በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ፍቅር መሆን አለመሆኑን እንዴት አውቃለሁ?

እውነተኛ ፍቅር መሆን አለመሆኑን እንዴት አውቃለሁ?

ምዕራፍ 31

እውነተኛ ፍቅር መሆን አለመሆኑን እንዴት አውቃለሁ?

ፍቅር ከጥሩ ጎኑ በስተቀር መጥፎ ጎኑ ለማይታያቸውና በፍቅር ለታወሩ ሰዎች፣ በሕይወት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ የሚያጋጥም፣ በጣም ጥልቅና ምሥጢራዊ የሆነ የደስታ ስሜት የሚያሳድር ነገር ነው። ፍቅር፣ እነሱ እንደሚያምኑት፣ በልብ ውስጥ ብቻ የሚሰማ፣ ለመረዳት የማይቻል፣ ሲያጋጥም ብቻ የሚታወቅ ነገር ነው። ፍቅር ሁሉንም ነገር አሸንፎ ለዘላለም ይዘልቃል . . .

ስለ ፍቅር የሚነገረው ተደጋጋሚ መግለጫ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። በፍቅር መያዝ ልዩ የሆነ አስደሳች ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እውነተኛ ፍቅር ምንድን ነው?

ወዲያው እንደተያዩ መዋደድ?

ዴቪድ ጃኔትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኛት በአንድ ድግስ ላይ ነበር። ወዲያውኑም ውብ ቁመናዋና ስትስቅ ፀጉሯ በዓይኗ ዙሪያ ከንበል ማለቱ ማረከው። ጃኔትም በደማቅ ቡናማ ዓይኖቹና በተጨዋችነቱ ተማረከች። ያጋጠማቸው ሁኔታ ወዲያው እንደተያዩ የሚዋደዱ ሰዎችን የመሰለ ነበር።

በቀጣዩቹ ሦስት ሳምንታት ጃኔትና ዴቪድ አልተነጣጠሉም። ከዚያ በኋላ ግን ጃኔት ከቀድሞ የወንድ ጓደኛዋ አስፈሪ የስልክ ጥሪ ደረሳት። ዴቪድን እንዲያጽናናት ጠራችው። እሱ ግን ግራ ስለተጋባና ስለ ፈራ የሰጣት ምላሽ በጣም ቀዝቀዝ ያለ ነበር። ለዘላለም ይዘልቃል ብለው ያሰቡት ፍቅር በዚያ ዕለት ማታ አከተመ።

ፊልሞች፣ መጻሕፍትና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በመጀመሪያ እይታ የሚይዛችሁ ፍቅር ዘላቂነት እንደሚኖረውና ዘላለማዊ እንደሚሆን ሊያሳምኗችሁ ይፈልጋሉ። ሁለት ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ግለሰቦች ሲተያዩ አንዳቸው በሌላው ላይ ልዩ ትኩረት እንዲያሳድሩ የሚያደርጋቸው የመጀመሪያ ነገር አብዛኛውን ጊዜ አካላዊ ውበት መሆኑ ጥርጥር የለውም። አንድ ወጣት ሰው እንደተናገረው “የአንድን ሰው ባሕርይ ‘ማየት’ ከባድ ነው።” ይሁን እንጂ ትውውቁ የቆየው ለሰዓታት ወይም ለቀናት ብቻ በሚሆንበት ጊዜ ፍቅር የያዘው ሰው “የሚወደው” ምንድን ነው? የተወደደውን ሰው ውጫዊ መልክ ብቻ አይደለምን? በእርግጥ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ስለ ግለሰቡ አስተሳሰብ፣ ተስፋ፣ ስጋት፣ እቅድ፣ ልማድ፣ ሙያ ወይም ችሎታ ብዙ ማወቅ አይቻልም። የተዋወቃችሁት ውጫዊ ሽፋን ከሆነው ከቁርበቱ ጋር ነው እንጂ “ከተሰወረው የልብ ሰው” ጋር አይደለም። (1 ጴጥሮስ 3:​4) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ምን ያህል ዘላቂ ሊሆን ይችላል?

