ለማግባት ደርሻለሁን?
ምዕራፍ 30
ለማግባት ደርሻለሁን?
ጋብቻ ጨዋታ አይደለም። የአምላክ ዓላማ ባልና ሚስት ከማንም ሰው ይበልጥ እንዲቀራረቡና ዘላቂነት ያለው ጽኑ ትስስር እንዲመሠርቱ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) በመሆኑም የትዳር ጓደኛ በቀሪው ሕይወታችሁ በሙሉ ተቆራኝቷችሁ ወይም ተቆራኝታችሁት የምትኖሩት ግለሰብ ነው።
ትዳር የመሠረተ ማንኛውም ሰው አንድ ዓይነት “ሥቃይና ኀዘን” እንደሚያጋጥመው የተረጋገጠ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:28 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ይሁን እንጂ የባሕርይ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርሲያ ላስዌል እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃሉ፦ “አንድ ጋብቻ ዘላቂ መሆንና አለመሆኑን የሚወስን፣ ብዙ ሰዎች አላንዳች ክርክር የሚቀበሉት ነገር ቢኖር በጣም ወጣት ሳሉ የሚያገቡ ሰዎች ጋብቻቸው ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ችግር የሚገጥማቸው መሆኑ ነው።”
በወጣትነት ዕድሜ የሚመሠረቱ ብዙ ትዳሮች የማይሰምሩት ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ለጋብቻ መድረስ አለመድረሳችሁን እንድትወስኑ ያስችላችኋል።
ከፍተኛ ተስፋዎች
“ስለ ጋብቻ ምንነት የነበረን አስተሳሰብ በጣም ደካማ ነበር” በማለት በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ልጃገረድ አምናለች። “መጣ ሄድ ማለት፣ እንደፈለግን ማድረግ፣ የበላንባቸውን ዕቃዎች ስንፈልግ ማጠብ ሳንፈልግ ደግሞ መተው የምንችል መስሎን ነበር። ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም።” ብዙ ወጣቶች ስለ ጋብቻ ያላቸው አመለካከት ይህን የመሰለና ብስለት የጎደለው ነው። ጋብቻ ፍቅር ብቻ የሚኖርበት የሕልም ዓለም ይመስላቸዋል። ወይም ደግሞ በጋብቻ ቃል ኪዳን ውስጥ የሚገቡት ትልቅ ሰው መስለው ለመታየት ስለሚፈልጉ ብቻ ነው። ሌሎች ደግሞ የሚያገቡት በቤታቸው፣ በትምህርት ቤት ወይም በማኅበረሰባቸው ውስጥ ከሚያጋጥማቸው መጥፎ ሁኔታ ለማምለጥ ሲሉ ነው። አንዲት ልጃገረድ ለእጮኛዋ “ካገባሁ በኋላ በጣም ደስተኛ እሆናለሁ። ምክንያቱም የራሴን ውሳኔ መወሰን አይኖርብኝም!” ብላዋለች።
ይሁን እንጂ ጋብቻ የሕልም ዓለም ወይም ለሁሉም ዓይነት ችግሮች ፈውስ የሚያስገኝ መድኃኒት አይደለም። ጋብቻ የሚያመጣው ነገር ቢኖር ልትቋቋሟቸው የሚገቡ ጨርሶ አዳዲስ የሆኑ ችግሮችን ነው። “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የሚያገቡት ዕቃ ዕቃ ለመጫወት ነው” በማለት በ20 ዓመቷ የመጀመሪያ ልጅዋን የወለደችው ቪኪ ትናገራለች። “ዋ! ነገሩ እንዲህ ቀልድ ይመስላል! የምትወልዱት ልጅ የሚያምር ቆንጆ አሻንጉሊት፣ በጣም ውብ የሆነ መጫወቻ የሚሆንላችሁ ይመስላችኋል። ነገሩ ግን እንዲህ አይደለም።”
ብዙ ወጣቶች ከወሲባዊ ግንኙነት እውን የማይሆን ደስታ ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። በ18 ዓመቱ ያገባ አንድ ወጣት ሰው “ካገባሁ በኋላ በታላቅ ጉጉት ይጠበቅ የነበረው የወሲብ ደስታ ፈጥኖ እንደሚሰክንና አንዳንድ እውነተኛ ችግሮች ብቅ ማለት እንደሚጀምሩ ተገነዘብኩ” ብሏል። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው በተጋቡ ባልና ሚስቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ከገንዘብ ችግሮች ቀጥሎ ብዙ ጭቅጭቅ የሚነሳው በወሲባዊ ግንኙነት ጉዳይ እንደሆነ ደርሶበታል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት አርኪ የጋብቻ ግንኙነት የሚኖረው ከራስ ወዳድነት ነፃ በመሆንና ራስን ከመቆጣጠር ነው። እነዚህ ደግሞ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ገና ያላዳበሯቸው ባሕርያት ናቸው። — 1 ቆሮንቶስ 7:3, 4
መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘ከአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ካለፉ በኋላ’ እንዲያገቡ ያበረታታል። (1 ቆሮንቶስ 7:36) የፍትወት ስሜት አይሎ በሚገኝበት ዕድሜ ማግባት አስተሳሰባችሁን ሊያዛባውና ወደፊት የትዳር ጓደኛችሁ የሚሆነውን ሰው ጉድለቶች እንዳይታያችሁ ሊያሳውራችሁ ይችላል።
ትዳራቸው ለሚጠይቅባቸው የሥራ ድርሻ ዝግጁ ያልሆኑ
በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የምትገኝ አንዲት ሙሽራ ስለ ባሏ እንደሚከተለው ብላለች፦ “አሁንማ ከተጋባን በኋላ ለእኔ ስሜት ያለው የሚመስለው ወሲባዊ ግንኙነት በሚፈልግበት ጊዜ ብቻ ነው። ከወንድ ጓደኞቹ ጋር አብሮ መሆን ከእኔ ጋር የመሆንን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማዋል። . . . ጓደኛው እኔ ብቻ የምሆን መስሎኝ ነበር። ግን ተሞኝቻለሁ።” በወጣቶች ላይ የሚታየውን አንድ የተሳሳተ አስተሳሰብ አጉልቶ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። አባወራ ከሆኑም በኋላ ገና እንደ ነጠላ ወንዶች መኖር የሚችሉ ይመስላቸዋል።
አንዲት 19 ዓመት የሆናት ሙሽራ በወጣት ሚስቶች ዘንድ የተለመደ አንድ ችግር ገልጻለች፦ “ቤት ከማጽዳትና ምግብ ከማሰናዳት ይልቅ ቴሌቪዥን ብመለከትና ብተኛ እመርጣለሁ። የባሌ ወላጆች ሊጠይቁን ሲመጡ በጣም አፍራለሁ። ምክንያቱም የእነሱ ቤት ሁልጊዜ ንጽሕናው የተጠበቀ ሲሆን የእኔ ግን ሁልጊዜ የተዝረከረከ ነው። በምግብ አሠራርም በጣም ደካማ ነኝ።” አንዲት ሴት የቤት ውስጥ ሥራዋን አጠናቅቃ የማትሠራና ሞያ የሌላት ከሆነች በትዳርዋ ላይ ተጨማሪ ውጥረት ታመጣለች! ቀደም ብለን የጠቀስናት ቪኪ “ጋብቻ አንዱ ለሌላው የሚኖርበት ቃል ኪዳን ነው” ብላለች። “ጋብቻ ጨዋታ አይደለም። የሠርጉ ዕለት ደስታ ፈጥኖ ያልፋል። ወዲያውኑ የዕለት ተዕለት ኑሮ መኖር ይጀመራል። ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም።”
ቤተሰብን ለማኖር ስለሚደረገው የዕለት ተዕለት ልፋትስ ምን ሊባል ይቻላል? የቪኪ ባል የሆነው ማርክ እንደሚከተለው ብሏል፦
“በመጀመሪያው ሥራዬ ላይ ሳለሁ በሥራ ገበታዬ ላይ ለመገኘት ጧት በ12 ሰዓት መነሳት እንደነበረብኝ አስታውሳለሁ። ‘በጣም ከባድ ሥራ ነው። ከዚህ ድካም የምገላገልበት ጊዜ ይኖር ይሆን?’ እያልኩ አስብ ነበር። ወደ ቤት ስመለስ ደግሞ ቪኪ የቀኑን ልፋቴን ፈጽሞ እንደማትረዳልኝ ይሰማኝ ነበር።”የገንዘብ ችግር
ይህም ለወጣት ተጋቢዎች የትዳር መበጥበጥ ሌላ መንስኤ ወደሆነው ወደ ገንዘብ ችግር ያመጣናል። አርባ ስምንት የሚያክሉ ወጣት ባልና ሚስቶች ከተጋቡ ከሦስት ወር በኋላ ትልቁ ችግራቸው ሆኖ ያገኙት “የቤተሰቡን ገቢ ማብቃቃት” እንደሆነ አምነዋል። ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ ከእነዚህ ባልና ሚስቶች መካከል 37ቱ እንደገና ያንኑ ጥያቄ ተጠይቀው ነበር። አሁንም የገንዘብ ጉዳይ ዋነኛ ችግር እንደሆነባቸውና እንዲያውም ምሬታቸው ከበፊቱ የከፋ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። “ከኑሮ እርካታ ለማግኘት የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች የምትገዙበት ገንዘብ ሳይኖራችሁ ከሕይወት ምን ዓይነት ደስታ ልታገኙ ትችላላችሁ?” በማለት ቢል ጠይቋል። “ከወር እስከ ወር የሚያደርሳችሁ ገንዘብ ከሌላችሁ ብዙ ጥልና ኀዘን ሊያጋጥማችሁ ይችላል።”
