነበር። በምንሠራበት ጊዜ ደግሞ ብዙ እናወራለን። ይህም አስተሳሰቡን እንድገነዘብ ረድቶኛል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘ምንም’ ነገር ሳንነጋገር አጠገቡ እቀመጣለሁ።

ቫለሪየእንጀራ እናቴና እኔ አብረን ብዙ ጊዜ እናሳልፍ ስለ ነበር በእርግጥ ስሜቷን እረዳላት ጀመር። በጣም የምንቀራረብ ጓደኛሞች ሆንን።

ሮቢንእናቴ ሌላ ባል ያገባችው አባቴ ከሞተ ከአንድ ዓመት በኋላ ብቻ ነበር። የእንጀራ አባቴ በአባቴ እግር መተካቱን ስላልወደድሁ ልቀርበው አልፈለግሁም ነበር። በአባቴ መሞት ምክንያት የደረሰብኝን ኀዘን እንድረሳና የእንጀራ አባቴን እንድቀርበው አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይሁ። በተደጋጋሚ ጸለይሁ። ይሖዋም ጸሎቴን በእርግጥ መልሶልኛል።

ጠያቂከእንጀራ አባታችሁ/ከእንጀራ እናታችሁ ጋር ለመቀራረብ ምን ያደረጋችሁት ነገር አለ?

ቫለሪአንዳንድ ጊዜ የእንጀራ እናቴን ሁለታችን ብቻ ሆነን ወደ ሲኒማ ቤት እንድንሄድ እጠይቃት ነበር። ወይም ደግሞ ውጭ ቆይቼ ስመጣ ሳስባት እንደቆየሁ ለማሳየት አበባ ወይም የአበባ ማስቀመጫ ገዝቼላት እመጣ ነበር። እርስዋም እንዲህ በማድረጌ በጣም ትደሰት ነበር።

ኤሪክሁለታችንንም የሚያስደስት ነገር መፈለግ ነበረብኝ። ከእንጀራ አባቴ ጋር በጋራ የሚያገናኘኝ አንድ ነገር ቢኖር እናቴን አግብቶ በአንድ ቤት መኖራችን ብቻ ነበር። የሚረዳኝ ትልቅ ነገር ያገኘሁት እኔም እንደ እርሱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ማሳየት ስጀምር ነበር። ከይሖዋ ጋር በተቀራረብሁ መጠን ከእንጀራ አባቴም ጋር ይበልጥ መቀራረብ ቻልኩ። አሁን በእርግጥ ሁለታችንንም የሚያገናኘን የጋራ ነገር አለን!

ጠያቂወላጃችሁ ሌላ የትዳር ጓደኛ በማግባቱ/በማግባቷ በግል የተጠቀማችሁት እንዴት ነው?

ሮቢንከእናቴ ጋር ብቻችንን ሳለን ዓመፀኛና ሞልቃቃ ነበርኩ። ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ይሁን ባይ ነበርኩ። አሁን ግን ስለ ሌሎችም ማሰብንና እያደር ራሴን ከመውደድ መራቅን ተምሬያለሁ።

ሊንችየእንጀራ አባቴ እንደ ወንድ እንዳስብ ረድቶኛል። የእጅ ሞያ እንዲኖረኝና በእጆቼ እንዴት መጠቀም እንደምችል እንዳውቅ ረድቶኛል። ችግር አጋጥሞኝ የሚረዳኝ ሰው በምፈልግበት ጊዜ ሁሉ ይደርስልኝ ነበር። አዎን፣ ማንም ሰው ሊያገኘው የማይችል ጥሩ አባት ነው።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸው ሌላ የትዳር ጓደኛ ሲያገቡ ምን ይሰማቸዋል? ለምንስ?

◻ አንድ ወጣት ይህን ሁኔታ እንዲቋቋም ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየት የሚረዳው እንዴት ነው?

◻ የእንጀራ እናት ወይም የእንጀራ አባት በሚቀጣችሁ ጊዜ ቅጣቱን መቀበል ይኖርባችኋልን?

◻ ከእኔ ይቅር ማለትንና ለሌሎች ማካፈልን መማር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ የእንጀራ እናታችሁ ወይም የእንጀራ አባታችሁ ከልጆቻቸው ጋር እኩል አድርገው እንዲያዩአችሁ መጠበቅ ይኖርባችኋልን? አድልዎ እንደተደረገባችሁ ከተሰማችሁ ምን ለማድረግ ትችላላችሁ?

◻ ከእንጀራ እናታችሁ ወይም ከእንጀራ አባታችሁ ጋር እንድትስማሙ የሚረዷችሁ ምን ምን ነገሮችን ለማድረግ ትችላላችሁ?

[በገጽ 45 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የአባቴ እጮኛ በእናቴ እግር መተካቷን እያሰብኩ በጣም የሚያስቀይማትን ነገር ማድረግ ጀመርኩ”

[በገጽ 43 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጅ ሌላ የትዳር ጓደኛ ሲያገባ ብዙውን ጊዜ የንዴት፣ የስጋትና የቅናት ስሜት ይቀሰቅሳል

[በገጽ 46 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ የእንጀራ እናት ወይም የእንጀራ አባት የሚሰጠው ቅጣት ተቃውሞ ያጋጥመዋል