መልክ አታላይ ነው

በተጨማሪም ውጫዊ መልክ አሳሳች ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው” ይላል። አንድ የስጦታ ዕቃ የተሸፈነበት አብረቅራቂ መጠቅለያ በውስጡ ስላለው ዕቃ ምንም የሚነግራችሁ ነገር የለም። እንዲያውም በጣም አሸብራቂ የሆነ መጠቅለያ ምንም ጥቅም የሌለው ስጦታ ተሸፍኖበት ሊሆን ይችላል።​— ምሳሌ 31:​30

የምሳሌ መጽሐፍ “የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፣ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት” ይላል። (ምሳሌ 11:​22) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በአፍንጫ ላይ ጌጥ ማድረግ የተለመደ ነበር። ጌጡ በጣም የሚያምርና ብዙ ጊዜም ከጥሩ ወርቅ የሚሠራ ነበር። በአንዲት ሴት ገጽታ ላይ ለመታየት የመጀመሪያው የሚሆነው እንዲህ ያለው ጌጥ እንደሆነ ግልጽ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ከውጭ ስትታይ ውብ ሆና “ጥበብ” የሚጎድላትን ሴት ‘በእርያ አፍንጫ ላይ ካለ የወርቅ ቀለበት’ ጋር ማወዳደሩ ተገቢ ነው። ውበት ጥበብ ለሌላት ሴት ምንም አይጠቅማትም። ምንም ጥቅም የማይሰጣት ጌጥ ነው። በመጨረሻም አንድ ቆንጆ የወርቅ ቀለበት አንድን አሳማ እንደማያሳምረው ሁሉ ይህችንም ሴት ሊያሳምራት አይችልም! ስለዚህ በአንድ ሰው ውጫዊ መልክ ‘በፍቅር’ ተይዞ ውስጣዊ ማንነቱን ችላ ማለት ምንኛ ታላቅ ስህተት ነው።

ከሁሉ የበለጠ አታላይ የሆነው ነገር”

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች የሰው ልብ የማይሳሳት የፍቅር መመዘኛ እንዳለው ይሰማቸዋል። ‘ብቻ ልባችሁን አዳምጡት። የያዛችሁ ፍቅር እውነተኛ መሆንና አለመሆኑን ይነግራችኋል!’ ይላሉ። ሐቁ ከዚህ አስተሳሰብ ጋር አይስማማም። ከ18 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ 1,079 ወጣቶች እስከዚህ ዕድሜያቸው ድረስ በአማካይ ሰባት ጊዜ ፍቅር እንደያዛቸው መናገራቸውን አንድ ጥናት ሪፖርት አድርጓል። ከእነዚህም የሚበዙት ከዚህ በፊት የያዛቸው ፍቅር ዘላቂነት ያልነበረውና ጊዜያዊ የሆነ የወረት ፍቅር እንደነበረ አምነዋል። ሆኖም እነዚህ ወጣቶች “በተጠየቁበት ጊዜ የያዛቸው ፍቅር እውነተኛ ፍቅር እንደሆነ ተናግረዋል”! ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል የሚበዙት አሁን የያዛቸውም ፍቅር ቢሆን እንደ ቀድሞው ተራ የሆነ የወረት ፍቅር ነው የሚሉበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።

የሚያሳዝነው ነገር በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች በየዓመቱ ‘ፍቅር’ ይዞኛል በሚል ቅዠት ተነሳስተው መጋባታቸውና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን በጣም ተሳስተው እንደነበረ መገንዘባቸው ነው። ወረት “ያልጠረጠሩ ወንዶችንና ሴቶችን ወደ መታረድ እንደሚነዳ በግ ፍጻሜው የማያምር ጋብቻ እንዲመሠርቱ ያደርጋቸዋል” በማለት ሬይ ሾርት ሴክስ፣ ላቭ ኦር ኢንፋችዌሽን በተባለ መጽሐፋቸው ላይ ተናግረዋል።

“በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ [“ደደብ” አዓት] ነው።” (ምሳሌ 28:​26) በጣም ብዙ ጊዜ የልባችን ሚዛን አሳሳች ወይም አቅጣጫውን የሳተ ይሆናል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉ የበለጠ አታላይ የሆነው ነገር ልብ ነው” ይላል። (ኤርምያስ 17:​9 ዘ ሊቪንግ ባይብል) ሆኖም ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ምሳሌ በመቀጠል “በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል” ይላል። እናንተም በወረትና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለዘወትር አይወድቅም ከተባለለት እውነተኛ ፍቅር መካከል ያለውን ልዩነት ካወቃችሁ በሌሎች ወጣቶቸ ላይ ከደረሰው አደጋና ተስፋ መቁረጥ ልትድኑ ትችላላችሁ።

እውነተኛ ፍቅር ከወረት ጋር ሲነጻጸር

“የወረት ፍቅር ዕውር ነው። ዕውር ሆኖ መኖርንም ይመርጣል። እውነታውን ማየት አይወድም” በማለት የ24 ዓመቱ ካልቪን አምኗል። ኬንያ የተባለችው የ16 ዓመት ልጃገረድ ደግሞ “ከአንድ ሰው ጋር የወረት ፍቅር ሲይዛችሁ ያ ሰው የሚያደርገው ነገር ሁሉ ፍጹም ትክክል እንደሆነ አድርጋችሁ ታስባላችሁ” በማለት አክላለች።

የወረት ፍቅር አስመሳይ ፍቅር ነው። ገሃድ የሆነውን ሐቅ ለማየት የማይፈልግና ራስ ወዳድ ነው። የወረት ፍቅር የያዛቸው ሰዎች ‘ከእርሱ ጋር ስሆን በጣም ትልቅ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል። እንቅልፍ አይወስደኝም። እንዴት ያለ ግሩም ስሜት እንደሆነ ማመን ያቅተኛል’ ወይም ‘በጣም ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ ታደርገኛለች’ የማለት ዝንባሌ አላቸው። በዚህ አባባል ለራስ የተሰጠውን ትኩረት ልብ ብላችኋል? በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ውሎ አድሮ መፍረሱ የማይቀር ነው! ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውነተኛ ፍቅር የሚሰጠው መግለጫ እንዲህ ይላል:- “ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም።”​— 1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ፍቅር ‘የራሱን ጥቅም የማይፈልግ’ በመሆኑ ለኔ ብቻ የሚል ወይም ራስ ወዳድ አይደለም። እውነት ነው፣ አንድ ወንድና ሴት ጠንካራ የሆነ የመዋደድ ስሜት ሊኖራቸውና እርስ በርሳቸው ሊሳሳቡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ስሜታቸው ከምክንያታዊ አስተሳሰብና አንዱ ለሌላው ባለው ጥልቅ አክብሮት መለዘብ ይኖርበታል። እውነተኛ ፍቅር ሲይዛችሁ ለራሳችሁ ደህንነትና ደስታ የምታስቡትን ያህል ለወደዳችሁት ሰው ደህንነትና ደስታ ታስባላችሁ። ከልክ ያለፈ የስሜት ግንፋሎት የማመዛዘን ችሎታችሁን እንዲያጠፋባችሁ አትፈቅዱም።

የእውነተኛ ፍቅር ምሳሌ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የያዕቆብና የራሔል ታሪክ ለእውነተኛ ፍቅር ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። እነዚህ ባልና ሚስት መጀመሪያ የተገናኙት ራሔል የአባቷን በጎች ውኃ ልታጠጣ በመጣችበት በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ነበር። ያዕቆብ ወዲያውኑ በራሔል የተማረከው ‘መልከ መልካምና ፊትዋም የተዋበ’ ስለነበረ ብቻ ሳይሆን የይሖዋ አምላኪ በመሆኗ ጭምር ነበር።​— ዘፍጥረት 29:​1–12, 17

