በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርኩ ለመጫወት ደርሻለሁን?

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርኩ ለመጫወት ደርሻለሁን?

ምዕራፍ 29

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርኩ ለመጫወት ደርሻለሁን?

በብዙ አገሮች ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት በፍቅር መዝናናትና አስደሳች የሆነ ተግባር እንደመፈጸም ተደርጎ ይታያል። በመሆኑም ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ብዙ መልኮች ሊኖሩት ይችላል። አንዳንዶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥረው በሚጫወቱባቸው ጊዜያት የሚያደርጓቸው ነገሮች በቅድሚያ የታወቁና የተወሰኑ ሲሆን የአበባ ስጦታ መለዋወጥን፣ አስደሳች በሆነ አካባቢ አብሮ ራት መብላትንና ተሳስሞ መለያየትን ያካትታል። ለሌሎቹ ደግሞ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ከሚወዱት ተቃራኒ ጾታ ያለው ሰው ጋር የተወሰነ ጊዜ አብሮ ከማሳለፍ የተለየ ትርጉም የለውም። ሁልጊዜ አብረው ‘የሚታዩና ከጥሩ ጓደኝነት’ ሌላ ምንም የተለየ ግንኙነት የለንም የሚሉ ወንዶችና ሴቶችም አሉ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚቀጣጠሩ ወጣቶች፣ አብሮ መሄድም ተባለ እንዲሁ መተያየት፣ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅ አብዛኛውን ጊዜ ሌላ ሰው በሌለበት ብቻቸውን አብረው በመሆን በርካታ ጊዜ ያሳልፋሉ።

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተለመደ ባሕል አልነበረም። ቢሆንም ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት በአስተዋይነት፣ በጥንቃቄና በሚያስከብር መንገድ ከተደረገ ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሁለት ሰዎች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ የሚያስችል ጥሩ መንገድ ነው። ደግሞም፣ አስደሳችም ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት እናንተም ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ መጫወት ይኖርባችኋል ማለት ነውን?

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ እንድትጫወቱ የሚያደርጋችሁ ግፊት

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ እንድትጫወቱ ግፊት ሊደረግባችሁ ይችላል። ከእኩዮቻችሁ አብዛኞቹ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ የሚጫወቱ ይሆኑና እናንተም የተለያችሁ ሆናችሁ ለመታየት አትፈልጉ ይሆናል። ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ እንድትጫወቱ የሚገፋፏችሁ ያስቡልኛል የምትሏቸው ጓደኞች ወይም ዘመዶች ሊሆኑ ይችላሉ። የ15 ዓመት ዕድሜ ያላት ሜሪ አን ከአንድ ልጅ ጋር ተቀጣጥራ እንድትጫወት በተጠየቀችበት ጊዜ አክስቷ “ልጁን ለማግባት መፈለግሽም ሆነ አለመፈለግሽ እየተቀጣጠርሽ ከመጫወት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርሽ መጫወት ማድረግ ከሚኖርብሽ የተፈጥሮ እድገት አንዱ ክፍል ነው። . . . ደግሞም እኮ ከወንዶች ልጆች ጋር ተቀጣጥረሽ ለመጫወት ሁልጊዜ እምቢ የምትይ ከሆነ ተወዳጅነት ታጪና ከዚያ በኋላ የሚጠይቅሽ ወንድ ታጪያለሽ” የሚል ምክር ሰጥታታለች። ሜሪ አን ስታስታውስ “የአክስቴ አባባል በጥልቅ ተሰማኝ። ምናልባት ጥሩ አጋጣሚ እያመለጠኝ ይሆን? ልጁ የራሱ መኪናና ብዙ ገንዘብ ያለው ስለነበር ዓለም እንደሚያሳየኝ አውቅ ነበር። ታዲያ ከእርሱ ጋር ልውጣ ይሆን ወይስ ልተው?” ብላ ታመነታ እንደነበረ ተናግራለች።

ለአንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ግፊቱ የሚመጣው ከራሳቸው የመወደድና የመፈቀር ፍላጎት ነው። “መወደድና መደነቅ እፈልግ ነበር” በማለት የ18 ዓመቷ አን ገልጻለች። “ከወላጆቼ ጋር ስለማልቀራረብ ከእነርሱ ያላገኘሁትን ቅርርብ ለማግኘትና ስሜቴን የሚረዳልኝና ስሜቴን የምገልጽለት ሰው ለማግኘት ወደ ወንድ ጓደኛዬ ዞር አልኩ።”

