በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወላጆቼን ቤት ትቼ መውጣት ይኖርብኛልን?

የወላጆቼን ቤት ትቼ መውጣት ይኖርብኛልን?

ምዕራፍ 7

የወላጆቼን ቤት ትቼ መውጣት ይኖርብኛልን?

“እማማና አባባ፦

“አሁን ቤታችሁን ትቼ መውጣቴ ነው። ይህን የማደርገው እናንተን ለማናደድ ወይም ለመበቀል አይደለም። እናንተ በምትፈልጉት ዓይነት ነፃነቴ ተገድቦ በመኖር ደስተኛ ልሆን አልችልም። ከቤት በመውጣቴም ቢሆን ደስተኛ አልሆን ይሆናል፤ ግን ልሞክረው እፈልጋለሁ።”

አንዲት የ17 ዓመት ልጃገረድ ለወላጆቿ የጻፈችው የስንብት ደብዳቤ የሚጀምረው ከላይ እንደተጠቀሰው በማለት ነበር። ለምሳሌ ያህል በፌዴራላዊት ጀርመን ሪፑብሊክ ውስጥ በ15 እና በ24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ከሦስት ልጃገረዶች ውስጥ አንዷና ከአራት ወንዶች ልጆች ውስጥ አንዱ የሚኖሩት ከወላጆቻቸው ቤት ውጭ ነው። ምናልባት እናንተ ራሳችሁም ከወላጆቻችሁ ቤት ወጥታችሁ ለመኖር ታስቡ ይሆናል።

አንድ ሰው ለማግባት ፈልጎ ‘አባቱንና እናቱን እንደሚተው’ አምላክ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 2:​23, 24) ለአምላክ የሚቀርበውን አገልግሎት ማስፋትን የመሳሰሉ ከቤት ለመውጣት የሚያስገድዱ ሌሎች ተገቢ ምክንያቶችም አሉ። (ማርቆስ 10:​29, 30) ይሁን እንጂ ለብዙ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ቤት መውጣት ሊቋቋሙት የማይችሉት መስሎ ከሚታያቸው ሁኔታ መላቀቂያ መንገድ ብቻ ነው። አንድ ወጣት ሲናገር “ከቤት የምትወጡት ራሳችሁን ችላችሁ ለመኖር ስለምትፈልጉ ብቻ ነው። ከወላጆቻችሁ ጋር አብራችሁ መኖር አያረካችሁም። ሁልጊዜ ከነርሱ ጋር ትጨቃጨቃላችሁ። እነርሱም ፍላጎታችሁን አይረዱላችሁም። በተጨማሪም እያንዳንዷን እንቅስቃሴያችሁን ለወላጆቻችሁ መናገር ስለሚኖርባችሁ ዙሪያችሁን በአጥር እንደተከበባችሁ ያህል ሆኖ ይሰማችኋል” ብሏል።

ራሳችሁን ችላችሁ ለመኖር ደርሳችኋልን?

ነገር ግን ከቤት ወጥታችሁ ራሳችሁን ችላችሁ ለመኖር ፍላጎት አላችሁ ማለት ለዚህ ዝግጁ ሆናችኋል ማለት ነውን? መጀመሪያ ነገር ብቻችሁን መኖር የምታስቡትን ያህል ቀላል ላይሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል። የቤት ኪራይ በጣም ውድ ሆኗል። በኢኮኖሚ ችግሮች ታንቀው የተያዙ ወጣቶች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ለማድረግ የሚገደዱት ምንድን ነው? ፑሊንግ አፕ ሩትስ የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲዎች ሲናገሩ “ወደ ቤታቸው ይመለሱና እንደገና በወላጆቻቸው ላይ ሸክም ሆነው ለመኖር ይጠብቃሉ” ብለዋል።

አእምሮአዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ብስለታችሁስ እንዴት ነው? እናንተ በራሳችሁ ሐሳብ አድገናል ብላችኋል፤ ወላጆቻችሁ ግን አሁንም በውስጣችሁ አንዳንድ ‘የሕፃንነት ጠባዮችን’ ያዩባችሁ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 13:​111980 ትርጉም) በእርግጥም በምን ያህል ነፃነት ለመጠቀም እንደደረሳችሁ ሊገመግሙ በሚችሉበት ደረጃ ላይ ያሉት ወላጆቻችሁ አይደሉምን? ከእነርሱ ግምገማ ውጭ እምቢ ብሎ መውጣትና የራሳችሁን ኑሮ መጀመር ጣጣ ሊያመጣባችሁ ይችላል!​— ምሳሌ 1:​8

‘ከወላጆቼ ጋር አልስማማም!’