ያዕቆብ በራሔል ቤተሰቦች ቤት አንድ ወር ከተቀመጠ በኋላ ራሔልን እንደወደዳትና ሊያገባት እንደሚፈልግ አስታወቀ። ታዲያ ያዕቆብን የያዘው የወረት ፍቅር ነበርን? አልነበረም! በዚያ ወር ውስጥ የራሔልን ተፈጥሮአዊ ባሕርይ፣ ለወላጆቿና ለሌሎች ሰዎች የምታሳየውን አያያዝ፣ የበግ እረኝነት ሥራዋን እንዴት እንደምታከናውን፣ የይሖዋን አምልኮ ምን ያህል አክብዳ እንደምትመለከት አይቷል። “ስትደሰትም” ሆነ “ስትከፋ” የምታሳየውን ጠባይ እንደተመለከተ አያጠራጥርም። ስለዚህ ለእርሷ የነበረው ፍቅር ልጓም የሌለው ስሜት ሳይሆን በምክንያታዊ አስተሳሰብና በጥልቅ አክብሮት ላይ የተመሠረተ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ነበር።

ይህም በመሆኑ ራሔልን እንዲድርለት ያዕቆብ ለአባቷ ሰባት ዓመት ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኑን ሊያስታውቅ ችሏል። የወረት ፍቅር ቢሆን ኖሮ ያን ያህል ረዥም ጊዜ ሊቆይ እንደማይችል ጥርጥር የለውም! እነዚያ ሰባት ዓመታት “እንደ ጥቂት ቀን” የሆኑለት እውነተኛ ፍቅር ስለነበረው ብቻ ነው። በዚያ ሁሉ ጊዜ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለመኖር የቻሉትም በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር ስለነበረ ነው።​— ዘፍጥረት 29:​20, 21

በቂ ጊዜ ያስፈልጋል!

ስለዚህ እውነተኛ ፍቅር በጊዜያት ማለፍ አይቀዘቅዝም። እንደ እውነቱ ከሆነ ለአንድ ሰው ያላችሁ ስሜት እውነተኛ መሆኑን የምትፈትኑበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጊዜያት እንዲያልፉ ማድረግ ነው። በተጨማሪም ሳንድራ የተባለች አንዲት ወጣት እንደገለጸችው “አንድ ሰው ‘እኔ እንዲህ ነኝ። አሁን ስለ እኔ ሁሉንም ነገር አውቀሻል/አውቀሃል’ በማለት መላ ባሕርዩን ወዲያው አይገልጽላችሁም።” የምትፈልጉትን ሰው ማንነት ለማወቅ በቂ ጊዜ ያስፈልጋችኋል።

በተጨማሪም በቂ ጊዜ ማለፉ ያደረባችሁን የፍቅር ስሜት በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛን እንድትመረምሩም ያስችላችኋል። ፍቅር ‘የማይገባውን እንደማያደርግና የራሱንም እንደማይፈልግ’ አስታውሱ። ታዲያ ጓደኛችሁ የእናንተ ግብና ዓላማ እንዲሳካ ይፈልጋል ወይስ የሚጥረው የራሱ ግብና ዓላማ ብቻ እንዲሳካ ነው? ለስሜታችሁና ለአመለካከታችሁ አክብሮት አለውን? በራስ ወዳድነት መንፈስ የፍትወት ስሜቱን ለማርካት ሲል ‘የማይገባ ነገር’ እንድታደርጉ ገፋፍቷችኋልን? በሌሎች መካከል ስትሆኑ ክብራችሁን ይጠብቅላችኋል ወይስ ያዋርዳችኋል? እንደነዚህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ለዚያ ሰው ያላችሁን ስሜት በረጋና በሰከነ መንፈስ እንድትገመግሙ ይረዳችኋል።

ተገቢው ጊዜ ያልተሰጠውና ማመዛዘን ያልተደረገበት የችኮላ ፍቅር ችግር ይጋብዛል። “የሚያከንፍ ፍቅር ያዘኝ” በማለት የ20 ዓመቷ ጂል ገልጻለች። ከሁለት ወር የሚያከንፍ ፍቅር በኋላ አገባች። ከተጋቡ በኋላ ግን ቀደም ሲል ተደብቀው የነበሩ አንዳንድ ጉድለቶች ብቅ ማለት ጀመሩ። በጂል ላይ አንዳንድ ከስጋትና ከራስ ወዳድነት የሚመነጩ ጠባዮች መታየት ጀመሩ። ባሏ ሪክ ማራኪነቱን አጣና ራስ ወዳድ ሆነ። ለሁለት ዓመታት ተጋብተው ከቆዩ በኋላ ጂል አንድ ቀን ባሏ “ርካሽ፣” “ሰነፍ” እና “እንከፍ” እንደሆነና ለባልነት እንደማይበቃ ጮሃ ተናገረች። ሪክም በምላሹ ፊቷ ላይ በቡጢ መታት። ጂል እንባዋን እያፈሰሰች ቤትዋንም ሆነ ትዳርዋን ትታ ሄደች።