የገንዘብ ችግር በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥማቸው ችግር ነው። ምክንያቱም ከፍተኛ የሥራ አጥነት የሚደርስባቸውና አነስተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው እነርሱ በመሆናቸው ነው። “ቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ማቅረብ ስላልቻልኩ ከወላጆቼ ጋር ለመኖር ተገደድን” በማለት ሮይ አምኗል። “ይህም፣ በተለይ ልጅ ስለነበረን፣ ብዙ ጭንቀት ፈጥሮብናል።” ምሳሌ 24:27 (የ1980 ትርጉም) “በመጀመሪያ በርስትህ ላይ ለኑሮህ የሚያስፈልግህን ሁሉ አደራጅ፤ ከዚያ በኋላ ቤት መሥራትና ትዳር መመሥረት ትችላለህ” በማለት ይመክራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ወንዶች ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ሀብት ለማፍራት ጠንክረው ይሠሩ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት ባሎች እንዲህ ዓይነቱን በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ በመቅረታቸው ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ማቅረብ ከባድ ሸክም ይሆንባቸዋል።
ይሁን እንጂ ባልና ሚስቱ ስለ ቁሳዊ ነገሮች ያልበሰለ አመለካከት ያላቸው ከሆኑ ጥሩ ደመወዝ ማግኘታቸው ብቻውን የገንዘብ ችግራቸውን አያስወግድላቸውም። አንድ ጥናት “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች አዲስ ለሚመሠርቷቸው ጎጆዎች ወላጆቻቸው ምናልባት ከብዙ ዓመታት ልፋት በኋላ ካፈሯቸው ዕቃዎች ብዙዎቹን 1 ጢሞቴዎስ 6:8–10
ወዲያውኑ ትዳር እንደያዙ መግዛት እንደሚችሉ ተስፋ አድርገው እንደነበረ” ገልጿል። እነዚህን ቁሳቁሶች አሁኑኑ ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ በማድረጋቸውም ብዙዎቹ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል። “ምግብና ልብስ” በማግኘታቸው ብቻ በቃኝ ለማለት የሚያስፈልገው ብስለት ስለሚጎድላቸው በጋብቻቸው ላይ ውጥረት ይጨምራሉ።—“የማይገናኙ ግቦች”
ሞሪን እንደሚከተለው በማለት ታስታውሳለች፦ “ዶንን እወደው ነበር። በጣም መልከ ቀና፣ ጠንካራ፣ ጥሩ ቁመና የነበረውና ዝነኛ ነበር። . . . ጋብቻችን ጥሩ መሆን ነበረበት።” ግን አልሆነም። በመካከላቸው የነበረው ቅሬታ እየሰፋ ሄዶ ሞሪን “ዶን የሚያደርገው ነገር ሁሉ፣ ምግብ ስንበላ የሚያሰማው ድምፅ ሳይቀር ያናድደኝ ጀመር። በመጨረሻም ሁለታችንም መቻቻል አቃተን” እስከማለት ደረሰች። ጋብቻቸው በሁለት ዓመት ውስጥ ፈረሰ።
ችግራቸው ምን ነበር? ሞሪን “የኑሮ ግቦቻችን የማይገናኙ ነበሩ” በማለት ትገልጻለች። “የአእምሮ ብስለት ካለው ሰው ጋር መነጋገርና መጨዋወት እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። የዶን ጠቅላላ ሕይወት ግን ያተኮረው በስፖርት ላይ ብቻ ነበር። በ18 ዓመት ዕድሜዬ በጣም አስፈላጊ ናቸው ብዬ አስባቸው የነበሩት ነገሮች ወዲያውኑ ለኔ ምንም ትርጉም የማይሰጡ ሆኑብኝ።” ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ለመልክ ቅድሚያ ስለሚሰጡ ከትዳር ጓደኛ ስለሚፈልጉት ነገር ያላቸው አመለካከት ብስለት የጎደለው ነው። ምሳሌ 31:30 “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል።
ራስን መመርመር
መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ አንድ ስዕለት ከተሳለ ‘በኋላ የሚጸጸትን’ ሰው ችኩል ይለዋል። (ምሳሌ 20:25) እንግዲያስ የጋብቻ ስዕለትን የመሰለ ከባድ ነገር ውስጥ ከመግባታችሁ በፊት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ተመሥርታችሁ ራሳችሁን ብትመረምሩ አስተዋይነት አይሆንምን? ለመሆኑ የሕይወታችሁ ግብ ምንድን ነው? ጋብቻችሁስ በዚህ ግባችሁ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ያስከትላል? ለማግባት የፈለጋችሁት ወሲባዊ ግንኙነት ለማድረግ ወይም ከችግር ለመሸሽ ብቻ ነውን?