ይሁን እንጂ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ እንዲጫወቱ ግፊት ስለተደረገባቸው ብቻ መቀጣጠር መጀመር የለባቸውም! መጀመሪያ ነገር ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ከባድ ጉዳይ ነው። የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የሚደረገው ሂደት አንዱ ክፍል ነው። ጋብቻ? ጋብቻ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ ከሚጫወቱት ወጣቶች በአብዛኞቹ ሐሳብ ውስጥ ጨርሶ የሌለ ነገር እንደሆነ የታወቀ ነው። ግን እውነት እንነጋገርና ሁለት ተቃራኒ ጾታዎች እየተቀጣጠሩ በመጫወት ብዙ ጊዜ አብረው የሚያሳልፉት ሊጋቡ ይችሉ እንደሆነ ለመጠናናት ካልሆነ ሌላ ምን አጥጋቢ ምክንያት ሊኖር ይችላል? ከዚህ ለተለየ ማንኛውም ሌላ ምክንያት ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት የኋላ ኋላ ብዙ ‘መዘዝ’ ሊያስከትል ይችላል። እንዲህ የሆነው ለምንድን ነው?

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ የመጫወት አስከፊ ጎኖች

መጀመሪያ ነገር ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ “አፍላ ጉርምስና” ብሎ በሚጠራው አደገኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:​36 አዓት) በዚህ ዕድሜ ላይ ኃይለኛ የወሲብ ፍላጎት ሊሰማቸው ይችላል። ይህ በራሱ ምንም ስህተት የለበትም፤ የዕድገታችሁ አንዱ ክፍል ነውና።

ይሁን እንጂ እዚህ ላይ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ላይ ያሉ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወታቸው የሚያስከትለው ችግር አለ። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ይህን ለእነርሱ አዲስ የሆነውን ወሲባዊ ፍላጎት እንዴት መቆጣጠር እንደሚችሉ ገና መማር መጀመራቸው ነው። እውነት ነው፣ አምላክ ስለ ወሲብ ያወጣውን ሕግ ታውቁና በንጽሕና ለመቆየትም ከልብ ትመኙ ይሆናል። (ምዕራፍ 23ን ተመልከቱ።) ቢሆንም ባዮሎጂያዊ የሆነ የሕይወት ሐቅ ይገጥማችኋል:- ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር ብዙ ጊዜ ባሳለፋችሁ መጠን ፈለጋችሁም አልፈለጋችሁ የወሲብ ፍላጎታችሁ ይበልጥ ይጨምራል። (ገጽ 232–3 ተመልከቱ።) ይህ የሁላችንም የአፈጣጠር ባሕርይ ነው! በዕድሜ ከፍ ብላችሁ ስሜቶቻችሁን በተሻለ ሁኔታ መቆጣጠር እስክትችሉ ድረስ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ መጫወት ከአቅማችሁ በላይ ይሆንባችኋል። የሚያሳዝነው ነገር ብዙ ወጣቶች ይህን የሚገነዘቡት ከሚደርስባቸው ችግር ነው።

“አብረን እየተቀጣጠርን መጫወት ስንጀምር . . . እጅ ለእጅ አንያያዝም ወይም አንሳሳምም ነበር። የምፈልገው ከእርሷ ጋር በመሆንና በማውራት መደሰት ብቻ ነበር” በማለት አንድ ወጣት ሰው ተናግሯል። “ይሁን እንጂ እሷ በጣም ሰው ወዳድ ስለነበረች በጣም ተጠግታኝ ትቀመጥ ነበር። ከጊዜ በኋላ እጅ ለእጅ መያያዝና መሳሳም ጀመርን። ከዚያ በኋላ ለማውራት ብቻ ሳይሆን እንድይዛት፣ እንድዳስሳትና እንድስማት ብዬ ከእርሷ ጋር ለመሆን እስከ መፈለግ ድረስ አስተሳሰቤ ተለወጠብኝ። ያም አልበቃኝም! ቃል በቃል በኃይለኛ ፍትወት ሰከርኩ። አንዳንድ ጊዜ በጣም የርካሽነት ስሜት ይሰማኝና አፍር ነበር።”

ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ሕገ ወጥ ሩካቤ ሥጋ ወደ መፈጸም ማድረሱ አያስደንቅም። በአያሌ መቶዎች በሚቆጠሩ በአፍላ ጉርምስና የዕድሜ ክልል በሚገኙ ወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደደረሰበት ከልጃገረዶች 87 በመቶዎቹና ከወንዶች ልጆች ደግሞ 95 በመቶ የሚሆኑት ከተቃራኒ ጾታ ጋር ለመጫወት ሲቀጣጠሩ ወሲብ “መጠነኛ ወይም በጣም አስፈላጊ ጉዳይ” እንደነበረ ተሰምቷቸዋል። ይሁን እንጂ ከልጃገረዶቹ ውስጥ 65 በመቶዎቹና ከወንዶች ልጆች ደግሞ 43 በመቶዎቹ ተቀጣጥረው በሚጫወቱበት ጊዜ ወሲባዊ ግንኙነት የፈጸሙት ምንም ፍላጎት ሳይኖራቸውና ሳያስቡት እንደሆነ አምነዋል!

የ20 ዓመቷ ሎሬታ እንደሚከተለው በማለት ታስታውሳለች:- “አዘውትረን በተያየን መጠን ይበልጥ መደፋፈር ጀመርን። ወዲያውም መሳሳም ምንም የማያስደስት ሆነና አንዳችን የሌላውን ብልት ማሻሸት ጀመርን። እኔ በጣም ቆሻሻነት ይሰማኝ ስለነበር መንፈሴ በጣም ይጨነቅ ነበር። ጓደኛዬም ከጊዜ በኋላ ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽም ይጠይቀኝ ጀመር። . . . በጣም ተምታታብኝና ግራ ገባኝ። ያሳስበኝ የነበረው ነገር እርሱን ለማጣት አለመፈለጌ ነበር። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ወድቄ ነበር!”

እውነት ነው፣ ሩካቤ ሥጋ እስከመፈጸም የሚደርሱት ሁሉም ተጓዳኞች አይደሉም። አንዳንዶች ፍቅራቸውን ለመገላለጥ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ወሲብ ለመፈጸም ትንሽ ሲቀራቸው ያቆማሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ስሜቱ እንዲቀሰቀስ ካደረገ በኋላ እነዚህን ስሜቶች የሚወጣበት የተከበረ መንገድ ከሌለው ውጤቱ ምን ይሆናል? የስሜት እርካታ ለማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ብስጭት እንደሚደርስበት የተረጋገጠ ነው። ይህ ዓይነቱ ብስጭት የሚደርሰው በወሲባዊ ስሜት ብቻ አይደለም።

የስሜት ቁስል

አንድ ወጣት የተደቀኑበትን ሁለት አስቸጋሪ አማራጮች ተመልከቱ:- ‘መጀመሪያ ላይ ካቲን በጣም እወዳት ነበር። እሷ ትክክል ነው ብላ የማታስበውን ነገር እንድታደርግ ገፋፍቼያት እንደነበር አልክድም። አሁን ግን ለእርሷ ያለኝ ስሜት ስለጠፋ በጣም ቆሻሻነት ይሰማኛል። ካቲን ስሜቷን ሳልጎዳ ልተዋት የምችለው እንዴት ነው?’ እንዴት ያለ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ነው! እናንተስ በካቲ ቦታ ብትሆኑ ኖሮ ምን ይሰማችሁ ነበር?

በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚያጋጥም የቅስም መሰበር የተለመደ ደዌ ነው። እውነት ነው፣ ወንድና ሴት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲሄዱ ማራኪ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ እነዚያ ያያችኋቸው ወንድና ሴት መጋባት ቀርቶ ከአሁን በኋላ ለዓመት ያህል አብረው የመቆየት አጋጣሚያቸው ምን ያህል ነው? በጣም የመነመነ ነው። በመሆኑም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ክልል ላይ የሚያጋጥም ፍቅር ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል፣ ውድቅ እምብዛም ወደ ጋብቻ የማያደርስ፣ ብዙውን ጊዜም በቅስም መሰበር የሚያከትም ግንኙነት ነው።