በእናንተም ላይ የደረሰው ይህ ነውን? ቢሆንም ይህ ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ ለመውጣት የሚያበቃ ምክንያት አይደለም። ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን አሁንም ወላጆቻችሁ ያስፈልጓችኋል፣ ከእነርሱም የምታገኙት ማስተዋልና ጥበብ ለወደፊት ሕይወታችሁ ሳይጠቅማችሁ አይቀርም። (ምሳሌ 23:​22) ታዲያ ከእነርሱ ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ለመስማማት ባለመቻላችሁ ብቻ ከሕይወታችሁ ፈጽማችሁ ልታስወጧቸው ይገባልን?

በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ለመሥራት ከቤቱ የወጣው ካርስተን የተባለ አንድ ጀርመናዊ ወጣት ሁኔታውን እንደሚከተለው ገልጾታል:- “ከወላጆቻችሁ ጋር ልትስማሙ ስላልቻላችሁ ብቻ ፈጽሞ ከቤት አትውጡ። ከወላጆቻችሁ ጋር መስማማት ካልቻላችሁ ከሌሎች ሰዎችስ ጋር እንዴት ልትስማሙ ትችላላችሁ? ከቤት መውጣት ችግሮቻችሁን አያቃልልም። በተቃራኒው ከቤት መውጣታችሁ የሚያረጋግጠው ራሳችሁን ችላችሁ ለመኖር ገና ያልበሰላችሁ መሆናችሁን ብቻ ነው፤ ይህም ይብሱን ከወላጆቻችሁ ጋር ያቆራርጣችኋል።”

ሥነ ምግባርና የልብ ግፊት

ወጣቶች አለጊዜው ከቤት ወጥቶ መኖር የሚያስከትለውን ሥነ ምግባራዊ አደጋ ችላ ማለት ይቀናቸዋል። በሉቃስ 15:​11–32 ላይ ኢየሱስ ከወላጅ ቁጥጥር ነፃ ሆኖ ለመኖር ከቤቱ ስለወጣ አንድ ወጣት ሰው ይናገራል። ወጣቱ ከወላጆቹ ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ በዝሙት ኑሮ በመጠመድ ‘ብኩን’ ሕይወት መኖር ጀመረ። ገንዘቡንም ወዲያውኑ አባክኖ ጨረሰ። ሥራ ለማግኘት ባለመቻሉም አይሁዳውያን በጣም ይንቁት የነበረውን የአሳማ ጥበቃ ሥራ ጀመረ። ይሁን እንጂ አባካኙ ልጅ ወደ ልቡ ተመልሷል። ትዕቢቱን ዋጥ አድርጎም ወደ ቤቱ ተመለሰና አባቱን ይቅርታ ለመነ።

ይህ ምሳሌ የተነገረው የአምላክን ምሕረት ለማጉላት ቢሆንም የሚከተለውን ተግባራዊ ትምህርትም ይዟል:- ጥበብ በጎደለው የልብ ግፊት ተነድቶ ከቤት መውጣት ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትልባችሁ ይችላል! ከወላጅ ነፃ ሆነው መኖር የጀመሩ አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶችም መንፈሳዊ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ያሳዝናል። አንዳንዶቹ በገንዘብ ረገድ ራሳቸውን ችለው ለመኖር ስለሚያቅታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ አኗኗር ካላቸው ወጣቶች ጋር አብረው በመኖር በወጪ መተጋገዝን እንዲመርጡ ተገደዋል።​— 1 ቆሮንቶስ 15:​33

ሆርስት የሚባል አንድ ጀርመናዊ ወጣት ከወላጆቹ ቤት ወጥቶ መኖር የጀመረ አንድ የዕድሜ እኩያው የሆነ ወጣት ትዝ ይለዋል:- “ሕጋዊ ጋብቻ ሳይኖረው ከሴት ጓደኛው ጋር መኖር ጀመረ። መጠጥ እንደ ውኃ በሚንቆረቆርባቸው ግብዣዎች ላይ ይገኝ ስለነበር ብዙውን ጊዜ ይሰክር ነበር። በቤቱ የሚኖር ቢሆን ኖሮ ወላጆቹ ይህን ሁሉ ነገር እንዲያደርግ አይፈቅዱለትም ነበር።” ሆርስት ንግግሩን ሲያጠቃልል “ከቤት ከወጣችሁ በኋላ ብዙ ነፃነት እንደምታገኙ የተረጋገጠ ነው። ይሁንና በፍጹም ሐቀኝነት እንናገር ከተባለ ይህ ነፃነት ብዙውን ጊዜ የሚያገለግለው መጥፎ ነገሮችን ለመሥራት አይደለምን?” ብሏል።