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ቢከተሉ ጋብቻቸው ከመፍረስ ይድን እንደነበረ ጥርጥር የለውም። (ኤፌሶን 5:​22–33) ይሁን እንጂ ከመጋባታቸው በፊት ይበልጥ ተዋውቀው ቢሆን ኖሮ ነገሮች ምን ያህል የተለየ መልክ ይኖራቸው ነበር! ፍቅራቸው “መልክን” በመውደድ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን እውነተኛውን ባሕርይ፣ ጉድለቶቹንና ጠንካራ ጎኖቹን ሁሉ ከግምት በማስገባት የተመሠረተ ይሆን ነበር። ከጋብቻቸው ለማግኘት ተስፋ ያደረጉት ነገርም ይበልጥ ተጨባጭነት ያለው ይሆን ነበር።

እውነተኛ ፍቅር በአንድ ቀን ጀንበር የሚመጣ ነገር አይደለም። ወይም ደግሞ ጥሩ የትዳር ጓደኛ የሚሆናችሁ ሰው የግድ በጣም ማራኪና ቆንጆ ሆኖ ያገኛችሁት ሰው ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ባርባራ የተዋወቀችው ወጣት መጀመሪያ ላይ እምብዛም እንዳልማረካት አምናለች። “ይሁን እንጂ ይበልጥ እያወቅሁት ስሄድ” በማለት ታስታውሳለች ባርባራ፣ “ነገሮች እየተለወጡ መጡ። ስቲፈን ለሌሎች ሰዎች የሚያስብና ሁልጊዜ የሌሎችን ጥቅም ከራሱ ጥቅም የሚያስቀድም መሆኑን ተመለከትኩ። ከጥሩ ባል የሚፈለጉት ባሕርያት እነዚህ መሆናቸውን አውቅ ነበር። በእርሱ ተማረኩና ላፈቅረው ጀመርኩ።” በዚህም ምክንያት ጥሩ ትዳር ሊመሠርቱ ቻሉ።

ታዲያ የያዛችሁ ፍቅር እውነተኛ መሆኑንና አለመሆኑን እንዴት ታውቃላችሁ? ልባችሁ የሚናገረውን ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው አእምሮአችሁ የሚነግራችሁን እመኑ። ግለሰቡን ከውጪያዊ “መልኩ” አልፋችሁ ውስጣዊ ማንነቱን ለማወቅ ጣሩ። በቂ ጊዜ ወስዳችሁ ዝምድናችሁ እንዲዳብር አድርጉ። የወረት ፍቅር በአጭር ጊዜ ውስጥ ግሎ ወዲያው እንደሚጠፋ አስታውሱ። እውነተኛ ፍቅር ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እያደገ የሚሄድና “ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ” የሚሆን ነው።​— ቆላስይስ 3:​14 አዓት

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ አንድን ሰው መልኩን ብቻ አይቶ መውደድ ምን ችግር ያስከትላል?

◻ እውነተኛ ፍቅር መሆንና አለመሆኑን እንዲለይ ልባችሁ እምነት ሊጣልበት ይችላልን?

◻ በእውነተኛ ፍቅርና በወረት ፍቅር መካከል ያሉ አንዳንድ ልዩነቶች ምንድን ናቸው?

◻ እየተቀጣጠሩ የሚጫወቱ ወንድና ሴት ብዙውን ጊዜ ተጣልተው የሚለያዩት ለምንድን ነው? ይህስ ሁልጊዜ ስህተት ነውን?

◻ ከወደዳችሁት ሰው ጋር መለያየት ቢኖርባችሁ ይህ መለያየት የሚያስከትልባችሁን ተፈላጊነት የማጣት ስሜት እንዴት ልትቋቋሙ ትችላላችሁ?