ያም ሆነ ይህ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያችሁ የእናንተም ባሕሪ ገና በመለዋወጥ ላይ ነው። ማንነታችሁን፣ ምን እንደምትወዱ፣ በሕይወታችሁ ምን ልታደርጉበት እንደምትፈልጉ ፍተሻ በማድረግ ላይ ናችሁ። ዛሬ የምትወዱት ሰው ምናልባት ነገ የሚሰለቻችሁ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የፍቅር ስሜቶች እንዲያድጉ ከተፈቀደላቸው ጉዳት ማድረሳቸው እንደማይቀር የተረጋገጠ ነው። አያሌ ጥናቶች “ከሴት ጓደኛ ጋር መጣላት” እና “የፍቅር አለመሳካት” ወጣቶች ራሳቸውን እንዲገድሉ ከሚያደርጓቸው ሁኔታዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ማረጋገጣቸው አያስደንቅም።

ደርሻለሁን?

አምላክ ለወጣቶች “አንተ ጎበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ” ይላቸዋል። ወጣቶች ደግሞ ‘በልባቸው መንገድ መሄድ’ ይቀናቸዋል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ይህ አስደሳች መስሎ የሚታየው “መንገድ” ኀዘንና መከራ ማምጣቱ የማይቀር ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ባለው ቁጥር ላይ “ሕፃንነትና ጉብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ኀዘንን አርቅ፣ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ” በማለት ይመክራል። (መክብብ 11:​9, 10) “ኀዘን” በጥልቅ መረበሽን ወይም በጣም መጨነቅን ያመለክታል። “ክፉ ነገር” በግለሰቡ ላይ የሚመጣውን መከራ ያመለክታል። ሁለቱም ሕይወት መራራ እንዲሆን ሊያደርጉ ይችላሉ።

ታዲያ ይህ ማለት ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ራሱ የኀዘንና የመከራ ምንጭ ነው ማለት ነውን? ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ የምትጫወቱት ለተሳሳተ ዓላማ (‘ለደስታ’) ከሆነ ወይም ዕድሜያችሁ ለዚህ ከመድረሱ በፊት ከሆነ የኀዘንና የመከራ ምንጭ ሊሆን ይችላል! ስለዚህ የሚከተሉት ጥያቄዎች ሁኔታችሁን ለመገምገም ሊረዱአችሁ ይችላሉ።

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ለስሜታዊ እድገት ይረዳል ወይስ እንቅፋት ይሆናል? ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ ስትጫወቱ ማኅበራዊ ግንኙነታችሁ በወንድና በሴት መካከል በሚኖር ጓደኝነት ብቻ እንዲወሰን ያደርግባችኋል። ከዚህ ይልቅ ከሌሎች ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ይበልጥ ብታሰፉት አይጠቅማችሁምን? (ከ2 ቆሮንቶስ 6:​12, 13 ጋር አወዳድሩ።) ሱዛን የተባለች አንዲት ወጣት ሴት እንዲህ ብላለች:- “በጉባኤ ካሉት ትልልቅ ሴቶች ጋር ጥብቅ ጓደኝነት መመሥረትን ተምሬያለሁ። እነሱ አብሮአቸው የሚሆን ሰው ያስፈልጋቸዋል፣ እኔ ደግሞ እምነት የሚጣልብኝ ሰው ለመሆን እንድችል የእነርሱ ምሳሌነት ያስፈልገኝ ነበር። ስለዚህ ቡና ለመጠጣት ወደ ቤታቸው ጎራ እል ነበር። አብረን እያወራን እንስቃለን። ከእነርሱ ጋር የዕድሜ ልክ ወዳጅነት ልመሠርት ችያለሁ።”

ከብዙ ዓይነት ሰዎች ጋር፣ ከትላልቆችና ከወጣቶች፣ ነጠላ ከሆኑና ካገቡ፣ ከወንዶችና ከሴቶች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ከቻላችሁ ከተለያዩ ዓይነት ሰዎች ጋር ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ጋር ተቀጣጥራችሁ በምትጫወቱበት ጊዜ ጭምር የስሜት ውጥረት ሳይኖርባችሁ ተዝናንታችሁ ለመጫወት ትችላላችሁ። በተጨማሪም ከባለ ትዳሮች ጋር አብራችሁ በመዋል ስለ ጋብቻ ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖራችሁ ለማድረግ ትችላላችሁ። በኋላም ጥሩ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የተሻለ ዝግጅትና ጋብቻ የሚጠይቅባችሁን ግዴታ ለመፈጸም የተሻለ ብቃት ሊኖራችሁ ይችላል። (ምሳሌ 31:​10) ጌይል የተባለች ወጣት እንደሚከተለው ብላለች:- “በአሁኑ ጊዜ ትዳር ይዤ የራሴን ኑሮ ለመመሥረት አልደረስኩም። ገና ከራሴ ጋር በመተዋወቅ ላይ ነኝ። ልደርስባቸው የሚገቡኝ ብዙ መንፈሳዊ ግቦችም አሉኝ። ስለዚህ በእርግጥ ተቃራኒ ጾታ ካለው ከማንም ሰው ጋር በጣም መቀራረብ አያስፈልገኝም።”