ስለዚህ ተጨማሪ ነፃነት ማግኘት ካማራችሁ ራሳችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ጠይቁ:- ተጨማሪ ነፃነት ለማግኘት የምፈልገው ለምንድን ነው? ተጨማሪ ነፃነት ለማግኘት የምፈልገው የራሴ ንብረት እንዲኖረኝ ወይም እቤት ብኖር ወላጆቼ የሚከለክሉትን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ነፃነት ለማግኘት ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ በኤርምያስ 17:9 ላይ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?” እንደሚል አስታውሱ።

ከወላጆቼ ተለይቼ መኖር ካልጀመርሁ እንዴት ላድግ እችላለሁ?

አዶለሰንስ የተሰኘው መጽሐፍ “ከቤተሰብ ጉያ መውጣቱ ብቻ በተሳካ ሁኔታ [ወደ አዋቂነት] ለመሸጋገር ዋስትና አይሆንም። ከወላጆች ጋር መኖርም ቢሆን አለማደግን አያመለክትም” ይላል። በእርግጥም ማደግ ማለት የራስ ገንዘብ፣ ሥራና መኖሪያ መያዝ ማለት ብቻ አይደለም። መጀመሪያ ነገር ስለ ሕይወት የሚታወቀው ችግሮችን በሁሉም አቅጣጫ በመጋፈጥ ነው። ከማንወዳቸው ሁኔታዎች ሸሽቶ በመሄድ የሚገኝ ጥቅም የለም። “ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው” በማለት ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:​27 ይናገራል።

ለምሳሌ ያህል አብሮ ለመኖር አስቸጋሪ የሆኑ ወይም በጣም ጥብቅ የሆኑ ወላጆችን እንውሰድ። አሁን 47 ዓመት የሆነው ማክ ከትምህርት ቤት ሲመለስ አባቱ የቤት ውስጥ ሥራ ይጭንበት ነበር። ትምህርት ቤት በሚዘጋባቸው ወራት ሌሎች ወጣቶች ሲጫወቱ ማክ ግን መሥራት ነበረበት። “አባታችን እንድንጫወትና ራሳችንን እንድናዝናና ስለማይፈቅድልን በዓለም ካሉት ጨካኝ ሰዎች ሁሉ የበለጠ ጨካኝ ሰው ነው ብዬ አስብ ነበር” ይላል ማክ። “ብዙውን ጊዜ ‘ከዚህ ወጥቼ የራሴ መኖሪያ ባገኘሁ!’ እያልኩ አስብ ነበር።” አሁን ግን ማክ ስለነበረበት ሁኔታ ከበፊቱ የተለየ አመለካከት አለው:- “አባባ ለእኔ እጅግ ውድ የሆነ ነገር አድርጎልኛል። ከባድ ሥራ እንዴት እንደምሠራና ችግርን እንዴት እንደምቋቋም አስተምሮኛል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ከባድ ችግሮች ደርሰውብኛል፣ ይሁን እንጂ እንዴት ችግሮቹን እንደምቋቋም ተምሬ ነበር።”

መቀማጠል

ይሁን እንጂ ከወላጆች ጋር መኖር ብቻውን ብስለት እንድታገኙ ዋስትና አይሆንም። አንድ ወጣት ሲናገር “ከወላጆቼ ጋር ስኖር በጣም ተቀማጥዬ ነበር። ሁሉንም ነገር ያደርጉልኝ ነበር” ብሏል። አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት መለማመድ የማደግ አንዱ ክፍል ነው። እርግጥ ነው ቆሻሻ መድፋትና ልብስ ማጠብ የምትወዱትን ዘፈን እንደማዳመጥ አያስደስትም። ይሁን እንጂ እነዚህን ሥራዎች መሥራት ካልተለማመዳችሁ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? በወላጆቻችሁ ወይም በሌሎች ጫንቃ ላይ የምትኖሩ ራሳችሁን መርዳት የማትችሉ ትላልቅ ሰዎች ልትሆኑ ትችላላችሁ።

ወጣት ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች ምግብ ማብሰል፣ ልብስ ማጠብ፣ መተኮስ፣ ወይም የቤት ውስጥ ዕቃዎችን ወይም መኪናን መጠገን በመማርና በመለማመድ ራሳችሁን ችላችሁ ለመኖር በመዘጋጀት ላይ ናችሁን?