◻ በቂ ጊዜ ወስዶ መተዋወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 242 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የወደዳችሁት ግለሰቡን ወይም ግለሰቧን ነው ወይስ “መልኩን” ወይም “መልኳን” ብቻ?

[በገጽ 247 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የወረት ፍቅር ዕውር ነው፤ ዕውር ሆኖ መኖርንም ይመርጣል። እውነታውን ማየት አይወድም።” —አንድ የ24 ዓመት ሰው የተናገረው

[በገጽ 250 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከእንግዲህ ‘ታዲያስ፣ እንደምነህ’ ከማለት ያለፈ ግንኙነት አይኖረኝም። ከማንም ሰው ጋር ከዚህ ያለፈ ቅርርብ አልመሠርትም”

[በገጽ 248, 249 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]

ከደረሰብኝ የመንፈስ ስብራት ላገግም የምችለው እንዴት ነው?

ማግባት የሚኖርባችሁ እሱን ወይም እሷን እንደሆነ እንዲሁ ይታወቃችኋል። አብራችሁ ስትሆኑ በጣም ደስ ይላችኋል። ፍላጎቶቻችሁ ይመሳሰላሉ። በመካከላችሁ ጠንካራ የመሳሳብ ስሜት እንዳለ ይሰማችኋል። ይሁን እንጂ በድንገት በመካከላችሁ የነበረው ግንኙት በታላቅ ቁጣ ወይም በመራራ ልቅሶ ያከትማል።

ዶክተር ማይክል ሊቦዊዝ ዘ ኬሚስትሪ ኦቭ ላቭ በተሰኘ መጽሐፋቸው የፍቅርን አጀማመር አንድ ኃይለኛ ዕፅ ከሚፈጥረው የስሜት ግለት ጋር አመሳስለዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ሲያልቅ አንድ የዕፅ ሱሰኛ የለመደውን ዕፅ ሲያጣ የሚሰማው ዓይነት ‘መጥፎ ስሜት’ እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። በዚህ ረገድ ፍቅሩ ወረት ወይም ‘እውነተኛ’ መሆኑ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ሁለቱም የሚያስፈነጥዝ ደስታና ግንኙነቱ በሚያከትምበት ጊዜ ደግሞ የሚያሠቃይ ኀዘንና ትካዜ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በተለያያችሁ ማግስት የሚሰማችሁ ተቀባይነት የማጣት ስሜት፣ የስሜት መጎዳትና ምናልባትም ንዴት ለወደፊቱ ሕይወታችሁ ያላችሁን አመለካከት ሊያጎመዝዘው ይችላል። አንዲት ወጣት ሴት በመከዳቷ ምክንያት ‘እንደቆሰለች’ ተናግራለች። “ከእንግዲህ [ከተቃራኒ ጾታ ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት ረገድ] ‘ታዲያስ፣ እንደምነህ’ ከማለት ያለፈ ቅርርብ አልመሠርትም” ትላለች። “ከማንም ሰው ጋር ከዚህ ያለፈ ቅርርብ አልመሠርትም።” ለግንኙነታችሁ የነበራችሁ ግምት በጣም የጠነከረ ከነበረ በመለያየታችሁ ምክንያት የሚደርስባችሁ የመንፈስ ስብራትም የዚያኑ ያህል የጠበቀ ይሆናል።

አዎን፣ በእርግጥም ደስ ካላችሁ ሰው ጋር ቅርርብ ለመፍጠር ያላችሁ ነፃነት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍላችሁ ይችላል። ፈላጊ የሌላችሁ እንደሆናችሁ ሊሰማችሁና የመንፈስ ስብራት ሊደርስባችሁ ይችላል። ቅርርባችሁ እውነተኛ ፍቅር ወደ መመሥረት እንደሚያደርሳችሁ እርግጠኛ ልትሆኑ የምትችሉበት መንገድ የለም። ስለዚህ አንድ ሰው ሐቀኛ ዓላማ ኖሮት ከእናንተ ጋር ጥናታዊ ቅርርብ ማድረግ ቢጀምርና ኋላ ግን ጋብቻ ቢመሠርት ጥበብ እንደማይሆን ቢወስን በደል ተፈጽሞባችኋል ማለት ላይሆን ይችላል።