የሌላውን ስሜት መጉዳት እፈልጋለሁን? የመጋባት ዓላማ ሳይኖር በፍቅር መተሳሰር በእናንተም ሆነ በሌላው ሰው ላይ የስሜት ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። በእርግጥም ከተቃራኒ ጾታ ጋር የመቀራረብ ተሞክሮ ለማግኘት ስትሉ ብቻ ለማታገቡት ሰው የፍቅር ስሜት ማሳየት ተገቢ ነውን?​— ማቴዎስ 7:​12ን ተመልከቱ።

ወላጆቼ ምን ይላሉ? ወላጆች ብዙውን ጊዜ እናንተ ማየት የተሳናችሁን አደገኛ ሁኔታ ማየት ይችላሉ። እነሱም ባንድ ወቅት ወጣቶች ነበሩ። ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሁለት ወጣቶች አብረው ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ሲጀምሩ ምን ዓይነት ችግር ሊመጣ እንደሚችል ያውቃሉ! ስለዚህ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ መጫወታችሁን ወላጆቻችሁ የማይደግፉት ከሆነ የሚሏችሁን ብትሰሙ ጥሩ ነው። (ኤፌሶን 6:​1–3) የሚከለክሉአችሁ በዕድሜ ጠንከር እስክትሉ ድረስ መቆየት እንዳለባችሁ ስለተሰማቸው ብቻ ሊሆን ይችላል።

የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መስፈርት ማሟላት እችላለሁን? አንድ ሰው የሚቀሰቀስበትን ወሲባዊ ስሜት በተሻለ ሁኔታ መቋቋም የሚችለው “የአፍላ ጉርምስና ዕድሜው” ካለፈ በኋላ ነው። በዚያ ጊዜም እንኳን ቢሆን ቀላል አይደለም። በዚህ ለጋ ዕድሜያችሁ ንጽሕናችሁን ሳታበላሹ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የተቀራረበ ግንኙነት ለመመሥረት ትችላላችሁን?

ብዙ ወጣቶች ራሳቸውን እነዚህን ጥያቄዎች እየጠየቁ ሜሪ አን (ቀደም ብለን የጠቀስናት ወጣት) የደረሰችበት ድምዳሜ ላይ እየደረሱ መሆናቸው በጣም ያስደስታል። ሜሪ አን “ማንም ሰው ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠርኩ መጫወት እንድጀምር እንዳይገፋፋኝ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌአለሁ። ላገባ በምችልበት ዕድሜ ላይ እስክደርስና ባል የሚሆነኝ ሰው እንዲኖሩት የምፈልጋቸው ባሕርያት ያሉት ሰው እስካገኝ ድረስ ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር እየተቀጣጠርኩ አልጫወትም።”

ሜሪ አን እናንተም ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ መጫወት ከመጀመራችሁ በፊት ራሳችሁን ልትጠይቁ የሚገባችሁ አሳሳቢ ጥያቄ ጠይቃለች።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ “ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት” የሚለው አባባል ለእናንተ ምን ትርጉም አለው?

◻ አንዳንድ ወጣቶች ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ ለመጫወት የሚገፋፉት ለምንድን ነው?

◻ “በአፍላ ጉርምስና” ላይ የሚገኝ ወጣት ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠረ ቢጫወት ጥበብ የማይሆነው ለምንድን ነው?

◻ አንድ ወጣት ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ በመጫወት ረገድ “ክፉን ነገር ሊያስወግድ” የሚችለው እንዴት ነው?

◻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ‘እንዲሁ ጓደኞች’ በሚሆኑበት ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉ አንዳንድ ችግሮች ምንድን ናቸው?

◻ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠራችሁ ለመጫወት ደርሳችሁ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት ታውቃላችሁ?