በኢኮኖሚ ራስን መቻል

በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ገንዘብን ለማግኘትም ሆነ ለማጥፋት ቀላል እንደሆነ ነገር አድርገው ይመለከቱታል። የትርፍ ጊዜ ሥራ ካላቸው ገንዘባቸውን በሙዚቃ ማጫወቻዎችና በፋሽን ልብሶች መጨረስ ይቀናቸዋል። ይሁንና እንዲህ ዓይነት ወጣቶች ከወላጆቻቸው ተለይተው ብቻቸውን በሚኖሩበት ጊዜ ፈጽሞ ያልጠበቁት ነገር ያጋጥማቸዋል! (ቀደም ሲል የተጠቀሰው) ሆርስት ሲናገር “[ለብቻዬ መኖር ከጀመርኩ በኋላ] በወሩ መገባደጃ ላይ ቦርሳዬም ሆነ ጓዳዬ ባዶ ይሆናሉ” ብሏል።

ታዲያ ለምን ከወላጆቻችሁ ጋር እያላችሁ የገንዘብ አያያዝ አትማሩም? ወላጆቻችሁ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ለዓመታት ያካበቱት ተሞክሮ ስላላቸው ብዙ ዕንቅፋቶችን እንድታስወግዱ ሊረዷችሁ ይችላሉ። ፑሊንግ አፕ ሩትስ የተሰኘው መጽሐፍ ‘ለኤሌክትሪክ፣ ለማገዶ፣ ለውኃ፣ ለስልክ፣ በየወሩ ምን ያህል ይከፈላል? ለቤት ኪራይና ለግብርስ?’ ብሎ ወላጆችን መጠየቅ ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ ይሰጣል። ሥራ ያላቸው አንዳንድ ወጣቶች ከወላጆቻቸው የበለጠ የኪስ ገንዘብ እንዳላቸው ስታውቁ ልትገረሙ ትችላላችሁ! ስለዚህ እናንተም ሥራ ካላችሁ የቤቱን ወጪ ለመደጎም መጠነኛ አስተዋጽኦ አድርጉ።

ከቤት ከመውጣታችሁ በፊት ተማሩ

ለማደግ ከወላጆቻችሁ ቤት መውጣት አያስፈልጋችሁም። ቢሆንም ከወላጆቻችሁ ጋር በምትኖሩበት ጊዜ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታንና ራስን ዝቅ የማድረግን ባሕርይ ለማዳበር መጣር አለባችሁ። በተጨማሪም ከሌሎች ጋር እንዴት ተስማምታችሁ ለመኖር እንደምትችሉ ተማሩ። ትችትን፣ አለመሳካትን፣ ወይም ያሰቡት ሳይሆን ሲቀር ተስፋ መቁረጥን ለመቋቋም እንደምትችሉ አረጋግጡ። ‘ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ የዋህነትንና ራስን መግዛትን’ ኮትኩቱ። (ገላትያ 5:​22, 23) የአንድ የበሰለ ክርስቲያን ወንድ ወይም የበሰለች ክርስቲያን ሴት እውነተኛ መለያ ምልክቶች እነዚህ ባሕርያት ናቸው።

ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ ጋብቻን የመሳሰሉት ሁኔታዎች ከወላጆቻችሁ ጎጆ መንጥቀው ማውጣታቸው አይቀርም። ታዲያ ከዚያ በፊት ከቤት ለመውጣት ለምን ትቸኩላላችሁ? ለመውጣት ያነሳሳችሁን ምክንያት ከወላጆቻችሁ ጋር ተነጋገሩበት። በተለይ ለቤተሰቡ ደህንነት አስተዋጽኦ የምታበረክቱ ከሆነ ከእነርሱ ጋር ብትኖሩ ደስ ይላቸዋል። በእነርሱ እርዳታም እቤታችሁ ሆናችሁ ማደጋችሁን፣ መማራችሁንና ብስለት ማግኘታችሁን ልትቀጥሉ ትችላላችሁ።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ብዙ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ቤት ወጥተው ለመኖር የሚቻኮሉት ለምንድን ነው?