ችግሩ ግን የተለያያችሁት በተቻለ መጠን በማያስከፋ መንገድና በደግነት ቢሆንም ስሜታችሁ መጎዳቱና ተፈላጊነት የማጣት ወይም የመከዳት ስሜት መሰማቱ የማይቀር መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ለራሳችሁ ያላችሁ ግምት ዝቅ እንዲል የሚያበቃ ምክንያት አይደለም። በዚህ ሰው ዓይን “ተስማሚ” አለመሆናችሁ በሌላ ሰው ዓይንም ተስማሚ አትሆኑም ማለት አይደለም!

የተጨናገፈውን ፍቅር በሰከነ አመለካከት ለማየት ሞክሩ። መለያየቱ የተጎዳኛችሁት ሰው የስሜት አለመብሰል፣ ውሳኔ ለማድረግ አለመቻል፣ ሐሳበ ግትርነት፣ መቻቻልን አለማወቅ፣ ለስሜታችሁ ደንታ ቢስ መሆንና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ጥሩ ያልሆኑ ባሕርያት እንዳሉት ሊያሳይ ይችላል። እነዚህ ደግሞ አንድ የትዳር ጓደኛ ፈጽሞ ሊኖሩት የማይገባ ጠባዮች ናቸው።

የመለያየቱ ውሳኔ የተደረገው በአንደኛው ወገን ብቻ ከሆነና ጋብቻው ሊሰምር ይችል ነበረ ብላችሁ የምታምኑ ከሆነስ? ተጓዳኛችሁ ስሜታችሁን እንዲያውቅ የማድረግ መብት እንዳላችሁ ጥርጥር የለውም። ምናልባት በመካከላችሁ የተፈጠረው ተራ የሆነ አለመግባባት ሊሆን ይችላል። በስሜት ግንፋሎት መጯጯህና መጨቃጨቅ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። መለያየት አለብን ብሎ/ብላ ድርቅ ካለ/ካለች ለእናንተ ምንም ስሜት እንደሌለው/እንደሌላት በግልጽ ማሳየቱ/ማሳየቷ ስለሆነ እንዲያፈቅራችሁ/እንድታፈቅራችሁ ብላችሁ በማልቀስና በመለማመጥ ራሳችሁን ማዋረድ አያስፈልጋችሁም። ሰሎሞን “ፈልጎ ለማግኘት ጊዜ አለው፤ ያገኙትንም ለማጣት ጊዜ አለው” ብሏል።​— መክብብ 3:​6 የ1980 ትርጉም

ከመጀመሪያው አንስቶ ከእናንተ ጋር ለመጋባት ከልቡ ያልፈለገ ሰው ሲጠቀምባችሁ እንደቆየ ለመጠርጠር ጠንካራ ምክንያት ካላችሁስ? የበቀል አጸፋ መመለስ አያስፈልጋችሁም። ተንኮሉን ወይም ተንኮሏን አምላክ ሳያየው እንደማያልፍ እርግጠኞች ሁኑ። ቃሉ “ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጎዳል” ይላል።​— ምሳሌ 11:​17፤ ከምሳሌ 6:​12–15 ጋር አወዳድሩ።

አልፎ አልፎ የብቸኝነት ስሜት ወይም ያሳለፋችሁት የፍቅር ትዝታ ያሠቃያችሁ ይሆናል። እንዲህ በሚሰማችሁ ጊዜ አልቅሳችሁ ቢወጣላችሁ ጥሩ ነው። በተጨማሪም በሥራ መጠመድ፣ ምናልባትም አንድ ዓይነት የጉልበት ሥራ መሥራት ወይም በክርስቲያናዊ አገልግሎት መጠመድ ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 18:​1) አእምሯችሁ በሚያስደስቱና በሚያንጹ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ። (ፊልጵስዩስ 4:​8) ለቅርብ ጓደኛችሁ ችግራችሁን አዋዩ። (ምሳሌ 18:​24) ራሳችሁን የቻላችሁ አዋቂዎች እንደሆናችሁ ቢሰማችሁም ወላጆቻችሁ ከፍተኛ ማጽናኛ ሊሰጧችሁ ይችላሉ። (ምሳሌ 23:​22) ከሁሉ በላይ ደግሞ ችግራችሁን ለይሖዋ አዋዩት።