[በገጽ 231 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወዲያውም መሳሳም ምንም የማያስደስት ሆነና አንዳችን የሌላውን ብልት ማሻሸት ጀመርን። እኔ በጣም ቆሻሻነት ይሰማኝ ስለነበር መንፈሴ በጣም ይጨነቅ ነበር። ጓደኛዬም ከጊዜ በኋላ ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽም ይጠይቀኝ ጀመር”

[በገጽ 234 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ካቲን ስሜቷን ሳልጎዳ ልተዋት የምችለው እንዴት ነው?’

[በገጽ 232, 233 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሣጥን]

አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ‘እንዲሁ ጓደኞች’ ሊሆኑ ይችላሉን?

ወሲብ አልባ ዝምድና (በወንዶችና በሴቶች መካከል ወሲብ የማይፈጸምበት የፍቅር ዝምድና) የሚባለው በወጣቶች መካከል በጣም የታወቀ ነው። የ17 ዓመት ዕድሜ ያለው ግሪጎሪ ሲናገር “ብዙውን ጊዜ ልጃገረዶች ከወንዶች ልጆች ይበልጥ ርኅሩኆችና ነገሮች በቀላሉ የሚሰሙአቸው ስለሆኑ ከእነርሱ ጋር ማውራት ይቀለኛል” ብሏል። ሌሎች ወጣቶች እንዲህ ዓይነቶቹ ወዳጅነቶች ይበልጥ ሁለገብ የሆነ ባሕርይ ለማዳበር ይረዱናል ብለው ይከራከራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ወጣት ወንዶችን “ወጣት ሴቶችን እንደ እኅቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ተመልከታቸው” በማለት ያሳስባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​2 የ1980 ትርጉም) ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ በማዋል ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ጋር ንጹሕና ጤናማ ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ከክርስቲያን ሴቶች ጋር ጥሩ ወዳጅነት የነበረው ነጠላ ወንድ ነበር። (ሮሜ 16:​1, 3, 6, 12ን ተመልከቱ።) “ከእኔ ጋር አብረው በወንጌል የተጋደሉ ሴቶች” በማለት ስለ ሁለት ሴቶች ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:​3 አዓት) ኢየሱስ ክርስቶስም ሚዛናዊና ጤናማ በሆነ መንገድ ከሴቶች ጋር ይሆን ነበር። ማርታና ማርያም በተደጋጋሚ ጊዜያት ባደረጉለት መስተንግዶና ጭውውት ተደስቷል።​— ሉቃስ 10:​38, 39፤ ዮሐንስ 11:​5

ይሁን እንጂ “ወሲብ አልባ” ወዳጅነት ብዙውን ጊዜ ከድብቅ ፍቅር ወይም ያለ አንዳች ቃል ኪዳን የተቃራኒ ጾታን ትኩረት ማግኛ ዘዴ ከመሆን የተለየ አይደለም። ደግሞም ስሜት በቀላሉ ሊለወጥ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ዶክተር ማሪዮን ሂሊያርድ ሲያስጠነቅቁ “በሰዓት አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ለመጓዝ የተጀመረ ጓደኝነት አለአንዳች ማስጠንቀቂያ በሰዓት መቶ ስልሳ ኪሎ ሜትር ወደሚጓዝ ዕውር ፍትወት ሊቀየር ይችላል” ብለዋል።

የአሥራ ስድስት ዓመቱ ሚኪ 14 ዓመት ከሆናት ልጃገረድ ጋር “ጓደኛ” በሆነ ጊዜ ይህ ደርሶበታል:- “ሁለት ሰዎች አዘውትረው መተያየት ከጀመሩ እንዲሁ ጓደኞች ብቻ ሆነው ሊቆዩ እንደማይችሉ ቶሎ ተገነዘብኩ። ዝምድናችን ማደጉን ቀጠለ። ወዲያውም አንዳችን ለሌላው ልዩ ስሜት ነበረን፣ አሁንም አለን።” አንዳቸውም ቢሆኑ ለማግባት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ ያልደረሱ በመሆናቸው ይህ ስሜታቸው ትርፉ ብስጭት ብቻ ነው።