◻ አብዛኞቹ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ቤት ወጥተው ለመኖር ዝግጁ ያልሆኑት ለምንድን ነው?

◻ አለጊዜው ከወላጅ ቤት ወጥቶ መኖር የሚያመጣቸው አንዳንድ አደጋዎች ምንድን ናቸው?

◻ ከቤታቸው የኮበለሉ ወጣቶችን የሚያጋጥሟቸው አንዳንድ ችግሮች ምንድን ናቸው?

◻ ከወላጆቻችሁ ጋር እየኖራችሁ ልትጎለምሱ የምትችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 57 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከወላጆቻችሁ ጋር ልትስማሙ ስላልቻላችሁ ብቻ ፈጽሞ ከቤት አትውጡ . . . ከሌሎች ሰዎችስ ጋር እንዴት ልትስማሙ ትችላላችሁ?”

[በገጽ 60, 61 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መኮብለል መፍትሄ ነውን?

በየዓመቱ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ወጣቶች ከቤታቸው ይኮበልላሉ። አንዳንዶቹ የሚኮበልሉት አካላዊ ወይም ጾታዊ በደልን የመሳሰሉ ሊቋቋሙ የማይችሏቸው መጥፎ ሁኔታዎች ሲደርሱባቸው ነው። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ቤት የሚኮበልሉት ከወላጆቻቸው ጋር በሰዓት እላፊ፣ በትምህርት ውጤት፣ በቤት ውስጥ ሥራ፣ በጓደኛ ምርጫና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ጭቅጭቅ በመነሳቱ ምክንያት ነው።

ምናልባት የእናንተም ወላጆች በነገሮች ላይ ያላቸው አመለካከትና አስተሳሰብ ከእናንተ አመለካከትና አስተሳሰብ ጋር አይጣጣም ይሆናል። ይሁን እንጂ ወላጆቻችሁ እናንተን ‘በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ’ እንዲያሳድጉ በአምላክ ፊት ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ተገንዝባችኋልን? (ኤፌሶን 6:​4) ስለዚህ ወደ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎችና ተግባሮች አብራችኋቸው እንድትሄዱ ይጎተጉቷችሁ ይሆናል። ወይም ደግሞ ከሌሎች ወጣቶች ጋር ባላችሁ ጓደኝነት ላይ ገደብ ይወስኑባችሁ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 15:​33) ታዲያ እንዲህ ማድረጋቸው ለማመፅ ወይም ለመኮብለል ምክንያት ይሆናልን? እናንተም በአምላክ ፊት “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው ግዴታ አለባችሁ።​— ኤፌሶን 6:​1–3

ከዚህም ሌላ መኮብለል ለምንም ነገር መፍትሔ አይሆንም። “መኮብለል የሚያስገኘው ነገር ቢኖር ተጨማሪ ችግሮችን ብቻ ነው” ትላለች በ14 ዓመቷ ኮብልላ የነበረችው አሚ። ማርጋሬት ኦ ሃይድ ማይ ፍሬንድ ዎንትስ ቱ ራን አዌይ (ወዳጄ ሊኮበልል ይፈልጋል) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “እንደ እውነቱ ከሆነ ከኮብላዮች መካከል ሥራ የሚያገኙትና ራሳቸውን ችለው ለመኖር የሚችሉት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ለብዙዎቹ ግን ኑሮ ከቤታቸው ከመውጣታቸው በፊት ከነበሩበት የበለጠ የከፋ ይሆንባቸዋል” ብለዋል። በተጨማሪም ቲን የተሰኘው መጽሔት ሲያስገነዝብ “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በጎዳና ተዳዳሪነት ኑሮ ነፃነት አያገኙም። በነፃነት ፈንታ የሚያገኙት በጾታ ከሚደፍሯቸው ወይም ከሚዘርፏቸው ሰዎች ሊያስጥሏቸው በማይችሉ ወና ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ እንደ እነርሱ ከቤታቸው የኮበለሉ ወይም የተባረሩ ወጣቶችን ነው። በተጨማሪም ወጣቶችን በመበዝበዝ ርካሽ ተግባር ላይ የተሠማሩ ሰዎች ያጋጥሟቸዋል። በእነዚህ ሰዎች እጅ በቀላሉ ሊገቡ የሚችሉት ደግሞ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣት ኮብላዮች ናቸው” ይላል።