በዚህ ጊዜ የባሕርያችሁን አንዳንድ ገጽታዎች ማሻሻል እንደሚያስፈልጋችሁ ሊታያችሁ ይችላል። የትዳር ጓደኛችሁ እንዲሆን የምትፈልጉት ሰው እንዴት ያለ መሆን እንደሚገባው ከምንጊዜም የበለጠ ግልጽ ሆኖ ይታያችኋል። ወዳችሁ ያጣችሁ እንደመሆናችሁ መጠን እንደገና ለትዳር ተስማሚ የሆነ ሰው ብታገኙ፣ ደግሞም የማግኘት አጋጣሚያችሁ ከምታስቡት በላይ ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል የምታደርጉትን ጥናታዊ ቅርርብ ይበልጥ በጥንቃቄ ለመያዝ ልትወስኑ ትችላላችሁ።

[በገጽ 245 ላይ የሚገኝ ግራፍ]

እውነተኛ ፍቅር ነው ወይስ ወረት?

ፍቅር

1. ስለ ሌላው ሰው ጥቅም ያስባል እንጂ ራስ ወዳድ አይደለም

2. ብዙውን ጊዜ ፍቅር የሚጀምረው ቀስ ብሎ፣ ወራት ወይም ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው

3. የምትማረኩት በሌላው ሰው ጠቅላላ ጠባይና መንፈሳዊ ባሕርያት ነው

4. ፍቅር ከቀድሞው የተሻላችሁ ሰዎች እንድትሆኑ ያደርጋችኋል

5. የወደዳችሁትን ሰው በሚዛናዊ አመለካከት ታያላችሁ፣ ጉድለቱ ይታያችኋል። ቢሆንም ትወዱታላችሁ

6. አለመግባባቶች ያጋጥሟችኋል። ቢሆንም አለመግባባቶቹ ተነጋግራችሁባቸው ልትፈቷቸው የምትችሉ ሆነው ታገኟቸዋላችሁ

7. ለመስጠትና ከወደዳችሁት ሰው ጋር ለመካፈል ትፈልጋላችሁ

ወረት

1. ራስ ወዳድ፣ እገዳ የሚያበዛ ነው። የወረት ፍቅር የያዘው ሰው የሚያስበው ‘ምን ጥቅም ያስገኝልኛል?’ ብሎ ነው

2. የወረት ፍቅር ቶሎ ብሎ፣ ምናልባትም በሰዓት ወይም በቀን በሚቆጠር ጊዜ ውስጥ ይጀምራል

3. በጣም የምትማረኩት በግለሰቡ ወይም በግለሰቧ ውጫዊ መልክ ነው። (‘ዓይኖቹ በጣም ያምራሉ።’ ‘ቆንጆ ቁመና አላት’)

4. ይጎዳችኋል፣ መላ ያሳጣችኋል

5. ሚዛናዊ አመለካከት የለውም። የተወደደው ሰው ፍጹም ሆኖ ይታያችኋል። ከባድ የባሕርይ ጉድለቶች እንዳሉበት ቢከነክናችሁም ችላ ትሉታላችሁ

6. አለመግባባቶች ዘወትር ያጋጥሟችኋል። በውይይት የምትፈቱት ምንም ነገር የለም። ብዙዎቹ አለመግባባቶች “የሚፈቱት” በመሳሳም ነው

7. ግንኙነታችሁ የሚያተኩረው በመቀበል ወይም በማግኘት ላይ፣ በተለይም ወሲባዊ ስሜቶችን በማርካት ላይ ነው

[በገጽ 244 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማራኪ መልክ ያለው ወይም ያላት፣ ጥበብ ግን የሌለው ወይም የሌላት ከሆነ ‘በአሳማ አፍንጫ ላይ እንዳለ የወርቅ ቀለበት’ ነው

[በገጽ 246 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁልጊዜ በሌሎች ሰዎች ፊት የሚያዋርዳችሁ ሰው ለእናንተ እውነተኛ ፍቅር የሌለው ሊሆን ይችላል