በተጨማሪም የባልነትን ወይም የሚስትነትን የሥራ ድርሻ ለመወጣት ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል? ቤተሰብን ለማስተዳደር ወይም ለመተዳደሪያ የሚበቃ ገቢ ለማግኘት ችሎታ አላችሁን? ከወላጆቻችሁ ጋር ዘወትር የምትጨቃጨቁ ከሆነ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ለመስማማት ትችላላችሁን? ከጋብቻ ጋር የሚመጡትን ችግሮችና መከራዎች ለመቋቋም ትችላላችሁን? የገንዘብ አያያዝን በተመለከተ በእርግጥ ‘የልጅነት ጠባያችሁን’ አስወግዳችኋልን? (1 ቆሮንቶስ 13:11) ወላጆቻችሁ በዚህ ረገድ ምን ያህል ብቃት እንዳላችሁ ሊነግሯችሁ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም።
ጋብቻ የከፍተኛ ደስታ ወይም ደግሞ የከፍተኛ ምሬትና ሥቃይ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ይህ በአብዛኛው የሚመካው ለጋብቻ ባላችሁ ዝግጁነት ላይ ነው። ገና በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የምትገኙ ከሆነ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ መጫወት ለመጀመር አትቸኩሉ። ጥቂት ብትቆዩ የሚደርስባችሁ ጉዳት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ ጋብቻን ያህል ከባድና ዘላቂ እርምጃ ለመውሰድ በምትፈልጉበትና በምትወስኑበት ጊዜ ጋብቻው ለሚጠይቅባችሁ ኃላፊነት ዝግጁ ለመሆን የሚያስፈልጋችሁን ጊዜ ይሰጣችኋል።
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ አንዳንድ ወጣቶች ስለ ጋብቻ እንዴት ያሉ ያልበሰሉ አመለካከቶች ይይዛሉ?
◻ ለወሲብ ብቻ ሲባል ማግባት ትክክል አይደለም ብላችሁ የምታስቡት ለምንድን ነው?
◻ አንዳንድ ወጣቶች ባል ወይም ሚስት መሆን ለሚያስከትለው የሥራ ኃላፊነት ዝግጁ ሆነው ያልተገኙት እንዴት ነው?
◻ ወጣት ባልና ሚስቶች ብዙውን ጊዜ በገንዘብ ጉዳይ ከባድ ችግር የሚያጋጥማቸው ለምንድን ነው?
◻ አንዳንድ ወጣቶች የትዳር ጓደኛ በሚመርጡበት ጊዜ ምን ስህተት ይሠራሉ?
◻ ለጋብቻ ደርሳችሁ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ራሳችሁን ምን ጥያቄዎች መጠየቅ ትችላላችሁ? በዚህ ርዕስ ላይ የቀረበውን እውቀት ካገኛችሁ በኋላ ጋብቻ ለመመሥረት ምን ያህል የተዘጋጃችሁ እንደሆናችሁ ይሰማችኋል?
[በገጽ 240 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“አንድ ጋብቻ ዘላቂ መሆንና አለመሆኑን የሚወስን፣ ብዙ ሰዎች አላንዳች ክርክር የሚቀበሉት ነገር ቢኖር በጣም ወጣት ሳሉ የሚያገቡ ሰዎች ጋብቻቸው ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ችግር የሚገጥማቸው መሆኑ ነው።”— ማርሲያ ላስዌል፣ የባሕርይ ሳይንስ ፕሮፌሰር
[በገጽ 237 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ወጣቶች ትዳር የሚመሠርቱት ከእነዚህ ሕፃናት የተሻለ ዝግጅት ሳያደርጉ ነው