በጣም ብዙ መቀራረብ ሌላም አሳዛኝ መዘዞች ሊኖረው ይችላል። አንድ ወጣት አንድ ዓይነት ችግር አጋጥሟት የነበረች ጓደኛውን ለማጽናናት ሞከረ። ብዙም ሳይቆዩ መደባበስ ጀመሩ። ውጤቱስ ምን ሆነ? የተረበሸ ሕሊናና በመካከላቸው መጥፎ ስሜት ተፈጠረ። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ሌሎች ሰዎች ወሲባዊ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል። ሳይኮሎጂ ቱደይ በተባለው ጽሑፍ ላይ የወጣ አንድ ጥናት የሚከተለውን ገልጿል:- “ጥናት ከተደረገባቸው ሰዎች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት (49 በመቶዎቹ) ጓደኝነታቸው ወደ ወሲባዊ ግንኙነት ተለውጦባቸዋል።” እንዲያውም “ወደ ሲሶ የሚጠጉት (31 በመቶዎቹ) ባለፈው ወር ወሲባዊ ግንኙነት እንደፈጸሙ ገልጸዋል።”

‘ይሁን እንጂ ጓደኛዬ አይማርከኝም/አትማርከኝም። ስለዚህ ከእርሱ/ከእርሷ ጋር ፍቅር አይዘኝም’ ትሉ ይሆናል። ምናልባት ልክ ትሆኑ ይሆናል። ግን ወደፊትስ ምን እንደሚሰማችሁ እንዴት ታውቃላችሁ? በተጨማሪም “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ [“ደደብ” አዓት] ነው።” (ምሳሌ 28:​26) ልባችን ትክክለኛውን ውስጣዊ ስሜታችንን እንዳንመለከት የሚያደርግ አታላይና አሳሳች ሊሆን ይችላል። ደግሞስ ጓደኛችሁ ለእናንተ ምን ስሜት እንዳለው በእርግጥ ታውቃላችሁን?

አላን ሎይ ማክጊንስ ዘ ፍሬንድሽፕ ፋክተር በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ “ራሳችሁን ብዙ አትመኑት” በማለት መክረዋል። ምናልባትም አብራችሁ የምትሆኑበትን ጊዜ በቡድን ተግባራት ውስጥ ሌሎች ሊመለከቷችሁ በሚችሉበት ሁኔታ እንዲወሰን ልታደርጉ ትችሉ ይሆናል። ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን ወይም ፍቅርን በሚያነሳሱ ሁኔታዎች ብቻችሁን መሆንን አስወግዱ። ችግር ካጋጠማችሁ ችግራችሁን ተቃራኒ ጾታ ላለው ወጣት ሳይሆን ለወላጆቻችሁ ወይም በዕድሜ ከእናንተ ለሚበልጥ ሰው ተናገሩ።

ማንኛውንም ጥንቃቄ ብታደርጉም ሌላው ወገን ፍቅር ቢይዘው ምን ታደርጋላችሁ? “እውነቱን ተነጋገሩ” እና ጓደኛችሁ አቋማችሁን እንዲያውቅ አድርጉ። (ኤፌሶን 4:​25) ይህ ለችግሩ መፍትሔ ካላስገኘ ከሁሉ የሚሻለው ነገር መራራቃችሁ ሊሆን ይችላል። “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል።” (ምሳሌ 22:​3) ወይም ደግሞ ዘ ፍሬንድሽፕ ፋክተር የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “አስፈላጊ ከሆነ ሸሽታችሁ አምልጡ። አንዳንዴ የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚደረግ ጓደኝነት ከቁጥጥር ውጭ ይሆንና ወዳልተፈለገ ሁኔታ እንደሚያመራ እናውቃለን።” “ወደኋላ ለመመለስ የምንችለው እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ነው።”

[በገጽ 227 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ እንዲጫወቱ ወይም ጥንድ ጥንድ እየሆኑ እንዲሄዱ ግፊት ይደረግባቸዋል

[በገጽ 228 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከተቃራኒ ጾታ ጋር እየተቀጣጠሩ መጫወት ወጣቶች አላስፈላጊ የፍቅር መግለጫዎችን እንዲለዋወጡ ግፊት ያሳድርባቸዋል

[በገጽ 229 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ወጣት ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት የሚያስከትለው የስሜት ውጥረት ሳይደርስበት ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር ሊጫወትና ሊደሰት ይችላል

[በገጽ 230 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወሲባዊ መፈላለግ የሌለባቸው ናቸው የሚባሉት ግንኙነቶች የሚያቆሙት ብዙውን ጊዜ ቅስም በሚሰብር መንገድ ነው