አሚ ከወላጆችዋ በኮበለለችበት ጊዜ “ጓደኛዋ” የሆነው የ22 ዓመት ወጣት ከእርሱ ጋር ለተቀመጠችበት ኪራይ “ከእርሱና ከዘጠኝ ጓደኞቹ ጋር የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽም በማድረግ” ያስከፍላት ነበር። በተጨማሪም “ትሰክርና አደንዛዥ ዕፆችን በብዛት ትወስድ ነበር።” ሳንዲ የተባለች ሌላ ልጃገረድ ደግሞ የሚያሳድጋት አያቷ በጾታ እየተዳፈረ ስላስቸገራት ኮበለለች። ከዚያ በኋላ በመንገድ ላይ የምትኖርና በመናፈሻ ውስጥ ባሉ አግዳሚ መቀመጫዎች ወይም ባገኘችበት የምትተኛ ዝሙት አዳሪ ሆነች። እነዚህ ወጣቶቸ የብዙዎቹን ኮብላዮች ዕጣ የሚያመለክቱ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው።

አብዛኞቹ ኮብላዮች ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችል ሞያ የላቸውም። ወይም ደግሞ ሥራ ለመያዝ የሚያስፈልጉት የወረቀት መረጃዎች ማለትም የልደት የምሥክር ወረቀት፣ የመንግሥት ድጎማ ካርድ፣ ቋሚ አድራሻና የመሳሰሉት የላቸውም። ሉወስ “ለመስረቅ ወይም ሰዎችን አቁሜ ገንዘብ እንዲሰጡኝ ለመለመን እገደድ ነበር። ብዙውን ጊዜ ግን ለምኜ የሚሰጠኝ ስለማላገኝ እሰርቅ ነበር” ይላል። 60 በመቶ የሚሆኑት ኮብላዮች ሴቶች ሲሆኑ ብዙዎቹ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩት በዝሙት አዳሪነት ነው። ወሲባዊ ሥዕሎችን የሚያዘጋጁ ሰዎች፣ የዕፅ ነጋዴዎችና ለዝሙት አዳሪነት የሚደልሉ ሰዎች ኮብላይ ወጣቶችን ፈልገው መጠቀሚያ ለማድረግ ወደ አውቶቡስ ተራዎች መሄድን ያዘወትራሉ። ለተደናገጡት ወጣቶች የሚተኙበት ቦታና የሚበሉት ምግብ ይሰጧቸው ይሆናል። ምናልባትም የተወደዱ መሆናቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ እቤታቸው ሳሉ ያላገኙትን ነገር ይሰጧቸው ይሆናል።

ይሁንና ከጊዜ በኋላ እነዚህ “በጎ አድራጊዎች” ክፍያ ይጠይቃሉ። ይህም ክፍያ በዝሙት አዳሪነት ተሰማርቶ ለእነርሱ ጥቅም ማስገኘት ወይም ከተፈጥሮ ውጭ በሆኑ የጾታ ድርጊቶች መካፈል፣ ወይም ወሲባዊ ፎቶግራፎችን መነሳት ሊሆን ይችላል። ብዙ ኮብላዮች በመጨረሻው አሠቃቂ የአካል ጉዳት የሚደርስባቸው ወይም የሚገደሉ መሆናቸው አያስደንቅም!

እንግዲያውስ ከመኮብለላችሁ በፊት ከወላጆቻችሁ ጋር ለመነጋገር ማንኛውንም ጥረት በተደጋጋሚ ማድረግ አስተዋይነት ነው። ምን እንደሚሰማችሁና ምን ለማድረግ እንዳሰባችሁ ለወላጆቻችሁ አሳውቋቸው። (ምዕራፍ 2 እና 3ን ተመልከቱ።) ጉዳዩ አካላዊ ወይም ጾታዊ በደልን የሚመለከት ከሆነ የውጭ ዕርዳታ ማግኘት ሊያስፈልግ ይችላል።

ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን፣ ተነጋገሩበት እንጂ አትኮብልሉ። በወላጆቻችሁ ቤት የምትኖሩት ኑሮ እንከን የሌለበት ባይሆንም እንኳን በምትኮበልሉበት ጊዜ ነገሮች የባሰ መጥፎ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውሱ።

[በገጽ 59 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ራስን ችሎ ለብቻ ለመኖር የሚያስፈልጉትን የቤት ውስጥ ሞያዎች ለመማር የሚቻለው ከወላጆች ጋር ሳላችሁ ነው